ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የሐዋርያቱን የቅዱስ ጴጥሮስን እና ጳውሎስን ሰማዕትነት ሐምሌ አምስት ቀን ታስባለች፡፡ እነዚህ ሁለት ቅዱሳን አባቶቻችን የቅድስት ቤተክርስቲያናችን አዕማድ ናቸው፡፡ በመሠረትነት በአጸኗት ቤተክርስቲያን ያላቸው የክብር ሥፍራ ላቅ ያለ ነው፡፡ ይህ የሆነው እንዲሁ አይደለም፡፡ ለቤተክርስቲያንና በቤተክርስቲያን የፈጸሙት አገልግሎት በዚህም የተቀበሉት ሰማዕትነት ነው፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍትም ይህን መልካም የሆነውን ታሪካቸውን ለእኛ አርአያነት በሚሆን መልኩ ከትበውልናል፡፡ እኛም ለአርአርያነት በሚሆን መልኩ የእነዚህን ደጋግ ሁለት ቅዱሳን አባቶች ታሪክ፣ ዕውቀትና መንፈሳዊ አገልግሎታቸውን ከዚህ በመቀጠል አቅርበናል፡፡
ቅዱስ ጴጥሮስ
ትውልዱ እና እድገቱ
ቅዱስ ጴጥሮስ የተወለደው በገሊላ ባሕር ባለች ቤተሳይዳ በተባለች ከተማ ውስጥ ነው የአባቱስም ዮና ሲሆን ትውልዱም ከነገደ ሮቤል ነው። እናቱ ደግሞ ከነገደ ስምዖንወገንየሆነች ነበረች። በመሆኑም እንደ ኦሪት ሥርዓት ስም ሲያወጡለት በእናቱ ነገድ ስም ስምዖን ብለውታል። አባቱ ዮና የያዕቆብና የዮሐንስ አባት ከሆነውከዘብዴዎስጋር የሥራ ባልንጀራ ሲሆን የሁለቱም ሥራቸው ዓሣ እያጠመዱ መሸጥነበር።እድሜው ፭ ዓመት ሲሆን ኦሪትን እየተማረ እንዲያድግ በአቅራቢያቸው ወዳለወደቅፍርናሆም ምኩራብ ሰደዱት። ቅዱስ ጴጥሮስ በቅፍርናሆም እየተማረ ካደገበኋላበዚያው ቤት ሠርቶ ኮንኮርድያ (ጴርጴቱዋ) የምትባል ሚስት አግብቶ እንደ አባቱ ዓሣ እያጠመደ በመሸጥ መኖር ጀመረ። ለቅዱስ ጴጥሮስ እንድርያስ የተባለ ወንድም ነበረው። ሥራውም ልክ እንደ ወንድሙ ዓሣ ማጥመድ ነበር። ነገር ግን ይህ እንድርያስ የመጥምቀ መለኮት ቅዱስዮሐንስ ደቀ መዝሙርነበር። መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ “ነዋ በግዑ ለእግዚአብሔር ዘየአትት ኃጢአተ ዓለም፤ እነሆ የዓለሙን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ” እያለ ስለ ክርስቶስ ሲመሰክር ሰምተው ክርስቶስን ከተከተሉት የመጀመሪያዎቹ ሁለት ሐዋርያት አንዱ ነው /ዮሐ. ፩: ፴፭ – ፵/።
የቅዱስ ጴጥሮስ መጠራት
ቅዱስ ጴጥሮስ ለመጀመሪያ ጊዜ ከክርስቶስ ጋር የተዋወቀው በወንድሙ በእንድርያስ ግብዣነው። እንድርያስ ከመምህሩ ከመጥምቁ ዮሐንስ ምስክርነትሰምቶ ክርስቶስን ከተከተለ በኋላወዲያውኑ ለወንድሙ ለቅዱስ ጴጥሮስ“በትርጓሜው ክርስቶስ የሚሉት መሲሕን አገኘነው”በማለት ወደ ኢየሱስ ክርስቶስወስዶታል። ጌታም ቅዱስ ጴጥሮስን ባየው ጊዜ “አንተ የዮናልጅ ስምዖን ነህ፤አንተ ኬፋ (ጴጥሮስ) ትባላለህ” አለው /ዮሐ. ፩ : ፵፪ – ፵፫/። ይህም ወደ ፊት እርሱን እንደሚከተለውና “አንተ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ ነህ”ብሎሲመሰክር ስሙን ቀይሮ “አንተ ዐለት (ጴጥሮስ) ነህ …” እንሚለው ትንቢትሲነግረውነው /ማቴ. ፲፮ : ፲፫ – ፳/።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በገሊላ አውራጃ እየተዘዋወረ ሲያስተምር አንድ ቀን ጠዋትበጌንሴሬጥ ባሕር ወደብ ብዙ ሰዎች ቃሉን ለመስማት ተሰበሰቡ። ጌታችን በወደቡ ሌሊቱን ሙሉ ዓሣ በማጥመድ ሥራ ሲደክሙ ያደሩ ዓሣ አጥማጆችን አገኘ። ከነዚህም መካከል ቅዱስ ጴጥሮስና ወንድሙ እንድርያስ እንዲሁም ሁለቱ የዘብዴዎስ ልጆች ያዕቆብና ዮሐንስ ነበሩ።ጌታችንም ቃሉን ለመስማትየተሰበሰበውን ሕዝብ ብዛት አይቶ ከሕዝቡ ጋር ፊት ለፊትእየተያየ ለማስተማር እንዲመቸው ወደ ቅዱስ ጴጥሮስ ታንኳ ገብቶ በታንኳው ላይ ሆኖማስተማርጀመረ። ትምህርቱን ሲጨርስ ቅዱስ ጴጥሮስን “መረብህን ጣልና ዓሣ ያዝ”አለው።ሌሊቱን ሙሉ ሲደክሙ አድረው ምንም አይነት ዓሣ አላገኙም ነበርና ቅዱስጴጥሮስ“መምህር ሆይ! ሌሊቱን ሁሉ ስንደክም አድረን ምንም አላገኘንም፤ ነገርግን እንደቃልህመረቡን ወደ ባሕር እንጥላለን” በማለት ሳይጠራጠር መረቡን ወደባሕር ጣለ። በዚህ ጊዜመጎተት እስኪያቅታቸውና እስኪደነቁ ድረስ ጌታችን ብዙዓሦች ወደ መረቡ እንዲገቡአደረገ።
ቅዱስ ጴጥሮስ የተደረገውን ተዓምር አይቶ ከጌታችን እግር ሥር ሰገደና እንዲህአለ፡-“እኔ ኃጢአተኛ ሰው ነኝና አቤቱ ከኔ ፈቀቅ በል” /ሉቃ. ፭: ፰/። አባቶች ይህንንሲተረጉሙ ቅዱስ ጴጥሮስ ይህንየተናገረው “ባሕርንና በውስጧ ያሉትን ፍጥረታት የሚያውቅየእኔንማ ኀጠአት እንዴት መርምሮ ይፈርድብኝ ይሆን?!” ብሎ በመፍራትና ስለራሱ ኃጢአት በማሰብ “ካንተ ጋር መኖር የማይገባኝ ኀጥእ ነኝ” በማለት ስለፍጹም ትኅትና ነው ይላሉ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የቅዱስ ጴጥሮስን ፍርሃትና ድንጋጤ አይቶ፡-“ስምዖን ሆይ አትፍራ! ከእንግዲህ ወዲህ ዓሣ ሳይሆን ሰውን የምታጠምድ ትሆናለህ” ብሎ ሁለቱንም “ተከተሉኝ” አላቸው። በዚህ ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስናወንድሙ እንድርያስ ሁሉን ትተው ተከተሉት /ሉቃ. ፭ : ፩ – ፲፩/። ከዚህ ጊዜጀምሮ ቅዱስ ጴጥሮስ ሚስቱን፣ ትዳሩን፣ሥራውን፣ ዘመዶቹን በአጠቃላይየዚህን ዓለም ኮተት በሙሉ እርግፍ አድርጎ ትቶ ሙሉ ጊዜውን ከጌታ ጋር በማድረግ መደበኛ ደቀ መዝሙሩ ሆነ። ለዚህም ማስረጃው በሌላ ቦታ ቅዱስጴጥሮስ ጌታችንን “ሁሉን ትተን ተከተልንህ፣ እንግዲህ ምን እናገኛለን?”ሲልመጠየቁና ጌታም “የተከተላችሁኝ እናንተ በዳግም ልደት በ፲፪ ዙፋን ትቀመጣላችሁ፤በ፲፪ቱም ነገደ እሥራኤል ትፈርዳላችሁ። ስለስሜም ቤትን፣ ወይም ወንድሞችን፣ ወይም እኅቶችን፣ ወይም አባትን፣ ወይም እናትን፣ ወይም ሚስትን፣ ወይም ልጆችን፣ ወይም ርስቱን የተወ መቶ እጥፍ ዋጋ ያገኛል” ብሎ መመለሱ ነው /ማቴ. ፲፱ : ፳፯ – ፳፱/።
ጌታ የቅዱስ ጴጥሮስን አማት መፈወሱን
ጌታችን እንደ ልማዱ በገሊላ ባሕር ዳር ባሉ መንደሮችና ከተሞች እየገባ ሲያስተምር አንድ ቀን በቤተ ሳይዳ በቅዱስ ጴጥሮስ ቤት ገብቶ አማቱን ከበሽታዋ ፈወሰለት። ይህንንምሲያደግለት የቅዱስ ጴጥሮስ እምነት ይበልጥ ጸና፤ልቡንም ደስ አሰኘው።
ቅዱስ ጴጥሮስ ጌታን ከተከተለ ጊዜ ጀምሮ ከዋለበት እየዋለ ካደረበት እያደረ የጌታችንን ትምህርት በሚገባ ተከታትሏል። ይህ ብቻም አይደለም፤ ጌታ በሚያስተምራቸው ወቅት በጥያቄና መልስ ፈጣንና ንቁ ተሳትፎም ነበረው። ጌታችን ሐዋርያትን ጥያቄ ሲጠይቃቸውብዙ ጊዜ ፈጥኖ ይመልሳል፤ እርሱም ያልገባውን ነገር ለመረዳትና የሚፈልገውን ነገር ለማድረግ በተደጋጋሚ ለጌታችን ጥያቄ ያቀርብ ነበር። ጌታም በበኩሉ የተለያዩ ትዕዛዛትን ሲያዘው እንመለከታለን። ለአብነትም የተወሰኑትን ብንመለከት፡-
ቅዱስ ጴጥሮስ በባሕር ስለመራመዱ
1. ጌታችን አምስት እንጀራና ሁለት ዓሣ አበርክቶ አምስት ሺህ ሕዝብ ሲያጠግብ ዓይተው ሕዝቡ ይህንንስ እናንግሠው ብንራብ ያበላናል፣ብንታመም ይፈውሰናል፣ብንሞት ያሥነሣናል በሚል ሥጋዊ አስተሳሰብሊ ያነግሡት ፈለጉ። ጌታችንም ይህንሐሳባቸውን አውቆ የመጣበት ዓላማ ይህ አይደለምና ደቀ መዛሙርቱ ቀድመውትበጀልባ ተሻግረው እንዲሄዱአድርጎ እርሱ ብቻውን ወደ ተራራ ወጥቶ መጸለይጀመረ። ደቀ መዛሙርቱ እንደታዘዙት በመርከብ ሲሄዱ ብርቱ ነፋስ ተነሥቶአናወጣቸው።በአራተኛው ሰዓተ ሌሊት ጌታችን በባሕሩ ላይ በእግሩተከተላቸውናአጠገባቸው ደረሰ። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ የማዕበሉብርታትከጨለማው ጋር ተዳምሮ እጅግ በተጨነቁበት ጊዜ ወደ እነርሱ የሚመጣው “ምትሐት ነው” ብለው እጅግ ተረበሹ። በዚህ ጊዜ ጌታችን“አይዟችሁ አትፍሩ እኔ ነኝ” ብሎ ማንነቱን ነገራቸው። ድምጹን ሰምተው ከተረጋጉ በኋላ ቅዱስ ጴጥሮስ “ጌታ ሆይ አንተስ ከሆንህ በባሕሩ ላይ በእግሬ ወደ አንተ እንድመጣ እዘዘኝ” ብሎ ጠየቀው። ጌታም “ና” አለው። ቅዱስጴጥሮስከመርከቡ ወረዶ መጓዝ እንደጀመረ ገና በመንፈስ ቅዱስ አልታደሰም ነበርና የማዕበሉን መበርታት እይቶ ስለፈራ መስጠም ጀመረ፤ ወደ ጌታም “አድነኝ” ሲልጮኸ። ጌታም እጁን ዘርግቶ ወደ መርከቡ ካወጣው በኋላ “ከእኔ ጋር ሆነህ እንዴትትጠራጠራለህ” በሚል ገሰጸው/ማቴ. ፲፬ ፥ ፳፭ – ፴፬/።
የቅዱስ ጴጥሮስ ምስክርነት

2. ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እያስተማረ ወደ ፊልጶስ ቂሣርያ ሲደርስ ሐዋርያትን በጥበብ ስለራሱ ማንነት ለማስረዳት ሲል በተዘዋዋሪ ሌሎች ሰዎች ምን እንደሚሉትሐዋርያትን ጠየቃቸው። ሐዋርያትም “አንዳንዱ መጥምቁ ዮሐንስ ነው፣ አንዳንዱ ኤልያስ ነው፥ ሌሎች ደግሞ ከነቢያት አንዱ ነው ይሉሃል” ሲሉ መለሱለት። ጌታችንም“ለመሆኑ እናንተስ ምንትሉኛላችሁ” ብሎ ስለ እርሱ ያላቸውን ግንዛቤ ጠየቃቸው።በዚህ ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ “አንተ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ ነህ”ሲል መሰከረ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “የእኔ ትክክለኛ ማንነት ሌሎች(አይሁድ) እንዳሉት ሳይሆን ቅዱስ ጴጥሮስ እንዳለው(እንደተናገረው) ነው” በማለት ቅዱስ ጴጥሮስን እጅግ አድርጎ አመስግኖታል:- “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ አንተ ብፁዕ ነህ፤በሰማያትያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም ይህን አልገለጠልህምና። እኔምእልሃለሁ፥ አንተ ዐለት ነህ፥ በዚያች ዐለት ላይም ቤተ ክርስቲያኔን እሠራታለሁ፥የሲኦል በሮችም አይበረታቱባትም” /ማቴ. ፲፮ ፥ ፲፫ – ፲፱/። ቅዱስ ጴጥሮስ የክርስቶስን የባሕርይ አምላክነት ከመሰከረ በኋላ ጌታችንስሙንቀይሮለታል። ስምዖን ይባል የነበረው “ዐለት” ተባለ (በዕብራይጥኬፋ፣በጽርዕ(ግሪክ) ጴጥሮስ፣ በግዕዝ ኰኵሕ በአማርኛ ዐለት ማለት ነው)። ጌታበዚህች ዐለት ላይ ቤተክርስቲያኑን እንደሚሠራትም ተናግሯል። ይህምማለትቤተክርስቲያን የምትመሠረተው በቅዱስ ጴጥሮስ ሃይማኖት ማለትምበክርስቶስ ማንነት ላይ ባለ ትክክለኛ እምነት ነው ማለት ነው። እርሱም“ጌታችን ኢየሱስክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ” መሆኑንጠንቅቆ ማመን ነው።ሁሉም ሐዋርያት ከጌታ ጋር በነበራቸው የተማሪነትቆይታ ከተረዷቸው ትምህርተ ሃይማኖት (ዶግማዎች) አንዱ ይህ ነው።ጌታም “የሰውን ልጅ ሰዎች ማን እንደ ሆነይሉታል?” ብሎ የጠየቃቸውናቅዱስ ጴጥሮስ ትክክለኛውን መልስ ሲመልስ ማመስገኑ ይህንንሊያስተምራቸው ስለወደደ ነው።
ቅዱስ ጴጥሮስ በደብረ ታቦር
3. ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጌትነቱን በደብረ ታቦር ተራራ ከገለጠላቸውሦስትሐዋርያት መካከል ቅዱስ ጴጥሮስ አንዱ ነው። “ከስድስት ቀንም በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ወንድሙ ዮሐንስን ይዞለብቻቸው ወደ ረጅም ተራራ አወጣቸው። መልኩም በፊታቸው ተለወጠ፥ፊቱም እንደ ፀሐይ አበራ፥ ልብሱምእንደ ብርሃን ነጭ ሆነ። እነሆ፥ሙሴና ኤልያስም ከእርሱ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው/ማቴ. ፲፯ ፥ ፩ – ፫/።ቅዱስ ጴጥሮስ የጌታችንን ጌትነት ከተመለከተ በኋላከደስታው ብዛትየተነሣ ጌታችንን እንዲህ ብሎ ጠይቆት ነበር፤ “አቤቱ በዚህ መኖርለእኛመልካም ነው፤ ብትወድስ፥ ሦስት ቤቶችን በዚህ እንሥራ፤ አንዱን ለአንተአንዱንም ለሙሴ አንዱንም ለኤልያስ” /ማቴ. ፲፯ ፥ ፩ – ፯/።ሙሴና ኤልያስ በደብረ ታቦር ከጌታችን ጋራ መታየታቸው ለቅዱስ ጴጥሮስእምነቱን የሚያረጋግጥለትና የሚያጸናለት ነገር ነው። “ሰዎች እኔን ማንይሉኛል” ብሎ በጠየቀ ጊዜ “ኤልያስ ነው ወይም ከነብያት አንዱ (ሙሴ)ነው” ብለውት ነበርና የሙሴና ኤልያስ ከጌታችን ጋር ሲነጋገሩ መታየት ጌታችን ሙሴ ወይም ኤልያስ አለመሆኑን ያረጋግጣል። በተጨማሪምለቅዱስ ጴጥሮስ “አንተ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ ነህ” ብሎ የመሰከረውን አብ ደግሞ በደመና ሆኖ “የምወደው በእርሱ ደስየሚለኝ ልጄይህ ነው፤ እርሱን ስሙት” ማለቱ የቅዱስ ጴጥሮስን ምስክርነት የሚያረጋግጥ ነው። ቅዱስ ጴጥሮስ በደብረ ታቦር ለመኖር አስቦ ሶስት ቤት ብቻ እንሥራ ብሎ በተናገረ ጊዜ አንዱን ለአንተ አንዱን ለሙሴ አንዱን ለሙሴ አንዱን ለኤልያስ አለ እንጂ ለእኔና ለባልንጀሮቼ ብሎ አልተናገረም ይህም ንግግሩ ቅዱስ ጴጥሮስ እንደ ቤተሰብ ሆኖ ጌታውን እያገለገለ ከጌታው ጋራ ለመኖር ማሰቡን ያስረዳል እንጂ ከጌታው ተለይቶ ለብቻው ጌታ ሆኖ ለመኖር ማሰቡን አያስረዳምና ያስመሰግነዋል
4. ጌታችንና ደቀ መዛሙርቱ ወደ ቅፍርናሆምም በመጡ ጊዜ የቤተ መቅደስ ግብር የሚቀበሉ ሰዎች ቅዱስ ጴጥሮስን “መምህራችሁ ለቤተ መቅደስግብር ይገብራልወይስ አይገብርም” የሚል ጥያቄ አቅርበውለት ነበር። “ወደቅፍርናሆምም በመጡጊዜ ግብር የሚቀበሉ ሰዎች ወደ ጴጥሮስ መጥተውመምህራችሁ ሁለቱን ዲናርአይገብርምን?አሉት። እርሱም መልሶ አዎን(ይገብራል) አለ” እንዲል /ማቴ. ፲፯ ፥፳፬ – ፳፭/። ቅዱስ ጴጥሮስግብር ተቀባዮች በጠየቁት ጊዜ ጌታችን የእግዚአብሔርልጅ እንደሆነየመሰከረውንናልጅ ደግሞ ከግብር ነጻ መሆኑን ባለማገናዘብ“አዎንይገብራል” አላቸው። ጌታችንም “አዎን” ማለቱን አውቆ እርሱ ከግብር ነጻ መሆኑን በነገሥታት ልጆች ምሳሌ ካስረዳው በኋላ ነገር ግን እነርሱን ላለማሰናከል በተአምራት ከዓሣ ሆድ ገንዘብ አስገኝቶ ለሁለታቸውምእንዲሰጥ አዘዘው። “ወደቤትም በገባ ጊዜ ጌታችን ኢየሱስ አስቀድሞ ስምዖን ሆይ፥ ምን ትላለህ? የምድር ነገሥታት ቀረጥና ግብር ከማን ይቀበላሉ? ከልጆቻቸው ወይስ ከሌሎች? አለው።ጴጥሮስም፦ ከሌሎችነው አለ፤ ጌታችን ኢየሱስም አለው፤ እንኪያስ ልጆቻቸው ነጻ ናቸው።ነገር ግን እንዳያጉረመርሙ፥ ወደ ባሕር ሂድና መረብ ጣል፥በመጀመሪያም የያዝከውን ዓሣ ወስደህ አፉን ክፈት፤ በውስጡም ሰጣጢራታገኛለህ፤ ይከውምአራት ድሪም ነው፤ እርሱንም ወስደህ ስለ እኔና ስለአንተ ስጣቸው አለው” እንዲል“ማቴ. ፲፯ ፥፳፭ ፍጻሜ/።እንዳያጉረመርሙ (እንዳናሰናክላቸው) ማለቱ ጌታችንየእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ብሎ ለቤተመቅደስ ግብር ሳይገብር ቀርቶ ቢሆን ኖሮአምላክነት ብቻእንጂ ሰውነት የለውም ባሉ ነበርና ነው።
ቅዱስ ጴጥሮስ ስለሚያገኘው ዋጋ መጠየቁ
5. ቅዱስ ጴጥሮስ ትዳሩን፣ ቤቱን፣ ንብረቱን፣ ዘመዶቹን በአጠቃላይ ይህ ዓለም እርግፍ አድርጎ ትቶ ጌታችንን በመከተሉ ምን እንደሚያገኝ ጌታችንን በአንድ ወቅት ጠይቆት ነበር። “ከዚህም በኋላ ጴጥሮስ መልሶ፥ ሁሉንትተን ተከተልንህ፣ እንግዲህምን እናገኛለን አለው” እንዲል። ጌታችንም ሐዋርያት በጠቅላላ በፍጹም ልባቸው ዓለም በቃኝ ብለው እርሱንበመከተላቸው የሚያገኙትን ዋጋ ነገራቸው፤ እንዲህምአላቸው፡-“እውነት እላችኋለሁ የተከተላችሁኝ እናንተ በዳግም ልደት የሰውልጅበክብሩ ዙፋን በተቀመጠ ጊዜ እናንተም በ፲፪ ዙፋን ትቀመጣላችሁ፤ በ፲፪ቱምነገደ እሥራኤል ትፈርዳላችሁ። ስለስሜም ቤትን፣ ወይምወንድሞችን፣ ወይምእኅቶችን፣ ወይም አባትን፣ ወይም እናትን፣ወይም ሚስትን፣ ወይም ልጆችን፣ ወይምርስትን የተወ መቶ እጥፍ ዋጋ ያገኛል” /ማቴ. ፲፱ : ፳፯ – ፳፱/።
የቅዱስ ጴጥሮስ ትኅትና
6. መዝገበ ትኅትና የሆነው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀመዛሙርቱትሕትናን ሊያስተምራቸው ዝቅ ብሎ እግራቸውን ማጠብ በጀመረ ጊዜ ወደ ቅዱስጴጥሮስ ሲደርስ ለጌታው ካለው አክብሮትና ፍቅርየተነሣ እንዲሁም እርሱ አምላክሲሆን ዝቅ ብሎ የእነርሱን እግር በማጠቡእጅግ ተደንቆ “በፍጹም አታጥበኝም”አለ። ጌታችን ኢየሱስም “እኔየምሠራውን አንተ ዛሬ አታውቅም፥ ኋላ ግንታስተውለዋለህ” ቢለውም አሁንም ቅዱስ ጴጥሮስ በጌታውና በአምላኩ እግሩንመታጠብ እጅግስለደነቀውና ስለከበደው “መቼም ቢሆን አንተ እግሬን አታጥበኝም”አለው። በዚህ ጊዜ ፈጽሞ እንቢ ማለቱን ባየ ጊዜ “እውነት እውነት እልሃለሁ እኔ እግርህን ካላጠብሁህ፥ ከእኔ ጋር ዕድል ፋንታ የለህም”ብሎ መለሰለት። በዚህ ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ ሁሉን ትቶ የተከተለውን ጌታ ከማጣት የሚበልጥ ምንም ነገር እንደሌለ ስለሚያውቅ “አቤቱ፥ እንኪያስየምታጥበኝእጆቼንና ራሴንም እንጂ እግሮቼን ብቻ አይደለም አለው።ጌታችን ኢየሱስም፦
ፈጽሞ የታጠበ ከእግሩ በቀር ሊታጠብአያስፈልገውም፥ ሁለንተናው ንጹሕ ነውና፤እናንተማ ንጹሐን ናችሁ፥ ነገር ግን ሁላችሁ አይደላችሁም አለው።” /ዮሐ. ፲፫ ፥ ፩- ፲፩/።
የቅዱስ ጴጥሮስ ንስሐ
7. ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በካህናት አለቆችና በአይሁድ ሽማግሌዎችተላልፎ የሚሰጥበትና መከራ የሚቀበልበት ሰዓት ሲደርስ ይህንን መራራእውነት ለደቀመዛሙርቱ ሲነገራቸው እጅግ ተረብሸው ነበር። ይባስ ብሎ ደግሞ በመጨረሻው ሰዓት ሁሉም ደቀ መዛሙርት እንደሚክዱትበነገራቸው ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ “ሌሎች ቢክዱህ እንኳን እኔ በፍጹም አልክድህም” አለው። ጌታችን እርሱ ባወቀ ዶሮሳ የጮህ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ ቢለውም እርሱ “በፍጹም” አለ። ነገር ግን አይሁድጌታችንንይዘው መከራ ሲያጸኑበት አይቶ እርሱን ያገኘ ያገኘኛል ብሎ “አንተ ከእርሱ ወገን ነህ” ሲሉት “በፍጹም አይደለሁም” እያለ መማል ጀመረ። ወዲያው ዶሮ ሲጮክ ጌታ የተናገረውን ቃል አስታውሶ በዚያችው ቃል“አላበጀሁም”በማለት በፍጹም ጸጸት ማንባት ጀመረ(ንስሓ ገባ) /ማቴ. ፳፮ ፥ ፳፱-ፍጻሜ/።ቅዱስ ጴጥሮስ ለጌታችን ካለው ፍቅርና ቀረቤታ ታሪኩ በቅዱስ ወንጌል በስፋትተገልጿል፤ሁሉንም ዘርዝሮ መጥቀስ ባይቻልም። ቅዱስ ጴጥሮስ ጌታችንበእውነት ከሙታን ተለይቶመነሣቱን መቃብሩን በማየት ያረጋገጠ፣ ጌታችንግልገሎቼን ጠቦቶቼንና በጎቼን ጠብቅ ብሎ እንደሾመው እርሱም ልክ እንደጌታው ለበጎቹ መልካም እረኛ በመሆን የታመነ፣ መንፈስቅዱስ ከወረደላቸው በኋላበመንፈስ ቅዱስ ታድሶ በአንድ ጊዜ ሦስት ሺህ ነፍሳትን አሳምኖያጠመቀ፣ ብዙተአምራትን በጌታችን ኃይል ያደረገ፣ የሐናንያንና የሰጲራን ድብቅ ሥራ በመንፈስ የመረመረ፣ በሰማርያ በኢዮጴና በልዳ ዞሮ ወንጌልን ያስተማረ፣ በመጨሻምበሮማወንጌልን ሲሰብክ በአደባባይ የቁልቁሊት ተሰቅሎ ፍጹም ጌታውን የመሰለ ታላቅ ሐዋርያ ነው።

ቅዱስ ጴጥሮስ ስለ ክርስትና ሃይማኖት የአይሁድ መሪዎችንና ሊቃነ ካህናቱን ይሞግት፤ ከእነርሱም ፊትምስክርነት ይሰጥ ነበር፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ የአይሁድን ሊቃነ ካህናት «ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል» እያለ በሸንጎ ይሟገት ነበር፡፡ /የሐዋ.5.29/ በዚህም ብዙውን ጊዜ ይገረፍ ይታሰር ነበር ቅዱስ ጴጥሮስ እየተዘዋወረ ሲያስተምር በወንጌል የወለዳቸውን ክርስቲያኖች ከልዩ ልዩ ፈተናዎች ለማጽናት ሲል ሁለት መልእክታትን ጽፏል። የመጀመሪያመልእክቱን የጻፈውአይሁድ ለሚያሳድዷቸውና መከራ ለጸኑባቸው ከእስጢፋኖስ ሰማዕትነት በኋላ በስደትለተበተኑ ክርስቲያኖች ነው። ሁለተኛውን መልእክቱንየጻፈበት ምክንያት ደግሞ በወቅቱ የሮማ ግዛት መሪ የነበረው ኔሮን ቄሣር ክርስቲያኖች ሁሉ እየተያዙ እንዲፈረድባቸው አዋጅነግሮ ነበርና በዚሁ ምክንያት ለተጨነቁ በእስያ ላሉ ክርስቲያኖች ነው። ከዚህም በተጨማሪ ሐሰተኞች መምህራን ተነሥተው በሐሰተኛ ትምህርታቸው ስላስጨነቋቸው ለማጽናት ጽፎላቸዋል።
ቅዱስ ጴጥሮስ በሮም የወንጌል አርበኛ ሆኖ የቃለ እግዚአብሔርን ዝናር በወገቡ ታጥቆ ርኩሳን መናፍስትን በቃለ ወንጌል እያሳደደ ክርስትናን ባእድ አምልኮ ቀስፎ በያዛት በሮም ምድር እያስፋፋ ሳለ አንድ ያልታሰበ ነገር ተከሰተ፡፡ታላቋን የሮም ከተማ የፅልመት ሠራዊት ከቧታል በሰማይ ላይ የፈሰሱት ከዋክብት እርስ በእርሳቸው ከመጠቃቀስ በስተቀር ለከተማዋ ብርሃናቸውን በመለገስ ጨለማውን በመጠኑም አላስወገዱላትም፡፡ ሞቃቱ የምሽት ነፋስ የሮም ከተማን ይዞራል።የሮም ከተማ እሳት ቃጠሎ ከመሃል ከተማው የፈነጠቀው ውጋገን በአንድ ጊዜ እንደ ሞት ከብዶ የነበረውን ጨለማ ገፎ ከተማዋን በብርሃን ጎርፍ እንድትጥለቀለቅ አደረገ ፡፡ የእሳቱ ነበልባል እየተጎረደ፣ እየተጎረደ ግዛቱን ያሰፋል የእሳቱ ቃጠሎ መላ የሮም ከተማን ባጭር ጊዜ አጥለቀለቃት ፡፡ ከተማዋ በእሳት ባህር ተከበበች፡፡ ታላላቅ ቤቶች የእሳት ራት ሆኑ፡፡ ቤተ መቅደሶቹ ፈራረሱ ሱቆች በውስጣቸው ከያዙት ዕቃ ጋር አመድ ሆኑ፡፡ ነገር ግን የእሳቱን አደጋ በቁጥጥር ሥር ማዋል አልተቻለም፡፡ አንድ ጊዜ ፎክሮ የመጣ ይመስል የነበረውን እንዳልነበር አድርጎ አፍርሶና አወዳድሞ ከስድስት ቀን በኋላ ፀጥ ረጭ አለ፡፡
የሮም ከተማ ሕዝብ የብርቅየ ከተማውን አሳዛኝ ፍፃሜ በሐዘን ተውጦ ተመለከተው ፡፡ ከበርቴዎች ባዶ እጃቸውን አጨብጭበው ቀሩ ፡፡ ብዙ የሮሜ ሰዎች ቤት አልባ ሆኑ፡፡ የእሳት ቃጠሎው መንስዔ ምን እንደሆነ በውል ባይታወቅም የሮም ሕዝብ ግን በይሆናል ማውራት የጀመረው ወዲያውኑ ነበር ፡፡ በስፋት ይወራ የነበረው የእሳት አደጋ በተነሳበት ወቅት ኔሮን ቄሳር በቤተ መንግስቱ ሠገነት ላይ የተዋናይ ልብስ ለብሶ በገናውን እየደረደረ ሲዘፍን ታይቷል የሚለው ሲሆን በዚህም በእሳቱ ቃጠሎ የኔሮን እጅ አለበት እየተባለ ስለተወራም ምንም እንኳን ኔሮን በዚያ ምሽት ከሮም ከተማ ብዙ ርቆ በሚገኘው ባማረ ቤተ መንግስቱ የነበር ቢሆንም ይህን የሕዝቡን ሐሜት ለማስለወጥ ዘዴ ያውጠነጥን ጀመር፡፡
ኔሮን ቄሣር

የእሳቱን ቃጠሎም በሚጠላቸው ክርስቲያኖች ላይ አሳበበ አማልክቶች በክርስቲያኖች ሥራ ስላልተደሰቱ በቁጣ ሮምን ኣቃጠሏት ብሎ አስወራ፡፡ ይህንንም ለሕዝቡ እንዲሠራጭ አደረገ፡፡ በዚህ የተነሣ ብዙ ክርስቲያኖች ከያሉበት ታድነው በአሠቃቂ ሁኔታ መሥዋዕት ሆኑ ፡፡የኔሮን ቄሣር የቅርብ ባልንጀሮች የሆኑት የአልቢኖስና አግሪጳ ሚስቶች በቅዱስ ጴጥሮስ ስብከት ተማርከው ክርስቲያን ሆነው ስለነበር ባሎቻቸው በእርሱ ላይ የሸረቡበትን ሤራ ሄደው በመንገር ከሀገር እንዲወጣ ቅዱስ ጴጥሮስን ግድ አሉት፡፡ እርሱም ለክርስቶስ ታማኝ ወታደር ሆኖ በወንጌል ተጋድሎው ጸንቶ በሰማዕትነት ማለፍ እንዳለበት ቢነገራቸውም እነርሱ ግን ስለ እነርሱና ስለሌሎች ክርስቲያኖች ሲል ለጥቂት ጊዜ በሕይወት መኖሩ ለወንጌል አገልግሎት እንደሚጠቅም ገልጸውለት መሸሹ አማራጭ የሌለው መሆኑን በማሰብ ከሮም ከተማ ወጥቶ ሲሄድ በሮም መግቢያ መውጫ በር ወደ እሱ እየተራመደ የሚመጣ ሰው አየ፡፡ ያም ስው ወደ ሮም ቅጥር እየተጠጋ መጣ፡፡ ለካስ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ኑሮአል፡፡ ጴጥሮስም ደንግጦ ጌታዬ ወዴት ነው የምትሄደው? ብሎ ጠየቀው ጌታም ጴጥሮስ፣ ዳግመኛ በሮም ልሰቀል መሄዴ ነው ብሎ መለሰለት፡፡

ቅዱስ ጴጥሮስም የራእዩ ምስጢር ስለገባው ወደ ሮም ከተማ ተመልሶ ድምፁን ከፍ አድርጎ ስለተሰቀለው ጌታ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ማስተማር ጀመረ ኔሮን ቄሣርም ወደ አካይያ ዘምቶ ነበርና በዘመቻው ድል አድርጎና ደስ ብሎት ወደ ሮሜ ሲመለስ አረማውያን የሆኑ መኳንንቱን ደስ ለማሰኘትና አማልክቱን ለማክበር ሲል በቅ.ጴጥሮስና በሌሎች ክርስቲያኖች ሁሉ የሞት ፍርድ ፈረደባቸው የቅዱስ ጴጥሮስንም ሞት በመስቀል እንዲሆን አዘዘ ቅዱስ ጴጥሮስ በመስቀል ተሰቅሎ እንዲሞት መፈረዱን በሰማ ጊዜ ጌታችን፡- “በሸመገልህ ጊዜ እጆችህን ትዘረጋለህ፤ ሌላውም ያስታጥቅሃል ወደማትወደውም ይወስድሃል” ያለውን ቃል /ዮሐ.21፡18/ ትዝ አለውና “አላውቀውም ብዬ መካዴን ሳያስብብኝ በዚህ ፍጹም ይቅርታ ያደርግልኛል” በማለት እጅግ ደስ አለው፡፡ የሚሰቀልበትም ሰዓት በደረሰ ጊዜ ከኔሮን ቄሣር የታዘዙ አራት ወታደሮች ጴጥሮስን እጁን በሰንሠለት አሥረው ፍርዱ ወደሚፈፀምበት ከግዞት ቤት አውጥተው ሲወስዱት፡- “ከጌታዬ ከኢየሱስ ክርስቶስ እኩል እንዳልሆን ራሴን ወደ ታች ዘቅዝቃችሁ ስቀሉኝ” ብሎ ለመነ፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስንም እንደ ሥርዓታቸው አስቀድመው ገርፈው በኋላ ራሱን ወደ ታች እግሩን ወደ ላይ አድርገው ሰቅለው ገደሉት።እነርሱም እንደለመነው አድርገው ሰቅለው ገደሉት፡፡ የተሰቀለውም ሐምሌ አምስት ነው፡፡ ይህን ዕለት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በታላቅ የጸሎት ሥነ ሥርዓት ታከብረዋለች፡፡ ከሞተም በኋላ መርቄሎስ የሚባለው ደቀመዝሙር ከመስቀል አውርዶ እንደ ሀገሩ ልማድ ሬሳውን በወተትና በወይን አጥቦ ሽቱ ቀብቶ በነጭ ልብስ ገንዞ ማር በተመላ ሣጥን ውስጥ አግብቶ አሁን ዛሬ ቫቲካን(በሮም ከተማ ውስጥ)በሚባለው ስፍራ ቀበረውበአጠቃላይ የቅዱስ ጴጥሮስ ሕይወት ታሪክ በአጭሩ ከላይ የቀረበው ነው፡፡ ከዚህ ቅዱስ አባት ሕይወት ብዙ የምንማረው አለ፡፡ አንድ ጊዜ ባጠፋው ጥፋት ሁል ጊዜ እየተጸጸተ የጌታውን ይቅር ባይነት ተስፋ ሳይቆርጥ በመረረ አንብዓ ንስሐው ይቅርታን ስላገኘ ለዘመኑ ተነሳሕያን (ንስሐ ለሚገቡ) ጥሩ ምሳሌ ነው፡፡ መዝሙረኛው ዳዊት መተላለፉን የቀረችለት፣ ኃጢአቱ የተከደነችለት፣ በደሉን የማይቆጠርለት ሰው ምስጉን ነው እንዳለ /መዝ.31፡1-2/ እስከ ሞት ድረስ ፍቅሩን በመግለጽ ሰማዕትነትን በሮማ አደባባይ እስከተሰቀለበት ድረስ የአይሁድን ዱላ ፈርቶ በቀላሉ አላውቀውም ብሎ ለካደው አምላክ በቆራጥነትና በታማኝነት ቁልቁል እስከ መሰቀል የደረሰ ታላቅ ሐዋርያ ነው፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ
ትውልዱ እና እድገቱ
የአያቱና የቅድመ አያቱ አገር ገሊላ ነበር አባቱና እናቱ ግን የተመቸ ኑሮ ሲፈልጉ ያን ጊዜ በፍልስፍና ብሎም በንግድ ማዕከልነቷ ወደ ምትታወቀው ኪልቅያ ወደ ዋና ከተማዋ ጠርሴስ ሄዱ።የተወለደውም በጠርሴስ (አሁን በደቡብ ምስራቅ ቱርክ)ነው። ስለ ተወለደበት ጊዜ ሊቃውንት ከ7-10 ቅ.ል.ክ ይላሉ። በተወለደም በስምንተኛው ቀን እንደ ሕገ ኦሪት በቤተ-ግዝረት ሲገዘር ስሙን ሳውል(sh’aul) ብለው ሰየሙት ይኽም ከ ነገደ ብንያም በሚወለዱ እስራኤላውያን የተለመደ ስም ነው ይህም ከ ንጉሥ ሳኦል በኋላ ነው በከተማዋ እስከ አምስት መቶ ሺህ የሚገመት ከየሀገሩ የተሰባሰቡ ሕዝቦች ነበሩባት፡፡ ሮማውያን በሥራቸው ለሚተዳደሩት ሕዝቦች ሮማዊ ዜግነት ይሰጡ ስለነበር የቅዱስ ጳውሎስ አባት በዜግነት ሮማዊ ነበር፡፡ ይህም ለቅዱስ ጳውሎስ ተላልፎለታል፡፡ አባቱ የሮም ዜግነት ይኑረው እንጂ፡- ከብንያም ወገን የሆነ ፈሪሳዊ ነበረ ሐዋ ፳፫፥፮። በፊልጵስዩስ መልእክቱ፡- «በስምንተኛው ቀን የተገረዝሁ ከእስራኤል ትውልድ፥ ከብንያም ወገን፥ ከዕብራውያን ዕብራዊ ነኝ፤ ስለ ሕግ ብትጠይቁኝ ፈሪሳዊ ነበርሁ፤ በሕግ ስለሚገኝ ጽድቅ ያለ ነቀፋ ነበርሁ።» ያለው ለዚህ ነው። ፊል ፫፥፭።አይሁድ ልጆቻቸውን ሕይወታቸው ችግር ውስጥ ሲገባ እንዲጠቅማቸው ብለው እደ ጥበብ ያስተምሯቸው ነበርና እርሱም በከተማዋ ይዘወተር የነበረውን ድንኳን መስፋት በጠርሴስ ተምሯል ይህ ብቻ ሳይሆን የግሪክን የሮምን የሌሎችንም በጠርሴስ ከተም የሚኖሩትን የልዩ ልዩ የአሕዛብን ቋንቋ ተምሯል ለሐዋርያነትም በተመረጠ ጊዜ ለማስተማር የረዳውና የጠቀመው በጠርሴስ ሳለ ቋንቋቸውንና ልማዳቸውን እየተማረ ማደጉ ነው እድሜውም 15 ዓመት በሆነ ጊዜ ቅዱስ ጳውሎስ በአባቱ ፈቃድ ለትምህርት ወደ ኢየሩሳሌም ሄዶ ነበር።
በኢየሩሳሌምም ባል አግብታ ልጅ ወልዳ የምትኖር እኅት ነበረችውና ያለ ችግር በትልቁ ረቢ(መምህር) በገማልያል እግር በታች ሆኖ ይማር ነበር ሐዋ ፳፪፥፫።፡፡ በዚያም የአይሁድን ሕግና ሥርዓት እየተማረ እስከ 30 ዓመቱ ቆየ፡፡ ገማልያል ፈሪሳዊ ስለነበር ቅ.ጳውሎስ ከእርሱ በመማሩ ለሕግ ቀናተኛ ሆኖ ነበር ፡፡ በ30 ዓመቱ የአይሁድ ሸንጐ (ሳንኽርይን) አካል ሆኖ ተቆጠረ፡፡ የምሥራቅ ቤተክርስቲያን ሊቃውንት ከመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ ሲተላለፍ የኖረውን ትውፊት በማሰባሰብ ስለ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ተክለ ሰውነት እንዲህ ይላሉ፡፡
ጭንቅላቱ ትልቅ ሲሆን ራሰ በራ ነበር፡፡ የሁለቱም ቅንድቦቹ ጠጉር የተጋጠሙ፣ ዓይኖቹ ሰማያዊ ቀለም ያላቸው ሲሆኑ ዘወትር ብሩሃን ነበሩ፡፡ አፍንጫው ትልቅና ቀጥ ብሎ የወረደ ጽሕሙና ሪዙም ረጃጅም ናቸው፡፡ አንገቱ አጠር ያለ ሆኖ ትከሻው ክብና ጐባባ እግሮቹ ደግሞ ከጉልበቱ ላይ የተቃረቡ ናቸው፡፡ ቁመቱ አጠር ያለ ደንዳና ሰው (ከድንክ የረዘመ) እንደነበር ይነገርለታል።
ጳውሎስ ቅድመ ክርስትና
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሚያስተምርበት ዘመን ቅዱስ ጳውሎስ በኢየሩሳሌም ስለነበረ ሁኔታዎቹን ሁሉ ያውቃል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በአይሁድ ሸንጎ አባልነት ለሁለት ዓመታት በነበረበት ወቅት ለኦሪታዊ እምነቱ ቀናተኛ ፈሪሳዊ በመሆኑ ክርስቲያኖችን በማናቸውም አጋጣሚ ይቃወም ነበር፡፡ እንዲያውም ሊቀ-ዲያቆናት እስጢፋኖስ በማስተማሩ ምክንያት ተከሶ ለአይሁድ ሸንጎ በቀረበ ጊዜ የተከራከረው እርሱ ነበር፡፡ በድንጋይ ተወግሮ በሰማዕትነት ሲያርፍም የወጋሪዎችን ልብስ ይጠብቅ የነበረው እርሱ ነው፡፡ ወንጌላዊው ሉቃስ «ወሳውልሰ ኮነ ኅቡረ ውስተ ቀቲለ ዚአሁ»ሐዋ7፡60 እንዳለ ቅዱስ አውግስጢኖስም ‹በእስጢፋኖስ ጸሎት ቤተ ክርስቲያን የጠፋውን ጳውሎስን አገኘች፡፡› በማለት አመስጥሮ ተናግሯል፡፡
የቅዱስ ጳውሎስ መጠራት
በ32 ዓመት ዕድሜው ከኢየሩሳሌም 223 ኪ.ሜ ርቀት በስተሰሜን በኩል በምትገኘው የደማስቆ ከተማ ብዙ ክርስቲያኖች መኖራቸውን ሲሰማ በዘመኑ ሊቀ-ካህናት ወደ ነበረው ቴዎፍሎስ ቀርቦ ክርስቲያኖችን ለማጥፋት የሚያስችለውን የፈቃድ ደብዳቤ አገኘ፡፡ ከዚህ በኋላ ጭፍሮችን አስከትሎ ወደ ደማስቆ አመራ፡፡ ሐዋርያውጳውሎስ ወደ ከተማዋ ለመድረስ ጥቂት ሲቀረው ነበር ከሰማይ የወረደው ብርሃን አካባቢውን ያለበሰውና ‹ሳውል ሳውል ለምን ታሳድደኛለህ?› የሚለውን ድምፅ የሰማው፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስም ‹ጌታ ሆይ ማን ነህ?› ብሎ ጠየቀ፡፡ ‹አንተ የምትሳድደኝ እኔ የናዝሬቱ ኢየሱስ ነኝ፡፡ የመውጊያውን ብረት ብትቃወም ለአንተ ይብስበኻል› ሲል መድኃኒታችን ተናገረው፡፡ ያን ጊዜም በወደቀበት ሆኖ እየተንቀጠቀጠ ‹ጌታ ሆይ ምን አደርግ ዘንድ ትወዳለህ?› ሲል ጠየቀ፡፡ ከዚህ በኋላ ተነሥቶ ወደ ደማስቆ እንዲገባ ተነገረው፡፡ የሐዋ. 9.1፡፡ የሐዋርያው ዓይኖች ለማየት አይቻሉም፡፡ እየተመራ ወደ ደማስቆ ገባ፡፡ ለሦስት ቀናት ያህልም እህል ሳይቀምስ ቆየ፡፡ በዚያች ዕለት እግዚአብሔር አምላክ በደማስቆ ለሚገኘው እና ሐናንያ ለተባለው አባት በራእይ ተገለጠለት፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም ያለበትን አድራሻ ነገረውና ሄዶ እንዲያጠምቀው አዘዘው፡፡ ሐናንያ አስቀድሞ የቅዱስ ጳውሎስን ማንነት ያውቃል፡፡ አብዛኞቹ በደማስቆ የሚገኙት ክርስቲያኖች ከኢየሩሳሌም በስደት የመጡ ናቸው፡፡ ያን ስደት ያስነሣው ደግሞ በቅዱስ እስጢፋኖስ ላይ የደረሰው መከራ ነው፡፡ በዚህ የቅዱስ እስጢፋኖስ ሰማዕትነት ደግሞ ዋናው ተዋናይ ሐዋርያው ጳውሎስ ነበር፡፡
ይህን የሚያውቀው ሐናንያ በቅድሚያ ከእግዚአብሔር ጋር መከራከር ጀምሮ ነበር፡፡ እግዚአብሔር አያውቀው ይመስል ስለ ቅዱስ ጳውሎስ ማስረዳት ጀመረ፡፡ በመጨረሻ ግን ‹ይህ በአሕዛብም በነገሥታትም በእሥራኤልም ልጆች ፊት ስሜን ይሸከም ዘንድ ለእኔ የተመረጠ ዕቃ ነውና ሂድ፤ ስለ ስሜ ስንት መከራ ሊቀበል እንዲያስፈልገው እኔ አመለክተዋለሁና› በማለት እግዚአብሔር ሐናንያን ላከው፡፡ ይህንንም እርሱ ራሱ በሐዋ22፡12 ላይ ተናግሮታል ሐናንያ ቅዱስ ጳውሎስን ካጠመቀውና ካስተማረውም በኋላ ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ዓረብ ሀገር መሄዱን ራሱ ተናግሮአል፡፡ ገላ 1.17፡፡ ቅዱስ ጳወሎስ የተጠራው ሦስት ጊዜ ነው፡፡ የተጠራው በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም ነው፡፡ የእርሱ ጥሪ በአብ ስም የተከናወነው በእናቱ ማኅፀን ነው፡፡ ይህንንም ራሱ ቅዱስ ጳዉሎስ ሲገልጽ «ነገር ግን በእናቴ ማኅጸን ሳለሁ የለየኝ፤ በጸጋውም የጠራኝ፤ እግዚአብሔር በአሕዛብ መካከል ስለ እርሱ ወንጌልን እሰብክ ዘንድ በእኔ ልጁን በእኔ ሁኔታ ሊገልጥ በወደደ ጊዜ ወዲያው ከሥጋና ከደም ጋር አልተማከርሁም፤» በማለት ነው፡፡ በዚህም አብ እግዚአብሔር በሚለው አምላካዊ ስሙ እንዳጠራው በምስጢር እንረዳለን፡፡ /ገላ.1.15-16/ ሌላኛው ጥሪ ደግሞ በወልድ የተከናወነው ነው፡፡ አስቀድመን እንደገለጽነው እግዚአብሔር ወልድ በደማስቆ ጎዳና ላይ «ሳውል ሳውል ለምን ታሳድደኛለህ የምታሳድደኝ እኔ ኢየሱስ ነኝ» ብሎ ከገሰጸው በኋላ ወደ ካህኑ ሐናንያ በላከው ወቅት ነው፡፡
በዚህ ወቅትም ጌታ ቅዱስ ጳዉሎስን ለምን እንደመረጠው ለካህኑ ሐናንያም ሲያስረዳ «ይህ በአሕዛብምበነገሥታትም በእስራኤልም ልጆች ፊት ስሜን ይሸከም ዘንድ ለእኔ የተመረጠ ዕቃነውና፤»በማለት ነው፡፡/የሐዋ.9.15/
ቅዱስ ጳዉሎስ ከአብና ከወልድ ባሻገር በመንፈስ ቅዱስም ለአገልግሎት የተመረጠ ነው፡፡ ይህም የሆነው መንፈስ ቅዱስ ለአባቶቻችን «በርናባስንና ሳዉልን ለጠራኋቸው ሥራ ለዩልኝ» /ሐዋ.13.21/ ባለበት ወቅት እና እንዲሁም
«በዚያን ጊዜም ከጦሙ፤ ከጸለዩም፤ እጃቸውንም ከጫኑ በኋላ አሰናበቱአቸው፡፡ እነርሱም በመንፈስ ቅዱስ ተልከውወደ ሰሌውቅያ ወረዱ፤» በሚለው አምላካዊ ቃል መሠረት ነው፡፡ /የሐዋ.13.3-4/ በመሆኑም የቅዱስ ጳዉሎስመጠራት ከጥሪነት ባሻገር ምሥጢረ ሥላሴ የተገለጠበት ነው፡፡ በእርሱ መመረጥ ውስጥ የቅድስት ሥላሴ ልዩ አንድነትና ሦስትነት ተገልጧል፤ /ተመስክሯል/፡
፡

የቅዱስ ጳውሎስ ወደ ክርስትና መመለስ
ለ3 ዓመታት በዓረቢያ በረሃ ከቆየ በኋላ ወደ ደማስቆ ከተማ ተመለሰ፡፡ በዚያም በነበሩ አይሁድ መካከል በፊት ያሳድደው የነበረውነን ኢየሱስ ክርስቶስን መስበክ ጀመረ፡፡ ከዚያ በፊት በፈሪሳዊነቱ ለአይሁድ ሕግ በነበረው ቅንዓት የሚታወቀው ጳውሎስ ዛሬ ወንጌል ሲሰብክ በማየታቸው አይሁድ ተነሡበት፡፡ በዚህም የተነሣ የደማስቆ ክርስቲያኖች በቅርጫት አውርደው ወደ ኢየሩሳሌም ላኩት፡፡ቅዱስ ጳውሎስ ኢየሩሳሌም ሲደርስ የገጠመው ሁለት ችግር ነበር፡፡
1- አይሁድ ጳውሎስን እንደሚያውቁት እና እንደለመዱት ሆኖ ስላላገኙት ሊገድሉት ተነሡ፡፡
2- ክርስቲያኖች የቅዱስ ጳውሎስን መመለስ ሊያምኑ አልቻሉም፡፡ በመጨረሻ ግን በርናባስ ወደ ሐዋርያት ዘንድ ወስዶ
የጳውሎስን መመለስ በመተረክ እንዲያምኑት አደረጋቸው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎሰ በኢየሩሳሌም በድፍረት በማስተማሩ አይሁድ ስለተቃወሙት ከተማዋን ትቶ በቂሳርያ በኩል ወደ ትውልድ ሀገሩ ጠርሴስ ተመለሰ፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በጠርሴስ ከተማ ለዘጠኝ ዓመታት ቆይቷል፡፡ ከኢየሩሳሌም ውጭ የአሕዛብ ከተማ በነበረችው በአንጾኪያ የክርስትና ሃይማኖት ተስፋፋ፡፡ ከኢየሩሳሌም የተሰደዱት ክርስቲያኖች የአንጾኪያን ሕዝብ ተግተው በማስተማራቸው ዝናው እስከ ኢየሩሳሌም ደረሰ፡፡ በዚህም ምክንያት በኢየሩሳሌም የነበሩት ሐዋርያት በርናባስን ወደ አንጾኪያ ላኩት፡፡ በርናባስ የግሪክ ቋንቋ ችሎታ ያለውን፣ ከማንኛውም ሰው ጋር መግባባት የሚችለውን፣ ደግሞም እግዚአብሔር ለአሕዛብ ሐዋርያ እንዲሆን የመረጠውን ቅዱስ ጳውሎስን ከጠርሴስ በማምጣት በአንጾኪያ ሥራቸውን ጀመሩ፡፡
በገላትያ መልእክቱ ምዕራፍ 2 ላይ ራሱ እንደገለጠው ከአሥራ አራት ዓመት በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ከአንጾኪያ ክርስቲያኖች የሰበሰበውን ርዳታ ይዞ ወጣ፡፡ በዚህም በአይሁድ በአሕዛብ መካከል የነበረውን መለያየት ክርስትና አንድ እንዳደረገው አስመስክሮአል፡፡
የቅዱስ ጳውሎስ ሐዋርያዊ ሥራ

የመጀመሪያው የቅዱስ ጳውሎስ ጉዞ
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ከኢየሩሳሌም ወደ አንጾኪያ ከተመለሰ በኋላ በልዑል እግዚአብሔር ጥሪ (የሐዋ. 13.1-3) በአሕዛብ ሀገር ወንጌልን ለመስበክ ከበርናባስ ጋር ወጡ፡፡ በዚህ ጉዞቸው በጠቅላላ ወደ 2000 ኪ.ሜ የሚደርስ መንገድ በእግር ተጉዟል፡፡ ይህም ጉዞ የተከናወነው በ46 ዓ.ም አካባቢ ነው፡፡ የተሸፈኑትም ሀገሮች ሲሊንውቂያ፣ ቆጵሮስ፣ ስልማና፣ ጳፋ፣ ጰርጌን፣ ገላትያ፣ ጵስድያ፣ ኢቆንዮን፣ ሊቃኦንያ፣ ልስጥራ፣ ደርቤን፣ ጵንፍልያ፣ አታልያ እና አንጾኪያ ናቸው፡፡
ሁለተኛ የሐዋርያው የቅዱስ ጳውሎስ ጉዞ
ሁለተኛው ጉዞ የተከናወው በ50 ዓ.ም ገደማ ነው፡፡ በመጀመሪያው ጉዞ ማርቆስ አብሮ ተጉዞ ነበር፡፡ ነገር ግን ጵንፍልያ ከተማ ሲደርስ እናቱ ስለናፈቀችው መመለስ በመፈለጉ በርናባስ ወደ ኢየሩሳሌም ይዞት መጣ፡፡ ስለዚህም በሁለተኛው ጉዞው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ሲላስን ይዞ ወደ ኪልቋያ ሶርያ ሲጓዝ በርናባስ ደግሞ ማርቆስን አስከትሎ ወደ ቆጵሮስ ሄደ፡፡ በዚህ ጉዞው ቅዱስ ጳውሎስ እስከ ግሪክ ደርሶአል፡፡ የተጓዘባቸውና ያስተማረባቸው ከተሞችም፡- ደርብያ፣ ልስጥራ፣ ፍርግያ፣ ገላትያ፣ ሚስያ፣ ጢሮአዳ፣ ሳሞትራቄ፣ ናፒሊ፣ ፊልጵስዩስ፣ ተሰሎንቄ፣ በርያ፣ አቴና፣ ቆሮን፣ ቶስ፣ አንክራኦስ፣ ኤፌሶን፣ ቂሳርያ፣ ኢየሩሳሌም እና አንጾኪያ ናቸው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የመንፈስ ልጁ ጢሞቴዎስን ያገኘው በዚሁ ጉዞው በልስጥራ ከተማ ነው፡፡
ሦስተኛው የቅዱስ ጳውሎስ ጉዞ
ይህ ጉዞ የተከናወነው በ54 ዓ.ም ሲሆን የተሸፈኑትም ሀገሮች የሚከተሉት ናቸው፡፡ ገላትያ፣ ፍርግያ፣ ኤፌሶን፣ መቄዶንያ፣ ፊልጵስዩስ፣ ቆሮንቶስ፣ ጢሮአዳ፣ አሶን፣ ሚሊጢኒን፣ አንጠቀከስዩ፣ ትሮጊሊዩም፣ መስጡ፣ ቆስ፣ ሩድ፣ ጳጥራ፣ ጢሮስ፣ ጵቶልማይስ፣ ቂሳርያ፣ ኢየሩሳሌም፡፡ ክርስቲያኖች የሰበሰበውን ዕርዳታ ለኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያኖች በመያዝ ሦስተኛውን ጉዞ አጠናቅቆ ኢየሩሳሌም ገባ፡፡ ነገር ግን ኢየሩሳሌም የገባበት ጊዜ የፋሲካ በዓል ስለነበር ከልዩ ልዩ ሀገሮች የተሰበሰቡ አይሁድ በከተማዋ ነበሩ፡፡ እነዚህ በዝርወት የሚኖሩ አይሁድ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስን በየሀገራቸው በትምህርቱ የተነሣ ሲቃወሙት የነበሩ ናቸው፡፡ እኒህ አይሁድ ቅዱስ ጳውሎስን በኢየሩሳሌም ሲያዩት ታላቅ ተቃውሞ አነሡበት፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ተቃውሞአቸውን ለመግታት እንደ አይሁድ ሕግ በቤተ መቅደስ የመንጻት ሥርዓት መፈጸም ጀመረ፡፡ ነገር ግን ከኤፌሶን የተከተለውን ጥሮፊሞስን ወደ መቅደስ ያስገባው ስለመሰላቸው ተቃውሞአቸው በረታ፡፡ የሐዋ. 22.29፡፡ ከተማውንም አወኩት፤ ይህ ነበር ቅዱስ ጳውሎስን በ58 ዓ.ም ለሮም እሥር የዳረገው፡፡ከብዙ መከራና ስቃይ በኋላ ታሥሮ ሮም ገባ፡፡ በዚያም በቁም እሥር ሆኖ ለሁለት ዓመታት ያህል ወንጌል ሰበከ፡፡ የሁለቱን ዓመት የቁም እሥር እንደጨረሰ ወደ ኔሮን ፍርድ ቤት ቀረበ፡፡ ይህም በ60ዎቹ ዓ.ም ነው፡፡ በፍርድ ቤቱ በተደረገው ምርመራ የሮሜን ሕግ የሚቃወም ምንም ወንጀል ስላልተገኘበት በነፃ ተለቀቀ
አራተኛው የቅዱስ ጳውሎስ ጉዞ
ከዚህ በኋላ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ አራተኛውንና የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ያልመዘገበውን ጉዞውን ያደረገው፡፡ ይህ ጉዞው በመታሠሩ አዝነው ተክዘው የነበሩ ክርስቲያኖችን ለማጽናናት የጀመራቸውን ሥራዎች ፍጻሜ ለማየት የተደረገ ጉዞ ነው፡፡ በዚህም ጉዞው ኢየሩሳሌምን፣ ኤፌሶንን፣ ሎዶቅያን፣ መቄዶንያን፣ ቀርጤስን፣ ጢሮአዳን፣ ድልማጥያን፣ እልዋሪቆን፣ ኒቆጵልዮን፣ ብረንዲስን፣ ጐብኝቷል፡፡ በዚህ የመጨረሻ የስብከት ጉዞው ለአራት ዓመታት ያህል ቆይቷል፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ የመጀመሪያው ስነ መለኮትንና ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን አምልቶ አስፍቶ የጻፈ በትምህርቱ እጅግ ተጽእኖ ማሳደር የቻለ የቤተክርስቲያን ታላቅ መምህር ነው እርሱ የክርስቶስ ቤተክስርቲያን የአሕዛብ ሐዋርያ ነው። ግብረ ሐዋርያት የሚጀምረው በቅዱስ ጴጥሮስ ሥራ ሲሆን የምዕራፉም መጨረሻ የሚጠናቀቀውበቅዱስ ጳዉሎስ አገልግሎት ነው፡፡ በዚህ መሠረት ቅዱስ ጴጥሮስ አይሁድን /የተገረዙትን/ በአባትነት እንዲጠብቅ ሲሾም በተመሳሳይ መልኩ ደግሞ ቅዱስ ጳዉሎስ አሕዛብን /ያልተገረዙትን/ እንዲጠብቅና እንዲያስተምር ተሹሞ ነበር፡፡ ስለዚህም ነገር ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለገላትያ ሰዎች በጻፈው መልእክቱ «… ጴጥሮስ ለተገረዙት የሆነው ወንጌል አደራ እንደተሰጠው እንዲሁ ለእኔ ላልተገረዙት የሆነው ወንጌል አደራ እንደተሰጠኝ እዩ፤ ለተገረዙት ሐዋርያ እንድሆን ለጴጥሮስ የሠራለት ለእኔ ደግሞ ለአሕዛብ ሐዋርያ እንድሆን ሠርቶአልና፡፡» በማለት ነው የገለጸው፡፡/የሐዋ.2.7-9/
ሰማዕትነት
ቅዱስ ጳውሎስ ና ኔሮን ቄሳር በ ማናቸውም ነገር የማይስማሙ አጥፊና ጠፊ ነበሩ ኔሮን ቄሣር ክፉና አመጸኛ ነበር ቅ/ጳውሎስ ግን ደግና ፈቃደኛ ነበር ኔሮን ቄሳር ከኀዲና ጨለማ በቃኝ የማይል ንፉግ የሠይጣን ማደርያ ነበር ቅ.ጳውሎስ ግን ሃይማኖታዊና ብርሃን ፣ በቃኝ የሚል ቸር የመንፈስቅዱስ ማደርያ ነበር በመጨረሻ በ64 ዓ.ም ኔሮን በጥጋቡ የሮማ ከተማ ስትቃጠል ምን እንደምትመስል ማየት እፈልጋለሁ ብሎ አቃጠላት፡፡ የሮም ሕዝብ በከተማው መቃጠል በማዘኑና በማመፁ ነገሩን ሁሉ በክርስቲያኖች ላይ አሳበበ፡፡ በዚህም የተነሣ ክርስቲያን የተባለ ሁሉ መሰደድ፣ መሠየፍ፣ መታረድ፣ ዕጣ ፈንታው ሆነ፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም በኒቆጵልዮን ከተማ ሲያስተምር በ65 ዓ.ም ተይዞ ወደ ወኅኒ ገባ፡፡ ለሁለት ዓመት ከስድስት ወር በጨለማ ቤት ታሥሮ ቆየ ቅዱስ ጳውሎስ በኔሮን ቄሳር ፊት በቀረበ ጊዜ በቀኝ እጁ ከሰንሰለቱ ጋር መስቀሉን ይዞ ሳይፈራ የክርስቶስን ነገር መሰከረ ኔሮን ቄሳርም በቁጣ ቃል ይሙት በቃ ፈረደበት ለልማዱ ሮማውያን በወንጀለኛ የሞት ፍርድ ሲፈርዱ የተፈረደበት ሰው የውጭ ሀገር ዜጋ የሆነ እንደሆነ አስቀድሞ በግርፋትና በሌላም በልዩ ልዩ ሥቃይ ካሠቃዩት በኋላ በመስቀል ወይም በሰይፍ ይገድሉት ነበር
ቅዱስ ጳውሎስ ግን በጠርሴስ ተወላጅነቱ የሮማውያን ዜጋ ስለሆነ ሥቃዩ ቀርቶለት ባንድ ሥቃይ ብቻ በሠይፍ እንዲሞት ተፈረደበት ወደ መሞቻው ስፍራ ሲወስዱት በንግግሩና በአስተዬቱ ሁሉ ምንም ፍርሃት አልነበረበትም እንዲያውም በጦርነት ላይ ድል አድርጎ ገድሎና ማርኮ እየፎከረ በደስታ ወደ ቤቱ የሚመለስ ወታደር ይመስል ነበር፡፡ በመጨረሻም በ74 ዓመት ዕድሜው በሮማ ከተማ በኦስትያ መንገድ አንገቱን ተሠይፎ በ67 ዓ.ም ሐምሌ አምስት ቀን በሰማዕትነት ዐረፈ፡፡
በአጠቃላይ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ :-ፀባዩ ቅዱስ ጳውሎስ ለእውነት ነገር ይሉኝታና ፍርሃት የሌለበት ደፋር ነበር (ሮሜ1፡16) ለ ጊዜውም በሚሆነው ንቁ ወደፊትም በሚሆነው አሳቢና ጠርጣሪ ነበር (ሐዋ27፡30) በድንገተኛ ነገር ምላሽ ለመስጠት የሚችል ና ንግግር አሳማሪ ነበር(ሐዋ26፡1-7) መጻሕፍትንም ለማንበብና ለመተርጎም መልዕክትን ለመጻፍና የሰውን ልብ በፍቅር ለመሳብ ሁሉንም ለመምሰልና ደስ ለማሰኘት ከመንፈስ ቅዱስ ሥጦታ ነበረው
የስሙ ትርጓሜ
ቅዱስ ጳውሎስ የስሙ ትርጓሜ ብርሃን ማለት ነው፥ ሰርግዮስ ጳውሎስ የተባለ ሀገረ ገዥ የገዛ ስሙን ሰጥቶት ነው፥ የቀደመ ስሙ ሳውል ነበር። ይህ ሀገረ ገዥ አስተዋይ ሰው ስለነበር፡- የእግዚአብሔርን ቃል ሊሰማ ወድዶ፥ በርናባስንና ሳውልን ወደ እርሱ አስጠራቸው። ኤልማስ የተባለው ጠንቋይ ግን አገረ ገዥውን ከማመን ለማጣመም ፈልጐ ተቃወማቸው። ሳውል ግን መንፈስ ቅዱስ ባደረበት ሰውነት ሆኖ ትኩር ብሎ በመመልከት ጋኔኑን ነሠጸው አይኑንም አሳወረው በዚያን ጊዜ አገረ ገዥው የተደረገውን ባየ ጊዜ ከጌታ ትምህርት የተነሣ ተገርሞ አመነ። የጠንቋዩን ዓይነ ሥጋ በተአምራት ሲያጠፋበት፥ የእርሱን ደግሞ ዓይነ ኅሊናውን ሲያበራለት አይቶ ጳውሎስ (ብርሃን) የሚለው ስም ለአንተ ይገባሃል አለው። የሐዋ ፲፫፥፮።ጳውሎስ ማለት ንዋይ ኅሩይ (ምርጥ ዕቃ) ማለትም ነው። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ጳውሎስ ለሐናንያ በመሰከረለት ጊዜ፡- «ይህ በአሕዛብም፥ በነገሥታትም፥ በእስራኤልም ልጆች ፊት ስሜን ይሸከም ዘንድ ለእኔ የተመረጠ ዕቃ ነውና ሂድ፤» ብሎታል። የሐዋ ፱፥፲፭። ምርጥ ዕቃ የተባለው መዶሻ ነው። እርሱም ሰባት የማዕድን አይነቶችን ቀጥቅጦ አንድ የሚያደርግ ነው፤ ቅዱስ ጳውሎስም እግዚአብሔርን እና ሰውን፥ሰውን እና መላእክትን፥ ሕዝብን እና አሕዛብን፥ ነፍስን እና ሥጋን አስታርቆ አንድ ያደርጋል። አንድም ምርጥ ዕቃ የተባሉ ወርቅና ብር ናቸው። ወርቅና ብር ለንዋያት ሁሉ ጌጥ እንደሆኑ፡- እርሱም የቤተ ክርስቲያን ጌጥ ነው።
አንድም፡- ጳውሎስ ማለት፡- አመስጋኝ፥ ደስታ፥ ምዑዝ ነገር የሚናገር፥ ልሳነ ክርስቶስ፥ ሰላም፥ ፍቅር ማለት ነው።ዕውቀትን ከትህትና ደርቦ የያዘ ነበር፡- ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በኢየሩሳሌም በሚገኘው በታላቁ የአይሁድ ትምህርት ቤት በሊቁ በገማልያል እግር ሥር ብሉይ ኪዳንን የተማረ ነበር፡፡ በኋላም ትምህርተ ክርስትናን ከሐዋርያት አግኝቷል፡፡ ይህን ሁሉ ዕውቀት ይዞ ሁል ጊዜ ኑሮው የትህትና ነበር፡፡ እኔ ጭንጋፍ ነኝ እስከማለትም ደርሶ ነበር፡፡ (1ቆሮ. 15.8)ትጉህና ታታሪ ነበረ፡- ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስለ42 ዓመታት ያህል በሐዋርያነት አገልግሎአል፡፡ እስከ እስጳኝ ድረስ ሄዶም አስተምሯል፡፡ በባሕር እና በእግር፣ ተመላልሷል፡፡ በ12ቱም ሐዋርያት ሀገረ ስብከት እየገባ ወንድሞቹን አግዞአቸዋል፡፡
ትዕሥተኛ ነበረ፡- ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች በላከው ቀዳማዊ መልእክቱ እንደገለጠው (11.25-33) ብዙ ፈተናዎችን አልፏል፡፡ ሁለት ጊዜ ታሥሯል ተደብድቧል፣ በረሃብ ተገርፏል ይህ ሁሉ ቢሆንም በኑሮው ደስተኛ ነበር፡፡ በሮሜ ታሥሮ እያለ ለፊልጵስዩስ ሰዎች መልእክት ስጽፍ በደስታ የተሞላ ነበረ፡፡ በመጀመሪያ ጉዞው ያልተቀበሉትን ከተሞች በሁለተኛው አልያም በሦስተኛ ጉዞው ጎብኛቸው እንጂ እምቢ አሉኝ ብሎ ተስፋ አልቆረጠም፡፡ ጥበበኛ ነበረ፡- ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስን የቤተ ክርስቲያን አበው (መዶሻ) ይሉታል፡፡ መዶሻ ማዕድናቱን ቀጥቅጦ አንደ ያደርጋቸዋል፤ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም በትምህርቱ ሕዝብንና አሕዛብን አንድ ያደረገ ሐዋርያ ነው፡፡
በ50 ዓ.ም አካባቢ ወደ ኢየሩሳሌም ሲወጣ ቲቶንና በርናባስን አስከትሎ ነበር፡፡ ቲቶን ከአሕዛብ ወገን በርናባስን ደግሞ ከአይሁድ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ሰውን እንዴት መቅረብ እንደሚቻል የሚያውቅ ሰው ነበረ፡- ከተራ ሰዎች እስከ ነገሥታት ቤተሰቦች በፍቅር እየሳበ ክርስቲያን አድርጓቸዋል፡፡ በመልእክቱ መጨረሻ የቤተክርስቲያን ልጆች በስማቸው እየጠራ ሰላምታ ማቅረብ የዘወትር ልማዱ ነበረ፡፡ ይህም ሁሉም በልቡ እንደታተሙ ያውቁ ዘንድ ነው፡፡
ጸሐፊ ነበር፡- ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በቃል ያለ ይረሳል በጽሑፍ ያለ ይወረሳል ነውና ያስተማራቸውን ክርስቲያኖች እንዲሁ አይተዋቸውም፡፡ ለሃይማኖታቸው ማጽኛ ለመንፈሳዊ ሕይወታቸው መመሪያ የሚሆኑ መልእክታትን ጽፎላቸዋል፡፡ አብዛኛዎቹ መልእክታት በእሥር ቤት ውስጥ ነው፡፡ ለመጓዝ የሚያስችለው አመቺ ጊዜ ሲያገኝ በአካል፣ በቃል፣ ያስተምራቸዋል፡፡ ሲታሠር መንቀሳቀስ ሲከለከል ደግሞ ጣቶቹ ብዕር ይጨብጣሉ፡፡ መልእክቶቹ በየሀገረ ስብከቱ ይላካሉ፡፡
ሥራ ወዳድ ነበር፡- ቅዱስ ጳውሎስ ሌት ተቀን ለስብከተ ወንጌል ቢባክንም ለምእመናን እንዳይከብድባቸው ድንኳን እየሰፋ የዕለት ጉርሱን የዓመት ልብሱን ያገኝ ነበር፡፡ የሐዋ. 18.3፣4 ለዚህም ነው ‹ሊሠራ የማይወድ ቢኖር አይብላ› እያለ ያስተምር የነበረው፡፡ 2ተሰ.3.10፡፡

ሐዋርያው ጳውሎስ በዘመናት ውስጥ
33 ዓ.ም ለሐዋርያነት ተጠራ:: ወደ ዓረብ ምድር ሄደ በዚያም ፫ ዓመት ቆየ
35 ዓ.ም ወደ ኢየሩሳሌም ለአጭር ጉብኝት ሄደ
35-45 ዓ.ም ኪልቅያ ሶርያ አንጾኪያ
46 ዓ.ም ከአዕማድ መሪዎች ጋር በኢየሩሳሌም መገናኘቱ (ገላ 2:1-10) ከአንጾኪያ ይዞት የሄደውን እርዳታ ለኢየሩሳሌም ቅዱሳን ማድረሱ (ሐዋ 11:27-30)
47-48ዓ.ም ጳውሎስ እና በርናባስ የመጀመሪያውን ሐዋርያዊ ጉዞ ማድረጋቸው (ሐዋ 13:4-14:28)
48/49ዓ.ም የሐዋርያት ጉባኤና ውሳኔ (ሐዋ 15፡1-20)
49-51/52 ዓ.ም ጳውሎስና ሲላስ በመቄዶንያና በአካይያ:: የፊልጵስዩስ በተሰሎንቄ በቤሪያ እና በቆሮንቶስ
አብያተ ክርስቲያናት ተመሠረቱ፡፡ (ሐዋ 16:9-18:18)
51/52 ዓ.ም ጳውሎስ በኢየሩሳሌም አስቸኳይ ጉብኝት አደረገ
52-55 ዓ.ም ጳውሎስ በኤፌሶን (ሐዋ 19:1-20:1)
55-57 ዓ.ም ጳውሎስ በመቄዶንያ በእልዋሪቆን እና በቆሮንቶስ
57 ዓ.ም ጳውሎስ ለመጨረሻ ጊዜ ኢየሩሳሌምን መጎብኘቱ:: መያዙ እና መታሠሩ::
57-59ዓ.ም በቂሳርያ መታሠሩ (ሐዋ23:35-26:32)
59-60ዓ.ም ወደ ኢጣሊያ ጉዞ
60-62ዓ.ም በቁም እስር በሮም መቀመጡ
62 ዓ.ም ጳውሎስ በቄሳር ፊት
64 ዓ.ም የሮም መቃጠል
65ዓ.ም ቅዱስ ጳውሎስ በቄሳር ወታደሮች ተያዘ
65-66ዓ.ም በሮም እስር ቤት ቆየ
67 ዓ.ም በኔሮን ቄሳር ትዕዛዝ በሰማዕትነት አረፈ

የአባታቶቻችን የቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ጳውሎስ ጸሎትና በረከት በሁላችን ይደርብን አሜን
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
No comments:
Post a Comment