በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
በዲ/ን ፍሬው ለማ
ኦርቶዶክሳዊት
ቤተክርስቲያናችን በየዓመቱ ከምታከብራቸው በዓላት መካከል የጌታችን ልደት ገና እነሆ ደረሰ፡፡ ቅዳሴያዊ የሆነው ዘመን አቆጣጠራችን
ዘመኑን በመንገድ ጠራጊው በመጥምቁ ዮሐንስ በዓል ጀምሮ እነሆ የጌታን ልደት የምናከብርበት ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡ ይህንንም በዓል
ነቢያት ተስፋ እንዳደረጉት ተስፋን ሠንቀን በጾም የምንጠባበቀው ነው፡፡ በተለይም ከልደት በዓል አስቀድሞ ያሉትን ሰንበታት በተለየ
ኹኔታ ስለጌታ መምጣት ስለነቢያቱ ተስፋና ስለእውነተኛው ጠባቂ በስፋት የሚተነተንበት ነው፡፡በተለይ ስብከት ብርሃን እና ኖላዊ በምንላቸው
ሰንበታትም የበዓሉን ዜና ማብሰር እንጀምራለን፡፡
በኦርቶዶክሳዊት
ቤተክርስቲያን የአምልኮ ሥርዓት መሠረት በዓላት ያለቅድመ ዝግጅት አይከበሩም፡፡ ምዕመናንም ከዚህ ቀጥሎ ምን ይሆን? እያሉ የሚደናገሩበት
በዓል የለንም፡፡ ለምሳሌ በዕለተ ዓርብ የጌታ ትንሣኤ ከሕማሙ ጋር አስቀድመን እናውጃለን ‹‹ ለመስቀልከ ንሠግድ ኦ ሊቅነ ወለትንሣኤከ ቅድስት ንሴብሕ ኩልነ ይእዜኒ ወዘልፈኒ›› የቤተክርስቲን
የሥርዓተ አምልኮ ቀለሞች ታሪክን የሚያስታውሱ ብቻ አይደሉም፡፡ ይልቁኑም የእግዚአብሔር ኃይሉን እና ፍቅሩን የምንካፈልባቸው ጊዜያት
ናቸው እንጂ፡፡ የጌታን ብርሃንነት በመረዳት በመንፈስ ቅዱስ ተመልተን በኩረ በዓላት ልደትን ለማክበር እንዘጋጅ፡፡
የአዳምን
የተስፋ ቃል ለመፈጸም ወልድ ሰው ሆነ፡፡ ተደርጎ የማያውቅ ከእንግዲህም የማይደረግ በይሁዳ በቤተልሔም ተደረገ፡፡ ምድር አምላኳን አስተናገደች በረት መንግስተ ሰማያትን
መሠለች መልዐኩም በደስታ ቃል ተመልቶ ለፍጥረት ሁሉ ደስታ ለእመቤታችን ደስ ይበልሽ አላት፡፡ ታላቅ ደስታ የምሥራችም እንደሚደረግ
ተናገረ ይህን ታላቅ ደስታ ሁልጊዜ እናስበው ዘንድ ይገባናል ልደት ዓመታዊ ቀን አይደለም፤ ገና ታሪካዊ ሁኔታን የምናስብበት ብቻ
አይደለም፡፡ ይልቁኑም ነፍሳችን በደስታ የሚመላበት እንደእረኞቹ ሕጻኑን እና እናቱን እናይ ዘንድ የምንቸኩልበት እንደጥበብ ሠዎች
ያለንን የከበረውን ሁሉ ለእርሱ የምንገብርበት ነው፡፡ እንደመላዕክት ቃላት እስኪያጥረን ድረስ ለእግዚአብሔር ምስጋና የምናቀርብበት
በስብሐተ እግዚአብሔር የምንፋጠንበት ነው፡፡
አረጋዊ
ተወልደ
በአምሳሊከ
ከመ
ይለድከ
በአምሳሊሁ እንዳለ እርሱን አስመስሎ ይወልደን ዘንድ አስቀድሞ እኛን መስሎ እንደተወለደ እናስተውል
፡፡ ለእርሱ በባሕርይ የሆኑትን ሁሉ እኛ በፀጋ ተካፋይ እንድንሆን አድሎናልና ደስ ይበለን፡፡ ሥጋችንንም ነፍሳችንን ነስቶ ሰው
እንደሆነ እናስተውል፡፡ በዚህ መንሣቱም የነሳቸውን ሁሉ አዳነ እንዲህም
ከሆነ በሥጋችን ኃጢአት እንዳይነግስ መዋጋትን ቸል አንበል፡፡ ከሌሎች ቀናትም በበለጠ በገና ዕለት ይህን እናደርግ ዘንድ እንቸኩል፡፡
‹‹ ከእኔ ዘንድ ያለሽ ይቅርታ አያልቅም፥የሰላምሽ
ቃል ኪዳንም አይጠፋም፥መሐሪሽ እግዚአብሔር ይህን ተናግሮአልና›› ኢሳ 54፡10 እንዳለ ነቢዮ ኢሳይያስ የተገናን ሆነን ተገኝተን ሳይሆን ስለፍፁም ፍቅሩ እንድንበት ዘንድ ወደደ፡፡ይህም
መድኃኒት ይሆነን ዘንድ ነው ዘወትር በጸሎተ ሃይማኖት ‹‹ዘበእንተ መድኃኒትነ ወረደ እም ሰማያት›› እንደምንለው ነው፡፡ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን ወደ
ዓለም ላከ፡፡ በዓለም ይፈርድ ዘንድ አይደለም ፡፡ ዓለም ሁሉ በእርሱ ይድን ዘንድ ወደደ እንጂ (ዮሐ 3፡17)
የሰውን ነፍሳት ብቻ ሳይሆን አካላቸውን ይፈውስ ዘንድ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆነ፡፡ የሰውን ልጅ ብቻ አይደለም ፍጥረታትን ሁሉ
ያስተካክል ዘንድ ቀዳማዊ ቃል ሰው ሆነ፡፡ በቀዳሚ አዳም የተነሣ
ምድር ተረገመች በዳግማዊ አዳም ክርስቶስ የተነሣ ደግሞ ምድር ተባረከች፡፡
በዓለም
ላይ ካሉ ሰዎች ዘንድ ክርስቲያኖች ላይ ከሚቀርቡ ክሶች(አስተያየቶች)
እዱ ደስተኞች አይደሉም የሚለው ነው፡፡ ክርስቲያን ሆኖ ደስተኛ
አለመሆነ በራሱ የሚጋጭ ነው መራሪ፤የሚኮንን ፤የሚወቅስ ፤የማይረካ ሆነን ክርስቲያን ነን ብለን አፋችንን ሞልተን ማውራት አንችልም፡፡
ተስፋችንን በክርስቶስ ባለማድረጋችን ደስታችን ተወስዶብናል እኛ የክርስቶስ ደስታ ነንና ‹‹ በእነርሱ ደስታዬ ፍፁም ይሆን ዘንድ ይህን በዓለም እናገራለሁ›› ዮሐ 17፡13
እንዳለ ክርስቶስም የእኛ ደስታ ነው፡፡ በተለይ በገና ይህን አብዝተን እናስባለን ስለዚህም ክርስቲያን ከማያስብሉን ምግባራት እንራቅ፡፡
ከዚህ ዓለም ገዥ ራሳችንን ነጻ እናውጣ፡፡(ዮሐ 12፡31) እኛ ሰማያውያን
ነንና የሆነውንና የሚሆነውን በማሰብ እንጨነቅ ዘንድ አይገባም እግዚአብሔር በመግቦቱ ከእኛ ጋር እንዳለ እናስተውል፡፡ ክርስቲያን
መሆን በዓለም ያለ ብቸኛ ደስታ ነውና ዕፁብ ድንቅ እያልን በደስታ
እንድንኖር ከሚያደርጉን ነገሮች አንዱ የጌታ ልደት ነው፡፡ በመደነቅ ውስጥ ካልሆነ ማንም ሊመረምረው የማይችላቸውን የእግዚአብሔርን
ሥራዎች እናስተውል፡፡ በመንግሥተ ሰማያት እንኖረው ዘንድ የምንናፍቀውም ይህንን ዓይነት ደስታ ነው፡፡ ‹‹ወደ ጌታህ ደስታ ግባ››
እንደተባለ
ከልደቱ በረከት ተሳታፊ ያድርገን፡፡
ስብሐት ለእግዚአብሔር
No comments:
Post a Comment