ዲ/ን ሚክያስ ይልማ
‹‹ ይህንን እዘዝና አስተምር በቃልና በኑሮ በፍቅርም በእምነትም በንጽሕናም ለሚያምኑት ምሳሌ ሁን እንጂ ማንም ታናሽነትህን አይናቀው››
የቅዱስ ጳውሎስ ደቀ መዝሙር ጢሞቴዎስ ወደ ክርስትናው የተጠራው ገና በልጅነቱ ነበር፡፡ የክርስትናን ትምህርት
ያስተማሩትም እናቱ ኤውንቄና አያቱ ሎይድ ነበሩ፤ ቅዱስ ጳውሎስ ስለዚህ ሲናገር ‹‹ በአንተ ያለውን ግብዝነት
የሌለበትን እምነትን አሳስባለው ይህም እምነት ቀድሞ በአያትህ በሎይድ በእናትህም ኤውንቄ ነበረባቸው፤ በአንተ ደግሞ
እንዳለ ተረድቻለሁ›› ሲል መስክሮለታል፡፡ (2ኛ ጢሞ.1፤5)
ቅዱስ ጳውሎስ የጢሞቴዎስን ልጅነት በመመልከት ያለውን የእምነቱን ጽናትና ቆራጥነት አስጠብቆ በመያዝ ለሌሎች
እንዲተርፍ ያስተምረው ይመክረው ነበር፡፡ ልጅ በመሆኑም የሚያስተምረው ትምህርት እንዳይንቁበት ‹‹ ልጅነትህን ማንም
የሚንቃት አይኑር በቃልና በኑሮ በፍቅርም በእምነትም በንጽህናም ለሚያምኑት ምሳሌ ሁን እንጂ በማለት ነግሮታል፡፡ለመሆኑ ምሳሌ የሚኮነው እንዴት ነው?
1. በቃል
ክርስትያኖች ከአንደበታቸው የሚወጣውን ንግግር ያማረና የተወደደ መሆን አለበት፤የሰው ማንነቱ የሚለካው ከአንደበቱ በሚወጣው ቃል ነውና በእንደ ራስም፤ ሁለት ምላስ ይዞ መገኘት የለበትም፡፡ዛሬ እግዚአብሔር ሆይ ከአንተ ጋር ነኝ ብሎ ሲያመሰግን ሲዘምር የዋለ አንደበት ተመልሶ በአርአያ ሥላሴ የተፈጠረውን ሰው የሚረግምና የሚወቅስ ከሆነ ምሳሌ ሆኖ መገኘት አይችልም፡፡
‹‹ በምላሳችን እግዚአብሔርን እናመሰግናለን በእርሱም በእግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠሩትን ሰዎች እንረግማለን›› ያዕ.13፤5-9 እንዲህ ከሆነ ከአንደበታችን የሚወጣው ቃል ሰውን የሚያንጽ ሳይሆን የሚገድል ክፉ መርዝ ይሆናል፡፡
ቅዱስ መጽሐፍ ከአንደበት ስለሚወጣ ቃል ሲናገር ‹‹ ለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ እንደሚያስፈልግ ለማነጽ የሚጠቅም ማናቸውም በጎ እንጂ ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ›› ይላል (ኤፌ 4፤29-30) አንድ ክርስቲያን የሚናገረውን የሚያውቅ አስቦ የሚናገር፤የማይዘባርቅ ሊሆን ይገባዋል የተመረጡና ያልተመረጡ ቃላትን ከአንደበት ማውጣት ለጽድቅና ለኩነኔም መለያ ነው ‹‹ ከቃልህ የተነሳ ትኮነናለህ›› እንዲል (ማቴ.12፡37) ንግግሩ ቁጥብ የሆነ ሰው ስለራሱ ብዙ በማውራት ክብር የማይፈልግ ነው፡፡
2. በኑሮ
ቅዱስ ጳውሎስ ለደቀመዝሙሩ ለጢሞቴዎስ በኑሮም ምሳሌ መሆን እንዳለበት አስጠንቅቆታል፡፡ ክርስትና የሚኖሩት ሕይወት ነው፡፡ ጌታችንም ‹‹በሰማያት ያለውን አባታችሁን ያከብሩ ዘንድ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ›› እንዳለ (ማቴ.5፤16 ) እምነታችን በሚያምኑትም በማያምኑትም ፊት የበለጠ እንዲከብር ሥራችን መልካም፤ አኗኗራችንም የማይነቀፍ መሆን አለበት፡፡ የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን የምናሳየው መልካም አኗኗርን በመያዝ ነው፡፡ ስለ ሌሎችም ማሰብ የተቸገረውን ፣የተራበውን ፣የታመመውን በመርዳት በመጎብኘት በመደገፍ መሆን አለበት፡፡‹‹ በመጥፎና ጠማማ ትውልድ መካከል ያለነቀፋ የዋሆች፤ ነውርም የሌለባቸው የእግዚብሔር ልጆች እድትሆኑ ሳታንጎራጉሩ ክፉም ሳታስቡ ሁሉን አድርጉ፤ በእነርሱም መካከል የሕይወት ቃል እያቀረባችሁ በዓለም እንደ ብርሃን ትታያላችሁ››እንዲል ፊሊ. 2፤4 አሁን በዚህ ዘመን እኛ ክርስቲያኖች ራሳችንን መለየት ይጠበቅብናል ዘመኑ የከፋ ነውና ስለሆነም በኑሯችን እግዚአብሔር አምላክ ያዘዘንን እየፈፀምን መኖር ይጠበቅብናል፡፡ ጌታችን በመዋዕለ ስብከቱ ‹‹ መልካሙን ስራችሁን ዓይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ›› በማለት ያስተማረው ምዕመናን ምሳሌነት ያለውን ኑሮ እንዲኖሩ ነው፡፡ በዚህ መሠረት አንድ ክርስቲያን ከቤተሰቡ አባላት ጋር ያለውን ሰላማዊ ፍቅርን የተሞላና መተሳሰብን ገንዘብ ያደረገ ኑሮ፤ ከሌሎችም ጋር ሰላማዊ ጉርብትና ሊኖረው ይገባል፡፡
3. በፍቅር
ጢሞቴዎስ መምህሩ ጳውሎስ ሲያስተምረው ለሰዎች በፍቅርም ምሳሌ ሁን ብሎ ጽፎለታል፡፡ ፍቅር ሕግ ሁሉ የሚጠቃለልባት ናት ሐዋርያው በመልዕክቱ ‹‹ እንግዲህ እንደ ባለ አእምሮ አስብ ትጸልዩም ዘንድ በመጠን ኑሩ ፍቅር የኃጢአትን ብዛት ትሸፍናለችና ከሁሉ በፊት እርስ በእርሳችሁ አጥብቃችሁ ተዋደዱ›› በማለት ጽፎላቸዋል(1ኛ ጴጥ 4፤8) እንዳለ ፡፡ፍቅር የእግዚአብሔር የባሕሪ ገንዘቡ ነው፡፡ ቀዳሜ ሰማዕት እስጢፋኖስ ለሚወግሩት ‹‹ ጌታ ሆይ ይህንን ኃጢአት አትቁጠርባቸው›› እስከ ማለት ያደረሰው ፍቅር ነው፡፡ (ሐዋ 7፤60) እኛም በፍቅር ሌሎችን ምሳሌ የምንሆነው የሚወዱንን ስንወድ ብቻ አይደለም የበደለንን ስንወድ፤ ፍቅራችንን ለሰዎች ሁሉ ያለ አድልዎ መስጠት ስንችል ይሆናል፤ ምክንያቱም ፍቅር እውነተኛ የሚሆነው ሰዎችን አተካክለን እንዲሁ ያለ ስጋዊ ምክንያት ስንወዳቸው ነው፡፡
ዛሬ አፍቃሪያን ነገ ደግሞ ግልብጥ ብለን በጥላቻ የተሞላን ሰዎች የምንሆን ከሆነ ከማፍቀር ይልቅ ጠላትነትን የምናነግስ ከሆነ ‹‹ ፍቅር ለዘወትር አይወድቅም ›› የተባለውን ቃል መጣስ ይሆንብናል፡፡ (1ኛ ቆሮ 13፡8) እንግዲህ ፍቅር እንደሞት የበረታች ናት እንደተባለ በአርአያ ሥላሴ የተፈጠረውን ሰው በጊዜውም ያለ ጊዜውም መልካም ቢያደርግልንም ሆነ ክፉ ቢያደርግብን ልንወደው ይገባል፡፡
4. በንጽሕና
በክርስትና ኑሮዋችን በቅድስናና በንጽህና መመላለስ ይገባናል፡፡ አፍአዊም ሆነ ውስጣዊ ማንነታችን ለእግዚአብሔር የተመቸ እግዚአብሔርን ደስ የሚያስኝ እንጂ የሚያሳዝን እንዳይሆን ልንጠነቀቅ ይገባል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ለደቀ መዝሙሩ ለጢሞቴዎስ በንጽህና እየተመላለስህ ምክር አስተምር ያን ጊዜ የምታስተምራቸውም ሰዎችም ሁሉ ሌሎች አንተንም ሆነ እግዚአብሔርን ያከብራሉ ትምህርትህንም ሳያመነቱ ይቀበላሉ ፍሬ ሃይማኖትን፤ፍሬ ምግባርን በማፍራት ለእግዚአብሔር የታመኑ ይሆናሉ በማለት ምሳሌ እንዲሆን አሳስቦታል፡፡በተለይ በወጣትነት ዘመን በምኞች ምክንያት ከሚመጡ የተለያዩ ሥጋዊ ፈተናዎች ራስን በንጽህና ጠብቆ መገኘት ይገባል፡፡ ብዙ ቅዱሳን ስጋቸውን ለነፍሳቸው አስገዝተው ሰውነታቸውን እየጎሰሙ ሰማያዊውን መንግስትን በመሻት ኖረዋል አልፈዋል እኛም እነሱን አብነት አድርገን በንጽህና በቅድስና መኖር እንዳለብን ማስተዋል ይገባናል፡፡
5. በእምነት
በእኛ በክርስቲያኖች እምነታችን የክርስትና መሠረት መሆኑን ማወቅ አለብን እምነት የሌለው ሰው ከእግዚአብሔር ዘንድ አንዳች አይደረግለትም፡፡ ሙሴ የፈርዖንን የልጅ ልጅ እንዳይባል በእምነቱ ጸንቶ እንቢ በማለቱ ነበር ለጊዜው በኃጢአት ከሚገኝ ደስታ ይልቅ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራን መቀበልን መርጦ ነው በእምነቱ ጽናት ምሳሌ ሊሆን የቻለው፡፡ቅዱሳን አባቶቻችን ለእምነታቸው ሲሉ፤ ለእምነት እየኖሩ የዚህችን ዓለም ጣዕም በመናቅ መከራን እየተቀበሉ እየተጨነቁ የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ተንከራተዋል፣ እነዚህም በእምነታቸው ተመስክሮላቸዋል ፡፡ (ገላ 11፡37) በእምነት ጸንቶ ለቀናችው ለርትዕት ሃይማኖት እስከ መጨረሻው ድረስ መቆየት በየጊዜው ከሚመጣው የክህደት ትምህርት በመጠበቅ በእምነት ማደግን ከቀደሙ አባቶቻችን እንማራለን ፡፡ እንግዲህ ‹‹ ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለተሰጠ ሃይማኖት ተጋደሉ›› አንዴ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለመሠረታት ቅዱሳን፣ሰማዕታት የተለያዩ መከራን ለተቀበሉላት ሐዋርያዊት ሃይማኖት አርአያ ልንሆን ይገባናል፡፡
በቅዱሳን ጸሎት እግዚአብሔር ደስ የሚሰኝበትን ሕይወት ለመኖር መዘጋጀት አለብን፤ስለሆነም በቃልና በኑሮ በፍቅርም በእምነትም በንጽህናም ለሚያምኑት ምሳሌ እንሆን ዘንድ የእግዚአብሔር ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን አሜን፡፡
እጅግ ግሩም የሆነ ትምህርት ነው ቃለ ህይወትን ያሰማልን
ReplyDeleteቃለ ሕይወት ያሰማልን
ReplyDelete