Tuesday, 28 May 2024

ኦርቶዶክሳዊ የንስሐ ሕይወት (ክፍል ፩)

በዲያቆን ያሬድ መለሰ
ለአስታየትዎ ymelese04@gmail.comን ይጠቀሙ

"እንደእግዚአብሔር ፍቃድ የሆነ ሐዘን ጸጸት የሌለበትን ወደ መዳንም የሚያደርሰውን ንስሐ ያደርጋልና የዓለም ኃዘን ግን ሞትን ያመጣል።"

(2 ቆሮ. 710)

ውድ ኦርቶዶክሳዊያን የዛሬው ርዕሳችን የኦርቶዶክሳዊ የንስሐ ሕይወት ነው፡፡ በዚህ ተከታታይ ጽሑፍ ዋና ዓላማ ንስሐን በተመለከተ ግንዛቤ ለመፍጠር ነው። በዚህ ጽሑፍ በዋንኝነት የንስሐ ምንነት(ከኃጢአት ትርጉም በመሳት)፣እንዲሁ የንስሐ ደረጃዎች፣የንስሐ ጥቅም፣ኃጢአትን መናዘዝ፣ የካህኑ ድርሻ ፣ቀኖና፣ ኃጢአትን የመናዘዝ (ኑዛዜ) ጥቅምና እንዴት መናዘዝ እንደሚገባ እንመለከታለን በመጨረሻም እውነተኛ ኑዛዜን እንዳንፈጽም የሚያግዱን ዘመኑ መሰናክሎችን(ፈተናዎች) በዝርዝር በተከታታይ ክፍሎች ለማየት እንሞክራልን። ስለዚህም ክፍል የኃጢአት ምንነት የንስሐ ምንነት እናያለን መልካም ንባብ።

ኃጢአት ምንድን ነው?

ኃጢአትበግሪክ ቃልአማርቲያሲሆን ቀጥተኛ ትርጉሙ ምልክቱን ማጣት ማለት ነው። ለክርስቲያኖች ምልክት” የምንለው ሕይወታችንንና ድርጊታችንን በኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወትና ተግባር ላይ በመመሥረት ከእግዚአብሔር ጋር በኅብረት መኖር ነው። ስለዚህይህን ምልክት ስናጣእንበድላለን። በሌላ አገላለጽ ኃጢአት እግዚአብሔር የሰውን ልጅ ከፈጠረለት የክብር ዓላማ ጐድሎ መውደቅ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ኃጢአትን በተመለከተ ልዩ ልዩ ትርጉም ሰጥቶት እናገኛለን፡፡ ጥቂቱን ለማየት ያክል

ኃጢያት እግዚአብሔርን መበደል ነው።

መጽሐፍ ስለዚህ ነገር ሲናገር ‹‹አንተን ብቻ በደልኩ በፊትህም ክፋትን አደረኩ›› እንዲል መዝ 504

ኃጢያት መሥራት ሀልዎተ እግዚአብሔርን መዘንጋት ነው፡፡

ኃጢያት ሀልዎተ እግዚአብሔርን መካድ ነው ማለታችን እንደሰነፍ ሰው እግዚአብሔር የለም እንደሚለው ሳይሆን እግዚአብሔር አያየኝም ብሎ በእግዚአብሔር ፊት ኃጢአትን ማድረግ ሀልዎቱን እንደመካድ ስለሆነ ነው፡፡ እንደ ዮሴፍ ያለ ጻድቅ ሰው ግን ‹‹በእግዚአብሔር ፊት እንዴት ኃጢያት እሰራለሁ? ›› ይላል (ዘፍ 399)

ኃጢያት መሥራት ማመጽ ነው፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ በመልእክቱ እንዳለን ‹‹ኃጢያት የሚያደርግ ሁሉ አመጻን ደግሞ ያደርጋል፡፡›› እንዲል አመጻን ማድረግ ነው፡፡ (1 ዮሐ 39) ይሁዳም ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው መልእክት አስቀምጧል፡፡ከአዳም ጀምሮ ሰባተኛ የሆነ ሄኖክ፦ እነሆ፥ ጌታ በሁሉ ላይ እንዲፈርድ፥ በኃጢአተኝነትም ስላደረጉት ስለ ኃጢአተኛ ሥራቸው ሁሉ ዓመፀኞችም ኃጢአተኞች በእርሱ ላይ ስለ ተናገሩ ስለ ጭከና ነገር ሁሉ ኃጢአተኞችን ሁሉ እንዲወቅስ ከአእላፋት ቅዱሳኑ ጋር መጥቶአል ብሎ ለእነዚህ ደግሞ ትንቢት ተናገረ።” (ይሁዳ 114-15)

ኃጢያት መሥራት የእግዚአብሔር ጠላት መሆን ነው፡፡

 ቅዱስ ያዕቆብ በመልክእቱ እንዳለን ‹‹ዓለምን መውደድ ለእግዚአብሔር ጥል እንዲሆን አታወቁምን? ›› (ያዕ. 44) ከእግዚአብሔር የተወለደ ኃጢያት አያደርግም እንዲል ቅዱስ ዮሐንስ ኃጢአትን ማድረግ የእግዚአብሔርን ልጅነት ያሳጣል (1 ዮሐ 39)


ንስሐ ምንድን ነው?

ስለ ኃጢአት ማዘን፣ የጥፋተኝነት ስሜት፣ የኃዘን ስሜት... በሠራነው ኃጢአት ምክንያት የሚመጣ ሕመም ብለን ልንተረጉመው እንችላለን ሆኖም እንዲህ ዓይነቱ ትርጉም የተሟላ አይደለም። የግሪክ ቃል ንስሐ ለሚለው ሜታኖያετάνοια metanoia) ማለት ሲሆን ትርጉሙም “የአስተሳሰብ ለውጥ” ማለት ነው፡ እናም ላለፈው መጸጸት ብቻ ሳይሆን የአመለካከታችን መሠረታዊ ለውጥ፣ እራሳችንን፣ ሌሎችን እና እግዚአብሔርን የምንመለከትበት አዲስ መንገድ ነው።

ንስሐ ሐዘን ጸጸት ቁጭት ብቻ ሳይሆን አንድ ሰው ዳግመኛ የተቆጨበትን ኃጢያት መልሶ ላለማድረግ የሚወስነው ቁርጥ ውሳኔ ነው፡፡

Ø  ንስሐ ወደ እግዚአብሔር መመለስ ነው፡፡ (ሉቃ 1518-20)

Ø  ንስሐ ከእግዚአብሔር ጋር መታረቅ ነው፡፡ (2 ጢሞ 520)

Ø   ንስሐ ከኃጢያት እንቅልፍ መንቃት ነው፡፡ (ሮሜ 1311)

Ø   ንስሐ ስለፍቅረ እግዚአብሔር ስለቅድስና ብሎ ኃጢያትን መተው ነው፡፡

Ø  ንስሐ ጊዜያዊ ስሜት ሳይሆን ፍጹም የሕይወት ለውጥ ነው፡፡ (ሮሜ 122)

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “እውነትን በዓመፃ በሚከለክሉ ሰዎች በኃጢአተኝነታቸውና በዓመፃቸው ሁሉ ላይ የእግዚአብሔር ቍጣ ከሰማይ ይገለጣል፡፡” (ሮሜ 1፡18) እንዳለን ሰው ከእግዚአብሔር ቁጣ ያመልጥ ዘንድ ንስሐ አስፈላጊ ነው፡፡ ንስሐ በሚታይ አገልግሎት የማይታይ ፀጋ የሚሰጥበት ታላቅ ምሥጢር ነው፡፡ የሚታየው ተነሳሒው ጸጸትና ኑዛዜ የካህኑ ጸሎተ ንስሐ ሲሆን የማይታየው ፀጋ ደግሞ ተነሳሒው የሚያገኘው ሥርየተ ኃጢአት ነው፡፡ ንስሐ በየዕለቱ ከሚደረገው ጸሎት ውስጥ አንዱ ክፍል ነው፡፡ ሰው ኹሉ በጸሎት ውስጥ ስለኃጢአቱ ሥርየት ስለበደሉ ይቅርታ በመጠየቅ ፈጣሪውን መለመን ይገባዋልና፡፡ ንስሐ በጸሎት ሕይወታችን ውስጥ ታላቅ ሥፍራ አለው።
ሰው ኹሉ ፍጹም አይደለምና ሲበድል በየዕለቱ ደግሞ ራሱን ለንስሐ ማዘጋጀት ይገባዋል፡፡ የቆሸሸ ልብስ በውሃ ሲያጥቡት እንደሚነጻ ሰውም እንዲሁ በኃጢያት ያደፈው ሕይወቱን በንስሐ ይጸዳል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለን “ወይስ የእግዚአብሔር ቸርነት ወደ ንስሐ እንዲመራህ ሳታውቅ የቸርነቱንና የመቻሉን የትዕግሥቱንም ባለጠግነት ትንቃለህን? ነገር ግን እንደ ጥንካሬህና ንስሐ እንደማይገባ ልብህ የእግዚአብሔር ቅን ፍርድ በሚገለጥበት በቍጣ ቀን ቍጣን በራስህ ላይ ታከማቻለህ።” (ሮሜ 2፡5) እንዳለ ሰው ቆሽሾ ከታጠበ በኋላ ዳግመኛ እንዳይቆሽሽ እንደሚጠነቀቅ ኹሉ እንዲሁ በንስሐ ከእግዚአብሔር ጋር ከተታረቅን በኋላ ወደ ኃጢአት እንዳይገባ ይጠነቀቅ ዘንድ ይገባዋል፡፡ ከቆሸሸም በፍጥነት እንደሚታጠብ ኹሉ እንዲሁ በኃጢያት ቢቆሽሽ በንስሐ ይታጠብ ዘንድ መገስገስ ይገባዋል።ለዚህም ቸርነቱ ትርዳን።

 

ይቆየን

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

 


No comments:

Post a Comment