ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ከቅዱስ ያሬድ በመቀጠል ወደር አቻ አምሳያ የሌለዉ ነዉ፡፡ ከትምህርቱ ጣፋጭነት፣ ለቤተክርስቲያን
ካለዉ ፍፁም ፍቅር፣ ይልቁኑም ዘመናትን ተሻግረዉ የሚሄዱ የሚነበቡ የሚተረጎሙ መጻህፍትን የጻፈ፣ የኢትዮጵያን ምድር ያበራት የክብር
ኮከብ ነዉ፡፡ ዜና ገድሉም ስለዚህ ቅዱስ አባት ሲናገር የኢትዮጵያ ብሩህ ፀሀይ፣ የሃይማኖት መጋቢ መምህር፣ የቋንቋዎች አባት የጥበባት
ባህር፣ የቤተ ክርስትያን ፋና፣ እዉነተኛ ካህን፣ የሥላሴን ሚስጥር የሚናገር ወንጌላዊ፣ በድንግል ምስጋና የሚቆምና የሚያመሰግን፣
ከሀዲዮችን የሚረታ …… እያለ እጅግ በሚጥሙ ዉብ ቃላት ያመሰግነዋል፡፡
ይህ ቅዱስ አባት እንደ ሰማዕታት ግርፋትንና እስራትን፣ እንደ ሊቃዉንት መናፍቃንን የሚረታ፣ እንደ መሐንዲስ ሐናጺ፣ የሕግና
የሥርዐት የሚስጥራት የትርጓሜያት መመህር፣ የጸሎትና የትምህርት መጻሕፍት ደራሲ፣ የሥርዐተ ገዳምና ማህበረ መነኮሳት አባት፣ በድርሰት
እስካሁን በሀገራችን ተወዳዳሪ የሌለዉ ነዉ፡፡ እጆቹ ከብእር በተጨማሪም ከጠንካራ ሥራ ሳይቦዝኑ ዋሻ ሲፈለፍል የዉኃ ጉድጓድ ሲቆፍር
ድልድይ ሲሰራ ኖሯል አንደበቱ እና ህሊናዉ ከምስጋና ሳያቋርጡ ለቤተክርስቲያን የጸሎት እና የምስጋና ሥርዓት ሲሰራ ኖሯል፡፡ ስለዚህ
ቅዱስ አባት ተነግሮም ሆነ በቀላሉ ተጽፎ የሚያልቅ አይደለም ሆኖም እግዚአብሔር የፈቃደልንን ያህል መጻፍ እንጀምራለን፡፡
ዉልደትና እድገት
- የአባታችን የአባ ጊዮርጊስ አባቱ ሕዝበ ጽዮን እናቱ እምነ ጽዮን ይባላሉ፡፡ እግዚአብሔርን የሚፈሩ ደጋግ ነበሩ ነገር ግን ልጅ ስለሌላቸው ዘወትር እያዘኑ ወደ እግዚአብሔር ይጸልዩ ነበር፡፡ የነገሩት የማይረሳ የለመኑትን የማይነሳ እግዚአብሔር መላእኩ ቅዱስ ኡራኤልን ልኮ አበሰራቸዉ፡፡ አባታችንም ታህሳስ 3 ቀን ተጸንሶ ሐምሌ 7 ቀን ተወለደ፡፡ መልኣኩም በብስራቱ እንደነገራቸዉ ስሙን ጊዮርጊስ አሉት አንድም ሊቀ ሰማእቱን ይማፀኑት ነበርና እንደርሱ የእምነት ምስክር እንዲሆንላቸዉ ጊዮርጊስ አሉት፡፡
- አባ ጊዮርጊስ የመጀመርያውን የቤተ ክርስቲያን ትምህርት የተማረው ከአባቱ ሲሆን ካስተማረውም በኋላ በዘመኑ ጳጳስ ከነበሩት ከአባ ሰላማ መተረጉም ዘንድ ወስዶ ዲቁና አሹሞታል፡፡
- ዲቁና ከተቀበለ በኋላ ለትምህርት ወደ ሐይቅ እስጢፋኖስ ተላከ፡፡ ሐይቅ እስጢፋኖስ የተለያዩ ሊቃውንት የሚገኙባት፣በብዙ መጻሕፍት የተሞላችና ዙሪያዋን በሐይቅ በመከበቧ የተማሪን ሃሳብ ለማሰባሰብ አመቺ የሆነች ቦታ ናት፡፡ አባ ጊዮርጊስ በሐይቅ እስጢፋኖስ ትምህርት አልገባው ብሎ ለሰባት ዓመታት ተቀምጦ ነበር፡፡ አብረውት የሚማሩት ተማሪዎች ይህ ትምህርት የማይገባው ስለ ምንድን ነው? በእርሱ ኃጢአት ነው ወይስ በወላጆቹ ? ይሉት ነበር፡፡ በዚያ ጊዜ የሐይቁ መምህር የነበረው ዐቃቤ ሰዓት ሠረቀ ብርሃን ለአባቱ «ልጅህ ትምህርት አይገባውምና የቤተ መንግሥት ነገር አስተምረው» ብሎ መለሰው፡፡አባቱ ሕዝበ ጽዮን ግን «አንድ ጊዜ ለእግዚአብሔር ሰጥቼዋለሁ፤ እዚያው ገዳሙን ያገልግል » ብሎ እንደ ገና ላከው፡፡
- አባ ጊዮርጊስ ዕውቀት ስለ ተሠወረው ሁልጊዜ በሥዕለ ማርያም ሥር እየተንበረከከ ይጸልይ ነበር፡፡ የሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳምንም እህል በመፍጨት ያገለግል ነበር ፡፡ አባታችን እህል ይፈጭበት የነበረዉ የድንጋይ ወፍጮ አሁንም በሐይቅ ይገኛል፡፡ ከእለታትም በአንድ ቀን እመቤታችን ተገለጠችለትና «አይዞህ ዕውቀት የተሠወረብህ ትምህርት ስለማይገባህ ሳይሆን የእግዚአብሔር ድንቅ ሥራ እንዲገለጥ ነውና ታገሥ» አለችው፡፡ በሱባኤም እንዲጠብቃት ነግራችዉ አባታችንም በተስፋ በስእለ ማርያም ፊት እየተማፀነ ሱባኤ ያዘ በነሀሴ በ21 ቀንም እመቤታችን ቅዱስ ኡራኤልን አስከትላ መጣች ጽዋዕ ልቦናም አጠጣችው፡፡
- ከዚህ በኋላ በሐይቅ እስጢፋኖስ ትምህርቱን በሚገባ ተምሮ አጠናቀቀ፡፡ በዕውቀቱም ቀድሞ የሚያውቁት ሁሉ ይደነቁበት ነበር፡፡
መምህርነት
- የማስተማር ሥራውን የጀመረው በዚያው በሐይቅ እስጢፋኖስ መሆኑን ገድሉ በሚከተለው መልኩ ይገልጠዋል «ወአብርሃ ለቤተ ክርስቲያን እንተ ተሐንጸት በሐይቅ ባሕር፣ ወእም አሜሃ አሐዙ ይስአሉ እም ኀቤሁ ኩሎሙ ሰብአ ሀገር ቃለ መጻሕፍት ወትርጓሜሆሙ፣ ወኩሉ ቃለ ማኅሌት፡፡»
- አባታችን በቅዱስ ያሬድ የዜማ ትምህርት ሊቃዉንት መካከል 10ኛ የዜማ መምህር ነዉ፡፡ የቅዱስ ያሬድን ዜማ በዘመንና በየበዓላቱ ከፋፍሎ ማስተማር የጀመረዉ እርሱ ነዉ፡፡ አባታችን የተማረበትና ብዙ ደቀ መዛሙርት ያፈራበት ቦታ ደብረ እግዚአብሔር ይባላል፡፡
- በዜማዉ ከቅዱስ ያሬድ በኋላ የተነሳዉ ዳግማዊ ያሬድ ይባላል፡፡ አፄ ዳዊትም የደብረ ነጎድጓድ የዜማ ምስክር አድርገዉ ሾሞታል፡፡
- ከሐይቅ በኋላ በዚያ ዘመን ሸግላ በመባል ትጠራ ወደ ነበረችው ወደ ትውልድ ሀገሩ ወደ ጋሥጫ ተጓዘ፡፡ አባ ጊዮርጊስ ወደ ሸግላ ሲመጣ አባቱ በጣም አርጅቶና መንኩሶ ነበር፡፡ ስለዚህም በአባቱ እግር ተተክቶ በቤተ መንግሥቱ ያለችውን ሥዕል ቤት እንዲያገለግል ወደዚያው አስገቡት፡፡
- በቤተ መንግሥቱም የንጉሡን ልጆች ከማስተማሩም በላይ በቤተ መንግሥቱ ዙርያ ከነበሩት ሊቃውንት መካከል አባ ጊዮርጊስ አንዱ ነበር፡፡ በቤተ መንግሥቱ በነበረ ጊዜም የንጉሡን ልጆች ይስሐቅን፣ ቴዎድሮስን፣ እንድርያስን፣ ሀብተ ኢየሱስን፣ ሕዝቅያስን፣ ኢዮስያስን፣ ዘርዐ ያዕቆብንና ሴት ልጁን እሌኒን በምግባርና በሃይማኖት ቀርጿቸዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል ዘርዐ ያዕቆብ በድርሰቱ ሲመስለው ቴዎድሮስ ደግሞ በሕይወት መስሎታል፡፡ ዐፄ ዳዊት የአባ ጊዮርጊስን ሊቅነትና መልካም ሥነ ምግባር በሚገባ ስላወቀ በጋብቻ ሊዛመደው ወዶ ስለነበር ልጁን እንዲያገባ ዘወትር ይጠይቀው ነበር፡፡
ምንኩስና
- አባ ጊዮርጊስ የዐፄ ዳዊት ጥያቄ ስለበዛበት ወደ አቡነ በርተሎሜዎስ ሄዶ ቅስናን ተቀብሎ የአመክሮ ልብስን ለበሰ፡፡ እስከ አፄ ይስሀቅ ዘመን አንደዚህ ኖረ፡፡
- አፄ ይስሀቅ በነገሰ ጊዜ አባታችን ምንኩስናን ይቀበል ዘንድ ወደ አባታችን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም ወደ ደብረ ሊባኖስ በእጨጌ ዮሃንስ ከማ ዘመን መጣ፡፡ የዚህ ገዳም መነኮሳት እንደ አባታቸዉ ደጋግ ቢሆኑም ቀዳሚት ሰንበትን የሽሩ ነበርና ስለዚህ ስራቸዉ ከዚያ ሄደ ድንግልና ሰማዕት ወደ ሆነዉ ወደ አባታችን አባ በጸሎተ ሚካኤል መቃብር ደረሰ በዚያም ፍጹም ከሆነዉ የገዳሙ ኀላፊ ከ አባ ቴዎድሮስ የምንኩስና ልብስን ለበሰ፡፡
አባታችንና መናፍቃን
- አባታችን አባ ጊዮርጊስ የመናፍቃን መዶሻ ነዉ፡፡ ለዚህም ‹‹ኢትዮጵያዊዉ ቄርሎስ ዐምደ ሃይማኖት›› ተብሎ ተጠርቷል፡፡ መናፍቃንን በማሳፈርና ምዕመናን በማስተማር በ መጻፍ (መጽሀፈ ሚስጥር፣ ፍካሬ ሀይማኖት )ብዙ ተጋድሏል፡፡ ለ አብነት ያህል በገድሉ የተመዘገበዉን አንድ ሃይማኖት ክርክር እንመልከት፡
- ከአይሁድ መካከል አንዱ ከክርስቲያኖች ጋር በነገረ ሃይማኖት ለመከራከር ጥሪ አቀረበ፡፡ «ክርስቲያኖች ከረቱኝ ወደነርሱ ሃይማኖት እገባለሁ እኔ ከረታኋቸውም ወደኔ ሃይማኖት ይገባሉ» ሲል ነገሩን ጥብቅ አደረገው፡፡ ዐፄ ዳዊት ይህን ጉዳይ ሲሰማ በጣም ስለ ተናደደ ሊቃነ ካህናቱን፣ ንቡራነ እዱንና የመጻሕፍት ዐዋቂዎችን ሁሉ ከየሀገሩ እንዲሰባሰቡ አዘዘ፡፡ አይሁዳዊው በአንድ ወገን መምህራኑ በአንድ ወገን ሆነው ክርክሩን ጀመሩ፡፡
- የመጀመርያው እድል የተሰጠው ለአይሁዳዊው በመሆኑ ቀጥሎ ያለውን ጥያቄ አቀረበ፡- «እናንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነው የምትሉት ይሄ ክርስቶስ እውነት የእግዚአብሔር ልጅ ከሆነ፣ ወደ ቢታንያ በመጣ ጊዜ አልዓዛር የተቀበረበትን ቦታ ሳያውቅ ቀርቶ 'አልዓዛርን የት ቀበራችሁት?» ብሎ እንደ ጠየቀ በወንጌላችሁ ተጽፏል፡፡ ለዚህ መልስ ስጡኝ፣እኔንም ከመጽሐፈ ኦሪቴ ጠቅሳችሁ ጠይቁኝ? » ሲል የመከራከርያ ነጥቡን አቀረበ፡፡
- በዚህ ጊዜ አባ ጊዮርጊስ ታሞ አልጋ ላይ ነበር፡፡ ሊቃውንቱም እንዲህ ያለው ነገር ያለ እርሱ አይሆንምና አባ ጊዮርጊስ ይምጣ ሲሉ ለዐፄ ዳዊት ጥያቄ አቀረቡ፡፡ አባ ጊዮርጊስም በአልጋ ላይ እያለ እንዲመጣ ተደረገ፡፡ በአልጋ ላይ ሆኖም በጉባኤው ላይ ተገኘ፡፡
- ጉባኤተኞቹ የቀረበውን ጥያቄ ነገሩት፡፡ አባ ጊዮርጊስ የሰጠውን መልስ ገድሉ በሚከተለው መንገድ ይገልጥልናል «እኔ ግን በወንጌል ሳይሆን በኦሪት እከራከርሃለሁ፡፡ የምኩራብ መጻሕፍት ሁሉ ለቤተ ክርስቲያን የታወቁ ናቸውና፡፡ ምኩራብ ዘራች ቤተ ክርስቲያንም አጨደችው፤ ምኩራብ ፈተለችው ቤተ ክርስቲያን ለበሰችው፤ አዳምን በገነት ሳለ አዳም ሆይ ወዴት ነህ? ብሎ የጠየቀው ማነው? አብርሃምንስ ሚስትህ ሣራ ወዴት ናት? ብሎ የጠየቀው ማነው? እስቲ መልስልኝ? ሰይጣንንስ ከወዴት መጣህ? ብሎ የጠየቀው ማነው? እግዚአብሔር አብ አይደለምን?» በዚህ ጊዜ አይሁዳዊው መልስ አጥቶ ዝም አለ፡፡ ንጉሡ፣ ሊቃውንቱና መኳንንቱም እጅግ ተደሰቱ፡፡
§
የአባ ጊዮርጊስ የ ድርሰት ስራዎች ከ ብዙ በ ጥቂቱ
1. ኖኅተ ብርሃን /ከመጽሐፈ አርጋኖን
ጋር አብሮ ታትሟል/
|
8. ፍካሬ ሃይማኖት
|
2. አርጋኖነ ውዳሴ
|
9. መጽሐፈ ምሥጢር
|
3. ሰዓታት ዘመዓልት ወዘሌሊት
|
10. ውዳሴ ስብሐት
|
4.ውዳሴ መስቀል
|
11. እንዚራ ስብሐት
|
5. ቅዳሴ
|
12. ሕይወተ ማርያም
|
6. ውዳሴ ሐዋርያት
|
13. ተአምኖ ቅዱሳን
|
7. ጸሎት ዘቤት ቤት
|
14. መጽሐፈ ብርሃን ወዘተ
|
በዘመን ከነገሡ ነገስታት የደረሰበት ፈተና
- መናፍቁ ቢቱ ተንኮል ሰርቶ ከንጉሥ ዳዊት ጋር አጣላዉ ንጉሡም ተንኮሉ ሳይገባዉ አባ ጊዮርጊስን በደም አበላ እስኪነከር ድረስ እንዲደበደብ አድርጎ ወደ እስር ቤት አስገባው፡፡ ዐፄ ዳዊት እስኪሞትና ልጁ ቴዎድሮስ እስኪነግሥ ድረስም በዚያ ቆየ፡፡ ቢቱ ግን በመልአክ ተቀስፎ ሞተ፡፡
- አባ ጊዮርጊስ በወኅኒ ቤት እያለ ጴጥሮስና ጳውሎስ እየመጡ ያጽናኑት ነበር፡፡ዐፄ ዳዊት በሞተ ጊዜ አባ ጊዮርጊስ እጅግ አድርጎ አዘነ፡፡ እንዲያውም አንዳንዶች «በመሞቱ ደስ ልትሰኝ ይገባሃል እንጂ እንዴት ታለቅሳለህ?» ብለው ጠይቀውት ነበር፡፡ አባ ጊዮርጊስ ግን «ጥቂት ቢኖር እወዳለሁ፤ እመቤታችንን የሚወድ ሰው ነውና» ብሎ ነበር የመለሰው፡፡
- ዐፄ ቴዎድሮስ አባ ጊዮርጊስን ከወኅኒ ቤት አውጥቶት በጥንቱ ቦታ አስቀመጠው፡፡ አባ ጊዮርጊስ ግን የቤተ መንግሥትን ነገር ለመሸሽ ስለ ፈለገ በጋሥጫ ከመቀመጥ ይልቅ ርቆ ጥንት ወደ ነበረበት ወደ ዳሞት በመሄድ ማስተማር ጀመረ፡፡ ወደ ዳሞት ሲሄድ እግረ መንገዱን ወደ ደብረ ሊባኖስ ገብቶ የአቡነ ተክለ ሃይማኖትን መቃብር ተሳልሟል፡፡ ነገር ግን በዕውቀቱ የሚቀኑበት፣ በችሎታው የሚመቀኙት ሰዎች ነገር ሠርተው ከንጉሥ ቴዎድሮስ ጋር ስላጣሉት እልም ካለ በረሃ እንዲጋዝ ተደረገ፡፡ አባ ጊዮርጊስ ከግዞት የወጣው ዐፄ ቴዎድሮስ ሲሞት ነበር፡፡
- የአባ ጊዮርጊስ ሌላው ተማሪ የነበረው ዐፄ ይስሐቅ በ1399 ዓ.ም መንግሥቱን ሲይዝ አባ ጊዮርጊስን ከግዞት አውጥቶ ወደ ጋሥጫ መለሰው፡፡ በዚያ ጊዜ አባ ጊዮርጊስ እድሜው 42 ዓመት ሲሆን በስደትና በጤንነት መታወክ የተነሣ ከባድ ጉዳት ደርሶበት ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ብዙውን ጊዜውን በጾም፣ በጸሎትና በድርሰት ያውለው ነበር፡፡
- አንድ ቀን ቴዎድሮስ የተባለ መስፍን፣ አባ ጊዮርጊስን ስለ ርትዕት ሃይማኖት ጠየቀው፡፡ አባ ጊዮርጊስም ፍካሬ ሃይማኖት የተባለውን መጽሐፍ ደርሶ ሰጠው፡፡ ንጉሡና የምሥጢር ሊቃውንት የሆኑ ካህናት ይህንን በተመለከቱ ና ባነበቡ ጊዜ ‹‹ በእውነት ዮሐንስ አፈወርቅና አፈ በረከት የሆነው ቄርሎስ በዘመናችን ተነሥተዋል፡፡ ኢትዮጵያም ቁስጥንጥንያን መስላለች፣ ከእስክንድርያም በላይ ከፍ ከፍ ብላለች›› ብለው አደነቁ ፡፡
- አባ ጊዮርጊስ መከራ ያልተለየው አባት ነበር፡፡ ገድሉ እንደሚተርከው በቤተ መንግሥቱ የነበሩ ሰዎች የርሱን መከበርና መወደድ አይፈልጉትም ነበር፡፡ በተለይም ፍካሬ ሃይማኖት የተሰኘውን መጽሐፍ በመጻፉ የተነሣ መከበሩ አልተዋጠላቸውም፡፡ ስለዚህም ነገር ሠርተው ከዐፄ ይስሐቅ ጋር አሁንም አጣሉት፡፡
- ዐፄ ይስሐቅ አባ ጊዮርጊስን አሳስሮ ውኃ ወደማይገኝበት ዐለታማ ቦታ አጋዘው፡፡ በዚያም በመከራ ለብዙ ጊዜ ኖረ፡፡ በዚያ እያለ ዘወትር በጸሎት አብዝቶ ይተጋ ነበር፡፡ እግዚአብሔርም ዐፄ ይስሐቅ ወደ ልቡናው እንዲመለስ አደረገ፡፡ ንጉሡ በአባ ጊዮርጊስ ላይ የፈጸመው ነገር ሁሉ ፀፀተው፡፡ አገልጋዮቹንም ጠርቶ አባ ጊዮርጊስን እንዲያመጡት አዘዘ፡፡ ነገር ግን እነዚያ ተንኮል ሠሪዎች የአባ ጊዮርጊስ መምጣት ተንኮላቸውን ስለሚያጋልጠው አባ ጊዮርጊስ ሞቷል ብለው አስወሩ፡፡ ይህንን ሲሰማ ዐፄ ይስሐቅ ፈጽሞ አዘነ፡፡
- አባ ጊዮርጊስ ሞቷል እየተባለ መወራቱን ከደቀ መዝሙሩ ስለ ሰማ በሕይወት የመኖሩን ዜና ጽፎ ለዐፄ ይስሐቅ እንዲያደርስለት አውሎ ንፋስን ላከው፡፡ደብዳቤው ከአባ ጊዮርጊስ የተላከ መሆኑን ሲያውቅ ዐፄ ይስሐቅ ደነገጠ፡፡ እነዚያን መልእክተኞች ይዞ ወደ ወኅኒ ጨመራቸው፡፡ አባ ጊዮርጊስንም ከግዞት ያወጡት ዘንድ ላከ፡፡
- አባ ጊዮርጊስ ወደ ቤተ መንግሥቱ ሲመጣ ንጉሡ በደስታ ተቀበለው፡፡ ደብዳቤውን በማን እጅ እንደ ላከውም ጠየቀው፡፡ አባ ጊዮርጊስም ደብዳቤውን በሰው ሳይሆን በእግዚአብሔር ፈቃድ በነፋስ እንደ ላከው አስረዳ፡፡ ከዚያም በኋላ ዐፄ ይስሐቅ ለአባ ጊዮርጊስ ምድረ ሰዎን የተባለውን የጳጳሳት መቀመጫ የነበረውን ሀገር በርስትነት ሰጠዉ፡፡ አባ ጊዮርጊስ በምድረ ሰወን ንጉሥ ይስሐቅ ክረምቱን ያሳልፍበት በነበረው ቦታ ላይ ቤተ ክርስቲያን ሠራ፡፡ በዚያም በማስተማርና በጾም በጸሎት ይተጋ ነበር፡፡
እረፍቱ ለ አባ ጊዮርጊስ
- በጋሥጫ እያለ ዐፄ ይስሐቅ አስጠራው፡፡ በዚያ ጊዜ ንጉሡ የመናገሻ ማርያምን ቤተ ክርስቲያን አሠርቶ ስለ ነበር እንዲባርክለት ፈልጎ ነበር፡፡ አባ ጊዮርጊስ ምንም እንኳን በዚያ ጊዜ ታምሞ የተኛም ቢሆን ወደ ንጉሡ ተጓዘ፡፡ እዚያ ሲደርስ በጣም ተዳክሞ ነበር፡፡ ሥርዓቱን ለመፈጸምም ዐቅም አልነበረውም፡፡ ስለዚህም ንጉሥ ይስሐቅ በአልጋ ተሸክመውት እንዲዞሩና ቤተ ክርስቲያኗን እንዲባርካት አደረገ፡፡
- ቡራኬውን ከፈጸመ በኋላ ደቀ መዝሙሮቹን ሰብስቦ «ከሞትኩ አባቴ በጸሎተ ሚካኤል መከራ ወደ ተቀበለባትና እኔም ቤተ ክርስቲያን ወዳነፅኩባት ቦታ ወስዳችሁ ቅበሩኝ» ሲል አዘዛቸው፡፡ ለደቀ መዛሙርቱ የመጨረሻ የስንብት ትምህርቱን እያስተማራቸው እነርሱም በአልጋ ተሸክመውት ወደ ጋሥጫ እያመሩ ሳለ በመንገድ ላይ ሐምሌ ሰባት ቀን 1417 ዓ.ም በ60 ዓመቱ ዐረፈ፡፡
‹‹የአባታችን የቅዱስ
አፈበረከት አባ ጊዮርጊስ በረከታቸዉ ትደርብን››
‹‹ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወወላዲቱ ድንግል ወመስቀሉ ክቡር አሜን››
No comments:
Post a Comment