ትርጉም በዲ/ን ፍሬው ለማ
በብጹዕ አቡነ ሙሳ የግብጽ ቤተክርስቲያን የወጣቶች ጳጳስ
በዘመናችን ብዙ ጩኸቶችን እንሰማለን ሰዎች «እግዚአብሔር ይህን ሃሳብ ለምን በእኛ ውስጥ ፈጠረ ለምንስ
ያስጨንቀናል» ሲሉ እናደምጣቸዋለን ይህ የሥጋ ሃሳብ የሰውልጅ ከተፈጠረ ጀምሮ በምድር ላይ ብዙ ችግሮችን ፣ውጣ
ውረዶችን አምጥቷል ለእነዚህም የሰዶምና የገሞራ ሰዎችን ማንሳት እንችላለን ዮሴፍም ለእስር የተዳረገው በጲጥፋራ
ሚስት ውስጥ በነበረ የዝሙት ሃሳብ ነው ይህ ብቻ አይደለም በኦሪት ዘሌዋውያን የምናገኛቸው ታሪኮች፣የሶምሶን
መውደቅ፣የነገደ ብንያም በደል፣የዳዊት ኃጢአት እነዚህ ሁሉ ከዚህ የሥጋ ፈቃድ ጋር የተያያዙ ናቸውበዚህ ጊዜ ዓለምን ለመምሰል የሚደረግ ሩጫ በብዙ እንመለከታለን በጓደኝነትም በብዙሃን መገናኛዎች(ሚዲያዎች) ይህን መስማት የተለመደ ነገር እየሆነ ነው በሃገራች በድብቅ ከመከናወን ያለ ኀፍረት በአደባባይ ወደ መደረግ ተሸጋግሯል
እውን ጌታ ሩካቤ ሥጋን የፈጠረው ነፍሳችንን ሊያስጨንቃት ነውን?
ብዙ እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰማያዊውን መንግስት የሚናፍቁ ክርስቲያን ወጣቶች በዚህ ሃሳብ አዕምሯቸው ሲጨነቅ ይስተዋላል ከዚህ ጋር በተያያዘ ድኅነታቸው ከባድ እንደውም የማይቻል ይመስላቸዋል ቅዱስ ጳውሎስ ግን በሮሜ13፡11 ላይ«ካመንበት ጊዜ ይልቅ መዳናችን ወደ እኛ ቀርቧል » ይላል
ታዲያ ለምን ጌታ ሩካቤ ሥጋን ፈጠረ?
ጌታ የሰው ዘርን በምድር ላይ ማቆየት ቢፈልግ በሁለት ጾታ ሳይሆን ሁላችንም የተለያየን አድርጎ ሊፈጥረን ይችል ነበር ከሩካቤ ሥጋ ውጭ በራሳቸው ብቻ የሚራቡ ዕፅዋት እና ጥቃቅን ተህዋስያን አሉና ይህም ማለት በ(self-pollination እና binary production) የሚራቡ አሉና እንደነርሱ ያደርገን ነበር ወይም ደግሞ በአብዛኞቹ እንስሳት ውስጥ እንዳለ ጌታ ይህን ስሜት ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ንቁ የሚሆን ሌላ ጊዜ ደግሞ የሚጠፋ ሊያደርገውም ይችል ነበር ነገር ግን ጌታ ሩካቤ ሥጋን የፈጠረው የሰው ዘርን በምድር ከማቆየት በላይ ዓላማ ስላለው ነው የእግዚአብሔር ሃሳብ በእኛ መካከል ፍቅርን መተሳሰብን በእግዚአብሔርና በሰው መካከል ያለ ህብረትን የሚመስል በእኛ መካከል መፍጠር ነውይህም እጅግ በተረዳ መልኩ በምስጢረ ተክሊል ይገለጻል አንድ ክርስቲያን ለሌላ ሁለተኛ ሰው ራሱን አሳልፎ በመስጠት ከሁለትነት ወደ አንድነት በመንፈስ ቅዱስ የሚሸጋገሩበት በመሆኑ ነው ለዚህም ነው ከዚህ ከተቀደሰ ሩካቤ ሥጋ ያፈነገጡ ሁሉ ከእውነተኛው የህይወታቸው መስመር ጭምር የሚያፈነግጡት
ሩካቤ ሥጋ ትክክል የማይሆነው እንዴት ነው?
ከሩካቤ ሥጋ ጋር የተያያዙ የዝሙት የማመንዘር ኃጢአቶች ከሥጋ ብቻ የሚመነጩ አይደሉም ነገር ግን በርከት ካሉ ከሰው ጋር ከተያያዙ ስሜቶች፣ፍላጎቶች ነው። በሥጋችን ላይ የምናሳያቸው ነገሮች የእነዚህ ስሜቶቻችን ውጤቶች ናቸው። እነዚህ ውስጣዊ ሃይሎች ናቸው አንድን ሩካቤ ሥጋ ከትክክለኛው ነገር እንዲያፈነግጥ የሚያደርጉት እነዚህ ውስጣዊ ስሜቶች አራት ናቸው እነዚህም
1.ራስ ወዳድነት(ego centrism)
ያለ ጥርጥር እንደሚታወቀው እግዚአብሔር ሰውን የፈጠረው በህብረት እንዲኖር ነው ራሱ ጌታ እንዲህ ብሏልና«ሰው ብቻውን ይኖር ዘንድ መልካም አይደልም»ዘፍ 2፡18 ከዚህም በተጨማሪ ጌታ ደስታዬ በአዳም ልጆች ነው ብሏል ከእርሱም ጋር ህብረት እንዲኖረን ይፈልጋል ነገር ግን የሰው ልጅ ስህተት የሚጀምረው ስለራሱ ብቻ ማሰብ ሲጀምር ነው ጌታንም ሌሎቹንም ሲተው ነው ይህ በራስ ብቻ የሚል ስሜት ራስ ወዳድነት ነው ይህ ከሌሎች መገንጠል ሩካቤ ሥጋን አፈንጋጭና ጎጂ ከሚያደርጉት ሃሳቦች ዋነኛው ነው
የሰው ልጅ በራሱ መደሰት፣ራሱን መውደድና ራሱን ወደ ማምለክ እና በራሱ ወደ መኩራራት ሲያመራ ሌሎቹን ለራሱ ሲል ለማጥፋት ይነሳሳል ይህ መሰረታዊ የሆነና ለምኞት የሚያነሳሳን ነው አንድ ሰው ራሱን የሚወድና ራሱን ለማስደሰት ሌሎችን ሲጠቀም (ከእርሱ ውጭ ያሉትን ሰዎች ለእርሱ መደሰቻ ብቻ ሲያደርግ) ራስ ወዳድነቱ ይገለጣል
ክርስቶስን በማወቅ ወደ እርሱም በመጠጋት ለጸጋ ሥራዎች ራስን ክፍት በማድረግ የሕወትን ትክክለኛ መስመር ማወቅ ይቻላል ክርስቶስ ነፍስህን ከዚህ ራስን ማግለል(መገንጠል) ያወጣት ዘንድ በጽኑ ያፈልጋል «እኅቴ ወዳጄ ርግቤ መደምደሚያዬ ሆይ በራሴ ጠል በቆንዳላዬም የሌሊት ነጠብጣብ ሞልቶበታልና ክፈችልኝ»መኃ፭፡፪
ወዳጄ ሆይ ጌታ አንተን እየጠራህ ነው ልብህን ለእርሱ ከፍተህለታል? ከእርሱ ጋር መነጋገርስ ትፈልጋለህ?ህይወትህንስ ለእርሱ በመስጠት ከተጠላ ራስ ወዳድነት ትድን ዘንድ በፍቅሩ ትኖር ዘንድ ትፈልጋለህ?
በቅዳሴ ላይም «ያንተን ስም ሰምቶ ሞት ይደንግጥ ቀላያትም ይሰንጠቁ አለማመን ይራቅ…»ቅዳሴ እግዚእ እንላለን ጸሎት በቅዳሴ መሳተፍ ስሙን መከታ ማድረግ ከዚህ መጎምዠት ያላቅቀናል
2.ማቴሪያሊዝም(በቁስ አካል ብቻ መደስት)
የሰው ልጅ በሩካቤ ሥጋ የተለየ ደስታን የሚያገኝ ይመስለዋል ይህ ግን በቅጽበት ወደ ባዶነት ና ድብርት ይቀየርበታል ይህም ሩካቤ ሥጋን ከእውነተኛ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ፍቅር ስለገነጠሉት ነው ይህም ከቅዱስ ጋብቻ ውጭ ያጣጥመው ዘንድ ስለሞከሩ ነው
የብዙ ክርስቲያን ወጣቶች ችግር በጌታ የሆነ የንጽሕና ህይወትን ለመኖር አለመፈለግ ነው የሥጋ ህይወታቸው አድካሚ እንደሆነ የህይወትን እውነተኛ ትርጉም እንደሚያዛባ ቢያውቁ ኖሮ መንፈሳዊ ህይወትን ጥልቅ በደስታዎች የተሞላ እውነተኛ ህይወት እንደሆነ ይረዱ ነበር
የሰው ልጅ በምድራዊ እና ደስታ ብቻ መጠመዱ የሰው ልጅን የሥጋ ትኩረት ብሎም በሚያየው ነገር የማያየውን እግዚአብሔርን ና ጸጋውን መለወጡን ያመለክተናል ሰዎች አብዝተው ምድራዊ ነገር ብቻ ህይወትና ደስታ እንደሚሆናቸው ያስባሉ ይህ በቀዳማዊው አዳም የተጀመረ ነው ነገር ግን ዳግማዊ አዳም ክርስቶስ ወደ ምድር በመውረድ እኛን በመምሰል አዲስ ነገርን አሳይቶናል ይህም በሥጋ ሳይሆን በመንፈስ መመራትን በጸጋ እግዚአብሔር መኖርን ነው በቤተክርስቲያን ምስጢራትም በመሳተፍ ይህን እናሳያለን በገዛ ሜቶቻችን በምድራዊ ነገሮች ብቻ አንገደብም የምናየው ብቻ ደስታ ይሰጠናል አንልም መርካታችን በሥጋ ብቻ አይሆንም
ወዳጄ ሆይ በንጽሕና ለመኖር አስበህ ታውቃለህ ?ሰማያዊቷን ኢየሩሳሌምን ትናፍቃታለህ? እይታህን ቀስ ብለህ መርምር በሁሉም ፍጥረት ላይ እግዚአብሔር ይታይሃል? ይሄኔ እይታህ ፣መውጣት መውረድህ ሁሉ ንጹህ ይሆናል
3.ስንፍና
የሰው ልጅ በስንፍና ይኖር ዘንድ አይችልም በሕይወት ውስጥ ዓላማ ሳይዙ መጓዝ ህይወትን ባዶ ያደርጋታል ዓላማ ቢስነት ያለ ምክንያት መጓዝ እነዚህ ሁሉ በብዙዎች ውስጥ የሞሉ አሳቦች ናቸው ብዙዎች ህይወት ትመራቸዋለች ትርጉሙ ይርቅባቸዋል በመኖራቸው ምን እንደሚያገኙ አይገነዘቡም የሰውልጅ ዓላማውን ከሳተ ህይወቱ አሳዛኝ ይሆናል
ጌታ አዲስ የእይታ አድማስን ከፍቶልናል «እኔ እንደወደድኳችሁ እርስ በእርሳችሁ ተዋደዱ »ዮሐ13፡34 በማለት የሰው ልጅ የፍቅር መልዕክተኛ እንደሆነ አድርጎ ራሱን ሊያስብ ይገባል ይህን ጊዜ ራሱን ይረሳል ሌላውን ከራስ ወዳድነት በጸዳ ይወዳል
ስለ ሥጋዊ ስሜቶቻችን ብቻ አብዝታችሁ አታስቡ ወጣ በሉ በየመንገዱ ከመንጋው የጠፉ በጎችን ታገኛላችሁ ወዳጡት ፍቅርም ጋብዟቸው ወደ ቤተክርስቲያን ወደ ተቀደሰው ህብረትም ቀላቅሉአቸው
ወዳጄ ሆይ የህይወት ጣዕሟን በማጣትህ ብቻ ወደ ሥጋ ፈቃድ ለምን አዘነበልክ? አንተ እኮ በዓላማ ነው የተፈጠርከው ጌታን በሙሉ ልብህ ታገለግለዋለህ ?ወይስ ምድራዊ ህይወትን ብቻ ትመራለህ በመንፈስም በገንዘብም ድሃ የሆነውን ለምን ትረሳለህ
ህይወትህ ዓላማ አለው አጭር አይደለም ረዥም ነው የተፈጠርከው ከጌታ ጋር ለመኖር ነው
4.ጭንቀት
ወጣቶች ሁል ጊዜ በጭንቀት የተሞሉ ናቸው የወደፊቱን በማሰብ በቤተሰባዊ ማኅበራዊ ና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ምክንያት ዘወትር የሚጨነቁ ናቸው ስለዚህም ከእነዚህ ነገሮች ለማረፍ ወደ ኃጢአት ዓይናቸውን የሚያነሱ ጥቂቶች አይደሉም ያልሞከሯቸውን ነገሮች በመሞከር ደስታቸውን ይፈልጓታል
ስለዚህ በንጽህና ህይወት ውስጥ ያሉ ወጣቶች በምንም ሃሳብ ሊጨነቁ ስለየትኛውም ችግር ብቻ በማሰብ ጊዜአቸውን ሊያጠፉ አይገባም በአስተማማኙ በጌታ እጅ ውስጥ እንዳሉ ሊሰማቸው ይጋባል በልበ ሙልነት አባቴ የሙሉት እግዚአብሔር እንዳለ ሊያውቁ ይገባል እርሱ ፍላጎቶቻቸውን ሳይነግሩት የሚያውቅ የሚያስፈልጋቸውንም በትክክለኛው ጊዜ የሚቀርብ ነውና
ከጌታ ጋር በፀጥታ ስለ ቤተሰባዊ ፣ሥጋዊ ችግሮችህ በመነጋገር የውስጥህ ሰላም እንደሚመለስ እነግርሃለሁ ስለዚህ ስሜቶችህ ሊጎዱ አይገባም ተስፋ በመቁረጥ በኃጢአት ና ባልተገቡ ልማዶች መውደቅ የለብህም ተነሣ ጌታም ይደግፍሃል
እርሱ በሥጋ መነ ር ብቻ ነጻነት የሚመስለው ካለ ተሳስቷል እንደውም የሥጋ ምኞት የሥጋ ቀንበር የሰይጣን ደሞዝ ነው እውነተኛ ደስታም በውስጡ የለም ይልቁንም በኃጢአት የተሞላ ነው የሰው ልጅን በባዶ የሚያስርበው የህይወቱን ጣዕም የሚያበላሸው እርሱ ነው አንተ ግን ከጌታ ጋር እንዲህ በል «እኔ ግን ዘወትር ከአንተ ጋር ነኝ ቀኝ እጄንም ያዝኸኝ በአንተ ምክር መራኸኝ ከክብር ጋር ተቀበልኸኝ በሰማይ ያለኝ ምንድር ነው? በምድርስ ውስጥ ከአንተ ዘንድ ምን እሻለሁ»መዝ72፡24
ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን
No comments:
Post a Comment