እግዚአብሔር የጽዮንን ምርኮ በመለሰ ጊዜ እንደ ተጽናና ሰው ሆንን በዚያን ጊዜ አፋችን ደስታን አንደበታችን ሐሴትን መላ በዚያን ጊዜም በአህዛብ ዘንድ እግዚአብሔር ታለቅ ነገር አደረገላቸው ተባለ
መዝሙረኛው ዳዊት እግዚአብሔር ከባቢሎን ምርኮ በመለሳቸው ጊዜ የሚዘምሩትን ዝማሬ አስቀድሞ በዚህ መዝሙሩ ነገረን ዕዝራ እና ነህምያ 70 ዓመት በምርኮ የነበረውን ህዝብ ከንጉሡ ዘሩባቤል ጋር ይዘው በተመለሱ ጊዜ ኢየሩሳሌም ጽዮን ምርኮዎን ሰበሰበች ተባለ ኢየሩሳሌምን በመምጣታቸው ሞልተዋታልና እኛም በዚህ በትንሣኤው ወቅት ሰማያዊቷ ኢየሩሳሌም መንግሥተ ሰማያት በክርስቶስ ደም ከሲኦል የወጡትን ነፍሳት እያሰብን ፍጹም ደስታን እናድርግ
ይህንን የመዝሙረኛውን የዳዊት ቃል በቤተክርስቲያን በእሁድ ሌሊት የሰዓታት ጸሎት ላይ ከወንጌል በፊት የምንሰማው ምስባክ ነው እሁድ ሰንበት ትንሣኤአችን የተደረገበት ቀን ነውና እሁድ ሰንበት የጌታን መምጣት የዚህ ዓለምን ማለፍ የመንግሥተ ሰማያትን ህይወት የምናስብበት ዕለት ነውና
ትንሣኤው በተደረገበት በዚህ ዕለት አፋችን በደስታ የተመላ ነው በአፉ ምግብ የያዘ ሰው ይናገር ዘንድ እንዳይቻለው እኛም በአፋችን ሌላ ነገር የምናወራበት አይደለም አንደበታችን ሁሉ የእርሱን ድንቅ ሥራ በማሰብ እና እንደ መላዕክት በመዘመር እናሳልፈዋለን እንጂ ዕዝራ እና ነህምያ ሲጠባበቁት የነበረው ሚጠት(መመለስ) በተደረገላቸው ጊዜ ያደረጉትን ደስታ እናስብ ነህ8፤10-17፣ነህ12፤43
እኛ ደግሞ ይልቅ ደስታን እናደርግ ዘንድ ይገበል እነርሱ ከምድራዊቷ ባቢሎን ከ70 ዓመት ምርኮ ተመለሱ እኛ ከሲዖል ከ5500 ዓመት ግዞት በኋላ ተመለስን እነርሱ ይገዛቸው ከነበረ ከአህዛብ ንጉሥ ወደ ነፃነት ተመለሱ እኛ ነፍሳትን ሁሉ ቀጥቅጦ ይገዛ ከነበረ ከሰይጣን(ዲያቢሎስ) ነጻ ወጣን እነርሱ ከባቢሎን ምርኮ ለጊዜው ወጡ እንጂ የሮማውያን ምርኮ አልቀረላቸውም እኛ ግን ካገኙ ማጣት ወደሌለባት ሰማያዊት መንግሥቱ ለዕረፍት ገባን
እንግዲህ በክርስቶስ የማዳን ሥራ ወደ ዘላለማዊ መንግሥቱ እንደ ገባን የምናምን ከሆነ የባቢሎንን(የዚህ ዓለምን) ፍለጋ እንተው ባቢሎን ማለት ድብልቅልቅ እንደሆነ ይህ ዓለምም ዮሐንስ በራዕዩ እንደተናገረ ድብልቅልቅ ነው ራዕ18 ዳግመኛም የዚህን የተደባለቀ ዓለም ነገር በማሰብ ሠውነታችንን አናድክማት ምድር ሁሉ ታጥባ ፋሲካ በምታደርግበት ቀን ከበጉ ሰርግ በአፍኣ አንሁን
ይህ የተደረገልን ቀን ዳዊት እንዳለ በአህዛብም ዘንድ እግዚአብሔር ታላቅ ነገር አደረገላቸው እንደተባለ ታላቅ ነው
የአምላክ ሰው መሆን አስደንቆን ሳናበቃ ለፍጥረቱ ሁሉ በሥጋ መሞቱን እናስባለን እንዲህ ያለ ነገር የተሰማበት ጊዜም የለምና የአምላክ ትህትናው ዕፁብ ድንቅ ና ሰውን የወደደበት ፍቅሩ የማይመረመር ነው በኪዳን ፀሎት ላይ እንደምንሠማው ‹‹ ነፍሳት ያመጡትን የጎርፉን ፈሳሽነት ከእኛ ጸጥ ያደረክልን ከጥፈት አድነህ የሕይወት ወደብ የሆንከን አንደምንለው በእርሱ ፈቃድ በአባቱም ፈቃድ በመንፈስቅዱስም ፈቃድ መጥቶ አድኖናል ይህ ታላቅ ነገር ነው ይህም የታወቀ የተረዳ ይሆን ዘንድ ቤተክርስቲያን ትንሣኤን ከሌሎች በዓላት ሁሉ አብልጣ ታከብራለች
ይህ ታላቅ ነገር በመጽሐፍት ሁሉ የተገለጠ ነው ኢሳይያስም ይህንን ሁሉ ተመልክቶ ‹‹ ሲዖል በመምጣትህ ታወከች አለ›› ኢሳ14፤9 አለ ሶዖል ታወከች ምክንያቱም መሳለቂያ ሆናለችና ሶዖል ተናደደች
ምክንያቱም ድል ተነሠታለችና አሁን ምርኮኛ ሆናለችና ሶዖል እርሱንም አስገባችው(እንደ ሌሎች ሙታን ሁሉ መስሏት) ነገር ግን ይደንቃል ከመንግሥተ ሰማያት ጋር ተገናኘች የሚታየውን ያዘችው በማይታየውን መለኮታዊ ሥልጣኑ ድል ተነሳች ባዶም አደረጋት
እንግዲህ ከፊታችን ያሉትን 50 የበዓል ቀናት እንደ ክርስቲያን ሆነን እናክብር ቀናቶቹ የትንሣኤውን ኃይል ና የመንግሥተ ሰማያትን ህይወት እንድናጣጥም የተሰሩ ናቸውና(ፊልጵ3፤10-11) ፍፁም ደስታን በማድረግ በመዘመርም እናክብራቸው እንደ አህዛብ በምግብና በመጠጥ ብቻ በዓልን አናክብር ለዚህ ዓለም ብቻ በሚሆኑ ደስታዎች ሠውነታችንን አናድክማት ለእርሱ ትዘምር ዘንድ እናሰልጥናት እንጂ በቤተመቅደሱ ተገኝተን እንደ ሃዋሪያቱ የትንሣኤው ምስክር እንሁን እንጂ ክርስቶስ ከሙታን ተነሣ ሞትን አጠፋው በመቃብርም የለም ህይወትንና ዘላለማዊ ዕፈርትን ሠጠን እንበል
ይህ ከሆነ ከዳዊት ጋር አፋችን ደስታን መላ ማለት እንችላልን እንደ ተጽናኑትም እንደ መላዕክት ሆንን እንበል እግዚአብሔር ታላቅ ነገር አደረገልን ደስም አለን እንበል በህሊናችን እንደ ዮሐንስና ጴጥሮስ ወደ መቃብሩ ለመገሥገሥ እንሽቀዳደም ትንሣኤውንም ፈጥና እንዳመነች እንደ ማርያም መግደላዊት እንሁን እንጂ ወደ ኤማሁስ እንደ ተጓዙት መንገደኞች ማንም ከእኛ ውስጥ ተስፋ በመቁረጥ ውስጥ አይሁን እርስ በእርሳቸን ምርኮኞች እኛን ነጻ ስላወጣን በትንሣኤው ሰላምታ ክርስቶስ በታላቅ ኃይልና ሥልጣን ከሙታን ተነሣ ሰይጣንን አሠረው አዳምንም ነፃ አወጣው ሰላም ከእንግዲህም ደስታና ሰላም ተደረገ እንበል
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን
ዲ/ን ፍሬው ለማ