Thursday, 25 September 2025

የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮትን…. እንደ መስቀል እንሸክም (1ኛ ዮሐ. 2፡15-16)

 

በቀሲስ ያሬድ መለሰ

እግዚአብሔር ሰውን ሲፈጥረው በልቡ ውስጥ መልካሙን ከክፉ የሚለይበትን ሕሊናና መንገዱን የመምረጥ ነጻነት ሰጥቶታል። በዚህ ስጦታ ሰው ወደ ፈጣሪው መቅረብ ወይም ከእሱ መራቅ ይችላል። ለሰው ልጅ ከተሰጡት ታላላቅ ኃይሎች መካከል ምኞት አንዱ ነው። መመኘት በራሱ ክፉ አይደለም ምኞት እንደእሳት ያለ ነው ልንሞቀውና ሕይወት ሊሰጥን አልያም ሊያቃጥለንና ሊያጠፋን የሚችል ነው። በክርስትና ሕይወት ይህንን ምኞታችን እንደ መስቀል ተሸክም በክርስቶስ ታዛዥነት ሥር ማድረግ ታላቅ ተጋድሎን የሚፈልግ ጉዳይ ነው።

ምኞት ምንድን ነው?

ምኞት በራሱ ተፈጥሯዊ ነው። ምኞቱ ክፉም በጎም ሊሆን ይችላል።በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ ምኞት ሁለት ገጽታዎች አሉት። በአንድኛ ምኞት የእግዚአብሔር የተፈጥሮ ስጦታ ነው። ያለ ፍላጎት ሰው ምግብን፣ ፍቅርን፣ እውቀትን፣ ወይም እራሱን እግዚአብሔርን እንኳን አይፈልግም።(መዝ. 42፡1) በሌላ በኩል፣ ምኞት ሲታወክ እና ከእግዚአብሔር ፈቃድ ሲርቅ፣ ወደ ሥጋ ምኞትነት ይለወጣል ይህም የምኞት ሁለተኛው ገጽ ነው። ይህም ነፍስን ባሪያ የሚያደርግና ወደ ኃጢአት የሚመራ ነው። ምኞት ሲበላሽና ሲሳሳት፣ ነፍስን በባርነት የሚገዛ ፍትወት ይሆናል።

እግዚአብሔርን የመፈለግ እርሱን የመምሰል ምኞት በጎ ምኞት ነው።  ነገር ግን ይህ ምኞት ከእግዚአብሔር ፈቃድ ውጭ ሲሆን ይጣመማል በራሳችን ምኞት ስንሳብና ስንታለል እንፈተናለን። ሐዋርያው ​​ያዕቆብ እንዳለን "እያንዳንዱ በራሱ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ይፈተናል፡ ምኞት ፀንሳ ኃጢአትን ትወልዳለች፡ ኃጢአትም ካደገች በኋላ ሞትን ትወልዳለች" (ያዕ. 1፡14-15) ። ስለዚህ ምኞት ወደ ራስ ወዳድነት፣ ልንቆጣጥረው ወደ የማንችለውና የእግዚአብሔርን ሕግ ጋር ወደ የሚጻረር ምኞት ሊለወጥ ይችላል። ይህም ሐዋርያው እንዳለው ወደ ኃጢአትና ሞት ይወስደናል።

የሥጋ ምኞት

ነባቤ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ሦስት ዋና ዋና የኃጢአት ምኞት ምድቦችን ለይቷል። "ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ፤ ማንም ዓለምን ቢወድ የአባት ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም፤ ምክንያቱም በዓለም ያለው ሁሉ እርሱም የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት ስለ ገንዘብም መመካት ከዓለም ስለ ሆነ እንጂ ከአብ አይደለም" (1ኛ ዮሐ. 2፡15-16) ።

እዚህ ላይ ሦስት ዓይነት የተዘበራረቀ ፍላጎት ተገልጧል፡ የሥጋ ምኞት (የሥጋ ደስታ) የዓይን አምሮት (ስግብግብነትና ምቀኝነት) እና የሕይወት ኩራት (ራስን ከፍ ከፍ ማድረግ) ዲያብሎስ በምድረ በዳ ወደ ጌታችን የቀረበባቸው ፈተናዎች እነዚህ ናቸው (ማቴ 41-11) ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን እነዚህን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዲያቢሎስ የተፈተነባቸውን ፈተናዎች «አርዕስተ ኃጣውዕ» በማለት ትጠራለች እነዚህም ስስት ፣ ትዕቢትና ፍቅረ ነዋይ ናቸው፡፡ እነዚህ ኃጢያቶች ‹‹ሦስቱን የኃጢያት አለቆች›› መባላቸውም የሁሉም ኃጢያቶች መገኛ ስለሆኑና እነዚህን ሦስቱ ኃጢያቶች ድል ያደረገ ሌሎቹንም ኃጢያቶች ድል ያደርጋልና ነው፡፡ ይህም ፍላጎትን የእግዚአብሔርን ቃል በመታዘዝ መምራት እንደሚቻል አሳይቶናል።


 

እግዚአብሔር የሥጋ አምሮትን ወደ በጎ ሐሳብ ይለውጥ ዘንድ የታመነ ነው

አንድ ሰው የሥጋ ምኞትን ሲተው እግዚአብሔር ባዶ አይተወውም። ከዚህ ይልቁንም መንፈስ ቅደስ ልቡን በቅዱስ ምኞት ይሞላል። ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለገላትያ ሰዎች በጻፈው መልዕክቱ በመንፈስ ተመላለሱ የሥጋንም ምኞት ከቶ አትፈጽሙ" (ገላ. 5:16)

ይህ ፍላጎታችንን እንድንገድብ ብቻ ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ ፀጋ ይህንን ሊለውጥ ጌታችን የታመነ መሆኑን ማወቅ ይገባናል የልቅ ፍቅርን ወደ ቅዱስና ንጽሕ ወደሆነ ፍቅር ይለወጣል። ገንዘብ ወዳድነትን ወደ ለጋስነት የሥልጣን ፍቅርን ወደ ትህትና ከምድራዊ ምኞት ወደ ሰማያዊ ፀጋን መፈለግና መሻት ይለውጥ ዘንድ የታመነ ነው። አስተውሉ እውነተኛ ምኞት ወደ ላይ የሚያደርስ መሰላል እንጂ ወደ ታች የሚጎትተን አይደለም።

የሥጋ ምኞትን እንደ መስቀል መሸከም

ጌታችን እንዲህ ብሏል፡- “ሊከተለኝ የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ” (ማቴ. 1624)

ምኞትየሚለውን ቃል ልብ በሉ። ክርስቶስን የመከተል ምርጫ እንኳን የሚጀምረው በምኞት ነው። ነገር ግን ይህ ፍላጎት ራስን በመካድ መንጻት አለበት። መስቀሉን ለማንሳት፡- “ጌታ ሆይ፣ ፈቃዴን፣ ምኞቴን፣ ሐሳቤን እሰጥሃለሁ፤ ደስ የሚያሰኝህ ብቻእኔ እንዲሆንበማለት የራስን ምኞት ክዶ በእርሱ ሐሳብ ለመኖር መሰናዳትን ይጠይቃል።

የግል ፍላጎቶቻችንን ለእግዚአብሔር አሳልፈን ስንሰጥ እርሱ ደግሞ ሰላሙን እንደሚሰጠን አባቶች ያስተምራሉ። ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ “ምኞት ማሸነፍ ሙታንን ከማስነሣት ይበልጣል” ይላል። እረፍት የሌለውን ልብ ከማስገዛት ተአምራት ማድረግ ይቀላልና። ስለዚህም ምኞትን መግዛት ትልቅ ተጋድሎን የሚጠይቅ ነው።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ "ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ብፁዓን ናቸው፥ ይጠግባሉና" (ማቴ 5፡6) ። ብሎ ለሚታመኑነት የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት ያስገዙትን ሁሉ በቅዱሱን ምኞት ሊሰጣቸው የታመነ ነው።

በሥጋ ምኞቶች ሲሰቀሉ በቅዱስ ምኞቶች የልባችንን ቦታ ይይዛሉ የጸሎት፣ የቅድስና፣ የንጽሕና፣ የምሕረት፣ የዘላለም ሕይወት ፍላጎት በልባችን ይሞላሉ። እነዚህ የመንፈስ ስጦታዎች እንጂ ሸክሞች አይደሉም። በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ፣ ፊት ለፊት ስለምናየው ቅዱሳን ምኞቶች ሁሉ ይፈጸማሉ (1ኛ ቆሮ. 13፡12) ።

ወድ ክርስቲያኖች የምኞት እሳትን አንናቅ ግን ወደ ክርስቶስ እናምራው። ምኞታችንን እንደ መስቀል በመታዘዝ መሠዊያ ላይ እናቅርባቸው። እርሱን ለማየት እንደወደደው እንደ አባታችን አብርሃም የእግዚአብሔርን ክብር ለማየት እንደናፈቀ እንደ ሊቀ ነቢያት ሙሴ (ዘጸ. 33፡18) ፤ ከሁሉ በላይ በእግዚአብሔር ቤቱን ሊሰራ እንደ ወደደ እንደልበ አምላክ ዳዊት (መዝ. 27፡4) ። ያዩና ይሰሙሰት ዘንድ የእርሱን መወለድ እንደናፈቁ ነቢያት፣ ክርስቶስን ለመከተል ሁሉን ትተው እንደተከተሉ እንደ ሐዋርያት (ሉቃ. 18፡28) ፤ ክርስቶስን በማወቁ ከሁሉ የላቀ ዋጋን ነገር ሁሉ እንደ ኪሳራ እንደ ቈጠረው እንደ ቅዱስ ጳውሎስ (ፊል. 3፡8) ለሥጋ ምኞት ሳይሆን እርሱን ለመምሰል እንመኝ ልክ እንደቅዱሳኑ እግዚአብሔር ልባቸውን በሰላም ሕይወታቸውንም ለዘለዓለም በሚኖር ፍሬ ሞላ። እግዚአብሔርንም "ከአንተ በቀር በሰማይ ያለኝ ማን ነው? በምድርም ላይ ከአንተ በቀር የምወደው ማንም የለም" (መዝ. 73:25) እንበለው። ለዚህም የእመቤታችን አማላጅነት የቅዱሳኑ ምልጃና ጸሎት ይርዳን።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር