Thursday, 25 September 2025

የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮትን…. እንደ መስቀል እንሸክም (1ኛ ዮሐ. 2፡15-16)

 

በቀሲስ ያሬድ መለሰ

እግዚአብሔር ሰውን በምድር ላይ ሲያበቅለው፣ በልቡ ጓዳ ውስጥ ብርሃንና ጨለማን የሚለይበትን የሕሊና ሚዛን አብሮ አስቀመጠ። ይህ የነጻነት ስጦታ ሰው ወደ ፈጣሪው ብርሃን የሚገሰግስበት ክንፍ፣ አሊያም ከእርሱ ርቆ የሚጠፋበት የገደል መንገድ እንዲሆን ተፈቅዶለታል። በሰው ሕይወት ውስጥ እንደ ማዕበል ከሚናወጡ ኃይሎች መካከል "ምኞት" ዋነኛው ነው።

ምኞት በራሱ ክፋት የለበትም፤ እርሱ እንደ እሳት ነው። በሥርዓት ከተያዘ ብርዱን የምናሸንፍበት የሕይወት ሙቀት ይሆነናል፤ ካልተገራ ግን ሕይወታችንን አመድ አድርጎ የሚያጠፋ ሰደድ እሳት ነው። በክርስትና ተጋድሎ ውስጥ ይህንን እሳታዊ ምኞት እንደ መስቀል ተሸክሞ፣ በክርስቶስ ታዛዥነትና ፍቅር መገራት ታላቅ መንፈሳዊ ጀግንነትን ይጠይቃል። ምኞታችንን በክርስቶስ ፊት ማስተንፈስና ለፈቃዱ ማስገዛት፣ እሳቱን ወደ ብርሃን የመለወጥ ምሥጢራዊ ጥበብ ነው።

ምኞት ምንድን ነው?

ምኞት በሰው ልጅ ተፈጥሮ ውስጥ የተተከለ ባለ ሁለት ገጽታ ምሥጢር ሲሆን፣ በአንድ በኩል ነፍስ ለፈጣሪዋ፣ ለፍቅርና ለእውቀት የምትሰጠው ቅዱስ ምላሽና የእግዚአብሔር ስጦታ ነው። ያለ ተፈጥሯዊ ፍላጎት ሰው ሕይወትንም ሆነ ፈጣሪውን ሊፈልግ አይችልም፤ በመዝሙረኛው በቅዱስ ዳዊት ቃላት "ነፍሴ ወደ አንተ ትናፍቃለች" (መዝ. 421) ተብሎ እንደተገለጸው፣ በጎ ምኞት ነፍስን ወደ ሕይወት ምንጭ የምታደርስ መንፈሳዊ ክንፍ ናት።

ሆኖም ይህ ኃይል ከመለኮታዊ ፈቃድ ወጥቶ በራስ ወዳድነት ሲታወክ፣ መልክ በመለወጥ ነፍስን በባርነት የሚገዛና ወደ ኃጢአት የሚመራ "ፍትወት" ይሆናል። ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ እንዳስተማረን፣ ምኞት ከቁጥጥር ውጭ ሆና ስትፀንስ ኃጢአትን፣ ኃጢአትም ካደገች በኋላ ሞትን ትወልዳለች (ያዕ. 114-15) ይህም የሚያሳየው ምኞት ካልተገራና ከእግዚአብሔር ሕግ ጋር የሚጻረር ከሆነ፣ ሰውን ከነጻነቱ አውርዶ የፍላጎቱ ባሪያ እንደሚያደርገው ነው።

ስለዚህ ትልቁ መንፈሳዊ ተጋድሎ ይህንን እሳታዊ ምኞት በክርስቶስ ታዛዥነት ሥር በማድረግ ለበጎ ተግባር ማዋል ነው። ምኞታችንን እንደ መስቀል ተሸክመን በፈቃደኝነት ለፈጣሪ ስናስገዛው፣ የጥፋት ሰደድ እሳት የነበረው ኃይል ተለውጦ የሕይወት ሙቀትና ወደ መንግሥተ ሰማያት የምንገሰግስበት ብርሃን ይሆንልናል።

የሥጋ ምኞት

ነባቤ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ የዚህን ዓለም የጥፋት ወጥመዶች በሦስት ታላላቅ መጋረጃዎች ይገልጻቸዋል። "ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ፤ ማንም ዓለምን ቢወድ የአባት ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም፤ ምክንያቱም በዓለም ያለው ሁሉ እርሱም የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት ስለ ገንዘብም መመካት ከዓለም ስለ ሆነ እንጂ ከአብ አይደለም" (1ኛ ዮሐ. 2፡15-16) በማለት ነፍሳችን ከምድራዊ ፍቅር ወጥታ ወደ ሰማያዊው አድማስ እንድትመለከት ይመክራል። በዚህ ወርቃማ ጥቅስ ውስጥ ሦስት የሰው ልጅን ነፍስ የሚያውኩ ፍላጎቶች ተገልጠዋል፦ የሥጋ ምኞት (ጊዜያዊ ደስታ)፣ የዓይን አምሮት (ስግብግብነትና ምቀኝነት) እንዲሁም የሕይወት ኩራት (ራስን ከፍ ከፍ ማድረግ) ናቸው።

እነዚህ ሦስት የጥፋት መንገዶች ዲያብሎስ ጌታችንን በምድረ በዳ የተፈተነባቸው ስልቶች ነበሩ። ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን እነዚህን "አርዕስተ ኃጣውዕ" (የኃጢአት ራሶች) ብላ ትጠራቸዋለች። ስስት፣ ትዕቢትና ፍቅረ ነዋይ የኃጢአት ሁሉ አለቆች መባላቸው፣ ማንኛውም በደል ምንጩ ከእነዚህ ስለሆነና እነዚህን ግንባር ቀደም ጠላቶች ድል ያደረገ ሌሎቹን ኃጢአቶች ሁሉ በቀላሉ ድል ማድረግ ስለሚችል ነው። ጌታችን በገዳመ ቆሮንቶስ በፈጸመው ተጋድሎ፣ እኛም የተዘበራረቀ ፍላጎታችንን በእግዚአብሔር ቃል በመታዘዝ መግራት እንደምንችል በተግባር አሳይቶናል።(ማቴ. 4፥1)

ይህንን ድል ለመቀዳጀት ግን ተጋድሎአችን በጾምና በጸሎት የታጀበ ሊሆን ይገባል። በስስት ምትክ ትዕግሥትን፣ በትዕቢት ምትክ ትኅትናን፣ በፍቅረ ነዋይ ምትክ ደግሞ ምጽዋትን ስንተካ የነፍሳችንን መዝጊያ ለሰማያዊው ንጉሥ እንከፍታለን። የዓለም ፍቅር በወጣበት ልብ ውስጥ መለኮታዊው ፍቅር ይነግሣል፤ ያን ጊዜ ምኞታችን ከምድራዊ እስራት ተፈትቶ ወደ ዘለዓለም ሕይወት የሚያደርሰን የብርሃን ክንፍ ይሆናል።


 

እግዚአብሔር የሥጋ አምሮትን ወደ በጎ ሐሳብ ይለውጥ ዘንድ የታመነ ነው

እግዚአብሔር የሰውን ልጅ ባዶነት የሚሞላ እንጂ ባዶ አድርጎ የሚተው አምላክ አይደለም፤ አንድ ሰው የሥጋን አምሮትና ምድራዊ ምኞትን ትቶ ወደ ፈጣሪው ሲመለስ፣ መንፈስ ቅዱስ በዚያ ልብ ውስጥ አድሮ በቅዱስ ናፍቆትና በሰማያዊ መሻት ይሞላዋል። ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ "በመንፈስ ተመላለሱ፥ የሥጋንም ምኞት ከቶ አትፈጽሙ" (ገላ. 5:16) ሲል የመከረን፣ በመንፈስ መመላለስ የሥጋን ክፋት የሚያሸንፍበትን ምስጢር ስላወቀ ነው። ይህ ጉዞ ፍላጎታችንን የመገደብ ብቻ ሳይሆን፣ በመለኮታዊ ጸጋ የመለወጥ ድንቅ ሂደት በመሆኑ ጌታችን በታመነ ቃሉ የልባችንን ትርታ ወደ በጎነት ይለውጠዋል።

በዚህ መንፈሳዊ ለውጥ ውስጥ ጥፋት የሞላበት የልቅነት ፍቅር ወደ ቅዱስና ንጹሕ ፍቅር፣ አጥፊውን የገንዘብ ወዳድነት ወደ ለጋስነት፣ እንዲሁም የሥልጣን ጥማት ወደ ትኅትና አገልግሎት ይለወጣል። እግዚአብሔር ምድራዊ ምኞታችንን ወደ ሰማያዊ ጸጋ መሻት ይለውጥ ዘንድ የታመነ ረዳት ነውና፤ በእርሱ እጅ የተገራ ምኞት ወደ ታች የሚጎትተን የኃጢአት ሰንሰለት መሆኑ ቀርቶ ወደ ላይ ወደ ፈጣሪ የሚያደርስ የብርሃን መሰላል ይሆናል። እውነተኛ ምኞትም ፍጻሜው ከምድራዊው ባርነት ወጥቶ በሰማያዊው ክብር መመላለስ ነው።

የሥጋ ምኞትን እንደ መስቀል መሸከም

ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስሊከተለኝ የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ፣ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ” (ማቴ. 1624) በማለት ያቀረበልን ጥሪ፣ ከምኞት ወደ ፍቅር የምንሻገርበት መለኮታዊ ግብዣ ነው። መስቀሉን መሸከም ማለት የራስን ፈቃድ፣ ሐሳብና ምድራዊ ምኞት በፈቃደኝነት ለፈጣሪ አሳልፎ መስጠት ሲሆን፤ ይህ ደግሞጌታ ሆይ፣ የእኔ ሳይሆን አንተን ደስ የሚያሰኝህ ብቻ በእኔ ይሁንበሚል ትኅትና የሚገለጥ ራስን የመካድ ተጋድሎ ነው።

የግል ፍላጎቶቻችንን ለእግዚአብሔር መሠዊያ አሳልፈን ስንሰጥ፣ እርሱ ደግሞ በውስጣችን የማይታወክ ሰላሙን ያሰፍናል። ታላቁ ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊምኞትን ማሸነፍ ሙታንን ከማስነሣት ይበልጣልእንዳለው፣ የሰው ልጅን እረፍት የሌለው ልብ ማሸነፍ ከማንኛውም ተአምራት ይበልጣል። ጌታችንጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ብፁዓን ናቸው” (ማቴ. 56) ብሎ ተስፋ እንደሰጠን፣ የሥጋ ምኞታቸውንና የዓይን አምሮታቸውን ለፈቃዱ ያስገዙትን ሁሉ በቅዱስ ምኞትና በመንፈሳዊ እርካታ ሊሞላቸው የታመነ ነው።

የሥጋ ምኞቶች በመስቀል ላይ ተሰቅለው ሲሞቱ፣ በልባችን ውስጥ የመንፈሳዊ ናፍቆት ብርሃን ይፈነጥቃል፤ ያን ጊዜ ልባችን በጸሎት፣ በቅድስና፣ በንጽሕናና በምሕረት ፍላጎት ይሞላል። እነዚህ የቅድስና ጥማቶች የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች እንጂ ለሰው ልጅ ሸክሞች አይደሉም። እንደ አባታችን አብርሃም፣ እንደ ሊቀ ነቢያት ሙሴና እንደ ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት ሁሉ፣ የእኛም የውስጥ ናፍቆት የእግዚአብሔርን ክብር ከማየትና በእርሱ ቤት ውስጥ ከመኖር ጋር ሲቆራኝ፣ ምድራዊው ባርነት በሰማያዊ ነጻነት ይተካል።

ስለዚህ ውድ ክርስቲያኖች ሆይ፣ በውስጣችን ያለውን የምኞት እሳት ሳንንቀው ወደ ክርስቶስ ፍቅር እናምራው። እንደ ቅዱስ ጳውሎስ ክርስቶስን ከማወቅ ክብር በቀር ሌላውን ሁሉ እንደ ኪሳራ በመቁጠር (ፊል. 38) ለሥጋ ምኞት ሳይሆን እርሱን ለመምሰል እንትጋ።ከአንተ በቀር በሰማይ ያለኝ ማን ነው?” (መዝ. 7325) እያልን ልባችንን ለሰላሙ ንጉሥ ስንሰጥ፣ ሕይወታችን ለዘላለም በሚኖር ፍሬ ይሞላል። ለዚህም የመንፈስ ድል የእመቤታችን አማላጅነትና የቅዱሳን ጸሎት አይለየን።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

1 comment:

  1. ቃለ ሕይወትን ያሰማልን

    ReplyDelete