በቀሲስ ያሬድ መለሰ
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ፋሲካችን ክርስቶስ ታርዶልናል” በማለት ያወጀው በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን የታየውን የምግባር መጓደልና የኃጢአት “እርሾ” ለመገሰጽ የተነገረ መንፈሳዊ መመሪያ ነበር። አይሁድ ለፋሲካ በዓል ዝግጅት ሲያደርጉ ቤታቸውን ከአሮጌ እርሾ እንደሚያጸዱ ሁሉ፣ ክርስቲያኖችም አማናዊው የፋሲካ በግ ክርስቶስ ስለ እነርሱ መታረዱን አውቀው ሕይወታቸውን ከክፋትና ከኃጢአት እርሾ ሊያነጹ እንደሚገባ መክሮቸዋል። ይህ ኃይለ ቃል ክርስቲያናዊ ሕይወት በሥጋዊ መብልና መጠጥ ብቻ ሳይሆን፣ በቅድስናና በንጽሕና ሊከበር የሚገባው የነጻነት በዓል መሆኑን የሚያበስር የምስራች ነው።
ይህ ጥቅስ ከብሉይ ኪዳን ጋር ያለው ዝምድና እጅግ ጥልቅ ነው። በግብጽ ባርነት ለነበሩት እስራኤላውያን ከሞት መልአክ መትረፊያና ወደ ተስፋይቱ ምድር መሻገሪያ የሆነው የፋሲካ በግ የክርስቶስ ጥላና ምሳሌ ነበረ። በብሉይ ኪዳን የበጉ ደም በመቃን ላይ ተቀብቶ እስራኤልን ከሥጋዊ ሞት እንደታደገ፣ በአዲስ ኪዳን ደግሞ የእግዚአብሔር በግ የተባለው ክርስቶስ በመስቀል ላይ ታርዶ በፈሰሰው ደሙ የሰውን ልጅ ሁሉ ከዘለዓለም ሞትና ከሰይጣን ባርነት ነጻ አውጥቶታል(ዘጸ. 12፥12-13)። ስለዚህም ትንሣኤው ጥላው ተወግዶ እውነቱ የተገለጠበት፣ የብሉይ ኪዳን ትንቢትና ምሳሌ በክርስቶስ መሥዋዕትነት ፍጻሜ ያገኘበት ታላቅ የታሪክ ምዕራፍ ነው።
“ፋሲካ” የሚለው ቃል ቀጥተኛ ትርጉሙ “ማለፍ” ማለት ሲሆን፣ መነሻውም እግዚአብሔር እስራኤላውያንን ከግብጽ ባርነት ነጻ ባወጣበት ታላቅ ታሪክ ላይ የተመሠረተ ነው። በዚያች ሌሊት እስራኤላውያን እንከን የሌለበትን በግ አርደው ደሙን በቤታቸው መቃን ላይ እንዲቀቡ ታዘው ነበር፤ ይህም የሆነው የሞት መልአክ በግብጽ በኩር ላይ ሁሉ ሞትን ሲያመጣ፣ ደሙ የተቀባባቸውን የእስራኤል ቤቶች ግን “አልፎአቸው” እንዲሄድ ነው። ያ በግ መታረዱ እስራኤላውያንን ከሥጋዊ ሞት ከመታደጉም በላይ፣ ለዘመናት ቀንበር ሆኖባቸው ከነበረው የፈርዖን ጨካኝ አገዛዝ ነጻ እንዲወጡ በር ከፍቶላቸዋል። ይሁን እንጂ ይህ በብሉይ ኪዳን የተፈጸመው ታሪክ በራሱ ፍጻሜ ሳይሆን፣ ወደፊት ለሚመጣው መለኮታዊ ድኅነት እንደ ጥላና ምሳሌ የሚያገለግል ነበረ። በጉ መታረዱ እስራኤልን ለጊዜው ከሥጋዊ ባርነት ቢያወጣቸውም፣ የሰውን ልጅ ከዘለዓለም ሞትና ከኃጢአት ባርነት ሊያድን የሚችል ግን አልነበረም። ስለዚህም ያ ምሳሌያዊ በግ እውነተኛውና አማናዊው የፋሲካ በግ ለሆነው ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መንገድ ጠራጊ ነበረ። መጥምቁ ዮሐንስ ጌታችንን ሲያይ “እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ” (ዮሐ. 1፥29) በማለት የመሰከረው፣ ያ በጥላ ሲጠበቅ የነበረው እውነተኛ መታረድ በእርሱ እንደሚፈጸም ለማብሰር ነው።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እኛ “ታረደ” ሲባል፣ እንደ ማንኛውም ፍጥረት በሁኔታዎች ተገፋፍቶ ወይም በግዴታ ሳይሆን፣ ዓለም ሳይፈጠር በነበረው መለኮታዊ ምክር መሠረት ራሱን በፈቃዱ አሳልፎ መስጠቱን የሚያሳይ የታላቅ ፍቅር መግለጫ ነው። ይህ መሥዋዕትነት የሰው ልጅ በኃጢአቱ ምክንያት የገባበትን የሞት ዕዳ ለመክፈል የቀረበ አማናዊ ዋጋ ሲሆን፣ የፈሰሰው ደሙም ከጨለማው ግዛት ወደ ብርሃኑ መንግሥት የገዛንበት የቤዛነታችን ማኅተም ነው። ቅዱስ ጳውሎስ “በውድ ልጁም እንደ ጸጋው ባለጠግነት መጠን በደሙ የተደረገ ቤዛነታችንን አገኘን፤ እርሱም የኃጢአት ሥርየት ነው” (ኤፌ. 1፥7) በማለት እንደገለጸው፣ የክርስቶስ መታረድ ተራ ሞት ሳይሆን፣ የሰው ልጅ ባሕርይ ከነበረበት የኃጢአት እድፍ ታጥቦ የቅድስናን ልብስ የለበሰበትና በመለኮታዊ ጸጋ የተከበረበት ድንቅ ምስጢር ነው። ይህ የፍቅር መሥዋዕትነት እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ያለውን የማይመረመርና ጥልቅ የሆነ ምሕረት ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው። “እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና” (ዮሐ. 3፥16) ተብሎ እንደተጻፈው፣ የክርስቶስ መታረድ በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ተከፍቶ የነበረውን የጥል ግድግዳ አፍርሶ ዓለምን ሁሉ ከገሃነም ባርነት ወደ ዘለዓለም ሕይወት ያሻገረ የማይናወጥ ድልድይ ሆኗል። በእርሱ መታረድ ምክንያት ሞት መሸነፊያነቱ ቀርቶ ወደ መንግሥተ ሰማያት መግቢያ በር ሆኗል፤ የሰው ልጅም ከመሬት በታች ካለው የሲኦል እስራት ወጥቶ በክርስቶስ ትንሳኤ አማካኝነት የሰማያዊው ርስት ወራሽ ለመሆን በቅቷል።
ፋሲካችን ክርስቶስ ስለ እኛ የታረደው ለሥጋዊ መብልና መጠጥ ሳይሆን፣ እኛም እንደ እርሱ በቅድስናና በንጽሕና እንድንኖር አዲስ የሕይወት መሠረት ለመጣል ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ፋሲካችን ክርስቶስ ታርዶልናልና፤ ስለዚህ በቅንነትና በእውነት ቂጣ በዓሉን እናድርግ እንጂ በአሮጌ እርሾ በክፋትና በክፉነት እርሾም አይደለም” (1 ቆሮ. 5:6-8) በማለት ያስተማረው፣ ክርስቲያናዊ በዓል ከውስጥ ማንነት መለወጥ ጋር የተያያዘ መሆኑን ለማሳወቅ ነው። እዚህ ላይ “ቂጣ” የተባለው በምሳሌነት ነው፤ ቂጣ እርሾ እንደሌለበት ሁሉ፣ በትንሣኤው ብርሃን የታጠበ ክርስቲያንም ሕይወቱ ከኃጢአት እርሾ የጸዳ ሊሆን ይገባል። ይህ “አዲሱ ሊጥ” በክርስቶስ ቤዛነት የተፈጠረ አዲስ ማንነት ሲሆን፣ ይህም በደሙ የታጠብን ምእመናን ሁሉ ከድሮው የክፋትና የኃጢአት ልምምድ ወጥተን በቅድስና መመላለስ እንዳለብን የሚያሳስብ መንፈሳዊ ለውጥ ነው። ስለሆነም ፋሲካን ስናከብር ትልቁ ትኩረታችን ሊሆን የሚገባው በሥጋዊ ዝግጅት ላይ ብቻ ሳይሆን፣ ልባችንን ከኃጢአት “አሮጌ እርሾ” በማጽዳት ላይ ነው። “እርሾ” የተባሉትና የሰውን መንፈሳዊ ሕይወት የሚያመረቅዙት እንደ ጥላቻ፣ ዘረኝነት፣ ምቀኝነት፣ ክፋትና በቀል ያሉት አሮጌ ጠባዮች ከውስጣችን ተወግደው በምትካቸው የፍቅርና የእውነት ፍሬዎች ሊተኩ ይገባል። ክርስቶስ ለዓለም ሁሉ ቤዛ ሆኖ የታረደው የሰውን ልጆች ሁሉ በፍቅር አንድ ለማድረግ እንደ መሆኑ፣ እኛም ይህን ታላቅ በዓል ስናከብር ቂም የያዝንባቸውን ይቅር በማለት፣ የተጣሉትን በማስታረቅና በወንድማማችነት ፍቅር በመኖር ሊሆን ይገባል። እውነተኛው የበዓል ደስታ የሚገኘው በአዲስ መንፈስ ተለውጠን፣ በልባችን መቅደስ ውስጥ ለክርስቶስ ስፍራ ስንሰጠውና በቅንነትና በእውነት ብርሃን ውስጥ ስንመላለስ ብቻ ነው።
ታላቁ የቤተክርስቲያን ሊቅ ቅዱስ ያሬድ በድጓው ላይ” ሃሌ ሉያ ይትፌሣሕ ሰማይ ወትትሐሰይ ምድር፤ ወይንፍሑ ቀርነ መሠረታተ ሕምዝ፤ወይወውዑ አድባር ወአውግር ወኲሉ ዕፀወ ገዳም፤ ወዮምሰ ዓባይ ፍስሐ በሰማያት፤ወምድርኒ ትገብር ፋሲካ፤ ተሐጺባ በደመ ክርስቶስ።” (ሰማያት ደስ ይበላቸው፣ ምድርም ሐሴትን ታድርግ፤ የምድር መሠረቶችም መለከትን ይንፉ፤ ተራሮችና ኮረብቶች፣ የዱር ዕፅዋትም ሁሉ እልል ይበሉ። ዛሬ በሰማያት ታላቅ ደስታ ነው፤ ምድርም በክርስቶስ ደም ታጥባ ፋሲካን (በዓልን) ታደርጋለች) በማለት እንደዘመረው፣ የክርስቶስ ትንሣኤ መላውን ፍጥረት ያዳረሰ ዓለም አቀፋዊ ድል ነው። ይህ ድል ክርስቶስ በሞቱ ሞትን የገደለበትና በመቃብር ውስጥ ለነበሩት ሙታን ሁሉ የሕይወትን ብርሃን ያበሰረበት በመሆኑ፣ ለሰው ልጅ ብቻ ሳይሆን ለፍጥረት ሁሉ የታደሰ ተፈጥሮን ሰጥቷል። ትንሳኤው ተስፋ ለቆረጠው አዳም የሕይወት ተስፋን፣ በሞት ጨለማ ለተዋጠው ዓለም ደግሞ መለኮታዊ ብርሃንን የፈነጠቀ ታላቅ ምስጢር ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ “ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን በመነሣቱ ለሕያው ተስፋና ለማይጠፋ ርስት ሁለተኛ የወለደን አምላክ ይባረክ” (1 ጴጥ. 1፥3) እንዳለው፣ ትንሳኤው እኛን ከሞት ባርነት አውጥቶ የሰማያዊው ርስት ወራሾች ያደረገን ድንቅ የመለኮት ሥራ ነው። በመሆኑም ፋሲካን ስናከብር ይህንን የክርስቶስን ዓለም አቀፋዊ ፍቅር በተግባር በመግለጥ የክርስትና ተልዕኳችንን ልንወጣ ይገባል። ክርስቶስ በመስቀል ላይ እጆቹን ዘርግቶ የሰውን ልጆች ሁሉ እንደታደገ፣ እኛም ዘር፣ ቋንቋና ብሔር ሳይለየን ሁላችንም በአዳም ወገን አንድ መሆናችንን በማሰብ በፍቅር ልንመላለስ ይገባል። እውነተኛ የበዓል አከባበር የተጣሉትን በማስታረቅ የሰላም ሰዎች ስንሆን፣ የተራቡትን በማብላትና የተጠሙትን በማጥጣት የክርስቶስን ርኅራኄ ለዓለም ስናሳይ ብቻ ነው። “ፋሲካችን ክርስቶስ ታርዶልናል” ስንል ነጻነታችንን ማወጃችን ስለሆነ፣ እኛም ከኃጢአት መቃብር ወጥተን በፍቅርና በቅድስና ልብስ ተውበን ለትንሳኤው ብርሃን ሕያው ምስክሮች በመሆን ለዓለም ሁሉ የምስራቹን ልናበስር ይገባል።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

No comments:
Post a Comment