እጅግ አስተማሪ ሕይወት ያላቸው እውነተኛ እረኛ ናቸው፡፡ በትምህርታቸው የማይማረክ ጽሑፋቸውንም አንብቦ የማይመሰጥ የለም እኝህ አባት ስማቸው ከግብጽ አልፎ በዓለም የገነነ ነው ፡፡ ሕይወታቸው እጅግ ስለሚማርክና ከቤተ ክርስቲያን አልፈው ለግብጽ ባበረከቱት አስተዋጽዖ ባረፉበት ወቅት መላው ግብጽ አዝኖ ነበር፡፡ እኝህ አባት የግብጽ ፓትሪያሪክ አባታችን ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ ሳልሳዊ ናቸው፡፡ እኛም ለአገልጋዮች መልካም የሆነ ገድላቸውን ቢሰማ መልካም ነውና ታሪካቸውን ይዘን ቀርበናል መልካም ንባብ
በሐምሌ 18 ቀን 1954 ዓም እኤአ በዋዲ ኤል ናትሩን ወደሚገኘው የሶርያውያን ገዳም ገብተው ምንኩስናን ተቀበሉ፡፡ የገዳሙ አበ ምኔት እንጦንስ የሚል ስም ሰጧቸው፡፡ በዚያ ገዳም ሺኖዳ አያሌ ቀደምት የቤተ ክርስቲያን መጻሕፍትን ማንበባቸው ይነገራል፡፡ በመነኮሱ በዓመታቸው ክህነት ተቀብለው ቄስ ሆኑ፡፡ ሺኖዳ ከምንም በላይ ለምንኩስና እና ለምናኔ ሕይወት ልዩ ትኩረት አላቸው፡፡ በእርሳቸው ዘመን በግብጽ የነበሩት እና ለግብጻውያን ገዳማዊ ሕይወት እንደገና ማንሠራራት ታላቅ አስተዋጽዖ ያደረጉት የኢትዮጵያዊው አብዱል መሲሕ (ገብረ ክርስቶስ) ደቀ መዝሙር ነበሩ፡፡ የገብረ ክርስቶስን ፍጹማዊ መንገድም ለመከተል ይጥሩ ነበር፡፡ በዚህም የተነሣ ለብዙ ዓመታት የኖሩትም በተባሕትዎ ነበር፡፡ መጀመርያ ከገዳሙ ሦስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ አንድ ዋሻ ውስጥ ተቀመጡ፤ በመቀጠልም ከገዳሙ ዐሥር ኪሎ ሜትር ወደ ሚርቅ እና በባሕር አል ፋሪግ ወደሚገኝ ዋሻ ገብተው ተጋድሎዋቸውን ቀጠሉ፡፡
ባሕታዊው የተሰኘውንና በኋላ እኤአ በ1954 የታተመውን ቅኔያቸውን የጻፉት በዚህ ጊዜ ነበር፡፡ በ1959 እኤአ ቄርሎስ ስድስተኛ ልዩ ጸሐፊያቸው አድርገው ሾሟቸው፡፡ ሺኖዳ ግን ደስተኛ አልነበሩም፡፡ ከገዳማቸው መውጣት እና በኣታቸውን መልቀቅ አያስደስታቸውም ነበር፡፡ ብዙ ጊዜያቸውንም የሚያሳልፉት በዋሻቸው ውስጥ በጸሎት እና ቅዱሳት መጻሕፍትን በማንበብ ነበር፡፡ ለብዙ ጊዜያትም ወደ ኤጲስ ቆጶስነት እንዳይጠሩ ሲከላከሉ ኖረዋል፡፡ በ1962 እኤአ ሺኖዳ በነበሩበት ገዳም ውስጥ አንድ አስተዳደራዊ ችግር ተፈጠረ፡፡ ጉዳዩም ወደ ፓትርያርክ ቄርሎስ ስድስተኛ ዘንድ ቀረበ፡፡ በዚያ ጊዜ ሺኖዳ በገዳሙ አስተዳደር ውስጥ ነበሩበት፡፡ ገዳማውያኑ እንደ ጥንቱ አበው ሆነው እንዲኖሩ፣ ገዳማት የችግር ቦታዎች ሳይሆኑ የጸሎት ቦታዎች እንዲሆኑ፤ የግብጽ ገዳማት አዲሱን ትውልድ ለመቀበል በሚችሉበት መንገድ እንዲደራጁ፤ ገዳማውያኑ ሥራ፣ ጸሎት እና ትምህርትን አጣምረው እንዲይዙ ይታገሉ ነበር፡፡ ይህ የሺኖዳ ሃሳብ
ያልተስማማቸው አንዳንድ ገዳማውያንም ሺኖዳን ከስሰው ወደ ቄርሎስ ዘንድ አቀረቧቸው፡፡ አቡነ ቄርሎስ ስድስተኛ ሺኖዳን አስጠሯቸው፡፡ ሺኖዳ በቄርሎስ እግር ሥር ተደፍተው «አጥፍቻለሁ፣ ድሮም ኃላፊነቱን የተቀበልኩት ያለ ዐቅሜ ነው፡፡ እባክዎ ከኃላፊነት ያንሱኝና በዋሻዬ ብቻ ተወስኜ ልኑር፡፡ እኔ ደካማ ሰው ነኝ» ሲሉ ለመኗቸው፡፡ ቄርሎስም «ዛሬ እንደርና ነገ ውሳኔዬን አሳውቃለሁ» አሉ፡፡
በማግሥቱ መስከረም 30 ቀን 1962 ዓም እኤአ ፓትርያርክ ቄርሎስ እና ሌሎች ጳጳሳት የሺኖዳን ጉዳይ ለማየት በመንበረ ፓትርያርኩ ተሰባሰቡ፡፡ ሺኖዳ ውሳኔውን በጉጉት ነበር የጠበቁት፡፡ ኃላፊነት ከሚባለው ነገር ተገላግለው የምናኔ ሕይወታቸውን ብቻ ለመያዝ ፈልገዋል፡፡ ሺኖዳ ተጠሩ፡፡ ጳጳሳቱ ቆሙ፡፡ ሁሉም ቄርሎስን ያይ ነበር፡፡ ሺኖዳ እንዲንበረከኩ ተነገራቸው፡፡ ተንበረከኩ፡፡ ቄርሎስ እጃቸውን በሺኖዳ ላይ ጫኑ፡፡ ሌሎች ጳጳሳትም ወደ እርሳቸው መጡ፡፡ ሳይታሰብ አቡነ ሺኖዳ ተብለው የግብጽ የመንፈሳውያን ኮሌጆች እና የትምህርት ተቋማት ጳጳስ ሆነው ተሾሙ፡፡ ሺኖዳ ደነገጡ፡፡ አለቀሱም፡፡ በግብጽ ቤተ ክርስቲያን ላይ ጥናት በማድረግ የታወቀው የካይሮ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰሩ ጀርመናዊው ኦቶአ ሜናድረስ የአቡነ ሺኖዳን መሾም ሲሰማ እንኳን ደስ ያለዎት የሚል ደብዳቤ ላከላቸው፡፡ ሺኖዳ ግን የመለሱለት የሚከተለውን ነበር « የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ እና ሰላም ካንተ ጋር ይሁን፡፡ እንኳን ደስ ያለዎት ብለህ በቅንነት ስለላክህልኝ መልእክት አመሰግንሃለሁ፡፡ ያንተን ወዳጅነት እና ፍቅር መቼም አልዘነጋውም፡፡ እውነቱን ለመናገር ግን ለእኔ መላክ ያለበት የኀዘን ደብዳቤ እንጂ የደስታ ደብዳቤ አይደለም፡፡ አንድ መነኩሴ ጸጥታ የተሞላበትን የጸሎት በረሃ ለቅቆ ጫጫታ እና ሁካታ በተሞላበት ከተማ እንዲኖር ሲደረግ እንዴት እንኳድ ደስ ያለህ ይባላል? ማርያምን ከክርስቶስ እግር ሥር ተነሥታ ማርታን ልታግዝ ወደ ጓዳ ስትገባ ማነው እንኳን ደስ ያለሽ የሚላት? ለእኔ ይህ ደስታ ሳይሆን ሀፍረት ነው፡፡ እኔ ኤጲስ ቆጶስ ሆኜ የተሾምኩበትን ቀን በደስታ ሳይሆን በኀዘን እና በለቅሶ ነው የማስታውሰው፡፡ ብሕትውና እና የተጋድሎ ጸሎት ከምንም በላይ የሚበልጥ ነገር ነው፡፡ ብሕትውና እና ምናኔ ከኤጲስ ቆጶስነት ቀርቶ ከፓትርያርክነት ጋር እንኳን የሚወዳደር አይደለም፡፡ «ወዳጄ ሆይ እውነተኛው ቅድስና ሲመት ሳይሆን ልብን ቤተ መቅደስ አድርጎ ለክርስቶስ መቀደስ ነው፡፡ ክርስቶስ በመጨረሻው ቀን የልባችንን ንጽሕና እንጂ የክህነታችንን መዓርግ አይጠይቀንም፡፡ ይህንን ደብዳቤ የምጽፍልህ በምወድዳት ዋሻዬ፣ በባሕር አል ፋሬግ፣ በዋዲ ኤል ናትሩን ውስጥ ሆኜ ነው፡፡ እዚህም እስከ ጥምቀት ድረስ ለመቆየት አስባለሁ፡፡ ከዚያም ወደ ካይሮ እመለሳለሁ፡፡» አቡነ ሺኖዳ እያለቀሱ ያቺን የዋዲ ኤል ናትሩን ዋሻ ትተው ካይሮ ቢመጡም በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ወደ ዋሻቸው መሄድ ያዘወትሩ እንደ ነበር ታሪካቸውን የጻፈላቸው የቅርብ ወዳጃቸው እና
በእምነቱ ፕሮቴስታንት የነበረው ኦቶአ ሜናድረስ ይናገራል፡፡ እስከ 1969 እኤአ ድረስ የቤተ ክርስቲያኒቱን የትምህርት ተቋማት በዘመናዊ መልኩ አደራጇቸው፡፡
በዚህ የተነሣም በሙሉ ጊዜያቸው የሚማሩ ተማሪዎች ቁጥር ከአንድ መቶ ወደ 207 አደገ፡፡ ሺኖዳም በየሳምንቱ ዓርብ ዓርብ ሕዝቡን የሚያስተምሩበት እና የሕዝቡን ጥያቄዎች የሚመልሱበት የትምህርት መርሐ ግብር ከፈቱ፡፡ እስከ አሥር ሺ የሚጠጋ ሕዝብም መርሐ ግብሩን ይከታተለው ነበር፡፡ ለሰንበት ትምህርት ቤቶች የሚሆኑ መጻሕፍትን፣ መዝሙሮችን እና ትምህርቶችን ያዘጋጁ
ነበር፡፡ የሰንበት ትምህርት ቤት መምህራንንም ያሠለጥኑ ነበር፡፡ በዚህ የሥራ ብዛት ውስጥ እያሉ እንኳን የሳምንቱን ግማሽ በካይሮ ቀሪውን ደግሞ በገዳማቸው ዋሻ ውስጥ ያሳልፉ ነበር፡፡ በዚሁ ዓመት ሺኖዳ የመካከለኛው ምሥራቅ የነገረ መለኮት ተቋማት ማኅበር ፕሬዚዳንት ሆነው ተመረጡ፡፡ቤተ ክርስቲያኒቱን ከሌሎቹ ጋር የማቀራረቡን ሥራ የጀመሩት ገና በጳጳስነታቸው ዘመን ነው፡፡ በእርሳቸው መሪነት ቤተ ክርስቲያኒቱ በአያሌ የነገረ መለኮት ውይይቶች ላይ ተሳትፋለች፡፡ ፓርትያርክ ቄርሎስ በመጋቢት 9 ቀን 1971 ዓም ዐረፉ፡፡ በመጋቢት 22 የተሰበሰበው የግብጽ ሲኖዶስም ተተኪውን ለመምረጥ ዝግጅት ጀመረ፡፡ አምስት እጩዎችንም መረጠ፡፡ ነገር ግን በመካከሉ ቤተ ክርስቲያኒቱ አያሌ ፈተናዎች ገጠሟት፡፡ በዚህም ምክንያት ፓትርያርክ ሳይመረጠ ረዥም ጊዜ ቆየ፡፡ በጥቅምት 29 ቀን የተሰበሰበው ቅዱስ ሲኖዶስ የእጩዎችን ቁጥር ወደ ሦስት ዝቅ አደረገው፡፡ የሦስቱም እጩዎች ስም በመንበረ ማርቆስ ካቴድራል መንበር ላይ ተቀመጠ፡፡ ሕዝቡ እና ገዳማውያኑም ለሦስት ቀን ሱባኤ ያዙ፡፡
No comments:
Post a Comment