Saturday, 13 April 2019

የእግዚአብሔር መገለጥ

በስ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

የእግዚአብሔር መገለጥና እግዚአብሔርን መምሰል በነገረ መለኮት ዕይታ

በዲያቆን ያሬድ መለሰ

ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ከጌታችን ልደት እስከ ጥር አሥር ያለውን ጊዜ ዘመነ ልደት ብላ በዋነኝነት በዚህ ወቅት የክርስቶስን በሥጋ መገለጥን የሚዘክር ሥርዓተ አምልኮና ምስጋና ታቀርባለች። ከልደቱ እስከ ጥር አምስት ቀን ልደቱን ከጥር ስድስት እስከ አሥር ግዝረቱን ወደ ናዝሬት ገብቶ ማደጉን እናስባለን። ከጥር አሥራ አንድ እስከ ጾመ ነነዌ መግቢያ ዘመነ አስተርእዮ(ኤጲፋኒያ) እንዘክራለን ይህ ወቅት የሰይጣን ሥራ ሊያፈርስ በሥጋ መገለጡን የምናስብበት ወቅት ነው። ጠቅለል ባለ መልኩ ስናየው ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችን ከበዓለ ልደቱ አንስቶ ልደቱን፣ግዝረቱን፣በናዝሬት ማደጉን፣በማየ ዮርዳኖስ መጠመቁን፣ልዩ ሦስትነቱን(ምሥጢረ ሥላሴን) በዮርዳኖስ መግለጡን እንዲሁም በቃና ዘገሊላ አምላክነቱን መግለጡን ታስተምራለች። ለዚህም ነው ወቅቱን ዘመነ መገለጥ ብለን የጠራነው። ይህም በዋነኝነት ምክንያቱ ስለሦስት ነገር ነው አንደኛው በዚህ ወቅት በሥጋ መገለጡን ስለምናስብ ሁለተኛው በጥምቀቱ አንድነት ሦስትነቱን መግለጡን ስለምንዘክር ሦስተኛው ምክንያት በመጀመርያው አገልግሎቱ በተዓምራት በቃና ዘገሊላ አምላክነቱን መግለጡን እናስባለንና ዘመነ መገለጥ(ኤጲፋንያ) ብለን እንጠራዋለን።
የተገለጠ አምላክ (Revealed God)
እግዚአብሔር ከፍጡራን አዕምሮ በላይ ነው። ባሕርይው አይመረመርም ስንል በፍጡራን ውስን አዕምሮ ሊደረስበት አይችልም ማለታችን ብቻ ሳይሆን ከግብሩ የተነሳ ያወቅንውን ባሕርይ በፍጡራን ቋንቋ ሊገለጸ አይችልም ማለታችን ነው። እርሱ ራሱ በጥቂቱ ከገለጠው ግብሩ የተነሳ እናውቀዋለን እንጂ የማይመረመር የማይደረስበት ነው። ይህ ማለት ግን እግዚአብሔር ራሱን የማይገልጥ ከፍጥረቱ በርቀት ያለ ነው ማለታችን አይደለም። ራሱን ባሕርይውን እንደሰው አቅም ሲገለጥ እናገኘዋለን እንጂ። በዋነኝነት የእግዚአብሔርን መገለጥ በሁለት ክፍሎች ከፍሎ መመልከት ይኖርበናል። አንደኛው ፍጹም ያልሆነ መገለጡ (imperfect revelation) (ምሳሌያዊና ጥላ) ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ፍጹም መገለጡ (perfect revelation) ነው።
የእግዚአብሔርን የመገለጥ በዘመናት ከፍለን ካየነው በሦስት ዘመናት ከፍሎ መመልከት ይቻላል፡፡ የመጀመርያው ከመጀመርያው ሰው አዳም እስከ ሊቀ ነቢያት ሙሴ ድረስ ያለውን በሕገ ልቡና በቃል፣ በራእይ፣ በተዓምር እየተገለጠ በማነጋገር አምላክነቱን አስረድቷል።  ( ዘፍ.28-18 ዘፍ.39 ዘፍ.121) ሌላው ከሊቀ ነቢያት ሙሴ እስከ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መምጣት ያለውን የሕገ ኦሪት ዘመንም በቃል በራእይ በተአምር እና ሕግና ሥርዓት በመስጠት አምላክነቱን አስረድቷል(አስተምሯል)።(ዘኁ 125) በበሕገልቦናም ኦሪትም የነበሩት መገለጦች ምሳሌያዊ መገለጦች ሲሆኑ በሕገ ኦሪት ዘመን የእግዚአብሔር መገለጥ ከሕገ ልቡናው ዘመን ለየት የሚያደርገው  በሕግና በሥርዓት ለእስራኤል መገለጡ ነው። የእግዚአብሔር ፍጹም መገለጥ ብለን የምንጠራው ዘመኑ ሲደርስ ለአዳም በገባው ቃል መሠረት በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል መገለጡን ነው።(ዕብ 1፥2)
በፍጥረቱ እግዚአብሔር ይገለጣል
ፍጥረታት ማለት በሥላሴ መለኮታዊ የባሕርይ አንድነት በኃልዩ(በማሰብ)፣ በነቢብ(በመናገር) አልያም በገቢር(በመሥራት) የተፈጠሩ(ወደ ሕልውና የመጡ) የእግዚአብሔርን ባሕርይና አምላክነት የምንመለከትባቸው የሥራ ውጤቶች ናቸው። እግዚአብሔር አምላካዊ ሐሳብ ፍቃድ እቅድ ዓላማ አለው፤ይህንን ሰው አያውቅም። እግዚአብሔር ከሰው አእምሮ በላይ ነውና። ይህንን የእግዚአብሔርን ባሕርያዊ ሐሳብ ፍቃድና ዓላማ ዓለምን የፈጠረበት ምክንያት በፍጥረት ውስጥ በሚገባ እንረዳለን ከፈጠረው ፍጥረት በመነሳት የእግዚአብሔር ባሕርይ እንዲህ ነው እንላለን ምንም እንኳን ውስን በሆነው አእምሮችን የእግዚአብሔር ባሕርይ እንዲህ ነው ብለን በድፍረት መናገር ባንችለም እስካሁን ያወቅነውን ያወቅነው ከመገለጡ የተናሳ እንደሆነ ማስተዋል እንችላለን።
ስለዚህም እግዚአብሔር በፍጥረቱ ለፍጥረቱ ይታወቃል። ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ እንዳለ "ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ታይቶ የማይታወቅ እግዚአብሔር የፈጠረውን ፍጥረት በማሰብ በመመርመር ይታወቃል"(ሮሜ 1፥20)  ስለዚህም በእምነት ለሚያይ ሰው እግዚአብሔር በፍጥረታት በኩል መገለጡን ያያል። የእግዚአብሔርን ሥራ በማድነቅ ይመለከታል ስለዚህም በእርሱ ያምናል ሌላም ምልክት አያሻውም። ለአማኝ ቅዱስ ዳዊት እንዳለ "ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ የሰማይም ጠፈር የእጆቹን ሥራ ያወራል" (መዝ 18፥1) እንዳለ ባለንጹሕ አእምሮ በፍጥረታት ውስጥ የእግዚአብሔርን ሕልውና(መኖር) ብቻ ሳይሆን፤ የእግዚብሔርን ባሕርይ ጨምሮ ወደመረዳት ይደርሳል ከግብሩ(ከሥራው) በመነሳት እግዚአብሔር እንዲህ ነው ይላል። የእግዚአብሔርን ለጋስነት፣ ያለስስት ሰጭነት፣ ጠባቂነት፣አዋቂነት፣ ከሃሊነት ወዘተ መመልከት ይችላል።
እግዚአብሔርን በፍጥረታቱ ስናውቅ የምናደንቀው በመፍጠሩ ብቻ አይደለም የፈጠረውን ፈጥሮ ብቻ አልተዋቸውም ዘወትር ይጠብቃቸዋል ይንከባከባቸዋል ይመግባቸዋል። ስለዚህም አምላክ ሰራዒ መጋቢ ጠባቂ መሆኑን እናውቃለን ባሕርይውን በጥቂቱ እንረዳለን። እግዚአብሔር መጠነኛ ባሕርይውን ብቻም ሳይሆን ልዩ ሦስትነቱን(ምሥጢረ ሥላሴን) ጭምር በፍጥረታት ገልጦልናል። ምንም እንኳን እግዚአብሔር በፍጥረታት በኩል ቢገለጥም ይህን መገለጥ የነገረ መለኮት ሊቃውንት ፍጹም ካልሆነው  መገለጥ ይመድቡታል። ለዚህም ምክንያቱ መገለጡ በቀጥታ በራሱ ወደ ድኅነት የሚመራ ስላልሆነ ነው።
እግዚአብሔር ለነቢያት መገለጥ
እግዚአብሔር ምጡቅ ረቂቅ ከአእምሮ በላይ ቢሆንም ከአባታችን አዳም ጀምሮ በተለያየ ጊዜ ለቅዱሳን ተገልጦል፡፡ (ዘፍ 38) ሊቀ ነቢያት ሙሴ እግዚአብሔርን አምስት መቶ ሰባ ጊዜ ያህል አናግሮታል ተገልጦለታልም( ዘኁ 125 )ለቅዱሳኑም ለሄኖክ መዓዛ ባለው እንጨት ለአብርሃም በሦስት ሰዎች አምሳል ለኖኅ በቀስተ ደመና ለያዕቆብ በመሳላል ከፍታ ላይ ተቀምጦ ለኢሳይያስ በዙፍኑ ተቀምጦ ለዕዝራ በአንበሳ አምሳል ለዳንኤል በሽበታም ሰው አምሳል ተገልጦል፡፡ ለነቢያቱም በብዙ ምሳሌ መገለጡም የእግዚአብሔርን የተለያየ ባሕርይ የሚያስረዳ ነው፡፡ በሸመገለ ሰው አምሳል ሲገለጥ ፍትሐዊነቱን፤ ብርቱ ጦረኛ ሲሆን ተዋጊነቱን፤ አንድ ቦታ እንዳጣ ነዳይ መታየቱን በአንድ ቦታ እንደሚዘገይ በሌላ ቦታ የሚቀድመው እንደሌለ መጻፉን አስተውል የባሕርያቱ ጥልቅነትን በመገለጡ እንደሚያስረዳን እናስተውላለን፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም እንዳለ ‹‹እርሱ እንደ መራዳችን መጠን ተገለጠ(አስተማረን) ስንል እርሱ ራሱ እንደኛ ነው ማለታችን አይደለም፡፡ እርሱ በእኛ ምሳሌ ተገለጠ ወይም አልተገለጠ እርሱ ራሱ ነው አይለወጥም፡፡ ሲፈልግ እኛን ለማስተማር አንዱ ጠባያችን ተገልጦ ይታየናል ሌላ ጊዜ ደግሞ አስቀድሞ የለበሰውን እንደልብስ አውልቆ ሌላ ልብስ ለብሶ ይገለጥልናል እርሱ ለእኛ በመንገሩ እርሱ እንዲህ ነው ማለት አይደለም ነገር ግን ባሕርይው የማይመረመር ነውና በምንረዳው በእኛ ምሳሌ ተገኝቶ ፍቃዱን ገለጠልን›› ለዚህም ነው ይህንን መገለጥ ምሳሌያዊ የምንለው።
ይህ መገለጡ የኩነት መገለጥ አይደለም። ልክ በፍጥረቱ በኩል በጥቂቱ እዳወቅነው በጥቂቱ ደግሞ ስለእርሱ እንደአእምሮችን መጠን እንደቅድስናችን ከባሕርይው በጥቂቱ እንድንረዳ የሚገለጥበት መንገድ ነው። ለነቢያቱም በሕልም በራዕይ ይገለጥ ነበር። ይህም መገለጥ ምንም እንኳን ራሱ እግዚአብሔር በተለያየ ምሳሌያዊ መንገድ ቢገለጥ ከድኅነት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ስለሌለው ፍጹም አይደለም። ባሕርይውንም አንድንረዳ ያግዘናል እንጂ የኩነት አይደለም። ለዚህም ነው ነቢያቱ ምንም እንኳን ለእነርሱ ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ ቢገለጥም በሥጋ ይወለድ ዘንድ ሲናፍቁ የኖሩት በሥጋ መገለጡ ለድኅነታቸው አስፈላጊ ስለነበረ በጾም በጸሎት በተስፋ የእግዚአብሔርን መገለጥ ሲጠባበቁ ኖረዋል።
የወልደ እግዚአብሔር በሥጋ መገለጥ
ዘመኑ ሲደርስ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ በጠባብ ደረት በአጭር ቁመት ተመራልሶ ከሕግ በታች ሆኖ የሥጋን ባሕርይ ገንዘብ አድርጎ መገለጡን ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ ሆኖ በመካከላቸው ተገኝቶ መምህር ሆኖ የአምላክ ልጅ አምላክ መሆኑንበግልጽ አስረድቷል።

ቅድስት በቤተ ክርስቲያን ይህንን የክርስቶስን የመገለጥ ትልቅ ሥፍራ ትሰጠዋለች፡፡ አስቀድሞም ለነቢያቱ በነገረው መሠረት ተወለደ(ገላ 44) ለቃሉም መዘግየት አላስተዋልንም ይህም ከሌሎቹ መገለጦች ፍጹም ልዩና አስደናቂም ነው ስለዚህም ሁሌም በአንክሮ በአኮቴት በውዳሴና በምሥጋና እናደንቀዋለን፡፡ ለዚህም ነው አበው እግዚአብሔር ዓለምን ከፈጠረበት ጥበቡ ያዳነበት ይበልጣል የሚሉት ሥጋን የለበሰው አምላክ ተወለደ ተጠመቀ ሞተ ተቀበረ በሦስተኛው ቀን ተነሳ አረገ ተመልሶም ለፍርድ ይመጣል ይህ ሁሉ የሆነው ታዲያ በሥጋ በመገለጡ ነው(ራዕ 17) ፡፡ የክርስቶስን መገለጥ የምትሰብከውም ክርስትና የመገለጥ ሃይማኖት(Revealed religion) ናት መባልዋ ለዚህ ነው፡፡

አምላክ በሥጋ ተገለጠ ስንል ረቂቁ አምላክ በተአቅቦ ርቀቱን ሳይለቅ ውሱን ሥጋን ውሱኑም ሥጋ በተአቅቦ ውስንነቱን ሳይለቅ ረቂቅ መለኮትን የሆነበት በአጭር ቃል የቃል ግብር ለሥጋ የሥጋ ግብር ለቃል የሆነበት ረቂቅ ምስጢር ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ቀዳማዊ ደኃራዊ የሆነው አምላክ ሞት የሚስማማው ሆነ፤ ዘመን የሚቆጠርለት ሥጋ ዘመን የማይቆጠርለት ሆነ፡፡ ሥጋ በማይመረመር ምስጢር የመለኮትን ገንዘብ ገንዘቡ ቢያደርግፊተኛውና መጨረሻው ሕያውም እኔ ነኝ ሞቼም ነበርሁ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ሕያው ነኝ” (ራዕ. 117) ማለት የቻለበት ምስጢር ነው፡፡ የረቀቀው ገዝፎ የገዘፈው ረቆ፣ ሰማያዊው ምድራዊ ምድራዊው ሰማያዊ ሆኖ መታየት ማለት ነው፣ ከዓለም ተሰውሮ የነበረው ምሥጢር ግልጥ ሆኖ መታየት ማለት ነው ይህንንም ምሥጢር ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በጢሞቴዎስ መልእክቱእግዚአብሔርን የመምሰል ምስጢር ያለጥርጥር ታላቅ ነው፤ በሥጋ የጠገለጠ፣ በመንፈስ የጸደቀ፣ ለመላእክት የታየ፣ በአሕዛብ የተሰበከ፣ በዓለም የታመነ፣ በክብር ያረገ (1 ጢሞ 316) ያለው ነው።
በጥምቀተ እግዚእ የምሥጢረ ሥላሴ መገለጥ
ስለእግዚአብሔር አንድነትና ሦስትነት መገለጥ በብሉይ ከተነገሩት ሁሉ ጎልቶ የሚታየው የአብርሃም ታሪክ(የሥላሴ በቤተ አብርሃም መገኘት) ነው፡፡ በሐዲስ ውስጥም በየትኛውም ታሪክ ይሁን የእግዚአብሔር ሦስትነት ምሥጢር በይፋ የተገለጠው በዮርዳኖስ ወንዝ በእደ ዮሐንስ ጌታ ሊጠመቅ ከገሊላ በመጣ ጊዜ ነው፡፡ ነገረ ሥላሴ በብሉይ ኪዳን የተሸሸገ ለእስራኤላዊያን ያልተገለጠ ነው፡፡ አንዳንድ ጭላንጭሎች ካልሆነ በቀር አንድ አማላክ እንደሆነ ብቻ እየገለጠ በነቢያቱ አማካኝነት መልእክት እያስተላለፈ ቆየ ይህም የሆነበት ምክንያት ምሥጢሩ ለእስራኤል ተገልጦ ቢሆን ኖሮ ምሥጢሩን ካለመረዳትና ካለመገንዘብ ሦስት አማልክት ብለው ባመለኩት ነበር ይህን የልባቸውን ነገር የሚያውቀው ቅዱስ እግዚአብሔር ለእስራኤል ለአንዳንድ ቅዱሳን ካልሆነ በቀር ሦስትነቱ ሳይገለጽ ኖሯል።
በጌታ ጥምቀት ታላቅ ምሥጢር ተገለጠለው ያለምክንያት አይደለም በዚህ ወቅት ነበር ሰማይ ተከፍቶ መለኮታዊ መገለጥ በገሃድ የታየው። ምንም ባጭሩ ቢጻፍ ድርጊቱ ግን ከሰማይና ከምድር ከበደ ነው። አሮጌው ዓለም በምሥጢረ ጥምቀት እንዲታደስና አዲስ ፍጥረት እንዲሆን በቅድስት ሥላሴ መባረኩን እናያለን። የጌታ መጠመቅና የሥላሴ መገለጥ ከሰው ልጆች ድኅነት ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው። ቅዱስ ማቴዎስ ይህንን አስደናቂ መገለጥ በአጭሩ ሲገልጥ ተጠምቆም ከውኃው ከወጣ በኋላ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ወርዶ በራሱ ላይ ሲቀመጥበት ታይቷል:: አብም " “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው” ይህ ነው ብሎ መስክሯል።(ማቴ 3፥10)
በክርስቶስ ጥምቀትና ጸሎት ሰማያት ተከፍተው ሰማያዊ ምሥጢር መገለጡን በማሰብ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ወቅቱን አስተርዮ(መገለጥ) ጋር ታያይዘዋለች፡፡ በመጥምቁ ዮሐንስ ስብከት ንስሐ ገብተው በዮርዳኖስ ወንዝ ተጠምቀው የመንግስተ ሰማየት መቅረብ አውቀው ለሚጠባበቁ ሰዎች  ሁሉ የሥላሴ ምሥጢረ ሥላሴ ምሥጢር ተገልጦላቸዋል፡፡እንግዲህ በዚህ መለኮታዊ ክስተት ውስጥ ሦስት መሠረታዊ ገነር እንመለከታለን፡፡ የመጀመርያው የመንፈስቅዱስ በአካል መልክ በርግብ አምሳል  መገለጥ ሁለተኛው የአብ በደመና መገለጥ ሲሆን ሦስተኛው በእደ ዮሐንስ የተጠመቀው ክርስቶስ የአብ የባሕርይ ልጅ እንደሆነ አመልካች የሆነው የአብ ምስክርነት ነው።
በጥምቀት ምሥጢረ ሥላሴ መገለጡ ጌታችን በሥጋ በመገለጡ ያገኘነው ተጨማሪ መገለጥ ነው። ለዚህም ነው እግዚአብሔርን ያየው አንድስ እንኳን የለም በአባቱ እቅፍ ያለ ወልድ ተረከው እንጂ (ዮሐ 1፥18) የተባለው ሰው በክርስቶስ ሲያምን በአብና በመንፈስ ቅዱስ እንዲያምን ይሆናል። ወልድን እንደልጅ የተቀበለ አብን እንደአባት ይቀበላልና ስለዚህም ሰው በፍጹማዊ መገለጡ (በኩነት መገለጡ ወይም በሥጋዌው) ሲያምን ተጨማሪ ምሥጢር ይገለጥለታል። በእርሱ በኩል አብን ወደ ማወቅ እንደርሳለን ለዚህም ነው ጌታችን በእኔ ካልሆነ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም ያለው።
በሐዲስ ኪዳን ያለ ሰው የእግዚአብሔርን ተጨማሪ መገለጥ(በሥጋ መገለጡን) ያየ ስለሆነ በብርሃን አለ። ከጌታችን በሥጋ መገለጥ ተጨማሪ ሌሎች መገለጦችን እንዲያይ እግዚአብሔር የአምላክነት ጸጋ ሰጥቶናል ቀድሞ በብሉይ እንደነበሩ ሰዎች ሳይሆን ከዚያ በተለየ ደረጃ እግዚአብሔርን መረዳት እንድንችል ሆነናል። አምላክን ለማየት ግን ንጹሕ ልብና ቅድስና ያስፈልገናል። ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙ ይህንን በሚመለከት ሲናገር ደካማ ዓይኖች የፀሐይ ብርሃንን ለማየት እንደሚቸገሩ ልቡ ንጹሕ ያልሆነ ሰው እግዚአብሔርን  ለማየት ትቸገራል።
 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

 

No comments:

Post a Comment