በንስሐ የሚገኙ ለውጦች
በሕይወት ውስጥ መንፈሳዊ ለውጥ ከሌለ የክርስትና ሕይወት ጣዕም ያጣል፡፡ ይህንን መንፈሳዊ ለውጥ ለማምጣት ታዲያ ንስሐ አስፈላጊ ነው፡፡ ንስሐ ማለት መናዘዝን ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን መቀበል ብቻ ማለት አይደለም፡፡ ኃጢያትን በፍጹም በመተው በተቀደሰ የሕይወት ጎዳና መመላለስ እንጂ፡፡ ንስሐ አንድ ወቅት ከክርስቶስ እግር በታች ራስን መጣል ብቻ ሳይሆን በመንፈሳዊ ሕይወት መኖርና የእግዚአብሔርን ትእዛዛት በመፈጸም ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ‹‹በእርሱ የሚኖር ኹሉ ኃጢያትን አያደርግም፡፡ ኃጢያትን የሚያደርግ ኹሉ አላየውም አላወቀውም››(1 ኛ ዮሐ 3፥6) እንዳለን ለአንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ኹሌም ብሆን በእርሱ የምንኖር ኹላችን ኃጢያትን ማድረግ የለብንም፡፡
በንስሐ የተመለሰ ሰው ጠባያት
• ትኁት ሰብእና አለው (ሉቃ 14፥10)
ትዕቢት መታጀርን አያውቅም፡፡ በጉባኤ እንኳን ዝቅ ያለ ሥፍራ ላይ መቀመጥን ይመርጣል፡፡
• ትእግስተኛ ነው
ስለሰዎች ኃጢያት ሲሰማ ወይም ስህተትን ሲያይ ሲሰድቡት ወይም ከክብሩ ዝቅ ቢያደርጉት እርሱም ያንን በደል ከዚህ በፊት ስለሰራ ይታገሳል፡፡ የእርሱ ሐሳብ ብቻ ተቀባይነት እንዲኖረው አይሞክርም ከእኔ ከኃጥኡ አእምሮ ምን መልካም ነገር ይገኛል ይላልና ራሱንም በትኅትና ዝቅ ያደርጋል፡፡
• ምሕረትን ያውቃል (ማቴ 6፥15 1ኛ ሳሙ 26፥11)
ሰዎች ክፉ ነገር ቢያደርጉት ክፋትን አይመልስም ቢሰድቡት አይራገምም እርሱ ይቅር ካላለ ኃጢያቱ እንደሚያዝበት ያውቃል፡፡ የዘወትር ጸሎቱንም በተግባር በይቅር ባይነቱ ይተገብረዋል፡፡
• አርምሞን ገንዘብ ያደርጋል
ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ ‹‹እኔ ሌሎች ሲናገሩ ባደምጥ ከንግግራቸውም መማር ይሻለኛል›› እንዳለ (ያዕ 1፥19) ንስሐ የገባ ከእግዚአብሔር ጋር እርቅ የፈጸመ ንግግሩ የማይሰማ በአርምሞ የተሞላ ነው፡፡
• የመንፈስ ደኃ ይሆናል
በመንፈስ ድሆች(ነዳያነ መንፈስ) የሆኑ ማለት የዋሐን ትሑት የሆኑ ማለት ነው፡፡ እንዲህ ያሉ ሰዎች ራሳቸውን ችሎታ እንዳላቸው አድርገው አይቆጥሩትም፡፡ በራሳቸው ዘር፣ ጠባይ፣ ተፈጥሮ፣ ሀብት፣ አቅምና ችሎታ ተስፋ አያደርጉም፡፡
ነዳያን በመንፈስ ያልተማሩ ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን ማንነታቸውን አውቀው በፈቃዳቸው ሁሉን የተዉ ማለት ነው፡፡ ነዲያን በመንፈስ በእግዚአብሔር ፊት የተሰበረና የተዋረደ ልብ ይኖራቸዋል፡፡ ይህን የሚያደርጉት ከእነሱ እጅግ የሚበልጥ ሁሉን የሚያውቅ አምላክ መኖሩን በማሰብ ነው፡፡
አንድ ሰው ራሱን ዝቅ ካላደረገ የትኅትናም ሥራ ካልሰራ አምላካዊ ጸጋን አያገኝም እርሱም አይፈልገውም፤ ሁሉ ያለው ይመሰለዋልና፡፡ ክርስቲያን የሆኑ ሁሉ ግን ይህን የትሩፋት ሥራ መንገድ መከተል ራስን ከመውደድ መራቅ እያለውም እንደሌለው ሆኖ መታየት ተገቢው ነው፡፡
መኮንነ ተሰሎንቄ ዮሐንስ አፈ ወርቅን እንደጠየቀው ብፁዓን ከበቁ በኋላ ነዳያነ አእምሮ መሆናቸው እንደምንድነው? አለው ዮሐንስም ‹‹አንተ በሃገርህ እንደምን ትኖራለህ›› አለው ‹‹ከሁሉ በላይ ነኝ›› አለው እልፍ ብለህ ‹‹በቂሳርያሳ›› ‹‹የምበልጣቸውም የሚተካከሉኝም አሉ›› አለው ዝቅ እያለ ሄደ፡፡ ‹‹አንጾክያስ አለው›› ‹‹የሚያውቀኝ የለም›› አለው ቅዱሳንም በአእምሮ ነዳይ የሆኑት ከበላላቸው ያለውን ፈጣሬ መጋቤ ዓለማትን እያዮ ራሳቸውን ዝቅ ያደርጋሉ እንጂ አይታበዩም፡፡ በምግባር በሃይማኖት በንስሐ ድሆች ነን ብለው የሚያዝኑ የሚተክዙ ንዑዳን ክቡራን ናቸው፡፡
የምንመካበት ምንነታችን የእኛ አይደለም፡፡ የምንመካበትን ዕውቀት ሐብት ጉልበት ሥልጣን የሰጠን አምላካችን ነው፡፡ ነዳያነ መንፈስ ይህንን መመልከት የሚችሉ ናቸው፡፡ የእነርሱን ዕውቀት ከአምላክ ፍጹም እውቀት ጋር እያነጻጸሩ ኢምንትና ትንሽ መሆኑንን ይገነዘባሉ፡፡ ሐብታቸውን ጉልበታቸውንም ከሁሉ ኃያል ሁሉ በእጁ ከሆነው አምላክ ጋር እያነጻጸሩ ራሳቸውን በጌታ ፊት ያዋርዳሉ፡፡ መንግስቱን የሚርሱ እንደነዚህ ያሉት ናቸው፡፡ መመካታቸውን በአምላክ ላይ ያደረጉ በራሳቸው የማይመኩ የመንግስቱ ወራሾች ናቸው፡፡
የመንፈስ ደኃ መሆን ኹሉ እያለው እንደሌለው መሆን ማለት ነው፡፡ ጥበበኛ ሆኖ ሳለ ባለፀጋ ሆኖ ሳለ ደኃ መሆን ራስን በትኅትና መስበር ነው፡፡ ሰው በሌለው ነገር የሚኮራ ፍጡር ነው አላዋቂው አዋቂ ተብሎ ይመሰገን ዘንድ ይወዳል ንስሐ የገባ ሰው ግን እንኳን በሌለው ባለው ይወደስ ዘንድ አይሻም፡፡ ‹‹በሰማይና ምድር የተዋረዱትን የሚያይ ከአለቆች ጋር ከሕዝቡም አለቆች ጋር ያኖረው ዘንድ ችግረኛውን ከመሬት የሚያነሳ ምስኪኑን ከትቢያ ከፍ ከፍ የሚያደርግ››(መዝ 112፥8) ትዕቢተኞችን በልባቸው ሐሳብ የሚበትን ትኁታኑን ከፍ የሚያደርግ ጌታን በማሰብ ኹሌም በትኅትና የሚኖር ነው፡፡(ሉቃ 1፥52)
በአጠቃላይ ተነሳሒው በሕይወቱ ፈጽም ለውጥ ያሳያል አስተሳሰቡ አስታያየቱ አነጋገሩ ኹሉ ይቀየራል፡፡ ሰዎች ከአንደበቱ ይልቅ በሕይወቱ ይሰበካሉ ሳይናገር ምግባሩ ሰዎችን ይለውጣል፡፡ በእርሱም ምክንያት ብዙዎች ወደ ንስሐ ይቀርባሉ፡፡
ስብሐት ለእግዚአብሔር
No comments:
Post a Comment