Tuesday, 9 January 2018

ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ




ቅዱሱ ሐዋርያ ከዘብዴዎስና ከማርያም ባውፍልያ ተወልዶ: በገሊላ አካባቢ አድጐ: ገና በወጣትነቱ መድኃኔ ዓለምን ተከትሎታል:: ቅዱስ ዮሐንስ ከሐዋርያት ቀድሞ ጌታን ከመከተሉ ባሻገር በምንም ምክንያት ከጐኑ አይጠፋም ነበር:: ስለ ንጽሕናውና በጐ የፍቅር ሕሊናው ሕጻን ሳለ በወንድሞቹ ሐዋርያት ዘንድ ሞገሱ ከፍ ያለ ነው:: ይህ አባት መስከረም አራት ቀን በዚች ዕለት እንደተወለደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ታስተምራለች፡፡

ዮሐንስ የሚለው ስም ዮሐናን ከሚለው ቃል የተገኘ ሲኾንትርጓሜውም “ከያሕዌ (ከእግዚአብሔር) የተሰጠ” ማለትእንደኾነ ብዙ ሊቃውንት ይስማማሉ፡፡ ትርጓሜ ወንጌል ግን“ዮሐንስ ማለት ፍስሐ ወሐሴት ማለት ነው” ይላል፡፡ ቅዱስዮሐንስ ብዙ ቅጽል ስሞች አሉት፡፡ ከእነዚኽም መካከል፡-


  • የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክነት በመግለጡናለጌታችን ባለው ቅንዓት ባሳየውም የኃይል ሥራ “ቦኤኔርጌስ-ወልደ ነጐድጓድ” /ማር.፫፡፲፯/፣
  • የእግዚአብሔርን አንድነትና ሦስትነት ስለሚናገር “ታዖሎጐስ-ነባቤ መለኰት”፣

ኃላፍያትንና መጻእያትን ስለሚናገር “አቡቀለምሲስ-ረአየኅቡአት- ባለ ራዕይ”፣
  • እንዲሁም የጌታን ጸዋትወ መከራ አይቶ ፊቱ በኃዘን ተቋጥሮይኖር ስለ ነበር “ቁጹረ ገጽ- ፊቱ በሐዘን የተቋጠረ” ይባላል፡፡
  • ጌታችን ግርማ-መንግሥቱን ሲገልጥ /ማቴ.፲፯፡፩/፣ የኢያኢሮስንልጅ ሲያነሣ /ማር.፭፡፴፯/፣ በጌቴሴማኒ የአታክልት ቦታ ሲጸልይ/ማቴ.፳፮፡፴፯/፣ ስለ ኢየሩሳሌም መጥፋት ትንቢት ሲናገር/ማር.13፡3/ ዮሐንስ አብሮ ስለ ነበር “የምሥጢር ልጅ”ምይባላል፡፡
  • ቅዱስ ጳውሎስ አዕማደ ቤተ ክርስቲያን ብሎ ከሚጠራቸው ሐዋርያት አንዱ ዮሐንስ ነው /ገላ.፪፡፱/፡፡


  • ከሌሎቹ ደቀ መዛሙርት በተለየ አኳኋንም ጌታን ይወደው ስለነበር ሁሌ ከእቅፍ አይለይም ነበር፡፡ በዚህም “የጌታ ወዳጅ-ፍቁረ እግዚእ” ተብሏል /ዮሐ.፲፫፡፳፫/፡፡
  • ከነዚህ በተጨማሪ ወንጌላዊው፣ ሐዋርያው፣ ድንግል፣ ዘንሥር፣ዘረፈቀ ውስተ ህፅኑ ለኢየሱስ፣ ካልእ ረድእ፣ ባሕረ ጥበባት፣አበ ልሳናት… እየተባለም ይጠራል፡፡


የቅዱስ ዮሐንስ አባቱ ዘብዴዎስ የሚባል የሲዶና ሀገር ገሊላዊ ሲሆንዓሣ አጥማጅ ነበር፡፡ እናቱም ማርያም ባውፍልያ እንደምትባልናከ፴፮ቱ ቅዱሳት አንስት አንዷ መኾኗን የቤተ ክርስቲያናችንትውፊት ያስረዳል /ማቴ.፳፰፡፩/፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ በመጀመርያ የመጥምቁ ዮሐንስ ደቀ መዛሙር ነበር/ዮሐ.፩፡፴፭-፵/፡፡ በኋላ ግን ከታላቅ ወንድሙ ከያዕቆብ ጋር ሰዎችንእንደ ዓሣ በወንጌል መረብ ከዚሁ ዓለም ባሕር ለማጥመድ ጌታችንኢየሱስ ክርስቶስ የስብከት ሥራውን እንደ ጀመረ በቅፍርናሆምከተማ በገሊላ አጠገብ ሲመላለስ ሳለ ጠራው /ማቴ.፬፡፳፩/፡፡ እርሱምወዲያው ከወንድሙ ጋር ታንኳይቱንና አባቱን ትቶ ተከተለው፡፡ጌታችን ሲጠራው የ፳፭ ዓመት ወጣት እንደ ነበረም ሄሬኔዎስ የተባለደቀ መዝሙሩ ጽፏል፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ ከደቀ መዛሙርቱ ኹሉ የተለየ ፍቅር ስለነበረውጌታችንን እስከ እግረ መስቀሉ ድረስ ተከትሎታል፡፡ ለዚኽምመላው የሐዲስ ኪዳን ክርስቲያኖችን ወክሎ የእመቤታችንንእናትነት ከጌታ ተቀብሏል፡፡ በዚያች የመከራና የኑዛዜ ሰዓት የተገኘየቁርጥ ቀን ወዳጅ በመኾኑ በአደራ መልክ “እነኋት እናትኽ”ተብሏል፡፡ እርሱም ለእመቤታችን ልዩ አክብሮትና ፍቅር ስለነበረውበእናትነት ተቀብሎ ወደ ቤቱ ወስዷታል፡፡ አደራውን አክብሮበመጠበቅና በማጽናናትም ፲፮ ዓመት ሲታዘዛት ኖሯል /ዮሐ.፲፱፡፳፭-፳፯/፡፡

ሐምሌ ፭ የሚነበበው መጽሐፈ ስንክሳር እንደሚገልጠው ቅዱስዮሐንስ የስብከቱን ሥራዉን በኢየሩሳሌምና በአከባቢው የጀመረውወደ አንጾክያ ሄዶም ያስተማረው ከቅዱስ ጴጥሮስ ጋር ነው፡፡ከኢየሩሳሌም እስከ አንጾክያ በፈረስ ፳ ቀን ያስኬዳል፡፡ ቅዱስዮሐንስና ቅዱስ ጴጥሮስ ግን በእግዚአብሔር ርዳታ በአንዲት ሌሊትደረሱ፡፡ ዮሐንስም ወደ ከተማይቱ ቀደም ብሎ ገባና ስለ ሀገሩ ጥናትሲያደርግ የሀገሩ ሰዎች እጅግ ክፉዎች እንደኾኑ ተረዳ፡፡ ምንምእንኳ በክፋታቸው ቢያዝንም ቅዱስ ጴጥሮስ አጽናንቶ አደፋፈረውናወደ ከተማይቱ ገብተው በክርስቶስ ስም ወንጌልን ሰበኩ፡፡ ጣዖትንከሚያመልኩ ሰዎች ብዙ መከራ ቢደርስባቸውም በአንጾክያ ውስጥተአምራትን እያደረጉና በስብከት በክርስቶስ ወንጌል ብዙ ሰዎችንአሳመኑ፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ከዚህ ሌላ ያስተማረባት ሀገር ሎዶቅያእንደምትባል ስንክሳሩ ይገልጣል፡፡ በከተማ አጠገብ ያለ ቄድሮስየሚባል ወንዝ ሞልቶ የሀገሪቱን ብዙ ንብረት በወደመ ጊዜ ቅዱስዮሐንስ ከቅዱስ ጴጥሮስ ዘንድ ሄደና በተአምራት የውኃውን ሙላትአቆመላቸው፡፡ ወደ ከተማዋም ገብቶ ብዙ ተአምራትን እያደረገወንጌልን ሰበከ፡፡ ካዩት ተአምራትና ከሰሙት ትምህርት የተነሣምብዙዎች አመኑ፡፡

ጥር ፬ በሚነበበው ስንክሳር እንደምናነበው ደግሞ ቅዱስ ዮሐንስ በሕይወቱ መጨረሻ አከባቢ ያስተማረው በእስያ ሀገር ሲኾን ዋናመንበሩም ኤፌሶን ነበረች፡፡ ዮሐንስ ወደዚህች ከተማ የመጣውከደቀ መዝሙሩ ከአብሮኮሮስ ጋር ነው፡፡ የስብከት ሥራቸውንበቀጥታ መጀመር ስላልቻሉም ሮምና የምትባል አንዲት ሞግዚትቤት ውስጥ ባሮች ኾነው ገቡ፡፡ እርሷም ዮሐንስን እንጨት ፈላጭ፣አብሮኮሮስን ደግሞ ውኃ ቀጅ አደረገቻቸው፡፡ አንድ ቀንከምታሳድጋቸው ልጆች አንዱን ይዛ ወደ ቤተ ጣዖት ስትገባዮሐንስና አብሮኮሮስ አብረዋት ገቡ፡፡ ያን ጊዜ በቤተ ጣዖቱ ያደረውሰይጣን እነ ቅዱስ ዮሐንስን ሲያይ የቤቱን ዕቃ አደናብሮ ወጣ፡፡አስከትላው የነበረው ልጅም በድንጋጤ ሞተ፡፡ ያን ጊዜ “የእናንተመምጣት ነው ለዚህ ኹሉ ያበቃኝ” ብላ ደበደበቻቸው፡፡ ቅዱስዮሐንስም “አስነሡልኝ አትዪምን?” ብሎ መለሰላት፡፡ “ያሁኑ ይባስ!ከመቼ ወዲህ ነው ደግሞ የሞተ ሰው የሚነሣው?” ብላ የበለጠተቆጣች፡፡ ይህን ጊዜ ቅዱስ ዮሐንስና አብሮኮሮስ ጸሎት አቅርበውአስነሡላት፡፡ በዚህ ተአምር አምና ተጠምቃለች፡፡ በቤቷምየምእመናን ጉባዔ ተመሠረተ፡፡ እርሷም ለዚያ እመምኔት አድርገውሾሟት፡፡ ከዚያም በኤፌሶንና በአከባቢዋ ወንጌልን ለመስበክ ሰፊ በርተከፈተለት፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ በኤፌሶን በሚያስተምርበት ጊዜ ከኔሮን ቄሣር ቀጥሎበሮም የነገሠው ድምጥያኖስ (፹፮-፺፮ ዓ.ም) የራሱን ምስል አሠርቶእንዲሰገድለት ወደ ኤፌሶን ላከ፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ግን ከምእመናንጋር ኾኖ ይህን ድርጊት ተቃወመ፡፡ ከዚያም ወደ ሮም ተወሰደናበፍል ውኃ ተሰቃይቶ በመንግሥት ላይ ያመፁ ኹሉወደሚታሠሩባት በደሴተ ፍጥሞ እንዲታሰር ተፈረደበት፡፡ ራዕዩንያየውና የጻፈውም በዚያ ቦታ ነው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ድምጥያኖስከተገደለ በኋላ ከግዞቱ ተመልሶ ሦስቱን መልእክታቱና ወንጌሉንእንደ ጻፈ ይነገራል፡፡

ስለ ቅዱስ ዮሐንስ የመጨረሻ ሕይወት ኹለት የተለያዩአመለካከቶች አሉ፡፡ አንደኛው በዮሐ.፳፡፳-፳፫ ላይ የተጻፈውንመነሻ በማድረግ “ዮሐንስ ሞትን አልቀመሰም” የሚል ሲኾንኹለተኛው ደግሞ በማር.፲፡፴፰-፴፱ የተጻፈውን ቃል በመጥቀስ“የጌታን የሞት ጽዋ ጠጥቷል፤ የሞትን ጥምቀት ተጠምቋል፤በግልጽ አነጋገር ሞቷል” የሚል ነው፡፡

አባ ጀሮም ስለ ወንጌላዊው ሲገልጥ ዮሐንስ የመጨረሻውን በምድር የኖረበትን የዕድሜ ዘመን በኤፌሶን ከተማ እንዳሳለፈው ጽፏል፡፡ በዚህ ወቅትም እጅግ ከማርጀቱ የተነሣ “እርስ በራሳችሁ ተዋደዱ ይህ የጌታችን ትእዛዝ ነውና ይህን ከጠበቃችሁ ይበቃችኋል” የምትለዋን ቃል ብቻ ለደቀ መዛሙርቱ ይነግራቸው ነበር፡፡ ይህ የዮሐንስ የዘወትር ትምህርቱ ነው፡፡ ደቀ መዛሙርቱም “አባታችን ለምን ኹል ጊዜ አንድ ዓይነት ትምህርት ታስተምረናለህ” ሲሉትም “ልጆቼ ይህ የጌታ ትእዛዝ ነው” በማለት ይመልስላቸው ነበር፡፡

ሐዋርያዊትና ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችን የወንጌላዊው በዓል በየዓመቱ ጥር ፬ እና በየወሩ በ፬ እርሱ የደረሰው የቁርባን ምስጋና እንዲቀደስ ታዛለች፡፡


ቅዱስ ዮሐንስና የጌታ ሥዕል


ለጌታችን ሥዕል ምንጭ ከኾኑት አንዱ ወንጌላዊ ዮሐንስ ነው፡፡ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተሰቀለበት ዘመን የነበረው የሮማ ቄሣርጢባርዮስ ቄሣር ይባላል፡፡ የቄሣሩ ልጅም ታማሚ ነበር፡፡ ቄሣሩምየጌታን የማዳን ሥራ እየሰማና እነ ጲላጦስንም የጻፉለትን ደብዳቤእየተመለከተ “ከዚያ ደግ ሰው መቃብር ወስዶ ልጄን ማንባሳለመልኝ?” እያለ ይመኝ ነበር፡፡ በመጨረሻም ልጁን ወስደውበጌታ መቃብር ላይ ሲያኖሩት ከሕመሙ ስለተፈወሰለት ፍቅሩንለመግለጥ የጌታን ሥዕል የሚሥልለት ሰው ያፈላልግ ጀመር፡፡ከዚያ በኋላም ዮሐንስ ወልደ ነጐድጓድ ተገኘና ልክ በዕለተ ዓርብእንዳየው አድርጐ ሥሎ ሰጠው፡፡

ቅዱስ ዮሐንስና አስቸጋሪው የሽፍቶች አለቃ


አንድ ጊዜ ቅዱስ ዮሐንስ ከኤፌሶን ከተማ ተነሥቶ ክርስቲያኖችንለማስተማር ሲዘዋወር ወደ አንድ ትልቅ ከተማ ገባ፡፡ በዚያች ከተማየሚገኙ ምእመናንም ጊልስ ስለሚባልና በዐሥራዎቹ ዕድሜ ክልልስላለ አንድ ወጣት ታሪክ አጫወቱት፡፡ ወጣቱን በጣም ይወዱትስለነበርና እናትና አባቱ ስለሞቱ “የሚንከባከበውና የሚያስተምረውካጣ ሊበላሽ ይችላል” ብለው ለቅዱስ ዮሐንስ ነገሩት፡፡

ቅዱስ ዮሐንስም ይኽንን ሲሰማ ወጣቱ ጊልስን ወደ ከተማይቱ ጳጳስወሰደውና “እንደ ልጅህ ተንከባከበው፤ እውነተኛ ክርስቲያንምአድርገው” ብሎ ሰጠው፡፡ የከተማዋ ጳጳስም ደግ ስለነበረ ጊልስንበደስታ ተቀበለው፡፡ ዘወትርም ያስተምረውና ይንከባከበው ነበር፡፡በመጨረሻም የአከባቢው ምእመናን በተሰበሰቡበት ጊልስተጠመቀ፡፡

ከዚህ በኋላ ግን ነገሮች መቀያየር ጀመሩ፡፡ እኒያ አባት ሥራ በጣምሰለበዛባቸው ጊልስን “መቼም ተጠምቋል” ብለው እንደ በፊቱመቆጣጠርና ማስተማሩን ተዉት፡፡ ጊልስም የለመደው የአባትነትፍቅር ሲያጣ ወደ ከተማ ወጣ ብሎ ከእኩዮቹ ጋር መቀራረብጀመረ፡፡ ጓደኞቹ ግን መልካም አልነበሩም፡፡ ጠጭዎች፣ቁማርተኞችና ተደባዳቢዎች ነበሩ፡፡

አንድ ቀን ማታ በአንድ መጠጥ ቤት ውስጥ ጊልስና ጓደኞቹ ሲጠጡአመሹ፡፡ኹሉም ሰክረው በያሉበት ሲወደቁ ጊልስ ብቻውን ቀረ፡፡በመጨረሻም የኹሉንም የመጠጥ ሒሳብ ከፍሎ ያለውን ገንዘብጨረሰ፡፡ በነጋታው ጊልስ ለጓደኞቹ “ለእናንተ ስል ገንዘቤን ኹሉአባከንኹ፤ አሁን ባዶ ኪስ ሆኛለኹ” ብሎ ነገራቸው፡፡ ኹሉምሳቁበትና “ጅሉ ጊልስ! እኛ ገንዘብ ከየት የምናመጣ ይመስልኻል?ይልቅ የምታገኘውን አጋጣሚ ተጠቅመኽ ስረቅ” አሉት፡፡

በዚህ መሠረት ጊልስና ኹለቱ ጓደኞቹ የአንድ ሰው ቤት ሰብረውገቡና ገንዘቡንና ጌጣጌጡን ዘረፉ፡፡ በዚህም የተነሣ ጊልስ “መስረቅማለት በጣም ቀላል ሥራ ነው” ብሎ አመነ፡፡ ከዚያ በኋላ ጊልስናጓደኞቹ የታወቁ ዘራፊዎች ኾኑ፡፡ እነርሱ ባሉበት መንገድ ማንምበጤና ማለፍ አይችልም ነበር፡፡ አንድ ቀን ሰው ሲደበድቡ ነፍሱበእጃቸው ስለ ጠፋች ጊልስና ጓደኞቹ ከተማዋን ጥለው ጠፉ፡፡ከጥቂት ጊዜ በኋላም የጊልስ ስም በአከባቢው እየገነነ ስለ መጣ ሰውኹሉ ይፈራው ጀመር፡፡ እርሱና ጓደኞቹ አላፊ አግዳሚውንአላስቀምጥ አሉ፡፡ መንገደኞች ኹሉ በሰላም መጓዝ፣ ነጋዴዎችምበጤና መነገድ አልቻሉም፡፡ ጊልስ አለቃቸው ነበር፡፡ መግደልናመዝረፍም የዘወትር ሥራቸው ኾነ፡፡

ከጥቂት ዓመታት በኋላ ግን ቅዱስ ዮሐንስ ወደዚያች ከተማ መጣ፡፡እኒያን ጳጳስም ስለ ወጣቱ ጊልስ ጠየቃቸው፡፡ እርሳቸውም በጣምአፍረውና አዝነው፡- “ያልከኝን አልሰማኹም፤ ያዘዝኸኝንምአልፈጸምኩም፡፡ ጊልስ ዛሬ ሰው ኹሉ የሚፈራው ወንበዴ ኾኗል፡፡ዛሬ አላፊ አግዳሚውን አያስቀምጥም፡፡ ይህ ኹሉ ግን የእኔ ስሕተትነው” በማለት በፊቱ አለቀሱ፡፡

ቅዱስ ዮሐንስም ይህንን ሲሰማ በእጅጉ አዘነ፡፡ ወዲያውም ጊልስያለበትን ጠየቀና በፈረስ እየጋለበ ተጓዘ፡፡ የአከባቢው ምእመናን“ጨካኝ ናቸውና ይገድሉኻል” ቢሉትም አልተመለሰም፡፡

በተባለው ቦታ ሲደርስም ኹለቱ ሽፍቶቹ አገኙት፡፡ ወዲያውምጩቤያቸውን መዝዘው ከፊቱ ቆሙ፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም ፍቅርበተሞላበት ንግግር “እርሱ የድሮ ጓደኛዬ ነውና ከመግደላችሁ በፊትእባካችሁ ወደ አለቃችሁ ውሰዱኝ?” አላቸው፡፡

ሽፍቶቹም እየሳቁ ወደ አለቃቸው ዘንድ ወሰዱት፡፡ ጊልስ መጣ፡፡ቅዱስ ዮሐንስም በፍቅርና በፈገግታ ተመለከተው፡፡ ጊልስዐወቀው፡፡ ደነገጠ፡፡ ዘወር ብሎም መሮጥ ጀመረ፡፡ ያን ታላቁን ሰውዮሐንስን ፈራ፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም “ልጄ ለምን ትሸሻለህ? እኔ አባትህነኝ ምንም የሚጐዳ መሣርያም አልያዝኩም” አለው፡፡ ያ ጨካኝየሽፍቶች አለቃ ምርር ብሎ አለቀሰ፤ አነባ፡፡ መሣርያውን ኹሉአምዘግዝጎ ጣለ፡፡ ጓደኞቹንም፡- “እኔ ወደ ጌታዬ መመለሴ ነውናደኅና ኹኑ” አላቸውና ከቅዱስ ዮሐንስ ኋላ ተፈናጥጦ ወደ ጥንቱቦታው ተመለሰ፡፡ ትቷት ሄዶ በነበረችይቱ ቤተ ክርስቲያንም ዕድሜልኩን እግዚአብሔርን እያገለገለ ኖረ፡፡



ቅዱስ ዮሐንስና ምሳሌው


ቅዱስ ዮሐንስ ከአራቱ እንስሶች መካከል በንስር ይመሰላል፡፡በንሥር የመመሰሉ ምክንያትም እንዲህ ነው፡፡ በሥነ አንስርት(አሞሮች) ጥናት ሊቃውንት እንደሚነገረው ንስር ዐይኑ ፅሩይ ነው፡፡ወደ ላይ መጥቆ ይበራል፡፡ ወጥቶ ረቦ ቁልቁል በተመለከተ ጊዜምየሰናፍጭ ቅንጣት የምታኽል ሥጋ ብትኾንም አትሰወረውም፡፡ያቺን አንሥቶ ይመገባታል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም አካልና ሕልውናተገልጦለት፣ ንጽሐ ሥጋ ንጽሐ ነፍስ ንጽሐ ልቡና ተሰጥቶት“ቀዳሚሁ ቃል” ብሎ ተናግሯልና፡፡ ይህም መጥቆና ረቅቆ የሚያስብልዑለ ስብከት መኾኑን ያመለክታል፡፡ ዳግመኛም ንስር በእግሩይሽከረከራል፤ በክንፍ መጥቆ ይበራል፡፡ በእግር እንዲሽከረከርዮሐንስም እንደ ወንድሞቹ “ወልደ እጓለ እምሕያው ከሰማይ ወረደተወለደ” እያለ ይጽፋል፡፡ በክንፍ መጥቆ እንዲበር እርሱም አካልከሕልውና ተገልጦለት “ቀዳሚሁ ቃል” ብሎ ተናግሯልና፡፡

በዚህ ዕለት ቅዱሱ ሐዋርያ ከእናቱ ‪ማርያም_ባውፍልያ ከአባቱ ‪ ዘብዴዎስ መወለዱን ቤተ ክርስቲያን ታስተምራለች:: በረከቱ ይደርብን እኛንም በቅዱሱ ምልጃ ይማረን፡፡




Saturday, 6 January 2018

እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነው



በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

በዲ/ን ፍሬው ለማ


ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያናችን በየዓመቱ ከምታከብራቸው በዓላት መካከል የጌታችን ልደት ገና እነሆ ደረሰ፡፡ ቅዳሴያዊ የሆነው ዘመን አቆጣጠራችን ዘመኑን በመንገድ ጠራጊው በመጥምቁ ዮሐንስ በዓል ጀምሮ እነሆ የጌታን ልደት የምናከብርበት ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡ ይህንንም በዓል ነቢያት ተስፋ እንዳደረጉት ተስፋን ሠንቀን በጾም የምንጠባበቀው ነው፡፡ በተለይም ከልደት በዓል አስቀድሞ ያሉትን ሰንበታት በተለየ ኹኔታ ስለጌታ መምጣት ስለነቢያቱ ተስፋና ስለእውነተኛው ጠባቂ በስፋት የሚተነተንበት ነው፡፡በተለይ ስብከት ብርሃን እና ኖላዊ በምንላቸው ሰንበታትም የበዓሉን ዜና ማብሰር እንጀምራለን፡፡
በኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን የአምልኮ ሥርዓት መሠረት በዓላት ያለቅድመ ዝግጅት አይከበሩም፡፡ ምዕመናንም ከዚህ ቀጥሎ ምን ይሆን? እያሉ የሚደናገሩበት በዓል የለንም፡፡ ለምሳሌ በዕለተ ዓርብ የጌታ ትንሣኤ ከሕማሙ ጋር አስቀድመን እናውጃለን ‹‹ ለመስቀልከ ንሠግድ  ኦ ሊቅነ ወለትንሣኤከ ቅድስት ንሴብሕ ኩልነ ይእዜኒ ወዘልፈኒ›› የቤተክርስቲን የሥርዓተ አምልኮ ቀለሞች ታሪክን የሚያስታውሱ ብቻ አይደሉም፡፡ ይልቁኑም የእግዚአብሔር ኃይሉን እና ፍቅሩን የምንካፈልባቸው ጊዜያት ናቸው እንጂ፡፡ የጌታን ብርሃንነት በመረዳት በመንፈስ ቅዱስ ተመልተን በኩረ በዓላት ልደትን ለማክበር እንዘጋጅ፡፡
የአዳምን የተስፋ ቃል ለመፈጸም ወልድ ሰው ሆነ፡፡ ተደርጎ የማያውቅ ከእንግዲህም የማይደረግ በይሁዳ  በቤተልሔም ተደረገ፡፡ ምድር አምላኳን አስተናገደች በረት መንግስተ ሰማያትን መሠለች መልዐኩም በደስታ ቃል ተመልቶ ለፍጥረት ሁሉ ደስታ ለእመቤታችን ደስ ይበልሽ አላት፡፡ ታላቅ ደስታ የምሥራችም እንደሚደረግ ተናገረ ይህን ታላቅ ደስታ ሁልጊዜ እናስበው ዘንድ ይገባናል ልደት ዓመታዊ ቀን አይደለም፤ ገና ታሪካዊ ሁኔታን የምናስብበት ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁኑም ነፍሳችን በደስታ የሚመላበት እንደእረኞቹ ሕጻኑን እና እናቱን እናይ ዘንድ የምንቸኩልበት እንደጥበብ ሠዎች ያለንን የከበረውን ሁሉ ለእርሱ የምንገብርበት ነው፡፡ እንደመላዕክት ቃላት እስኪያጥረን ድረስ ለእግዚአብሔር ምስጋና የምናቀርብበት በስብሐተ እግዚአብሔር የምንፋጠንበት ነው፡፡


አረጋዊ ተወልደ በአምሳሊከ ከመ ይለድከ በአምሳሊሁ እንዳለ እርሱን አስመስሎ ይወልደን ዘንድ አስቀድሞ እኛን መስሎ እንደተወለደ እናስተውል ፡፡ ለእርሱ በባሕርይ የሆኑትን ሁሉ እኛ በፀጋ ተካፋይ እንድንሆን አድሎናልና ደስ ይበለን፡፡ ሥጋችንንም ነፍሳችንን ነስቶ ሰው እንደሆነ እናስተውል፡፡ በዚህ  መንሣቱም የነሳቸውን ሁሉ አዳነ እንዲህም ከሆነ በሥጋችን ኃጢአት እንዳይነግስ መዋጋትን ቸል አንበል፡፡ ከሌሎች ቀናትም በበለጠ በገና ዕለት ይህን እናደርግ ዘንድ እንቸኩል፡፡
‹‹ ከእኔ ዘንድ ያለሽ ይቅርታ አያልቅም፥የሰላምሽ ቃል ኪዳንም አይጠፋም፥መሐሪሽ እግዚአብሔር ይህን ተናግሮአልና›› ኢሳ 54፡10 እንዳለ ነቢዮ ኢሳይያስ የተገናን ሆነን ተገኝተን ሳይሆን ስለፍፁም ፍቅሩ እንድንበት ዘንድ ወደደ፡፡ይህም መድኃኒት ይሆነን ዘንድ ነው ዘወትር በጸሎተ ሃይማኖት ‹‹ዘበእንተ መድኃኒትነ ወረደ እም ሰማያት›› እንደምንለው ነው፡፡ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን ወደ ዓለም ላከ፡፡ በዓለም ይፈርድ ዘንድ አይደለም ፡፡ ዓለም ሁሉ በእርሱ ይድን ዘንድ ወደደ እንጂ (ዮሐ 3፡17) የሰውን ነፍሳት ብቻ ሳይሆን አካላቸውን ይፈውስ ዘንድ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆነ፡፡ የሰውን ልጅ ብቻ አይደለም ፍጥረታትን ሁሉ ያስተካክል ዘንድ ቀዳማዊ ቃል ሰው ሆነ፡፡  በቀዳሚ አዳም የተነሣ ምድር ተረገመች በዳግማዊ አዳም ክርስቶስ የተነሣ ደግሞ  ምድር ተባረከች፡፡
በዓለም ላይ  ካሉ ሰዎች ዘንድ ክርስቲያኖች ላይ ከሚቀርቡ ክሶች(አስተያየቶች) እዱ ደስተኞች አይደሉም የሚለው ነው፡፡ ክርስቲያን ሆኖ   ደስተኛ አለመሆነ በራሱ የሚጋጭ ነው መራሪ፤የሚኮንን ፤የሚወቅስ ፤የማይረካ ሆነን ክርስቲያን ነን ብለን አፋችንን ሞልተን ማውራት አንችልም፡፡ ተስፋችንን በክርስቶስ ባለማድረጋችን ደስታችን ተወስዶብናል እኛ የክርስቶስ ደስታ ነንና ‹‹ በእነርሱ ደስታዬ ፍፁም  ይሆን ዘንድ ይህን በዓለም እናገራለሁ›› ዮሐ 17፡13 እንዳለ ክርስቶስም የእኛ ደስታ ነው፡፡ በተለይ በገና ይህን አብዝተን እናስባለን ስለዚህም ክርስቲያን ከማያስብሉን ምግባራት እንራቅ፡፡ ከዚህ  ዓለም ገዥ ራሳችንን ነጻ እናውጣ፡፡(ዮሐ 12፡31) እኛ ሰማያውያን ነንና የሆነውንና የሚሆነውን በማሰብ እንጨነቅ ዘንድ አይገባም እግዚአብሔር በመግቦቱ ከእኛ ጋር እንዳለ እናስተውል፡፡ ክርስቲያን መሆን በዓለም ያለ ብቸኛ ደስታ ነውና ዕፁብ ድንቅ እያልን በደስታ እንድንኖር ከሚያደርጉን ነገሮች አንዱ የጌታ ልደት ነው፡፡ በመደነቅ ውስጥ ካልሆነ ማንም ሊመረምረው የማይችላቸውን የእግዚአብሔርን ሥራዎች እናስተውል፡፡ በመንግሥተ ሰማያት እንኖረው ዘንድ የምንናፍቀውም ይህንን ዓይነት ደስታ ነው፡፡ ‹‹ወደ ጌታህ ደስታ ግባ›› እንደተባለ
ከልደቱ በረከት ተሳታፊ ያድርገን፡፡
ስብሐት ለእግዚአብሔር

Monday, 1 January 2018

የወርቃማዉ ዘመን ወርቃማ ደራሲ ቅዱስ አፈ በረከት አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ




ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ከቅዱስ ያሬድ በመቀጠል ወደር አቻ አምሳያ የሌለዉ ነዉ፡፡ ከትምህርቱ ጣፋጭነት፣ ለቤተክርስቲያን ካለዉ ፍፁም ፍቅር፣ ይልቁኑም ዘመናትን ተሻግረዉ የሚሄዱ የሚነበቡ የሚተረጎሙ መጻህፍትን የጻፈ፣ የኢትዮጵያን ምድር ያበራት የክብር ኮከብ ነዉ፡፡ ዜና ገድሉም ስለዚህ ቅዱስ አባት ሲናገር የኢትዮጵያ ብሩህ ፀሀይ፣ የሃይማኖት መጋቢ መምህር፣ የቋንቋዎች አባት የጥበባት ባህር፣ የቤተ ክርስትያን ፋና፣ እዉነተኛ ካህን፣ የሥላሴን ሚስጥር የሚናገር ወንጌላዊ፣ በድንግል ምስጋና የሚቆምና የሚያመሰግን፣ ከሀዲዮችን የሚረታ …… እያለ እጅግ በሚጥሙ ዉብ ቃላት ያመሰግነዋል፡፡
ይህ ቅዱስ አባት እንደ ሰማዕታት ግርፋትንና እስራትን፣ እንደ ሊቃዉንት መናፍቃንን የሚረታ፣ እንደ መሐንዲስ ሐናጺ፣ የሕግና የሥርዐት የሚስጥራት የትርጓሜያት መመህር፣ የጸሎትና የትምህርት መጻሕፍት ደራሲ፣ የሥርዐተ ገዳምና ማህበረ መነኮሳት አባት፣ በድርሰት እስካሁን በሀገራችን ተወዳዳሪ የሌለዉ ነዉ፡፡ እጆቹ ከብእር በተጨማሪም ከጠንካራ ሥራ ሳይቦዝኑ ዋሻ ሲፈለፍል የዉኃ ጉድጓድ ሲቆፍር ድልድይ ሲሰራ ኖሯል አንደበቱ እና ህሊናዉ ከምስጋና ሳያቋርጡ ለቤተክርስቲያን የጸሎት እና የምስጋና ሥርዓት ሲሰራ ኖሯል፡፡ ስለዚህ ቅዱስ አባት ተነግሮም ሆነ በቀላሉ ተጽፎ የሚያልቅ አይደለም ሆኖም እግዚአብሔር የፈቃደልንን ያህል  መጻፍ እንጀምራለን፡፡
ዉልደትና እድገት
  • የአባታችን የአባ ጊዮርጊስ አባቱ ሕዝበ ጽዮን እናቱ እምነ ጽዮን ይባላሉ፡፡ እግዚአብሔርን የሚፈሩ ደጋግ ነበሩ ነገር ግን ልጅ ስለሌላቸው ዘወትር እያዘኑ ወደ እግዚአብሔር ይጸልዩ ነበር፡፡ የነገሩት የማይረሳ የለመኑትን የማይነሳ እግዚአብሔር መላእኩ ቅዱስ ኡራኤልን ልኮ አበሰራቸዉ፡፡ አባታችንም ታህሳስ 3 ቀን ተጸንሶ ሐምሌ 7 ቀን ተወለደ፡፡ መልኣኩም በብስራቱ እንደነገራቸዉ ስሙን ጊዮርጊስ አሉት አንድም ሊቀ ሰማእቱን ይማፀኑት ነበርና እንደርሱ የእምነት ምስክር እንዲሆንላቸዉ ጊዮርጊስ አሉት፡፡
  • አባ ጊዮርጊስ የመጀመርያውን የቤተ ክርስቲያን ትምህርት የተማረው ከአባቱ ሲሆን ካስተማረውም በኋላ በዘመኑ ጳጳስ ከነበሩት ከአባ ሰላማ መተረጉም ዘንድ ወስዶ ዲቁና አሹሞታል፡፡
  • ዲቁና ከተቀበለ በኋላ ለትምህርት ወደ ሐይቅ እስጢፋኖስ ተላከ፡፡ ሐይቅ እስጢፋኖስ የተለያዩ ሊቃውንት የሚገኙባት፣በብዙ መጻሕፍት የተሞላችና ዙሪያዋን በሐይቅ በመከበቧ የተማሪን ሃሳብ ለማሰባሰብ አመቺ የሆነች ቦታ ናት፡፡ አባ ጊዮርጊስ በሐይቅ እስጢፋኖስ ትምህርት አልገባው ብሎ ለሰባት ዓመታት ተቀምጦ ነበር፡፡ አብረውት የሚማሩት ተማሪዎች ይህ ትምህርት የማይገባው ስለ ምንድን ነው? በእርሱ ኃጢአት ነው ወይስ በወላጆቹ ? ይሉት ነበር፡፡ በዚያ ጊዜ የሐይቁ መምህር የነበረው ዐቃቤ ሰዓት ሠረቀ ብርሃን ለአባቱ «ልጅህ ትምህርት አይገባውምና የቤተ መንግሥት ነገር አስተምረው» ብሎ መለሰው፡፡አባቱ ሕዝበ ጽዮን ግን «አንድ ጊዜ ለእግዚአብሔር ሰጥቼዋለሁ፤ እዚያው ገዳሙን ያገልግል » ብሎ እንደ ገና ላከው፡፡
  • አባ ጊዮርጊስ ዕውቀት ስለ ተሠወረው ሁልጊዜ በሥዕለ ማርያም ሥር እየተንበረከከ ይጸልይ ነበር፡፡ የሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳምንም እህል በመፍጨት ያገለግል ነበር ፡፡ አባታችን እህል ይፈጭበት የነበረዉ የድንጋይ ወፍጮ አሁንም በሐይቅ ይገኛል፡፡ ከእለታትም በአንድ ቀን እመቤታችን ተገለጠችለትና «አይዞህ ዕውቀት የተሠወረብህ ትምህርት ስለማይገባህ ሳይሆን የእግዚአብሔር ድንቅ ሥራ እንዲገለጥ ነውና ታገሥ» አለችው፡፡ በሱባኤም እንዲጠብቃት ነግራችዉ አባታችንም በተስፋ በስእለ ማርያም ፊት እየተማፀነ ሱባኤ ያዘ በነሀሴ በ21 ቀንም እመቤታችን ቅዱስ ኡራኤልን አስከትላ መጣች ጽዋዕ ልቦናም አጠጣችው፡፡
  • ከዚህ በኋላ በሐይቅ እስጢፋኖስ ትምህርቱን በሚገባ ተምሮ አጠናቀቀ፡፡ በዕውቀቱም ቀድሞ የሚያውቁት ሁሉ ይደነቁበት ነበር፡፡


መምህርነት
  •  የማስተማር ሥራውን የጀመረው በዚያው በሐይቅ እስጢፋኖስ መሆኑን ገድሉ በሚከተለው መልኩ ይገልጠዋል «ወአብርሃ ለቤተ ክርስቲያን እንተ ተሐንጸት በሐይቅ ባሕር፣ ወእም አሜሃ አሐዙ ይስአሉ እም ኀቤሁ ኩሎሙ ሰብአ ሀገር ቃለ መጻሕፍት ወትርጓሜሆሙ፣ ወኩሉ ቃለ ማኅሌት፡፡»
  • አባታችን በቅዱስ ያሬድ የዜማ ትምህርት ሊቃዉንት መካከል 10ኛ የዜማ መምህር ነዉ፡፡ የቅዱስ ያሬድን ዜማ በዘመንና በየበዓላቱ ከፋፍሎ ማስተማር የጀመረዉ እርሱ ነዉ፡፡ አባታችን የተማረበትና ብዙ ደቀ መዛሙርት ያፈራበት ቦታ ደብረ እግዚአብሔር ይባላል፡፡
  • በዜማዉ ከቅዱስ ያሬድ በኋላ የተነሳዉ ዳግማዊ ያሬድ ይባላል፡፡ አፄ ዳዊትም የደብረ ነጎድጓድ የዜማ ምስክር አድርገዉ ሾሞታል፡፡
  • ከሐይቅ በኋላ በዚያ ዘመን ሸግላ በመባል ትጠራ ወደ ነበረችው ወደ ትውልድ ሀገሩ ወደ ጋሥጫ ተጓዘ፡፡ አባ ጊዮርጊስ ወደ ሸግላ ሲመጣ አባቱ በጣም አርጅቶና መንኩሶ ነበር፡፡ ስለዚህም በአባቱ እግር ተተክቶ በቤተ መንግሥቱ ያለችውን ሥዕል ቤት እንዲያገለግል ወደዚያው አስገቡት፡፡
  •  በቤተ መንግሥቱም የንጉሡን ልጆች ከማስተማሩም በላይ በቤተ መንግሥቱ ዙርያ ከነበሩት ሊቃውንት መካከል አባ ጊዮርጊስ አንዱ ነበር፡፡ በቤተ መንግሥቱ በነበረ ጊዜም የንጉሡን ልጆች ይስሐቅን፣ ቴዎድሮስን፣ እንድርያስን፣ ሀብተ ኢየሱስን፣ ሕዝቅያስን፣ ኢዮስያስን፣ ዘርዐ ያዕቆብንና ሴት ልጁን እሌኒን በምግባርና በሃይማኖት ቀርጿቸዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል ዘርዐ ያዕቆብ በድርሰቱ ሲመስለው ቴዎድሮስ ደግሞ በሕይወት መስሎታል፡፡ ዐፄ ዳዊት የአባ ጊዮርጊስን ሊቅነትና መልካም ሥነ ምግባር በሚገባ ስላወቀ በጋብቻ ሊዛመደው ወዶ ስለነበር ልጁን እንዲያገባ ዘወትር ይጠይቀው ነበር፡፡
ምንኩስና
  •  አባ ጊዮርጊስ የዐፄ ዳዊት ጥያቄ ስለበዛበት ወደ አቡነ በርተሎሜዎስ ሄዶ ቅስናን ተቀብሎ የአመክሮ ልብስን ለበሰ፡፡ እስከ አፄ ይስሀቅ ዘመን አንደዚህ ኖረ፡፡
  •  አፄ ይስሀቅ በነገሰ ጊዜ አባታችን ምንኩስናን ይቀበል ዘንድ ወደ አባታችን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም ወደ ደብረ ሊባኖስ በእጨጌ ዮሃንስ ከማ ዘመን መጣ፡፡ የዚህ ገዳም መነኮሳት እንደ አባታቸዉ ደጋግ ቢሆኑም ቀዳሚት ሰንበትን የሽሩ ነበርና ስለዚህ ስራቸዉ ከዚያ ሄደ ድንግልና ሰማዕት ወደ ሆነዉ ወደ አባታችን አባ በጸሎተ ሚካኤል መቃብር ደረሰ በዚያም ፍጹም ከሆነዉ የገዳሙ ኀላፊ ከ አባ ቴዎድሮስ የምንኩስና ልብስን ለበሰ፡፡
አባታችንና መናፍቃን
  • አባታችን አባ ጊዮርጊስ የመናፍቃን መዶሻ ነዉ፡፡ ለዚህም ‹‹ኢትዮጵያዊዉ ቄርሎስ ዐምደ ሃይማኖት›› ተብሎ ተጠርቷል፡፡ መናፍቃንን በማሳፈርና ምዕመናን በማስተማር በ መጻፍ (መጽሀፈ ሚስጥር፣ ፍካሬ ሀይማኖት )ብዙ ተጋድሏል፡፡ ለ አብነት ያህል በገድሉ የተመዘገበዉን አንድ ሃይማኖት ክርክር እንመልከት፡
  • ከአይሁድ መካከል አንዱ ከክርስቲያኖች ጋር በነገረ ሃይማኖት ለመከራከር ጥሪ አቀረበ፡፡ «ክርስቲያኖች ከረቱኝ ወደነርሱ ሃይማኖት እገባለሁ እኔ ከረታኋቸውም ወደኔ ሃይማኖት ይገባሉ» ሲል ነገሩን ጥብቅ አደረገው፡፡ ዐፄ ዳዊት ይህን ጉዳይ ሲሰማ በጣም ስለ ተናደደ ሊቃነ ካህናቱን፣ ንቡራነ እዱንና የመጻሕፍት ዐዋቂዎችን ሁሉ ከየሀገሩ እንዲሰባሰቡ አዘዘ፡፡ አይሁዳዊው በአንድ ወገን መምህራኑ በአንድ ወገን ሆነው ክርክሩን ጀመሩ፡፡
  • የመጀመርያው እድል የተሰጠው ለአይሁዳዊው በመሆኑ ቀጥሎ ያለውን ጥያቄ አቀረበ፡- «እናንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነው የምትሉት ይሄ ክርስቶስ እውነት የእግዚአብሔር ልጅ ከሆነ፣ ወደ ቢታንያ በመጣ ጊዜ አልዓዛር የተቀበረበትን ቦታ ሳያውቅ ቀርቶ 'አልዓዛርን የት ቀበራችሁትብሎ እንደ ጠየቀ በወንጌላችሁ ተጽፏል፡፡ ለዚህ መልስ ስጡኝ፣እኔንም ከመጽሐፈ ኦሪቴ ጠቅሳችሁ ጠይቁኝ? » ሲል የመከራከርያ ነጥቡን አቀረበ፡፡
  • በዚህ ጊዜ አባ ጊዮርጊስ ታሞ አልጋ ላይ ነበር፡፡ ሊቃውንቱም እንዲህ ያለው ነገር ያለ እርሱ አይሆንምና አባ ጊዮርጊስ ይምጣ ሲሉ ለዐፄ ዳዊት ጥያቄ አቀረቡ፡፡ አባ ጊዮርጊስም በአልጋ ላይ እያለ እንዲመጣ ተደረገ፡፡ በአልጋ ላይ ሆኖም በጉባኤው ላይ ተገኘ፡፡
  • ጉባኤተኞቹ የቀረበውን ጥያቄ ነገሩት፡፡ አባ ጊዮርጊስ የሰጠውን መልስ ገድሉ በሚከተለው መንገድ ይገልጥልናል «እኔ ግን በወንጌል ሳይሆን በኦሪት እከራከርሃለሁ፡፡ የምኩራብ መጻሕፍት ሁሉ ለቤተ ክርስቲያን የታወቁ ናቸውና፡፡ ምኩራብ ዘራች ቤተ ክርስቲያንም አጨደችው፤ ምኩራብ ፈተለችው ቤተ ክርስቲያን ለበሰችው፤ አዳምን በገነት ሳለ አዳም ሆይ ወዴት ነህ? ብሎ የጠየቀው ማነው? አብርሃምንስ ሚስትህ ሣራ ወዴት ናት? ብሎ የጠየቀው ማነው? እስቲ መልስልኝ? ሰይጣንንስ ከወዴት መጣህ? ብሎ የጠየቀው ማነው? እግዚአብሔር አብ አይደለምን በዚህ ጊዜ አይሁዳዊው መልስ አጥቶ ዝም አለ፡፡ ንጉሡ፣ ሊቃውንቱና መኳንንቱም እጅግ ተደሰቱ፡፡
§  የአባ ጊዮርጊስ የ ድርሰት ስራዎች ከ ብዙ በ ጥቂቱ
1. ኖኅተ ብርሃን /ከመጽሐፈ አርጋኖን ጋር አብሮ ታትሟል/
8. ፍካሬ ሃይማኖት
2. አርጋኖነ ውዳሴ
9. መጽሐፈ ምሥጢር
3. ሰዓታት ዘመዓልት ወዘሌሊት
10. ውዳሴ ስብሐት
4.ውዳሴ መስቀል
11. እንዚራ ስብሐት
5. ቅዳሴ
12. ሕይወተ ማርያም
6. ውዳሴ ሐዋርያት
13. ተአምኖ ቅዱሳን
7. ጸሎት ዘቤት ቤት
14. መጽሐፈ ብርሃን  ወዘተ

በዘመን ከነገሡ ነገስታት የደረሰበት ፈተና
  • መናፍቁ ቢቱ ተንኮል ሰርቶ  ንጉሥ ዳዊት ጋር አጣላዉ ንጉሡም ተንኮሉ ሳይገባዉ አባ ጊዮርጊስን በደም አበላ እስኪነከር ድረስ እንዲደበደብ አድርጎ ወደ እስር ቤት አስገባው፡፡ ዐፄ ዳዊት እስኪሞትና ልጁ ቴዎድሮስ እስኪነግሥ ድረስም በዚያ ቆየ፡፡ ቢቱ ግን በመልአክ ተቀስፎ ሞተ፡፡
  • አባ ጊዮርጊስ በወኅኒ ቤት እያለ ጴጥሮስና ጳውሎስ እየመጡ ያጽናኑት ነበር፡፡ዐፄ ዳዊት በሞተ ጊዜ አባ ጊዮርጊስ እጅግ አድርጎ አዘነ፡፡ እንዲያውም አንዳንዶች «በመሞቱ ደስ ልትሰኝ ይገባሃል እንጂ እንዴት ታለቅሳለህብለው ጠይቀውት ነበር፡፡ አባ ጊዮርጊስ ግን «ጥቂት ቢኖር እወዳለሁ፤ እመቤታችንን የሚወድ ሰው ነውና» ብሎ ነበር የመለሰው፡፡
  • ዐፄ ቴዎድሮስ አባ ጊዮርጊስን ከወኅኒ ቤት አውጥቶት በጥንቱ ቦታ አስቀመጠው፡፡ አባ ጊዮርጊስ ግን የቤተ መንግሥትን ነገር ለመሸሽ ስለ ፈለገ በጋሥጫ ከመቀመጥ ይልቅ ርቆ ጥንት ወደ ነበረበት ወደ ዳሞት በመሄድ ማስተማር ጀመረ፡፡ ወደ ዳሞት ሲሄድ እግረ መንገዱን ወደ ደብረ ሊባኖስ ገብቶ የአቡነ ተክለ ሃይማኖትን መቃብር ተሳልሟል፡፡ ነገር ግን በዕውቀቱ የሚቀኑበት፣ በችሎታው የሚመቀኙት ሰዎች ነገር ሠርተው ከንጉሥ ቴዎድሮስ ጋር ስላጣሉት እልም ካለ በረሃ እንዲጋዝ ተደረገ፡፡ አባ ጊዮርጊስ ከግዞት የወጣው ዐፄ ቴዎድሮስ ሲሞት ነበር፡፡
  • የአባ ጊዮርጊስ ሌላው ተማሪ የነበረው ዐፄ ይስሐቅ 1399 . መንግሥቱን ሲይዝ አባ ጊዮርጊስን ከግዞት አውጥቶ ወደ ጋሥጫ መለሰው፡፡ በዚያ ጊዜ አባ ጊዮርጊስ እድሜው 42 ዓመት ሲሆን በስደትና በጤንነት መታወክ የተነሣ ከባድ ጉዳት ደርሶበት ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ብዙውን ጊዜውን በጾም፣ በጸሎትና በድርሰት ያውለው ነበር፡፡
  •  አንድ ቀን ቴዎድሮስ የተባለ መስፍን፣ አባ ጊዮርጊስን ስለ ርትዕት ሃይማኖት ጠየቀው፡፡ አባ ጊዮርጊስም ፍካሬ ሃይማኖት  የተባለውን መጽሐፍ ደርሶ ሰጠው፡፡ ንጉሡና የምሥጢር ሊቃውንት የሆኑ ካህናት ይህንን በተመለከቱ ባነበቡ ጊዜ ‹‹ በእውነት ዮሐንስ አፈወርቅና አፈ በረከት የሆነው ቄርሎስ በዘመናችን ተነሥተዋል፡፡ ኢትዮጵያም ቁስጥንጥንያን መስላለች፣ ከእስክንድርያም በላይ ከፍ ከፍ ብላለች›› ብለው አደነቁ ፡፡
  • አባ ጊዮርጊስ መከራ ያልተለየው አባት ነበር፡፡ ገድሉ እንደሚተርከው በቤተ መንግሥቱ የነበሩ ሰዎች የርሱን መከበርና መወደድ አይፈልጉትም ነበር፡፡ በተለይም ፍካሬ ሃይማኖት  የተሰኘውን መጽሐፍ በመጻፉ የተነሣ መከበሩ አልተዋጠላቸውም፡፡ ስለዚህም ነገር ሠርተው ከዐፄ ይስሐቅ ጋር አሁንም አጣሉት፡፡
  • ዐፄ ይስሐቅ አባ ጊዮርጊስን አሳስሮ ውኃ ወደማይገኝበት ዐለታማ ቦታ አጋዘው፡፡ በዚያም በመከራ ለብዙ ጊዜ ኖረ፡፡ በዚያ እያለ ዘወትር በጸሎት አብዝቶ ይተጋ ነበር፡፡ እግዚአብሔርም ዐፄ ይስሐቅ ወደ ልቡናው እንዲመለስ አደረገ፡፡ ንጉሡ በአባ ጊዮርጊስ ላይ የፈጸመው ነገር ሁሉ ፀፀተው፡፡ አገልጋዮቹንም ጠርቶ አባ ጊዮርጊስን እንዲያመጡት አዘዘ፡፡ ነገር ግን እነዚያ ተንኮል ሠሪዎች የአባ ጊዮርጊስ መምጣት ተንኮላቸውን ስለሚያጋልጠው አባ ጊዮርጊስ ሞቷል ብለው አስወሩ፡፡ ይህንን ሲሰማ ዐፄ ይስሐቅ ፈጽሞ አዘነ፡፡
  • አባ ጊዮርጊስ ሞቷል እየተባለ መወራቱን ከደቀ መዝሙሩ ስለ ሰማ በሕይወት የመኖሩን ዜና ጽፎ ለዐፄ ይስሐቅ እንዲያደርስለት አውሎ ንፋስን ላከው፡፡ደብዳቤው ከአባ ጊዮርጊስ የተላከ መሆኑን ሲያውቅ ዐፄ ይስሐቅ ደነገጠ፡፡ እነዚያን መልእክተኞች ይዞ ወደ ወኅኒ ጨመራቸው፡፡ አባ ጊዮርጊስንም ከግዞት ያወጡት ዘንድ ላከ፡፡
  • አባ ጊዮርጊስ ወደ ቤተ መንግሥቱ ሲመጣ ንጉሡ በደስታ ተቀበለው፡፡ ደብዳቤውን በማን እጅ እንደ ላከውም ጠየቀው፡፡ አባ ጊዮርጊስም ደብዳቤውን በሰው ሳይሆን በእግዚአብሔር ፈቃድ በነፋስ እንደ ላከው አስረዳ፡፡ ከዚያም በኋላ ዐፄ ይስሐቅ ለአባ ጊዮርጊስ ምድረ ሰዎን የተባለውን የጳጳሳት መቀመጫ የነበረውን ሀገር በርስትነት ሰጠዉ፡፡ አባ ጊዮርጊስ በምድረ ሰወን ንጉሥ ይስሐቅ ክረምቱን ያሳልፍበት በነበረው ቦታ ላይ ቤተ ክርስቲያን ሠራ፡፡ በዚያም በማስተማርና በጾም በጸሎት ይተጋ ነበር፡፡
እረፍቱ ለ አባ ጊዮርጊስ
  • በጋሥጫ እያለ ዐፄ ይስሐቅ አስጠራው፡፡ በዚያ ጊዜ ንጉሡ የመናገሻ ማርያምን ቤተ ክርስቲያን አሠርቶ ስለ ነበር እንዲባርክለት ፈልጎ ነበር፡፡ አባ ጊዮርጊስ ምንም እንኳን በዚያ ጊዜ ታምሞ የተኛም ቢሆን ወደ ንጉሡ ተጓዘ፡፡ እዚያ ሲደርስ በጣም ተዳክሞ ነበር፡፡ ሥርዓቱን ለመፈጸምም ዐቅም አልነበረውም፡፡ ስለዚህም ንጉሥ ይስሐቅ በአልጋ ተሸክመውት እንዲዞሩና ቤተ ክርስቲያኗን እንዲባርካት አደረገ፡፡
  •  ቡራኬውን ከፈጸመ በኋላ ደቀ መዝሙሮቹን ሰብስቦ «ከሞትኩ አባቴ በጸሎተ ሚካኤል መከራ ወደ ተቀበለባትና እኔም ቤተ ክርስቲያን ወዳነፅኩባት ቦታ ወስዳችሁ ቅበሩኝ» ሲል አዘዛቸው፡፡ ለደቀ መዛሙርቱ የመጨረሻ የስንብት ትምህርቱን እያስተማራቸው እነርሱም በአልጋ ተሸክመውት ወደ ጋሥጫ እያመሩ ሳለ በመንገድ ላይ ሐምሌ ሰባት ቀን 1417 . 60 ዓመቱ ዐረፈ፡፡ 

‹‹የአባታችን የቅዱስ አፈበረከት አባ ጊዮርጊስ በረከታቸዉ ትደርብን››
‹‹ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወወላዲቱ ድንግል ወመስቀሉ ክቡር አሜን››