Wednesday, 30 April 2025

የምዕራቡ ዓለም ክርስትና ፈተና፡ የጀርመን "ጳጳሳት"ና የተመሳሳይ ጾታ "ጋብቻ" ቡራኬ

 ቤተ ሐዋርያት

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ፣ በምዕራቡ የክርስቲያን ዓለም ብዙ ለውጦችን አይተናል። ከእነዚህ ለውጦች መካከል አንዳንዶቹ ወደ እውነተኛው የወንጌል እውነት ከመመለስ ይልቅ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ከተገለጠው የማይለወጥ እውነት የራቁ ይመስላሉ።

በተለይ አሳዛኝ ክስተት የጀርመን የካቶሊክ "ጳጳሳት" የተመሳሳይ ጾታ "ጋብቻን" ቡራኬ መስጠትና "ጋብቻው"ን እንደቅዱስ ጋብቻ ለመቀበል ለማጽደቅ የወሰኑት ውሳኔ ነው። እንደዘገበው፣ ከ2026 ጀምሮ፣ እነዚህ ቡራኬያት በይፋ ተግባራዊ ይሆናሉ። ፖፕ ፍራንሲስ በሕይወት ዘመን ይህንን በመጠኑ ለመቀበል ተገ
ዋል። በእርሳቸው ዘመን ካቶሊካዊያን ካህናት ተመሳሳይ ጾታ ላሉ ሰዎች ቡራኬ እንዲሰጡ ጋብቻውን ግን እንዳይባርኩ ጋብቻቸውም በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን(ቅዳሴ) እንዳይፈጽሙ ለመከልከል ችለው ነበር። የጀርመን ጳጳሳት ግን ይህ ሁሉ እንዲሆን በአብላጫ ድምጽ ወስነው ነበር።

ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ጋብቻ በእግዚአብሔር በራሱ የተመሠረተ፣ በአንድ ወንድና በአንዲት ሴት መካከል ያለ አንድነት፣ የክርስቶስንና የቤተክርስቲያኑን አንድነት የሚያንጸባርቅ ቅዱስ ምሥጢር  እንደሆነ ታስተምራለች (ኤፌ. 5፥32)። ጋብቻ እንደፈለግን የሚቀያየር ወይም የሚለወጥ  ባሕል ወይም የሰው ፈጠራ አይደለም።ቅዱስ ጋብቻ የተለየ ዓላማ ያለው መለኮታዊ ተቋም ነው በዚህም የትዳር አጋሮች መዳንና ልጆችን በእምነት ማሳደግ ሁሉ የሚያካት ነው። 

ከቅዱሳት መጻሕፍትና ከቅዱሳን ትውፊት ትምህርት ጋር የሚቃረኑ ግንኙነቶች ሁሉ የበረከት የፍቅር ተግባር ሊሆኑ አይችሉም  ይህ አሳዛኝ ማታለል ነው። ክብር ይግባውና ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም እንዲህ ብሏል፡-

"እርሱ ግን መልሶ እንዲህ አለ፦ ፈጣሪ በመጀመሪያ ወንድና ሴት አደረጋቸው፥ አለም፦ ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፥ ከሚስቱም ጋር ይተባበራል፥ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ የሚለውን ቃል አላነበባችሁምን?" ( ማቴ. 19:4-5 )

ከተቀደሰው የጋብቻ ማሰሪያ ውጭ ያለውን ማንኛውንም ዓይነት  ግንኙነትን መባረክ ኃጢአትን መባረክ ነው ይህም ወደሞት ያመራል። (ያዕ. 1፡15)። ምንም ያህል "ነገረ መለኮታዊ" ፈጠራ ወይም የ"ሲኖዶስ" ድምጽ የእግዚአብሔርን ቃል መሻር አይችልምና።

የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሰዎች ሁሉ ተጋድሎአቸው ወይም ፈተናቸው ምንም ይሁን ምን ከእግዚአብሔር ጋር በንስሐ ትጠራለች። ከተመሳሳይ ጾታ ፍላጎት ጋር የሚታገሉትን አንጠላቸውም። ይልቁንም ክርስቶስ ለኃጢአተኞች ሁሉ ባቀረበው የቅድስና ሕይወት እንድንጠራቸው እንወዳቸዋለን፤ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ እንዳለ “ኃጢአተኞችን ሊያድን ክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዓለም መጣ የሚለው ቃል የታመነና ሁሉ እንዲቀበሉት የተገባ ነው፤ ከኃጢአተኞችም ዋና እኔ ነኝ፤” (1ኛ ጢሞ 1፡15)።

በተለይ በጀርመን ላሉ ይህን አደገኛ መንገድ ለተቀበሉ ለካቶሊክ ወንድሞቻችን አጥብቀን መጸለይ አለብን። ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ወደ ተሰጥተው እውነተኛ ሃይማኖት ለመመለስ ድፍረትን እንዲያገኙ ስለ መሪዎቻቸው መጸለይም ይገባናል (ይሁ. 1፥3)።

ስለ ፍቅር፣ ትዳር እና እውነት ግራ መጋባት በበዛበት ዓለም እንደ ኦርቶዶክሳዊት እምነት ተከታዮች በትኅትናና በፍቅር ጸንተን እግዚአብሔር ለሰው ልጅ የፈጠረውን ውበት እየመሰከርን ለእግዚአብሔር ምስክሮች እንድንሆን አምላከ ቅዱሳን ይፍቀድልን።

እግዚአብሔር ሁላችንንም በምሕረቱ ይጎብኘን።

No comments:

Post a Comment