Tuesday, 24 May 2016

‹‹ንሴብሕ ክርስቶስሃ ለዘ በመስቀሉ አርኀወ ገነተ›› ቅዱስ ያሬድ



‹‹ በመስቀሉ ገነትን የከፈለ ክርስቶስን እናወድሰዋለን››
በዲያቆን ፍሬው ለማ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በአደባባይ ከሚከበሩ በዓላት መካከል አንዱ የሆነው የቅዱስ መስቀል በዓል በሚከበርበት ወቅት ላይ ደርሰናል፡፡የዚህ ወቅት ማለትም የመስከረም ሶስተኛ ሳምንት(ከመስከረም 15-25) መዝሙር ውእቱ መስቀል ይባል በዚህ መዝሙር ውስጥ ነው በመግቢያ ላይ የጠቀስነው ቃል ያለው፡፡ የቅዳሴ ምንባባቱም ምልጣኑም ወረቡም ቁመቱም ይህን የጌታ ሥራ የሚያዘክሩ ናቸው፡፡
ይህ ወቀት በኢትዮጵያ ምዕመናን ዘንድ ታሪካዊ፣ሀይማኖታዊ እና ባህላዊ ገፅታ አለው በዚህ ጽሐፍ ውስጥ ሀይማኖታዊ ገፅታውን እናያለን፡፡ መስቀል የሚለው ቃል በኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል በተዘጋጀው የአማርኛ መዝገበ ቃላት ላይ 3 ነገሮች መጠሪያነት ሊያገለግል እንደሚችል ተፅፏል
1.     መስቀል ቀጥ ባለ እንጨት አናት አካባቢ ሌላ አጠር ያለ እንጨት በማጋደም ሁለቱን በማያያዝ የሚዘጋጅ በጥንት እስራኤላዊያንና ሮማውያን ጊዜ ወንጀለኞችን ለመግደል ያገለገለ መስቀያ
2.     ‹‹ ከብረት፣ እንጨት፣….›› የሚዘጋጅ ክርስቶስ የተሰቀለበት ምሳሌ እና የክርስትና እምነት ተከታዮች ምልክት
3.     የክርስቶስ መስቀል ከተቀበረበት ቦታ መገኘትን ምክንያት በማድረግ መስከረም 17 ቀን የሚከበር በዓል
ከዚህም በላይ በክርስትና ውስጥ ክርስቶስን ብሎ(ስለ ክርስቶስ ሲባል) የምንቀበለውን ፀዋትወ መከራም መስቀል እንለዋለን ‹‹ ዘኢጾረ መስቀለ ሞትየ ኢይክል ይፀመደኒ›› ማቴ 1038 እንዲል ይህም መከራ ውስጣዊም ውጫዊም ነው ውስጣዊው ከፍትወት/ምኞት የተነሳ የሚመጣብን የሐልዮው ነው ውጫዊው ከሰይጣን(ከአለም) የሚቀርብልን መከራ ነው ከእነዚህም በአኮቴት የምንቀበላቸው እና በመስቀሉ ድል የምንነሳቸው አሉ፡፡
መስቀል ከሥላሴ፣ከእመቤታችን ምስጋና ቀጥሎ ምስጋና የሚቀርብለት ታቦት የተቀረፀለት መልክዕ(ውዳሴ) የተደረሰለት የመማጸኛ ጸሎት (መስተብቁዕ መስቀል) የተጻፈለት በነገረ ድህነት ውስጥ ካሉ ታላላቅ ተስፋዎች፣ምልክቶች አንዱ ነው፡፡ በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በነገረ ድህነት ውስጥ ሁለት ታላላቅ ምስክሮችን(ተስፋዎችን) እንዘክራለን እነዚህም እመቤታች እና ቅዱስ መስቀል ናቸው፡፡ ሁለቱም በተለያዩ ህብረ አምሳል በብሉይ ኪዳን መጽሐፍት የተገለጡ ናቸው፡፡እመቤታችን ድንግል ማርያም የድህነታችን መሰረት እና መጀመሪያ የሆነች ጌታ ከእርሷ ሥጋን ይነሳ ዘንድ የተገባች ሆና የተገኘች ነችና አንድም የሰውነታችን ባሕርይ የከበረባት የታደሳበት ነች ቅዱስ መስቀሉም ለጠላት ማሳፈሪያ ምልክት ሆኖ የተሰጠን በእመቤታችን ማህፀን የተጀመረው ድህነት የተፈፀመበት በመለኮት ደም የተቀደሰ በክርስቶስ ያገኘነው የትንሣኤ ሰላማችን አርማ ነው፡፡ ለዚህም ነው አባቶች በመስተብቁዕ ዘመስቀል ጸሎታችን ‹‹ በእንተ ዝንቱ አዘዙ መምህራነ ቅዱስ ወንጌል አምሳለ ፈጣሪ ልዑል ንሰግድ ለመስቀል ወለማርያም ድንግል………ስለዚህም የቅዱስ ወንጌል መምህራን ለልዑል በሚቀርብ ስግደት አምሳል(በጸጋ) እንድሰግድላቸው አዘውናል ከማርያም ድንግልም ከሥጋዋ ሥጋን ነስቷልና ከእርሷም መድኃኒትን አግኝተናልና ለመስቀልም የቃል ደም በላዩ ተንጠባጥቧልና››ያሉት በመልክዐ ሥላሴም ላይ ሰላም ለኩልያቲክሙ በሚለው ሥር ‹‹ ተፈጸመ ተስፋ አበው በማርያም ድንግል ወበ ቀራንዮ ተተክለ መድኃኒት መስቀልየአበው ተስፋ በድንግል ማርያም ተፈጸመ በቀራንዮም መድኃኒት የሆነ መስቀል ተተከለ›› ተብሎ ተጽፏል ይህም ከላይ የጠቀስነውን ሀሳብ የሚያጠናክርልን ነው የሁለቱም(እመቤታችን እና ቅዱስ መስቀል) በአምልኳችን ውስጥ ተደጋግሞ መነሳት ከላይ ከጠቀስነው በነገረ ድህነት ውስጥ ካላቸው ሥፍራ የተነሣ ነው፡፡
ክርስቲያን ዘወትር በአዕምሮው ከሚያሰላስለው የክርስቶስ የማዳን ስራ በተጨማሪ በአንገቱ የሚያጠልቀው መስቀል፣በየአብያተ ክርስቲያናቱ ጉልላት ላይ የሚደረጉ መስቀሎች፣ በካህናት እጅ የምንሳለመው መስቀል….አለ እነዚህ ሁሉ በተግባርም ይህን ነገረ ድህነት የምንመሰክርባቸው ናቸው
መስቀል ታላቁ የፍቅር /ቤት ነው፡፡ በምድር ታሪክ ውስጥ ተደርጎ የማያውቅ ወደፊትም የማይደረግ ታላቁ የፍቅር ሥራ በመስቀል ተደርግዋል፡፡ እግዚአብሔር ፍጥረቶቹ ሲበድሉ ዝም ብሎ የሚያይ አምባገነን ወይም ምንም ማድረግ የምይቻለው ደካማ አይደለምና ወርዶ ተወልዶ ይልቁንም ሞቶ አዳነን‹‹ እርሱ ግን ፍጥረቶቹን አልተወንም ቸልም አላለንም እርሱን እንደበደልነው መጠን ፈጽመን እንጠፋ ዘንድ በኃጢአታችን አልተቀየመንም፣ወደደን እንጂ፣ጎበኘንም፣ማረን፣ይቅርም አለን፣ከሚገዛንም እጅ አዳነን…›› እንዲል ቅዳሴ ዮሐንስ አፈ ወርቅ
ከሌሎች የእምነት ድርጅቶችም ተለይተን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን (1ቆሮ123) የክርስቶስን ሞት መቀበል የክርስትና የእምነት መሠረት ነው፡፡ ይህም እንዴት የሰውን ሥጋ ይነሳል እንዴትስ ይሞታል ብለው አምላክን ያከበሩ ለሚመስላቸው ሞኝነት ነው፡፡ የሐዲስ ኪዳን ታላቁ ምስጢር ይህ የአምላክ ለፍጥረቶቹ ሲል መሞት ነው፡፡ በሐዲስ ኪዳን መጽሐፍት ክርስቶስ በሰውም፣ በእርሱም በመላዕክትም አንደበት ይሞት ዘንድ እንዳለው ተደጋግሞ ተገልጧል ይልቁንም ከትንሳኤው በኋላ እንኳን የሞተው፣የተሰቀለው ተብሎ ተቀፅሎለታል(ማቴ285፣ሮሜ834፣ራዕ118፣ራዕ28) የመምጣቱም ትልቅ አላማ ይሞት ዘንድ ነው ይህም በመስቀል ላይ የተፈጸመ ነው
አባታችን ዮሐንስ አፈ ወርቅ የመዝሙረኛውን ቃል ‹‹ ሰነፍ በልቡ አምላክ የለም ይላል››መዝ131 በተረጎመበት ድርሳኑ እንዲህ ብሏል ክርስቶስን ተሰቅሎ ማየት ያልቻለ በዚህ ስንፍናው ይገለጣል ብሏል ስንፍና የተባለውም ክርሰቶስን እንደተሰቀለ አለማመን አለማመን ነው (ገላ31)፡፡ በዚህም ቸልተኝነቱ እግዚአብሔርን አያየውም፡፡ የእግዚአብሔርን ኃይል፣ ድል፣ ጠላትን ማሳፈር ማየት፤ማወቅ ለሚፈልጉ ሁሉ መስቀል ታላቁ ምላሽ ነው
የክርስቶስ ህማም የአምልኳችን መሰረት እና ሁሉ ነገራችን ነው በየቅዳሴው ይህንን ህማሙን እንሳተፋለን በጥምቀት ከእርሱ ጋር እንሞታለን እንነሳለን የአመቱ የአምልኮ ጊዜያት በህማማት ማዕከልነት የተሰደሩ ናቸው ሳምንታችንም የአይሁድን ፍርድ እና ስቅለትን የሚያዘክሩ የአዕፅዋማት ቀኖች ያሉት ነው በቃልም፣በሀሳብም፣በተግባርም መከራውን እናስባለን፡፡
እግዚአብሔር ኃጢአትን፣ ሞትን በአጠቃላይ ክፉ ነገርን በምድር ላይ እንዲሆን አልፈቀደም አይፈቅድምም፡፡ ለዚህም ትልቁ ማሳያችን ጠላታችንን በመስቀል ጠርቆ ያሳየን ሰላም ነው፡፡ ያለ መስቀል እግዚአብሔርን እና በእኛ ላይ ያለውን አለማ መረዳት አይቻልም፡፡ ክርስቶስ እንደሞተ እና እንደተነሳ እኛም የዚህ ተሳታፊዎች መሆን እንዳለብን የማያስብ ሁሉ ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ እንዳስተማረን ለክርስቶስ ሊሆን አይገባውም(1ዮሐ423)
የሰው ልጅ በእግዚአብሔር አርአያ እና አምሳል የተፈጠረ ታላቅ ፍጡር ነው፡፡ ይህም ብቻ አይደለም አምላክ ሰው ሆኖ ያዳነውም ታላቅ ፍጡር ነው፡፡ ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ እርሱ በአማላክነት ያደረገውን(የሆነውን) ሁሉ እኛ በፀጋ እንሆን ዘንድ አድሎናል (ልጅነት፣ንጉሥነት፣ቅዱስነት……) ይህ ግን ብቻ አይደለም በስሙ መከራ እንቀበል ዘንድ ጭምር ነው እንጂ ‹‹ስለ እርሱ መከራ ደግሞ ልትቀበሉ እንጂ በእርሱ ልታምኑ ብቻ አይደለም›› ፊል129 እንዳለ ሐዋርያው ይህንን ተልዕኳንችን እንፈፅም ዘንድ መስቀል ምልክታችን ነው ክርስቲያን ሁሉ ክርስቶስ መከራ ተቀብሎ ካደለን ማዕድ(ሥጋ ወደሙ) እየተቀበለ መከራው አይንካኝ ይል ዘንድ አይገባም ይልቁንም እንደ ቅዱስ ጳውሎስ ቀኑን ሙሉ ስላንተ እንገደላለን እንል ዘንድ ይገባናል (ሮሜ836) መስቀል እግዚአብሔርን እና ፍጥረትን ሁሉ በመውደዳችን የምንጋፈጠው መከራ ነው፡፡ ከዚህም መከራ እንሸሽ ዘንድ አይገባም ‹‹በሥጋ መልካም ሆነው ሊታዩ የሚወዱ ሁሉ እንድትገረዙ ግድ አሉአችሁ፥ ነገር ግን ስለ ክርስቶስ መስቀል እንዳይሰደዱ ብቻ ነው››ገላ 612 ብሎ እንደወቀሳቸው ሰዎች ከዓለም ጋር ተመሳስለን ሳይሆን ከክርስቶስ ጋር ተባብረን በአኮቴት መስቀላችንን እንቀበል ዘንድ ይቻላል፡፡ ቅዱሳንን ሁሉ አንድ የሚያደርጋቸውም መከራውን በአኮቴት መቀበላቸው ነው እነርሱ እንደ ጌታቸው ከመከራው በኋላ ያለውን ደስታ ናፍቀው ሀይማኖታቸውን ጠብቀዋል ‹‹እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና።››ዕብ122 እንዲል ይህ መስቀል ከቤተክርስቲያን አይለይም ለዚህም ‹‹ስለ ስሜ ስንት መከራ ሊቀበል እንዲያስፈልገው እኔ አመለክተዋለሁና አለው››ሐዋ916 ተብሎ የተጠራው ቅዱስ ጳውሎስ ሲመሰክር ‹‹ስለ አካሉም ማለት ስለ ቤተ ክርስቲያን በሥጋዬ በክርስቶስ መከራ የጐደለውን እፈጽማለሁ።›› ቆላ124 ይህም ቃል የተነገረው በክርስቶስ ድህነት ህፀፅ ኖሮ ሳይሆን በክርስቶስ ላይ መከራ ያጸና አለም በዚያ አያቆምም የተረፈውን መከራ በቤተክርስቲያኒቷ ያደርሳል ለማለት ነው ለዚህም ሐዋርያው ራሱን ፊት አውራሪ አድርጓል፡፡ እኛም ይህን አሰረ ፍኖት እንከተል ዘንድ ይገባል፡፡
መስቀላችንን በአኮቴት ተቀብለን እንሸከም ዘንድ እንደ ምሳሌ ከተጠቀሱልን ታሪኮች መካከል የፊያታዊ ዘየማን ታሪክ አንደኛው ነው እርሱ በወንጌል እንደተጠቀሰ‹‹ ስለ አደረግነውም የሚገባንን እንቀበላለንና በእኛስ እውነተኛ ፍርድ ነው፤ ይህ ግን ምንም ክፋት አላደረገም ብሎ ገሠጸው።››ሉቃ2341 ተብሎ እንደተነገለት እርሱ ምንም እንኳን በኃጢአቱ ምክንያት የመጣበት ቢሆንም በግራው ከተሰቀለው ይልቅ ያለ ተስፋ መቁረጥ በእምነት መስቀሉን ተቀብሏል በዚህም ጌታ ስለ መሻቱ መድኃኒታችን እውነት እልሃለሁ፥ ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ አለው። ሉቃ2343 5500 ዘመን ተዘግቶ የነበረውን ገነትም በደመ ማህተሙ ሲከፍት እርሱን ቀዳሚ አደረገው ይህም አባቶቻችን እንዳስተማሩን በአኮቴት መስቀላችንን ተቀብለን በተከፈተልን ገነት በክብር እንመላለስ ዘንድ የተጻፈልን ነው፡፡
ቅዱስ ያሬድ ሌላው በዚህ(በመስቀል) መዝሙር የተናገረው ‹‹ ብከ ንወግዖሙ ለኩሎሙ ፀርነ ወበስምከ ነኀስሮሙ ለእለ ቆሙ ላእሌነ ይቤ ዳዊት በመንፈሰ ትንቢት በእንተ ዝንቱ ዕፀ መስቀል›› የሚለው ነው በዚህም በመዝ445 ላይ የተጠቀሰውን ‹‹በአንተ ጠላቶቻችንን እንወጋቸዋለን፥ በስምህም በላያችን የቆሙትን እናዋርዳቸዋለን።›› ለመስቀል ሰጥቶ ተርጉሟል ጌታችን መከራ እንቀበል ዘንድ መከራ በሚያመጡብን እንፈተን ዘንድ ዝም ብሎ አልተወንም በእርሱ ጠላቶቻችንን ድል እናደርግበት(እንወጋበት) ዘንድ ምልክቱን መስቀሉን ትቶልናል እርሱም ከዲያቢሎስ ፍላፆች ሁሉ የምንድንበት ነው ‹‹ በስምከ ተወከልነ ወበኃይልከ ተማኅፀነ መዓልተ ምስሌነ ወሌሊተ ማዕከሌነ ዝንቱ ትእምርተ መስቀል ቤዛነ በዘቦቱ ንመውዕ ለኩሉ ኃይለ እኩይ ›› እንዲል(መጽሐፈ ዚቅ መስቀል)
ጌታ በወንገል እንደተናገረው እነዚህ ነገሮች(መከራዎቸን)መቀበል ለቅዱስ ጴጥሮስ እንደ ነገረው በሰው ዘንድ የማይቻል በእግዚአብሔር ዘንድ ግን የሚቻል ነው ማቴ1926 ይህም እርሱ በእኛ ካላደረ ወይም ለእርሱ ማደሪያ ራሳችንን ካላመቻቸን ከምስጢራትም ተሳትፈን የእርሱ አካል ካልሆንን በስጋዊ ጥበብ በእውቀት ብዛት በሥጋችንም በነፍሳችንም (በኀልዮ፣በነቢብ፣በገቢር) የሚመጠብንን መስቀሎች እንሸከም ዘንድ የማንችለው ነው፡፡ መጋደላችን ከሥጋ እና ከመንፈስ ጋር አይደለምና
ከንጉሥ ቆስጠንጢኖስ እና ከንግስት እሌኒ በረከትን ያሳትፈን በኃጢአት ውስጥ የተቀበረውንም መስቀላችንን በተቃጠለ ልብ በክርስቶስ ፍቅር መዓዛ አውጥተን እንሸከም ዘንድ አምላከ ቅዱሳን ይርዳን

No comments:

Post a Comment