በዲያቆን ያሬድ መለሰ
ውድ ኦርቶዶክሳዊያን በክፍል አራት ንስሐና ኃጢአትን መናዘዝ(ኑዛዜ)፣የካህናት ድርሻ በንስሐና በኑዛዜ፣የክህነት ፀጋና የንስሐ አባትና የንስሐ ልጅ ግንኙነት በተመለከተ ለማየት ሞክረናል በዚህ ክፍል ቀኖና ለምን ይሰጣል? የኑዛዜ ጥቅም እንዴት መናዘዝ እንደሚገባ በተመለከተ በጥቂቱ እንላለን፡፡ መልካም ንባብ
ቀኖና ለምን ይሰጣል?
ቀኖና እንደ ቅጣት ዓይነት መታሰብ የለበትም። ተፈጥሯዊው ሕሊናም ወቃሽም አስተማሪም ነው። ቀኖና የሚሰጠው የተበሳጨውን እግዚአብሔርን ለማስደሰትና በመለኮታዊ ፍትህ ፊት ለኃጢአተኛው ሥርየት ሲባል አይደለም። ይህ ሙሉ በሙሉ የመናፍቃን ትምህርት ነው። ቀኖና አብዛኛውን ጊዜ የሚተገበረው ያልበሰለ የኑዛዜ ሕይወት ላለው ተነሣኢ ሊሆን ይገባዋል። ይህም ግንዛቤን ለመቀስቀስና የአንድን ሰው የኃጢአት መጠን ለማወቅ በማሰብ ነው። በኦርቶዶክሳዊ አረዳድ መሠረት "ኃጢአት" ማለት ሕግን መተላለፍ አይደለም። ለእግዚአብሔር ፍቅር ማጣት ነው። ንስሐም ካሣ አይደለም።ስለዚህም ይህንን በመንፈሳዊ ልምምድ ወደ ፍጹም ንስሐና ወደ እግዚአብሔር ፍቅር ማድረስን ከመንፈሳዊ አባት ይጠበቃል።
ካህኑ የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ሰጪ ሆኖ ይሠራል። እንደ ሳይኮሎጂስትና ሳይንቲስት አይሰራም እንደ ካህን፣ እንደ ልምድ ያለው ዶክተር፣ እንደ አሳቢ አባት ሆኖ ይሰራል። የተናዘዘውን ሰው ኃጢአት በሚያዳምጥበት ጊዜ አምላክ ብርሃን እንዲሰጠው፣ ከሁሉ የተሻለው መድኃኒት ምን እንደሆነ እንዲያመላክታለው እንዲሁም የኑዛዜውን ደረጃና ጥራት እንዲገልጽለት ይጸልይ ዘንድ ይገባል።
ራሱን ከተናዘዘ ሰው ጋር በጉጉት፣ በጥርጣሬ፣ በምቀኝነት፣ ከመጠን ያለፈ ቁጥብነት፣ ኃይልና እብሪተኝነት አያስቀምጥም። ግን በተመሳሳይ ሁኔታ በግዴለሽነትና በድካም አይደለም። የተናዛዡ ትኅትና፣ ፍቅርና ትኩረት የሚናዘዙትን ሰው በእጅጉ ይረዳል።
የኑዛዜ ጥቅም
ቅድስት እናታችን ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የትንሣኤው የክርስቶስ አካል ናት። እሷ ደካሞችን ለመፈወስ ሰፊ ማቆያ ናት። የቁስሎችን፣ የድዉያንንና የኃጢአት በሽታዎችን ትፈውሳለች(ማቴ.9፥10-12)። በሽታ አምጪ አጋንንት፣ከመርዛማ የአጋንንት ወጥመዶች፣በአጋንንት የሚነዱ ስሜቶችና ተጽእኖዎች ማረፍያችን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ናት። (ለውሉደ ሰብእ መድኃኒት ወእስከ ለዓለም ሰፋኒት የምንለው ለዚህ ነው)
ቤተ ክርስቲያናችን የማኅበራዊ አገልግሎት ተቋም አይደለችም። ነገር ግን ቤተክርስቲያን በዋነኛነት የሕይወት ትርጉም፣ ለዓለም ቤዛ የሆነው የጌታችን የአምላካችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አማናዊ ሥጋና ደም የሚፈተትባት የምእመናን ቤዛ እና ድኅነት አቅራቢ ነች።
እግዚአብሔር ካህኑን ለፍጡራን ይቅርታ ይጠቀምበታል። በኑዛዜ ቃሉ ‹‹ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የካህናት አለቃ ለአባቶቻችን ለቅዱሳን ሐዋርያት ሥልጣነ ክህነትን የሰጣቸው ከልጅነት እስከ እውቀት የሠራችሁትን ይቅር ይበል…እምማዕሰረ ኃጢአት እግዚአብሔር ይፍታ›› ብሎ ከእስራት መፍታትና ለፍጡራን ይቅርታ ስልጣንን ሰጥቶታል። ለዚህም ነው ካህኑ በጸሎተ ኪዳን ‹‹ከመ እምሰብእ ይኩኑ አማልክተ…… ከመ ንፍታሕ ዘኢይትፈታሕ ፍቅረ ለነ ኀበ አቡከ ገበርከ ለነ›› የማይፈታውን እንፈታ ዘንድ ከአባትህ ዘንድ ፍቅርን አደረክልን የሚለው።
እንዴት መናዘዝ እንደሚገባ
የተናዘዝናቸውን ኃጢአቶች እንደገና እንናዘዛቸው ዘንድ አይገባም። ይህ በኑዛዜ የምናገኘውን ፍጹም ይቅርታና ምሕረት እንደመጠራር ይቆጠራል። አንድ ሰው እግዚአብሔር የምንሠራውን ኃጢአትና በደል ካወቀ ለምን መናዘዝ ያስፈልገኛል ሊል ይችላል። በእርግጥም እግዚአብሔር ሁሉን ያውቃል ነገር ግን ራስን ለማዋረድ(ለትኅትና) መናዘዝ ያስፈልጋል። ዳግመኛም በደሉና ኃጢአቱን ዳግም እንዳይሰራ አስተማሪ የሆነ ጫና መሆኑን መገንዘብ አለበት።
አንድ ኦርቶዶክሳዊ አባት እንደገለጸው፣ ኑዛዜ ማለት የአንድን ሰው የሰራውን ክፉ ሥራ፣ ቃላቶች እና ሐሳቦች በፈቃደኝነት፣ በቃላት መግለጥ ነው። ለእግዚአብሔር ያለን እውነተኛ አክብሮት መገለጫ መጸጸትን፣ ኃጢአትን መጥላትን፣ በጎነትን መውደድና ለስጦታ ሰጪው አምላክ በማመስገን ነው።
አንድ ሰው ሽንፈቱን፣ ውድቀቱንና ድክመቱን አምኖ ለመቀበል ይቸገራል።ለሠራነው ኃጢአት ሌሎችን መክሰስ ምክንያት መደርደር የመሳሰለውን በእጅጉ ማስወገድ ያስፈልጋል።ኀፍረት ከኃጢያት በፊት መኖሩ ጥሩ ነገር ነው ከዚያም በኋላ አይደለም። ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ እንዳለው ንስሐ በገባህ ጊዜ ሳይሆን ኃጢአት በሠራህ ጊዜ እፈር። ሰይጣን የሚያዛባው ቅደም ተከተሉን ነው ኃጢአት ስንሰራ እንዳናፍር ንስሐ ስንገባ እንዳንናዘዘው በማሳፈር ያስተናል። ኀፍረት በመጨረሻው ፍርድ ከኃጢአታችን ነጻ ያደርገናል ተብሏል፡ ምክንያቱም ተናዛዡ የሚፈታው ሁሉ ዳግመኛ አይፈረድበትም።
በተጨማሪም ኑዛዜ ቀጣይነት ያለው መሆን አለበት፣ ስለዚህም "በሆን ብለው የሚደጋገሙ" ስሜቶች (እንደ ባለመሰላሉ ቅዱስ ዮሐንስ ገለጻ) እንዳይጠናከሩ፣ ይልቁንም በፍጥነት እንዲድኑ ያግዘናል። ስለዚህ በቋሚነት እራስን መከታተል ራስን መመርመር በእጅጉ ያስፈልጋል።ለዚሀም እግዚአብሔር ይርዳን።
ይቆየን
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
No comments:
Post a Comment