በዲያቆን ያሬድ መለሰ
ይህ ዘመን ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በተመለከተ የተዛቡ አስተሳሰቦችና አመለካከቶች የሚንጸባረቁበት ዘመን ነው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ “ሰዎች እኔ ማን እንደ ሆንሁ ይላሉ?” (ማቴ. 16፥13) ብሎ የጠየቀውን ጥያቄ በርግጥ ዛሬ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን “ሰዎች ቤተ ክርስቲያንን ማን እንደሆነች ይላሉ?” ብለን መጠየቅ የሚገባን ዘመን ነው። ዛሬ ዛሬ ሰዎች "በክርስቶስ እናምናለን" ይላሉ ግን ቤተ ክርስቲያንን “መልክና ውበት እንደሌላት” (ኢሳ. 53፥2) በሰው ልጆች ድኅነት ላይ ምንም ድርሻ እንደሌላት አንዲት ተቋም አድርገው የሚመለከቱ ብዙዎች አሉ። በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ ስለቤተክርስቲያን የምናገኘው ዋና ምስል ግን ከዚህ በእጅጉ ይለያል።በዚህ ጽሑፍ ይህን በቅዱሳት መጻሕፍት የተገለጠውን የቤተ ክርስቲያንን ምስል ለማየት እንሞክራለን።ለዛሬ በባልና በሚስት መካከል ባለው ግንኙነት የተመሰለውን የክርስቶስና የቤተ ክርስቲያን አንድነት እንመለከታለን።
ይህ ምሥጢር ታላቅ ነው (ኤፌ.5፥22-32)
በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ የምናገኘው የቤተክርስቲያን ዋና ምስል ቤተክርስቲያን የክርስቶስ ሙሽራ(ኤፌ.5፥22-32) እንደሆነች ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የክርስቶስንና የቤተ ክርስቲያንን ግንኙነት በተመለከተ በባልና በሚስት መካከል ባለው ግንኙነት መስሎን አስተምሮናል። ክርስቲያኖች ወደ መዳኑ ይቀርቡ ዘንድ የመለኮት ባሕርይ ተካፋዮች የሚሆኑባት (2ኛ ጴጥ. 1፥4) ቤተ ክርስቲያን ናት። ደራሲው እንዳለ በእውነት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ለሰው ልጆች መድኃኒትና እስከዘለዓለም ገዥ ናት።
የክርስቶስ አካልና ሙሽራ-ቤተ ክርስቲያን
የጋብቻ ወሳኝ ሀሳብ ከብዙነት አንድነትን መፍጠር ነው። ባልና ሚስት "አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ወደ ፊት ሁለት አይደሉም" (ማቴ. 19፥6) እንዳለን በቅዱስ ጋብቻ አንድነትን ይመሠርታሉ። በቤተክርስቲያኑ ውስጥ ይህ አንድነት በክርስቶስና በእያንዳንዱ አማኝ መካከል እንዲሁም በክርስቶስና በአማኖች መካከል ያለ ኅብረት ነው። የኅብረቱ መሠረትና አብነት በትምህርተ ሥላሴ እንደተማርነው በሦስቱ አካላት መካከል ያለው አንድነት የመሰለ ነው። ጌታችን በመዋዕለ ሥጋዌው ስለ ቤተ ክርስቲያን አንድነት እንደጸለየ "ሁሉም አንድ ይሆኑ ዘንድ…. አንተ አባት በእኔ እንዳለህ እኔም በአንተ፥ እነርሱ ደግሞ በእኛ አንድ ይሆኑ ዘንድ…...እኛም አንድ እንደ ሆንን አንድ ይሆኑ ዘንድ እኔም በእነርሱ አንተም በእኔ ስትሆን በአንድ ፍጹማን እንዲሆኑ የሰጠኸኝን ክብር እኔ ሰጥቻቸዋለሁ (ዮሐ. 17፥21-22) ።
ይህንን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው ወቅት የጸለየውን ጸሎት በቅድስት ሥላሴ መካከል የተገለጸው ኅብረትና አንድነትን የመሰለ አንድነትና ኅብረትን ቤተ ክርስቲያን እንዲሰጣት ዘወትር ትለምናለች። በቅዳሴያችን "ወበከመ አስተጋባእካ ለዛቲ ኅብስት እንዘ ዝሩት ይእቲ ወስተ አድባር ወአውግር ወተጋቢኣ ኮነት አሐተ ኅብስተ ፍጽምተ ወከማሁ ኪያነሂ አስተጋብአነ በመለኮትከ እምኩሉ ሕሊና እኩይ ውስተ ሃይማኖትከ ፍጽምት…" "ይህችን ኅብስት በተራራና በኮረብታ የተበተነች ስትሆን እንደ ሰበሰብካት ተሰብስባትም አንዲትም ፍጽምት ኅብስት እንደሆነች እንዲሁም እኛን በጌትነትህ ከክፉሕሊና ሁሉ ለይተህ በሃይማኖት አንድ አድርገን…."(ቅዳሴ ጎርጎርዮስ ካልዕ) ማለታችንም ይህንን የሚያመላክት ነው። ዳግመኛም « በኵሉ፡ ልብ፡ ናስተብቍዖ፡ ለእግዚአብሔር፡ አምላክነ፡ ኅብረተ፡ መንፈስ ቅዱስ፡ ሠናየ፡ ከመ፡ ይጸግወነ። በፍጹም ልብ አምላካችንን እግዚአብሔርን እንለምነው፥ ያማረ የመንፈስ ቅዱስን አንድነት ይስጠን ዘንድ» በማለት ዲያቆኑ በቅዳሴ ጊዜ የሚያሳስበንም ለዚህ ነው።
ቤተክርስቲያን የሥላሴ ፍጹም አንድነት ነጸብራቅ ናት። በዚህ የጸሎት ክፍል ውስጥ የክርስትና ምንነት በግልጽ ተቀምጧል። ክርስትና በአእምሮ የሚቀበለውና በእያንዳንዱ ሰው ተለይቶ የሚገኝ ረቂቅ ትምህርት አይደለም። ነገር ግን ክርስትና የተለያዩ አካላት እርስ በርሳቸው የተዋሐዱበት አንድነታቸው ከቅድስት ሥላሴ አካላት አንድነት ጋር የሚመሳሰልበት ሕይወት ነው። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው የጸለየው ጸሎት ትምህርቱ ተጠብቆ እንዲቆይ ብቻ ሳይሆን ትምህርቱ በመላው ዓለም ሁሉ እንዲሰራጭ ነው። በእርሱ ለሚያምኑት ሁሉ አንድነት ጸለየ። ቅዱስ ጳውሎስ የሰውን ወገኖች ሁሉ ከአንድ ፈጠረ (ሐዋ. 17፡26) እንዳለ የሰው ልጆች ሁሉ የተፈጥሮ አንድነት እንዲመሠረት፣በትክክል ወደቀደመ ማንነቱ እንዲታደስ ወደ ሰማያዊ አባቱ ጸለየ።
ቅዱስ ቄርሎስ ዘእስክንድርያ በተመለከተ ሲናገር “ክርስቶስ የባሕርዩ ምሳሌ (ዕብ. 1፥3) የማይከፋፈል ፍቅርን፣ መስማማትንና አንድነትን ከእርሱ ጋራ በአንድነት ብቻ የሚታሰብ አብ ከእርሱ ጋር ያለውን አንድነትና ምሳሌ አድርጎ በመውሰድ እርሱ ደግሞ ከአብ ጋር ያለው፣ እኛ ደግሞ እርስ በርሳችን እንዲኖረን እንደሚፈልግ ያመለክታል። ቅድስት ሥላሴ አንድ በመሆን መላው የቤተ ክርስቲያን አካል እንዲጸነስ በክርስቶስ አማካኝነት የአማኞች ውህደትም ወደ አዲሱ ፍጹም አንድነትና ኅብረት ይለወጣል። የቅድስት ሥላሴ ፍጹም መስተጋብር አንድ ልብ በሆኑ አማኞች አንድነት በአእምሮ በልብና በአካል ውስጥ መንጸባረቅ አለበት። ይህም አንድነት ሥጋዊ አንድነት አይደለም" ብሏል።
በክርስቲያናዊ ጋብቻ በአንድ ሥጋ ውስጥ ያለውን አንድነት የሚያመለክት ብቻ ሳይሆን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉ አማኞች ሁሉ የአንድነት አምሳል ነው። ይህም ለትልቁ ማኅበር መሠረት፣ እንደዝቅተኛ ሕዋስ ያለ ነው።ቅዱስ ጳውሎስ "በቤታቸው ላለች ቤተ ክርስቲያን ሰላምታ አቅርቡልኝ።" እንዳለ (ሮሜ 16፡5) ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም “ትንሿ ቤተ ክርስቲያን (little church)” የሚለው ይህንን ነው። የክርስቲያን ቤተሰብ “የቤት ውስጥ ቤተክርስቲያን” ማለት ብቻ አይደለም። ቤተክርስቲያኑ ሁለቱም ከትናንሽ ቤተሰቦች ወይም ከትናንሽ አብያተ ክርስቲያናት የተዋቀረች በክርስቶስ ስም የተሰየመች “በሰማይና በምድር ያለ ቤተሰብ በሙሉ” ያቀፈች (ኤፌ. 3፥15) አንድ ትልቅ ቤተሰብ ወይም ታላቅ ቤተክርስቲያን ናት።
ይቆየን
ወስብሐት ለእግዚአብሔር