በዲያቆን ያሬድ መለሰ
የአይሁድ አለቃቸው ኒቆዶሞስ በሌሊት ጎደለውን ይሞላ ዘንድ ወደ ጌታ ገሰገሰ። አይሁድ አለቃቸው መባሉም በትምህርት(ሙሑረ ኦሪት ነው) በሹመት(በሥልጣን) በባለጸግነት ነው። ኒቆዲሞስ ኹሉ የሞላለት ሰው የሚባል ነው፡፡ ዕውቀት አለው ሥልጣን አለው እንዲሁም ባለጸጋ ነው በሰውነት መመዘኛ ሁሉ የሞላለት ሰው ሆኖ ሳለ የተማረ ስለነበረ ቃሉን ይሰማ ዘንድ በሌሊት ወደ ጌታችን እየመጣ ይማራል፡፡
የኒቆዲሞስ ታሪክ ዮሐንስ ወንጌል ሰፍሮ የመገኘቱ ዋና ዓላማ ሕይወቱ አብነት ሊሆን የሚችል በመሆኑ ነው። አንደኛ በእምነት ጸንቶ እስከ መጨረሻው የሚከተለው በመሆኑ (ሉቃ 24÷13፣ ዮሐ 19÷39) ሦስት ዓመት ከሦስት ወር የተማሩት ሐዋርያት ከዮሐንስ በቀር ኹሉም ሸሽተው ነበር፡፡ ትምህርቱን መስማት ደስ የሚሰኙ ነገር ግን አይሁድ ከጌታ ጋር የተባበረ ሁሉ ከምኩራብ ይሰደድ በማለታቸው ምክንያት ብዙዎች ክርስቶስን ለመስማት ይፈሩ ነበር። እስከ መጨረሻው መጽናት ያቃታቸው ብዙዎች ናቸው። የሌሊት ተማሪው ኒቆዲሞስና ዮሴፍ ግን ገንዘው ቀብረውታል፡፡ ስለዚህም እስከመጨረሻው የጸና ደቀ መዝሙሩ ነውና ለአብነት የሚሆን ሰው በመሆኑ በኋላም የሚመሰክር ነውና፡፡ (ዮ7ሐ 7÷50) ያልተማሩ መጻሕፍት የማያውቁ ብቻ ሳይሆን ከተማሩ ከአዋቂዎች ከአለቆችና ከመምህራንም ወገን በእርሱ ያመኑ እንዳሉ ለመግለጥ በዚህም አብነት ይሆነናልና ዮሐንስ በወንጌሉ አንስቶታል።
ከኒቆዲሞስ ምን እንማር?
አትኅቶ ርዕስ
በወቅቱ ራስን በጌታ ፊት ዝቅ ማድረግ ከባድ ነበር። (እንኳን የአይሁድ መምህር ሆኖ) ኒቆዲሞስ ቀደም ሲል እንዳነሳነው ሙሑረ ኦሪት ነው ባለሥልጣን በባለጸጋ ነው። ምንም እንኳን ይህን ሁሉ ቢሆን ጉድለቱን ይሞላ ዘንድ በሌሊት ከሁሉ አስቀድሞ የጌትን ትምህርት ለመስማት ይገሰግስ ነበር። ወውእቱ መጽአ ኅበ እግዚእ ኢየሱስ ቀደሙ ሌሊቱ እንዲል
የእውነት ምስክር ነው
ይህንንም ስለጌታ ሲመሰክር ከእግዚአብሔር እንደተላክ እናውቃለን በማለቱ ይታወቃል። መርምሮ መረዳትን ኒቆዲሞስ ስለጌታ ከመመስከሩ በፊት (ከእግዚአብሔር እንደተላክ እናውቃለን ከማለቱ በፊት) ሁሉን መርምሮ ጌታን የተከተለ ነው። ይህም ምስክርነት እውነትም ሊቅነቱ(ሙሑረ ኦሪትነቱ) ያመለክታል፡፡ ተአምራቱን በማየት ወደ ማመን መጣ ቢሆንም የጌታን ትምህርትም በማመን ይመረምር ነበር ይህንንም ‹‹ኒቆዲሞስም ሠው ከሸመገለ በኋላ እንዴት ሊወልድ ይችላል? ዳግመኛ ወደ እናቱ ማኅጸን ገብቶ ይወለድ ዘንድ ይችላልን?›› ብሎ በጠየቀው መረዳት ይቻላል።
ጽናት
በእምነት ጸንቶ እስከ መጨረሻው ተከትሏል።(ሉቃ 24÷13፣ ዮሐ 19÷39) ሦስት ዓመት ከሦስት ወር የተማሩት ሐዋርያት ከዮሐንስ በቀር ኹሉም ሸሽተው ነበር፡፡ ትምህርቱን መስማት ደስ የሚሰኙ ነገር ግን አይሁድ ከጌታ ጋር የተባበረ ሁሉ ከምኩራብ ይሰደድ በማለታቸው ምክንያት ብዙዎች ክርስቶስን ለመስማት ለማመን ይፈሩ ነበር።ለአብነትም ስምዖን ቀሬናዊ የጌታችን ደቀመዝሙር ነበር። አይሁድ ከክርስቶስ ጋር የተባበረ ሁሉ ከምኩራብ ይሰደድ ብለው አዋጅ ሲያውጁ ፈርቶ ለብዙ ጊዜያት ከጌታ ርቆ ይኖር ነበር። ኋላ ወደ መንደሩ ሲመለስ ክርስቶስ መስቀል ተሰክሞ ቀራኒዮ ስወጣ አገኘው። ወታደሮቹም ባዮት ጊዜ የክርስቶስን መስቀል ይሸከም ዘንድ ጠርተውታል። የፈራው መከራ ኋላ መምጣቱ አልቀረም። "ሲወጡም ስምዖን የተባለው የቀሬናን ሰው አገኙ፤ እርሱንም መስቀሉን ይሸከም ዘንድ አስገደዱት። "(ማቴ 27፥32)" በወሰዱትም ጊዜ ስምዖን የተባለ የቀሬናን ሰው ከገጠር ሲመጣ ይዘው ከኢየሱስ በኋላ መስቀሉን እንዲሸከም ጫኑበት። " እንዲል መጽሐፍ (ሉቃ 23፥26) የሌሊት ተማሪው ኒቆዲሞስና ዮሴፍ ግን ገንዘው ቀብረውታል፡፡ ስለዚህም እስከመጨረሻው የጸና ደቀ መዝሙሩ ነውና ለአብነት የሚሆን ሰው በመሆኑ በኋላም የሚመሰክር ነውና፡፡ (ዮሐ 7÷50)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
No comments:
Post a Comment