ዓለም አቀፍ ጉባኤያትና አብያተ ክርስቲያናት በኦርቶዶክሳዊ ቅኝት
ጉባኤ ኒቅያ
የአርዮስ ኑፋቄ
ወልድ ባልነበረበት ጊዜ አብ ነበረ አብ ወልድን ከምንም ፈጠረና የእግዚአብሔር ልጅ እንዲሆን አደረገው ይህም መለት እግዚአብሔር አብ ወልድን እንደማንኛውም ፍጥረት ፈጥሮታል በኋላም ሥልጣን ስለሰጠው ፈጥሮ ፈጥሮበታል ብሎ አስተማረ፡፡
ለዚህ ትምህርቱ መነሻ የሆነው ኃይለ ቃል ምሳ 8፥26 ትቤ ጥበብ ፈጠረኒ መቅድመ ኩሉ ተግባሩ ጥበብ ከፍጥረታት ሁሉ እስቀድሞ እኔን ፈጠረችኝ በማለት ጥበብ የተባለ ወልድ ነው ብሎ አስታማረ
የአርዩስ ትምህርት የተቀዳው ከማን ነው?
አርዩስ ትምህርቱን የቀዳው ከፈላስፎቹ አፍላጦንና አሪስጣጣስ ሲሆን እነዚህ ፈላስፎች ዓለም የተፈጠረው በራሱ በእግዚአብሔር በቀጥታ ሳይሆን እግዚአብሔር በፈጠራቸው መናፍስት ወይም ኃይሎች አማካኝነት ነው ብለው አስተምረዋል፡፡ ይህን ትምህርት አርዮስ አዲስ ቅርጽ በማስያዝ መናፍስት ያሏቸውን ክብር ይግባውና ወልድ ነው በማለት የእነዚህን ‹‹ፈላስፎች›› ትምህርት መጽሐፋዊ በማድረግ ብዙዎችን አስቷል፡፡
የአባቶች መልስ
አባቶቻችን ጸሎተ ሃይማኖትን እስከ ሰባተኛው አንቀጽ ድረስ የነገጉት በዘህ ጉባኤ ላይ ነው ይህም ፍጹም መጽሐፋዊና ለመሠረተ እምነታችንን ማሳያ ነው፡፡
ሁሉን የፈጠረ አንድ አምላክ በሚሆን በእግዚአብሔር እናመናለን
ሰማይና ምድርን የፈጠረ የማይታየውንና የሚታየውን ዓለም ሳይፈጠር ከእርሱ ጋር የነበረ
አንድ የአብ ልጅ በአንድ ጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እናምናለን
ከብርሃን የተገኘ ብርሃን ከእውነተኛ አምላክ የተገኘ እውነተኛ አምላክ
የተወለደ እንጂ ያልተፈጠረ በባሕርዩ ከአብ ጋር የሚስተካከል ሁሉ በእርሱ የሆነ
በሰማይም በምድርም ካለው ያለእርሱ ምንም ምን የሆነ የለም
ስለእኛ ስለሰዎች እኛን ለማዳን ከሰማይ ወረደ
በመንፈስ ቅደስ ግብር ከቅድስት ድንግል ማርያም ፍጹም ሰው ሆነ
ደግሞ ስለእኛ ተሰቀለ ሞተ ተቀበረ በሦስተኛው ቀን ከሙታን ተነሣ
በቅዱሳን መጻሕፍት እንደተጻፈ በክብር ወደ ሰማይ ዐረገ፡፡
በአባቱም ቀኝ ተቀመጠ
ዳግመኛም በሕያዋንና በሙታን
ለመፍረድ በምስጋና ይመጣል ለመንግስቱም ፍጻሜ የለውም፡፡
አባቶች ከአርዮስ ትምህርት በተጨማሪ ከዚህ በተጨማሪ 20 ቀኖናዎች ተንግገዋል፡፡
ጉባኤ ቁስጠጥንጥንያ
በጉባኤው ላይ ትምህርታቸው የተወገዘባቸው መናፍቃን
አቡናርዮስ ዘላዞቅያ ክህደት
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መለኮት የሥጋ በሆነች ነፍስ ብቻ ተተክቶ ሕማምን ስቅለትንና ሞትን ከሥጋ ጋር ተቀበለ ይላል፡፡በዚህ ብቻ አላበቃም መንፈስ ቅዱስ ትልቅ ነው ወልድ ከመንፈስ ቅዱስ ትልቅ ነው አብ ከሁሉ ትልቅ ነው ብሎ አስተምሮል፡፡
የአባቶች መልስ
ጌታ ነፍስ ያላተዋሐደው ነው ወይም በነፍስ ፈንታ መለኮት ከሥጋ ጋር ተዋሐደ ማለት የቤተ ክርስቲያንን የነገረ ድኅነት ትምህርት ጋር የሚጋጭ ነው፡፡ ነፍስ የሌለውን ሥጋ ተዋሕዶ እንዴት የሰው ነፍስን ሊያድን ይችላል ብለው ብለው መልስ ሰጥተዋል፡፡
በሥላሴ መካከል መበላለጥ አለ የሚለው ትምህርት በጉባኤ ኒቅያም ጭምር የተወገዘ ነው፡፡ የጉባኤ ኒቅያ ትምህርት የሆነው ጸሎተ ሃይማኖት ‹‹ከአብ ጋር የሚተካከል ›› የሚለውን አንቀጽ የሚያነብ ሰው በቅድስት ሥላሴ መካከል የሥልጣን ልዩነት እንደሌለ በጉልህ ይረዳል፡፡ ይህ የአባቶች ትምህርት መጽሐፋዊ ሲሆን የመናፍቁ የአቡሊናርዮስ ትምህርት ግን የመጽሐፍ ማስረጃ የሌለው ተራ ክህደት ነው፡፡
የአውሳብዩስ ትምህርት
እንደሰባርዩስ ትምህርት ሦስቱ አካላት በተለያዩ ሁኔታዎች የተገለጡ ናቸው፡ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ የምንለው ሦስቱ አካላት በተለያዩ ሁኔታዎች መገለጥ ነው እንጂ የተለያዩ አካል ያላቸው ሆነው አይደለም፡፡ ይህን ትምህርት በመቅዳት በኦሪት እንደ አብ በሐዲስ እንደ ወልድ በዘመነ ሐዋርያት ደግሞ እንደ መንፈስ ቅዱሰ የተገለጠው አንድ ነው የአካል ሦስትነት የለውም ብሎ አስተማረ፡፡
ይህም ተራ ፍልስፍና ነው አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ፍጽም መልክ ፍጹም ገጽ ፍጽም አካል ያላቸው መሆኑን በሚያመለክት ሁኔታ በማቴ 3፡17 በተለያየ አምሳል በዩርዳኖስ ወንዝ ስለወልድ መመስከራቸው ምስክር ነው፡፡(1ኛ ዮሐ 5፥12)
የመቅዶንዩስ ትምህርት
ይህን ትምህርት ያሰራጨው መናፍቅ የአርዩስ ትምህርት ደጋፊ ነበር፡፡ ጌታችንን የካደውን አርዩስን የሚከተል ሰው መንፈስ ቅዱስን ቢክድ አይደንቅም፡፡ እንዲህም ብሎ ያስተምር ነበር፡፡ መንፈስ ቅዱስ በፍጥረታቱ ሁሉ የተሰራጨ የእግዚአብሔር ፍጡር ነው እንጂ በአብና በወልድ ደረጃ ያለ አይደለም በመላእክት መልክ ተፈጥሮ ከመላእክት ከፍ ያለ ነው ብሎ አስተማረ፡፡
አባቶቻችን የመቅዶንዩስን ትምህርት በማውገዝ የጸሎተ ሃይማኖት ክፍል ላይ ተጨማሪ ስለመንፈስ ቅዱስ የሚያወሱ ክፍሎችን ጨምረዋል፡፡ ይህ ምንፍቅና ተራ ፍልስፍና እንጂ መጽሐፋዊ አይደለም፡፡(1ኛ ዮሐ 5፥12)
የኤፌሶን ጉባኤ
በጉባኤው ላይ ትምህርታቸው የተወገዘባቸው መናፍቃንቢላግዩስ
የዚህ ሰው ክህደት የአዳም ኃጢአት ለልጆቹ አልተላለፈም፡፡ አንድ ሰው በሚወልድ ጊዜ ኣዳም ከኃጢአት ከመውቁ በፊት እንዳለ ሆኖ ይወለዳል፡፡በዚህም አንድ ሰው ወደ ከፍተኛ የቅድስና ደረጃ የሚደርሰው የእግዚአብሔርን እርዳታ ሳይጠይቅ ነው ብሎ አስተማረ፡፡
ይህ ትምህርት የምሥጢረ ድኅነትን ትምህርት ዋጋ የሚያሳጣ ነው፡፡ አምላክ ሰው ስለምን ሆነ ብለን ብንጠይቅ መልስ ለመመለስ ይቸግረናል፡፡ ምክንያቱም ሁሉም ሰው ከኃጢአት ነጻ ሆኖ ይወለዳል ብሎ ያስተምራልና
መጽሐፍትም ይህን ትምህርት ትክክል እንዳልሆነ ይመሰክራሉ፡፡(መዝ 51፥3 ሮሜ5፥12 1ኛ ቆሮ 15፥22)
ንስጥሮስ
የእግዚአብሔር ቃል ከሁሉ በፊት ነበረ መሆኑን አምናለሁ ማርያም የእምላክ እናት ነች የሚለውን አባባል ግን አላምንም፡፡ የክርስቶስ እናት መሆኗን አልክድም ነገር ግን እናትነቷ ለትስብእት ነው፡፡ ማርያም እግዚአብሔርን አልወለደችም ነገር ግን ከሥጋ የሚወለድ ሥጋ ነው ከመንፈስ የሚወለድ መንፈስ ነው፡፡ ፍጡር ሆና የወለደችው የእግዚአብሔር መሳርያ ፍጡር እንጂ ፈጣሪ አይደለም፡፡ በዚህም የተነሳ ጌታችን ሁለት ጠባይ ሁለት አካልና ሁለት ፍቃድ አለው፡፡ ሰብአ ሰገል ለጌታ መስገዳቸው አግባብ አይደለም ምክንያቱም ሕጻኑ ኢየሱስ ገና መለኮት ያልተዋሐደው ሥጋ ነውና፡፡(ማቴ 2፥11)
የአባቶች መልስ
ቅዱስ ቄርሎስ አባታችን እመቤታችን ወላዲተ አምላክ መባል እንደሚገባት አምላክንም እንደወለደች በጉባኤው ላይ አብራርቶል፡፡ የጌታችን የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተዋሕዶ የከበረ ያለመለወጥ ያለመከፈል ያለኅድረት ሥጋና መለኮት መዋሐዳቸውን አንዱ የአንዱን ባሕርይ ገንዘብ ማድረጉን በስፋት አስተማረ፡፡ ሁለት ፍቃድ ሁለት ባሕርይ ሁለት አካል የሚለው የንስጥሮስ ትምህርትም በዚህ ጉባኤ ተወግዞል፡፡
የኬልቄዶን ጉባኤና የአባቶች ተጋድሎ
የአውጣኪ ክህደትአውጣኪ የንስጥሮስን ትምህርት ከመጥላቱ የተነሳ ወደ ስሕተት የገባ ሰው ነው፡፡ ይህ ሰው ትምህርቱ አንድ ባሕርይ አንድ አካል ነው ቢልም በመጠፋፋት አንድ ሆኑ ብሎ ያስተምር ነበር፡፡ በዚህ ትምህርቱ ምክንያት በፍላፕያኖስ መጀመርያ (በሁለተኛው የኤፌሶን ጉባኤ) ቀጥሎም በቅዱስ አባታችን ዲዮስቆሮስ አማካኝነት ትምህርቱ የተወገዘ ነው፡፡
ሁለተኛው የኤፌሶን ጉባኤ በ449 ዓ.ም የአውጣኬን ትምህርት ለማውገዝ የተደረገ ነው፡፡በፍላፕያኖስ ዘቁስጠንጥንያ እንደተለመደው የቤተ ክርስቲያን መሪዎችን ሳይጠራና ኤጵስ ቆጶሳትን ሰብስቦ በ 431 አወገዛው፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት ፍላፕያኖስ ሁለት ባሕርይና ሁለት ፍቃድ አለው ከሚሉ ሰዎች በመሆኑ በችኮላ በመሆኑ ዳግመኛ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ በ449 ኤፌሶንን ጉባኤ አደረገ ነገር ግን አውጣኪ አንድ ባሕርይ በመጠፋፋት ካለው ትምህርት ለጊዜውም ገሸሽ ብሎ እምነቴ የሠለስቱ ምዕትና የቅዱስ ቄርሎስ ነው በማለቱ ከእስራቱ ፈትውታል፡፡ በኃላ ላይ ግን ይህን ትምህርት መልሶ በማስተማሩ ዳግመኛ ተወግዞል፡፡
የልዩን ክህደት
የልዩን ጦማር ወደ ፍላፕያኖስ(ፍላብያኖስ)
የልዩን ጦማር ፍጽም ክህደትና የንስጥሮስን ትምህርት በመድገም ዳግመኛ የአባቶቹን ድንበር ያፈረሰ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ጦማሩን የተመለከተው ንስጥሮስም የክህደቱ ትምህርት ስለሰመረለት የሮምን ቤተ ክርስቲያን አወድሶል፡፡ ጦመሰሩ በአጭሩ ክርስቶስ ሁለት ባሕርይ ሁለት ሕላዌ አንድ አካል አለው የሚል ነው፡፡ በልዩን ፍልስፍና አካልና ባሕርይ የተለያዩ ናቸው የሚል ነው፡፡
አባቶቻችን ከአካል የተለየ ባሕርይ የለም ከባሕርይ የተለየ አካል የለም ብለው አስተምረውናል፡፡ ከአካል የተለየ ባሕርይ ከሌለ ደግሞ ሁለት ባሕርይ ካልን ሁለት አካል ወደሚል ትምህርት ይወስደናል፡፡ ይህ ትምህርት ደግሞ የንስጥሮስ ትምህርት ነው ይህ የንስጥሮስ ትምህርት ታዲያ ቀድሞ በአባቶቻችን በጉባኤ ኤፌሶን የተወገዘ ነው፡፡ወይም አካልን አንድ ካልን በባሕርይም አንድ ወደ ማለት ይመራናል ይህም እንደ ቅዱስ ቄርሎስ ነው፡፡ ሁለቱ ባሕርያት በመተባበር የየራሳቸውን ድርሻ ይሰራሉ ‹‹መለኮት ይገብር ግብረ መለኮት ትስብእት ይገብር ግብረ ትስብአት›› የሚል ጦማር ነበር፡፡ይህም ጦማር ተአምራት ያደረገው መለኮት መከራን የተቀበለው ሥጋ ብሎ ያስተምራል፡፡
የኬልቄዶን ጉባኤ የተሳታፊዎች ቁጥር 636 ሲሆን ይህም የሆነበት ምክንያት ከቀድሞ ጉባኤያት ሁሉ ታላቅ ጉባኤ ለማስመሰል ነው፡፡ በዚህ ጉባኤ ላይ ከዚህ በፊት የንስጥሮስን ትምህርት በመደገፋቸው ምክንያት የተወገዙ ሰዎች ጭምር የተሳተፉበት በመሆኑ በአባቶች ዘንድ ግርታን ፈጥሮል፡፡ ቅዱስ ዲዮስቆሮስም የእስክንድርያን አብያተ ክርስቲያናትን ወክሎ በጉባኤው ላይ ተገኘ፡፡ የጉባኤያቱ አባላትም ተቃውሞ አጸኑበት ተከሳሽም አደረጉት የአውጣኪ ትምህርት ደጋፊ ነህ ውጣ አሉት፡፡ ቅዱሱም መንበሩን ለማስከበር ሲል ወጣ ይህንን የአርመን የሕንድና የሶርያ አብያተ ክርስቲያናት ተቃወሙ፡፡ ግሪኮቸቹና የምዕራብ አብያተ ክርስቲያናት ግን ከምሥራቃዊያኑ ጋር ተባበሩ፡፡
የልዮን ጦማር ውስጥ የተካተቱ ነጥቦች
- ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ ነው በኃላም ሰው ሆኖ ተገለጠ
- መለኮትና ሥጋ በእርሱ ውስጥ ተገናኙ ያለመቀላቀል በእርሱ ውስጥ ይኖራሉ
- እያንዳንዱ ባሕርይ የግብር ክልሉን ጠብቆ ይኖራል ማለት መለኮት የመለኮትን ትስብእት ትስብእትን ሥራ ይሠራል ማለት ነው፡፡
- የሁለቱም ባሕርያት ሀብት ለአንዱ አካል በእኩልነት ይገኛሉ
- ከመዋሐድ በፊት ሁለት ነበሩ ከተዋሐዱ በኃላ አንድ ናቸው ብሎ ማሰብ ሞኝነት ነው የሚሉ ይገኙበታል፡፡
ተገናኙ ተራከቡ አብረው ይኖራሉ?
ይህ ትምህርት ለተዋሐዶ ትምህርት ጸር ይሆን ዘንድ በንስጥሮስ የተቀመመ ክህደት ነው፡፡እነዚህ ቃላት የአማላክን ሰው መሆን የሰውን አምላክ መሆን አመልካች አይደሉም፡፡ ጽምረት ነው እንጂ እንደዳዊትና ማኅደሩ ኅድረት ተዋሕዶ ግን እንደነፍስና ሥጋ ነው፡፡የግብር ክልሉን ጠብቆ ይኖራል?
ተዋሕዶ መለኮት የሥጋን ባሕርይ ገንዘብ አደረገ ሥጋም የመለኮትን ባሕርይ ገንዘብ አደረገ ብላ ታስተምራለች፡፡ ቅዱስ ቄርሎስም እንደሚል‹‹ እንቲአሁ ለቃል ኮነ ለሥጋ ወእንቲአሃ ለሥጋ ኮነ ለቃል›.
አንዳንድ ጊዜ እንደሥጋ አንዳንድ ጊዜ እንደመለኮት ይሰራል ብሎ የሚከፍለው ልዩን በአንድ ጊዜ የአምላክነትና የሰውነት ሥራ አይሰራም ብሎ በመልእክቱ አስቀምጦል፡፡ እኛ ግን ሥግው ቃል መከራን ተቀበለ ሞተ ተነሳ ተአምራት አደረገ ተራበ ተጠማ እንላለን ይህም የአባቶቻችን ትምህርት ነው፡፡
ተዋሕዶን ያስተማሩ አባቶች
ከኬልቄዶን ጉባኤ በኃላ ለሚቀጥሉት 150 ዓመታት ያህል የነገሡ የቁስጥንጥንያ ነገሥታት ሁለቱን አብያተ ክርስቲያናት ለማዋሐድ ጥረት አድርገው ነበር፡፡ በሮም ቤተ ክርስቲያን ጣልቃ ገብነት ሳይሳካ ቀረ፡፡አጋግዩስ ብርቱ ጥረት የአንጾክያና የእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን ለስምምነት የሚያበቃቸውን ስምምነት ተፈራርመው ነበር፡፡ሳዊሮስን የመሰሉ ፊልክስዮስን የመሰሉ በአንጾክያና በሶርያ ተዋሕዶን የሰበኩ አልታጡም፡፡ ይህም የአባቶችን ተጋድሎ አመርካች የታሪከ ገጽ ነው፡፡
ጉባኤ ቁስጥንጥዮስ ሁለተኛ
ይህ ጉባኤ በዋነኝነት በጉባኤ ኬልቄዶን የተወሰነውንና በቅዱሳኑ በጥንታዊያን ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት መካከል ልዩነት የፈጠረውን ትምህርት ማለትም በእነሱ አጠራር ሞኖፈስትስ (ይህም በእነሱ አረዳድና ትርጉም የአውጣኪን ትምህርት ማለትም ተዋሕዶ በመጠፋፋት የሚለውን ትምህርት የሚወክል ነው) ለመቃወም ካቶሊካዊያኑና የቁስጥንጥንያ ቤተ ክርስቲያን ያደረጉት ነው፡፡
ለመሆኑ ሞኖፈስርስ ዳዩፈስቲስ ምንድን ነው?
ሞኖፊሲትስ (Monothelitism)
ሞኖፊሲትስ ማለት በውላጤ የተገኘ አንድ ባሕርይ ይህ ስም ተዋሕዶን የሚገልጥ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ተዋሕዶ ስንል ያለ መጠፋፋት ተዋሐዱ አንዱ የአንዱ ባሕርይን ያለመለወጥ ያለፍልጠት ያለኅድረት ያለሚጠት ተዋሐደ ብለን እናስተምራለንና ነው፡፡ ይህ ትምህርት ግን የአውጣኪን ክህደት በትክክል የሚገልጥ ቃል ነው፡፡ ዳዩፊሲስትስ ይህ በትክክል የንስጥሮስን ክህደትና የልዩንን የፍልስፍና ትምህርት የሚገልጥ ነው ፡፡ የንስጥሮስ ሁለት ባሕርይ ሁለት አካል ሁለት ሕላዌ አለው ስለሚል ዳዩፊሲስትስ ነው የልዮንም ሁለት ባሕርይ ስለሚል ዳዩፊሲስትስ ብለን መጥራት እንችላለን፡፡
ይህን ጉባኤ ማድረግ የተፈለገበት ምክንያት የተዋሕዶ አርበኞች ተዋሕዶን በማስተማር ስለበረቱና በክርስትናው ዓለም ተዋሕዶ እየታወቀ እየተረዳ ስለመጣ በዚህ ምክንያት ካቶሊካዊያኑ የኬልቄዶን ጉባኤን አንደ ሕጋዊ ጉባኤ በመቁጠር የጉባኤውን ሐሳብ ለማጽናት ነው፡፡
ተዋሕዶ ከአውጣኪ ትምህርት ጋር ያለው ልዩነት
ጥንታዊያን ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት አውጣኪን ቁጥሩ ከመናፍቃን እንጂ ከቅዱሳኑ ተርታ አላኖሩትም፡፡ ትምህርቱም በቅዱስ አባታችን ዲዮስቆሮስ አማካኝነት የተወገዘ ነው፡፡
ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ስትል
እንበለ ዉላጤ(ያለ መለወጥ)
ዉላጤ ስንል ሥጋ ወደ መለኮት መለኮት ወደ ሥጋነት መለወጥ ማለታችን ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ከምናገኛቸው ታሪኮች የመለወጥን ትርጉም ለመረዳት ምሳሌ እንጥቀስ የሎጥ ሚስት ወደ ጨው አምድነት(ዘፍ 19፥26) መለወጥ የቃና ዘገሊላ ውኃ ወደ ወይን ጠጅነት (ዮሐ 2፥1-3) መለወጥም ፍጹም ባሕርውን ለቆ አዲስ ወደ ሆነ ባሕርይ መለወጡን የሚያመለክቱ ናቸው፡፡ለተዋሕዶ ግን እንዲህ አይደለም፡፡
መለኮት ወደ ሥጋነት ተለወጠ ካልን መለኮት ፍጹም ሰው ሆነ ማለት ነው፡፡ ይህም ነገረ ድኅነቱን ከንቱ ያደርገዋል ምክንያቱም የሰው ልጅ በፍጡር ደም አይድንምና በፍጡር ደም ቢድን ኖሮ ቀድሞ በዳነ ነበር፡፡ ሥጋ ወደ መለኮትነትም ተለወጠ ብንል ዓለም አልዳነም ወደሚል ሐሳብ የሚመራ ነው፡፡ መለኮት በባሕሪው ሊዳሰስ ሕማም ሊቀበል ወደ መቃብር ሊወርድ አይችልምና፡፡በተዐቅቦ(በመጠባበቅ) አንድ ሆኑ እንጂ መለኮት የሥጋን ባሕርይ ገንዘብ አደረገ ሥጋም የመለኮትን ባሕርይ ገንዘብ አደረገ
እንበለ ሚጠት(ያለመመለስ)
ይህም ዉላጤ ባሕርይው ከነበረበት ሁኔታ ከተቀየረ በኃላ መልሶ ወደ ቀድመ ግብሩ(ባሕርይው) ሲመለስ ሚጠት ይባላል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ የሙሴን በትር እንደምሳሌ ብናነሳ ወደ እባብነት ተለወጠ በኃላ መልሶ በትር እንደሆነው ሁሉ ለመለኮትና ለሥጋ እንዲሁ ነው ብሎ ማስተማር ሚጠት ይባላል፡፡
እንበለ ኅድረት
ይህ ትምህርት የተወገዘው የንስጥሮስ ትምህርት ነው፡፡ ዳዊት ከማኅደር ሰይፍ ከሰገባው እንደሚያድር በማርያም ልጅ በኢየሱስ ላይ አምላክ አደረበት በማለት የስህተት ትምህርት አስተምሮል ይህ ኅድረት ይባላል፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ተዋሕዶ ስትል ከዚህ የሚለይ ነው፡፡ ይህ ባሕርይን ለሁለትለመክፈል የተመቸ ነው ይኸውም ዳዊት ከማህደሩ ቢቀመጥ ማኅደር እነደማይባል ሁሉ ኢየሱስም የሰው ልጅ እንጂ አምላክ አይባልም እንደማለት ነው፡፡ ስለዚህም አምላክ ወሰብእ (ፍጹም ሰው ፍጹም)ማለት አይቻልም ማለት ነው፡፡ ይህን የስሕተት ትምህርት በጉባኤ ኤፌሶን የተወገዘ ትምህርት ነው፡፡
እንበለ ቱሳሔ(ያለመቀላቀል)
ቱሳሔ የአውጣኪ ትምህርት ነው ይህ ሰው በአካልም በባሕርይም አንድ ነው ብሎ ቢያስተምርም ነገር ግን በመቀላቀል በመደባለቅ ነው የሚል ነው፡፡
መለኮት ግን ምንም ቱሳሔ ሳይኖርበት ከእመቤታችን የነሣው ሥጋ ባለው አጽንቶ የፍጡር ልቡና መርምሮበማይደርስበት ግብረ አምላካዊ ጥልቅ በኾነ ምሥጢር(በመሆን) ተዋሕደው እንጂ በመቀላቀል እንደወተትና ቡና ተቀላቅለው በመካከላቸው ሌላ ነገርን ያስገኙ ወይም የተጠፋፉ አይደሉም
ወይም እንደ ትድምርት ያለ(በመደራረብ) እንደ ልብስ እንደእንጀራ ዓይነት ባለሆነ ወይም እንደቡዐዴ(ማዋሐድ ማያያዝ ተቃርቦ ተላስቆ) እንደእንጨትና ብረት ባልሆነ እንደነፍስናሥጋ በኃላ መለያየት ያለው ያለ ፍልጠት በተዋሕዶ ከበረ እንላለን፡፡ የጥንታዊያን ኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች እምነታቸው ይህ ነው፡፡
ጉባኤ ቁስጥንጥዮስ ሦስተኛ
ይህም ጉባኤ በተመሳሳይ ጉዳይ ላይ ዳግመኛ የተወያየ ጉባኤ ነው፡፡ በካቶሊካዊያኑ አነጋገርና አጠራር ሞኖፈስትስ (ይህም በእነሱ አረዳድና ትርጉም የአውጣኪን ትምህርት ማለትም ተዋሕዶ በመጠፋፋት የሚለውን ትምህርት የሚወክል ነው) አውጣኪያዊ ነው በማለት ውሳኔውን አጽንተዋል፡፡ ተዋሕዶን ፍጹም ያልተረዱት ካቶሊኮችና በወቅቱ የነበሩ የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ድዩፈስትስን(ምንታዌነትን) አጸኑት፡፡ ይህም በቤተ ክርስቲያኒቱ ታሪክ ታሪካዊ ስሕተት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡
ይቆየን
ስብሐት ለእግዚአብሔር