Monday, 30 June 2025

ኦርቶዶክሳዊ ንግድ

ውድ የቤተ ሐዋርያት ቤተሰቦች  

ሥራን ኦርቶዶክሳዊያን እንዴት መረዳት እንዳለባቸው

ንግድ(ማንኛውም ሥራ) መንፈሳዊ ሕይወት ጋር የተሳሰረ ስለመሆኑ

ክርስቲያኖች በየትኛው የንግድ ዘርፍ መሰማራት አለባቸው

ትርፍና የምሸጠው እቃ በተመለከተ መሠረታዊ ሐሳቦችን የዳሰስንበትን ቪድዩ ተጋበዙልን።




Thursday, 5 June 2025

በዓላት ታሪካዊ ትውስታና መታሰቢያነት ባሻገር….


በቀሲስ ያሬድ መለሰ

በትንሣኤ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መግለጫ ወቅት አንድ የታዘብኩትና በዚህ ዓመት ደግሞ ስህተቱ ከእኛም ቤት ገብቶ ‹‹እንኳን ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ መታሰቢያ በዓል አደረሳችሁ›› ዓይነት የእንኳን አደረሳችሁ መልእቶችን ስመለከት ትንሽ ቆም ብዬ ትርጉሙን ማጤን እንደሚያስፈልገን ተሰማኝ። ብዙ ጊዜ፣ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ፣ ነገረ መለኮታዊ አንድምታቸውን ሳናጤን አንዳንድ ሐረጎችንና ልምዶችን እንከተላለን ይህም ምናልባትም ጥልቅ ስህተት ውስጥ የሚከተን ሊሆን ይችላል። በተለይ ደግሞ ነገረ መለኮታዊ ቃላት አጠቃቀም ጥቂት ስህተት ጉልህ ችግሮችን ጎትቶ ሊያመጣ ይችላል። የዚህ ጽሑፍ ዋንኛ ዓላማ በዓላት ታሪካዊ ክስተቶች ለማሰብና ለማስታወስ ብቻ ወይስ ዘለዓለማዊ ጊዜ (በተቀደሰው ጊዜ) የተፈጸሙ በኦርቶዶክሳዊ ሥርዓተ ቅዳሴና ሥርዓተ አምልኮ ውስጥ የሚከበሩ ናቸው የሚለውን ጥያቄ በማንሳት ለመመለስ ያለመ ነው።

በዓል ማለት ‹‹አብዐለ-አከበረ›› ከሚለው የግእዝ ግስ የተገኘ ሲሆን ትርጕሙም ‹‹መታሰቢያ ማድረግ፣ ማክበር›› ማለት ነው። በአጠቃላይ በዓል ማለት ማሰብ፣ መዘከር፣ ማስታወስ የሚል ትርጕም አለው፡፡ ይህ ማለት ግን መታሰቢያ ብቻ ናቸው ማለት አይደለም።  ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችን ስለ ጊዜ፣ ሥርዓተ አምልኮና በዓላት ተሳትፎ ጥልቅና ልዩ የሆነ መረዳት አላት። በነገረ መለኮት ውስጥ በታሪካዊ ጊዜ እና በዘለዓለማዊ (ወይም በተቀደሰ) ጊዜ መካከል ያለው ልዩነት በቤተክርስቲያን በዓላት፣ የአምልኮ ሥርዓቶችንና የእግዚአብሔርን የማዳን አረዳድ ላይ ከሌሎች ጋር ያለን ልዩነት መነሻ ሆኖ እናገኘዋለን። እነዚህ ያለፉ ክንውኖች ታሪካዊ ክስተቶች አልያም መታሰቢያዎች ብቻ አይደሉም፣ ነገር ግን ከዘለዓለማዊ ሆነው የሚቀጥሉና ምእመናንን በዚህ ሱታፌያቸው ወደ ቅድስና የሚያመሩ ናቸው ብለን እናምነለን።

ታሪካዊ ጊዜና ዘለዓለማዊ ጊዜ በቅዱሳት መጻሕፍት

ቅዱሳት መጻሕፍት የጊዜን ሁለት ገጽታዎች ያቀርባሉ። የመጀመሪያው ታሪካዊ ጊዜ ነው። እሱም የፍጥረትና የሰው ጊዜ ነው። በኦሪት ዘፍጥረት 1፡14 ላይ፣ ‹‹እግዚአብሔርም አለ ቀንና ሌሊትን ይለዩ ዘንድ ብርሃናት በሰማይ ጠፈር ይሁኑ ለምልክቶች ለዘመናት ለዕለታት ለዓመታትም ይሁኑ›› በማለት እግዚአብሔር ብርሃናትን (ፀሐይ ጨረቃን ከዋክብትን) በሰማይ ላይ “ለምልክቶች፣ ለዘመናት፣ ለቀናትና ለዓመታት” ሾሞቸዋል። በዚህም ለፍጥረት ሁሉ ዘመን መቁጠርያና መስፈርያ ሆኑ። ይህ የዘመን ቅደም ተከተል መገለጥ የሰው ልጅ ታሪክ መሠረት ነው።

በአንጻሩ፣ ሁለተኛው ዓይነት ጊዜ ዘለዓለማዊ ጊዜ ነው—እግዚአብሔር ካለፈው፣ ከአሁኑና ከወደፊት በላይ መሆኑን አመልካች የሆነ ዘለዓለማዊ(ዮም) የምንለው ጊዜ ነው። በኦርቶዶክስ ትውፊት፣ ይህ ዘለዓለማዊ እውነታ ዘወትር “ዮም” በሚለው የግእዝ ቃል ተጠቅሷል፣ ትርጉሙም “ዛሬ” ማለት ነው። ይህ የተቀደሰ ጊዜ የእግዚአብሔርን የማይለወጥ ተፈጥሮ ያንጸባርቃል፣ ሁሉም መለኮታዊ ድርጊቶች አመላካች ጊዜ ነው። ለአብነትም በመዝ. 2፥7 “አንተ ልጄ ነህ እኔ ዛሬ ወለድኩህ” ይህንን የሚያንጸባርቅ ሆኖ እናገኘዋለን። በዚህ አውድ ውስጥ ያለው "ዛሬ(ዮም)" በአብ እና በወልድ መካከል ያለውን ጊዜ የማይሽረው ግንኙነት ይገልጣል ከሰው የዘመን አቆጣጠር በላይ ያለውን የመለኮታዊ ድርጊት ምሥጢርን ያመለክታል።

የኦርቶዶክስ ነገረ-መለኮት እንደሚያስተምረን ይህ ዘለዓለማዊ "ዛሬ" የክርስቶስን ከድንግል ማርያም ልደትና ከአብ የዘለዓለም መወለዱን ያጠቃልላል። እነዚህ በጊዜ ውስጥ እንደ ተለያዩ ክስተቶች በሰው ልጅ ሲለማመዱ፣ በእግዚአብሔር ዘለዓለማዊ እይታ አንድ ሆነዋል እናም በቤተክርስቲያኗ የአምልኮ ሕይወት ለአማኞች ተደራሽ ይሆናሉ።

በበዓላት ያለ ዘለዓለማዊ ተሳትፎ

በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በዓላት ታሪካዊ ክብረ በዓላት ብቻ አይደሉም፣ ነገር ግን ከክርስቶስ ዘለዓለማዊ ግንኙነት የምንፈጥራቸው እጅግ ምሥጢራዊ ናቸው። ቤተክርስቲያን በልደት በዓል ላይ "ርእይዎ ኖሎት አእኰትዎ መላእክት ለዘተወልደ እማርያም እምቅድስት ድንግል ዮም ሰማያዊ በጎል ሰከበ" ወይም በፋሲካ "ዛሬ ክርስቶስ ተነሥቷል" ስታውጅ ወይም በማኅሌቱ ‹‹ዮም ፍስሐ ኮነ በሰንበተ ክርስቲያን እስመ ተንስአ ክርስቶስ እሙታን ቀደሳ ወአክበራ እምኩሎን መዋዕል አላዓላ አማን ተንሥአ ክርስቶስ ሙታን።›› ስንል ዘይቤያዊ አነጋገር በመጠቀም በዓላቱን እየገለጥን አይደለም ይልቁንም እነዚህ መግለጫዎች የክርስቶስ ሕይወት፣ ሞት እና ትንሣኤ በእግዚአብሔር ውስጥ ለዘለዓለም እንደሚኖሩና በተቀደሰው ጊዜ በአምልኮ ሊደረስባቸው እንደሚችሉ ያለውን እምነት ያሳያሉ።

ይህ ግንዛቤ በሁለቱም በብሉይና በሐዲስ ኪዳን ላይ የተመሠረተ ነው። በብሉይ ኪዳን፣ የፋሲካ በዓልን (የአይሁድን ፋሲካ) እንደ መታሰቢያ ብቻ ሳይሆን በእግዚአብሔር የማዳኑ ተግባር ውስጥ ለዘለዓለም ተሳትፎ እንዲከበር ታዘዋል፡፡ ‹‹ይህም ቀን መታሰቢያ ይሁንላችሁ ለእግዚአብሔርም በዓል ታደርጉታላችሁ ለልጅ ልጃችሁ ሥርዓት ሆኖ ለዘለዓለም ታደርጉታላችሁ።›› (ዘጸ. 12፡14) ይህም ቃል እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር ያለውን ቀጣይነት ያለው ግንኙነት ያመለክታል። በተመሳሳይ፣ የሰንበት ቀን ትቀድሰው ዘንድ አስብ (ዘጸ. 20፡8) በማለት እስራኤላዊያን ወደ እግዚአብሔር ዕረፍት የሚጋብዝ ጊዜን እንደ ቅዱስ ለይተው እንዲያከብሩ ታዘዋል።

በአዲስ ኪዳን ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሉቃስ 4፡21 “ዛሬ ይህ መጽሐፍ በጆሮአችሁ ተፈጸመ” ሲል ይህን ጊዜ የማይሽረው ተሳትፎ አረጋግጧል። ቃላቶቹ እንደሚያሳዩት መዳን ባለፈው ክስተት ብቻ ሳይሆን በአሁኑ ጊዜ በንቃት የሚገለጥ ነው። በዮሐ. 1፡14 ላይ እንደተገለጸው ምሥጢረ ሥጋዌ “ቃልም ሥጋ ሆነ በእኛ አደረ” እንዳለ፣ ጊዜው ራሱ በክርስቶስ ተቀድሶ ከመለኮት ጋር መገናኘቱን ያረጋግጣል።


 

በቅዳሴና በቅዱስ ቁርባን የተቀደሰ ጊዜ

በሥርዓተ ቅዳሴ የምናከናውነው ሥርዓተ አምላኮ በተቀደሰ ጊዜ ውስጥ የምናከናውነው እንደሆነ ቤተ ክርስቲያን ታስተምራለች። ለዚህም ነው ቅዳሴ ገቡ ይባላል እንጂ ቅዳሴው ተጀመረ የማንለው የቅዳሴው ጊዜ እኛ ከምንገለገልበት ጊዜ ፈጽሞ የተለየ ነው።

ይህንን ለመረዳት፣ ሥርዓተ አምልኮ ከዕለት ተዕለት ተግባራችን በተለየ ጊዜ ውስጥ እንደሚሠራ ማወቅ አስፈላጊ ነው። በግሪክ፣ ለጊዜ ሁለት ዋና ቃላት አሉ፡ ክሮኖስ እና ካይሮስ

ክሮኖስ የሚያመለክተው የምንለካውን የዘመን አቆጣጠር ወይም የሰዓት ጊዜ ነው - በሰዓቶች እና በዘመን አቆጣጠር የሚያመለክት ነው።

ካይሮስ፣ በሌላ በኩል፣ የተቀደሰ ጊዜን ማለትም የእግዚአብሔርን ጊዜ ያመለክታል። በደቂቃ ወይም በሰዓታት አይለካም ነገር ግን በትርጉም፣ በመገኘትና በመለኮታዊ ተግባር የተሞላ ነው።

ክርስቶስ “ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት” ብሎ ሲያዝ (ሉቃ. 22፡19) “መታሰቢያ” የሚለው ቃል የግሪክ νάμνησις (አናምኔሲስ) ነው። ከማስታወስ በተለየ መልኩ አናማኔሲስ የአንድን ክስተት ያለፈ ክንውን አመልካች ብቻ ሳይሆን ምሥጢራዊ በሆነ መልኩ በካይሮስ ወደዛች የተቀደሰች ዕለት ቀን መግባትን አመላከች ሆኖ እናገኘዋለን። መሆኑንና ምዕመናንንም ከዚህ ስንካፈል ወደ ተቀደሰው ጊዜ እንደምንገባ በራሱ ክስተት ውስጥ መሳተፍን፣ ያመላክታል።

ስለዚህ፣ በሥርዓተ ቅዳሴ የክርስቶስን የመጨረሻ እራት (ምሴተ ሐሙስ) ፣ ሕማማትና ትንሳኤ እያሰብን ብቻ አይደለም—በእነሱ ውስጥ በምሥጢር እየተሳተፍን ነው። እኛ እንደምናውቀው ጊዜ - ክሮኖስ - አብቅቶ ወደ ካይሮስ፣ የእግዚአብሔር ዘለዓለማዊ “አሁን” እንገባለን።

በቅዱስ ቁርባን ውስጥ የኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች የክርስቶስን መሥዋዕትነት ዝም ብለው አያስታውሱም በእሱ ውስጥ ይሳተፋሉ። የቅዳሴውም እያንዳንዱ እንቅስቃሴ ያንን ጊዜ ታሳቢ ያደረጉ ምሳሌያዊ ትዕይንቶች የተሞሉ ናቸው። ምእመናን ከጊዜ እና ከቦታ በላይ ወደ ድኅነት ምሥጢር እንዲገቡ የሚያስችላቸው አንድ ጊዜ-ለሁሉም መሥዋዕትነት በዚህና አሁን አለ። ይህ ተመሳሳይ መርህ በእያንዳንዱ ክብረ በዓላት ላይ ይዘልቃል፡- ልደት፣ ጥምቀት፣ ቃና ዘገሊላ፣ ፍሲካ እና ሌሎችም ምሳሌያዊ መታሰቢያዎች አይደሉም ነገር ግን ከክርስቶስ ሥራ ጋር የተገናኙ ሕያው ስብሰባዎች፣ በቤተክርስቲያኗ የአምልኮ ሕይወት ውስጥ “ዛሬ” ተገለጡ ናቸው።

በልደቱ በዓል ወቅት፣ ቤተ ክርስቲያን በግእዝ “ዮም ክርስቶስ ተወልደ” (ዛሬ ክርስቶስ ተወለደ) በማለት የልደቱን ምሥጢራዊ እውነታ ያረጋግጣል። በተቀደሰ ጊዜ፣ አማኞች ያለፈውን ተመልካቾች ሳይሆኑ በእግዚአብሔር ዘላለማዊ የማዳን ተግባራት ውስጥ ተካፋዮች ናቸው።

በዓላትና ሰማያዊ ቅዳሴ

የኦርቶዶክስ በዓላትም የገነትን ዘለዓለማዊ አምልኮ ያንጸባርቃሉ። ቅዱስ ዮሐንስ በራእይ 4፡8 ላይ የሰማይ ሰራዊት “ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ የነበረውና ያለ የሚመጣውም ሁሉን የሚገዛ ጌታ አምላክ ነው” እያሉ ይጮኻሉ እንዳለ ይህ ዘመን የማይሽረው አምልኮ በቤተክርስቲያን ሥርዓተ አምልኮ ውስጥ በምድር ላይ ተስተጋብቷል። በዕብራውያን 13፥8 መሠረት “ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትና ዛሬ እስከ ለዘለዓለምም ያው ነው"። ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብም የክርስቶስ የማዳን ሥራ ለዘለዓለም ንቁና የማይለወጥ መሆኑን ያመላክታል።

እንደ ክርስቶስ አካል፣ ቤተ ክርስቲያን በጊዜና በዘለዓለማዊነት መጋጠሚያ ላይ ትቆማለች። በቅዳሴ፣ ምእመናን ወደ ሰማያዊው እውነታ ይስባሉ፣ እሱም የክርስቶስ ሥጋዌ፣ ስቅለት እና ትንሣኤ ያለማቋረጥ ይከበራል። ቤተክርስቲያን መለኮታዊ ጸጋ የሰውን ሕይወት የሚገናኝበት ቦታ ትሆናለች።

በዓላትን እንደ ምሳሌያዊ መታሰቢያ ወይም ታሪካዊ አከባበር ከሚያዩት ከብዙ ሰዎች በተቃራኒ፣ የኦርቶዶክስ ክርስትና እንደ እውነተኛ፣ የቅዱስ ቁርባን ስብሰባዎች አድርጎ ይመለከታቸዋል። ይህ ልዩነት የመነጨው ከኦርቶዶክስ ስለምሥጢረ ሥጋዌ እና የቅዱስ ቁርባን ሕይወት ባላት አረዳድ(ግንዛቤ)ነው። ክርስቶስ ወደ ጊዜ ስለገባ፣ ጊዜ ሁሉ በክርስቶስ ተቀድሷል። በዓላት አንድ ጊዜ የሆነውን ለማስታወስ ሳይሆን በእግዚአብሔር ዘለዓለማዊ ወደሆነው ነገር ውስጥ መግባት ናቸው።

እያንዳንዱ በዓል ወደ የዘለዓለማዊው መንግሥት መስኮት ናቸው። እነሱ ያለፈው የሚፈጸምበት፣ መጪው ጊዜ የሚጠበቅበት፣ እና አሁን ያለው በመለኮታዊ ጸጋ የተሞላበት ጊዜዎች ናቸው። የጊዜ ቅድስና በትልልቅ በዓላት ብቻ የተገደበ አይደለም ነገር ግን በሥርዓተ አምልኮው የቀን መቁጠሪያ ውስጥ ሁሉ የተሸመነ ዜማ ሲሆን የምእመናንን ሕይወት ከክርስቶስ ሕይወት ጋር የሚያስማማ ነው።

ማጠቃለያ

ኦርቶዶክሳዊያን ስለ በዓላት እና ቅዱስ ጊዜ መረዳቱ ጥልቅ ምሥጢራዊ እና መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነትን በጥልቀት እንድናይ ያስችለናል። በእግዚአብሔር ዘለዓለማዊ እውነታና በቤተክርስቲያን የቅዱስ ቁርባን ሕይወት ውስጥ የተመሠረተ የኦርቶዶክስ አምልኮ ጊዜን ወደ መለኮታዊ ኅብረት መንገድ ይለውጠዋል። በቅዳሴ፣ ምእመናን መታሰቢያን ብቻ ሳይሆን በክርስቶስ የማዳን ሥራዎች ውስጥ ይሳተፋሉ። እያንዳንዱ በዓል አማኞች እግዚአብሔርን የሚገናኙበት የተቀደሰ በር ይሆናል፣ እንደ ሩቅ ታሪካዊ ሰው ሳይሆን፣ የምናመልከውና የምንቀድሰው ጊዜን ጨምሮ ፍጥረትን ሁሉ የሚቀድስ ሁል ጊዜ ያለ ጌታን ነውና።

 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Wednesday, 30 April 2025

የምዕራቡ ዓለም ክርስትና ፈተና፡ የጀርመን "ጳጳሳት"ና የተመሳሳይ ጾታ "ጋብቻ" ቡራኬ

 ቤተ ሐዋርያት

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ፣ በምዕራቡ የክርስቲያን ዓለም ብዙ ለውጦችን አይተናል። ከእነዚህ ለውጦች መካከል አንዳንዶቹ ወደ እውነተኛው የወንጌል እውነት ከመመለስ ይልቅ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ከተገለጠው የማይለወጥ እውነት የራቁ ይመስላሉ።

በተለይ አሳዛኝ ክስተት የጀርመን የካቶሊክ "ጳጳሳት" የተመሳሳይ ጾታ "ጋብቻን" ቡራኬ መስጠትና "ጋብቻው"ን እንደቅዱስ ጋብቻ ለመቀበል ለማጽደቅ የወሰኑት ውሳኔ ነው። እንደዘገበው፣ ከ2026 ጀምሮ፣ እነዚህ ቡራኬያት በይፋ ተግባራዊ ይሆናሉ። ፖፕ ፍራንሲስ በሕይወት ዘመን ይህንን በመጠኑ ለመቀበል ተገ
ዋል። በእርሳቸው ዘመን ካቶሊካዊያን ካህናት ተመሳሳይ ጾታ ላሉ ሰዎች ቡራኬ እንዲሰጡ ጋብቻውን ግን እንዳይባርኩ ጋብቻቸውም በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን(ቅዳሴ) እንዳይፈጽሙ ለመከልከል ችለው ነበር። የጀርመን ጳጳሳት ግን ይህ ሁሉ እንዲሆን በአብላጫ ድምጽ ወስነው ነበር።

ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ጋብቻ በእግዚአብሔር በራሱ የተመሠረተ፣ በአንድ ወንድና በአንዲት ሴት መካከል ያለ አንድነት፣ የክርስቶስንና የቤተክርስቲያኑን አንድነት የሚያንጸባርቅ ቅዱስ ምሥጢር  እንደሆነ ታስተምራለች (ኤፌ. 5፥32)። ጋብቻ እንደፈለግን የሚቀያየር ወይም የሚለወጥ  ባሕል ወይም የሰው ፈጠራ አይደለም።ቅዱስ ጋብቻ የተለየ ዓላማ ያለው መለኮታዊ ተቋም ነው በዚህም የትዳር አጋሮች መዳንና ልጆችን በእምነት ማሳደግ ሁሉ የሚያካት ነው። 

ከቅዱሳት መጻሕፍትና ከቅዱሳን ትውፊት ትምህርት ጋር የሚቃረኑ ግንኙነቶች ሁሉ የበረከት የፍቅር ተግባር ሊሆኑ አይችሉም  ይህ አሳዛኝ ማታለል ነው። ክብር ይግባውና ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም እንዲህ ብሏል፡-

"እርሱ ግን መልሶ እንዲህ አለ፦ ፈጣሪ በመጀመሪያ ወንድና ሴት አደረጋቸው፥ አለም፦ ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፥ ከሚስቱም ጋር ይተባበራል፥ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ የሚለውን ቃል አላነበባችሁምን?" ( ማቴ. 19:4-5 )

ከተቀደሰው የጋብቻ ማሰሪያ ውጭ ያለውን ማንኛውንም ዓይነት  ግንኙነትን መባረክ ኃጢአትን መባረክ ነው ይህም ወደሞት ያመራል። (ያዕ. 1፡15)። ምንም ያህል "ነገረ መለኮታዊ" ፈጠራ ወይም የ"ሲኖዶስ" ድምጽ የእግዚአብሔርን ቃል መሻር አይችልምና።

የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሰዎች ሁሉ ተጋድሎአቸው ወይም ፈተናቸው ምንም ይሁን ምን ከእግዚአብሔር ጋር በንስሐ ትጠራለች። ከተመሳሳይ ጾታ ፍላጎት ጋር የሚታገሉትን አንጠላቸውም። ይልቁንም ክርስቶስ ለኃጢአተኞች ሁሉ ባቀረበው የቅድስና ሕይወት እንድንጠራቸው እንወዳቸዋለን፤ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ እንዳለ “ኃጢአተኞችን ሊያድን ክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዓለም መጣ የሚለው ቃል የታመነና ሁሉ እንዲቀበሉት የተገባ ነው፤ ከኃጢአተኞችም ዋና እኔ ነኝ፤” (1ኛ ጢሞ 1፡15)።

በተለይ በጀርመን ላሉ ይህን አደገኛ መንገድ ለተቀበሉ ለካቶሊክ ወንድሞቻችን አጥብቀን መጸለይ አለብን። ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ወደ ተሰጥተው እውነተኛ ሃይማኖት ለመመለስ ድፍረትን እንዲያገኙ ስለ መሪዎቻቸው መጸለይም ይገባናል (ይሁ. 1፥3)።

ስለ ፍቅር፣ ትዳር እና እውነት ግራ መጋባት በበዛበት ዓለም እንደ ኦርቶዶክሳዊት እምነት ተከታዮች በትኅትናና በፍቅር ጸንተን እግዚአብሔር ለሰው ልጅ የፈጠረውን ውበት እየመሰከርን ለእግዚአብሔር ምስክሮች እንድንሆን አምላከ ቅዱሳን ይፍቀድልን።

እግዚአብሔር ሁላችንንም በምሕረቱ ይጎብኘን።

Friday, 6 December 2024

ሃይማኖት በድኅነት ውስጥ ያለው ሚና፡ በኦርቶዶክስ ክርስትናና በፕሮቴስታንት መካከል ያለው ንጽጽር

ቀሲስ ያሬድ መለሰ

በመገናኛ አደባባይ በተለይም በሥራ መግቢያና መውጫ ሰዓቶች ልዩ ልዩ ስብከቶችን መስማት የተለመደ ነው። በዚህ አካባቢ ያሉ ‹‹ሰባኪዎች›› በአብዛኛው የሌሎችን ሰዎች ቀልብ ለመሳል ‹‹ሃይማኖት አያስፈልግም ‹‹ኢየሱስን›› ብቻ እመኑ›› የሚል ትምህርትን ያስተምራሉ። ለአብነት በመገናኛ አካባቢ ያለውን ሁነት አየን እንጂ ይህ ትምህርት በፕሮቴስታንትና ፕሮቴስታንት መሰል የተሐድሶ ቡድኖች ዘንድ በስፋት የሚነገር አመለካከት ነው። በዛሬው ጽሑፌ ሃይማኖትን ለመዳን አስፈላጊነትን፣ ኦርቶዶክሳዊ ቤተ ክርስቲያናችን ሃይማኖትን እንዴት እንደምትረዳ እንዲሁም በፕሮቴስታቱ ዓለም ስላለው መረዳት ለማየት እንሞክራለን።

የፕሮቴስታንት አመለካከት፡ እምነት ብቻውን ያለ ሃይማኖት

በዚህ ዘመን የ‹‹ክርስቲያኑ›› ዓለም፣ በተለይም በአንዳንድ የፕሮቴስታንት ዓለም መካከል ያለው የተለመደ እምነት ሃይማኖት ለመዳን አስፈላጊ አይደለም፣ በኢየሱስ ማመን ብቻ በቂ ነውየሚል ነው።  በፕሮቴስታንት ነገረ መለኮት ውስጥ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን እንደ ብቸኛ የመዳን መስፈርት እንደሆነ ያስባሉ። ይህ አመለካከት የተመሠረተው እንደ ኤፌሶን 2፡8-9 ባሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባቦች ትርጓሜዎች ላይ ነው።"ጸጋው በእምነት አድኖአችኋልና፤ ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንተ አይደለም፤ ማንም እንዳይመካ ከሥራ አይደለም።" ለብዙ ፕሮቴስታንቶች ሃይማኖት ብዙውን ጊዜ የሚያመለክተው ውጫዊ የአምልኮ ሥርዓቶችን፣ ወይም ሃይማኖታዊ ልምዶችን አንዳንድ ጊዜ በክርስቶስ ላይ ያለውን እውነተኛ እምነት የሚያዘናጉ ወይም የሚተኩ ናቸው ብለው ያምናሉ። ለዚህም ነው ‹‹ሃይማኖት አያስፈልግም›› ወደሚል የተሳሳተ መደምደሚያ የሚያመሩት።

ፕሮቴስታንቶች ሃይማኖት ለመዳን አስፈላጊ አይደለም ብለው ለምን ያምናሉ? ብንል አራት መሠረታዊ ምክንያቶችን እናገኛለን

  • 1.   በሥራ ላይ የተመሠረተ ድኅነትን አለመቀበል፡- ብዙ ፕሮቴስታንቶች የአምልኮ ሥርዓቶች ወይም ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች ለድኅንት አስተዋጽኦ ማድረግ እንደማይችሉ ያምናሉ፣ ይህም ሙሉ በሙሉ በእምነት የተገኘ የእግዚአብሔር የጸጋ ስጦታ አድርገው ይመለከቱታል።
  • 2.  ከክርስቶስ ጋር ግላዊ ግንኙነት፡- ዋናው የፕሮቴስታንት አመለካከት መዳን የሚገኘው ከ‹‹ኢየሱስ›› ባለ ግላዊ ግንኙነት ነው ብለው በማመናቸው፡፡
  • 3.  ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያንንና ሥርዓተ አምልኮን አላስፈላጊ ናቸው ብለው ስለሚያምኑ
  • 4.  “ሃይማኖት” እንደ ሰው ሠራሽ ነው ብለው ስለሚያምኑ

“ሃይማኖትን” ለሚተቹ ፕሮቴስታንቶች ቃሉ ብዙውን ጊዜ የሚወክለው፡- ለድኅንነት አስፈላጊ አይደሉም ብለው የሚያምኑትን የአምልኮ ሥርዓቶች፣ ቁርባን ወይም የቤተ ክርስቲያን ትውፊትን ያካተተ ሰው ሰራሽ ብለው ነው። ይህ አመለካከት ለእነርሱ ድኅነት መዳን ከኢየሱስ ጋር ያለ ግላዊ ከቤተ ክርስቲያን ውጭ ባለ ግንኙነት ላይ የተመሠረተ መሆኑን በማመናቸው የሚመነጭ ነው፡፡ አንዳንዶቹ ሥልጣነ ክህነትንና የመንፈሳዊ ሥልጣን ተዋረድን ስለማይቀበሉ ከዚህ ጋር በተያያዘ ራሳቸው ለሃይማኖት በሰጡት ትርጉም መረዳት ላይ ተመሠረተ ሆኖ እናገኘዋለን።

ነገር ግን፣ ብዙ የፕሮቴስታንትዎች ለአምልኮ ከመሰብሰብ፣ ከመስበክና እንደ ጥምቀትና ቁርባን ያሉ ምስጢራትን ከማድረግ አንጻር አሁንም “ሃይማኖት” ብለው የሚተቹትን ነገር እንደሚለማመዱ ማስተዋል አስፈላጊ ነው።

ለኦርቶዶክሳዊያን የሃይማኖት ግንዛቤ

የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ድኅነት በእግዚአብሔር ጸጋና በሰዎች ምላሽ (ተግባራዊ ምላሽ) የሚገኝ እንደሆነ ታስተምራለች። ስለዚህም በቀላሉ በጸጋው ብቻ ወይም በሰዎች ሥራ ብቻ ሳይሆን የእግዚአብሔር ፀጋና የሰው ልጅ ለመዳን የሚያድገው ጥረት የሚፈጸም ነው፡፡ በክርስቶስ ማመን አስፈላጊ ነው፣ ነገር ግን በፍቅር፣ በመታዘዝ፣ በቅዱስ ቁርባን ውስጥ በመሳተፍና የክርስቶስ አካል በሆነው በቤተክርስቲያን አባልነት(አካልነት) መኖር አለብን። ለኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮች ከክርስቶስ ጋር አንድ ሆነው በእርሱ አምሳል የሚያድጉበት እግዚአብሔር የሰጠን ሥርዓት እንጂ ሰው ሰራሽ ሥርዓት አይደለም።

ይህ ልዩነት በኦርቶዶክስ እና በፕሮቴስታንት እምነት፣ ሥራ እና በቤተክርስቲያን መካከል ያለውን ግንኙነት እንዴት እንደሚመለከቱ ከላይ ያለውን መሠረታዊ ልዩነት አጉልቶ ያሳያል።

ከኦርቶዶክስ እይታ አንጻር “ሃይማኖት ለመዳን አስፈላጊ አይደለም በኢየሱስ ማመን ብቻ በቂ ነው” የሚለው ሃሳብ ያልተሟላና ቤተክርስትያን በምታስተምረው የክርስቶስን ትምህርትና መሠረታዊ የነገረ ድኅነትን ትምህርትን ያልተረዳ ነው። ሃይማኖትን እንዴት እንረዳለን ብንል

1. በክርስቶስ ማመን አስፈላጊ ነው ግን ማመን ብቻ በቂ አይደለም

ኦርቶዶክሳዊያን በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን ለድኅነት ፍጹም አስፈላጊ እንደሆነ እናምናለን። ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚሉት፣ “ያለ እምነት እርሱን ደስ ማሰኘት አይቻልም” (ዕብ 11፡6) ። ሆኖም፣ እውነተኛ እምነት በፍፁም ምሁራዊ ስምምነት ወይም የቃል እውቀት ብቻ ሊሆን አይገባም። የአንድን ሰው የሕይወት ገጽታ የሚቀይር ሕያው፣ ንቁ በእግዚአብሔር ላይ ያለ እውነታኛ መታመን ነው። ይህ እምነት በፍቅር ሥራዎችና ለክርስቶስ ትእዛዛት በመታዘዝ መገለጥ አለበት (ያዕቆብ 2፡17-26) ።

2. ለመዳን እምነት ከሥራ ጋር አስፈላጊ ነው

ኦርቶዶክሳዊነት ድኅነት በእግዚአብሔር ጸጋ እና በሰዎች ምላሽ መካከል ባለ አንድነት የሚገኝ ነው። ቅዱስ ጳውሎስ “…. በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ የራሳችሁን መዳን ፈጽሙ። ስለበጎ ፈቃዱ መፈለግንም ማድረግንም በእናንተ የሚሠራ እግዚአብሔር ነውና” (ፊልጵ. 2፡12-13) ። እንዳለ እምነት መሠረት ነው፣ነገር ግን በቤተክርስቲያኗ ሕይወት በመሳተፍ፣በመልካም ሥራ፣በጸሎትና በምሥጢራት መገለጽ አለበት ይህንን ነው ተግባራዊ ምላሽ የምንለው እነዚህ “ተጨማሪዎች” ሳይሆኑ እምነት የሚጎለብትበትና የሚያድግበት መንገዶች ናቸው።

3. ቤተክርስቲያንና ቁርባን የእግዚአብሔር የማዳን እቅድ አካል ናቸው።

ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን ተቋም ሳትሆን የክርስቶስ አካል ናት። የምትመለከተው (ኤፌሶን 1፡22-23) ። ቤተክርስቲያን አማኞች ከክርስቶስ ጋር በምስጢረ ቁርባን በተለይም በጥምቀት፣ በቅዱስ ቁርባን በሜሮንና በንስሐ(ኑዛዜ) አማካኝነት አንድ የሚሆኑበት ነው። እነዚህ “የሃይማኖታዊ ተጨማሪዎች” ሳይሆኑ ለሰው ልጅ መዳን እና መዳን በክርስቶስ በራሱ የተሰጡ መለኮታዊ ስጦታዎች ናቸው።

ለምሳሌ፡-

·         ጥምቀት ወደ ክርስቶስ ሕይወት መግባት ነው (ዮሐ. 3፡5) ።

·         ቁርባን በክርስቶስ ሥጋ እና ደም ውስጥ መሳተፍ ነው፣ ለዘለአለም ህይወት አስፈላጊ ነው (ዮሐ. 6፡53-56) ።

·         ንስሐ(ኑዛዜ) በኃጢአት ስንወድቅ ከእግዚአብሔር ጋር የምንታረቅበት መንገድ ነው (ዮሐ. 20፡22-23) ።

"ሃይማኖት አስፈላጊ አይደለም" ማለት የእነዚህን እግዚአብሔር የወሰናቸው መንገዶች በድኅነት ውስጥ ያላቸውን ሚና ችላ ማለት ነው።

4. ድኅነት በግል አይፈጸምም

ኦርቶዶክሳዊነት መዳን ከኢየሱስ ጋር ግላዊ የሆነ ግላዊ ግንኙነት ብቻ ነው የሚለውን ሃሳብ ትክክል አይደለም። ክርስቶስ የመጣው ቤተክርስቲያንን ለመመሥረት ነው (ማቴ. 16፡18) ቤተ ክርስቲያን ደግሞ የክርስቲያኖች ኅብረት(ማኅበረሰብ) ናት። አማኞች በፍቅር፣ በጸሎትና በአገልግሎት አብረው በሚያድጉበት በዚህ ማኅበረሰብ ውስጥ መዳን ይሠራል። ይህ የክርስትና የጋራ ገጽታ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ማዕከል ነው።

5. ሃይማኖት ስንል ስለባዶ የአምልኮ ሥርዓቶች የምንል አይደለም

እውነተኛው ሃይማኖት በቤተ ክርስቲያን ሕይወት ውስጥ የተገለጸው የእውነተኛው አምላክ አምልኮ ነው። ቅዱስ ያዕቆብ “ንጹሕ ነውርም የሌለበት አምልኮ በእግዚአብሔር አብ ዘንድ ይህ ነው፤ ወላጆች የሌላቸውን ልጆች ባልቴቶችንም በመከራቸው መጠየቅ በዓለምም ከሚገኝ እድፍ ሰውነቱን መጠበቅ ነው” (ያዕ. 1፡27) በማለት ጽፏል። ለኦርቶሶክሳዊያን ሃይማኖት ስንል ስለባዶ የአምልኮ ሥርዓቶች የምንል አይደለም ነገር ግን እምነትንና ሥራን የሚያካትት ሕያው፣ በቅዱስ ቁርባን ሰዎችን የሚለውጥ ግንኙነት ከእግዚአብሔር ጋር የምንፈጥርበት የመዳን መንገድ ነው።

6. እምነት ያለሥራ ያልተሟላ ነው።

ኦርቶዶክሳዊት እምነት ከቅዱስ ያዕቆብ ጋር ይስማማል፣ “ከሥራ የተለየ እምነት የሞተ ነው” (ያዕ. 2፡17) ። በክርስቶስ ላይ ያለው እውነተኛ እምነት በተፈጥሮ በቤተክርስቲያን ሕይወት ውስጥ መሳተፍን፣ የበጎ አድራጎት ስራዎችንና የተቀደሰ ሕይወትን ለመኖር ወደ መጣር ይመራል። የክርስቲያን ሕይወት ቀጣይነት ያለው ንስሐ፣ ማደግና በመለኮታዊ ሕይወት ውስጥ መሳተፍ (እግዚአብሔር ወደ መምሰል የሚያድግ) ነው፣ ይህም ከቤተ ክርስቲያን ተነጥሎ ሊገኝ አይችልም።

ማጠቃለያ

ለኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች መዳን የአንድ ጊዜ ክስተት ወይም የግል እምነት ጉዳይ አይደለም። ይልቁንም የእድሜ ልክ ጉዞ የእምነት፣ የንስሐና በቤተክርስቲያኗ ቅዱስ ቁርባንና የጋራ ሕይወት ውስጥ ተሳትፎ የሚገኝ ነው። ቤተክርስቲያን፣ ምስጢራቶቿ እና ትምህርቶቿ አማራጭ ሳይሆኑ ከድኅነት ሂደት ጋር የተያያዙ ናቸው፣ ምክንያቱም ምሥጢራቱ እኛን ከእርሱ ጋር ወደ አንድነት ለማምጣት በራሱ በክርስቶስ የተመሠረቱ ነው። ለዚህም ነው ሃይማኖት ለመዳን አስፈላጊ ነው የምንለው።

 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር