በቀሲስ ያሬድ መለሰ
የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ለቤተ ክርስቲያን ተራ የታሪክ መታሰቢያ ወይም ዓመታዊ በዓል ብቻ አይደለም፤ እርሱ የሥርዓተ አምልኮዋ እምብርት፣ የእምነቷ ጽኑ መሠረትና በሞት ላይ የታወጀ የድል አዋጅ ነው። ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ከላይ በጠቀስነው መለኮታዊ ቃሉ እንደተናገረው፣ ክርስትና ያለ ትንሣኤ ትርጉም አልባ ይሆን ነበር። ትንሣኤ ግን ያንን የሞት ጨለማ ገፎ ለሰው ልጅ የዘለዓለም ሕይወትን ብርሃን በማብራት፣ እምነታችን በሕያው መሠረት ላይ እንዲቆም አድርጓል።
ቤተ ክርስቲያናችን ለትንሣኤ የምትሰጠው ክብርና የምታሳየው ሥርዓት እጅግ ረቂቅና ልዩ ሲሆን፣ ገና ዓመቱ ሲጠባ በባሕረ ሐሳብ ቀመር የዕለቱን በዓል በማወጅ ዘመናችን ሁሉ በትንሣኤው ብርሃን እንዲቃኝ መንፈሳዊ ጉዞዋን ትጀምራለች። የትንሣኤ ማኅሌትም እንደ ሌላው ጊዜ በ"ነግሥ" ሳይሆን ለእመቤታችን በሚቀርብ "ሰላም ለኪ" ሰላምታ መጀመሩ፣ "ተፈሥሒ ማርያም ለአዳም ፋሲካሁ" በሚል ምስጋና ታጅቦ ተአምረ ማርያምና ተአምረ ኢየሱስ ተነቦ ወንጌላትም በየተራ የሚነበቡበት "ወንጌለ ትንሣኤ" መኖሩ ልዩ ድምቀት ይሰጠዋል። ከዚህም በላይ በማኅሌቱ አጋማሽ ካህናቱና ምእመናኑ ጧፍ አብርተው ጨለማውን በብርሃን የሚተኩበት ሥርዓት ክርስቶስ መቃብርን በብርሃን መስበሩን የሚያበሥር ሲሆን፣ "ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን፤ አሠሮ ለሰይጣን አግዓዞ ለአዳም" የሚለው የነጻነት አዋጅ በከበሮና በጽናጽል ታጅቦ ሲታወጅ ማኅሌቱን ወደ ፍጹም ሰማያዊ ደስታ ይለውጠዋል። ከበዓሉ ማግሥት ጀምሮ ያሉት ሃምሳ ቀናትም (በዓለ ሃምሳ) ጾም የማይታሰብባቸው የድል ቀናት መሆናቸው፣ ትንሣኤ ለሰው ልጅ የሞት ሽረት ትግል ሳይሆን የሰማያዊ ሕይወትና የእውነተኛ መንፈሳዊ ሙላት አዋጅ መሆኑን በሚገባ ያስረዳል።
እውነተኛ የምሥራች የምንለው "ወንጌል" ራሱ ሕያው ትርጉም የሚኖረው ከትንሣኤ ጋር ሲያያዝ ብቻ ነው። ወንጌላውያን ስለ ጌታችን መወለድ፣ ስለ ሕማሙና ስለ ሞቱ የጻፉት የተነሣውንና ድል አድራጊውን ክርስቶስን በልባቸው ስላነገሡ ነው፤ ስለዚህም "ተወለደ፣ ታመመ፣ ሞተ" ሲሉ፣ ያ የተነሣውና ሞትን የረገጠው ጌታ መሆኑን እያረጋገጡልን ነው። እንዲሁ እያንዳንዱን እሑድ "ሰንበተ ክርስቲያን" ብለን የምናከብረው እርሱ በዚች ዕለት መቃብርን ከፍቶ፣ የሞትን ሰንሰለት ሰብሮ፣ ለሰው ልጅ አዲስ ሕይወትን ስላበረከተ ነው።
በአጠቃላይ ትንሣኤ የሞት መጨረሻና የሕይወት መጀመሪያ ሆኖ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ትልቅ ስፍራ ይይዛል። በትንሣኤው ወደ ክርስቶስ አካልነት የምንገባበትና ድል አድራጊነታችንን የምናውጅበት በመሆኑ፣ ለምንጾመው ጾምና ለምንቀበለው መከራ ሁሉ ታላቁ ምላሻችን እርሱ ነው። ለሙሽራው ክርስቶስ አንዲት ሙሽራ ቤተ ክርስቲያን እንዳለችው ሁሉ፣ በትንሣኤውም የምናገኘው ሕይወት አንድና ዘለዓማዊ ነው።
ትንሣኤ ማለት ምን ማለት ነው?
"ትንሣኤ" የሚለው የግእዝ ቃል "ተንሥአ" (ተነሣ) ከሚለው ግስ የወጣ ሲሆን፣ ትርጉሙም ከውድቀት መነሣት፣ ከጨለማ ወደ ብርሃን መሸጋገርና አዲስ ሕይወትን ማግኘት ማለት ነው። በቤተ ክርስቲያን ጥልቅ ትምህርት ውስጥ ትንሣኤ በሥጋ መነሣት ብቻ ሳይሆን የነፍስና የሕሊና መታደስን የሚያካትት አምስት ደረጃዎች ያሉት ምስጢር ነው። የመጀመሪያው ትንሣኤ ሕሊና ሲሆን፣ ይህም የሰው ልጅ አእምሮ ከምድራዊ ጭንቀትና ከኃጢአት ዝንባሌ ወጥቶ ዘወትር እግዚአብሔርን በማሰብ የሚታደስበት የብርሃን ጉዞ ነው። በመቀጠልም ትንሣኤ ልቡና ይመጣል፤ ይህም በንስሐ የታጠበ ልብ የእግዚአብሔርን ቃል ሰምቶ በቅድስና መኖር መጀመሩን ያመለክታል። እነዚህ ሁለት የትንሣኤ ደረጃዎች በሕይወት እያለን በየዕለቱ የምንለማመዳቸው መንፈሳዊ ድሎች ሲሆኑ፣ ቅዱስ ጳውሎስ "ከክርስቶስ ጋር ከተነሣችሁ በላይ ያለውን እሹ" (ቆላ. 3:1) በማለት የገለጠውን ሕያው ሕይወት የሚወክሉ ናቸው።
በሌላ በኩል ደግሞ ትንሣኤ በተአምራትና በመለኮታዊ ሥልጣን የሚገለጥባቸው ደረጃዎች አሉት። ትንሣኤ ለጊዜው የሚባለው እንደ አልዓዛርና እንደ ኢያኢሮስ ልጅ ያሉ ሙታን በጌታ ቃል ለጊዜው ከሞት መነሣታቸውን የሚገልጽ ቢሆንም፣ የሁሉ መሠረትና የድላችን ምንጭ ግን ትንሣኤ ክርስቶስ ነው። ጌታችን በገዛ ሥልጣኑ ሞትን ድል አድርጎ በመነሣቱ የሞትን ኃይል የሻረበትና ለእኛም የትንሣኤ በኵር የሆነበት ታላቅ ምስጢር ነው። ይህ የክርስቶስ ትንሣኤ ለሰው ልጅ ሁሉ ተስፋን የሰጠ ሲሆን፣ ፍጻሜውም በዓለም መጨረሻ ለፍርድና ለክብር የምንነሣበት ትንሣኤ ዘጉባኤ ነው። ያን ጊዜ "መቃብር ያሉቱ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል" (ዮሐ. 5:28) ተብሎ እንደተጻፈ፣ የዘላለም ሕይወትን ወርሰን በፈጣሪ ፊት በክብር የምንቆምበት የመጨረሻው የድል አክሊላችን ይሆናል።
የትንሣኤያችን በኵር ክርስቶስ ነው። (1ኛ ቆሮ. 15፥20)
ክርስቶስ "በኵር" ተብሎ ሲጠራ ለእኛ ለሰው ልጆች ሁሉ የሕይወትን ጎዳና የቀደደና ቀዳሚ ሆኖ የመዳን በርን የከፈተልን መሆኑን ያመለክታል። በፍጥረት በኩራችን ነው የምንለውም ዓለም ሳይፈጠርና ዘመን ሳይቆጠር እኛን ፈጥሮ ለማስገኘት በኵር ሆኖ በመገኘቱ ነው። ቅዱስ ጳውሎስ "እርሱም ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኵር ነው" (ቆላ. 1፥15) እንዳለው፣ እርሱ የፍጥረት ሁሉ መገኛና መሠረት ነው። ይህ ቀዳሚነቱ ነው እምነታችን በከንቱ ላይ ሳይሆን በሁሉ ፈጣሪ ላይ እንዲመሠረት ያደረገው፤ ምክንያቱም እምነታችን ትርጉም የሚኖረው ከፈጣሪያችን ጋር ስንታረቅ ብቻ ነውና።
በሁለተኛ ደረጃ ክርስቶስ በተቀድሶ ወይም በምስጋና በኵራችን ነው፤ ይህም ቅዱሳንና ጻድቃን በጸጋ የሚያገኙት ምስጋና ሁሉ መሠረቱ እርሱ መሆኑን ያስረዳል። ያለ እርሱ የባሕርይ ቅድስና የእኛ የጸጋ ቅድስና ዋጋ የማይኖረው በመሆኑ፣ እርሱ ቅዱስ ሆኖ እኛም ቅዱሳን እንድንባል መንገድ የከፈተልንና ለክብራችን ሁሉ ቀዳሚ መሠረት የሆነልን ታላቅ በኩራችን ነው። "ስብከታችን ከንቱ" የማይሆነውም እርሱ በከፈተልን የቅድስና መንገድ ተጉዘን የዘላለም ሕይወት ክብር ተካፋዮች ስለሆንን ነው።
በትንሣኤው ደግሞ ሞትን ድል አድርጎ በመነሣት ለሰው ልጅ ሁሉ የትንሣኤን ተስፋ አብስሯል። "አሁን ግን ክርስቶስ ላንቀላፉት በኵራት ሆኖ ከሙታን ተነሥቷል" (1ኛ ቆሮ. 15፥20) ተብሎ እንደተጻፈው፣ እርሱ መቃብርን በመስበር ቀዳሚ በመሆኑ እኛም በእርሱ በኵርነት ከሞት ለመነሣትና የሞትን መውጊያ ለማሸነፍ ጽኑ መተማመኛ አገኘን። ሐዋርያው "ክርስቶስ ካልተነሣ እምነታችን ከንቱ ናት" ማለቱ፣ የክርስቶስ የትንሣኤ በኵርነት ከሌለ ሞት የመጨረሻችን፣ ተስፋችንም የጨለማ ይሆን እንደነበር ለማሳሰብ ነው። አሁን ግን እርሱ በመነሣቱ እምነታችን ሕያውና ድል አድራጊ ሆኗል።
በመጨረሻም መንግሥተ ሰማያትን በመክፈት ረገድ ክርስቶስ በኵር ሆኖልናል። ነፍሳትን ከሲኦል አውጥቶ፣ ምርኮን ማርኮ፣ ወደ ገነት ቀድሞ በመግባት ለእኛ የዘላለም መኖሪያን አዘጋጀልን። አዳም ከገነት ከወጣ ጀምሮ ተዘግቶ የነበረውን የምሕረት በር የከፈተልንና ወደ አብ ቤት የመራን እርሱ ራሱ በመሆኑ፣ የእኛ ስብከትና እምነት ፍሬው መንግሥተ ሰማያት መሆኑን ያረጋግጣል። ስለዚህ በትንሣኤው በኵር የሆነልን ክርስቶስ፣ እምነታችንን ከከንቱነት አውጥቶ ወደ ዘላለም ሕይወት ሙላትና ወደ ሰማያዊው ርስት አሸጋግሮናል።
በአጠቃላይ፣ የሐዋርያው የቅዱስ ጳውሎስ ቃል እንደሚያስረዳን የክርስትና እምነትና የስብከታችን ሁሉ ትርጉም የሚገኘው በጌታችን ትንሣኤ ውስጥ ነው። ክርስቶስ "ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ" እንዳለ፣ እርሱ ራሱ መንገዱም በሩም ሆኖ ከሞት ወደ ዘለዓማዊ ሕይወት መርቶናል። ይህ ባይሆን ኖሮ እምነታችን መሠረት የሌለው፣ ተስፋችንም በመቃብር የሚቀጭ ከንቱ አምልኮ ይሆን ነበር። አሁን ግን በትንሣኤው በኵርነቱ አማካኝነት የሞት ሰንሰለት ተበጥሶ የሕይወት ብርሃን በርቷል።
ስለሆነም፣ እኛም በእርሱ በኵርነት ታጅበን፣ ከፍጥረት ጀምሮ እስከ መንግሥተ ሰማያት ያለውን የክብር መንገድ ለመውረስ በቅተናል። የትንሣኤያችን በኵር ክርስቶስ ነውና፣ ስብከታችን በሕያው ቃል፣ እምነታችንም በጽኑ መሠረት ላይ ቆሟል። እርሱ ሞትን በሥልጣኑ ድል አድርጎ በመነሣቱ፣ እኛም በእርሱ ትንሣኤ እውነተኛውን ሕይወት አግኝተናል፤ ተስፋችንም ለዘለዓም ለምልሟል።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!

No comments:
Post a Comment