Saturday, 15 July 2017

ነገረ ሃይማኖት ክፍል ሃያ




ተዋሕዶ ስንል
አምላክ ፍጹም ሰው ሆነ፣ ሰውም ፍጹም አምላክ ሆነ ስንል በእንዴት አይነት ሁኔታ የሚለውን ማየት ያስፈልጋል፡፡ አምላክ ሰው የሆነው ሰውም አምላክ የሆነው፡-
እንበለ ውላጤ/ያለመለወጥ/ ነው

አንድነገር የራሱን ማንነት አጥቶ በሌላ ማንነት ሲተካ ተለወጠ ይባላል፡፡ ይህም የማንኛውንም ነገር መሠረታዊ መገለጫ የሆነውን የባሕርይ ለውጥ ያሳየናል፡፡ ለምሳሌ የሎጥ ሚስት ወደ ጨው ዐምድነት፣ የቃናው ውሃ ወደ ወይን ጠጅነት እንደተለወጠ ማለት ነው፡፡ አምላክ ሰው የሆነው ግን በመለወጥ አይደለም፡፡ የሎጥ ሚስት ወደ ጨው ዐምድነት ከተለወጠች በሆላ የጨው ዐምድ እንጂ የሎጥ ሚስት ኤደለችም፡፡ የቃና ውሃም ወይን ጠጅ እንጂ ውሃ አይባልም፡፡ እንደሎጥ ሚስት ወይም እንደቃና ውሃ መለኮት ተለውጦ ሥጋ የሆነ አይደለም፡፡ ቃል ሥጋ ሆነ ስንል መለኮታዊ ባሕርዩን ሳይለቅ ነው፡፡ ሥጋም አምላክ ሆነ ስንል ሥጋዊ ባሕርዩን ሳይለቅ ነው፡፡ ሁለቱም በተዋሕዶ አንድ ሲሆኑ ግን በተዐቅቦ የቃል ባሕርይ ለሥጋ ፤ የሥጋ ባሕርይ ለመለኮት ሆኗል፡፡ በመሆኑም ሥጋ ወደ ቃልነትሳይለወጥ ቃል ወደ ሥጋነት ሳይለወጥ ነገር ግን ሁለትነት ጠፍቶ አንድ አካል አንድ ባሕርይ ሆነ ይህም ተዋሕዶ ነው፡፡ ተዋሕዶ ከመለወጥ የራቀና የጸዳ ነው፡፡
እንበለ ሚጠት/ያለመመለስ/ ነው

አንድ ነገር ለጊዜው ከተለወጠ በኋላ ወደ ቀደመ ማንነቱ /ባሕርዩ/ የሚመለስ ከሆነ ሚጠት /መመለስ/ ይባላል፡፡ ይህም እንደ ሙሴ በትር እንደ ግብፅ ውሃ ያለ ነው፡፡ የሙሴ በትር ወደ እባብነት የግብፅም ውሃ ወደ ደምነት ተለውጠው ነበር፡፡ ኋላ ግን ወደ በትር እና ውሃነት ተመልሰዋል፡፡ ተዋሕዶ ግን እንደዚህ አይደለም፡፡ ቃል መጀመሪያ አምላክ የነበረ ሥጋ ሲዋሐድ ሰው የሆነ ከዚያም ወደ ቃልነቱ የተመለሰ አይደለም፡፡ ቃል ገንዘብ ለሥጋ ገንዘብ ሲሆን ባሕርያቸውን ሳይለቁ በመጠባበቅ ነው እንጂ፡፡
እንበለ ቱሳሔ/ያለመቀላቀል/ነው

ቱሳሔ ቅልቅል ማለት ነው፡፡ የሚቀላቀሉ ነገሮች ነባራዊ ባሕርያቸውን ይለቁና ሌላ አንድ የጋራ ባሕርይ ይፈጥራሉ፡፡ ለምሳሌ ወተትና ውሃ ቢቀላቀሉ ስማቸውን መልካቸውን ጣዕማቸውን ይዘታቸውን ይቀይራሉ፡፡ ውሃ እና ማርም እንደዚሁ ፡፡አምላክ ሰው የመሆን ምሥጢር ውስጥ ግን ይህ የለም፡፡ ሥጋ እና መለኮት ተቀላቅለው ያስገኙት ሦስተኛ አካል ወይም ባሕርይ የለም፡፡ ሥጋ ሥጋዊ ባሕርዩን ሳይለቅ መለኮትም መለኮታዊ ባሕርዩን ሳያጣ በመጠባበቅ አንድ ሆነዋል፡፡
እንበለ ኅድረት/ያለ ማደር/ ነው

ኅድረት አንድ አካል በሌላው አካል ውስጥ ገብቶ ማደር ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ እንደ ዳዊትና ማኅደሩ ፤ እንደ ሰይፍና ሰገባው ማለት ነው፡፡ በኤፌሶን ጉባኤ የተወገዘው ንስጥሮስ “ዳዊት በማኅደር ሰይፍ በሰገባው እንደሚያድር የማርያም ልጅ ኢየሱስ ላይ አምላክ አደረበት” በማለት የስህተት ትምህርቱን አስተምሮ ነበር፡፡
ዳዊት በማኅደር ቢያድር ዳዊት ይባላል እንጂ ማኅደር እንደማይባል ጌታም እንደ ዳዊትና ማኅደር አደረ ካልን መጽሐፍት አንዱን አካል ወልደ አብ ወልደ ማርያምን አምላክ ወሰብእ ከማለት ይልቅ የአምላክ ማደሪያ እያሉ ይጠሩት ነበር፡፡ ነገር ግን ይህ አልሆነም ፡፡ ሥጋ የቃል ማደሪያ ቃልም በሥጋ አዳሪ ስላልነበረ ከጽንሰት ጀምሮ አንድ አካል አንድ ባሕርይ ስለሆኑ እግዚአብሔር አብ ምስክርነቱን ሲሰጥ “በእርሱ ደስ የሚሰኝ ልጄ እርሱን ስሙት” በማለት ተናገረ እንጂ በእርሱ ውስጥ አድሮ ያለውን ልጄን ስሙት አላለም፡፡ በተዋሕዶ አንድ የሆነውን ሳይከፍል “ይህ የምወደው ልጄ ነው” አለ፡፡ (ማቴ 3÷17 ፤ ዮሐ 3÷12 ፤ ማቴ 16÷13-17)
እንበለ ትድምርት/ያለመደራረብ /ነው

ትድምርት ማለት መደራረብ ማለት ነው እንጂ እንጀራ አነባብሮ' እንደልብስ ያለ ነው፡፡ የቃል ሰው መሆን ግን መደራረብንና መነጠል ሲፈልግ የሚነጠል አይደለም፡: ሥግው ቃል ባለመነጣጠል ባለመለያየት በተዋሕዶ አንድ ሆኗል፡፡ “ሁለቱ ባሕርያት አንድ አካል አንድ ባሕርይ በመሆን አንድ ሆኑ ብንልም ከተዋሕዶ በኋላ በየራሳቸው አድርገን አንለያያቸውም፡፡ መከፈል የሌለበትን አንዱንም ሁለት እናድርገው ዘንድ አንከፍለውም፡፡ አንድ ወልድ አንድ እንደሆነ እንናገራለን እንጂ “ በማለት ቅዱ ቄርሎስ እንዳስተማረ ( ሃይ.አበው ምዕ 78 ክፍል 48÷ 17)
እንበለ ቡዐዴ /ያለማዋደድ/ነው

ቡዐዴ ማዋደድ ማያያዝ ነው፡፡ እንደ እንጨት እና ዛቢያው ያለ ነው፡፡ እንጨትና ዛቢያው ለአገልግሎት ስንፈልጋቸው በብሎን በሚስማር አንድ ልናደርጋቸው እንችላለን፡፡ ስንፈልግም ልንለያያቸው እንችላለን፡፡ የምሥጢረ ተዋሕዶ ነገር ግን እንደዚህ አይደለም ሥጋና ቃል ከተዋሕዶ በኋላ መለያየት የለባቸውም፡፡ ሲዋሐዱም እንደ እንጨት እና ዛቢያው ያለ ውሕደት አይደለም፡፡

እንበለ ፍልጠት /ያለ መለያየት/
ፍልጠት ማለት ሁለት ነገሮች ከተዋሐዱ በኋላ የሚመጣ መለያየት ነው እንደ ሥጋና ነፍስ፡፡ ሥጋና ነፍስ ተዋሕደዋል ግን በሞት መለያየት /ተፈልጦ/ አለባቸው፡፡ የመለኮት እና የሥጋ ተዋሕዶ ግን እንደ ሥጋና ነፍስ ቢሆንም ቅሉ ተፈልጦ/መለያየት/ የለበትም አንድ አካል አንድ ባሕርይ ሆነው ይኖራሉ እንጂ፡፡
እንበለ ተጋውሮ/ያለ መጎራበት/

ተጋውሮ ማለት መጎራበት ማለት ነው፡፡ ቤት ከቤት ጋር አጠጋግተው ቢሠሩት አንድ መንደር እንጂ አንድ ቤት አይባልም ምክንያቱም አካሉ የየራሱ ነውና፡፡ መለኮት ግን እንዲህ አይደለም አንድ ባሕርይ አንድ አካል ነው ስንል ባለመለያየት አንድ ናቸው ማለታችን ነው፡፡ ባል ከሚስቱ ጎረቤት ከቤቱ እንደሚጣበቅ ዓይነት አይደረም (ርቱ.ሃይማኖት)
ይቆየን ይቀጥላል
ስብሐት ለእግዚአብሔር

No comments:

Post a Comment