Wednesday, 21 December 2016

እግዚአብሔርን መምሰል


እግዚአብሔር ፍጥረታቱን ፈጥሮ ባገባደደበት በዕለተ አርብ ከፍጥረታት ሁሉ ልዩ ንዑድ ክቡር የሆነውን አዳምን ፈጠረ፡፡ በኦሪት ዘልደት መጽሐፍ ተጽፎ እንደምናገኘው እግዚአብሔር ‹‹ ሰውን እንደመልካችን እንደምሳሌያችን እንፍጠር›› ብሎ በመልኩና በምሳሌ ፈጠረው፡፡ (ዘፍ. 1÷26)  ሰው ገና ሲፈጠር በጸጋ አምላክ እንዲሆን ተደርጎ በእግዚአብሔር አርአያና አምሳል የመፈጠሩ ጉዳይ ኦርቶዶክሳዊያን አባቶቻችን በብዙ ትርጉም ይተረጉሙታል፡፡
ይህም እግአዚአብሔርን የመምሰላችንን ጉዳይ በስፋትና ጥልቀት የሚተነተን ነው፡፡
ቅዱስ ባስልዮስ ዘቄሳርያ ‹‹አንድ ሰው ራሱን ካወቀ እግዚአብሔርን ያውቃል እግዚአብሔርን ካወቀ ደግሞ እግዚአብሔርን ይመስላል››ሲል ያስቀምጣል፡፡ የእስክንድርያው አባት ቅዱስ ቀሌምንጦስ ‹‹ወንድምህን አስተውለህ ስትመለከተው እግዚአብሔርን ትመለከተዋለህ›› ይላል፡፡ ዘወትር ቤተክርስቲያን የምትገለገልበትና መጽሐፈ ሰዓታትን ያበረከተው ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ አባ ጊዩርጊስም ‹‹ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እግዚአብሔር ዘገብሮ ለአዳም በዘዚአሁ  አርአያ ወአምሳል›› ይላል  ይህም እግዚአብሔር ሰውን በአርአያና አምሳሉ መፍጠሩን በጉልህ የሚያመለክት ንግግር
ነው፡፡

አርዓያና አምሳል
የሰው ነፍስ ስንል በሰው ልጅ ተፈጥሮ ውስጥ ሕያው ሆኖ የሚኖረውና የማይሞተው ክፍል ነው፡፡እግዚአብሔር የሰው ልጅን ከምድር አፈር ከፈጠረው በኃላ የማይሞት ነፍስን እስትንፋስ እፍ ብሎበት ሕያው ፍጥረት አድርጎ ፈጥሮታል፡፡ (ትምህርተ መለኮት ዓስራት ገብረ ማርያም) ቅዱስ ኤፍሬም በእግዚአብሔር መልክ የተፈጠረችው ነፍሳችን ናት ብሎ ሲያስተምር ‹‹አንተ መንፈሳዊ ተፈጥሮ አለህ፤ ነፍስ የእግዚአብሔር አርዓያና አምሳል ናት›› ይላል፡፡ ሰው በነፍስ ተፈጥሮው ነጻ ፈቃድ፣ ነገሮችን የማገናዘብ ችሎታ እንዲሁም ሓላፊነት የሚሰማው ሆኖ የተፈጠረ ፍጥረት ነው፡፡ በእነዚህ ሰው እግዚአብሔር አምላኩን ይመስላል፡፡
የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንትም ይህን ነጥብ ይጋሩታል እግዚአብሔር ሰውን በአርአያው ፈጠረው ማለት በነፍሱ ላይ ሦስቱን ባሕርያት አኑሮ ፈጠረው ማለት እንደሆነ ይስማማሉ፡፡ እነዚህ ሦስት የነፍስ ባሕርያት ለባዊነት ነባቢነት(ተናጋሪነቱ) እንዲሁም ሕያውነቱ ናቸው በዚህ ባሕርያቱም የሰው ልጅ ከሌሎች ፍጥረታት የሚለይበት ከእግዚአብሔር ጋር ደግሞ የሚመሳሰልበት ነው፡፡ ሌላው አርአያ ስንል አዳም ነጻ ፈቃድ ያለው መሆኑ እንደሆነ
ያስተምራሉ፡፡
ቅዱስ ያዕቆብ ዘስሩግ ግን ነፍሳችንም ሥጋችንም በእግዚአብሔር አርዓያ እንደተፈጠሩ ግልጽ በሆነ መልኩ ሲያስረዳ በአዳምና በሔዋን አስቀድሞ ያሳየን ምሳሌ ይፈጸም ዘንድ የሙሽራው ጎን በጦር ተወጋ፤ ከጎኑም (በፈሰሰው ደሙ) ቤተክርስቲያን ተመሠረተች፤ እግዚአብሔር ይህን ባወቀ አዳምንና ሔዋንን በብቸኛ ልጁ አርአያና አምሳል ፈጠራቸው፡፡ይለናል፡፡ሰው ሰማያዊት አካል ስላለችው ረቂቁን ዓለም የመረዳት ችሎታ ሲኖረው ምድራዊውም አካል
ስላለው ምድራዊውም እውቀት አለው፡፡ ሰውን ከሰማያውያን መላእክትና ከምድራውያን መላእክት ጋር ስናስተያየው ለሁለቱም ዓለማት እንግዳ እንዳልሆነ በሁለቱም ዓለማት እኩል የመኖር ተፈጥሮአዊ ባሕርይ እንዳለው፣ የሰማያውያንንም የምድራውያንንም እውቀት ገንዘቡ ያደረገ ፍጥረት መሆኑን ስናስተውል በእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ መፈጠሩን እንገነዘባለን ፡፡
ቅዱስ ባስልዩስ አርዓያ ለሁሉ የተሰጠ ነው ምሳሌ (አምሳል) ስንል ግን  በተፈጥሮ የተሰጠንን ዕውቀት ተጠቅመን በተግባር እርሱን የምንመስልበት ሂደት እርሱ ምሳሌ (አምሳል)ይባላል፡፡ እግዚአብሔር በባሕርይው ፍቅር ነው፣ ትሑትና የዋህ ነው፣ ቅን ፈራጅ ነው፣ ጻድቅ ነው፣ ርኅሩኅ ነው፣ መሐሪ ነው፣ ታጋሽ ነው፡፡ እነዚህ ባሕርያት ሁሉ በእኛ ተፈጥሮ ውስጥ ያሉ ናቸው፡፡ እነዚህን ባሕርያት ወደ ተግባር መልሰን ስንፈጽማቸው እግዚአብሔርን መስለነዋል ወይም የእግዚአብሔር ምሳሌ ወይም አምሳል በእኛ ላይ ተንጸባርቆ ይታያል፡፡
በአርአያና በአምሳሉ የተፈጠረው ሰው ከሕጉ ፈቀቅ አለ
የሰው ልጅ በእግዚአብሔር አርአያና አምሳል ተፈጥሮ ሳለ ከክብሩ በኃጢያት ምክንያት ተዋረደ፡፡ በአዳም ምክንያት ሞት በሰው ሁሉ ላይ ታወጀ፡፡ ቅድስና እንደመርገም ሆነ ቅዱሳን ከሲኦል እስራት የሚፈታቸውን በመፈገለግ ተጨነቁ በዚህን ጊዜ አምላክ አንደኛ ልጁን ወደ ምድር ላከ(ዮሐ. 3፥16) አምላኩን መምሰል ያቃተው የሰው ልጅ የእግዚአብሔር ልጅ ሰው ሆኖ በመጣ ጊዜ ከሕግጋቱ እየፈጸመ በሕይወቱ የጎለበተ ይሆን ዘንድ ሕግን እየፈጸመ
አሰለጠነው፡፡ የሰለጠነበትና የገዛውን ዲያቢሎስን በመስቀሉ ድል አደረገው፡፡ እግዚአብሔርን ይመስል ዘንድ ዳግመኛ ሕጉን  አጸናለት፡፡ ትዕዛዙንም የሚፈጽሙት ሁሉ ወደ እርሱ መምሰል ይቀርቡ ዘንድ፡፡ቅዱስ ሄሬኔዎስ፣ ቅዱስ አትናቴዎስ፣ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙ እንዲሁም ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ በአንድነት ‹‹ሰው በጸጋ አምላክ ይሆን ዘንድ ከሦስቱ አካላት አንዱ እግዚአብሔር ቃል ሰው ሆነ›› ብለው ያስተምራሉ፡፡ቅዱስ ያሬድም በዜማ ድርሰቱ
‹‹ ቃል ሥጋ ኮነ … ደመረ መለኮቶ ምስለ ሥጋ ዚአነ›› የመለኮትና የሥጋን ተዋሕዶ በተመለከተ ይሀም ቅዱስ አትናቴዎስ እንዳለው የሰውና የእግዚአብሔር ተዋሕዶ ምሥጢረ ሥጋዌን እግዚአብሔር ጋር መመሳሰል ጋር በእጅጉ ያገናኘዋል፡፡
 በትንሣኤውም ዳግመኛ መነሳትን አደለው ከሙታን ጋር እነዳይቆጠር ወልደ እግዚአብሔር ሞትን ድል አድርጎ ወደ ቀደመ መምሰሉ መለሰው፡፡ ቀድሞም ሲፈጠር የሚተኛና የሚነሳፍጥረት አድርጎ መፍጠሩ አዳም ሕያው ፍጥረት መሆኑን አመልካች ነው(መጽሐፈ አክስማሮስ)
እንዴት እንምሰለው?
1.       በጥምቀት
እኛ የሰው ልጆች የመንፈስ ቅዱስን እገዛ በኃጢአት ምክንያት ከማጣታችን የተነሣ ምንም እግዚአብሔርን በጸጋ የምንመስልበት ተፈጥሮ ቢኖረንም አልተቻለንም ነበር፡፡ ወደዚህ ወደ ቀደመ ክብራችን ለመመለስ ሰው ግዴታ ሊጠመቅና ሰውነቱን የመንፈስ ቅዱስ ቤተመቅደስ ሊያደርገው ይገባል፡፡ እንዲህ ከሆነ በእርሱ ሰውነት ውስጥ ያደረው መንፈስ
ቅዱስ እግዚአብሔር አምላክን መስሎ የሚኖርበትን ጸጋ ያገኛል፡፡ በእርሱም በተፈጥሮ ያገኘውን እግዚአብሔርን የመምሰል አቅም ተጠቅሞ በጸጋ እግዚአብሔርን ወደ መምሰል ያድጋል፡፡
ስለዚህ አንድ ሰው በትክክለኛው ተፈጥሮ ለመኖር ከፈቀደ የግድ ተጠምቆ ክርስቲያን በመሆን የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ ሊያገኝ ይገባዋል፡፡ ያለበለዚያ ምኞት ቢኖረው እንኳ በትክክለኛው ተፈጥሮ መኖር ይሳነዋል፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ ከቅድስት ድንግል ማርያም በነሣው ሰውነቱ በኩል ሰው እንደሆነ እንዲሁ እኛም ከመንፈስ ቅዱስ ተካፋዮች በመሆን እርሱን በጸጋ ወደ መምሰል ልንመጣ ይገባናል፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም ስለዚህ ሲያስረዳ በሥጋዊ ልደት ካልተወለደ በቀር
መንፈሳዊ የሆነውን እርሱን ግዘፈ አካል አለው አንደማንለው ሁሉ አንዲሁ እኛም መንፈሳዊ በሆነ ልደት ካልተወለድን በቀር መንፈሳውያን አንባልም  ይለናል፡፡
ቅዱስ ጳውሎስም በመንፈስ ቅዱስ ካልሆነ በቀር ጽድቅን መፈጸም እንደሚሳነን ሲያስረዳ የማደርገውን አላውቅምና የምጠላውን ያን አደርጋለሁና ዳሩ ግን የምወደውን እርሱን አላደርግም፡፡ በውስጥ ሰውነቴ በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለኛልና፤ ነገር ግን በብልቶቼ ባለ በኃጢአት ሕግ የሚማርከኝን ሌላ ሕግ አያለሁ፡፡ እኔ ምንኛ ጎስቋላ ሰው ነኝ ለዚህ ሞት ከተሰጠ ሰውነት ማን ያድነኛል ይልና በቀጣዩ ምዕራፍ ላይ ለዚህ መልስ ሲሰጥ €œእንግዲህ በክርስቶስ
ኢየሱስ ላሉት አሁን ኩነኔ የለባቸውም፡፡ በክርስቶስ ኢየሱስ ያለው የሕይወት መንፈስ ሕግ ከኃጢአትና ከሞት ሕግ አርነት አውጥቶኛልና፡፡ ይላል (ሮሜ 7፡15-25፣8፡1-2)
2.      በመንፈሳዊ ጉዳዩች በመጠመድ

በዚህ ዘመን የሚኖሩ ወጣቶች ትልቁ ተግዳሮት ዓለም የሚትሰጠን አማራጮች መብዛትና የቱን መከተል እንዳለብን ውሳኔ ለመስጠት መቸገር ወይም ሁሉን መፈለግ ዓይነት ተግዳሮቶች ይገጥሙናል፡፡ እግዚአብሔር ግን ከሁሉ በፊት እርሱን እንድናስቀድም ይፈልጋል፡፡ በኦሪት መጽሐፍ እንደምናነበው ለሙሴ ከተሰጡት ሕግጋት መካከል የመጀመያዎቹ ሦስቱን ብንመለከት ከሁሉ በፊት እርሱን ማስቀደም እንደሚገባ የሚያስተምሩ ናቸው( ዘጽ 20፥3-) ዓለም ከምታቀርብልን አማራጮች ሁሉ እርሱን መምረጥ ተገቢ ነው፡፡
3.      መልካም ሥራን በማድረግ
እንግዲህ እኛ ክርስቲያኖች እዳ አለብን እንደ ሥጋ ፈቃድ ግን እንኖር ዘንድ ለሥጋ አይደለም፡፡ እንደ ሥጋ ፈቃድ ብንኖር እንሞት ዘንድ አለን፡፡ በመንፈስ ግን የሰውነትን ሥራ ብንገድል በሕይወት እንኖራለን፡፡ (ሮሜ.8፡12-17) አሁን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ተጠምቀን እግዚአብሔርን ለመምሰል የሚያግዘንን የመንፈስ
ቅዱስ ጸጋን አግኝተናል፡፡ ስለዚህም ቅዱስ ጳውሎስ እንዳስተማረው መልካምን ሥራ ለማድረግ በክርስቶስ ኢየሱስ ተፈጥረናል፡፡  (ኤፌ.2፡10) ስለዚህ እንፍራ ከአሁን በኋላ ለምንፈጽማቸው ኃጢአቶች ምንም ምክንያት ማቅረብ
አንችልም፡፡ ጽድቅን ከማድረግ ብንመለስ ወይም እያወቅን ከመፈጸም ብንለግም ቅጣቱ በእኛ ላይ ይከፋል፡፡
4.      ዘመናችንን ለእርሱ በመለየት
ይህ የወጣትነት ዘመን ለመጸለይ ዓይኔን ፣ለመስገድ ወገቤን ፣ለመፆም አቅሜን የማንልበት ዘመን ነው።ከልብ ከተነሳን በዚህ ዕድሜ በፈጣሪ እርዳታ ብዙ መስራት እንችላለን።ለአገልግሎት ከአንዱ ስፍራ ወደ ነንዱ ብንሮጥ፣ገዳማቱን በየሥፍራው ዞረን ብንሳለም ፣አበውን ለመርዳት ገንዘብ ብናወጣ ፣ብንረዳ ፣መንፈሳዊ ማኅበር ብንመሰርት ሁሉም ይቻላል።ጉልበትን ። ገንዘብን፣እውቀትን፣ሁሉንም በስራ ለማዋል የሚመቸው በዚህ ዕድሜ ነው። የመናፍቃንን ተንኮል ለመከላከል ዘመኑን ዋጅተን መልስ ማዘጋጀት የምንችልበት እድሜ ወጣትነት ነው።በየዋህነት
የኮበለለውን ምዕመን ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ለመመለስ በአፍ በመጽሐፍ የምንልበት ሃይማኖታችንን ለመጠበቅ ሌትና ቀን የምንድክምበት ዕድሜ ወጣትነት ነው።በዚህ ዕድሜ ቅዱስ ዮሐንስ ነገረ መለኮትን አርቅቆ አምጥቆ እንደጻፈ / ዮሓ 21-24 / ቅድስ አትናቴዎስ የሃይማኖት ጸሎትን ከሦስት መቶ አስራ ስምንት ሊቃውንት ጋር በመሆን እንዳረቀቀ አንርሳ።
ሰማዕትነት ቢመጣ አንገትን ለሰይፍ ለስለት ፣ሰውነትን ለሞት ለመስጠት የሚታገሱበት ዕድሜ ወጣትነት ነው።ስለቤተክርስቲያን ሕይወትን እንኳን ዋጋ አድርጎ ለመስጠት ይህ ዕድሜ ይመቻል።ቀዳሜ ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስ የአይሁድን ቁጣ ሳይፈራ እውነትን መስክሮ በሰማዕትነት ያረፈው በእዚህ እድሜ መሆኑንም አንዘንጋው።ሊቀ ሰማዕታት
ቅዱስ ጊዮርጊስ በዐላውያን ነገሥታት ፊት ስለአምላኩ መስክሮ የገጠመውን መከራ ሁሉ በጽናት የተቀበለው ገና በሃያ ሦስት ዓመቱ ነው ፡፡ይህ ዘመን ታዲያ ከእግዚአብሔር ጋር ሕብረት ኖሮን እርሱን በመምሰል ማሳለፍ ይገባናል፡፡
በቅድስና በመኖር እርሱን እንድመስል አምላከ ቅዱሳን እግዚአብሔር ይርዳን

No comments:

Post a Comment