ስብከት



‹‹በእውነት እኔ ከአንተ ጋር እሆናለሁ›› ዘጸ. 2፥12
እግዚአብሔር በልዩ ልዩ መንገድ ሰዎችን ወደ እርሱ ይጠራል በልዩ መንገድም የራቁትን ይሰበስባል የተሰደዱትንም ይጠብቃል በባርነት በምርኮም ያሉትን ነጻ ያወጣል፡፡ ይህንንም በሰዎች አማካኝነት ይሰራል የመረጣቸውን ሰዎችም እርሱ ክብርና ሥልጣን ይሰጣል፡፡
እግዚአብሔር እስራኤል ዘሥጋ ለአራት መቶ ሠላሳ ዓመታት በበባርነት ከኖሩት ምድረ ግብጽ ነጻ ሊያወጣቸው ባሰበ ጊዜ በፈርዖን ቤት የእናቱን ጡት እየጠባ ያደገውን ሙሴን መረጠ፡፡ ዘጸ. 3፥9 እግዚአብሔር ሕዝቤ የሚላቸውን ፍጥረታቱን(ሕዝብና አእዛብ) ከባርነት አውጥቶ ከሲኦል እስራት ፈቶ ከጥፍት ወደ ሕይወት መንገድ ሊያሸጋግራቸው ከጥንተ ጠላቻቸው ዲያቢሎስ ነጻ አውጥቶ ልጆቹ ሊያደርጋቸው ቢነሣም ሰዎች ግን ሰብዓዊ ደካማ አስተሳሰባቸው ብቻ እየመዘኑ እንደማይቻል ያስባሉ፡፡
በሰው ደካማ አስተሳሰብ ፈርዖን በኮልታፋው ሙሴ ፊት አስፈሪ ነው፡፡ ይህ ግን በሙሴ እይታ ነው የእኛም እይታም ሊሆን ይችላል፡፡ ሰዎች ስልጣንን የላይኛውን እይታን ስለምንመለከት ሙሴም ይህን ሰፍሮና መዝኖ ‹‹ወደ ፈርዖን የሚሄድ የእስራኤልን ሕዝብ ነጻ የማወጣ እኔ ማን ነኝ?›› ሲል ፍርሃቱን ገለጠ፡፡ ሰዎች ወደ ሃይማኖት ለመሳብ በቅድስና እንዲመለሱ ለማድረግ ለመገሰጽና ከእስራታቸው እንዲፈቱ ለማድረግ የላዩን ስለምንመለከት እንፈራለን፡፡ ከሁሉ በላጭ የሆነውን ኃያሉን ጌታ እግዚአብሔርን እንደያዝን ልናስብ እንዲገባን መሆን አለበት፡፡
እግዚአብሔር ሕዝቡን እንዲሰበስብ አርነትም እንዲያወጣ የሚልካቸውን ነቢያቱን ቅዱሳኑንን መምህራኑን ሰባኪያኑን ሐዋርያቱን ሲያሰማራ ፍርሐት በውስጣቸው ነግሦ የተላኩበትን ዓላማ እንዳይዘነጉ በመልእክቱ እኔ ከአንተ ጋር እኖራለሁ ብሎ ኃይል ጉልበት ብርታት ሆኖል፡፡ ከእኛ ሚጠበቀው እግዚአብሔር በሰዎች ልጆች ላይ አድሮ ድንቅ ማድረግ እንደሚችል ማመን ነው፡፡
ቅዱሳን ሐዋርያቱም ሂዱና አእዛብን ሁሉ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችሁ ደቀመዛሙርቴ አድርጎቸው ባላቸው ጊዜ ከእነርሱ ጋር ለዘለዓለም እኖራለሁ ብሎ በማይታበይ ቃሉ ተናግሮል፡፡ ሐዋርያቱም ለአገልግሎት ሲወጡ እርሱ ከእነርሱ ጋር ስለነበር ድውያንን ሲፈውሱ ሳይፈሩ ሳያፍሩ ስለክርስቶስ ሲመሰክሩ አእዛብን ሲያሳፍሩ ሕዝቡን ስያጸኑ ሲያጸናኑ እናያለን ይህ ሁሉ የሆነው ታዲያ እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር ስለነበረ ነው፡፡
ለነቢያት ለሐዋርያት የተሰጠው ጥብዓት ጽናት ጥበብ አሁንም ፍኖተ ሐዋርያትን ተከትለው ሕዝቡን ለሚያስተምሩ በሐዋርያዊ ኑሮና አስተሳሰብ ከሚወጡት ጋር እግዚአብሔር ከፊት እየቀደመ አንደበት ኃይል ጉልበት ይሆናቸዋል፡፡
አገልግሎትና ፍርሃት
ቅዱስ እግዚአብሔር እርሱን እንዲያገለግሉ ለተመረጡ ሁሉ ብርታት እንደሚሆን ተናግሮል ይህን ያመኑ ነቢያት ሐዋርያት ሰማዕታት ጻድቃን ስላመኑበት ነገር በተጋድሎ ያለፍርሃት ሰብከዋል አስተምረዋል ነገሥታቱ ፊት አስተምረዋል፡፡ የሚመጣባቸው መከራ ጽኑ ቢሆንም እንኳን እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር ነበርና እንበለ ፍርሃት መስክረዋል፡፡ ከእነዚህ አበው ክርስቲያን ሊማር የሚገባው ቁም ነገር እግዚአብሔር ጎዶሎችንን እንደሚሞላ ጌታ በአገልግሎታችን ከፊት እንደሚቆም አምነን መነሳት እንዳለብን ነው፡፡
ጌድዮን የጌታን ጥሪ በሰማ ጊዜ ታናሽነቱንና የተናቀ መሆኑን አውቆ እንዴት ይሆናል አለ(መሳ. 6፥ ) ኢሳይያስ ግን ጉድለቱን(በለምጽ መመታቱን እንኳን) እያወቀ ጌታ እግዚአብሔር ማንን እልካለሁ ባለጊዜ እኔን ላከኝ አለ(ኢሳ. 6፥1-) ኢሳይያስ በለምጽ የነጻው ሐብተ ትንቢቱ የተመለሰው እግዚአብሔር አምላክ ፊት ባሳየው የአገልግሎት መታመን ነው፡፡ በባዕድ ሃገር በምርኮ ሳለች ስለእግዚአብሔርና ስለ ኤልሳዕ የመሰከረችው አንዲት ብላቴና (1ኛ ነገ. 5፥1) ምንኛ ድንቅ ናት፡፡ የእግዚአብሔርን አዳኝነት ለሰው ለመመስከር የግድ መጽሕፍትን መጠንቀቅ አያስፈልግም፡፡ እርሷም ለሁሉ የነቢዩን ድንቅ ማድረግ መሰከረች ፡፡ እግዚአብሔርም ድካሞን አገዛት የንጉሡን የንዕማንን ልብ ወደ ቀናው መንገድ መለሰ፡፡ እነዳንአኤል እነ ሠለስቱ ደቂቅ ሐዋርያቱ የእርሱን ድንቅ ሥራ ለመመስከር አልቦዘኑም፡፡ በብዙ መከራ ውስጥ እንኳን ለኃያሉ ለጌታ ታመኑ፡፡ ይህም ምን ያህል እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር እንደነበር የሚያመለክት ነው፡፡
እግዚአብሔር ድካማችንን ሊያግዝ የታመነ ነው፡፡
በዚህ ዘመን እግዚአብሔርን የምናገለግል የእርሱ አገልጋዮች አስቀድመን እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ሊሆን የሚችልበት ሕይወት ያስፈልገኛል፡፡ ለምስክርነት በመጣደፍ ያልኖርንበትን ሕይወት ለሰዎች ማሰስተማር የሚከብድ ነውና ቅድሚያ በተማሩት ትምህርት መኖር ይገባል፡፡ እግዚአብሔርን አስቀድመን የምናገለግልበት ወቅት ለሙሴ በገባው ቃል መሠረት ለመዝራት የተጋን የዘራነውን ለማጨድም የተጋን ያደርገናል፡፡ ሊቀ ነቢያት ሙሴ በእግዚአብሔር እንዲመረጥ ያበቃው ቀድሞም ቢሆን የእስራኤል መጨቆን ይንገበግበው ስለነበር ነው፡፡ መቆጨቱን አይቶ መሪ ይሆን ዘንድ መረጠው በድካሙም አገዘው ይህም ብቻ አይደለም ድንቅን አደረገ ባሕር አሻገረ ይህ በአእግዚአብሔር እርዳታ እንጂ ያለእርሱማ ሙሴ ብቻው አንዳች ሊያደርግ አይቻለውም፡፡ ሙሴን ጌታ ሲጠራ የጠራው በእስተእርጅና መሆኑን አስተውሉ ይህም ምንም እንኳን ማድረግ በማንችል ጊዜ እግዚአብሔር ከፊት እየቀደመ እልፍ ማድረግ እንደሚቻለው ነው፡፡
አምላከ ሙሴ ዛሬም በእጆቹ ድንቅን ይሰራል፡፡ በቁጭት በእንባ የአብያተ ክርስትያን ነገር የሚያሳሰስባቸውን ሊረዳ የታመነ ነው፡፡ የወገኖቻችን ከእግዚአብሔር እቅፍ መለየት ቢያሳስበን ከቤተ እግዚአብሔር መራቃቸው ቢያስቆጨን እናገለግላቸው ዘንድ ‹ከአንተ ጋር እኖራለሁና ሂድ› ብሎ በማይታበይ ቃሉ ለአገልግሎት ያበረታናል፡፡ ሕዝቡ ስደተኛ ሆነው እንዳይኖሩ ከኃጢያት ባርነት እንዲርቁ ጽድቅን እንሰብክላቸው ዘንድ የንስሐውን መንገድ እንመራቸው ዘንድ ከነቢያቱ ጋር እንደነበር ከሐዋርያቱ ጋራ እንደነበር ዛሬም ለዘለዓለም ከእኛ ጋራ ከአገልጋዮቹ ጋራ ይኖራል፡፡ ከእኛ የሚጠበቀው በመንፈሳዊ ምግባራት በተጋድሎ በክርስቲያናዊ ሕይወት ማመን በቃሉም መታመን ነው፡፡
የእግዚአብሔር ምስክሮቹ እንሆን ዘንድየአምላካችን የእመቤታችን ምልጃዋ ይርዳን
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

No comments:

Post a Comment