Saturday, 16 September 2017

ንስሐ ክፍል አንድ



እግዚአብሔር አምላክ በጥንተ ተፈጥሮ አዳምን ሲፈጥረው በንጽሕና ከቅዱሳን መላእክት ጋር ስሙን በማመስገን ክብሩን እንዲወርስ ነበር፡፡ አዳም ባለመታዘዙ ምክንያት በተፈረደበት ፍርድ ከማዘን በቀር ሌላ ኅሊና አልነበረውም። ማዘኑም ከማዕርጌ ተዋረድኩ ከሥልጣኔም ተሻርኩ ብሎ ሳይሆን ፈጣሪዬን በደልኩ ብሎ የንስሐ ነው። እግዚአብሔርም አዳም በኃጢአቱ ምክንያት መጨነቁን አይቶ አዘነለት በይቅርታውና በቸርነቱ ብዛት ያድነውም ዘንድ ወደደ። ቅዱስ ኤፍሬም በሰኞ ውዳሴ ማርያም ላይ “ጌታ ልቡ ያዘነና የተከዘ አዳምን ነፃ ያወጣውና ወደ ቀድሞ ቦታው ይመልሰው ዘንድ ወደደ።” ያለው ለዚህ ነው። እርሱ ከአብ እና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር አንዲት በሆነች ፈቃዱ ሞት ባመጣው ጨለማ ተግዘው በሲኦል ምሽግነት ያሉ ነፍሳትን በመሆኑም  “ከሰማየ ሰማያት ወርጄ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ በመስቀል ላይ ተሰቅዬ ሞቼ ተነሥቼ አድንሃለሁ።” በማለት ቃል ኪዳን ሰጥቶታል። አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ሲፈጸምም በቀራንዮ በመልዕልተ መስቀል ሥጋውን በመቍረስ ደሙን በማፍሰስ ነፍሱንም አሳልፎ በመስጠት አድኖታል። በዕፀ ሕይወት ፈንታም የእርሱን ሥጋ ደም ተመግቦ የዘለዓለም ሕይወት ባለቤት እንዲሆን አድሎታል። (ዮሐ፡6፥53)።ይኸንን በተመለከተ ቅዱስ ኤፍሬም በሐሙስ ውዳሴ ማርያም ላይ “ስለ ሔዋን የገነት ደጅ ተዘጋ ዳግመኛም ስለ ድንግል ማርያም ተከፈተልን፤ ከዕፀ ሕይወት እንበላ ዘንድ አደለን ይኸውም እኛን ስለመውደድ መጥቶ ያዳነን የክርስቶስ ክቡር ሥጋው ክቡር ደሙ ነው።” ብሎአል።


ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “እውነትን በዓመፃ በሚከለክሉ ሰዎች በኃጢአተኝነታቸውና በዓመፃቸው ሁሉ ላይ የእግዚአብሔር ቍጣ ከሰማይ ይገለጣል፡፡” (ሮሜ 1፡18) እንዳለን ሰው ከእግዚአብሔር ቁጣ ያመልጥ ዘንድ ንስሐ አስፈላጊ ነው፡፡ ንስሐ በሚታይ አገልግሎት የማይታይ ፀጋ የሚሰጥበት ታላቅ ምሥጢር ነው፡፡ የሚታየው ተነሳሒው ጸጸትና ኑዛዜ የካህኑ ጸሎተ ንስሐ ሲሆን የማይታየው ፀጋ ደግሞ ተነሳሒው የሚያገኘው ሥርየተ ኃጢአት ነው፡፡ ንስሐ በየዕለቱ ከሚደረገው ጸሎት ውስጥ አንዱ ክፍል ነው፡፡ ሰው ኹሉ በጸሎት ውስጥ ስለኃጢአቱ ሥርየት ስለበደሉ ይቅርታ በመጠየቅ ፈጣሪውን መለመን ይገባዋልና፡፡ ንስሐ በጸሎት ሕይወታችን ውስጥ ታላቅ ሥፍራ አለው፡፡
ሰው ኹሉ ፍጹም አይደለምና ሲበድል በየዕለቱ ደግሞ ራሱን ለንስሐ ማዘጋጀት ይገባዋል፡፡ የቆሸሸ ልብስ በውሃ ሲያጥቡት እንደሚነጻ ሰውም እንዲሁ በኃጢያት ያደፈው ሕይወቱን በንስሐ ይጸዳል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለን “ወይስ የእግዚአብሔር ቸርነት ወደ ንስሐ እንዲመራህ ሳታውቅ የቸርነቱንና የመቻሉን የትዕግሥቱንም ባለጠግነት ትንቃለህን? ነገር ግን እንደ ጥንካሬህና ንስሐ እንደማይገባ ልብህ የእግዚአብሔር ቅን ፍርድ በሚገለጥበት በቍጣ ቀን ቍጣን በራስህ ላይ ታከማቻለህ።” (ሮሜ 2፡5) እንዳለ ሰው ቆሽሾ ከታጠበ በኋላ ዳግመኛ እንዳይቆሽሽ እንደሚጠነቀቅ ኹሉ እንዲሁ በንስሐ ከእግዚአብሔር ጋር ከተታረቅን በኋላ ወደ ኃጢአት እንዳይገባ ይጠነቀቅ ዘንድ ይገባዋል፡፡ ከቆሸሸም በፍጥነት እንደሚታጠብ ኹሉ እንዲሁ በኃጢያት ቢቆሽሽ በንስሐ ይታጠብ ዘንድ መገስገስ ይገባዋል፡፡




ኃጢአት ምንድን ነው?
ኃጢያት በእግዚአብሔር ላይ ማመጽ
መጽሐፍ ስለዚህ ነገር ሲናገር ‹‹አንተን ብቻ በደልኩ በፊትህም ክፋትን አደረኩ›› እንዲል መዝ 50፥4
ኃጢያት መሥራት ሀልዎተ እግዚአብሔርን መዘንጋት ነው፡፡
ኃጢያት ሀልዎተ እግዚአብሔርን መካድ ነው ማለታችን እንደሰነፍ ሰው እግዚአብሔር የለም እንደሚለው ሳይሆን እግዚአብሔር አያየኝም ብሎ በእግዚአብሔር ፊት ኃጢአትን ማድረግ ሀልዎቱን እንደመካድ ስለሆነ ነው፡፡ እንደ ዮሴፍ ያለ ጻድቅ ሰው ግን ‹‹በእግዚአብሔር ፊት እንዴት ኃጢያት እሰራለሁ?›› ይላል(ዘፍ 39፥9)
ኃጢያት መሥራት ማመጽ (ሕገ ወጥ መሆን) ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ በመልእክቱ እንዳለን ‹‹ኃጢያት የሚያደርግ ሁሉ አመጻን ደግሞ ያደርጋል፡፡›› እንዲል አመጻን ማድረግ ነው፡፡(1ኛ ዮሐ 3፥9)  ይሁዳም ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው መልእክት አስቀምጧል፡፡ “ከአዳም ጀምሮ ሰባተኛ የሆነ ሄኖክ፦ እነሆ፥ ጌታ በሁሉ ላይ እንዲፈርድ፥ በኃጢአተኝነትም ስላደረጉት ስለ ኃጢአተኛ ሥራቸው ሁሉ ዓመፀኞችም ኃጢአተኞች በእርሱ ላይ ስለ ተናገሩ ስለ ጭከና ነገር ሁሉ ኃጢአተኞችን ሁሉ እንዲወቅስ ከአእላፋት ቅዱሳኑ ጋር መጥቶአል ብሎ ለእነዚህ ደግሞ ትንቢት ተናገረ።” (ይሁዳ 1፥14-15)
ኃጢያት መሥራት የእግዚአብሔር ጠላት መሆን ነው፡፡  ቅዱስ ያዕቆብ በመልክእቱ እንዳለን ‹‹ዓለምን መውደድ ለእግዚአብሔር ጥል እንዲሆን አታወቁምን?›› (ያዕ. 4፥4) ከእግዚአብሔር የተወለደ ኃጢያት አያደርግም እንዲል ቅዱስ ዮሐንስ ኃጢአትን ማድረግ የእግዚአብሔርን ልጅነት ያሳጣል (1ኛ ዮሐ 3፥9)

ንስሐስ ምንድን ነው?
ንስሐ ሐዘን ጸጸት ቁጭት ምላሽ ቅጣት ማለት ነው፡፡ ንስሐ አንድ ሰው ዳግመኛ የተቆጨበትን ኃጢያት መልሶ ላለማድረግ የሚወስነው ቁርጥ ውሳኔ ነው፡፡
ንስሐ ወደ እግዚአብሔር መመለስ ነው፡፡(ሉቃ 15፥18-20)
ንስሐ ከእግዚአብሔር ጋር መታረቅ ነው፡፡(2ኛ ጢሞ 5፥20)
ንስሐ ከኃጢያት እንቅልፍ መንቃት ነው፡፡(ሮሜ 13፥11)
ንስሐ ስለፍቅረ እግዚአብሔር ስለቅድስና ብሎ ኃጢያትን መተው ነው፡፡
ንስሐ ጊዜያዊ ስሜት ፍጹም የሕይወት ለውጥ ነው፡፡(ሮሜ 12፥2)
የንስሐ ጥቅም
ያለንስሐ ድኅነት የለም፡፡ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹ንስሐ ባትገቡ ኹላችሁ እንዲሁ ትጠፋላችሁ›› ብሏል (ሉቃ 13፥3) ‹‹እንኪያስ እግዚአብሔር ለአእዛብ ደግሞ ለሕይወት የሚሆን ንስሐ ሰጣቸው››(ሐዋ 11፥18) ‹‹በኃጢያታችን ብንናዘዝ ኃጢያታችንን ይቅር ሊለን ከአምጻም ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው፡፡››ይላል (1ኛ ዮሐ 1፥7-9) ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም ‹‹ንስሐ ግቡ ኃጢያታችኹም ይሰረይ ዘንድ›› ብሎናልና (ሐዋ 2፥38) ስለዚህም ንስሐ ከጥፋት ለመዳን የኃጢአት ሥርየት አግኝቶ እግዚአብሔርን ለመምሰል አስፈላጊ ነው፡፡
የንስሐ  ጥሪ
እግዚአብሔር ወደ ንስሐ እንድንመለስ የሚቀርብልን ጥሪ ለእኛ ያለው ጥልቅ ፍቅር የሚገልጥ ነው፡፡ እስራኤልን በብዙ የብሉይ መጽሕፍት ተጽፎ እንደምናነበው በደል በድለው ከአምላካቸው በሸሹ ሰዓት ወደ እርሱ ይመለሱ ዘንድ በነቢያቱ ጥሪ ያቀርብ ነበር ይህም ጥልቅ ፍቅር ነው፡፡ ‹‹ወደ እኔ ተመለሱ እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር›› ሚል 3፥7 ‹‹ንስሐ ግቡ ተመለሱ ፊታችሁንም ከእርኩሰታችሁ መልሱ›› (ሕዝ 14፥6) እንዲሁ ልባችሁን እንጂ ልብሳችሁን አትቅደዱ አምላካችን እግዚአብሔር ቸርና መሐሪ ቁጣው የዘገየ ምሕረቱም የበዛ ከክፋትም ኹሉ የተጸጸተ ነውና ወደ እርሱ ተመለሱ›› ኢዩ 2፥12-13 ብሎ ዘወትር ጥሪ ያቀርብ እብደነበር ዛሬም በኃጢያት ለምንቆሽሽ ለእኛ ዘወትር ተመለሱና በሕይወት ኑሩ ይለናል፡፡
በክፍል ኹለት ትምህርታችን የንስሐ መሰናክሎች ንስሐ እንዴት እንደምንገባ እንመለከታለን፡፡
ይቆየን

ስብሐት ለእግዚአብሔር


No comments:

Post a Comment