Thursday, 12 October 2017

የንስሐ ሕይወት ክፍል አራት(የመጨረሻ ክፍል)


ንስሐ የገባ ሰው ዳግም በኃጢያት እንዳይወድቅ ሊያደርጋቸው የሚገቡ ጥንቃቄዎች

ምንም እንኳን ንስሐ የሚደገም ምሥጢር ቢሆንም ወደፊትም ለምንሰራቸው ኃጢያቶች ንስሐ የሚገባ ቢሆንም ተነሳሒው በሕይወቱ አምላኩን ያከበረ ስለሆነ ኃጢያጥ በሕይወቱ ላይ ያደረሰውን ተረድቶ ከኃጢያት መጠንቀቅ መራቅ ብሎም ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለው መሸሽ ይገባዋል፡፡(1ኛ ቆሮ 6፥18 2ኛ ጢሞ 2፥22) ስለዚህም ተነሳሒው የሚከተሉትን ጥንቃቄዎች ያደርግ ዘንድ ይገባዋል፡፡

ለኃጢያት ሌላ ስም አለመስጠት

ኃጢያት እንደኃጢያት አለመቁጠር የዘመናችን ትልቁ በሽታ ነው፡፡ ኃጢያትን በሌላ ካባ ማሳመርና ማስጌጥ ለሰው ልጆች ውድቀት ዋንኛ መነሻ ነው፡፡ አንዳንዶችም የሰሩትን ኃጢያት ለመሸፈንና ሕሊናቸው እንዳይወቅሳቸው ስለንስሐ   መስማት አይፈልጉም፡፡ ጥንተ ጠላታችን ዲያቢሎስ አባታችን አዳምን ና እናታችን ሔዋንን ሲያስት ዕጸ በለሱን ‹‹ዓይን ከፋች እውቀት ገላጭ›› ብሎ ሲያሜ ሰጥቶ ለኃጢያት ቦታ እንዲኖራቸው አድርጎል፡፡(ዘፍ 3፥5) በዓለማችን የምናየውም ይህንን ነው፡፡ ተነሳሒው ግን ቀድሞ ንስሐ የገባ ኃጢያትን ጠልቶ ነውና ኃጢያት ለመሥራት መናፈቅ የለበትም፡፡

ክፉ ነገሮችን አለማወቅ

ጠቢቡ ሰሎሞን ‹‹የጥበብ መብዛት ትካዜ ያበዛልና ዕውቀትንም የሚጨምር ኃዘንን ይጨምራል፡፡›› (መክ 1፥18) እንዳለ ስለኃጢያት ማወቅ ወደ ሞት ያመራናል፡፡ ሔዋን አምላክ የመሆንን ክፉ ዕውቀት ባወቀች ጊዜ ዕጹን ትበላ ዘንድ ምኞት በውስጧ ተቀሰቀሰ፡፡ በሕገ ተፈጥሮ ንጹሕ የሆነው ሕጻን ኃጢያት መሥራት የሚጀምረው በአካባቢው ያሉ ሰዎችን በማየት ነው፡፡ ኃጢያትን ማወቅ ለመሥራት ይጋብዛልና ከዚህ መጠበቅ ይኖርብናል፡፡ አክአብ የናቡቴን እርሻ ቦታ መቀማት ብሎም መግደል የተማረው ከክፉ መካሪው ሚስቱ ኤልዛቤል ነው፡፡(1ኛ ነገ 20፥9) አምኖን እኅቱ ትዕማርን ከክብር ያሳነሳት በአሚናዳብ ክፉ ምክር ነው(2ኛ ሳሙ 13፥5) ሮብዓም ክፉ ነገር የተማረው ከገዛ አብሮ አደጎቹ ነው፡፡(1ኛ ነገ 12፥10) ስለዚህም ተነሳሒው ዳግመኛ ወደ ኃጢያት እንዳያመራ ክፉ ነገሮችን መሸሽ ማረቅ ከእውቀታቸውም ራሱን መከልከል ይገባዋል፡፡

ንስሐን ለመሞከር አለመጋበዝ

በቀልድ በዋዛ ፈዛዛ የሚጀመረው ቀላል ኃጢያት ‹‹ንዑስ ቀበሮ›› ሆኖ እንድንጠፋ ምክንያት ሊሆነን ይችላል፡፡ መጽሐፍ እንዳለን ‹‹የወይናችንን ቦታ የሚያጠፉትን ጥቃቅን ቀበሮዎች አጥምዳችሁ ያዙልን፡፡›› (መኃ 2፥15) ተነሳሒው ቀላሉ ኃጢያት ወደ ሞት እንዲወስደው ስለሚያምን ይህንን ከማድረግ ራሱን መጠበቅ አለበት የኃጢያት ቀላል የለውምና፡፡ ይሁዳ ጌታን ለመሸጥ ያባቃው አስቀድሞ ለድሆች ከሚሰጠው ገንዘብ ይሰርቅ ስለነበረ ነው፡(ዮሐ 12፥6) ይህንንም የሚያስተውል ሰው ጥቃቅኑን ቀድሞ ማቆም ይገባዋል፡፡

ከክፉ ባንጀራ መራቅ

ተነሳሒው ሌሎች በእርሱ እንዲሳቡ አስተማሪ እንጂ ሌሎችን እርሱን እንዲስቡት መሆን የለበትም፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋል›› እንዳለ(1ኛ ቆሮ 15፥33) ጌታም ‹‹ወደ ሳምራዊያን ከተማ አትግቡ›› (ማቴ 10፥5) እንዳለ ከሳምራዊያን ክፉ ግብር ተሳታፊ እንዳንሆን ጥንቃቄ ማድረግ ይገባናል፡፡ ቅዱስ ዳዊት እንዳለ ‹‹ከንጹሕ ጋር ንጹሕ ሆነህ ትገኛለህ ከጠማማ ጋር ጠማማ ሆነህ ትገኛለህ››(መዝ 17፥26) ስለዚህም በክፉዎች መንገድ አለመሄድ በኃጢያቶች መንገድ አለመቆም ይገባል የክፉዎችና የኃጢያተኞች መንገድ ትጠፋለችና፡(መዝ 1፥1-)
ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ መልእክቱ  “ለቀደመውም ዓለም ሳይራራ ከሌሎች ሰባት ጋር ጽድቅን የሚሰብከውን ኖኅን አድኖ በኃጢአተኞች ዓለም ላይ የጥፋትን ውኃ ካወረደ፥ “ኃጢአትንም ያደርጉ ዘንድ ላሉት ምሳሌ አድርጎ ከተማዎችን ሰዶምንና ገሞራን አመድ እስኪሆኑ ድረስ አቃጥሎና ገልብጦ ከፈረደባቸው ጻድቅ ሎጥም በመካከላቸው ሲኖር እያየና እየሰማ ዕለት ዕለት በዓመፀኛ ሥራቸው ጻድቅ ነፍሱን አስጨንቆ ነበርና በዓመፀኞች ሴሰኛ ኑሮ የተገፋውን ያን ጻድቅ ካዳነ ከክፉ አድራጊዎቻችን ግብር ሳንቀላቀል ነፍሳችን በእነሱ ሥራ እንዳይቆሽሽ ምንጨነቅ ከሆነ ከዓመፀኞች ሴሰኛ ኑሮ የተገፋውን ሰዎች ያድን ዘንድ ዛሬም የታመነ ነው፡፡

ሰይጣንን መቃወም

ቅዱስ ያዕቆብ ‹‹ዲያቢሎስን ተቃወሙት ከእናንተ ይሸሻል›› (ያዕ 4፥7) እንዳለ የዲያቢሎስ የሆነውን ሥራን መቃወም ይገባል፡፡ ሰይጣን ጌታን በሦስቱ ኃጢያቶች እንደፈተነ ጌታም ዲያቢሎስን ድል አድርጎ ‹‹ሑር እምኔየ›› ከእኔ ሂድ እንዳለ  እንዲሁ ዲያቢሎስንና የዓለምን ኃጢያት ከእኔ ራቅ ሂድ እንለው ዘንድ ይገባናል፡፡

ማጠቃለያ

ቅዱስ ጳውሎስ  “እውነትን በዓመፃ በሚከለክሉ ሰዎች በኃጢአተኝነታቸውና በዓመፃቸው ሁሉ ላይ የእግዚአብሔር ቍጣ ከሰማይ ይገለጣል፡፡” (ሮሜ 1፡18) እንዳለ የእግዚአብሔር ቁጣ ከመገለጡ በፊት ኹላችን ኃጢያት ከመሥራት መታቀብ ወደ ንስሐም መቅረብ ይገባናል፡፡ ለዚህም የእግዚአብሔር ቸርነት የእመቤታችን ምልጃ የቅዱሳኑ ጸሎት ይርዳን፡፡
ስብሐት ለእግዚአብሔር

የንስሐ ሕይወት ክፍል ሦስት


በንስሐ የሚገኙ ለውጦች

በሕይወት  ውስጥ መንፈሳዊ ለውጥ ከሌለ የክርስትና ሕይወት ጣዕም ያጣል፡፡ ይህንን መንፈሳዊ ለውጥ ለማምጣት ታዲያ ንስሐ አስፈላጊ ነው፡፡ ንስሐ ማለት መናዘዝን ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን መቀበል ብቻ ማለት አይደለም፡፡ ኃጢያትን በፍጹም በመተው በተቀደሰ የሕይወት  ጎዳና መመላለስ እንጂ፡፡ ንስሐ አንድ ወቅት ከክርስቶስ እግር በታች ራስን መጣል ብቻ ሳይሆን በመንፈሳዊ ሕይወት መኖርና የእግዚአብሔርን ትእዛዛት በመፈጸም ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ‹‹በእርሱ የሚኖር ኹሉ ኃጢያትን አያደርግም፡፡ ኃጢያትን የሚያደርግ ኹሉ አላየውም አላወቀውም››(1 ኛ ዮሐ 3፥6) እንዳለን ለአንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ኹሌም ብሆን በእርሱ የምንኖር ኹላችን ኃጢያትን ማድረግ የለብንም፡፡



በንስሐ የተመለሰ ሰው ጠባያት

ትኁት ሰብእና  አለው (ሉቃ 14፥10)

ትዕቢት መታጀርን አያውቅም፡፡ በጉባኤ እንኳን ዝቅ ያለ ሥፍራ ላይ መቀመጥን ይመርጣል፡፡ 

ትእግስተኛ ነው

ስለሰዎች ኃጢያት ሲሰማ ወይም ስህተትን ሲያይ ሲሰድቡት ወይም ከክብሩ ዝቅ ቢያደርጉት እርሱም ያንን በደል ከዚህ በፊት ስለሰራ ይታገሳል፡፡ የእርሱ ሐሳብ ብቻ ተቀባይነት እንዲኖረው አይሞክርም ከእኔ ከኃጥኡ አእምሮ ምን መልካም ነገር ይገኛል ይላልና ራሱንም በትኅትና ዝቅ ያደርጋል፡፡

ምሕረትን ያውቃል   (ማቴ 6፥15 1ኛ ሳሙ 26፥11)

ሰዎች ክፉ ነገር ቢያደርጉት ክፋትን አይመልስም  ቢሰድቡት አይራገምም እርሱ ይቅር ካላለ ኃጢያቱ እንደሚያዝበት ያውቃል፡፡ የዘወትር ጸሎቱንም በተግባር በይቅር ባይነቱ ይተገብረዋል፡፡ 

አርምሞን ገንዘብ ያደርጋል

ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ ‹‹እኔ ሌሎች ሲናገሩ ባደምጥ ከንግግራቸውም መማር ይሻለኛል›› እንዳለ (ያዕ 1፥19) ንስሐ የገባ ከእግዚአብሔር ጋር እርቅ የፈጸመ ንግግሩ የማይሰማ በአርምሞ የተሞላ ነው፡፡

የመንፈስ ደኃ ይሆናል

በመንፈስ ድሆች(ነዳያነ መንፈስ) የሆኑ ማለት የዋሐን ትሑት የሆኑ ማለት ነው፡፡ እንዲህ ያሉ ሰዎች ራሳቸውን ችሎታ እንዳላቸው አድርገው አይቆጥሩትም፡፡ በራሳቸው ዘር፣ ጠባይ፣ ተፈጥሮ፣ ሀብት፣ አቅምና ችሎታ ተስፋ አያደርጉም፡፡
ነዳያን በመንፈስ ያልተማሩ ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን ማንነታቸውን አውቀው በፈቃዳቸው ሁሉን የተዉ ማለት ነው፡፡ ነዲያን በመንፈስ በእግዚአብሔር ፊት የተሰበረና የተዋረደ ልብ ይኖራቸዋል፡፡ ይህን የሚያደርጉት ከእነሱ እጅግ የሚበልጥ ሁሉን የሚያውቅ አምላክ መኖሩን በማሰብ ነው፡፡
አንድ ሰው ራሱን ዝቅ ካላደረገ የትኅትናም ሥራ ካልሰራ አምላካዊ ጸጋን አያገኝም እርሱም አይፈልገውም፤ ሁሉ ያለው ይመሰለዋልና፡፡ ክርስቲያን የሆኑ ሁሉ ግን ይህን የትሩፋት ሥራ መንገድ መከተል ራስን ከመውደድ መራቅ እያለውም እንደሌለው ሆኖ መታየት ተገቢው ነው፡፡
መኮንነ ተሰሎንቄ ዮሐንስ አፈ ወርቅን እንደጠየቀው ብፁዓን ከበቁ በኋላ ነዳያነ አእምሮ መሆናቸው እንደምንድነው? አለው ዮሐንስም ‹‹አንተ በሃገርህ እንደምን ትኖራለህ›› አለው ‹‹ከሁሉ በላይ ነኝ›› አለው እልፍ ብለህ ‹‹በቂሳርያሳ›› ‹‹የምበልጣቸውም የሚተካከሉኝም አሉ›› አለው ዝቅ እያለ ሄደ፡፡ ‹‹አንጾክያስ አለው›› ‹‹የሚያውቀኝ የለም›› አለው ቅዱሳንም በአእምሮ ነዳይ የሆኑት ከበላላቸው ያለውን ፈጣሬ መጋቤ ዓለማትን እያዮ ራሳቸውን ዝቅ ያደርጋሉ እንጂ አይታበዩም፡፡ በምግባር በሃይማኖት በንስሐ ድሆች ነን ብለው የሚያዝኑ የሚተክዙ ንዑዳን ክቡራን ናቸው፡፡
የምንመካበት ምንነታችን የእኛ አይደለም፡፡ የምንመካበትን ዕውቀት ሐብት  ጉልበት ሥልጣን የሰጠን አምላካችን ነው፡፡ ነዳያነ መንፈስ ይህንን መመልከት የሚችሉ ናቸው፡፡ የእነርሱን ዕውቀት ከአምላክ ፍጹም እውቀት ጋር እያነጻጸሩ ኢምንትና ትንሽ መሆኑንን ይገነዘባሉ፡፡ ሐብታቸውን ጉልበታቸውንም ከሁሉ ኃያል ሁሉ በእጁ ከሆነው አምላክ ጋር እያነጻጸሩ ራሳቸውን በጌታ ፊት ያዋርዳሉ፡፡ መንግስቱን የሚርሱ እንደነዚህ ያሉት ናቸው፡፡ መመካታቸውን በአምላክ ላይ ያደረጉ በራሳቸው የማይመኩ የመንግስቱ ወራሾች ናቸው፡፡
የመንፈስ ደኃ መሆን ኹሉ እያለው እንደሌለው መሆን ማለት ነው፡፡ ጥበበኛ ሆኖ ሳለ ባለፀጋ ሆኖ ሳለ ደኃ መሆን ራስን በትኅትና መስበር ነው፡፡ ሰው በሌለው ነገር የሚኮራ ፍጡር ነው አላዋቂው አዋቂ ተብሎ ይመሰገን ዘንድ ይወዳል ንስሐ የገባ ሰው ግን እንኳን በሌለው ባለው ይወደስ ዘንድ አይሻም፡፡ ‹‹በሰማይና ምድር የተዋረዱትን የሚያይ ከአለቆች ጋር ከሕዝቡም አለቆች ጋር ያኖረው ዘንድ ችግረኛውን ከመሬት የሚያነሳ ምስኪኑን ከትቢያ ከፍ ከፍ የሚያደርግ››(መዝ 112፥8) ትዕቢተኞችን በልባቸው ሐሳብ የሚበትን ትኁታኑን ከፍ የሚያደርግ ጌታን በማሰብ ኹሌም በትኅትና የሚኖር ነው፡፡(ሉቃ 1፥52)
በአጠቃላይ ተነሳሒው በሕይወቱ ፈጽም ለውጥ ያሳያል አስተሳሰቡ አስታያየቱ አነጋገሩ ኹሉ ይቀየራል፡፡ ሰዎች ከአንደበቱ ይልቅ በሕይወቱ ይሰበካሉ ሳይናገር ምግባሩ ሰዎችን ይለውጣል፡፡ በእርሱም ምክንያት ብዙዎች ወደ ንስሐ ይቀርባሉ፡፡
ስብሐት ለእግዚአብሔር

እስመ ውእቱ ኮከብ ብሩህ ዘቤተክርስቲያን


         በዲ/ን ፍሬው ለማ
«ገብረ መንፈስ ቅዱስ ሞተከ ታብዕል ኢትዮጵያ ለጴጥሮስ በዓለ መርሆ ወለጳውሎስ
ሐዋርያ ከመ ተዝካሮም ታብዕል ሮምያ»
ትርጉም
«ገብረ መንፈስቅዱስ ሆይ ኢትየጵያ ሞትህን ከፍ አድርጋ ታስባለች የሮም ሀገር የሐዋርያትን ጴጥሮስ ና ጳውሎስ በዓል ከፍ አድርጋ እንደምታከብር»

                መልክዐ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ

ከወይን ፍሬ ይልቅ የጣፈጠ ከሮማን አበባም ይልቅ ቡሩክ የሆነ የአንድ ተጋዳይ ምስጋናን
እንነግራችኋለን ይኸውም በሰነፎቹ ዘንድ የተናቀ በአዋቂዎች ግን ተቀባይነት ያለው በቅዱሳን ዘንድ የተወደደ ለርኩሳኑ የሚያስፈራቸው ነው ይህም ኮከብ ለቤተክርስቲያን ጳዝዮን የሚባል ዕንቁ ጸሎቱ እንደ ዕጣን የሚሸት የታመነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ነው።

ደብራችን ደብረ ብርሃናት (የብርሃናተ ዓለም ቅዱስ ጴጥሮስ ወጳውሉስ ቤተ ክርስቲያንን ለማለት ነው) ከምትዘክራቸው ከጌታ ምስክሮች አንዱ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ናቸው ልክ በመልክአቸው እንደተገለጸው ኢትዮጵያ ዝክራቸውን ዘወትር ወር በገባ በ፭ ከፍ አድርጋ ታከብራለች፡፡ምዕመናንም አቡዬ(አባቴ) ብለው በፍቅር ቃል ይጠሯቸዋል ከገድላቸውና ከመጽሐፍ ባገኘው ከፍ አድርገን የማግነናችን ሥራ መሠረት ከዚህ በኃላ እንዳስሳለን

† ትውልዳቸውና እድገታቸው


አባታችን አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ በገድላቸው ተጽፎ እንደምናነበው የተወለዱት በግብጽ ሀገር ልዩ ስሙ ንሂሳ በሚባል ቦታ ነው። አባታቸው ስምዖን እናታቸው አቅሌስያ ይባላሉ። አቅሌስያ ልጅ አጥታ 30 ዘመን እያለቀስቸ ኖራለች። የንጹሀንን ጸሎት የሚቀበል ጌታም ደም ግባቱ ያማረ ልጅ ሰጣት። ይህም በመልክአቸው ላይ «ስምዖን ወ አቅሌስያ ዘ ነበሩ በንሂሳ በኃጢአ ውሉድ በከዩ መጠነ አመታት ሠላሳ» ተብሎ ተገልጿል አባታችን መጋቢት 29 ተጸንሰው በታህሣሥ 29 ተወልዱ። በተወለዱበት ቀንም መልአኩ ገብርኤል በሰው አምሳል ተመስሎ የዚህ ህጻን ስም ገብረ መንፈስ ቅዱስ ይሁን ብሎ ተናገረ። በዚያን ቀንም ህጻኑ ከእናቱ ጭን ወርዶ ለ ቅድስት ሥላሴ ሶስት ጊዜ ሰገደ።ከሦስት ዓመት በኋላ መልአኩ በክንፉ ተሸክሞ ኖብ ወደሚባል ገዳም ወስዶ ህጻኑን አባ ዘመደብርሀን ለሚባሉ አባትሰጠው። ያም አባት ሕጻኑን በፍቅር በስርዓት ቅዱሳት መጻሕፍትን እያስተማረ አሳደገው፣ አባ ዘመደ ብርሃንም ሕጻን ገብረመንፈስ በትምህርቱ በትህትናው እግዚአብሔርን በመፍራቱ ታዛዥ መሆኑን በተመለከተ ጊዜ አቡነ አብርሃም ወደ ተባሉ ጳጳስ ወስዶ መዓረገ ዲቁናንም አሰጠው ።

ከዚያ በኋላ ፍጹም መናኝ በጸሎት ትጉህ ሆነው ሲያገኛቸው መንኩሰው የቅስና መዓረግ እንዲቀበሉ ሆኑ አቡነ ገብረ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ እንደ ሐዋርያት በመንፈስቅዱስ ተሞልተው ቅዱስ ወንጌልን እያስተማሩ በጾም በጸሎትና በስግደት እግዚአብሔርን እየለመኑ ብዙ ሕሙማንን ያድኑ ነበር።የጻድቁ አቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ ዝናቸው ቅድስናቸው በኢየሱስ ክርስቶስ ስም የሚያደርጉትን ተዓምራት በብዙ አገር ስለተሰማ ውዳሴ ከንቱ እንዳይሆንባቸው ወደ ጫካ ገቡ ከነምሮችና ከአንበሶች ጋር ተስማምተው መኖር ጀመሩ። 300 ዓመትም በታላቅ ተጋድሎ በግብጽ፣የመን ፣ በሱዳን ና በሌሎችም ሃገሮችም እያስተማሩ ከኖሩ በኋላ የእግዚአብሔር መልአክ ከቦታ ቦታ የሚጓጓዙበት የብርሀን ሰረገላ ሰጣቸው ወደ ኢትዮጵያም እንዲመጡ አዘዘዛቸው። ይህም በዘመነ ላሊበላ በ11ዐዐ ዓ.ም. በጥቅምት ወር በ ፭ተኛው ቀን ነው። አባታችንም 60 አንበሶች በፊቱ 60 ነምሮች በኃላው ሆነው ወደ ኢትዩጵያ መጣ ። በመጀመሪያ ታቦተ ጽዮን ወደ አለችበት ወደ አክሱም ሄደው ለሶስት ሳምንታት እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ሰነበቱ ከዚያም ንጉሥ ላሊበላ ከአለት ፈልፍሎ ወደ አሰራቸው አብያተ ክርስቲያናት ወደ ሮሐ ሄዱ ንጉሥ ላሊበላ ከእግዚአብሔር የተሰጣቸውን ሞገስና ግርማ እያደነቀ በክብር ተቀብሎ አስተናገዳቸው ከዚያም ንጉሱን ና ቦታውን ባርከው እግዚአብሔር ወደ ፈቀደላቸው ዝቋላ ለመሄድ ተነሱ በዚያም በከበረ በጌታችን ስም ተጋድሎን ፈጽመዋል

† እረፍቱ ለአቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ


ስለ ዕረፍታቸው በገድላቸው እንዲህ ተጽፏል ቀኑ መጋቢት 5 ዕለቱ ቅዳሜ ለእሑድ አጥቢያ ሰዓቱ ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት ሆኗል፤ አሁንም ህማሙን እየታገለ እያላበው በድካም ለፍጥረቱ ሁሉ ይለምናል፤ “አቤቱ ህዝብህን አድን ርስትህን ኢትዮጰያንም ባርክ” ይላል። ሕመም የጀመረው መጋቢት 3 ዓርብ ቀን ነው፤ መታመሙን የሰሙ እንደርሱ ቅዱሳን የሆኑት ዘርአ ቡሩክ፤ ፍሬ ቅዱስ፤ያዕቆብ፤ብንያምና ዮሴፍ እንዲሁምበወቅቱ የኢትዮጰያ ንጉስ የነበረው እንድርያስ ሊጠይቁት ተሰብስበዋል ወደ አጠገቡ መድረስ ግንአልተቻላቸውም አባታችን ገብረመንፈስ ቅዱስ የሚጋርደው እንጨት ዛፍ በሌለበት በርሃ እንደ አንበሳ ተኝቶ አዩት በላዩ ያረፈው የእግዚአብሔር ጸጋ ከፊቱ የሚወጣው ብርሃን ቀይ መልኩ ረዥም የራስ ጠጉሩ እንደ ነጭ ሐር የሚሆን ጽሕሙ አስደነቃቸው። ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት ሲሆን ከሰማይ ታላቅ ነጎድጓድ ድምጽ ተሰማ ጌታችን መላአክትን አስከትሎ ወደ አባታችን ወረደ፤ ከሰማይ ወደ ምድር ህብሩ አምሳያው ልዩ ልዩ የሆነ እንደ ፀሐይናእንደ ጨረቃ የሚያበራ እንደ ወንጭፍ ድንጋይ ይወረ ወር ነበር ከዚያ የነበሩ ሁሉ ፈሩ ወደ ኃላም ሸሹ ምድር ራደች ተራሮች ኮረብቶች ተናወጡ ብርቱ ጩኸት ንውጽውጽታ ሆነ። “ወዳጄ ገብረመንፈስ ቅዱስ ሰላም ላንተ ይሁን” እነሆ የማይታበል ቃል ኪዳን እገባልኃለው ስምህን የጠራ መታሰቢያህን ያደረገውን፤ እጣን ቋጥሮ ግብር ሰፍሮ መባ ይዞ ቤትህ የመጣውን እምርልኃለው አንተ ከገባህበት ገነት መንግስተ ሰማያት አገባዋለሁ አላቸው፤ አባታችንም “አቤቱ ጌታ ሆይ የኢትዮጰያን ህዝብ ማርልኝ” አሉት፤ እነሆ ምሬልኃለው አስራት በኩራት አድርጌም ሰጥቼሃለው። ከዚህ በኃላ ሰባቱ ሊቃነ መላዕክት የአባታችንን ነፍስ ሊቀበሉ ወረዱ በታላቅ ምስጋናም ወደ ሰማይ አሳረጉት ስጋውንም ይዘውት ሄዱ የት እንደተቀበረ ግን እስካሁን አይታወቅም አንዳንዶች በኢየሩሳሌም ነው ይላሉ፤ ሌላው በምድረ ከብድ ነው ይላል ግን እስካሁን ልክ እንደ ሊቀ ነብያት ሙሴ ስጋ የት እንደተቀበረ አይታወቅም። ገድሉ ትሩፋቱ ከሰማይ ከዋክብት ከምድር አሸዋ ይበዛል ኢትዮጰያን አብዝቶ ይወዳታል፤ ምድራዊ ምግብ አልተመገበም የእናቱን ጡት እንኳን አልጠባም፤ ልብስ፤ መጠለያ አልፈለገም፤ የክረምት ቁር የበጋ ሐሩር እየተፈራረቀበት በተጋድሎ 562 ዓመት ኖረ፤ በመጋቢት 5 ቀን ሩጫውን ጨረሰ።

† አቡነ ገብረ መንፈስቅዱስና የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን

የኢትዮጲያ ቤተክርስቲያን ታሪክ የጥቂቶች ታሪክ አይደለም የብዙ ቅዱሳን ታሪክ ነው        ብዙዎች የደም ዋጋ ከፍለውበታል ከነዚህ ዕንቁዎች አንዱ አባታችን አቡነ ገብረመንፈስቅዱስ ናቸው። አባታችን ለቤተክርስቲያንችን ካበረከቱት አስተዋፅዎች በጥቂቱ እንኳን ብንዘረዝር

ምንኩስናን በማስፋፋት
ኢትዮጵያ በ34 ዓ.ም ክርስትናን በ4ተኛው መ/ክ/ዘ ደግሞ ክህነትን በአባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን ተቀብላለች፡፡ የምንኩስና ሥርዓት ደግሞ በተሰዓቱ ቅዱሳን ወደ ኢትዮጲያ መጥቶአል፡፡ በኢትዮጵያ የምንኵስናና የገዳማት ታሪክ ውስጥ ከ3ኛው – 12ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ያለው ጊዜ በአብዛኛው ከውጭ በመጡ አበው ሥርዓተ ምንኵስና የተስፋፋበት ሲሆን ከ12ኛው-15ኛው ያለው ደግሞ ከመላ ኢትዮጵያ በተነሡ አበው ቅዱሳን ሥርዓተ ምንኵስናና የገዳማት ትክል ከሰሜን ወደ ምዕራብ፣ ምሥራቅና ደቡብ የተስፋፋበት ወቅት ነው ከውጭ ከመጡት ቅዱሳንም አበታችን ተጠቃች ናቸው ፡፡

አባታችን አቡነ ገብረ መንፈስቅዱስ እግዚአብሔር በሰጣቸው የ562 ዓመት ዕድሜ አያሌ ገዳማትን የገደሙ ሲሆን በተለይም የዝቋላና የምድረ ከብድ ገዳማት እስከዛሬ የፀኑ ናቸው፡፡ ብዙ ደቀመዛሙርትንም አፍርተዋል፡፡

ወንጌልን በማስፋፋት
ክቡር አባታችን አቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ በኢትዮጲያ ምድር በየመንና በምድረ ሱዳን ሳይቀር እየተዘዋወሩ ቅዱስ ወንጌልን አስተምረዋል ጠንቋይ ቃልቻ በልዩ ልዩ አምልኮት የነበሩትን ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር መልሰዋል የታመሙትን በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም አድነዋል ለዚህም ማሳያ የሚሆኑን በአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ስም በተለያዩ የሃገራችን ክፍላት የታነጹት አብያተ ክርስቲያን ናቸው ዝክራቸውንም ሁሉም ኢትዮጵያውያን ያከብራሉ ለዚህም ነው አባቶች በጥቅምት ፭ ማኅሌት «ዝንቱሰ ሐዋርያ ገብረ ሕይወት ዘተፈነወ ውስተ ምድርነ ከመ ይክስት ብርሃነ ይፈውስ ዱያነ» ብለው የሚያመሰግኑት

ጸሎታቸውና በረከታቸው ከ እኛ ጋር ይሁን አሜን

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Sunday, 8 October 2017

አገልግሎታችንን ከየት እንጀምር?


                    

ጌታችን አምላካችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከዕርገቱ በፊት ሐዋርያትን መንፈስ ቅዱስን እስኪቀበሉ ድረስ ከኢየሩሳሌም እንዳይወጡ እና የተስፋውን ቃል እንዲጠብ አዟቸው ነበር (ሐዋ.1፡4) ግና መንፈስ ቅዱስን ከተቀበላችሁ በኋላ በኢየሩሳሌም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድርም ዳር ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ አለ (ሐዋ.1፡8) እነዚህ ቃላት ከዕርገት በፊት ጌታችን ለመጨረሻ ጊዜ ለሐዋርያት ያዘዛቸው ናቸው፡፡ እስኪ አእዚህ ጋር እንምና ጌታችን የተናገራቸውን እያንዳንዱን ቃላት እናስተውል፤ እነዚህ ለየትኛውም አገልጋይ መርሕ ሊሆኑት ይገባል፡፡ የጌታችን ቃላት  ሳይታሰቡ የተነገሩ እንዳልሆኑ መቼም አንዘነጋውም፡፡ መንፈስ ቅዱስን እስኪቀበሉ  በኢየሩሳሌም ከዛ በይሁዳ እንዲሁም በሰማርያ በመጨረሻም በዓለም ሁሉ እንዲሰብኩ ተናገረ፡፡

በኢየሩሳሌም

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት ኢየሩሳሌምን ለቅቀው እንዳይወጡና ምስክሩንም በዚያ እንዲጠብቁ ሲያዝዛቸው እናነባለን፡፡ ኢየሩሳሌም ሲል ምን ማለቱ ነው የመጀመርያ ምስክር የምንሆንላት እርሷ ማን ናት ኢየሩሳሌም  የታላቁ ንጉስ ከተማ ናት፤ እንዲሁም የመመስገኛ መቅደሱ የሚገኘባት፡፡ አዎ! ኢየሩሳሌም የጌታችን ማደሪያ የሆነች፤ ቅ/ጳውሎስ  በቤተ መቅደስ እያለ የሚጠራት (1ቆሮ.3፡16) ሊቁ አውግስጢኖስም አንተን እስክታገኝ ድረስ እንዳታርፍ አደረግካት ያላት ልባችን  ናት፡፡ ኢየሩሳሌም ፤ የጌታ የግሉ መኖርያ፡፡ በኢየሩሳሌም ምስክር ትሆኑኛላችሁ ማለት በግል ሕይወታችን እና በራሳችን ምስክር መሆን ማለት ነው፡፡
ብዙዎች ይህንን ቅደም ተከተል እናዛባዋለን፤ ወደ ሰማርያና ወደ ዓለም ዳርቻ እንጓዛለን፡፡በዚህም ብዙ ስህተቶች ይከተሉናል፡፡ የኛ ጌታ ያዘዘን ግን መጀመርያ በኢየሩሳሌም ምስክሮቹ እንድንሆን ነው፡፡ ከኢየሩሳሌም ጥሩ ዜና እንደተገኘ ሁሉ ከእኛም የግል ሕይወት ለሌሎች የሚተርፍ በረከት ይወጣል፡፡
ኢየሩሳሌም የይሁዳ ማዕከል ፣ የቤተ መቅደስ መገኛ መስዋዕቱ የሚቀርብባት ነበረች፡፡ ይህች ብ አይሁዶች ከተለያዩ ሀገራት የምትስብ አእና እረፍትም የምትሰጥ ነበረች፡፡ ልክ እንደዚሁ ኢየሩሳሌም ልባችን፤ መንፈሳዊ ሕይወታችን በብዙ ሰዎች ትታያለች፡፡ በዚህም በአንተ ሰማያዊው አምላክን ያመሰግናሉ፡፡ ስለዚ አንተ የእግዚአብሔር አገልጋይ ሆይ ከውስጠኛው ልብህ (ከኢየሩሳሌም) ምስጋናን መሥዋዕት አድርገህ አቅርብ፡፡
ግን ለምንድን ነው ከኢየሩሳሌም የምንጀምረው ይህች ለጌታችን ምስክር የምንሆንባት ቅርብ ከተማ ናት፡፡ በዚህ በጎ ትሩፋትን ከሰራን ቀደ ውጪ ለመውጣት የበቃን ነን ማለት ነው፤ ምክንያቱም የእግዚአብሔር ኃይል የምንቀበለው ከዚህ ነውና፡፡ ጌታችን ሐዋርያትን የመንፈስ ቅዱስን ኃይል እስኪቀበሉ ድረስ ከኢየሩሳሌም እንዳይወጡ አዟቸዋል፡፡እግዚአብሔር ሁልጊዜ አገልግሎታችን በመንፈስ ቅዱስ ኃይል እንዲከወን ይፈልጋል፤ በዚህም እርሱ ይመሰገናልና፡፡ በራሳችን ጥበብና አቅም ለማገልገል ስንሞክር ስንት ጊዜ በደልን ይሆን ይህ ኃይል ለሐዋርያት የተሰጣቸው በሰገነቱ ላይ (ከምድር ቤት በላይ) ሆነው የአብን የተስፋ ቃል እየጠበቁ በአንድ ልብ ሆነው ሲጸልዩ   ፡ መስኮትና በራቸውንም ዘግተው ስለነበር ነው፡፡(ሐዋ.1፡13) አዎ! በከፍታው ላይ ካልወጣን በስተቀር የመንፈስ ቅዱስን ኃይል መቀበል አይቻለንም፡፡ ይህም ከምድራዊ አስተሳሰብ ከፍ ማለት ፣የነፍስን በርና መስኮት (የስሜት ሕዋሳት) በመዝጋት የአምላካችን ሥራና እና እርዳታ መሻትን ያሳየናል፡፡ በዚህ መንፈሳዊ ሰገነት ላይ ለሐዋርያት ደስታንና ሰላምን ሊሰጣቸው የተገለጠ አምላክ ለእኛም እንዲሁ ይገለጣል፡፡ በዚህ መንፈሳዊ ኃይል ቅ/ጴጥሮስ በአንዲት ደካማ ሴት ፊት የካደውን ኢየሱስ ክርስቶስን ፡ በብዙ ሺ ሰዎች ፊት መሰከረ፤ እኛም በዚህ መንፈሳዊ ኃይል ብቻ አምላካችንን ማገልገል እና በየትኛውም ስፍራ መመስከር ይቻለናል፡፡

በይሁዳ

አይሁዶች የእግዚአብሔር ሕዝቦች የተባሉ፣ ትንቢት የተነገረላቸው፣ እርሱም በሥጋ የተገለጠላቸው እነርሱ ግን ያልተቀበሉት ናቸው፡፡ በይሁዳ ምስክር መሆን ማለት፡ በቤት በቤተሰብ መሐል እንዲሁም በአካባቢያችን ስለ እርሱ መመስከርን ያሳየናል በአብዛኛው ማናችንም ይህን አገልግሎት እንረሳዋለን ፤ ኢያሱ ግን እኔና ቤቴ ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን ይላል፡፡ (ኢያሱ 24፡15)
ቅ/ጳውሎስ ደግሞ ነገር ግን ለእርሱ ስለ ሆኑት ይልቁንም ስለቤተሰቦቹ የማያስብ ማንም ቢሆን ሃይማኖትን የካደ ከማያምን ሰው ይልቅ የሚከፋ ነው፡፡  (1ጢሞ.5፡8) አዎ! ሐዋርያው እውነተኛ አገልጋይ የሚመዘነው  በቤቱ ባለው ማንነት ነው  እያለ ያስረግጥልናል፡፡ስለቤተሰቡ የማያስብ እንዴት ስለእግዚአብሔር እጨነቃለሁ ይላል በእውነት ይህስ የመታየት ፍላጎት አይመስላችሁም

በሰማርያ

ሰማርያ የአይሁድ እና የአህዛብ ድብልቅ የሆነች ከተማ ናት፡፡ በዚህ የሚደረግ አገልግሎት በሃይማኖት ባሉና በማያምኑ መካከል የሚኖርን ምስክርነት ያሳየና ፡፡ በእውነተኛ ማንነቱ እንዲሁም በቤተሰቡ መካከል የክስቶስን ፍቅር የገለጠ አገልጋይ ብዙ ዝግጅት እና ተጋድሎ ወደሚጠይቀው የመንፈሳዊ ትግል ሜዳ ይገባል፡፡ በሰማርያ ማገልገል ፍቅርን ፣ ምሕረትን እንዲሁም ስለሌሎች መጨነቅን ይፈልጋል፡፡ መንፈሳዊውን ኃይል ሳይቀበሉ በፊት ወደዚህች ከተማ የገቡ ፍቁረ እግዚእ ዮሐንስና ወንድሙ ያዕቆብ ከተማዋ የጌታን ቃል ስላልተቀበለች እሳት ከሰማይ ወርዶ ሰዎቹን እንዲበላቸው ለምነው ነበር ፤ እርሱም ይህን ስጋዊ መንፈስ በመቃወም እንዲህ አላቸው ምን ዓይነት መነፈስ እንደሆነላችሁ አታቁም የሰው ልጅ የሰውን ነፍስ ሊያድን እንጂ ሊያጠፋ አልመጣም አላቸው፡፡ (ሉዋ9፡51-56)
አገልጋይ በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ለማገልገል የተለየ መንፈሳዊ አቅም ያስፈልገዋል፡፡ ይህ ከባድ የአገልግሎት ሜዳ ቢሆንም አንድ በእምነት የሆነ ለብዙዎች እንደሚተርፉ በዮሐንስ ወንጌል ያለችው ሳምራዊቷ ሴት ጠንካራ ማስረጃችን ናት፡፡ (ዮሐ.4፡6)

እስከ ዓለም ዳርም ድረስ

የጌታችን ወንጌል በየቦታው ሲነገር ማየትን የመሰለ ምን ደስታ አለ፡፡መልካሙ የምሰራች የሚያወሩ እግሮቻቸው እንዴት ያማሩ ናቸው፡፡ (ሮሜ.10፡15) ምንም በማያውቃቸው ሰዎች መሐል፤ ወገኖቼ አሉልኝ በማይባልበት ስፍራ፣ በቋንቋ እና መልክ ፣ በባህልና በሥርዓት በማይተሳሰርባቸው አካባቢዎች የጌታን ቃል የፍቅርን ኃይል ተሸክሞ መጓዝ ምንኛ ያስደስታል፤ እንዴት ያለ መባረክ ነው!
አምላኩን መስሎ ስለእርሱ በፍቅር የሞተለትን እያሰበ ለሰይጣን እንኳን ንስሐ የለመኑትን እነ ቅድስት ክርስቶስ ሠምራን በዓይነ ኅሊናው እየሳለ የፍቅርን ደሞዝ ለመቀበል የሚጓዝ እውነተኛ አገልጋይ ይህ ነው፡፡
በእርግጥ እነዚህ ሁሉ የተለየ ስብዕና ይፈልጋሉ ፤ እምነት እና እርጋታን ያስቀድማሉ፡፡ በሃይማኖትን መኖርን የክርስቶስን ትእዛዝ መከተልን አጥብቀው ይሻሉ፡፡


ምንጭ፡- Paradise of the spiritual service
 (By Bishop Youhanis )