Saturday, 24 December 2016

ነገረ ሃይማኖት ክፍል አንድ


ዶግማ ክፍል አንድ

ሰላም በዛሬዉ የነገረ ሃይማኖት ትምህርት የዶግማ ምንነት እንዲሁም የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዶግማ(መሠረተ እምነት) ምንጮች ምን እንደሆኑ እናያለን መልካም ንባብ


ዶግማ(መሠረተ እምነት) ምንነት
ዶከይን ከሚለው የግሪክ ቃል የተገኘ ሲኾን በጥሬው አመለካከት፣ አስተሳሰብ፣ አዋጅ ማለት ቢኾንም በምሥጢራዊ ትርጓሜው ግን ሃይማኖት (የእምነት መሠረት) ማለት ነው፡፡ በመኾኑም ዶግማ የተደነገገ ሳይኾን የተገለጠ ነው፡፡ መገኛውም እግዚአብሔር ነው፡፡ ከሰው ሊፈጠር አይችልም፡፡ ከእግዚአብሔር የተሰጠ እውነት ነው፡፡ በማኝኛውም አካል (በሲኖዶስም ጭምር)፣ በየትኛውም ዘመን፣ በየትኛውም ኹኔታ (በሞትም በሕይወትም) የማይለወጥ ማንነት አለው፡፡
በማንም የማይለወጥ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፡- “ነገር ግን (ሐሳባችንን ቀይረን) እኛ ብንኾን ወይም ከሰማይ መልአክ ከሰበክንላችኁ ወንጌል የሚለይ ወንጌልን የሚሰብክላችኁ የተረገመ ይኹን” ያለውም ስለዚኹ ነው /ገላ.1፡8/፡፡
ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን መሠረተ እምነት(ዶግማ) ስንል ቤተ ክርስትያን ስለነገረ እግዚአብሔር ስለነገረ መላእክት ስለነገረ ቅዱሳን ስለሕይወት ስለሰው ያላት አስትምህሮ(ትምህርት) ብቻ አይደለም የምንኖርበት ጭምር እንጂ፡፡ በሌላ አገላለጽ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዶግማ( መሠረተ እምነት) ስንል በእግዚአብሔር ላይ ያለን እምነት መግለጫ ማለታችን ነው፡፡ ስለዚህም የእኛንና የእግዚአብሔርን ግንኙነት በጉልህ የሚያስረዳ ነው፡፡

የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዶግማ(መሠረተ እምነት) ምንጮች
የእግዚአብሔር መገለጥ
መዝሙረኛው ቅዱስ ዳዊት‹‹ በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ ቡሩክ ነው በእግዚአብሔር ቤት መረቅናችሁ ጌታ እግዚአብሔር ተገለጠልን እስከ መሠዊያው ቀንዶች ድረስ በሚያስተነትኑበት በደስታ በዓል አደረጉ›› ይላል (መዝ 117÷26-27) የክርስትና መሠረትም በመዝሙሩ ላይ እንደተገለጠው የጌታ እግዚአብሔር መገለጥ ነው፡፡
እግዚአብሔር ራሱን በፍጥረቱ ለፍጥረቱ ይገለጣል፡፡ እግዚአብሔር ግብሩን በፍጥረቱ ማወቅ ቢቻልም ግን ባሕርዩን ጠቅልለን መራዳት አይቻልም፡፡እግዚአብሔር ፈጣሪ ዓለማት ሆኖ በፈጠረው ሰው ይመረመር ዘንድ እንዴት ይቻላለዋል? ነገር ግን እግዚአብሔር በየዘመናቱ ራሱን ለሰው ልጆች ገልጦል፡፡ እግዚአብሔር በግብሩ (በሥራው) ለሁሉ ይገለጣል ከዚህ በተጨማሪ ለቅዱሳኑ ለሊቀ ነቢያት ሙሴ እገዚአብሔርን 570 ጊዜ ያህል ተገልጦ አናግሮታል(ዘኁ 12÷5) ለቅዱሳኑም ለሄኖክ መዓዛ ባለው እንጨት ለአብርሃም በሦስት ሰዎች አምሳል ለኖኅ በቀስተ ደመና ለያዕቆብ በመሰላል ከፍታ ላይ ለኢሳይያስ በዙፋኑ ተቀምጦ ለዕዝራ በአንበሳ አምሳል ለዳንኤል በሽበታም ሰው አምሳል ተገልጦል፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም ይህንን በተመለከተ ሲናገር ‹‹ እርሱ እንደመረዳታችን መጠን ተገለጠ(አስተማረን) ስንል እርሱ ራሱ እንደኛ ነው ማለታችን አይደለም፡፡ እርሱ በእኛ አምሳል ተገለጠ አልተገለጠ እርሱ ራሱ ነው አይለወጥም፡፡ ሲፈልግ እኛን ለማስተማር አንዱ ለጠባያችን ተገልጦ ይታያል ሌላ ጊዜ ደግሞ አስቀድሞ የለበሰውን እንደልብስ አውልቆ ሌላ ልብስ ለብሶ ይገለጣል እርሱ ለእኛ በመንገሩ እርሱ እንዲህ ነው ማለት አይደለም ነገር ግን ባሕርይው የማይመረመር ነውና በምንረዳው በእኛ ምሳሌ ተገልጦ ፍቃዱን ገለጠልን›› ብሏል
በኋላም በሐዲስ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ተገልጦ በብሉይ በከፊል ሲገለጥ እንደነበር ሙሉ በሙሉ(በሰው አካል) ራሱን ገለጠልን፡፡ ክርስቶስ ከላይ የጠቀስነውን የቅዱስ ዳዊትን የትንቢት ቃል ፈጸመ፡፡ ለዚህም ነው ሁል ጊዜ በቅዳሴ አገልግሎታችን ቡሩክ ስሙ ለእግዚአብሔር ወቡሩክ ዘይመጽእ በስመ እግዚአብሔር እያልን እግዚአብሔርን የምናመሰግነው መገለጡንም የምናደንቀው፡፡
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዓለም በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ ሲመላለስ ሰዎች ረቡኒ ብለው ይጠሩት እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረኛል ፡፡ ረቡኒ ማለት መምህር ማለት ነው፡፡ ተከታዮቹም ደቀ መዛሙርት ተሰኝተዋል ከሄደበት እየሄዱ ካደረበት እያደሩ ትምህርቱን ሲያደምጡ ስለነበር ክርስቶስ ራሱን ለሰው ልጅ የገለጠው ከእግዚአብሔር የተላከ መምህር እንደሆነ በመግለጥ ነው፡፡ የእግዚአብሔርን ፍቃድ በማስተማር እግዚአብሔርን መንግስት ለዓለም ገለጠ፡፡ (ዮሐ 1÷18) የክርስቶስ እንደመምህርም መገለጥ ይመጣል ብለው የሚጠብቁት መሲሕ እርሱ መሆኑን ያመለክታል መሲሕ መምህር ማለት ነውና፡፡(ኢሳ 54÷13 ዮሐ 6÷45)
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሰው ራሱን የገለጠው መለኮታዊ መምህር ሆኖ ነው፡፡ የእርሱ ቃል የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን ገልጦ አስተምሯል፡፡ ሲያስተምርም ለአይሁድ የማስተማርም ለመገሰጽም ባለስልጣን እንደሆነ ይገልጥላቸው ነበር፡፡ ‹‹እንደጸሐፍቶቻቸው ሳይሆን እንደባለሥልጣን ያስተምራቸው ነበር›› (ማቴ 7÷29)
ዮሐ 12÷44-50
‹‹በእኔ የሚያምን በላከኝም ነው እንጂ በእኔ ብቻ የሚያምን አይደለም እኔን ያየ የላከኝን አየ፡፡ በእኔ የሚያምን ሁሉ በጨለማ እንዳይኖር ብርሃን እኔ ወደ ዓለም መጣው፡፡ ቃሌን ሰምቶ የማይጠብቀውን እኔ የምፈርድበት አይደለሁም እኔ ዓለምን ላላድን እንጂ
በዓለም ልፈርድ አልመጣሁምና፡፡የሚክደኝን ቃሌን የማይጠብቀውን ግን የሚፈርድበት አለ እኔ የተናገርኩት ቃል እርሱ በመጨረሻይቱ ቀን ይፈርድበታል፡፡ የተናገርኩት ቃል ከእኔ አይደለምና ነገር ግን የላከኝ አብ አንድናገር እንዲም እንድል እርሱ ትእዛዝን ሰጠኝ››
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቃል ብቻ አላስተማርም በተግባር እያሳየ ጭምር እንጂ፡፡ እርሱንም ለሰው ልጅ በእውነት ገለጠ(ዮሐ 14÷6) እውነትና ብርሃን መሆኑን አስተማረ(ዮሐ 8÷12) ሕግንም እየፈጸመ በጥቂቱ አደገ፡፡

ዮሐ 1÷1-5
‹‹በመጀመርያ ቃል ነበረ ቃልም እግዚአብሔር ዘንድ ነበረ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ፡፡ ይህም በመጀመርያ እግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፡፡ ሁሉም በእርሱ ሆነ ከሆነውም ሁሉ ያለእርሱ ምንም የሆነ የለም፡፡ ሕይወት በእርሱ ነበረ ሕይወትም የሰው ብርሃን ነበረ ብርሃንም በጨለማ ያበራል ጨለማም አላገኘውም፡፡››
ዮሐ 1÷14-18
‹‹ያም ቃል ሥጋ ሆነ በእኛ አደረ ለአባቱም አንድ እንደሆነ ልጅ ክብር ያለ ክብሩንአየነ ጸጋና እውነትን የተመላ ነው፡፡››
አካላዊ ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውልጅን በቃል ትምህርተና በተግባሩ አርአያ ሆነው፡፡ ይህን እርሱ ያስተማረውን ወንጌል እንለዋለን የምስራች ለዓለም ሁሉ የሚሆን የእግዚአብሔር መንግስት የምስራች ነው፡፡ሐዋርያትንም የክርስቶስን የምስራች ቃል ለዓለም ሰበኩ(ማቴ 28÷19) ዓለምን ይሰብኩ ያስተምሩ ዘንድ በዓለም ይፈርዱ ዘንድ መንፈስ ቅዱስን ልኮ አሰማራቸው፡፡(ዮሐ 15÷6)
በኦርቶዶክዊት ቤተ ክርስቲያን በሐዋርያት ትምህርት ጸንተን የምንኖር ናት ሐዋርያዊት መባሏም ለዚህ ነው፡፡(ሐዋ 2÷42) ይህም የሐዋርያት ትምህርት ለቅድስት ቤተ ክርስትያን ዶግማ የቤተ ክርስቲያኒቱ አስተምህሮ መመሪያ ወይም ትምህርት ነው፡፡ ይህም የሐዋርያት ትምህርት የጌታችን የመድኃኒተችን የኢየሱስ ክርስቶሰ ትምህርት ነው፡፡ በዚህ ትምህርት(ዶግማ) ዓለም ሁሉ የሚድንበት ዓለም የእግዚአብሔርን መንግስት የሚወርስበት እውነተኛ ቃል ነው፡፡
ስለእግዚአብሔር መገለጥ ስናወራ በብሉይ እግዚአብሔር ሕዝቤ ብሎ የሚጠላቸው እስራኤል ዘሥጋ ራሱን ይገልጥ እንደነበር ማንሳቱ ተገቢ ነው፡፡ በብሉይ እንደምናየው የነበረው መገለጥ በነቢያቱ ላይ እያደረ በኅድረት ተዋሕዶ በትንቢት በራዕይ በሕልም እየተገለጠ ሕዝቡን ያስተምር ነበር፡፡ ይህ የነቢያቱ ትንቢትና ምሳሌ ፍጻሜው የመሲሑ መምጣት ነው፡፡

ይህም የእግዚአብሔር መገለጥ የቅድስት ቤተ ክርሰትያን ዶግማ(መሠረተ እምነት) መሠረት ነው፡፡

No comments:

Post a Comment