በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
በዲ/ን ያሬድ መለሰ
ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ ተነሣ ይህ የክርስትና እምነት አዋጅ ነው፡፡ ይህ አዋጅ ለቤተክርስቲያን ስብከት ሥርዓተ አምልኮና መንፈሳዊ ሕይወት ልብ ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለ ‹‹ ክርስቶስ ካልተነሣ ስብከታችን ከንቱ እምነታችንም ደግሞ ከንቱ ነው፡፡›› 1ኛ ቆሮ 15፥14 ለዚህም ነው የክርስቶስ ትንሣኤ ለቤተ ክርስቲያን ሕልውናዋ ነው የምንለው፡፡የቅዱሳን ሐዋርያት የመጀመርያው ስብከት ትንሣኤ ክርስቶስን በመስበክ የተጀመረ ነው፡፡ ይኸውም የቅዱስ ጴጥሮስ ስብከት ነው፡፡ እንዲህ እያለ መንግስቱን ወንጌል ሰበከላቸው፡፡ ‹‹ የእስራኤል ልጆች ሆይ ይህንን ቃል ስሙ ራሳችሁን እንደምታውቁ የናዝሬቱ ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር በእርሱ በኩል ባደረገው በተአምራትና በድንቆች በምልክቶችም ከእርሱ ዘንድ ለእናንተ የተሰጠ ሰው ነበር፡፡ እርሱንም በእግዚአብሔር ዘንድ በተወሰነው ሐሳቡና በቀድሞው እውቀቱ ተሰጥቶ በአመጸኞች እጅ ሰቅላችሁ ገደላችሁት፡፡ እግዚአብሔር ግን የሞትን ጦር አጥፍቶ አስነሣው ሞት ይይዘው ዘንድ አይችልምና፡፡››(ሐዋ 2፥22-24) ቅዱስ ጴጥሮስ ለተሰበሰቡት አይሁድ እግዚአብሔር አስነሳው አለ እንጂ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወቱን ለመስጠት ደግሞም ዳግመኛ ለማስነሳት ኃይል የለውም ለማለት አይደለም፡፡ በመዋዕለ ሥጋዌው እንዳስተማረ ‹‹ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት በሦስተኛውም ቀን አስነሣዋለሁ›› ዳግመኛም እንዲህ አለ ‹‹ መልካም እረኛ እኔ ነኝ መልካም እረኛ ነፍሱን ስለበጎቹ ያኖራል፡፡›› (ዮሐ 10፥12) ካለ በኋላ እንዲህም አለን ‹‹ነፍሴን ደግሞ አነሣት ዘንድ አኖራለሁና ስለዚህ አብ ይወዶኛል፡፡ እኔ በፍቃዴ አኖራታለሁ እንጂ ከእኔ ማንም አይወስዳትም፡፡ ላኖራት ሥልጣን አለኝ ደግሞም ላስነሣትም ሥልጣን አለኝ፡፡ ይህችህን ትዕዛዝ ከአባቴ ተቀብያለሁ፡፡›› አለን(ዮሐ 10፥17-18)
እንደቅድስት ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ በእግዚአብሔርና በሥግው ቃል በጌታችን በክርስቶስ መካከል የሥልጣን ልዩነት የለም፡፡ አብ ሥሉጥ እንደሆነ ወልድም ሥሉጥ ነው መንፈስ ቅዱስም እንዲሁ፡፡ እግዚአብሔር ክርስቶስን አስነሣው በሚለውና ክርስቶስ በራሱ ኃይልና ሥልጣን ከሙታን ተለይቶ ተነሣ በሚለው መካከል ልዩነት የለም የአገላለጽ ልዩነት ካልሆነ በቀር አንድ ነው፡፡ጌታችን እንዳለ ‹‹ አብ በራሱ ሕይወት እንዳለው እንዲሁ ደግሞ ለወልድ በራሱ ሕይወት እንዲኖረው ሰጥቶታልና የሰው ልጅም ስለሆነ ይፈርድ ዘንድ ሥልጣን አለው፡፡›› (ዮሐ 5፥26) ዳግመኛም ‹‹ እኔና አብ አንድ ነን›› (ዮሐ 10፥30) እንዳለ፡፡
የክርስቶስ ትንሣኤ ዘወትር አስደናቂና ሊመረመር የማይችል ነው፡፡ ክርስቶስ ከትንሣኤው በኋላ ቦታ የማይወሰን ሆኖ ታይቷል፡፡ከረቂቅነቱም የተነሳ ደቀ መዛሙርቱ እርሱን መለየት አቅቷቸዋል፡፡(ሉቃ 24፥16 ዮሐ 20፥4) ምትሐት አለመሆኑን ለማሳየትም በልቷል ጠጥቷል፡፡ (ሉቃ 24፥30¸39) ይህም የነሣውን ሥጋን ይዞ መነሳቱን አመልካች ነው፡፡ ጎኑንም እንዲዳስሱት ፈቀደ የሚዳሰሰውን የሠው አካል ይዞ መነሳቱን ሲያመለክት(ዮሐ 20፥27¸21፥9) ዳግመኛም መለኮት መዋሐዱን ለደቀመዛሙርቱ በዝግ ቤት ሳሉ ተገለጠላቸው፡፡(ዮሐ 20፥19¸26) ይሰወርባቸውም ነበር(ሉቃ 24፥31) ክርስቶስ ሲነሣ ሥጋን ከመለኮት ጋር እንደተዋሐደ ሆኖ መሆኑን እነዚህ የመጻሕፍት ክፍለ ንባባት አስረጅ ናቸው፡፡በትንሣኤው ሞትን ድል አደረገ ደካማ ሆኖ ታየ፡፡ ረቂቅ መሆኑን ለደቀ መዛሙርቱ ገለጠ ነገር ግን በላ ጠጣ፡፡ በሚታይ አካል ተገለጠ ከአእምሮ በላይ መሆኑንም አሳየን፡፡ በትንሣኤ ምሥጢረ ሥጋዌ ይበልጥ ረቃ እናያለን ሊነገርና ሊገለጥ የማይችል ረቂቅ ከልቦና በላይ ነውና ዘወትር እያደነቅነው እንኖራለን፡፡
በክርስቶስ ትንሣኤ የሰው ልጅ ምን አገኘ?
በትንሣኤው እርሱን ወደ መምሰል መለሰን
መጽሐፍ ቅዱስ ስለመጀመርያው ሰው አዳም ሲናገር እግዚአብሔር ‹‹ ሰውን እንደመልካችን እንደምሳሌያችን እንፍጠር››ብሎ በመልኩና በምሳሌ ፈጠረው (ዘፍ. 1÷26) ይላል፡፡ ንዑድ ክቡር የሆነው የሰው ልጅ ሲፈጠር በሙሉ ክብር እንደአምላክ ነባቢ ለባዊና ሕያው ፍጥረት ሆኖ የተፈጠረ ነው፡፡ መምሰሉም በነፍሱ ነው፡፡ ነገር ግን የሰው ልጅ በሠራው በደል ምክንያት ሞት በምድር ነገሠ፡፡ ከኹሉ በላይ ከብሮ የተፈጠረ አዳም የዲያቢሎስ ባርያ ሆነ፡፡ የሰው ልጅ ከእግዚአብሔር ውጪ ሕይወት የለውና ከእግዚአብሔር የተለየ ምውት ሆነ፡፡ ሥጋዊ ሞት ብቻም አይደል ከእግዚአብሔር መለየቱ አዳምን ከነበረው ክብር አጉሎታል፡፡ ቅዱስ አትናቴዎስ ስለዚህ ሲናገር ‹‹ከእግዚአብሔር ይልቅ ራስህን ከመረጥክ ባዶ ነህ፡፡ ከእግዚአብሔር ውጪ አንተ ምንም ነህና ›› ይላል ስለዚህም አዳም በተሰጠው ምርጫ ባዶ ማንነትን መረጠ ሕይወት ምርጫ ናትና፡፡ ሰው ከእግዚአብሔር ከተለየ ምውት ነው የምንለው በእግዚአብሔር የሕይወት እስትንፋስ አማካኝነት ሕያው ስለሆነ ነው፡፡
ከትንሣኤው ለመደመር ምን እናድርግ?
በጥምቀት ከእርሱ ጋር መተባበር
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ እንግዲህ ክርስቶስ በአብ ክብር ከሙታን እንደተነሣ እንዲሁም እኛም በአዲስ ሕይወት እንድንመላለስ ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን ሞትን በሚመስለው ሞቱ ከእርሱ ጋር ከተባበርን ትንሣኤውን በሚመስለው ትንሣኤ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን›› (ሮሜ 6፥4-5) እንዳለ ሰው በጥምቀት አማካኝነት ከሞቱ ጋር ካልተባበረ በትንሣኤው አይደመርም፡፡ በጥምቀት ከሞቱ ጋር እንተባበራለን፡፡ ካህኑ ሲያጠምቅ ብቅ ጥልቅ እያረገ ሞትና ትንሣኤን እያመላከተ ያጠምቃልና፡፡ በጥምቀት ያልተባበረ በሕይወት ይኖር ዘንድ በራሱ ኃይል የለውም ሞት አለበት፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም ስለዚህ ሲያስረዳ ‹‹በሥጋዊ ልደት ካልተወለደ በቀር መንፈሳዊ የሆነውን እርሱን ግዘፈ አካል አለው አንደማንለው ሁሉ አንዲሁ እኛም መንፈሳዊ በሆነ ልደት ካልተወለድን በቀር መንፈሳውያን አንባልም››ይለናል፡፡
እኛ የሰው ልጆች የመንፈስ ቅዱስን እገዛ በኃጢአት ምክንያት ከማጣታችን የተነሣ ምንም እግዚአብሔርን በጸጋ የምንመስልበት ተፈጥሮ ቢኖረንም አልተቻለንም ነበር፡፡ ወደዚህ ወደ ቀደመ ክብራችን ለመመለስ ሰው ግዴታ ሊጠመቅና ሰውነቱን የመንፈስ ቅዱስ ቤተመቅደስ ሊያደርገው ይገባል፡፡ እንዲህ ከሆነ በእርሱ ሰውነት ውስጥ ያደረው መንፈስ ቅዱስ እግዚአብሔር አምላክን መስሎ የሚኖርበትን ጸጋ ያገኛል፡፡ በእርሱም በተፈጥሮ ያገኘውን እግዚአብሔርን የመምሰል አቅም ተጠቅሞ በጸጋ እግዚአብሔርን ወደ መምሰል ያድጋል፡፡
ስለዚህ አንድ ሰው በትክክለኛው ተፈጥሮ ለመኖር ከፈቀደ የግድ ተጠምቆ ክርስቲያን በመሆን የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ ሊያገኝ ይገባዋል፡፡ ያለበለዚያ ምኞት ቢኖረው እንኳ በትክክለኛው ተፈጥሮ መኖር ይሳነዋል፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ ከቅድስት ድንግል ማርያም በነሣው ሰውነቱ በኩል ሰው እንደሆነ እንዲሁ እኛም ከመንፈስ ቅዱስ ተካፋዮች በመሆን እርሱን በጸጋ ወደ መምሰል ልንመጣ ይገባናል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም በመንፈስ ቅዱስ ካልሆነ በቀር ጽድቅን መፈጸም እንደሚሳነን ሲያስረዳ‹‹የማደርገውን አላውቅምና የምጠላውን ያን አደርጋለሁና ዳሩ ግን የምወደውን እርሱን አላደርግም፡፡ በውስጥ ሰውነቴ በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለኛልና፤ ነገር ግን በብልቶቼ ባለ በኃጢአት ሕግ የሚማርከኝን ሌላ ሕግ አያለሁ፡፡ እኔ ምንኛ ጎስቋላ ሰው ነኝ ለዚህ ሞት ከተሰጠ ሰውነት ማን ያድነኛል››ይልና በቀጣዩ ምዕራፍ ላይ ለዚህ መልስ ሲሰጥ ‹‹እንግዲህ በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት አሁን ኩነኔ የለባቸውም፡፡ በክርስቶስ ኢየሱስ ያለው የሕይወት መንፈስ ሕግ ከኃጢአትና ከሞት ሕግ አርነት አውጥቶኛልና፡፡››ይላል (ሮሜ 7፡15-25፣8፡1-2)
ለኃጢአት መሞት
በመጻሕፍት እንደተገለጠው የመጀመርያው ሰው አዳም ሕያው ነፍስ ሆነ ተብሎ ተጽፎል የኋለኛው አዳም በክርስቶስ ግን ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ሆነ ከሞታን ማኅበር አውጥቶ በጽኑ ሥልጣንም ያከበረው ጌታችን ነውና፡፡የመጀመርያው አዳም መገኛው መሬት ነው ኹለተኛው አዳም መገኛው ከሰማይ ነው፡፡ ለዚህም ነው ‹‹ከሰማይ ከመጣው በቀር ወደ ሰማይ የወጣ የለም›› ተብሎ የተጻፈው፡፡ ከመጀመርያው አዳም የተገኙ መነሻቸው አፈር ነውና ምድራዊያን ናቸው፡፡ በኹለተኛው አዳም ያመኑ ዳግም የተወለዱ ግን ከሰማይ ናቸውና የሰማይ አባታቸውን ይመስላሉ፡፡(1ኛ ቆሮ 15፥42-50)
የጌታችን መነሣት የመጀመርያው ፍሬ የሰው ልጆችን ዳግም መነሣትን የማሳየቱ ነው፡፡ ክርስቶስ ሞትን ድል እንዳደረገ ስንል እንዲሁ በእርሱ ያመኑ ዳግም እንደሚነሡ ያየንበት ነው፡፡ የቅዱሳን ተስፋም ተፈጽሞል ቅዱስ ዳዊት ‹‹ነፍሴን በሲዖል አትተዋትምና››(መዝ 16፥11) ይላልና ይህ ተስፋው የተፈጸመው በክርስቶስ መነሳት ነውና የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የዘወትር ስብከቷ ነው፡፡
አሁን ወደ ቀደመ መምሰላችን በጥምቀት ተመልሰናል፡፡ በጥምቀት ከሞቱና ከትንሣኤው ጋር እንተባበራለን፡፡ አስቀድመን በአርአያውና በአምሳሉ ሕያው ሆነን የተፈጠርን ነንና ቅዱስ አባታችን ባስልዮስ አርአያ ለሁሉ የተሰጠ ነው ምሳሌ (አምሳል) ስንል ግን በተፈጥሮ የተሰጠንን ዕውቀት ተጠቅመን በተግባር እርሱን የምንመስልበት ሂደት እርሱ ምሳሌ (አምሳል)ይባላል እንዳለን እግዚአብሔር በባሕርይው ፍቅር ነው፣ ትሑትና የዋኅ ነው፣ ቅን ፈራጅ ነው፣ ጻድቅ ነው፣ ርኅሩኅ ነው፣ መሐሪ ነው፣ ታጋሽ ነው፡፡ እነዚህ ባሕርያት ሁሉ በእኛ ተፈጥሮ ውስጥ ያሉ ናቸው፡፡ እነዚህን ባሕርያት ወደ ተግባር መልሰን ስንፈጽማቸው እግዚአብሔርን መስለነዋል ወይም የእግዚአብሔር ምሳሌ ወይም አምሳል በእኛ ላይ ተንጸባርቆ ይታያል፡፡ ይህን ማድረግ ካላ,ልቻልን ግን ለኃጢአት አልሞትንምና ዳግመኛ እርሱን እንዳንመስል ሕይወትም እንዳናገኝ በክፉ ሥራችን እንያዛለን፡፡ በምድራዊ ሕይወቱ ለክፉ ሥራ ያልሞተ ዳግመኛ ሞት አለበትና በሕይወት እንድንኖር በትንሣኤ ልቡና ከእርሱ ጋር መጣበቅ በመልካም ሥራ እርሱን መምሰል ለኃጢአት መሞት(ከኃጢአት መራቅ) ይገባናል፡፡ ለዚህም የቅዱሳኑ ጸሎት ትርዳን፡፡
ስብሐት ለእግዚአብሔር