በዲያቆን ያሬድ መለሰ
ለአስታየትዎ ymelese04@gmail.comን ይጠቀሙ
ውድ ኦርቶዶክሳዊያን በክፍል ሦስት ኃጢአትን መናዘዝ(ኑዛዜ)ና የኑዛዜ ምንነትና ጥቅም?
በተመለከተ ለማየት ሞክረናል በዚህ ክፍል ንስሐና ኃጢአትን መናዘዝ(ኑዛዜ)ና የካህናት ድርሻ በንስሐና በኑዛዜ በተመለከተ በጥቂቱ
እንላለን፡፡ መልካም ንባብ
ንስሐና ኃጢአትን መናዘዝ(ኑዛዜ)
ኑዛዜ ከእግዚአብሔር የተሰጠ ትእዛዝ ነው፣ እርሱም ከቤተ ክርስቲያናችን ምሥጢራት አንዱ ነው። ኑዛዜ ሁል
ጊዜ ከንሰሐ ጋር መቀላቀል አለበት። አንድ ኦርቶዶክሳዊ አረጋዊ አባት እንዳለ “ብዙዎች ይናዘዛሉ፣ ንስሐ የገቡ ግን ጥቂቶች ናቸው!” ይላቸው ነበር። (Elder Aemilianos of
Simonopetra Monastery, Mt. Athos)
ንስሐ በራስ ፍቃድ እራሳችንን ከእግዚአብሔር ስለራቅን በውስጥ
የሚሰማ ልባዊ ስብራት ነው።
እውነተኛ
ንስሐ ከማይቋቋሙት ስቃይ፣ ከመጠን ያለፈ ኃዘንና የማያቋርጥ የጥፋተኝነት ስሜት ጋር ምንም ግንኙነት የለውም። ያ እውነተኛ ንስሐ ሳይሆን በውስጣችን ያለ የትምክህተኝነት ስሜት ነው። በራሳችን ላይ ያነጣጠረ ቁጣ ራሱን ስለሚያጋልጥና ስለሚያሳፍረው የበቀል እርምጃ ይወስዳል። በይሁዳ የሆነው ይህ ነው።
ለድርጊታችን የሚሰማን የጸጸት እና የኃዘን ስሜት፤ በተለይ በእንባ ታጅቦ ለነፍሳችን መዳን የመጀመሪያ እርምጃ
ነው። ቁስላችን መክፈትና እውነተኛ መድኃኒት መሻት ደግሞ ቀጣይ እርምጃ ሊሆን ይገባል፡፡ ከዚህ ውጭ ግን ማድረግ ቁስሉ እየጠነከረና
እየተስፋፋ ትልቅ ጉዳት ሊያደርስብን ይችላል ማለት ነው።
ጸጸት ጥሩ ጅምር ቢሆንም፣ መጸጸቱ ብቻ በቂ አይደለም። ይሁዳ ጌታችንን ከዳ በኋላ በድርጊቱ አዘነ። በጣም አዝኖ
የደም ገንዘቡን መልሶ ወጣና ራሱን ሰቀለ። ኀዘኑ እዚያ ቆመ እና ወደ ንስሐ አላበበም። ጴጥሮስም ወድቆ አዝኖ ነበር፣ ነገር ግን
በዚህ ብቻ አላቆመም። ወደ ክርስቶስ ተመለሰ።
ንስሐ ማለት የአስተሳሰብ፣ የአመለካከት ለውጥ ማለት ነው፤ ሥነ ምግባርን መከተብና ኃጢአትን መጥላት ነው። ንስሐ መግባት ማለት በሁሉን ቻይ በሆነው መንፈስ ቅዱስ ጸጋ አማካኝነት ፍላጎትን፣ ፍቃደኝነትንና ከክርስቶስ ኅብረት ጋር እንደገና ለመቀላቀል መሻት(መፈለግ) ማለት ነው። ንስሐ የሚጀመረው ከልብ ነው፣ ነገር ግን በመለኮታዊና ቅዱስ ኑዛዜ ታግዞ በመጨረሻም በቅዱስ ቁርባን በመሳተፍ ያበቃል።
በኑዛዜ ወቅት፣ አንድ ሰው
በክርስቶስ
ፊት እንዳለ ሆኖ በቅንነትና በትኅትና በካህኑ ፊት ይናዘዛል። የትኛውም ሳይንቲስት፣ ሳይኮሎጂስት፣ ሳይኮአናሊስት፣ ሳይካትሪስት፣ ሶሺዮሎጂስት ወይም
ፈላስፋ ካህኑን ሊተካ አይችልም።
የካህናት ድርሻ በንስሐና በኑዛዜ
የካህኑ
አገልግሎት ኃጢአትን ማስተስረይ መንፈሳዊ ልጁን ተቀብሎ የተበጠሰውን(የደፈረሰውን) ኅብረት ማስተካከልና ዳግም ማደስ ነው። የትኛውም
ሰው ቢሆን ካህኑን ሊተካ አይችልም። ለዚህም ነው መንፈሳዊ
አባት፣አበ ነፍስ ወይም የንስሐ አባት ተብሎ የሚጠራው። በካህኑና በንስሐ ልጁ መካከል ያለው ግንኙነት ከቤተሰብ ትስስር
በላይ ነው።የንስሐ ልጁን እግዚአብሔርን በመፍራት፣ በማስተዋል፣ በትኅትናና በፍቅር መከታተል የመንፈሳዊ ሕይወት ጎዳናውን በጥንቃቄ
መምራት አለበት።
ካህኑ
ምሥጢረ ንስሐን ጨምሮ ቅዱሳት ምሥጢራትን የሚፈጽመው በተሰጠው የክህነት ፀጋ እንጂ ባለው መንፈሳዊ እውቀት፣ጥበብ፣ የሳይንስ እውቀት፣ የመጻፍ ችሎታ፣ አንደበተ ርቱዕነት(የስብከት የንግግር ችሎታ) አሊያም
ጉልበት አይደለም። (ማቴ. 18፥18 ማቴ. 16፥17 ማቴ. 10፥8) በበጎነቱና በቅድስናው እንኳን አይደለም በክህነቱ ፀጋ
በመንፈስ ቅዱስ በኩል እንጂ።
የክህነት ፀጋ
ካህኑ
በሚሰራው ኃጢያት የተሰጠውን መለኮታዊ የክህነት ጸጋን አያጎድፈውም። የምግባር ጉድለት ቢኖርበት በሠራው ሁሉ ተጠያቂ መሆኑ እንደተጠበቀ
ሆኖ ግን ክህነቱ አይጎድፍም ይህ ማለት ግን ለራሱ ንጽሕና መጨነቅ የለበትም ማለት አይደለም። በፍትሐ ነገሥት ላይ ‹‹እስመ ካሕን
ሕጹጸ ምግባር ከመ ማኅቶት ዘሰምዕ ውእቱ›› ምግባር የጎደለው ካህን እንደሰም መብራት ነው ይላል።የሚነደው እሳት በክህነቱ ይመሰላል
እሳቱ ሰሙን ያቀልጠወል ለሕዝቡ ግን ያበራል ከብርሃኑ የተነሣ ጨለማ አያገኛቸውም፡፡ (ፍ. ነገሥት መን. 9፥1) ኃጢአተኛ ካህንም
በኃጢአቱ እራሱን ቢጎዳም ለምእመናን ግን እርሱ ያላገኘው ጸጋና በረከት እንዲያገኙ የሚያደርግበት ሥልጣን አለው፡፡
በካህናት
ምግባር ከካህናት መሸሽ አይገባም የራስን በደልና ኃጢአት ማሰብ እንጂ። ለዚህም ይህ ታሪክ ያስረዳናል ‹‹አንድ ባለጠጋ ገበሬ ነበረው፡፡ ይህን ገበሬ ‹‹ሂድና የንስሐ አባቴን
ርስት እረስ ብሎ›› ይልከዋል፡፡ ይህም ገበሬ ከመምህረ ንስሐው ርስት ሆኖ ሲያርስ ድስት ሙሉ ወርቅ ያገኝና ሄዶ ለባለጸጋው ይነግረዋል፡፡
እርሱም ‹ለእኔ ለምን ነገርከኝ እኛማ ርስቱን ማረሳችን አርሰን ልንበላ አይደለምን? ወርቅ ለባለ ርስት ነው በል ለእርሱ ንገረው
ነገር ግን ለእኔ ነገርሁት አትበል ይጣላሃል›› አለው፡፡ ሄዶ ነገረው ያም ቄስ ‹‹የምናወጣበትን ስታሰናዳ ቆየኝ›› ብሎ እርሱን
ሰዶ ሰይፉን ሲስል አመሸ፡፡ ሄደው ቆፍረው ወርቁን ካወጡ በኋላ አንገቱን በሰይፍ ብሎ ገድሎታል። ወርቁም ደም ተፈንጥቆ ቢያርፍበት
ብረት ሆኖል፡፡ ያ ባለጸጋ ካሁን ከአሁን ይመጣል ብሎ ሲጠባበቅ ቀረ፡፡ ምን ሆኖ ይሆን እያለ እየፈለገ ሲሄድ ዐሠረ ደም አገኘ፡፡
‹‹ያ ክፉ ተጣለልቶታል ልጣለው›› ብሎ አሰበ፡፡ መልሶ ‹‹ምን እዳዬ አንተም አንድ ጊዜ ብጹዓን አግብርት ከተባሉት ተቆጥረሃል።
እኔም ከእንግዲህ በቄስ እጅ ሥጋ ወደሙን አልቀበልም ከቤተ እግዚአብሔርም አልሄድም›› ብሎ ከመሄድ ተከለከለ።
በኋላ መልአክ የምታየው ነገር አለና ወደ ቤተ
ክርስቲያን ውጣ አለው፡፡ ሰይጣን በዚህ ቄስ እጅ ላይ ሆኖ በእሳት ልጓም ለጉሞ በእሳት አለንጋ እየገረፈ ይዞት ሲወጣ አየ፡፡ ካህኑ
ከቤተ እግዚአብሔር ሲገባ ሰይጣኑ ሲወርድለት ሥራውን ሠርቶ ሲወጣ እንቀድሞ በላይ ላይ ሆኖ በእሳት ልጓም ለጉሞ በእሳት አለንጋ
እየገረፈ ይዞት ሲሄድ አይቶ ለካስ ቅዱስ ጳውሎስ ሁሉም የራሱን ሸክም ይሸከማል ያለው ለዚህ ነው (ገላ. 6፥4) ›› ብሏል ዳግመኛም
የወርቅ ገደል (ውሃው የሚያርፍበት ወርቅ ማንኪያው የወርቅ ሆኖ አንድ እጁ የቆደለ ድውይ ጠጣ ሲለው ተጸይፎ አልጠጣም ሲል‹‹ ምነዋ
ላይ እታቹ የወርቅ ማንኪያው የወርቅ ጠጣ እንጂ›› ብሎ ተጸጽቶ ሥጋ ወደሙን የሚቀበል ሆኗል፡፡›› ከዚህ ታሪክ እንደምንረዳው በካህናት ሰበብ
ከእግዚአብሔር ጸጋ መራቆት እንደማይገባ ነው።
የንስሐ አባትና የንስሐ
ልጅ ግንኙነት
ካህኑ
የንስሐ ልጁን በቅጽበት ለመለወጥ መጨነቅ የለበትም።ይህ ዓይነቱ ግንዛቤ(ዝንባሌ) መንፈሳዊ ብስለት የጎደለው ነው። የንስሐ ልጁን
ማስገደድ ለመንፈሳዊ ዓላማና ጉዳይ እንኳን ግድ ማለት ከልክ በላይ መጫን የንስሐ ልጁ የታሰረና የበላይ ሹማምንት ስር ያለ ባርያ
እንደሆነ እንዲያስብ ሊያደርገው ይችላል። ካህኑ እንደመንፈሳዊ አባትነቱ መንፈሳዊ ልጅን መውለድ የሚያደክም አገልገሎት እንደሆነ
መገንዘብና ከዚህ በተጨማሪ ለመንፈሳዊ ልጁ መንፈሳዊ እድገት እና ለቤተክርስቲያን ኅብረት መጸለይ ይገባዋል ።
የካህኑ
ሥራ የአንድን ሰው ኃጢአት በውጫዊ ሁኔታ(በሚገልጸው መጠን) መስማትና ከዚያ በኋላ ጸሎተ ኑዛዜን (ጸሎተ ፍትሐት) መጸለይ ብቻ
አይደለም። ክትትሉም በኑዛዜ ሰዓት ብቻም የተገደበ አይደለም። ልክ እንደ ጥሩ አባት ልጁን ያለማቋረጥ ይንከባከባል፣እርሱን ያዳምጠዋል በጥንቃቄ ይከታተለዋል፣ በትክክል ይመክረዋል፣ በወንጌል መስመር
ይመራዋል፣ ችሎታውን ያጎላል፣ አላስፈላጊ ሸክሞችን አይጭንበትም፣ ቀኖናዎችን (ንስሐን) በገርነት ይጭናል፣ተስፋ ሲቆርጥ፣ ሲደክም፣
ሲከፋው፣ ያጽናናው በዚህ መሠረት ይፈውሳል፣ ተስፋ ሳይቆርጥ፣ ነገር ግን ፍላጎቱን ለማጥፋትና በጎነትን ለመሰብሰብ የሚያደርገውን
ትግል ያለማቋረጥ ይከታተል፤ ያለማቋረጥ ዘላለማዊ ነፍሱን ክርስቶስን እንድትመስል ለመቅረጽ ይተጋል።
ይህ
በየጊዜው በማደግ ላይ ያለው የአባት እና የልጅ ግንኙነት ያጠናክራል። በመጨረሻ በመካከላቸው መተባበር መተጋገዝ መከባበርን ይፈጥራል።
በሚናዘዙበት ጊዜ፣ አንድ ሰው ለተናዛዡ ልቡን ይከፍታል የውስጡን ከራሱ ወይም ለቅርብ ዘመድ አልያም ለቅርብ ጓደኛው በቀር ለማንም
መንገር ሁሉንም ምስጢሮቹን፣ የኃጢያት ምኞቶቹን ጭምር ይናዘዛል።
በኦርቶዶክስ
ኑዛዜ ውስጥ ምንም አጠቃላይ መመሪያዎች የሉም ፣ ምክንያቱም እያንዳንዱ
ልዩ ነፍስ የሚፈልገው መንፈሳዊ መመሪያ ሙሉ በሙሉ ግላዊ ነው። እያንዳንዱ ሰው ከዚህ በፊት ታይቶ የማያውቅ፣ የተለየ የሥነ-ልቦና-ሳይንስ፣
የተለየ ባሕርይ፣ የተለያየ አቅምና ችሎታ፣ ውስንነቶች፣ ዝንባሌዎች፣ መቻቻል፣ እውቀት፣ ፍላጎቶችና ዝንባሌዎች አሉት። በእግዚአብሔር
ጸጋና በመለኮታዊ መገለጥ፣ የተናዘዘው ሰው በተሻለ መንገድ እንዲረዳው፣ በተሻለ መንገድ ሊጠቀምበት የሚችለውን ለመወሰን፣ እነዚህን
ሁሉ ባሕርያት መለየት አለበት። አንዳንድ ጊዜ፣ ገርነት፣ በሌላ ጊዜ ደግሞ መቆጠብ (ቁጥብ መሆን) ያስፈልጋል።
ለእያንዳንዱ ሰው ተመሳሳይ ነገር አይተገበርም። ካህኑ ሁል ጊዜ ጥብቅ መሆን የለበትም “የብዙዎች መንፈሳዊ አባት” ተብሎ ለመቆጠር ሁል ጊዜ ከልክ ያለፈ ቸልተኛም መሆን የለበትም። ከእርሱ የሚጠበቀው እግዚአብሔርን መፍራት፣ ማስተዋል፣ ሐቀኝነት፣ በትኅትና፣ በትጋት መምከርና ጸሎት ነው።
ይቆየን
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
No comments:
Post a Comment