Thursday, 12 October 2017

እስመ ውእቱ ኮከብ ብሩህ ዘቤተክርስቲያን


         በዲ/ን ፍሬው ለማ
«ገብረ መንፈስ ቅዱስ ሞተከ ታብዕል ኢትዮጵያ ለጴጥሮስ በዓለ መርሆ ወለጳውሎስ
ሐዋርያ ከመ ተዝካሮም ታብዕል ሮምያ»
ትርጉም
«ገብረ መንፈስቅዱስ ሆይ ኢትየጵያ ሞትህን ከፍ አድርጋ ታስባለች የሮም ሀገር የሐዋርያትን ጴጥሮስ ና ጳውሎስ በዓል ከፍ አድርጋ እንደምታከብር»

                መልክዐ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ

ከወይን ፍሬ ይልቅ የጣፈጠ ከሮማን አበባም ይልቅ ቡሩክ የሆነ የአንድ ተጋዳይ ምስጋናን
እንነግራችኋለን ይኸውም በሰነፎቹ ዘንድ የተናቀ በአዋቂዎች ግን ተቀባይነት ያለው በቅዱሳን ዘንድ የተወደደ ለርኩሳኑ የሚያስፈራቸው ነው ይህም ኮከብ ለቤተክርስቲያን ጳዝዮን የሚባል ዕንቁ ጸሎቱ እንደ ዕጣን የሚሸት የታመነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ነው።

ደብራችን ደብረ ብርሃናት (የብርሃናተ ዓለም ቅዱስ ጴጥሮስ ወጳውሉስ ቤተ ክርስቲያንን ለማለት ነው) ከምትዘክራቸው ከጌታ ምስክሮች አንዱ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ናቸው ልክ በመልክአቸው እንደተገለጸው ኢትዮጵያ ዝክራቸውን ዘወትር ወር በገባ በ፭ ከፍ አድርጋ ታከብራለች፡፡ምዕመናንም አቡዬ(አባቴ) ብለው በፍቅር ቃል ይጠሯቸዋል ከገድላቸውና ከመጽሐፍ ባገኘው ከፍ አድርገን የማግነናችን ሥራ መሠረት ከዚህ በኃላ እንዳስሳለን

† ትውልዳቸውና እድገታቸው


አባታችን አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ በገድላቸው ተጽፎ እንደምናነበው የተወለዱት በግብጽ ሀገር ልዩ ስሙ ንሂሳ በሚባል ቦታ ነው። አባታቸው ስምዖን እናታቸው አቅሌስያ ይባላሉ። አቅሌስያ ልጅ አጥታ 30 ዘመን እያለቀስቸ ኖራለች። የንጹሀንን ጸሎት የሚቀበል ጌታም ደም ግባቱ ያማረ ልጅ ሰጣት። ይህም በመልክአቸው ላይ «ስምዖን ወ አቅሌስያ ዘ ነበሩ በንሂሳ በኃጢአ ውሉድ በከዩ መጠነ አመታት ሠላሳ» ተብሎ ተገልጿል አባታችን መጋቢት 29 ተጸንሰው በታህሣሥ 29 ተወልዱ። በተወለዱበት ቀንም መልአኩ ገብርኤል በሰው አምሳል ተመስሎ የዚህ ህጻን ስም ገብረ መንፈስ ቅዱስ ይሁን ብሎ ተናገረ። በዚያን ቀንም ህጻኑ ከእናቱ ጭን ወርዶ ለ ቅድስት ሥላሴ ሶስት ጊዜ ሰገደ።ከሦስት ዓመት በኋላ መልአኩ በክንፉ ተሸክሞ ኖብ ወደሚባል ገዳም ወስዶ ህጻኑን አባ ዘመደብርሀን ለሚባሉ አባትሰጠው። ያም አባት ሕጻኑን በፍቅር በስርዓት ቅዱሳት መጻሕፍትን እያስተማረ አሳደገው፣ አባ ዘመደ ብርሃንም ሕጻን ገብረመንፈስ በትምህርቱ በትህትናው እግዚአብሔርን በመፍራቱ ታዛዥ መሆኑን በተመለከተ ጊዜ አቡነ አብርሃም ወደ ተባሉ ጳጳስ ወስዶ መዓረገ ዲቁናንም አሰጠው ።

ከዚያ በኋላ ፍጹም መናኝ በጸሎት ትጉህ ሆነው ሲያገኛቸው መንኩሰው የቅስና መዓረግ እንዲቀበሉ ሆኑ አቡነ ገብረ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ እንደ ሐዋርያት በመንፈስቅዱስ ተሞልተው ቅዱስ ወንጌልን እያስተማሩ በጾም በጸሎትና በስግደት እግዚአብሔርን እየለመኑ ብዙ ሕሙማንን ያድኑ ነበር።የጻድቁ አቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ ዝናቸው ቅድስናቸው በኢየሱስ ክርስቶስ ስም የሚያደርጉትን ተዓምራት በብዙ አገር ስለተሰማ ውዳሴ ከንቱ እንዳይሆንባቸው ወደ ጫካ ገቡ ከነምሮችና ከአንበሶች ጋር ተስማምተው መኖር ጀመሩ። 300 ዓመትም በታላቅ ተጋድሎ በግብጽ፣የመን ፣ በሱዳን ና በሌሎችም ሃገሮችም እያስተማሩ ከኖሩ በኋላ የእግዚአብሔር መልአክ ከቦታ ቦታ የሚጓጓዙበት የብርሀን ሰረገላ ሰጣቸው ወደ ኢትዮጵያም እንዲመጡ አዘዘዛቸው። ይህም በዘመነ ላሊበላ በ11ዐዐ ዓ.ም. በጥቅምት ወር በ ፭ተኛው ቀን ነው። አባታችንም 60 አንበሶች በፊቱ 60 ነምሮች በኃላው ሆነው ወደ ኢትዩጵያ መጣ ። በመጀመሪያ ታቦተ ጽዮን ወደ አለችበት ወደ አክሱም ሄደው ለሶስት ሳምንታት እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ሰነበቱ ከዚያም ንጉሥ ላሊበላ ከአለት ፈልፍሎ ወደ አሰራቸው አብያተ ክርስቲያናት ወደ ሮሐ ሄዱ ንጉሥ ላሊበላ ከእግዚአብሔር የተሰጣቸውን ሞገስና ግርማ እያደነቀ በክብር ተቀብሎ አስተናገዳቸው ከዚያም ንጉሱን ና ቦታውን ባርከው እግዚአብሔር ወደ ፈቀደላቸው ዝቋላ ለመሄድ ተነሱ በዚያም በከበረ በጌታችን ስም ተጋድሎን ፈጽመዋል

† እረፍቱ ለአቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ


ስለ ዕረፍታቸው በገድላቸው እንዲህ ተጽፏል ቀኑ መጋቢት 5 ዕለቱ ቅዳሜ ለእሑድ አጥቢያ ሰዓቱ ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት ሆኗል፤ አሁንም ህማሙን እየታገለ እያላበው በድካም ለፍጥረቱ ሁሉ ይለምናል፤ “አቤቱ ህዝብህን አድን ርስትህን ኢትዮጰያንም ባርክ” ይላል። ሕመም የጀመረው መጋቢት 3 ዓርብ ቀን ነው፤ መታመሙን የሰሙ እንደርሱ ቅዱሳን የሆኑት ዘርአ ቡሩክ፤ ፍሬ ቅዱስ፤ያዕቆብ፤ብንያምና ዮሴፍ እንዲሁምበወቅቱ የኢትዮጰያ ንጉስ የነበረው እንድርያስ ሊጠይቁት ተሰብስበዋል ወደ አጠገቡ መድረስ ግንአልተቻላቸውም አባታችን ገብረመንፈስ ቅዱስ የሚጋርደው እንጨት ዛፍ በሌለበት በርሃ እንደ አንበሳ ተኝቶ አዩት በላዩ ያረፈው የእግዚአብሔር ጸጋ ከፊቱ የሚወጣው ብርሃን ቀይ መልኩ ረዥም የራስ ጠጉሩ እንደ ነጭ ሐር የሚሆን ጽሕሙ አስደነቃቸው። ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት ሲሆን ከሰማይ ታላቅ ነጎድጓድ ድምጽ ተሰማ ጌታችን መላአክትን አስከትሎ ወደ አባታችን ወረደ፤ ከሰማይ ወደ ምድር ህብሩ አምሳያው ልዩ ልዩ የሆነ እንደ ፀሐይናእንደ ጨረቃ የሚያበራ እንደ ወንጭፍ ድንጋይ ይወረ ወር ነበር ከዚያ የነበሩ ሁሉ ፈሩ ወደ ኃላም ሸሹ ምድር ራደች ተራሮች ኮረብቶች ተናወጡ ብርቱ ጩኸት ንውጽውጽታ ሆነ። “ወዳጄ ገብረመንፈስ ቅዱስ ሰላም ላንተ ይሁን” እነሆ የማይታበል ቃል ኪዳን እገባልኃለው ስምህን የጠራ መታሰቢያህን ያደረገውን፤ እጣን ቋጥሮ ግብር ሰፍሮ መባ ይዞ ቤትህ የመጣውን እምርልኃለው አንተ ከገባህበት ገነት መንግስተ ሰማያት አገባዋለሁ አላቸው፤ አባታችንም “አቤቱ ጌታ ሆይ የኢትዮጰያን ህዝብ ማርልኝ” አሉት፤ እነሆ ምሬልኃለው አስራት በኩራት አድርጌም ሰጥቼሃለው። ከዚህ በኃላ ሰባቱ ሊቃነ መላዕክት የአባታችንን ነፍስ ሊቀበሉ ወረዱ በታላቅ ምስጋናም ወደ ሰማይ አሳረጉት ስጋውንም ይዘውት ሄዱ የት እንደተቀበረ ግን እስካሁን አይታወቅም አንዳንዶች በኢየሩሳሌም ነው ይላሉ፤ ሌላው በምድረ ከብድ ነው ይላል ግን እስካሁን ልክ እንደ ሊቀ ነብያት ሙሴ ስጋ የት እንደተቀበረ አይታወቅም። ገድሉ ትሩፋቱ ከሰማይ ከዋክብት ከምድር አሸዋ ይበዛል ኢትዮጰያን አብዝቶ ይወዳታል፤ ምድራዊ ምግብ አልተመገበም የእናቱን ጡት እንኳን አልጠባም፤ ልብስ፤ መጠለያ አልፈለገም፤ የክረምት ቁር የበጋ ሐሩር እየተፈራረቀበት በተጋድሎ 562 ዓመት ኖረ፤ በመጋቢት 5 ቀን ሩጫውን ጨረሰ።

† አቡነ ገብረ መንፈስቅዱስና የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን

የኢትዮጲያ ቤተክርስቲያን ታሪክ የጥቂቶች ታሪክ አይደለም የብዙ ቅዱሳን ታሪክ ነው        ብዙዎች የደም ዋጋ ከፍለውበታል ከነዚህ ዕንቁዎች አንዱ አባታችን አቡነ ገብረመንፈስቅዱስ ናቸው። አባታችን ለቤተክርስቲያንችን ካበረከቱት አስተዋፅዎች በጥቂቱ እንኳን ብንዘረዝር

ምንኩስናን በማስፋፋት
ኢትዮጵያ በ34 ዓ.ም ክርስትናን በ4ተኛው መ/ክ/ዘ ደግሞ ክህነትን በአባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን ተቀብላለች፡፡ የምንኩስና ሥርዓት ደግሞ በተሰዓቱ ቅዱሳን ወደ ኢትዮጲያ መጥቶአል፡፡ በኢትዮጵያ የምንኵስናና የገዳማት ታሪክ ውስጥ ከ3ኛው – 12ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ያለው ጊዜ በአብዛኛው ከውጭ በመጡ አበው ሥርዓተ ምንኵስና የተስፋፋበት ሲሆን ከ12ኛው-15ኛው ያለው ደግሞ ከመላ ኢትዮጵያ በተነሡ አበው ቅዱሳን ሥርዓተ ምንኵስናና የገዳማት ትክል ከሰሜን ወደ ምዕራብ፣ ምሥራቅና ደቡብ የተስፋፋበት ወቅት ነው ከውጭ ከመጡት ቅዱሳንም አበታችን ተጠቃች ናቸው ፡፡

አባታችን አቡነ ገብረ መንፈስቅዱስ እግዚአብሔር በሰጣቸው የ562 ዓመት ዕድሜ አያሌ ገዳማትን የገደሙ ሲሆን በተለይም የዝቋላና የምድረ ከብድ ገዳማት እስከዛሬ የፀኑ ናቸው፡፡ ብዙ ደቀመዛሙርትንም አፍርተዋል፡፡

ወንጌልን በማስፋፋት
ክቡር አባታችን አቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ በኢትዮጲያ ምድር በየመንና በምድረ ሱዳን ሳይቀር እየተዘዋወሩ ቅዱስ ወንጌልን አስተምረዋል ጠንቋይ ቃልቻ በልዩ ልዩ አምልኮት የነበሩትን ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር መልሰዋል የታመሙትን በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም አድነዋል ለዚህም ማሳያ የሚሆኑን በአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ስም በተለያዩ የሃገራችን ክፍላት የታነጹት አብያተ ክርስቲያን ናቸው ዝክራቸውንም ሁሉም ኢትዮጵያውያን ያከብራሉ ለዚህም ነው አባቶች በጥቅምት ፭ ማኅሌት «ዝንቱሰ ሐዋርያ ገብረ ሕይወት ዘተፈነወ ውስተ ምድርነ ከመ ይክስት ብርሃነ ይፈውስ ዱያነ» ብለው የሚያመሰግኑት

ጸሎታቸውና በረከታቸው ከ እኛ ጋር ይሁን አሜን

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

No comments:

Post a Comment