በዲያቆን ያሬድ መለሰ
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀመዛሙርት በጽርሐ ጽዮን በዝግ ቤት ሳሉ የመንፈስ ቅዱስን ፀጋ ተቀብለዋል፡፡ አስቀድሞም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹እንሆም አባቴ የሰጠውን ተስፋ እኔ እልክላችኋለሁ እናንተ ግን ኃይልን እስክትቀበሉ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቆዩ››(ሉቃ. 24÷49) እንዳለ እንደተናገረ መንፈስ ቅዱስን ልኮላቸዋል፡፡ የመንፈስ ቅዱስም ፀጋ ከጥምቀት ጋር መሆኑን ሲያመለክት ‹‹ዮሐንስ በውሃ አጥምቆ ነበርና እናንተ ግን ከጥቂት ቀን በኋላ በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ›› በማለት አመላክቷል፡፡(ሐዋ. 1÷5) ከመንፈስ ቅዱስም ፀጋ የተነሳ ወንጌልን በዓለሙ ሁሉ እንደሚሰብኩም የመንግስቱ ወንጌል በሰማርያ በይሁዳ እስከዓለም ዳርቻ እንደሚሰብኩ ተናግሯል፡፡(ሐዋ. 1÷8) ምንም እንኳን በዚህ ዕለት መንፈስ ቅዱስ ለደቀ መዛሙርቱ ቢወርድም ይህ ግን ለመጀመርያ ጊዜ ነው አያስብልም፡፡ ለአብነትም ቅዱስ ገብርኤል እመቤታችንን ሲያበስራት መንፈስ ቅዱስ ወደ አንቺ ይመጣል የልዑልም ኃይል ይፀልልሻል (ሉቃ. 1÷26-35) በቅዱሱ ካህን በዘካርያስ ላይ (ሉቃ.1÷67) እንዲሁም በቅድስት ኤልሳቤጥም መንፈስ ቅዱስ ሞላባት(ሉቃ.1÷41) ማለቱ የመንፈስ ቅዱስ ፀጋ በተመረጡ ቅድሳን ላይ መውረዱን የሚመላክቱ ናቸው። በብሉይ ኪዳንም ለተወሰኑ ቅዱሳን የመንፈስ ቅዱስ ሀብትና ፀጋ እንደሚሰጥ በጉልህ ሰፍሮ እናገኛለን፡፡ ለአብነትም ነቢዩ ኢሳይያስ የጌታ መንፈስ በእኔ ላይ ነዉ ለድሆች የምስራችን እሰብከ ዘንድ ቀብቶኛልና ማለቱ(ኢሳ. 61÷1) ይህንን የሚመላክት ነው(ይህ ገጸ ንባብ በትንቢት መልክ በኋላ ልመጣ ላለው ክርስቶስ ትንቢት መሆኑን ሳንዘነጋ(ሉቃ. 4÷18-19) ራሱም ጌታ የነቢዩ ቃል እንሆ ተፈጸመ ማለቱን ሳንረሳ በማስተዋል)። የጽርሐ ጽዮን ከላይ ከገለጽነው ለየት የሚያደርገው ከልጅነት ጋር ከብዙ ፀጋዎች ጋር ለብዙ አማኞች መገለጹ ነው፡፡ ይህንንም በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀባላችሁ ባለው ተገልጦል። በጥቅሉ ቤተ ክርስቲያን በመንፈስ ቅዱስ የተወለደችበት ዕለት ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስም ዘወትር ከቤተ ክርስቲያን አይለይም፡፡ አስቀድሞም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹ወሶበ መጸአ ጰራቅሊጦስ ዘአነ እፌኑ ለክሙ እምኅበ አብ መንፈስ ጽድቅ ዘይወጽእ እምኅበ አብ ውእቱ ሰማዕየ›› ዳሩ ግን እኔ ከአብ ዘንድ የምልክላችሁ አጽናኝ እርሱም ከአብ የሚወጣ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ እርሱ ስለእኔ ይመሰክራል፡፡ (ዮሐ 15፥26 ዮሐ 14፥16) እንዳለ ደቀ መዛሙርቱ ስለክርስቶስ በጥብአት ያለፍርሃት በሥልጣን የመንግሥቱን ወንጌል ለዓለም ሁሉ ሰብከዋል። ደቀ መዛሙርቱ ጌታችን በሚያስተምርበት ወቅት የነበራቸውን ድክመትና ከመንፈስ ቅዱስ መውረድ በኋላ ያላቸውን አገልግሎትና ቆራጥነትን ያስተዋለ ይህንን በቀላሉ ይረዳዋል። ያለ መንፈስ ቅዱስ እርዳታ የሚደረግ አገልግሎት ስንኩል ነው ለዚህም ነው የቤተ ክርስቲያንን ልደት ከመንፈስ ቅዱስ መውረድ ጋር ማስተሳሰራችን።
መንፈስ ቅዱስ ማነው?
መንፈስ ቅዱስ መንጽሂ(የሚያነጻ)፣መጽንኢ(የሚያጸና)፣ናዛዚ(የሚያረጋጋ)፣ከሣቲ(ምሥጢር የሚገልጽ) መስተፈሥሒ(የሚያስደስት)፣መስተሰርይ (ኃጢአትን የሚያስተሰርይ) ማለት ነው። ይህም መንፈስ መንፈሰ ጽድቅ፣መንፈሰ ሕይውት፣ ባሕርያዊ እስትንፋስ፣ አካላዊ እስትንፋስ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስም ውስጥ በተለያዩ ስሞች ይጠራል። ለአብነትም መንፈስ (ዮሐ 1፥32) የእግዚአብሔር መንፈስ (ሮሜ 8፥14) ቅዱስ መንፈስ (መዝ 50፥11, መዝ 142፥10) የጌታ የክርስቶስ መንፈስ (ሮሜ 8፥9,2ኛ ቆሮ 3፥17 የእውነት መንፈስ (ዮሐ 15፥26) አጽናኝ ተብሎ ይጠራል ። (ዮሐ 14፥26)
ይህም መንፈስ ከአብ የሰረጸ ነው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳለ ‹‹ወሶበ መጸአ ጰራቅሊጦስ ዘአነ እፌኑ ለክሙ እምኅበ አብ መንፈስ ጽድቅ ዘይወጽእ እምኅበ አብ ውእቱ ሰማዕየ›› ዳሩ ግን እኔ ከአብ ዘንድ የምልክላችሁ አጽናኝ እርሱም ከአብ የሚወጣ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ እርሱ ስለእኔ ይመሰክራል፡፡
ይህ ቃል ስለመንፈስ ቅዱስ ጌታችን የተናገረበት ክፍለ ትምህርት ነው ስለመንፈስ ቅዱስ ሲነግረን ከአብ የሚወጣ ማለቱን ልብ በሉ ከአብ የሚወጣ አለ እንጂ ከእኔ የሚወጣ አላለም ስለዚህም የመስረጽ ግብር የማን እንደሆነ የማስረጽ ግብር የማን እንደሆነ በዚህ የመጽሐፍ ክፍል በጉልህ ተጽፎ እናገኛለን፡፡ (ዮሐ 15፥26 ዮሐ 14፥16) የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች መንፈስ ቅዱስ አካሉ አንድ ሀብቱ ብዙ ነው። የቤተ ክርስቲያኒቱ ማንኛውም አገልግሎት የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ነው። ለዚህም ነው መንፈስ ቅዱስ ለአብና ለወልድ እስትንፋሳቸው እንደሆነ ሁሉ ለቤተ ክርስቲያንም እስትንፋሷ ነው ማለታችን። እኝህም የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች ከልጅነት ጥምቀት ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ነገር በብዙ ሲናገራል በሐዋ. 9÷2 ‹‹አንዳንድ ደቀመዛሙርትም አገኘ። ባመናችሁ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ተቀበላችሁን? አላቸው። እነርሱም። አልተቀበልንም መንፈስ ቅዱስ እንዳለ ስንኳ አልሰማንም አሉት። እንኪያስ በምን ተጠመቃችሁ? አላቸው። እነርሱም።በዮሐንስ ጥምቀት አሉት።…›› ይህ ገጸ ንባብ ስለሦስት ነገሮች አስረጅ ተደርጎ ይጠቀሳል አንደኛ ስለዳግም ጥምቀት (እነዚህ ደቀ መዛሙርት የዮሐንስን ጥምቀት የተጠመቁ ቢሆኑም ዳግመኛ የልጀነት ጥምቀት በመጠመቃቸው) ሁለተኛ መንፈስ ቅዱስ ባመኑ ሰዎች ላይ ስራ እንደሚሰራ (እንደተጠመቁ መንፈስ ቅዱስ በብዙ ቋንቋዎች እንዲናገሩ ትንቢት እንዲተነበዩ ፀጋ እንዳሳደረባቸው) ሦስተኛው የመንፈስ ቅዱስ ሐብትና ፀጋ በክርስቲያኖች ላይ ዘወትር እንደሚሰራ። ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ በንባቡ ላይ ደቀ መዛሙርት ተብለው የተገለጡ የመጥመቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ደቀመዛሙርት መሆናቸውን አስፍሮል። እነዚህ ደቀ መዛሙርት በቅዱስ ዮሐንስ ጥምቀት የንስሐ ጥምቀት የተጠመቁ ናቸውና ቅዱስ ጳውሎስ የልጅነት ጥምቀት አጥምቋቸዋል፡፡ራሱ ቅዱስ ዮሐንስ ‹‹ እኔ በውሃ አጠምቃችሃለሁ የሚመጣው ግን በእሳትና በመንፈስ ያጠምቃችሃል›› ማለቱ ለዚህ አስረጂ ነው፡፡ ወደ ተነሳንበት ነጥብ ስንመለስ ይህ ገጸ ንባብ የመንፈስ ቅዱስ ፀጋ የሚገኘው በጥምቀት መሆኑን ያስረዳናል፡፡ አንዳንድ ሰዎች ግን ሳያምኑና ሳይጠመቁ የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ አገኘን ይላሉ ይህ ፍጹም ስህተት ነው የመንፈስ ቅዱስ ፀጋ ያለልጅነት ጥምቀት አትገኝም። አሁንም እንደአባቶቻችን እንዲህ እያልን እናመስግነው ሰላም ለርደትከ አምሳለ ነፋስ ረቂቅ ውስተ ጽርሕ አሐቲ ኀበ ሀለው ደቂቅ ጰራቅሊጦስ ኃይል መንፈሰ ጸጋ ወጽድቅ ይሰደድ እምላዕሌየ ጽልመተ ኃጢያት ጽፉቅ ሶበ ያስተርኢ ስንከ መብረቅ። የጸጋ ሁሉ ባለቤት፤ ፈጣሪ ፍጡራን፤ አምጻኤ ዓለማት፤ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በቸርነቱ ለክብርና ለመንግሥተ ሰማያት ያብቃን፤ ከተራፊ ከከራሚዎቹ ደምሮ የዓመት ሰው ይበለን አሜን!!!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር