Saturday, 15 June 2024

ኦርቶዶክሳዊ የንስሐ ሕይወት (ክፍል አራት)

በዲያቆን ያሬድ መለሰ

ለአስታየትዎ ymelese04@gmail.comን ይጠቀሙ

ውድ ኦርቶዶክሳዊያን በክፍል ሦስት ኃጢአትን መናዘዝ(ኑዛዜ)ና የኑዛዜ ምንነትና ጥቅም? በተመለከተ ለማየት ሞክረናል በዚህ ክፍል ንስሐና ኃጢአትን መናዘዝ(ኑዛዜ)ና የካህናት ድርሻ በንስሐና በኑዛዜ በተመለከተ በጥቂቱ እንላለን፡፡ መልካም ንባብ

ንስሐና ኃጢአትን መናዘዝ(ኑዛዜ)

ኑዛዜ ከእግዚአብሔር የተሰጠ ትእዛዝ ነው፣ እርሱም ከቤተ ክርስቲያናችን ምሥጢራት አንዱ ነው። ኑዛዜ ሁል ጊዜ ከንሰሐ ጋር መቀላቀል አለበት። አንድ ኦርቶዶክሳዊ አረጋዊ አባት እንዳለ ብዙዎች ይናዘዛሉ፣ ንስሐ የገቡ ግን ጥቂቶች ናቸው!” ይላቸው ነበር። (Elder Aemilianos of Simonopetra Monastery, Mt. Athos)

ስሐ በራስ ፍቃድ እራሳችንን ከእግዚአብሔር ስለራቅን በውስጥ የሚሰማ ልባዊ ስብራት ነው። እውነተኛ ንስሐ ከማይቋቋሙት ስቃይ፣ ከመጠን ያለፈ ኃዘንና የማያቋርጥ የጥፋተኝነት ስሜት ጋር ምንም ግንኙነት የለውም። እውነተኛ ንስሐ ሳይሆን በውስጣችን ያለትምክህተኝነት ስሜት ነው። በራሳችን ላይ ያነጣጠረ ቁጣ ራሱን ስለሚያጋልጥና ስለሚያሳፍረው የበቀል እርምጃ ይወስዳል። በይሁዳ የሆነው ይህ ነው።

ለድርጊታችን የሚሰማን የጸጸት እና የኃዘን ስሜት፤ በተለይ በእንባ ታጅቦ ለነፍሳችን መዳን የመጀመሪያ እርምጃ ነው። ቁስላችን መክፈትና እውነተኛ መድኃኒት መሻት ደግሞ ቀጣይ እርምጃ ሊሆን ይገባል፡፡ ከዚህ ውጭ ግን ማድረግ ቁስሉ እየጠነከረና እየተስፋፋ ትልቅ ጉዳት ሊያደርስብን ይችላል ማለት ነው።

ጸጸት ጥሩ ጅምር ቢሆንም፣ መጸጸቱ ብቻ በቂ አይደለም። ይሁዳ ጌታችንን ከዳ በኋላ በድርጊቱ አዘነ። በጣም አዝኖ የደም ገንዘቡን መልሶ ወጣና ራሱን ሰቀለ። ኀዘኑ እዚያ ቆመ እና ወደ ንስሐ አላበበም። ጴጥሮስም ወድቆ አዝኖ ነበር፣ ነገር ግን በዚህ ብቻ አላቆመም። ወደ ክርስቶስ ተመለሰ።

ንስሐ ማለት የአስተሳሰብ፣ የአመለካከት ለውጥ ማለት ነው፤ ሥነ ምግባርን መከተብና ኃጢአትን መጥላት ነው። ንስሐ መግባት ማለት በሁሉን ቻይ በሆነው መንፈስ ቅዱስ ጸጋ አማካኝነት ፍላጎትን፣ ፍቃደኝነትንና ከክርስቶስ ኅብረት ጋር እንደገና ለመቀላቀል መሻት(መፈለግ) ማለት ነው። ንስሐ የሚጀመረው ከልብ ነው፣ ነገር ግን በመለኮታዊና ቅዱስ ኑዛዜ ታግዞ በመጨረሻም በቅዱስ ቁርባን በመሳተፍ ያበቃል።

በኑዛዜ ወቅት፣ አንድ ሰው በክርስቶስ ፊት እንዳለ ሆኖ በቅንነትና በትኅትና በካህኑ ፊት ይናዘዛል። የትኛውም ሳይንቲስት፣ ሳይኮሎጂስት፣ ሳይኮአናሊስት፣ ሳይካትሪስት፣ ሶሺዮሎጂስት ወይም ፈላስፋ ካህኑን ሊተካ አይችልም።

የካህናት ድርሻ በንስሐና በኑዛዜ

የካህኑ አገልግሎት ኃጢአትን ማስተስረይ መንፈሳዊ ልጁን ተቀብሎ የተበጠሰውን(የደፈረሰውን) ኅብረት ማስተካከልና ዳግም ማደስ ነው። የትኛውም ሰው ቢሆን ካህኑን ሊተካ አይችልም።  ለዚህም ነው መንፈሳዊ አባት፣አበ ነፍስ ወይም የንስሐ አባት ተብሎ የሚጠራው። በካህኑና በንስሐ ልጁ መካከል ያለው ግንኙነት ከቤተሰብ ትስስር በላይ ነው።የንስሐ ልጁን እግዚአብሔርን በመፍራት፣ በማስተዋል፣ በትኅትናና በፍቅር መከታተል የመንፈሳዊ ሕይወት ጎዳናውን በጥንቃቄ መምራት አለበት።

ካህኑ ምሥጢረ ንስሐን ጨምሮ ቅዱሳት ምሥጢራትን የሚፈጽመው በተሰጠው የክህነት ፀጋ እንጂ ባለው መንፈሳዊ እውቀት፣ጥበብ፣ የሳይንስ እውቀት፣ የመጻፍ ችሎታ፣ አንደበተ ርቱዕነት(የስብከት የንግግር ችሎታ) አሊያም ጉልበት አይደለም። (ማቴ. 18፥18 ማቴ. 16፥17 ማቴ. 10፥8) በበጎነቱና በቅድስናው እንኳን አይደለም በክህነቱ ፀጋ በመንፈስ ቅዱስ በኩል እንጂ።

የክህነት ፀጋ

ካህኑ በሚሰራው ኃጢያት የተሰጠውን መለኮታዊ የክህነት ጸጋን አያጎድፈውም። የምግባር ጉድለት ቢኖርበት በሠራው ሁሉ ተጠያቂ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ግን ክህነቱ አይጎድፍም ይህ ማለት ግን ለራሱ ንጽሕና መጨነቅ የለበትም ማለት አይደለም። በፍትሐ ነገሥት ላይ ‹‹እስመ ካሕን ሕጹጸ ምግባር ከመ ማኅቶት ዘሰምዕ ውእቱ›› ምግባር የጎደለው ካህን እንደሰም መብራት ነው ይላል።የሚነደው እሳት በክህነቱ ይመሰላል እሳቱ ሰሙን ያቀልጠወል ለሕዝቡ ግን ያበራል ከብርሃኑ የተነሣ ጨለማ አያገኛቸውም፡፡ (ፍ. ነገሥት መን. 9፥1) ኃጢአተኛ ካህንም በኃጢአቱ እራሱን ቢጎዳም ለምእመናን ግን እርሱ ያላገኘው ጸጋና በረከት እንዲያገኙ የሚያደርግበት ሥልጣን አለው፡፡

በካህናት ምግባር ከካህናት መሸሽ አይገባም የራስን በደልና ኃጢአት ማሰብ እንጂ። ለዚህም ይህ ታሪክ ያስረዳናል ‹‹አንድ ባለጠጋ ገበሬ ነበረው፡፡ ይህን ገበሬ ‹‹ሂድና የንስሐ አባቴን ርስት እረስ ብሎ›› ይልከዋል፡፡ ይህም ገበሬ ከመምህረ ንስሐው ርስት ሆኖ ሲያርስ ድስት ሙሉ ወርቅ ያገኝና ሄዶ ለባለጸጋው ይነግረዋል፡፡ እርሱም ‹ለእኔ ለምን ነገርከኝ እኛማ ርስቱን ማረሳችን አርሰን ልንበላ አይደለምን? ወርቅ ለባለ ርስት ነው በል ለእርሱ ንገረው ነገር ግን ለእኔ ነገርሁት አትበል ይጣላሃል›› አለው፡፡ ሄዶ ነገረው ያም ቄስ ‹‹የምናወጣበትን ስታሰናዳ ቆየኝ›› ብሎ እርሱን ሰዶ ሰይፉን ሲስል አመሸ፡፡ ሄደው ቆፍረው ወርቁን ካወጡ በኋላ አንገቱን በሰይፍ ብሎ ገድሎታል። ወርቁም ደም ተፈንጥቆ ቢያርፍበት ብረት ሆኖል፡፡ ያ ባለጸጋ ካሁን ከአሁን ይመጣል ብሎ ሲጠባበቅ ቀረ፡፡ ምን ሆኖ ይሆን እያለ እየፈለገ ሲሄድ ዐሠረ ደም አገኘ፡፡ ‹‹ያ ክፉ ተጣለልቶታል ልጣለው›› ብሎ አሰበ፡፡ መልሶ ‹‹ምን እዳዬ አንተም አንድ ጊዜ ብጹዓን አግብርት ከተባሉት ተቆጥረሃል። እኔም ከእንግዲህ በቄስ እጅ ሥጋ ወደሙን አልቀበልም ከቤተ እግዚአብሔርም አልሄድም›› ብሎ ከመሄድ ተከለከለ።

በኋላ መልአክ የምታየው ነገር አለና ወደ ቤተ ክርስቲያን ውጣ አለው፡፡ ሰይጣን በዚህ ቄስ እጅ ላይ ሆኖ በእሳት ልጓም ለጉሞ በእሳት አለንጋ እየገረፈ ይዞት ሲወጣ አየ፡፡ ካህኑ ከቤተ እግዚአብሔር ሲገባ ሰይጣኑ ሲወርድለት ሥራውን ሠርቶ ሲወጣ እንቀድሞ በላይ ላይ ሆኖ በእሳት ልጓም ለጉሞ በእሳት አለንጋ እየገረፈ ይዞት ሲሄድ አይቶ ለካስ ቅዱስ ጳውሎስ ሁሉም የራሱን ሸክም ይሸከማል ያለው ለዚህ ነው (ገላ. 6፥4) ›› ብሏል ዳግመኛም የወርቅ ገደል (ውሃው የሚያርፍበት ወርቅ ማንኪያው የወርቅ ሆኖ አንድ እጁ የቆደለ ድውይ ጠጣ ሲለው ተጸይፎ አልጠጣም ሲል‹‹ ምነዋ ላይ እታቹ የወርቅ ማንኪያው የወርቅ ጠጣ እንጂ›› ብሎ ተጸጽቶ ሥጋ ወደሙን የሚቀበል ሆኗል፡፡›› ከዚህ ታሪክ እንደምንረዳው በካህናት ሰበብ ከእግዚአብሔር ጸጋ መራቆት እንደማይገባ ነው።

 


የንስሐ አባትና የንስሐ ልጅ ግንኙነት

ካህኑ የንስሐ ልጁን በቅጽበት ለመለወጥ መጨነቅ የለበትም።ይህ ዓይነቱ ግንዛቤ(ዝንባሌ) መንፈሳዊ ብስለት የጎደለው ነው። የንስሐ ልጁን ማስገደድ ለመንፈሳዊ ዓላማና ጉዳይ እንኳን ግድ ማለት ከልክ በላይ መጫን የንስሐ ልጁ የታሰረና የበላይ ሹማምንት ስር ያለ ባርያ እንደሆነ እንዲያስብ ሊያደርገው ይችላል። ካህኑ እንደመንፈሳዊ አባትነቱ መንፈሳዊ ልጅን መውለድ የሚያደክም አገልገሎት እንደሆነ መገንዘብና ከዚህ በተጨማሪ ለመንፈሳዊ ልጁ መንፈሳዊ እድገት እና ለቤተክርስቲያን ኅብረት መጸለይ ይገባዋል ።

የካህኑ ሥራ የአንድን ሰው ኃጢአት በውጫዊ ሁኔታ(በሚገልጸው መጠን) መስማትና ከዚያ በኋላ ጸሎተ ኑዛዜን (ጸሎተ ፍትሐት) መጸለይ ብቻ አይደለም። ክትትሉም በኑዛዜ ሰዓት ብቻም የተገደበ አይደለም። ልክ እንደ ጥሩ አባት ልጁን ያለማቋረጥ ይንከባከባል፣እርሱን ያዳምጠዋል በጥንቃቄ ይከታተለዋል፣ በትክክል ይመክረዋል፣ በወንጌል መስመር ይመራዋል፣ ችሎታውን ያጎላል፣ አላስፈላጊ ሸክሞችን አይጭንበትም፣ ቀኖናዎችን (ንስሐን) በገርነት ይጭናል፣ተስፋ ሲቆርጥ፣ ሲደክም፣ ሲከፋው፣ ያጽናናው በዚህ መሠረት ይፈውሳል፣ ተስፋ ሳይቆርጥ፣ ነገር ግን ፍላጎቱን ለማጥፋትና በጎነትን ለመሰብሰብ የሚያደርገውን ትግል ያለማቋረጥ ይከታተል፤ ያለማቋረጥ ዘላለማዊ ነፍሱን ክርስቶስን እንድትመስል ለመቅረጽ ይተጋል

ይህ በየጊዜው በማደግ ላይ ያለው የአባት እና የልጅ ግንኙነት ያጠናክራል። በመጨረሻ በመካከላቸው መተባበር መተጋገዝ መከባበርን ይፈጥራል። በሚናዘዙበት ጊዜ፣ አንድ ሰው ለተናዛዡ ልቡን ይከፍታል የውስጡን ከራሱ ወይም ለቅርብ ዘመድ አልያም ለቅርብ ጓደኛው በቀር ለማንም መንገር ሁሉንም ምስጢሮቹን፣ የኃጢያት ምኞቶቹን ጭምር ይናዘዛል።

በኦርቶዶክስ ኑዛዜ ውስጥ ምንም አጠቃላይ መመሪያዎች የሉም ፣ ምክንያቱም እያንዳንዱ ልዩ ነፍስ የሚፈልገው መንፈሳዊ መመሪያ ሙሉ በሙሉ ግላዊ ነው። እያንዳንዱ ሰው ከዚህ በፊት ታይቶ የማያውቅ፣ የተለየ የሥነ-ልቦና-ሳይንስ፣ የተለየ ባሕርይ፣ የተለያየ አቅምና ችሎታ፣ ውስንነቶች፣ ዝንባሌዎች፣ መቻቻል፣ እውቀት፣ ፍላጎቶችና ዝንባሌዎች አሉት። በእግዚአብሔር ጸጋና በመለኮታዊ መገለጥ፣ የተናዘዘው ሰው በተሻለ መንገድ እንዲረዳው፣ በተሻለ መንገድ ሊጠቀምበት የሚችለውን ለመወሰን፣ እነዚህን ሁሉ ባሕርያት መለየት አለበት። አንዳንድ ጊዜ፣ ገርነት፣ በሌላ ጊዜ ደግሞ መቆጠብ (ቁጥብ መሆን) ያስፈልጋል።

ለእያንዳንዱ ሰው ተመሳሳይ ነገር አይተገበርም። ካህኑ ሁል ጊዜ ጥብቅ መሆን የለበትምየብዙዎች መንፈሳዊ አባትተብሎ ለመቆጠር ሁል ጊዜ ከልክ ያለፈ ቸልተኛም መሆን የለበትም። ከእርሱ የሚጠበቀው እግዚአብሔርን መፍራት፣ ማስተዋል፣ ሐቀኝነት፣ በትኅትና፣ በትጋት መምከርና ጸሎት ነው።

ይቆየን

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

 

Wednesday, 12 June 2024

ኦርቶዶክሳዊ የንስሐ ሕይወት (ክፍል ሦስት)

 

በዲያቆን ያሬድ መለሰ

ለአስታየትዎ ymelese04@gmail.comን ይጠቀሙ

ውድ ኦርቶዶክሳዊያን በክፍል ሁለት የንስሐ ሦስቱ ደረጃዎችና የንስሐ ጥቅም(አስፈላጊነትን) በተመለከተ ለማየት ሞክረናል በዚህ ክፍል ኃጢአትን መናዘዝ(ኑዛዜ)ና የኑዛዜ ምንነትና ጥቅም? በጥቂቱ እንላለን፡፡ መልካም ንባብ

የኑዛዜ ምንነትና ጥቅም?

ኑዛዜ በሚለው ቃል በግሪክኛው ሆሞሎጊያ Homologeia ሁለት ቃላትን ያቀፈ ነው። ሆሞ "ተመሳሳይ" እና ሎጊያ "ቃል" ማለት ነው። መናዘዝ ከክርስቶስ ጋር ሐሳብና ቃል ጋር መስማማት ነው ይህም ክርስቶስ የገለጠውን መግለጥ ክርስቶስ የሰበከውን መስበክ ማለት ነው።

ኑዛዜ ሁለት ዓይነት እንዳለው ተናግረናል፡- የእምነት መናዘዝ እና ኃጢአትን መናዘዝ። የመጀመሪያው የቤተክርስቲያንን እምነት በተመሳሳይ ቃላት በማወጅ የሚገለጽ ነው። ይህ ደግሞ በቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ አምልኮ ሕይወት ውስጥ በግልጽ ይታወቃል። "በእውነት በአንድ አምላክ እናምናለን"! እኛም እምነታችንን ለመግለጽ በቤተክርስቲያን የሠራችልንን ተመሳሳይ ቃል እንጠቀማለን፤ ጌታችን እንዳለ "ደግሞ እላችኋለሁ፥ በሰው ፊት የሚመሰክርልኝ ሁሉ፥ የሰው ልጅ ደግሞ በእግዚአብሔር መላእክት ፊት ይመሰክርለታል።"(ሉቃ. 12:8)

ኢየሱስ ጌታ እንደ ሆነ በአፍህ ብትመሰክር እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልብህ ብታምን ትድናለህና።በልቡ አምኖ ይጸድቃልና በአፉም መስክሮ ይድናልና። (ሮሜ 10:9-10)

ሁለተኛው ዓይነት ኑዛዜ ኃጢአትን መናዘዝ ነው። ስለራሳችን መናዘዝ…...ያለ ሰበብ፣ ያለማስረጃ ወይም ያለማሳመር ኃጢአቴን በእውነት መናዘዝና ምን እንደሆነ ልጠራው እችላለሁ! ዋሽቻለሁ፣ ሰርቄአለሁ፣ ተመኝቻለሁ፣ በሰው ላይ ክፋትን ሰርቻለሁ ወይም ለመሥራት አስቢለሁ፣…. ወዘተ.

ዲያቢሎስ ስለ ድርጊታችን፣ ሀሳባችን እና ሕይወታችን ስንናገር ሁላችንም የተለያዩ ቃላትን እንድንጠቀም ስለሚፈትነን መጠንቀቅ አለብን። ኃጢአትን በእውነት ነው ብሎ ከመጥራት ይልቅ የተለያዩ ቃላት እንድንጠቀም ይፈትነናል። ፍትወትን ሸፍኖ ፍቅር ይለዋል። ስግብግብነትን አስመስሎ ምኞት ይለዋል። ትዕቢትን ይሸፍናልና በራስ መተማመን ይለዋል ሆኖም እኛ እንደ ክርስቲያኖች እውነትን ለመስበክ ደፋር መሆን አለብን፣ እናም በዚህ ምክንያት ኃጢአትን በኃጢአት ስሙ መጥራት ይገባናል።

ኃጢአትን መናዘዝ

ኑዛዜ (ኃጢአትን መናዘዝ) አራት መሠረታዊ ነጥቦችን ያጠቃልላል፡፡ አንደኛው ኃጢያትን ለራስ ሕሊና መናዘዝ ኹለተኛው በጸሎት በደልን ለእግዚአብሔር መናዘዝ ሦስተኛ በደልን ለካህን መናዘዝ አራተኛው ለበደሉት ሰው መናዘዝ ናቸው፡፡

·         ኃጢያትን ለራስ ሕሊና መናዘዝ

ኃጢያትን በመናዘዝ ውስጥ የመጀመርያው ደረጃ ኃጢያትን ለራስ ሕሊና መናዘዝ ነው፡፡ የሰው ልጅን እግዚአብሔር ሲፈጥረው ማመዛዘን የሚችልበትን አእምሮ ሰጥቶ ፈጥሮታል ስለዚህም ይህ ሕሊና ለሰው ልጅ ሲበድል ወቃሹ እውነተኛ ዳኛ ነው፡፡ ሕግ ተሰርቶልን ኦሪትንና ወንጌልን ሳናውቅ በፊት ክፉውን ከበጎ እንድንለይበት እግዚአብሔር በድንቅ አፈጣጠሩ ፈጥሮልናል፡፡ ሰዎች ታዲያ ክፉ ሲያደርጉ ይወቅሳቸው ዘንድ በጎ ሲሰሩ ያበረታቸው ዘንድ፡፡ በጎ ሕሊና ያለው ሰው ኃጢያት በሰራ ጊዜ ኃጠያቱን እንደሰራ ያምናል፡፡ ለራሱም ኃጢያቱን አምኖ ይናዘዛል በድያለኹ ይላል ይህም የንስሐ የመጀመርያው ደረጃ ነው፡፡ታላቁ መቃርስ እንዳለን ኃጢያትን ለራስ መናዘዝ እግዚአብሔር ሳይፈርድብን አስቀድመን ራሳችን ላይ መፍረድ ነው፡፡ በቅዱስ ወንጌል ተጽፎ የምናገኘው የጠፋው ልጅ ወደ ልቡ ተመልሶ እንዳለ ‹‹ እንጀራ የሚተርፋቸው የአባቴ ሙያተኞች ስንት ናቸው እኔ ግን ከዚህ በረኃብ እጠፋለሁ፡፡ ተነስቼም ወደ አባቴ እሄዳለሁና፡፡ አባቴ ሆይ በሰማይና በምድር በደልኹ ወደ ፊትም ልጅ እባል ዘንድ አይገባኝም ከሞያተኞትህ እንዳንዱ አድርገኝ እለዋለኹ›› ብሎ ኃጢያትን በቅድሚያ ለራስ እንደተናዘዘ እንዲሁ እኛም ከኹሉ በፊት ኃጢያታችንን በማመን እንናዘዝ ዘንድ ይገባል፡፡ (ሉቃ 15፥17-19)

·         በጸሎት በደልን ለእግዚአብሔር መናዘዝ

ኃጢያት መስራት በመጀመርያ ደረጃ እግዚአብሔርን መበደል(ማሳዘን) ስለሆነ ለእግዚአብሔር መናዘዝ ይገባናል፡፡ ቅዱስ ዳዊት በኃጢያት በወደቀ ጊዜ እንዲህ አለ ‹‹ አንተን ብቻ በደልኩ በፊትህም ክፉን አደረኹ›› (መዝ 50፥4) ነቢዩ ዳንኤልም በጸሎቱ እንዲህ አለ ‹‹ አምላክ ሆይ ኃጢያትን ሰርተናልና በድለንማል ክፍትም አድርገናል አምጸናል ከትእዛዝህና ከፍርድህም ፈቀቅ ብለናል፡፡›› እንዳለ (ት. ዳን 9፥5) እንዲሁ እኛም የእነዚህን ታላላቅ አባቶች ጸሎት ጸሎታችን እናደርግ ዘንድ ይገባናል፡፡


 

·         በደልን ለካህን መናዘዝ

የእግዚአብሔር እንደራሴ በሆነ አገልጋይ ፊት መናዘዝ በእግዚአብሔር ፊት መናዘዝ ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ እንደምናነበው ኢያሱ አካንን ‹‹ልጄ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ክብርን ስጥ ለእርሱም ተናዘዝ ያደረከውንም ንገረኝ አትሸሽገኝ›› (ኢያ 7፥19) እንዲሁም ወደ መጥምቁ ዮሐንስ የመጡ ኹሉ ኃጢያታቸውን እየተናዘዙ የንስሐ ጥምቀት ተጠምቀዋል፡፡ (ማቴ 3፥6) በሐዋርያት አገልግሎትም ያመኑ ብዙ ሰዎች ኃጢያታቸውን ይናዘዙ ነበር (ሐዋ 19፥18)

ካህኑ ፊት ኃጢያትን መናዘዝ አንደኛ በካህኑ ፊት የተናዘዘውን ኃጢያት ዳግም እንዳይሰራ መንፈሳዊ ብርታት ይሆነዋል፡፡ ኹለት ፍጹም የኃጢያት ሥርየት የሚገኝበትን ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ለመቀበል የሚያስችል ፍቃድ ያገኛል፡፡

ኃጢአታችን ለካህን መናገር ለምን አስፈለገ?

ብዙ ሰዎች ኃጢአታቸውን ለካህን ለመናገር ስለሚያፍሩ ኑዛዜን ይርቃሉ።እግዚአብሔር ሁሉን አዋቂ ነው ኃጢአቴን ሁሉ ያውቃል ለካህኑ መናዘዝ ኃጢአቴን ለሚያውቀው ጌታ መንገር ለምን ያስፈልጋል? የሚል አመለካከት ይይዛሉ፣ በመሠረቱ ኃጢአት የሰራ ሰው የሚያብለው የእግዚአብሔርን ሀልዎት ነው በሕይወታችን ሁሉ እግዚአብሔር እንዳለ ካመንንና ካወቅን ኃጢአት ባልሰራን ነበር። ኃጢአቴን ለሚያውቀው ጌታ መንገር ነው የሚል ሰው ይህንን አስተሳሰቡንና አመለካከቱን ኃጢአት ከመሥራቱ በፊት ቢያምንና ቢያውቅ በኃጢአት ባልወደቀ በነበር….

ኃጢአታችንን ለካህናት የምንናዘዘው ካህናት ኃጢአትን የማስተሥረይ ሥልጣን ጌታችን ስለሰጣቸው ነው

ጌታችን ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱንና ቅዱሳን ሐዋርያትን ወደ ዓለም ሄደው አገልግሎታቸውን እንዲጀምሩ ሲያዘጋጃቸው ጌታ በሚገለጥበት ጊዜ ይነግራቸዋል። ከትንሣኤው በኋላ ለእነርሱ፡- “ኢየሱስም ደግሞ፡— ሰላም ለእናንተ ይሁን! አብ እንደ ላከኝ እኔ ደግሞ እልካችኋለሁ። ይህንም ብሎ እፍ አለባቸውና መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ አላቸው። የአንዱን ኃጢአት ይቅር ብትሉ ይሰረይላቸዋል የአንዱንም ኃጢአት ብትይዙ ተይዟል።” ዮሐ 20፡21-23

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ‹‹ካህኑ እግዚአብሔር ለመላእክትና ለመላእክት አለቆች ያልሰጠውን ሥልጣን ተቀብሏል። ……እግዚአብሔር የሰማያትን ሥልጣን ሁሉ አልሰጣቸውምን? ኃጢአታቸውን ይቅር የምትላቸው ይቅር የባልላቸዋል ኃጢአታቸው የያዛችሁባቸው ተይዟል ይላል። ከዚህ የበለጠ ምን ኃይል አለ። አብ ፍርድን ሁሉ ለወልድ ሰጠው አሁን ወልድ ይህንን ሁሉ ስልጣን በሰዎች እጅ ለካህናቱ ሰጠ። ….››

·         ኃጢያትን ለበደሉት ሰው መናዘዝ

ይህን ማድረግ የራስብ ልብ ለማስተካከልና ለማረጋጋት ከተበደለው ሰው ጋርም እርቅን ለመመሥረት ይረዳናል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹በመሰዊያው ፊት መባህን አስቀምጠህ ሂድ አስቀድመህ ከወንድምህ ታረቅ ከዛ በኋላ መስዋዕትን ታቀርባለህ›› እንዳለን (ማቴ 5፥24) አስቀድመን ወደ በደልነው ሰው በመሄድ በድያለሁና ይቅር በለኝ ማለት ይገባል፡፡ አባቶቻችን ሳል ይዞ ስርቆት ቂም ይዞ ጸሎት አስሰምርም እንዲሉ በቅዱስ ቃሉ መሠረት ያስቀየምነውን ይቅር ማለት ይገባናል፡፡

 

ይቆየን

ወስብሐት ለእግዚአብሔር