በዲያቆን ያሬድ መለሰ
ጥንት በቀደመው ዘመን አባቶቻችን በቃል የተማሩትን በቃል ሲያስተምሩ እኩሌታዎቹ በቃል የተማሩትን ብዕር ቀርጸው ብራና ዳምጠው ቀለም በጥብጠው በጽሑፍ ሲያሰፍሩ በብዙ ድካም ነበር አያሌ ነገሮችን ያቆዩልን፡፡ ከእነርሱም ሲወርድ ሲወራረድ ከእኛ የደረሰው አንዱ የአንድምታ ትርጓሜ ትምህርት ነው፡፡ አንድምታ ቅዱሳት መጻሕፍትን ለማብራራት፣ የተቋጠረን ለመፍታት የሚያገለግል የትምህርት ዓይነት ነው፡፡ እንዲሁም ምዕመናን እምነታቸውን በስፋትና በጥልቀት እንዲገነዘቡት ያደርጋል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ትርጓሜ የሰውን ልብ እንዲያበራና አስተዋይ እንደሚያደርግ ተጠቅሷል (መዝ 118፡130) ስለዚህም የትርጓሜ ትምህርት ለአንድ ክርስቲያን እንደሚያስፈልገው ምንም ጥርጥር የሌለው ነገር ነው፡፡ ከዚህ የተነሳ ትርጓሜን ማወቅና መማር የግድ አስፈላጊ ነው፡፡ ምክንያቱም ክርስቲያኖች በቀላልና ግልጽ በሆነ መንገድ ወንጌልን እንዲረዱ ስለሚደረግ እና የአባቶችን ትምህርት በሚገባ እንዲያውቁ አንድምታን መነሻ በማድረግ እንመለከታለን፡፡ የምሥጢር መጻሕፍትን ክቡር ማዕድ የመፈተትና የማደል ሙያ የተቀዳጁ (የታደሉ) ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ‹‹አንባቢ የሆነ አስቀድሞ የመጽሐፍን አርዕስቱን' መቅደመ ነገሩን' ምክንያተ ጽሕፈቱን ሳይዝ ወይም ሳያውቅ ምልዐተ ንባቡን የሚመለከት አይኑር›› ብለዋል፡፡ ሊቃውንቱ እንዲህ የሚያደርግ ቢኖር እርካብ ሳይረግጥ ወደ ኮርቻ'ድንክ (ደረጃ) ሳይረግጥ ወደ ዙፋን የሚወጣ የዋህ ሰውን ይመስላል እንዳሉት እንዳይሆንብን የወንጌል አንድምታ ትምህርት ከመጻፋችንና ከመናገራችን በፊት ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን አስቀድሞ መማር ይገባል፡፡
የትርጓሜ አስፈላጊነት
ሰው እንደመላእክት አዋቂ ብሩህ አእምሮ ያለው ሆኖ ተፈጥሮ ሳለ በኃጢአት ምክንያት ብሩህ አእምሮው ጨለመ'ፀጋ እግዚአብሔር ተለየው'ተሰጥቶት የነበረውን ክብር በማጣቱም የፈጣሪውን ቃል ትቶ የፍጡር ቃል በመስማቱ አዋቂ ሆኖ ሳለ አላዋቂ ሆነ፣ የእግዚአብሔርን መልእክት በቀጥታ ከማስተዋል ተገታ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው ‹‹መጻሕፍትንና የእግዚአብሔርን ኃይል አታውቁምና ትስታላችሁ›› ማቴ 22፣29 እንዲህ ሲል የሰው ልቡና ነገረ እግዚአብሔር እንደተሰወረበት የሚያስረዳ ነው፡፡ ስለዚህ የእግዚአብሔርን መልዕክታት የያዙ ቅዱሳት መጻሕፍት እንደመሆናቸው ሰው የእግዚአብሔርን ምስጢር እንዲያውቅና እንዲረዳ ትርጓሜ አስፈላጊ ነው፡፡ ነገረ እግዚአብሔር ተሰውሮበታልና፡፡
የእግዚአብሔር ቃል እንደ ድንች እና እንደ ካሮት ተቆፍሮ ወጥቶ የሚበላ እንጂ በዓይን ታይቶ በእጅ የሚቀነጠስ አይደለም፡፡ ሥጋዊ ምግብ እንኳን በእሳት በስሎ ሲበሉት ለሰውነት ተስማሚ እንደሚሆን ሁሉ መጽሐፍ ቅዱስን በትርጓሜ ተብራርቶ ሲማሩት ሲመገቡት ለህይወት ተስማሚ ይሆናል ብሎም ለሰማዕትነት ያበቃል፡፡ ስለዚህ የሰው ልጅ መንፈሳዊ ሕይወቱ እንዲያምር የመጻሕፍት ትርጓሜ ትምህርት አስፈላጊ ነው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም ከዚህ በታች ያሉትን ነገሮች ለመረዳት ለመገንዘብ አስተዋጽኦ ስለሚያደርግ ነው፡፡
ሰዎች አንዱ ከሌላው በብዙ መንገድ ይለያሉ፡፡ ለምሳሌ፡-
በሀገር፡- የአንዱ ሀገር ትምህርት'ባህል ወግና ልማድ ቋንቋ ወዘተ ከሌላው ሀገር ይለያል፡፡
በትምህርት፡- አንዱ ምሁር ሌላው ኢምሁር ሊሆን ይችላል፡፡ እንዲሁም በማስተዋል በሞራል በማገናዘብ አንዱ ሰው ከሌላው ሰው በትምህርቱ ብቃት በእውቀት የመቀበል የመረዳት ችሎታው ይለያያል፡፡ ስለዚህ እነዚህን የመሳሰሉት እውነታዎች ከግንዛ ያስገባ ግሩም የሆነ ገለጻና ማብራሪያ ለመስጠት ትርጓሜ አስፈላጊ ነው፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ የተነገረበትና የተጻፈበት ዘመን እጅግ ሩቅ ነው፡፡ ቦታው ባህሉ ሥርዓቱ ኑሮው ልማዱ ቋንቋው ዛሬ ካንበት ዘመን የተለየ ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ በመጀመሪያ የተነገረላቸው ህብረተሰቦች በአስተሳሰብና በዕውቀት ከእግዚአብሔርም ጋር ከነበራቸው ቅርብነት አኳያ ከዛሬው ህብረተሰብ የተለዩ ነበሩ፡፡ ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስን ለዛሬው ኅብረተሰብ መተርጎም አስፈላጊ ነው፡፡
ሌላው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተለያዩ የንግግር ዓይነቶች እንደ ሕልም፣ እንቆቅልሽ፣ ምሳሌያዊና ቅኔያዊ፣ ራዕይና ትንቢት ጥበብም ስላሉት ሌላም በእንስሳት ጠባይ በርካታ መልእክቶች አሉ፡፡ እነዚህን ለመረዳት ትርጓሜ አስፈላጊ ነው፡፡ የቀድው ንባብ በኋለኛው ተተርጉሞ ይገኛል፡፡ ብሉይ ኪዳን በሐዲስ ኪዳን፣መጽሐፈ ሳሙኤልና መጽሐፈ ነገሥት በመጽሐፈ ዜና መዋዕል ተብራርተዋል፡፡ እንዲሁም ቀደም ያሉ የሐዲስ ኪዳን ምንባባት በኋለኞቹ ተተርጉመዋል፡፡ ዘፍ 40፣1-23፣ መሳ 14፣12፣ ዳኤል 5፣12፣ ሉቃ 13፣32፣ ዮሐ 10፣11፣ ኤር 31፣29-30 ሕዝ 18፣1፣ ማቴ 10፣10 በ1ኛጢሞ 5፡18 ዮሐ 2፣21፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ ከመጀመሪያ እርስ በርሱ የተያያዘ እንደመሆኑ በአንድ ቦታ ትንቢት የተነገረለት በሌላ ቦታ ተፈጽሞ በአንድ ቦታ ያልተተረጎመው በሌላኛው ተተርጉሞ ይገኛል፡፡ ሌላው መጽሐፍት እርስ በእሳቸው የሚጋጩ መስለው የሚታዩት ትርጉማቸውን ካለማወቅ የተነሣ ነው፡፡ ትርጓሜ ግን ይህን ሁሉ ያስታርቀዋል፡፡ ስለዚህ ከላይ እንደተገለጸው የመጻሕፍትን ከላይ አርእስታቸውን ከታች ህዳጋቸውን ተመልክቶ አንዱን በአንዱ መርምሮ አመዛዝኖ እነ ዮሐንስ አፈወርቅ እነ ቅዱስ ቄርሎስ በአጠቃላይ በሃይማኖተ አበው ያሉ ሊቃውንት ከተረጎሙት ትርጓሜ ከሰጡት አስተያየት ሳይወጡ መተርጎም ይገባል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ እንደተናገረው በቃል ከመምህራን በመማር የተቀበለውንም እንዳለ በትውፊትም በትርጓሜ መጻሕፍትም ማግኘት ይችላል(ፊሊ 4፣9)፡፡ አባቶቻችን ገጽ በገጽ ከሐዋርያት የተማሩትን ያዩትንና የሰሙትን በትውፊትም በትርጓሜ መጻሕፍትም ማግኘት ይቻላል በጽሑፍም በቀጥታ ለእኛ አድርሰዋል፡፡ በተለይም በቤተ ክርስቲያን የተለመደው የትምሀርት አሰጣጥ የቃል ትምሀርት ይህንን የቅዱስ ጳውሎስን ቃል መሠረት ያደረገ ነው፡፡ እንግዲህ ከአባቶቻችን የአስተምህሮ ሥርዓት እንዳንወጣ ልንጠነቀቅ ይገባናል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን የመተርጎም ሥልጣንን በተመለከተም ማንም ሰው የመጽሐፍ ቅዱስን ቃል በራሱ ሐሳብ እንደራሱ ፈቃድ ሊተረጉም እንደማይገባው ተጽፎአል፡፡ 2ኛ ጀጴጥሮ 1፣20 ከዚህ የምንረዳው አንድምታ ትርጉም ማንም እንደፈለገው ርዕስ መዞ የሚጽፈው ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ ያልተቃኘ' ሐዋርያትን፣ የሐዋርያነ አበውን ከእነርሱም ቀጥለው የተነሡ የኦርቶዶክሳውያን አበው ሊቃውንትን ትውፊት ያልተከተሉ መጽሐፍ ቅዱስን በነጻነት ለመተርጎም ቢሞክሩም እንኳን በሥጋዊ ጥበብ በፍልስፍና ብቻ ስለሚመሩ ከስህተት ላይ ይወድቃል፡፡ 2ኛ ጴጥ 3፣18
የትርጓሜ ዓይነት
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የራሷ የሆነ የትርጓሜ ስልት አላት፡፡ የራቀውን አቅርባ የቀረበውን አጉልታ የምታቀርብባቸው ልዩ ልዩ የትርጓሜ ዓይነቶች ሲኖሯት ከእነዚህ ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው፡፡ ነጠላ ትርጓሜ'ምሳሌ'ምስጢራዊ ትርጉም እና አንድምታ ትርጓሜ ናቸው፡፡
ነጠላ ትርጓሜ
ነጠላ ትርጓሜ የሚባለው ዘይቤውን ብቻ በቀጥታ የሚተረጉም ምንም ዓይነት ሐተታ የማያደርግ የትርጓሜ ስልት ሲሆን ከአንድ ቋንቋ ወደ ሌላ ቋንቋ የሚተረጉም ነጠላ ትርጓሜ ይባላል፡፡ በዚህ ዓይነት ትርጉም ጥንታውያን የሆኑት መጻሕፍት ከውጪ ቋንቋ ወደ ግእዝ ከግእዝም ወደ አማርኛ ተተርጉመዋል፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍት በዓለም ላይ አንድ ሆነው የተገኙት እንዲሁ በቀጥተኛው ዘይቤ ብቻ በመተርጎማቸው ነው፡፡ ለምሳሌ በግእዝ ልሳን ‹‹በልዋ ለዛቲ ቁንጽል›› ይላል ወደ አማርኛ ሲተረጎም ‹‹ለዚያች ቀበሮ እንዲህ በሏት›› ይላል፡፡ ነጠላ ትርጓሜ ማለት ይህ ነው፡፡
ምሳሌያዊ
ምሳሌ ማለት አንድን ነገር ግልጽ ለማድረግ የሚረዳ ስለሆነ በምሳሌ ሲነገር ነገርን በቀላሉ መረዳት ይችላል፡፡ ‹‹ነገር በምሳሌ. . . . .›› እንዲሉ፡፡ ይህንን የአስተምህሮ መንገድ ጌታ ከምስጢራዊ ትርጓሜ ጋር በማጣመር በወንጌልም ላይ ብዙ ቦታ ካስተማረባቸው መንገዶች አንደኛው ነው፡፡ ልበ አምላክ ዳዊት ‹‹አፌን በምሳሌ እከፍታለሁ›› መዝ 77፣2 ማር 4፣34 እንዳለው እንግዲህ ምሳሌ ሁልጊዜ ከሚመስለው ነገር ያንሳል፡፡ ስለዚህም ምሳሌ ‹‹ዘይሐጽጽ›› ይባላል ‹‹የሚያንስ›› ‹‹ጎዶሎ›› ለማለት ፡፡ ምሳሌ በዕብራይስጥ ‹‹ማሻል›› ይባላል፡፡
ምሥጢራዊ
ምስጢር ማለት የተሰወረ ግን በውስጥ ያለ ላይ በላይ የማይታይ እንደ ማለት ነው፡፡ ሌላው የምስጢር ትርጓሜ የሚባለው ደግሞ ምንባቡን ሳይሻ አገባቡን ሳይጠበቅ ምስጢሩን ብቻ በመጠበቅ የሚተረጉም ነው፡፡ በዕብራይስጥ ‹‹ሳተር›› በዐረብኛ ‹‹ሰተር›› በሱርስት ደግሞ ‹‹ስታር›› በእንግሊዝኛም ‹‹ Mystery ›› ይሉታል፡፡ በምሳሌ የተነገረውን ኃይለ ቃል በውስጡ ምስጢር ይዟል ስለዚሁ ሲያስረዱን ትርጓሜ ይሆናል፡፡ ምስጢር የሚባለው ነገር እኛ ልንረዳው የምንችለው ነገር ግን ነጠላ ትርጓሜውን ይዟል ስለዚሁ ሲያስረዱን ትርጓሜ ይሆናል፡፡ ምስጢር የሚለው ነገር እኛ ልንረዳው የምንችለው ነገር ግን ነጠላ ትርጓሜውን ነው፡፡ በሥጋዊ ጥበብ መርምረን ልንደርስበት የማንችለውን ነገር ነው፡፡ ለምሳሌ፡- በምሥጢራዊ ትርጉም ‹‹አንተ ኮክህ›› የሚለው ፍቺ ‹‹አንተ መሠረት ነህ›› ማለት ነው፡፡ በኮክህ(ዓለት መሠረት) የተመሰለው ቅዱስ ጴጥሮስ ነው፡፡ ‹‹በልዋ ለዛቲ ቁንጽል›› ‹‹ለዚያች ቀበሮ እንዲህ በሏት›› ሲል በቀበሮ የተመሰለው ሄሮድስ ነው፡፡ ማቴ 16፣18 ሉቃስ 13፣22
የአንድምታ ትርጓሜ
የአንድምታ ትርጓሜ የሚባለው አንድ ጊዜ ከተተረጎመ በኋላ መሠረታዊ የሐሳብ አንድነቱን ሳይለቅ እንደገና አንድም እያለ እስከ አሥርና አስራ አምስት ጊዜ የሚያወርዱበት አወራረድ የሚሰጡት ሐተታ ነው፡፡ አንድምታ ትርጉም በግእዝ ቋንቋ አንድም በማለት ፈንታ ‹‹ቦ›› ይላል፡፡ የዚህም ፍቺ ሌላ ይህንን የመሰለ ትርጉም አለው እንደማለት ነው፡፡ በአማርኛ ግን ሁለተኛ ሦስተኛ አይልም እንጂ አንድ እያለ እስከ አስራ አምስትና ከዚያ በላይ ጊዜ ይወርዳል፡፡ ሆኖም ግን ሁለተኛ ሦስተኛ እንደማለት ሦስተኛ አይልም እንጂ አንድም እያለ እስከ አሥራ አምስትና ከዚያ በላይ ጊዜ ይወርዳል፡፡ ሆኖም ግን ሁለተኛ ሦስተኛ እንደማለት የሚያስቆጥር ነው፡፡
የአንድምታ ትርጓሜ (ትምህርት) መቼ ተጀመረ?
የአንድምታ ትምህርት በግልጽ ሊታወቅ የቻለው በአንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ ነው፡፡ ከዚያ በፊት ሊቃውንተ አይሁድ አምስቱን የሙሴ መጻሕፍትንና መጻሕፍተ ነብያትን በአንድምታ ለውጠዋል፡፡ ይህ እንዲህ ሲሆን የጌታችን ተከታዮች ቅዱሳን ሐዋርያት ትክክለኛውን የአንድምታ ትርጓሜ ትምህርት በር ከፍተዋል፡፡
ጌታ ለደቀ መዛሙርቱ (ሐዋርያት) ወንጌልን ባስተማራቸው ጊዜ መጽሐፍ ስላልነበራቸው ትርጓሜውንም የነገራቸው በጥቂት ሥፍራ ላይ ብቻ ስለነበር ለጊዜው ትምህርቱን ፈጽመው አልተረዱትም ነበር፡፡ ከዕርገቱ በኋላ ግን መንፈስ ቅዱስን በጽርሐ ጽዮን ተቀብለው በአእምሮ ጎለመሱ፣ ምሥጢር ተረጎሙ፣ ብዙ ቋንቋም ተገለጸላቸው፡፡ ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ እንደገለጸላቸው ወንጌልን ጽፈው ለሕዝብ ለአሕዛብም እየተረጎሙ ማስተማር ጀመሩ፡፡
ሐዋርያት 3 ዓመት ከ3 ወር ያጠኑትን ትምህርት ለዓለም ለማስተላለፍ የረዳቸው ት/ቤቶችን ማቋቋማቸው ነበር፡፡ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ የሚታወቀው የመጀመሪው የክርስቲያኖች ት/ቤት በ60 ዓ.ም በቅ/ማርቆስ ወንጌላዊ የተመሠረተው የእስክንድሪያ የትርጓሜ ት/ቤት ነው፡፡ ሌላው መንፈሳዊ ት/ቤት ደግሞ በሦተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተመሰረተው የሦሪያ ትምህርት ቤት ነበር፡፡ በተለይ ከ2ኛው እስከ 3ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ ከነዚህ ት/ቤቶች በሚወጡ መምህራን አማካኝነት የትርጓሜ ትምህርት ሊያድግና ሊስፋፋ ችሏል፡፡ ከዚህም ሌላ ሠለስቱ ምእት /318ቱ ሊቃውንት/ በ325 ዓ.ም አርዮስን ለማውገዝ በኒቂያ ጉባኤ በተሰበሱ ጊዜ የመጽሐፍተ ብሉያትና መጽሐፍተ ሐዲሳትን እየተረጎሙ ጽፈዋል፡፡
ከ150ው ሊቃውንት በኋላም 200ው ሊቃውንት ንስጥሮን ለማውገዝ በ431 ዓ.ም በኤፌሶን ጉባኤ ባደረጉ ጊዜ እንደዚሁ የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍትን ተርጉመዋል፡፡ዮሐንስ ዘቡርልስና አባ ሚካኤል ዘሀገረ አትሪብ በሦስቱ ጉባኤያት የተሰበሰቡ አባቶች የጻፏቸውን ለሰው ልብ እንዲረዳ አድርገው ባጭሩ ጽፈውታል፡፡ ይህም መጽሐፈ ሃይማኖተ አበው በመባል ይታወቃል፡፡ ከዚህም በቀር በ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበሩ እንደ ቅ/አትናቴዎስ፣ ቅ/ዮሐንስ አፈወርቅ ወዘተ ያሉ ቅዱሳን አባቶች ቅዱሳት መጻሕፍትን እየተረጎሙ ጽፈዋል፡፡
የአንድምታ ትርጓሜ ትምህርት በኢትዮጵያ
የመጻሕፍት አንድምታ ትርጓሜ ስልት በሀገራችን መቼ እንደተጀመረ የትና በማን እንደተጀመረ ግልጽ ሆኖ ስለማይታወቅ ያለው አስተያየት ግምታዊ ነው፡፡ይህም፡-መጻሕፍተ ኦሪት ከዕብራይስጥ ወደ ግእዝ ተተርጉመው ወደ ሀገራችን ሲገቡ የመጻሕፍቱ ጥንታዊ የአንድምታ ትርጉም አብሮ እንደገባ ይታመናል፡፡ ከዚህም ሌላ ከሕገ ኦሪት ጋር ሊቃውንተ ኦሪት በንግሥተ ሳባ ጊዜ ከቀዳማዊ ምኒልክ ጋር አብረው ወደ ኢትዮጵያ ስለመጡ እነርሱ ሲተረጉሙት ሲያስተምሩት ኑረዋል በማለት አስተያየት ይሰጣል፡፡ በእርግጥም ኦሪት በጥንት ዘመን ተተርጉሞ በሀገራችን ቋንቋ ይሰራበት ነበር የሚለው ታሪክ እውነተኛ እስከሆነ ድረስ ሊቃውንተ ኦሪትም ወደ ሀገራችን መግባታቸውን አምነን ከተቀበለን መጻሕፍትም ሲተረጎሙ መኖራቸው ከቶ ሊያጠራጥረን አይችልም፡፡
በኋላም በዘመነ ክርስትና መጻሕፍተ ሐዲሳት ከጽርእ ወደ ግእዝ በቀጥታ በተተረጎሙ ጊዜ የአንድምታ ትርጓሜ ስልት የሆኑ መጻሕፍት ሁሉ ሳይተረጎሙ አልቀሩም የሚል አስተያየት ይሰጣል፡፡
ከዚያም አያይዞ ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚውሉ ብዙ መጻሕፍተ ሊቃውንት ሲተረጎሙ የትርጓሜ ስልት የሆኑ መጻሕፍት ሁሉ ሳይተረጎሙ አልቀሩም የሚል አስተያየት ይሰጣል፡፡ ነሐሴ 20 ቀን የሚነበበው ስንክሳር የአንድምታ ትርጓሜ ወደ ኢትዮጵያ የገባው በአባ ሰላማ በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንደሆነና አባ ሰላማ እንደጀመረው ይተረካል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ቅዱስ ያሬድ ጥበባት ሁሉ ከእግዚአብሔር ስለተገለጹለት የመጻሕፍትን ትርጓሜ ሁሉ ያወቀው ወይም የጀመረው እሱ ራሱ ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ነው ሲል ገድሉ ይናገራል፡፡
ይህ አይነት አስተያየት የወል በመሆኑ እንደ እውነት ይቆጠራል እንጂ የትርጓሜውንም መጻሕፍት ቃል በቃል አጥንቶ ወይም ከሰው አግኝቶ ወይም ራሱ ተጣጥሮ እገሌ ደረሰው ጀመረው ስለማይባልና ታሪኩም ከታሪክ ጋር ተያይዞ ስላልመጣ ልብ አኩርቶ አፍን ሞልቶ እንዲናገሩ አያደርግም፡፡
የአንድምታ ትርጓሜ አካል ገዝቶ መልክ አግኝቶ ለመታወቅ የቻለው በጎንደር ዘመነ መንግሥት ነው፡፡ ሊስፋፋ የቻለውም በየጊዜው የተነሡ የኢትዮጵያ ሊቃውንት የተለያዩ መጻሕፍትን በአንድምታ እየተረጎሙ በማቅረባቸው ነው፡፡
ይቆየን
ስብሐት ለእግዚአብሔር