ንስሐ የገባ ሰው ዳግም በኃጢያት እንዳይወድቅ ሊያደርጋቸው የሚገቡ ጥንቃቄዎች
ምንም እንኳን ንስሐ የሚደገም ምሥጢር ቢሆንም ወደፊትም ለምንሰራቸው ኃጢያቶች ንስሐ የሚገባ ቢሆንም ተነሳሒው በሕይወቱ አምላኩን ያከበረ ስለሆነ ኃጢያጥ በሕይወቱ ላይ ያደረሰውን ተረድቶ ከኃጢያት መጠንቀቅ መራቅ ብሎም ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለው መሸሽ ይገባዋል፡፡(1ኛ ቆሮ 6፥18 2ኛ ጢሞ 2፥22) ስለዚህም ተነሳሒው የሚከተሉትን ጥንቃቄዎች ያደርግ ዘንድ ይገባዋል፡፡ለኃጢያት ሌላ ስም አለመስጠት
ኃጢያት እንደኃጢያት አለመቁጠር የዘመናችን ትልቁ በሽታ ነው፡፡ ኃጢያትን በሌላ ካባ ማሳመርና ማስጌጥ ለሰው ልጆች ውድቀት ዋንኛ መነሻ ነው፡፡ አንዳንዶችም የሰሩትን ኃጢያት ለመሸፈንና ሕሊናቸው እንዳይወቅሳቸው ስለንስሐ መስማት አይፈልጉም፡፡ ጥንተ ጠላታችን ዲያቢሎስ አባታችን አዳምን ና እናታችን ሔዋንን ሲያስት ዕጸ በለሱን ‹‹ዓይን ከፋች እውቀት ገላጭ›› ብሎ ሲያሜ ሰጥቶ ለኃጢያት ቦታ እንዲኖራቸው አድርጎል፡፡(ዘፍ 3፥5) በዓለማችን የምናየውም ይህንን ነው፡፡ ተነሳሒው ግን ቀድሞ ንስሐ የገባ ኃጢያትን ጠልቶ ነውና ኃጢያት ለመሥራት መናፈቅ የለበትም፡፡ክፉ ነገሮችን አለማወቅ
ጠቢቡ ሰሎሞን ‹‹የጥበብ መብዛት ትካዜ ያበዛልና ዕውቀትንም የሚጨምር ኃዘንን ይጨምራል፡፡›› (መክ 1፥18) እንዳለ ስለኃጢያት ማወቅ ወደ ሞት ያመራናል፡፡ ሔዋን አምላክ የመሆንን ክፉ ዕውቀት ባወቀች ጊዜ ዕጹን ትበላ ዘንድ ምኞት በውስጧ ተቀሰቀሰ፡፡ በሕገ ተፈጥሮ ንጹሕ የሆነው ሕጻን ኃጢያት መሥራት የሚጀምረው በአካባቢው ያሉ ሰዎችን በማየት ነው፡፡ ኃጢያትን ማወቅ ለመሥራት ይጋብዛልና ከዚህ መጠበቅ ይኖርብናል፡፡ አክአብ የናቡቴን እርሻ ቦታ መቀማት ብሎም መግደል የተማረው ከክፉ መካሪው ሚስቱ ኤልዛቤል ነው፡፡(1ኛ ነገ 20፥9) አምኖን እኅቱ ትዕማርን ከክብር ያሳነሳት በአሚናዳብ ክፉ ምክር ነው(2ኛ ሳሙ 13፥5) ሮብዓም ክፉ ነገር የተማረው ከገዛ አብሮ አደጎቹ ነው፡፡(1ኛ ነገ 12፥10) ስለዚህም ተነሳሒው ዳግመኛ ወደ ኃጢያት እንዳያመራ ክፉ ነገሮችን መሸሽ ማረቅ ከእውቀታቸውም ራሱን መከልከል ይገባዋል፡፡ንስሐን ለመሞከር አለመጋበዝ
በቀልድ በዋዛ ፈዛዛ የሚጀመረው ቀላል ኃጢያት ‹‹ንዑስ ቀበሮ›› ሆኖ እንድንጠፋ ምክንያት ሊሆነን ይችላል፡፡ መጽሐፍ እንዳለን ‹‹የወይናችንን ቦታ የሚያጠፉትን ጥቃቅን ቀበሮዎች አጥምዳችሁ ያዙልን፡፡›› (መኃ 2፥15) ተነሳሒው ቀላሉ ኃጢያት ወደ ሞት እንዲወስደው ስለሚያምን ይህንን ከማድረግ ራሱን መጠበቅ አለበት የኃጢያት ቀላል የለውምና፡፡ ይሁዳ ጌታን ለመሸጥ ያባቃው አስቀድሞ ለድሆች ከሚሰጠው ገንዘብ ይሰርቅ ስለነበረ ነው፡(ዮሐ 12፥6) ይህንንም የሚያስተውል ሰው ጥቃቅኑን ቀድሞ ማቆም ይገባዋል፡፡ከክፉ ባንጀራ መራቅ
ተነሳሒው ሌሎች በእርሱ እንዲሳቡ አስተማሪ እንጂ ሌሎችን እርሱን እንዲስቡት መሆን የለበትም፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋል›› እንዳለ(1ኛ ቆሮ 15፥33) ጌታም ‹‹ወደ ሳምራዊያን ከተማ አትግቡ›› (ማቴ 10፥5) እንዳለ ከሳምራዊያን ክፉ ግብር ተሳታፊ እንዳንሆን ጥንቃቄ ማድረግ ይገባናል፡፡ ቅዱስ ዳዊት እንዳለ ‹‹ከንጹሕ ጋር ንጹሕ ሆነህ ትገኛለህ ከጠማማ ጋር ጠማማ ሆነህ ትገኛለህ››(መዝ 17፥26) ስለዚህም በክፉዎች መንገድ አለመሄድ በኃጢያቶች መንገድ አለመቆም ይገባል የክፉዎችና የኃጢያተኞች መንገድ ትጠፋለችና፡(መዝ 1፥1-)ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ መልእክቱ “ለቀደመውም ዓለም ሳይራራ ከሌሎች ሰባት ጋር ጽድቅን የሚሰብከውን ኖኅን አድኖ በኃጢአተኞች ዓለም ላይ የጥፋትን ውኃ ካወረደ፥ “ኃጢአትንም ያደርጉ ዘንድ ላሉት ምሳሌ አድርጎ ከተማዎችን ሰዶምንና ገሞራን አመድ እስኪሆኑ ድረስ አቃጥሎና ገልብጦ ከፈረደባቸው ጻድቅ ሎጥም በመካከላቸው ሲኖር እያየና እየሰማ ዕለት ዕለት በዓመፀኛ ሥራቸው ጻድቅ ነፍሱን አስጨንቆ ነበርና በዓመፀኞች ሴሰኛ ኑሮ የተገፋውን ያን ጻድቅ ካዳነ ከክፉ አድራጊዎቻችን ግብር ሳንቀላቀል ነፍሳችን በእነሱ ሥራ እንዳይቆሽሽ ምንጨነቅ ከሆነ ከዓመፀኞች ሴሰኛ ኑሮ የተገፋውን ሰዎች ያድን ዘንድ ዛሬም የታመነ ነው፡፡
ሰይጣንን መቃወም
ቅዱስ ያዕቆብ ‹‹ዲያቢሎስን ተቃወሙት ከእናንተ ይሸሻል›› (ያዕ 4፥7) እንዳለ የዲያቢሎስ የሆነውን ሥራን መቃወም ይገባል፡፡ ሰይጣን ጌታን በሦስቱ ኃጢያቶች እንደፈተነ ጌታም ዲያቢሎስን ድል አድርጎ ‹‹ሑር እምኔየ›› ከእኔ ሂድ እንዳለ እንዲሁ ዲያቢሎስንና የዓለምን ኃጢያት ከእኔ ራቅ ሂድ እንለው ዘንድ ይገባናል፡፡ማጠቃለያ
ቅዱስ ጳውሎስ “እውነትን በዓመፃ በሚከለክሉ ሰዎች በኃጢአተኝነታቸውና በዓመፃቸው ሁሉ ላይ የእግዚአብሔር ቍጣ ከሰማይ ይገለጣል፡፡” (ሮሜ 1፡18) እንዳለ የእግዚአብሔር ቁጣ ከመገለጡ በፊት ኹላችን ኃጢያት ከመሥራት መታቀብ ወደ ንስሐም መቅረብ ይገባናል፡፡ ለዚህም የእግዚአብሔር ቸርነት የእመቤታችን ምልጃ የቅዱሳኑ ጸሎት ይርዳን፡፡ስብሐት ለእግዚአብሔር
No comments:
Post a Comment