<<እመቤታችንም ቅድመ ዓለም በአምላክ ኅሊና ታስባ ትኖር ነበር>>
ተአምረ ማርያም
ስለቃሉ ተናጋሪ በጥቂቱ
የዚህ ቃል ጸሐፊ የእመብርሃን ፍቅር ከበዛላቸው ቅዱሳን አባቶች አንዱ የጥልጥልያው ኤጲስ
ቆጶስ ቅዱስ ደቅስዮስ ነው፡፡ ይህ ቅዱስ አባት በተአምረ ማርያም ድርሰቱ ይህንን ቃል ተናግሮታል፡፡ አባታችን ቅዱስ ደቅስዮስ
ያለ አንዳች ምክንያት ይህን አላለም፡፡ ይህንን የቅዱስ ደቅስዮስን ምስክርነት ቅዱሳት መጻሕፍት ተባብረው የቃሉን እውነተኛነት
የእግዚአብሔርን ሁሉን አዋቂነት ይናገራሉ፣ይመሰክራሉ እንጂ፡፡
ስለአባባሉ ተገቢነት
የተአምረ ማርያም መጀመርያው ተአምር እመቤታችን በአምላክ ኅሊና ታስባ ትኖር ነበር
የሚለውን ክፍለ ንባብ ሲያብራራ እግዚአብሔር ይህንን የተናገረ የሰው ልጅን ለማዳን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍስዋ
ነፍስ ነስቶ ሰው መሆኑን ሲያጠይቅ ነው ይላል፡፡(ተአምረ ማርያም አንደኛ ተአምር ገጽ 44) አዳም በአምላክ መልክና አምሳልም
ከመፈጠሩ በፊት ታስባ ትኖር ነበር፡፡ አንዳንዶች ይህ እንዴት ይሆናል ዓለምስ ከመፈጠሩ በፊት በአምልክ ኅሊና ታስባ ትኖር
ነበር መባሉ አግባብ አይደለም በማለት መጽሐፉ(ተአምሩም) ለማጥላላት ጥረት ያደርጋሉ፡፡ ለዛሬ ባነሳነው ነጥብ ላይ ከመጽሐፍ
ቅዱስ አንጻር እመቤታችን በአምላክ ልቡና ታስባ ትኖር ነበር መባሉ ትክክል እንደሆነ እናያለን፡፡ አንባቢያን ሆይ በመጀመርያ ከሁሉ አስቀድመን ቃሉ የእግዚአብሔርን አዋቂነት የሚያጎላ እንጂ
እነሱ እንደሚሉት እመቤታችንን ‹‹የማይገባትን ክብር›› የሚሰጥ አይደለም፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
በመጽሐፍ ቅዱስ ከተጻፉ ታሪኮች መካከል የእግዚአብሔርን አዋቂነት የሚያጎሉ ክፍለ ንባባት
እንጀምር በትንቢተ ኤርምያስ ላይ ተጽፎ እንደምናነበው ቅዱሱ እግዚአብሔር ነቢዩን “በሆድ ሳልሰራህ አውቄሃለሁ ከማኅጸን ሳትወጣ
ቀድሼሃለሁ ለአሕዛብም ነቢይ አደርግሃለሁ” ኤር.1፥5 እንዲል “እግዚአብሔር አዋቂ ነው” 1ኛሳሙ.2፥3 ልብ ያሰበውን ኩላሊት
ያጤሰውን ያውቃል ይመረምራል(መዝ 7፥9) በሐዲስ ኪዳንም ጌታችን
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰዎችን ሁሉ ያውቅ ነበር፡፡ ስለሰውም ማንም ሊመሰክር አያስፈልገውም ነበር፡፡ ሳይጠይቅ ያውቅ
ሳይፈትን ይመረምር ነበር፡፡ (ወንጌለ ዮሐንስ አንደምታ ዮሐ.2፥24)ደጋግ የብሉይ ኪዳን አበውንም ያውቃቸው ስለእነርሱም
ይመሰክር ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት አይሁድ አንተ ከአባታችን አብርሃም በፊት ነበርክን ብለው ጠይቀዋል ስለሙሴም ሲመሰክር
ለመቀበል ያንገራግሩ ነበር አምላካችን ግን አዳምን ከመፍጠሩ በፊት አዳምን ከነግብሩ ያውቀው ነበር፡፡
ስራው ድንቅ የሆነው አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር ፍጥረታትን ከመፍጠሩ
በፊት ሁሉን ያውቃልና በረቂቅ ጥበቡ ሰማይና ምድርን ሲፈጥር ሁሉም ውብ ሆኖ እንደተፈጠረ የፈጠረውንም የእጁን ስራ ሰው ሁሉ
መርምሮ እንደማይደርስበት የታወቀ ነው፡፡ መክ.3፥10
አንድ
ሸክላ ሰሪ ሸክላውን ከመስራቱ በፊት እንደሚያውቀው ማለት ነው፡፡ ያ ሰው ሸክላውን ለጌጥ ይሁን ወይስ ለመዓድ ቤት ለምን
እንደሚሰራው አስቀድሞ በአእምሮ ዕቅድ እንደሚያወጣና በዛ መሠረት እንደሚሰራ እንዲሁ እግዚአብሔር ፍጥረታቱን አስቀድሞ ያለገደብ
ያውቃል፡፡ “ምድርን በኃይሉ የፈጠረ ዓለሙን በጥበቡ የመሠረተ ሰማያትንም በማስተዋሉ
የዘረጋ እርሱ ነው”(ኤር.51፥15 ት.አሞ.4፥13)
እመቤታችን በአምላክ ሕሊና ለመታሰቧ ዋናው ምክንያት
የአባታችን የአዳም እና የእናታችን የሔዋን በደል በዓለም ላይ መከራ ሞትን አመጣ ዘፍ. 3፥17-24 በዚህ ጊዜ ነበረ
አዳም ከገነት ሲሰደድ ወደ ገነት መመለሻዬ ከእግዚአብሔር መታረቂያ ብሎ እመቤታችንን በመንፈስ ቅዱስ ምሥጢር ተመልክቷት ተስፋ አድርጎ
ይጠባበቅ ነበር፡፡ይህም እንደምነው ቢሉ፡-ጌታ እግዚአብሔር አዳምን ከአራቱ ባሕርያተ ሥጋ አምስተኛ ባሕርየ ነፍስ ፈጥሮ በልጅነት
አክብሮ በገነት አኖረው ዘፍ.2፡8 ሰባቱን ዓመት በሕግ ጸንቶ አትብላ ያለውን ጠብቆ ኖረ፡፡ ከዚያ በኋላ አትብላ ያለውን እጸ በለስ
በላ ሕጉንም አፈረሰ እንግዲህ በገነት መኖር አይገባም ብሎ ከገነት አስወጥቶ በገነት አንጻር በደብረ ቅዱስ አኖረው ስለምን ቢሉ
ኀዘን እንዲጸናበትና ወደ ቀደመ ቦታዬ ይመልሰኝ ይሆን እያለ ተስፋ እንዳይቆርጥ ከዕለታት በአንድ ቀን አዳም ሄዋንን እንዲህ አላት
በአንቺ ምክንያት እግዚአብሔርን ያህል ጌታ ገነትን ያህል ቦታ አጣሁ ብሎ ወቀሳት፡፡ ሔዋንም ደንግጣ ሸሽታ ከአጠገቡ ሄደች መልአኩም
መጥቶ ታረቃት አለው፡፡ በእርሷ ምክንያት እግዚአብሔርንም አጣሁ ከገነትም ወጣሁ አልታረቃትም አለው፡፡ ወደ ገነት የምትመለሰው በእርሷ ምክንያት ነውና ታረቃት
አለው፡፡ አልታረቃትም አለው፡፡ አልታረቃትም ብሎ እምቢ ባለው ጊዜ ቅዱሳን መላእክትም በጸሎቱ ሰዓት አንድ ነገር አስተማሩት ይኽውም
በሔዋን ላይ ቂም ይዞ ጸሎት ብታደርግ ምን ይጠቅምሃል; ጸሎትህም በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነት አይኖረውም አሉት፡፡ አዳምም ለመልአኩ
አንተ ሄደህ አምጣልኛ አለው ፡፡ መልአኩም እንዳባረርካት አንተ ሂደህ አምጣት አለው፡፡ ከዚህ በኋላ ሄዶ አምጥቷታል፡፡ እርሷም
ከጫማው ወድቃ ማረኝ ብላለች መልአኩም ለአዳም ከዚህ በኋላ አትለያት ብሎታል........ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር እንደተጣላን ይቀር
ይሆን ;አለችው፡፡ እሱ መሐሪ ነው ዳሩ ግን አንቺ አለሽና ምን ይሆናል አላት፡፡ ከእንግዲህስ ወዲህ ካንተ ፈቃድ አልወጣም አለችው
ከዚያ በኋላ ሄደው ከባሕር ገብተው ይጸልዩ ጀመር እግዚአብሔር ይታረቃቸው ዘንድ ቀን ከሌሊት ተጉ ፡፡ እግዚአብሔርም ድካማቸውን
ተመልክቶ ተስፋ ቃል ኪዳን ገባላቸው ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ፡፡ (ሉቃ.3፥38) ብሎ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን
በርቀት አንድም፡-በትንቢታዊ ቃል አሳየው፡፡ (1ኛ. ቆሮ.15፥22 ገላ 4፥4)
ስብሐት ለእግዚአብሔር
No comments:
Post a Comment