Wednesday, 28 December 2016

ዓለም አቀፍ ጉባኤያት


ዓለም አቀፍ ጉባኤያትና አብያተ ክርስቲያናት በኦርቶዶክሳዊ ቅኝት

ጉባኤ ኒቅያ
የአርዮስ ኑፋቄ

ወልድ ባልነበረበት ጊዜ አብ ነበረ አብ ወልድን ከምንም ፈጠረና የእግዚአብሔር ልጅ እንዲሆን አደረገው ይህም መለት እግዚአብሔር አብ ወልድን እንደማንኛውም ፍጥረት ፈጥሮታል በኋላም ሥልጣን ስለሰጠው ፈጥሮ ፈጥሮበታል ብሎ አስተማረ፡፡
ፈጥሮ ፈጠረበት?
ለዚህ ትምህርቱ መነሻ የሆነው ኃይለ ቃል ምሳ 8፥26 ትቤ ጥበብ ፈጠረኒ መቅድመ ኩሉ ተግባሩ ጥበብ ከፍጥረታት ሁሉ እስቀድሞ እኔን ፈጠረችኝ በማለት ጥበብ የተባለ ወልድ ነው ብሎ አስታማረ
የአርዩስ ትምህርት የተቀዳው ከማን ነው?
አርዩስ ትምህርቱን የቀዳው ከፈላስፎቹ አፍላጦንና አሪስጣጣስ ሲሆን እነዚህ ፈላስፎች ዓለም የተፈጠረው በራሱ በእግዚአብሔር በቀጥታ ሳይሆን እግዚአብሔር በፈጠራቸው መናፍስት ወይም ኃይሎች አማካኝነት ነው ብለው አስተምረዋል፡፡ ይህን ትምህርት አርዮስ አዲስ ቅርጽ በማስያዝ መናፍስት ያሏቸውን ክብር ይግባውና ወልድ ነው በማለት የእነዚህን ‹‹ፈላስፎች›› ትምህርት መጽሐፋዊ በማድረግ ብዙዎችን አስቷል፡፡
የአባቶች መልስ
አባቶቻችን ጸሎተ ሃይማኖትን እስከ ሰባተኛው አንቀጽ ድረስ የነገጉት በዘህ ጉባኤ ላይ ነው ይህም ፍጹም መጽሐፋዊና ለመሠረተ እምነታችንን ማሳያ ነው፡፡
ሁሉን የፈጠረ አንድ አምላክ በሚሆን በእግዚአብሔር እናመናለን
ሰማይና ምድርን የፈጠረ የማይታየውንና የሚታየውን ዓለም ሳይፈጠር ከእርሱ ጋር የነበረ
አንድ የአብ ልጅ በአንድ ጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እናምናለን
ከብርሃን የተገኘ ብርሃን ከእውነተኛ አምላክ የተገኘ እውነተኛ አምላክ
የተወለደ እንጂ ያልተፈጠረ በባሕርዩ ከአብ ጋር የሚስተካከል ሁሉ በእርሱ የሆነ
በሰማይም በምድርም ካለው ያለእርሱ ምንም ምን የሆነ የለም
ስለእኛ ስለሰዎች እኛን ለማዳን ከሰማይ ወረደ
በመንፈስ ቅደስ ግብር ከቅድስት ድንግል ማርያም ፍጹም ሰው ሆነ
ደግሞ ስለእኛ ተሰቀለ ሞተ ተቀበረ በሦስተኛው ቀን ከሙታን ተነሣ
በቅዱሳን መጻሕፍት እንደተጻፈ በክብር ወደ ሰማይ ዐረገ፡፡
በአባቱም ቀኝ ተቀመጠ
ዳግመኛም በሕያዋንና በሙታን
ለመፍረድ በምስጋና ይመጣል ለመንግስቱም ፍጻሜ የለውም፡፡


ይህን የጸሎተ ሃይማኖት ክፍል ጥንታዊያን ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ሲጠቀሙት የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት(ከግሪካዊያን ውጪ)ና ካቶሊካዊያን እናምናለን በሚለው ፈንታ አምናለሁ ብለው ቅርጹን ቀይረው ይጠቀሙበታል፡፡ሌላው ልዩነት ከአብ የሰረጸ የሚለውን ካቶሊካዊያኑ ከአብና ከወልድ የሰረጸ ብለው ቀይረውታል፡፡
አባቶች ከአርዮስ ትምህርት በተጨማሪ ከዚህ በተጨማሪ 20 ቀኖናዎች ተንግገዋል፡፡
ጉባኤ ቁስጠጥንጥንያ

በጉባኤው ላይ ትምህርታቸው የተወገዘባቸው መናፍቃን
አቡናርዮስ ዘላዞቅያ ክህደት
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መለኮት የሥጋ በሆነች ነፍስ ብቻ ተተክቶ ሕማምን ስቅለትንና ሞትን ከሥጋ ጋር ተቀበለ ይላል፡፡በዚህ ብቻ አላበቃም መንፈስ ቅዱስ ትልቅ ነው ወልድ ከመንፈስ ቅዱስ ትልቅ ነው አብ ከሁሉ ትልቅ ነው ብሎ አስተምሮል፡፡
የአባቶች መልስ
ጌታ ነፍስ ያላተዋሐደው ነው ወይም በነፍስ ፈንታ መለኮት ከሥጋ ጋር ተዋሐደ ማለት የቤተ ክርስቲያንን የነገረ ድኅነት ትምህርት ጋር የሚጋጭ ነው፡፡ ነፍስ የሌለውን ሥጋ ተዋሕዶ እንዴት የሰው ነፍስን ሊያድን ይችላል ብለው ብለው መልስ ሰጥተዋል፡፡
በሥላሴ መካከል መበላለጥ አለ የሚለው ትምህርት በጉባኤ ኒቅያም ጭምር የተወገዘ ነው፡፡ የጉባኤ ኒቅያ ትምህርት የሆነው ጸሎተ ሃይማኖት ‹‹ከአብ ጋር የሚተካከል ›› የሚለውን አንቀጽ የሚያነብ ሰው በቅድስት ሥላሴ መካከል የሥልጣን ልዩነት እንደሌለ በጉልህ ይረዳል፡፡ ይህ የአባቶች ትምህርት መጽሐፋዊ ሲሆን የመናፍቁ የአቡሊናርዮስ ትምህርት ግን የመጽሐፍ ማስረጃ የሌለው ተራ ክህደት ነው፡፡
የአውሳብዩስ ትምህርት
እንደሰባርዩስ ትምህርት ሦስቱ አካላት በተለያዩ ሁኔታዎች የተገለጡ ናቸው፡ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ የምንለው ሦስቱ አካላት በተለያዩ ሁኔታዎች መገለጥ ነው እንጂ የተለያዩ አካል ያላቸው ሆነው አይደለም፡፡ ይህን ትምህርት በመቅዳት በኦሪት እንደ አብ በሐዲስ እንደ ወልድ በዘመነ ሐዋርያት ደግሞ እንደ መንፈስ ቅዱሰ የተገለጠው አንድ ነው የአካል ሦስትነት የለውም ብሎ አስተማረ፡፡
ይህም ተራ ፍልስፍና ነው አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ፍጽም መልክ ፍጹም ገጽ ፍጽም አካል ያላቸው መሆኑን በሚያመለክት ሁኔታ በማቴ 3፡17 በተለያየ አምሳል በዩርዳኖስ ወንዝ ስለወልድ መመስከራቸው ምስክር ነው፡፡(1ኛ ዮሐ 5፥12)
የመቅዶንዩስ ትምህርት
ይህን ትምህርት ያሰራጨው መናፍቅ የአርዩስ ትምህርት ደጋፊ ነበር፡፡ ጌታችንን የካደውን አርዩስን የሚከተል ሰው መንፈስ ቅዱስን ቢክድ አይደንቅም፡፡ እንዲህም ብሎ ያስተምር ነበር፡፡ መንፈስ ቅዱስ በፍጥረታቱ ሁሉ የተሰራጨ የእግዚአብሔር ፍጡር ነው እንጂ በአብና በወልድ ደረጃ ያለ አይደለም በመላእክት መልክ ተፈጥሮ ከመላእክት ከፍ ያለ ነው ብሎ አስተማረ፡፡
አባቶቻችን የመቅዶንዩስን ትምህርት በማውገዝ የጸሎተ ሃይማኖት ክፍል ላይ ተጨማሪ ስለመንፈስ ቅዱስ የሚያወሱ ክፍሎችን ጨምረዋል፡፡ ይህ ምንፍቅና ተራ ፍልስፍና እንጂ መጽሐፋዊ አይደለም፡፡(1ኛ ዮሐ 5፥12)
የኤፌሶን ጉባኤ
በጉባኤው ላይ ትምህርታቸው የተወገዘባቸው መናፍቃን
ቢላግዩስ
የዚህ ሰው ክህደት የአዳም ኃጢአት ለልጆቹ አልተላለፈም፡፡ አንድ ሰው በሚወልድ ጊዜ ኣዳም ከኃጢአት ከመውቁ በፊት እንዳለ ሆኖ ይወለዳል፡፡በዚህም አንድ ሰው ወደ ከፍተኛ የቅድስና ደረጃ የሚደርሰው የእግዚአብሔርን እርዳታ ሳይጠይቅ ነው ብሎ አስተማረ፡፡
ይህ ትምህርት የምሥጢረ ድኅነትን ትምህርት ዋጋ የሚያሳጣ ነው፡፡ አምላክ ሰው ስለምን ሆነ ብለን ብንጠይቅ መልስ ለመመለስ ይቸግረናል፡፡ ምክንያቱም ሁሉም ሰው ከኃጢአት ነጻ ሆኖ ይወለዳል ብሎ ያስተምራልና
መጽሐፍትም ይህን ትምህርት ትክክል እንዳልሆነ ይመሰክራሉ፡፡(መዝ 51፥3 ሮሜ5፥12 1ኛ ቆሮ 15፥22)
ንስጥሮስ
የእግዚአብሔር ቃል ከሁሉ በፊት ነበረ መሆኑን አምናለሁ ማርያም የእምላክ እናት ነች የሚለውን አባባል ግን አላምንም፡፡ የክርስቶስ እናት መሆኗን አልክድም ነገር ግን እናትነቷ ለትስብእት ነው፡፡ ማርያም እግዚአብሔርን አልወለደችም ነገር ግን ከሥጋ የሚወለድ ሥጋ ነው ከመንፈስ የሚወለድ መንፈስ ነው፡፡ ፍጡር ሆና የወለደችው የእግዚአብሔር መሳርያ ፍጡር እንጂ ፈጣሪ አይደለም፡፡ በዚህም የተነሳ ጌታችን ሁለት ጠባይ ሁለት አካልና ሁለት ፍቃድ አለው፡፡ ሰብአ ሰገል ለጌታ መስገዳቸው አግባብ አይደለም ምክንያቱም ሕጻኑ ኢየሱስ ገና መለኮት ያልተዋሐደው ሥጋ ነውና፡፡(ማቴ 2፥11)
የአባቶች መልስ
ቅዱስ ቄርሎስ አባታችን እመቤታችን ወላዲተ አምላክ መባል እንደሚገባት አምላክንም እንደወለደች በጉባኤው ላይ አብራርቶል፡፡ የጌታችን የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተዋሕዶ የከበረ ያለመለወጥ ያለመከፈል ያለኅድረት ሥጋና መለኮት መዋሐዳቸውን አንዱ የአንዱን ባሕርይ ገንዘብ ማድረጉን በስፋት አስተማረ፡፡ ሁለት ፍቃድ ሁለት ባሕርይ ሁለት አካል የሚለው የንስጥሮስ ትምህርትም በዚህ ጉባኤ ተወግዞል፡፡

የኬልቄዶን ጉባኤና የአባቶች ተጋድሎ
የአውጣኪ ክህደት
አውጣኪ የንስጥሮስን ትምህርት ከመጥላቱ የተነሳ ወደ ስሕተት የገባ ሰው ነው፡፡ ይህ ሰው ትምህርቱ አንድ ባሕርይ አንድ አካል ነው ቢልም በመጠፋፋት አንድ ሆኑ ብሎ ያስተምር ነበር፡፡ በዚህ ትምህርቱ ምክንያት በፍላፕያኖስ መጀመርያ (በሁለተኛው የኤፌሶን ጉባኤ) ቀጥሎም በቅዱስ አባታችን ዲዮስቆሮስ አማካኝነት ትምህርቱ የተወገዘ ነው፡፡
ሁለተኛው የኤፌሶን ጉባኤ በ449 ዓ.ም የአውጣኬን ትምህርት ለማውገዝ የተደረገ ነው፡፡በፍላፕያኖስ ዘቁስጠንጥንያ እንደተለመደው የቤተ ክርስቲያን መሪዎችን ሳይጠራና ኤጵስ ቆጶሳትን ሰብስቦ በ 431 አወገዛው፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት ፍላፕያኖስ ሁለት ባሕርይና ሁለት ፍቃድ አለው ከሚሉ ሰዎች በመሆኑ በችኮላ በመሆኑ ዳግመኛ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ በ449 ኤፌሶንን ጉባኤ አደረገ ነገር ግን አውጣኪ አንድ ባሕርይ በመጠፋፋት ካለው ትምህርት ለጊዜውም ገሸሽ ብሎ እምነቴ የሠለስቱ ምዕትና የቅዱስ ቄርሎስ ነው በማለቱ ከእስራቱ ፈትውታል፡፡ በኃላ ላይ ግን ይህን ትምህርት መልሶ በማስተማሩ ዳግመኛ ተወግዞል፡፡

የልዩን ክህደት
የልዩን ጦማር ወደ ፍላፕያኖስ(ፍላብያኖስ)
የልዩን ጦማር ፍጽም ክህደትና የንስጥሮስን ትምህርት በመድገም ዳግመኛ የአባቶቹን ድንበር ያፈረሰ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ጦማሩን የተመለከተው ንስጥሮስም የክህደቱ ትምህርት ስለሰመረለት የሮምን ቤተ ክርስቲያን አወድሶል፡፡ ጦመሰሩ በአጭሩ ክርስቶስ ሁለት ባሕርይ ሁለት ሕላዌ አንድ አካል አለው የሚል ነው፡፡ በልዩን ፍልስፍና አካልና ባሕርይ የተለያዩ ናቸው የሚል ነው፡፡
አባቶቻችን ከአካል የተለየ ባሕርይ የለም ከባሕርይ የተለየ አካል የለም ብለው አስተምረውናል፡፡ ከአካል የተለየ ባሕርይ ከሌለ ደግሞ ሁለት ባሕርይ ካልን ሁለት አካል ወደሚል ትምህርት ይወስደናል፡፡ ይህ ትምህርት ደግሞ የንስጥሮስ ትምህርት ነው ይህ የንስጥሮስ ትምህርት ታዲያ ቀድሞ በአባቶቻችን በጉባኤ ኤፌሶን የተወገዘ ነው፡፡ወይም አካልን አንድ ካልን በባሕርይም አንድ ወደ ማለት ይመራናል ይህም እንደ ቅዱስ ቄርሎስ ነው፡፡ ሁለቱ ባሕርያት በመተባበር የየራሳቸውን ድርሻ ይሰራሉ ‹‹መለኮት ይገብር ግብረ መለኮት ትስብእት ይገብር ግብረ ትስብአት›› የሚል ጦማር ነበር፡፡ይህም ጦማር ተአምራት ያደረገው መለኮት መከራን የተቀበለው ሥጋ ብሎ ያስተምራል፡፡
የኬልቄዶን ጉባኤ የተሳታፊዎች ቁጥር 636 ሲሆን ይህም የሆነበት ምክንያት ከቀድሞ ጉባኤያት ሁሉ ታላቅ ጉባኤ ለማስመሰል ነው፡፡ በዚህ ጉባኤ ላይ ከዚህ በፊት የንስጥሮስን ትምህርት በመደገፋቸው ምክንያት የተወገዙ ሰዎች ጭምር የተሳተፉበት በመሆኑ በአባቶች ዘንድ ግርታን ፈጥሮል፡፡ ቅዱስ ዲዮስቆሮስም የእስክንድርያን አብያተ ክርስቲያናትን ወክሎ በጉባኤው ላይ ተገኘ፡፡ የጉባኤያቱ አባላትም ተቃውሞ አጸኑበት ተከሳሽም አደረጉት የአውጣኪ ትምህርት ደጋፊ ነህ ውጣ አሉት፡፡ ቅዱሱም መንበሩን ለማስከበር ሲል ወጣ ይህንን የአርመን የሕንድና የሶርያ አብያተ ክርስቲያናት ተቃወሙ፡፡ ግሪኮቸቹና የምዕራብ አብያተ ክርስቲያናት ግን ከምሥራቃዊያኑ ጋር ተባበሩ፡፡
የልዮን ጦማር ውስጥ የተካተቱ ነጥቦች
  • ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ ነው በኃላም ሰው ሆኖ ተገለጠ
  • መለኮትና ሥጋ በእርሱ ውስጥ ተገናኙ ያለመቀላቀል በእርሱ ውስጥ ይኖራሉ
  • እያንዳንዱ ባሕርይ የግብር ክልሉን ጠብቆ ይኖራል ማለት መለኮት የመለኮትን ትስብእት ትስብእትን ሥራ ይሠራል ማለት ነው፡፡
  • የሁለቱም ባሕርያት ሀብት ለአንዱ አካል በእኩልነት ይገኛሉ
  • ከመዋሐድ በፊት ሁለት ነበሩ ከተዋሐዱ በኃላ አንድ ናቸው ብሎ ማሰብ ሞኝነት ነው የሚሉ ይገኙበታል፡፡
ተገናኙ ተራከቡ አብረው ይኖራሉ?
ይህ ትምህርት ለተዋሐዶ ትምህርት ጸር ይሆን ዘንድ በንስጥሮስ የተቀመመ ክህደት ነው፡፡እነዚህ ቃላት የአማላክን ሰው መሆን የሰውን አምላክ መሆን አመልካች አይደሉም፡፡ ጽምረት ነው እንጂ እንደዳዊትና ማኅደሩ ኅድረት ተዋሕዶ ግን እንደነፍስና ሥጋ ነው፡፡
የግብር ክልሉን ጠብቆ ይኖራል?
ተዋሕዶ መለኮት የሥጋን ባሕርይ ገንዘብ አደረገ ሥጋም የመለኮትን ባሕርይ ገንዘብ አደረገ ብላ ታስተምራለች፡፡ ቅዱስ ቄርሎስም እንደሚል‹‹ እንቲአሁ ለቃል ኮነ ለሥጋ ወእንቲአሃ ለሥጋ ኮነ ለቃል›.
አንዳንድ ጊዜ እንደሥጋ አንዳንድ ጊዜ እንደመለኮት ይሰራል ብሎ የሚከፍለው ልዩን በአንድ ጊዜ የአምላክነትና የሰውነት ሥራ አይሰራም ብሎ በመልእክቱ አስቀምጦል፡፡ እኛ ግን ሥግው ቃል መከራን ተቀበለ ሞተ ተነሳ ተአምራት አደረገ ተራበ ተጠማ እንላለን ይህም የአባቶቻችን ትምህርት ነው፡፡
ተዋሕዶን ያስተማሩ አባቶች
ከኬልቄዶን ጉባኤ በኃላ ለሚቀጥሉት 150 ዓመታት ያህል የነገሡ የቁስጥንጥንያ ነገሥታት ሁለቱን አብያተ ክርስቲያናት ለማዋሐድ ጥረት አድርገው ነበር፡፡ በሮም ቤተ ክርስቲያን ጣልቃ ገብነት ሳይሳካ ቀረ፡፡አጋግዩስ ብርቱ ጥረት የአንጾክያና የእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን ለስምምነት የሚያበቃቸውን ስምምነት ተፈራርመው ነበር፡፡
ሳዊሮስን የመሰሉ ፊልክስዮስን የመሰሉ በአንጾክያና በሶርያ ተዋሕዶን የሰበኩ አልታጡም፡፡ ይህም የአባቶችን ተጋድሎ አመርካች የታሪከ ገጽ ነው፡፡
ጉባኤ ቁስጥንጥዮስ ሁለተኛ
ይህ ጉባኤ በዋነኝነት በጉባኤ ኬልቄዶን የተወሰነውንና በቅዱሳኑ በጥንታዊያን ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት መካከል ልዩነት የፈጠረውን ትምህርት ማለትም በእነሱ አጠራር ሞኖፈስትስ (ይህም በእነሱ አረዳድና ትርጉም የአውጣኪን ትምህርት ማለትም ተዋሕዶ በመጠፋፋት የሚለውን ትምህርት የሚወክል ነው) ለመቃወም ካቶሊካዊያኑና የቁስጥንጥንያ ቤተ ክርስቲያን ያደረጉት ነው፡፡
ለመሆኑ ሞኖፈስርስ ዳዩፈስቲስ ምንድን ነው?
ሞኖፊሲትስ (Monothelitism)
ሞኖፊሲትስ ማለት በውላጤ የተገኘ አንድ ባሕርይ ይህ ስም ተዋሕዶን የሚገልጥ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ተዋሕዶ ስንል ያለ መጠፋፋት ተዋሐዱ አንዱ የአንዱ ባሕርይን ያለመለወጥ ያለፍልጠት ያለኅድረት ያለሚጠት ተዋሐደ ብለን እናስተምራለንና ነው፡፡ ይህ ትምህርት ግን የአውጣኪን ክህደት በትክክል የሚገልጥ ቃል ነው፡፡
ዳዩፊሲስትስ ይህ በትክክል የንስጥሮስን ክህደትና የልዩንን የፍልስፍና ትምህርት የሚገልጥ ነው ፡፡ የንስጥሮስ ሁለት ባሕርይ ሁለት አካል ሁለት ሕላዌ አለው ስለሚል ዳዩፊሲስትስ ነው የልዮንም ሁለት ባሕርይ ስለሚል ዳዩፊሲስትስ ብለን መጥራት እንችላለን፡፡
ይህን ጉባኤ ማድረግ የተፈለገበት ምክንያት የተዋሕዶ አርበኞች ተዋሕዶን በማስተማር ስለበረቱና በክርስትናው ዓለም ተዋሕዶ እየታወቀ እየተረዳ ስለመጣ በዚህ ምክንያት ካቶሊካዊያኑ የኬልቄዶን ጉባኤን አንደ ሕጋዊ ጉባኤ በመቁጠር የጉባኤውን ሐሳብ ለማጽናት ነው፡፡
ተዋሕዶ ከአውጣኪ ትምህርት ጋር ያለው ልዩነት
ጥንታዊያን ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት አውጣኪን ቁጥሩ ከመናፍቃን እንጂ ከቅዱሳኑ ተርታ አላኖሩትም፡፡ ትምህርቱም በቅዱስ አባታችን ዲዮስቆሮስ አማካኝነት የተወገዘ ነው፡፡
ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ስትል
እንበለ ዉላጤ(ያለ መለወጥ)
ዉላጤ ስንል ሥጋ ወደ መለኮት መለኮት ወደ ሥጋነት መለወጥ ማለታችን ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ከምናገኛቸው ታሪኮች የመለወጥን ትርጉም ለመረዳት ምሳሌ እንጥቀስ የሎጥ ሚስት ወደ ጨው አምድነት(ዘፍ 19፥26) መለወጥ የቃና ዘገሊላ ውኃ ወደ ወይን ጠጅነት (ዮሐ 2፥1-3) መለወጥም ፍጹም ባሕርውን ለቆ አዲስ ወደ ሆነ ባሕርይ መለወጡን የሚያመለክቱ ናቸው፡፡ለተዋሕዶ ግን እንዲህ አይደለም፡፡
መለኮት ወደ ሥጋነት ተለወጠ ካልን መለኮት ፍጹም ሰው ሆነ ማለት ነው፡፡ ይህም ነገረ ድኅነቱን ከንቱ ያደርገዋል ምክንያቱም የሰው ልጅ በፍጡር ደም አይድንምና በፍጡር ደም ቢድን ኖሮ ቀድሞ በዳነ ነበር፡፡ ሥጋ ወደ መለኮትነትም ተለወጠ ብንል ዓለም አልዳነም ወደሚል ሐሳብ የሚመራ ነው፡፡ መለኮት በባሕሪው ሊዳሰስ ሕማም ሊቀበል ወደ መቃብር ሊወርድ አይችልምና፡፡በተዐቅቦ(በመጠባበቅ) አንድ ሆኑ እንጂ መለኮት የሥጋን ባሕርይ ገንዘብ አደረገ ሥጋም የመለኮትን ባሕርይ ገንዘብ አደረገ
እንበለ ሚጠት(ያለመመለስ)
ይህም ዉላጤ ባሕርይው ከነበረበት ሁኔታ ከተቀየረ በኃላ መልሶ ወደ ቀድመ ግብሩ(ባሕርይው) ሲመለስ ሚጠት ይባላል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ የሙሴን በትር እንደምሳሌ ብናነሳ ወደ እባብነት ተለወጠ በኃላ መልሶ በትር እንደሆነው ሁሉ ለመለኮትና ለሥጋ እንዲሁ ነው ብሎ ማስተማር ሚጠት ይባላል፡፡
እንበለ ኅድረት
ይህ ትምህርት የተወገዘው የንስጥሮስ ትምህርት ነው፡፡ ዳዊት ከማኅደር ሰይፍ ከሰገባው እንደሚያድር በማርያም ልጅ በኢየሱስ ላይ አምላክ አደረበት በማለት የስህተት ትምህርት አስተምሮል ይህ ኅድረት ይባላል፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ተዋሕዶ ስትል ከዚህ የሚለይ ነው፡፡ ይህ ባሕርይን ለሁለትለመክፈል የተመቸ ነው ይኸውም ዳዊት ከማህደሩ ቢቀመጥ ማኅደር እነደማይባል ሁሉ ኢየሱስም የሰው ልጅ እንጂ አምላክ አይባልም እንደማለት ነው፡፡ ስለዚህም አምላክ ወሰብእ (ፍጹም ሰው ፍጹም)ማለት አይቻልም ማለት ነው፡፡ ይህን የስሕተት ትምህርት በጉባኤ ኤፌሶን የተወገዘ ትምህርት ነው፡፡
እንበለ ቱሳሔ(ያለመቀላቀል)
ቱሳሔ የአውጣኪ ትምህርት ነው ይህ ሰው በአካልም በባሕርይም አንድ ነው ብሎ ቢያስተምርም ነገር ግን በመቀላቀል በመደባለቅ ነው የሚል ነው፡፡
መለኮት ግን ምንም ቱሳሔ ሳይኖርበት ከእመቤታችን የነሣው ሥጋ ባለው አጽንቶ የፍጡር ልቡና መርምሮበማይደርስበት ግብረ አምላካዊ ጥልቅ በኾነ ምሥጢር(በመሆን) ተዋሕደው እንጂ በመቀላቀል እንደወተትና ቡና ተቀላቅለው በመካከላቸው ሌላ ነገርን ያስገኙ ወይም የተጠፋፉ አይደሉም
ወይም እንደ ትድምርት ያለ(በመደራረብ) እንደ ልብስ እንደእንጀራ ዓይነት ባለሆነ ወይም እንደቡዐዴ(ማዋሐድ ማያያዝ ተቃርቦ ተላስቆ) እንደእንጨትና ብረት ባልሆነ እንደነፍስናሥጋ በኃላ መለያየት ያለው ያለ ፍልጠት በተዋሕዶ ከበረ እንላለን፡፡ የጥንታዊያን ኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች እምነታቸው ይህ ነው፡፡

ጉባኤ ቁስጥንጥዮስ ሦስተኛ

ይህም ጉባኤ በተመሳሳይ ጉዳይ ላይ ዳግመኛ የተወያየ ጉባኤ ነው፡፡ በካቶሊካዊያኑ አነጋገርና አጠራር ሞኖፈስትስ (ይህም በእነሱ አረዳድና ትርጉም የአውጣኪን ትምህርት ማለትም ተዋሕዶ በመጠፋፋት የሚለውን ትምህርት የሚወክል ነው) አውጣኪያዊ ነው በማለት ውሳኔውን አጽንተዋል፡፡ ተዋሕዶን ፍጹም ያልተረዱት ካቶሊኮችና በወቅቱ የነበሩ የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ድዩፈስትስን(ምንታዌነትን) አጸኑት፡፡ ይህም በቤተ ክርስቲያኒቱ ታሪክ ታሪካዊ ስሕተት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡
ይቆየን
ስብሐት ለእግዚአብሔር

Saturday, 24 December 2016

‹‹በእውነት እኔ ከአንተ ጋር እሆናለሁ›› ዘጸ. 2፥12



እግዚአብሔር በልዩ ልዩ መንገድ ሰዎችን ወደ እርሱ ይጠራል በልዩ መንገድም የራቁትን ይሰበስባል የተሰደዱትንም ይጠብቃል በባርነት በምርኮም ያሉትን ነጻ ያወጣል፡፡ ይህንንም በሰዎች አማካኝነት ይሰራል የመረጣቸውን ሰዎችም እርሱ ክብርና ሥልጣን ይሰጣል፡፡
እግዚአብሔር እስራኤል ዘሥጋ ለአራት መቶ ሠላሳ ዓመታት በበባርነት ከኖሩት ምድረ ግብጽ ነጻ ሊያወጣቸው ባሰበ ጊዜ በፈርዖን ቤት የእናቱን ጡት እየጠባ ያደገውን ሙሴን መረጠ፡፡ ዘጸ. 3፥9 እግዚአብሔር ሕዝቤ የሚላቸውን ፍጥረታቱን(ሕዝብና አእዛብ) ከባርነት አውጥቶ ከሲኦል እስራት ፈቶ ከጥፍት ወደ ሕይወት መንገድ ሊያሸጋግራቸው ከጥንተ ጠላቻቸው ዲያቢሎስ ነጻ አውጥቶ ልጆቹ ሊያደርጋቸው ቢነሣም ሰዎች ግን ሰብዓዊ ደካማ አስተሳሰባቸው ብቻ እየመዘኑ እንደማይቻል ያስባሉ፡፡
በሰው ደካማ አስተሳሰብ ፈርዖን በኮልታፋው ሙሴ ፊት አስፈሪ ነው፡፡ ይህ ግን በሙሴ እይታ ነው የእኛም እይታም ሊሆን ይችላል፡፡ ሰዎች ስልጣንን የላይኛውን እይታን ስለምንመለከት ሙሴም ይህን ሰፍሮና መዝኖ ‹‹ወደ ፈርዖን የሚሄድ የእስራኤልን ሕዝብ ነጻ የማወጣ እኔ ማን ነኝ?›› ሲል ፍርሃቱን ገለጠ፡፡ ሰዎች ወደ ሃይማኖት ለመሳብ በቅድስና እንዲመለሱ ለማድረግ ለመገሰጽና ከእስራታቸው እንዲፈቱ ለማድረግ የላዩን ስለምንመለከት እንፈራለን፡፡ ከሁሉ በላጭ የሆነውን ኃያሉን ጌታ እግዚአብሔርን እንደያዝን ልናስብ እንዲገባን መሆን አለበት፡፡
እግዚአብሔር ሕዝቡን እንዲሰበስብ አርነትም እንዲያወጣ የሚልካቸውን ነቢያቱን ቅዱሳኑንን መምህራኑን ሰባኪያኑን ሐዋርያቱን ሲያሰማራ ፍርሐት በውስጣቸው ነግሦ የተላኩበትን ዓላማ እንዳይዘነጉ በመልእክቱ እኔ ከአንተ ጋር እኖራለሁ ብሎ ኃይል ጉልበት ብርታት ሆኖል፡፡ ከእኛ ሚጠበቀው እግዚአብሔር በሰዎች ልጆች ላይ አድሮ ድንቅ ማድረግ እንደሚችል ማመን ነው፡፡
ቅዱሳን ሐዋርያቱም ሂዱና አእዛብን ሁሉ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችሁ ደቀመዛሙርቴ አድርጎቸው ባላቸው ጊዜ ከእነርሱ ጋር ለዘለዓለም እኖራለሁ ብሎ በማይታበይ ቃሉ ተናግሮል፡፡ ሐዋርያቱም ለአገልግሎት ሲወጡ እርሱ ከእነርሱ ጋር ስለነበር ድውያንን ሲፈውሱ ሳይፈሩ ሳያፍሩ ስለክርስቶስ ሲመሰክሩ አእዛብን ሲያሳፍሩ ሕዝቡን ስያጸኑ ሲያጸናኑ እናያለን ይህ ሁሉ የሆነው ታዲያ እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር ስለነበረ ነው፡፡
ለነቢያት ለሐዋርያት የተሰጠው ጥብዓት ጽናት ጥበብ አሁንም ፍኖተ ሐዋርያትን ተከትለው ሕዝቡን ለሚያስተምሩ በሐዋርያዊ ኑሮና አስተሳሰብ ከሚወጡት ጋር እግዚአብሔር ከፊት እየቀደመ አንደበት ኃይል ጉልበት ይሆናቸዋል፡፡
አገልግሎትና ፍርሃት
ቅዱስ እግዚአብሔር እርሱን እንዲያገለግሉ ለተመረጡ ሁሉ ብርታት እንደሚሆን ተናግሮል ይህን ያመኑ ነቢያት ሐዋርያት ሰማዕታት ጻድቃን ስላመኑበት ነገር በተጋድሎ ያለፍርሃት ሰብከዋል አስተምረዋል ነገሥታቱ ፊት አስተምረዋል፡፡ የሚመጣባቸው መከራ ጽኑ ቢሆንም እንኳን እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር ነበርና እንበለ ፍርሃት መስክረዋል፡፡ ከእነዚህ አበው ክርስቲያን ሊማር የሚገባው ቁም ነገር እግዚአብሔር ጎዶሎችንን እንደሚሞላ ጌታ በአገልግሎታችን ከፊት እንደሚቆም አምነን መነሳት እንዳለብን ነው፡፡
ጌድዮን የጌታን ጥሪ በሰማ ጊዜ ታናሽነቱንና የተናቀ መሆኑን አውቆ እንዴት ይሆናል አለ(መሳ. 6፥ ) ኢሳይያስ ግን ጉድለቱን(በለምጽ መመታቱን እንኳን) እያወቀ ጌታ እግዚአብሔር ማንን እልካለሁ ባለጊዜ እኔን ላከኝ አለ(ኢሳ. 6፥1-) ኢሳይያስ በለምጽ የነጻው ሐብተ ትንቢቱ የተመለሰው እግዚአብሔር አምላክ ፊት ባሳየው የአገልግሎት መታመን ነው፡፡ በባዕድ ሃገር በምርኮ ሳለች ስለእግዚአብሔርና ስለ ኤልሳዕ የመሰከረችው አንዲት ብላቴና (1ኛ ነገ. 5፥1) ምንኛ ድንቅ ናት፡፡ የእግዚአብሔርን አዳኝነት ለሰው ለመመስከር የግድ መጽሕፍትን መጠንቀቅ አያስፈልግም፡፡ እርሷም ለሁሉ የነቢዩን ድንቅ ማድረግ መሰከረች ፡፡ እግዚአብሔርም ድካሞን አገዛት የንጉሡን የንዕማንን ልብ ወደ ቀናው መንገድ መለሰ፡፡ እነዳንአኤል እነ ሠለስቱ ደቂቅ ሐዋርያቱ የእርሱን ድንቅ ሥራ ለመመስከር አልቦዘኑም፡፡ በብዙ መከራ ውስጥ እንኳን ለኃያሉ ለጌታ ታመኑ፡፡ ይህም ምን ያህል እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር እንደነበር የሚያመለክት ነው፡፡
እግዚአብሔር ድካማችንን ሊያግዝ የታመነ ነው፡፡
በዚህ ዘመን እግዚአብሔርን የምናገለግል የእርሱ አገልጋዮች አስቀድመን እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ሊሆን የሚችልበት ሕይወት ያስፈልገኛል፡፡ ለምስክርነት በመጣደፍ ያልኖርንበትን ሕይወት ለሰዎች ማሰስተማር የሚከብድ ነውና ቅድሚያ በተማሩት ትምህርት መኖር ይገባል፡፡ እግዚአብሔርን አስቀድመን የምናገለግልበት ወቅት ለሙሴ በገባው ቃል መሠረት ለመዝራት የተጋን የዘራነውን ለማጨድም የተጋን ያደርገናል፡፡ ሊቀ ነቢያት ሙሴ በእግዚአብሔር እንዲመረጥ ያበቃው ቀድሞም ቢሆን የእስራኤል መጨቆን ይንገበግበው ስለነበር ነው፡፡ መቆጨቱን አይቶ መሪ ይሆን ዘንድ መረጠው በድካሙም አገዘው ይህም ብቻ አይደለም ድንቅን አደረገ ባሕር አሻገረ ይህ በአእግዚአብሔር እርዳታ እንጂ ያለእርሱማ ሙሴ ብቻው አንዳች ሊያደርግ አይቻለውም፡፡ ሙሴን ጌታ ሲጠራ የጠራው በእስተእርጅና መሆኑን አስተውሉ ይህም ምንም እንኳን ማድረግ በማንችል ጊዜ እግዚአብሔር ከፊት እየቀደመ እልፍ ማድረግ እንደሚቻለው ነው፡፡
አምላከ ሙሴ ዛሬም በእጆቹ ድንቅን ይሰራል፡፡ በቁጭት በእንባ የአብያተ ክርስትያን ነገር የሚያሳሰስባቸውን ሊረዳ የታመነ ነው፡፡ የወገኖቻችን ከእግዚአብሔር እቅፍ መለየት ቢያሳስበን ከቤተ እግዚአብሔር መራቃቸው ቢያስቆጨን እናገለግላቸው ዘንድ ‹ከአንተ ጋር እኖራለሁና ሂድ› ብሎ በማይታበይ ቃሉ ለአገልግሎት ያበረታናል፡፡ ሕዝቡ ስደተኛ ሆነው እንዳይኖሩ ከኃጢያት ባርነት እንዲርቁ ጽድቅን እንሰብክላቸው ዘንድ የንስሐውን መንገድ እንመራቸው ዘንድ ከነቢያቱ ጋር እንደነበር ከሐዋርያቱ ጋራ እንደነበር ዛሬም ለዘለዓለም ከእኛ ጋራ ከአገልጋዮቹ ጋራ ይኖራል፡፡ ከእኛ የሚጠበቀው በመንፈሳዊ ምግባራት በተጋድሎ በክርስቲያናዊ ሕይወት ማመን በቃሉም መታመን ነው፡፡
የእግዚአብሔር ምስክሮቹ እንሆን ዘንድየአምላካችን የእመቤታችን ምልጃዋ ይርዳን
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ነገረ ሃይማኖት ክፍል አንድ


ዶግማ ክፍል አንድ

ሰላም በዛሬዉ የነገረ ሃይማኖት ትምህርት የዶግማ ምንነት እንዲሁም የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዶግማ(መሠረተ እምነት) ምንጮች ምን እንደሆኑ እናያለን መልካም ንባብ


ዶግማ(መሠረተ እምነት) ምንነት
ዶከይን ከሚለው የግሪክ ቃል የተገኘ ሲኾን በጥሬው አመለካከት፣ አስተሳሰብ፣ አዋጅ ማለት ቢኾንም በምሥጢራዊ ትርጓሜው ግን ሃይማኖት (የእምነት መሠረት) ማለት ነው፡፡ በመኾኑም ዶግማ የተደነገገ ሳይኾን የተገለጠ ነው፡፡ መገኛውም እግዚአብሔር ነው፡፡ ከሰው ሊፈጠር አይችልም፡፡ ከእግዚአብሔር የተሰጠ እውነት ነው፡፡ በማኝኛውም አካል (በሲኖዶስም ጭምር)፣ በየትኛውም ዘመን፣ በየትኛውም ኹኔታ (በሞትም በሕይወትም) የማይለወጥ ማንነት አለው፡፡
በማንም የማይለወጥ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፡- “ነገር ግን (ሐሳባችንን ቀይረን) እኛ ብንኾን ወይም ከሰማይ መልአክ ከሰበክንላችኁ ወንጌል የሚለይ ወንጌልን የሚሰብክላችኁ የተረገመ ይኹን” ያለውም ስለዚኹ ነው /ገላ.1፡8/፡፡
ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን መሠረተ እምነት(ዶግማ) ስንል ቤተ ክርስትያን ስለነገረ እግዚአብሔር ስለነገረ መላእክት ስለነገረ ቅዱሳን ስለሕይወት ስለሰው ያላት አስትምህሮ(ትምህርት) ብቻ አይደለም የምንኖርበት ጭምር እንጂ፡፡ በሌላ አገላለጽ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዶግማ( መሠረተ እምነት) ስንል በእግዚአብሔር ላይ ያለን እምነት መግለጫ ማለታችን ነው፡፡ ስለዚህም የእኛንና የእግዚአብሔርን ግንኙነት በጉልህ የሚያስረዳ ነው፡፡

የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዶግማ(መሠረተ እምነት) ምንጮች
የእግዚአብሔር መገለጥ
መዝሙረኛው ቅዱስ ዳዊት‹‹ በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ ቡሩክ ነው በእግዚአብሔር ቤት መረቅናችሁ ጌታ እግዚአብሔር ተገለጠልን እስከ መሠዊያው ቀንዶች ድረስ በሚያስተነትኑበት በደስታ በዓል አደረጉ›› ይላል (መዝ 117÷26-27) የክርስትና መሠረትም በመዝሙሩ ላይ እንደተገለጠው የጌታ እግዚአብሔር መገለጥ ነው፡፡
እግዚአብሔር ራሱን በፍጥረቱ ለፍጥረቱ ይገለጣል፡፡ እግዚአብሔር ግብሩን በፍጥረቱ ማወቅ ቢቻልም ግን ባሕርዩን ጠቅልለን መራዳት አይቻልም፡፡እግዚአብሔር ፈጣሪ ዓለማት ሆኖ በፈጠረው ሰው ይመረመር ዘንድ እንዴት ይቻላለዋል? ነገር ግን እግዚአብሔር በየዘመናቱ ራሱን ለሰው ልጆች ገልጦል፡፡ እግዚአብሔር በግብሩ (በሥራው) ለሁሉ ይገለጣል ከዚህ በተጨማሪ ለቅዱሳኑ ለሊቀ ነቢያት ሙሴ እገዚአብሔርን 570 ጊዜ ያህል ተገልጦ አናግሮታል(ዘኁ 12÷5) ለቅዱሳኑም ለሄኖክ መዓዛ ባለው እንጨት ለአብርሃም በሦስት ሰዎች አምሳል ለኖኅ በቀስተ ደመና ለያዕቆብ በመሰላል ከፍታ ላይ ለኢሳይያስ በዙፋኑ ተቀምጦ ለዕዝራ በአንበሳ አምሳል ለዳንኤል በሽበታም ሰው አምሳል ተገልጦል፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም ይህንን በተመለከተ ሲናገር ‹‹ እርሱ እንደመረዳታችን መጠን ተገለጠ(አስተማረን) ስንል እርሱ ራሱ እንደኛ ነው ማለታችን አይደለም፡፡ እርሱ በእኛ አምሳል ተገለጠ አልተገለጠ እርሱ ራሱ ነው አይለወጥም፡፡ ሲፈልግ እኛን ለማስተማር አንዱ ለጠባያችን ተገልጦ ይታያል ሌላ ጊዜ ደግሞ አስቀድሞ የለበሰውን እንደልብስ አውልቆ ሌላ ልብስ ለብሶ ይገለጣል እርሱ ለእኛ በመንገሩ እርሱ እንዲህ ነው ማለት አይደለም ነገር ግን ባሕርይው የማይመረመር ነውና በምንረዳው በእኛ ምሳሌ ተገልጦ ፍቃዱን ገለጠልን›› ብሏል
በኋላም በሐዲስ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ተገልጦ በብሉይ በከፊል ሲገለጥ እንደነበር ሙሉ በሙሉ(በሰው አካል) ራሱን ገለጠልን፡፡ ክርስቶስ ከላይ የጠቀስነውን የቅዱስ ዳዊትን የትንቢት ቃል ፈጸመ፡፡ ለዚህም ነው ሁል ጊዜ በቅዳሴ አገልግሎታችን ቡሩክ ስሙ ለእግዚአብሔር ወቡሩክ ዘይመጽእ በስመ እግዚአብሔር እያልን እግዚአብሔርን የምናመሰግነው መገለጡንም የምናደንቀው፡፡
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዓለም በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ ሲመላለስ ሰዎች ረቡኒ ብለው ይጠሩት እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረኛል ፡፡ ረቡኒ ማለት መምህር ማለት ነው፡፡ ተከታዮቹም ደቀ መዛሙርት ተሰኝተዋል ከሄደበት እየሄዱ ካደረበት እያደሩ ትምህርቱን ሲያደምጡ ስለነበር ክርስቶስ ራሱን ለሰው ልጅ የገለጠው ከእግዚአብሔር የተላከ መምህር እንደሆነ በመግለጥ ነው፡፡ የእግዚአብሔርን ፍቃድ በማስተማር እግዚአብሔርን መንግስት ለዓለም ገለጠ፡፡ (ዮሐ 1÷18) የክርስቶስ እንደመምህርም መገለጥ ይመጣል ብለው የሚጠብቁት መሲሕ እርሱ መሆኑን ያመለክታል መሲሕ መምህር ማለት ነውና፡፡(ኢሳ 54÷13 ዮሐ 6÷45)
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሰው ራሱን የገለጠው መለኮታዊ መምህር ሆኖ ነው፡፡ የእርሱ ቃል የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን ገልጦ አስተምሯል፡፡ ሲያስተምርም ለአይሁድ የማስተማርም ለመገሰጽም ባለስልጣን እንደሆነ ይገልጥላቸው ነበር፡፡ ‹‹እንደጸሐፍቶቻቸው ሳይሆን እንደባለሥልጣን ያስተምራቸው ነበር›› (ማቴ 7÷29)
ዮሐ 12÷44-50
‹‹በእኔ የሚያምን በላከኝም ነው እንጂ በእኔ ብቻ የሚያምን አይደለም እኔን ያየ የላከኝን አየ፡፡ በእኔ የሚያምን ሁሉ በጨለማ እንዳይኖር ብርሃን እኔ ወደ ዓለም መጣው፡፡ ቃሌን ሰምቶ የማይጠብቀውን እኔ የምፈርድበት አይደለሁም እኔ ዓለምን ላላድን እንጂ
በዓለም ልፈርድ አልመጣሁምና፡፡የሚክደኝን ቃሌን የማይጠብቀውን ግን የሚፈርድበት አለ እኔ የተናገርኩት ቃል እርሱ በመጨረሻይቱ ቀን ይፈርድበታል፡፡ የተናገርኩት ቃል ከእኔ አይደለምና ነገር ግን የላከኝ አብ አንድናገር እንዲም እንድል እርሱ ትእዛዝን ሰጠኝ››
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቃል ብቻ አላስተማርም በተግባር እያሳየ ጭምር እንጂ፡፡ እርሱንም ለሰው ልጅ በእውነት ገለጠ(ዮሐ 14÷6) እውነትና ብርሃን መሆኑን አስተማረ(ዮሐ 8÷12) ሕግንም እየፈጸመ በጥቂቱ አደገ፡፡

ዮሐ 1÷1-5
‹‹በመጀመርያ ቃል ነበረ ቃልም እግዚአብሔር ዘንድ ነበረ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ፡፡ ይህም በመጀመርያ እግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፡፡ ሁሉም በእርሱ ሆነ ከሆነውም ሁሉ ያለእርሱ ምንም የሆነ የለም፡፡ ሕይወት በእርሱ ነበረ ሕይወትም የሰው ብርሃን ነበረ ብርሃንም በጨለማ ያበራል ጨለማም አላገኘውም፡፡››
ዮሐ 1÷14-18
‹‹ያም ቃል ሥጋ ሆነ በእኛ አደረ ለአባቱም አንድ እንደሆነ ልጅ ክብር ያለ ክብሩንአየነ ጸጋና እውነትን የተመላ ነው፡፡››
አካላዊ ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውልጅን በቃል ትምህርተና በተግባሩ አርአያ ሆነው፡፡ ይህን እርሱ ያስተማረውን ወንጌል እንለዋለን የምስራች ለዓለም ሁሉ የሚሆን የእግዚአብሔር መንግስት የምስራች ነው፡፡ሐዋርያትንም የክርስቶስን የምስራች ቃል ለዓለም ሰበኩ(ማቴ 28÷19) ዓለምን ይሰብኩ ያስተምሩ ዘንድ በዓለም ይፈርዱ ዘንድ መንፈስ ቅዱስን ልኮ አሰማራቸው፡፡(ዮሐ 15÷6)
በኦርቶዶክዊት ቤተ ክርስቲያን በሐዋርያት ትምህርት ጸንተን የምንኖር ናት ሐዋርያዊት መባሏም ለዚህ ነው፡፡(ሐዋ 2÷42) ይህም የሐዋርያት ትምህርት ለቅድስት ቤተ ክርስትያን ዶግማ የቤተ ክርስቲያኒቱ አስተምህሮ መመሪያ ወይም ትምህርት ነው፡፡ ይህም የሐዋርያት ትምህርት የጌታችን የመድኃኒተችን የኢየሱስ ክርስቶሰ ትምህርት ነው፡፡ በዚህ ትምህርት(ዶግማ) ዓለም ሁሉ የሚድንበት ዓለም የእግዚአብሔርን መንግስት የሚወርስበት እውነተኛ ቃል ነው፡፡
ስለእግዚአብሔር መገለጥ ስናወራ በብሉይ እግዚአብሔር ሕዝቤ ብሎ የሚጠላቸው እስራኤል ዘሥጋ ራሱን ይገልጥ እንደነበር ማንሳቱ ተገቢ ነው፡፡ በብሉይ እንደምናየው የነበረው መገለጥ በነቢያቱ ላይ እያደረ በኅድረት ተዋሕዶ በትንቢት በራዕይ በሕልም እየተገለጠ ሕዝቡን ያስተምር ነበር፡፡ ይህ የነቢያቱ ትንቢትና ምሳሌ ፍጻሜው የመሲሑ መምጣት ነው፡፡

ይህም የእግዚአብሔር መገለጥ የቅድስት ቤተ ክርሰትያን ዶግማ(መሠረተ እምነት) መሠረት ነው፡፡

ነገረ ሃይማኖት ክፍል ሁለት


ዶግማ ክፍል ሁለት

ሰላም በዛሬዉ የነገረ ሃይማኖት ትምህርት የዶግማ ምንነት እንዲሁም የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዶግማ(መሠረተ እምነት) ምንጮች ምን እንደሆኑ እናያለን መልካም ንባብ

  • መጽሐፍ ቅዱስ 


መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔርን መገለጥ በጽሑፍ የምናገኝበት መጽሐፍ ነው፡፡ ይህ መጽሐፍ ከብዙ ሺህ ዓመታት በፊት በተለያየ ጊዜ በተነሱ ቅዱሳን አበው የተጻፈ መጽሐፍ ነው፡፡ በሁለት ኪዳኖችም የተከፈለ ነው በብሉይና በሐዲስ፡፡ ኪዳን ማለት ውል ስምምነት ማለት ነው ይህም የእውነት መጽሐፍ የሕግ የትንቢት የታሪክ የመዝሙር የጸሎት የመልእክት ክፍል ያለው ነው፡፡
የብሉይ ኪዳን መጽሐፍት በአምስት ክፍሎች የተከፈሉ ናቸው፡፡ የሕግ(የኦሪት) ክፍል መጻሕፍት የታሪክ ክፍል መጻሕፍት የትምህርት ክፍል መጻሕፍት የመዝሙርና የጥበብ ክፍል መጻሕፍት የትንቢት ክፍል መጻሕፍት የሐዲስም መጽሐፍት እንዲሁ የወንጌል ክፍል የታሪክ ክፍል የሥርዓት ክፍል የመልዕክት ክፍል የትንቢት ክፍል በማለት እንከፍላቸዋለን፡፡
ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችን ትምህርቷ የሚቀዳው ከዚህ መጽሐፍ እውነት ነው፡፡ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የተመሩት አበው የጻፉትም ስለሆነ በመንፈስ ቅዱስ የምትመራው ቤተ ክርስቲያን ይህንን መጽሐፍ መሠረት በማድረግ ታስተምራለች፡፡ ሁላችንም ልናውቅና ልንረዳው የሚገባው እውነት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚቃረን ትምህርት ጋር የሚቃረን ትምህርት አታስተምርም፡፡ የዘወትር ዝማሬዋ ቅዳሴዋ ውዳሴዋ መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡
  • ሥርዓተ አምልኮ 


ከቤተ ክርስቲያን የሚለው ቃል ሦስት ዓይነት ሰዋስዋዊና ዘይቤአዊ ትርጕም አለው /አባ ጐርጐርዮስ (ሊቀ ጳጳስ)፣ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ፣ ገጽ 12-17/፡፡ የመዠመሪያው የተወሰነ ቦታን ያመለክታል፡፡ ይኸውም የክርስቲያኖች ቤት፣ መኖሪያ ማለት ነው /1ኛ ቆሮ.11፡18/፡፡ “ቤተ ክርስቲያን እንሒድ” /መዝ.121፡1/ ሲባልም ይኽን ፍቺ የያዘ ነው፡፡ በመጻሕፍትም ቤተ ክርስቲያን ብዙ ጊዜ የእግዚአብሔር ቤት ተብላለች /ዘፍ.18፡27፣ መዝ.5፡7፣ መዝ.26፡4፣ መዝ.83፡4፣ መዝ.92፡5፣ ሉቃ.2፡49፣ 1ኛ ጢሞ.3፡15፣ ዕብ.10፡21/፡፡ኹለተኛው ደግሞ ክርስቲያኖች ራሳቸው ቤተ ክርስቲያን ይባላሉ /1ኛ ቆሮ.3፡16፣ 1ኛ ቆሮ.6፡19/፡፡ ይኸውም በመንፈሳዊና በምሥጢራዊ ልደት ከክርስቶስ የተወለዱ፥ ርሱ አድሮባቸው የሚኖሩ፥ ከቅዱሱ ቅባት /1ኛ ዮሐ.2፡20/ እና ከሥጋ ወደሙ የተካፈሉ ምእመናንን ለማመልከት ነው፡፡ሦስተኛው ትርጕሙ ደግሞ የክርስቲያኖችን ኅብረት (ጉባኤን) የሚያመለክት ነው /1ኛ ጴጥ.5፡13/፡፡ እኛም በዚኹ ክፍል ትኵረት የምናደርገው በዚኹ በሦስተኛው ትርጓሜ ላይ ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያን ክርስቲያኖች በኅብረት እግዚአብሔርን ያመልካሉ ይህም  ሥርዓተ አምልኮ ቤተ ክርስቲያን በሠራችው ሥርዓት የሚካሄድ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ክርስቲያኖች በኅብረት የሚያከናውኖቸው ሥርዓተ አምኮዎች ቢኖሩም በዋንኝነት ቅዳሴ ቀዳሚ ነው፡፡ በብሉይ የሚከወነው ሥርዓተ አምልኮ በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ በመሰብሰብ የሚከወን ነው፡፡ ሥርዓተ አምልኮ በብሉይ ኪዳን ሥርዓተ አምልኮው ጾም ጸሎቱ በሙሴ ሕግ መሠረት የሚከወን ነበር ይህም በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ወይም በተለያዩ ቦታዎች በተሠሩ ምኩራቦች ይደረግ ነበር፡፡ ምኩራቦቹ በተለያየ ቦታ የሚሰሩ ሲሆን ቤተ መቅደሱ ግን አንድ እርሱም በኢየሩሳሌም የሚገኝ ነው፡፡ በሙኩራባቸው እስራኤላዊያን ለጸሎት ይሰባሰባሉ መጽሐፍትን ያጠናሉ ይሰብካሉ፡፡
በሓዲስ ኪዳን የሚካሄደው ሥርዓተ አምልኮ ክርስቶስን ማዕከል ያደረገ ነው ስለዚህም በብሉይ የነበረው ሥርዓተ አምልኮ በጌታችን በኢየሴስ ክርስቶስ አማናዊ ሥርዓተ አምልኮ ተተክቷል፡፡ በብሉይ የሚነበቡ መጻሕፍት የሚዜሙ መዝሙራት ክርስቶስን የሚሰብኩ ነበሩ በሐዲስ ደግሞ በጉልህ የሚሰብኩ ሆነዋል፡፡ እንዲሁም የነበረው መሥዋዕት በክርስቶስ አማናዊ ሥጋና ደም ተለውጧል፡፡
የአይሁድም የጾም ሥርዓት እንዲሁ አዲስ ትርጉም አግኝቶል፡፡ የፍሲካ ጾም የክርስቶስን ሞትና ትንሣኤ የምናስብበት የምንዘክርበትና የምናከብርበት ሆኖል፡፡ የአይሁድ ጰንጠቆስጤ በዓልም የመንፈስ ቅዱስን ለሐዋርያት መውረድ የምንዘክርበት በዓል ሆኖል፡፡
የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ምሥጢራትና ሥርዓተ አምልኮ ቀዳሚው የክርስትና መሠረተ እምነት መሠረት ነወ፡፡ ሥርዓተ አምልኮው መጽሐፍ ቅዱስና ቅዱስ ትውፊት የተረሱ ሳይሆኑ በክርስትና የዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ የምናገኛቸው ያለፉ ሳይሆኑ አሁንም ያሉ የምንገለገልባቸው ናቸው፡፡ በጸሎትና በቤተ ክርስቲያን ምሥጢራት አማካኝነት የሰው ልጅ ከእግዚአብሔር መማር ይችላል ጌታችን እንዳለ ‹‹ከእግዚአብሔር ዘንድ የተማሩ ይሆናሉ››ዮሐ 6÷45 ከዚህም በተጨማሪ ሥርዓተ አምልኮን ቤተ ክርስቲያኒቱ አገልግሎትን ምሥጢራቷን የሚያጠና ሰው የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን መሠረተ እምነት ማወቅ ይችላል፡፡


ይቆየን
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
 

Wednesday, 21 December 2016

አዕማደ ምሥጢራት



አምድ ማለት ምሶሶ ማለት ነው፡፡ በአምድ የተሠራ ቤት አይዛባም ያለዓምድ የተሠራ ቤት ግን ይፈርሳል አይጸናም፡፡ እንደዚህም ሁሉ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን አዕማድ የተባሉ ምሥጢራት ይዞ የተገኘ ሰው ልቡናው በፍቅረ እግዚአብሔር በተስፋ መንግስተ ሰማያት ይጸናል፡፡ እነዚህን አምስቱን እምነታት ሳይዝ የተገኘ ልቡናው በፍቅረ እግዚአብሔር በተስፋ መነንግስተ ሰማያት አይጸናምና አዕማድ ይባላሉ፡፡ስለምን ምሥጢር አላቸው ቢሉ በዓይኔ ካላሣያችሁኝ በእጄ ካላሲዛችሁኝ ብሎ አላምንም አልማርም ይሉ ዘንድ አይገባም በቃል ተምሮ በልቡና ተመራምሮ አዎን ብሎ የሚማሯቸው ስለሆኑ ምሥጢር አላቸው፡፡(ሃይ. አበው ዘአትናትዮስ 14÷ 39 ሃይ. አበው ዘኤራቅሊስ 11÷24 1 ቆሮ 1419 1 ሳሙ 1740)
አምስቱ አዕማደ ምስጢራት የሚባሉት
ጢረ ሥላሴ፡- የምሥጢረ ሥላሴ ነገር እንዴት ነው ቢሉ የሥላሴ አንድነት ሦስትነት ምልዓት ስፋት ርቀት ይህንን ማወቅ ማመን ነው፡፡ (ማቴ 2820) ማወቅ እንደምን ነው ቢሉ ምሥጢሩን መማር ነው ማመንስ እንደምን ነው ቢሉ መናፍቃን ካህናት አላዊያን ነገሥታት ሃይማኖታችሁን ተነስተዉ ፈጣራችሁን ካዱ ለጣዖት ስገዱ ብለው ሰይፍ ስለው እሳት አንድደወ በተነሱ ጊዜ አንክድም ብለው በተማሩት ሃይማኖት ተከራክሮ የደፈረ አንገቱን ለስለት ገላውን ለእሳት ለውግረት ለሞት የፈራ ስደት ይህንን መቀበል ነው፡፡
ስለምን ምሥጢር ተባለ
የሥላሴን አንድነት ሦስትነት በዓይኔ ካላየሁ በእጄ ካልዳሰስኩ አላምንም ይሉ ዘንድ አይገባም በቃል ተምሮ በልቡና ተመራምሮ አዎን ብሎ የሚማሩት የሚቀበሉት ነውና ምሥጢር ተብሏል፡፡
ምሥጢረ ሥጋዌ፡- የምሥጢረ ሥጋዌ ነገር እንደምን ነው ቢሉ ከሦስቱ አካላት ከሥላሴ አንዱ አካል ወልድ በተለየ አካሉ ሰው እንደሆነ ከእግዚእነ ማርያም እንደተወለደ በየጥቂቱ እንዳደገ በሠላሳ ዘመኑ በማየ ዮርዳኖስ በእደ ዮሐንስ እንደተጠመቀ ገዳመ ቆሮንቶስ ገብቶ አርባ መዓልት አርባ ሌሊት እንደጾመ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ሕገ ወንጌልን እንዳስተማረ እንደተሰቀለ እንደሞተ እንደተነሳ በአርባኛው ቀን እንደዐረገ በኋላም ይህችን ዓለም ለማሳለፍ እንደሚመጣ ማወቅ ማመን ነው፡፡(ዮሐ 119)
ስለምን ምሥጢር ተባለ
ረቂቅ መረኮት ርቀቱን ሳይለቅ ከግዙፍ ሥጋ ጋር ተዋሐደ ማለት ሰማይና ምድር የማይችሉት መለኮት ቁመቷ አጭር ወርዷ ጠባብ በሆነ እግዝእትኘ ማርያም ማኅጸን ተቻለ ይህንንም በዓይኔ ካላየሁ በእጄ ካልዳሰስኩ አላምንም ይሉ ዘንድ አይገባም በቃል ተምሮ በልቡና ተመራምሮ አዎን ብሎ የሚማሩት የሚቀበሉት ነውና ምሥጢር ተብሏል፡፡
ምሥጢረ ጥምቀት፡- ስለጌታ እና ስለ ክርስቲያኖች ጥምቀት የምንማርበት ነው (ማር 1616)
ስለምን ምሥጢር ተባለ
ካህኑ ምሥጢረ ጥምቀትን ሲፈጽም አሐዱ አብ ቅዱስ አሐዱ ወልድ ቅዱስ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ ብሎ ውሃውን ሲባርከው መንፈስቅዱስ በውሃው ላይ ያድርበታል፡፡ ከጌታችን ቀኝ የወጣው ውሃ ይሆናል(ማየ ገቦ) በዚያ የተጠመቀ ሰው ጸጋ መንፈስ ቅዱስ (ልጅነት) ያገኛል፡፡ ምሥጢሩ ሲፈጸም የሚያይ ወይም የሚጠመቅ ሰው የውሃው ቅዝቃዜ የውሃው ጥቁረት ይታየዋል እንጂ ከሥላሴ ሲወለድ ጸጋ መንፈስ ቅዱስ ሲያገኝ በዓይነ ሥጋ አይታይም ይህንንም በዓይኔ ካላየሁ በእጄ ካልዳሰስኩ አላምንም ይሉ ዘንድ አይገባም በቃል ተምሮ በልቡና ተመራምሮ አዎን ብሎ የሚማሩት የሚቀበሉት ነውና ምሥጢር ተብሏል፡፡
ምሥጢረ ቁርባን፡- ስለጌታችን መድኃኒታችን አማናዊ ስጋና ደም የምንማርበት (ዮሐ 654)
ስለምን ምሥጢር ተባለ
ካህኑ ምሥጢሩን ሲፈጽም አሐዱ አብ ቅዱስ አሐዱ ወልድ ቅዱስ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ ብሎ ኅብስቱን ጽዋውን ሲባርከው ኅብስቱ ተለውጦ ሥጋ አምልክ ወይኑ ተለውጦ ደመ አምላክ የሚሆንበት ምሥጢር ነው፡፡ ይህንን በዓይኔ ካላየሁ በእጄ ካልዳሰስኩ አላምንም ይሉ ዘንድ አይገባም በቃል ተምሮ በልቡና ተመራምሮ አዎን ብሎ የሚማሩት የሚቀበሉት ነውና ምሥጢር ተብሏል፡፡
ጌታ ይህንን ያህል ሥጋውን ደሙን ለምን ሰወረው ቢሉ ቢገልጠው የሚቆርብ የሚያቆርብ አይገኝምና፡፡ እንደምን ቢሉ ኅብስቱ በጻሕል ወይኑን በጽዋ አድርጎ አሐዱ አብ ቅዱስ አሐዱ ወልድ ቅዱስ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስፈኑ ጸጋ መንፈስ ቅዱስ ላዕሌነ ብሎ ሲባርከው ኅብስቱ ወይኑ ተለውጦ ሥጋ መለኮት ደመ መለኮት ይሆናል እንዴትስ የመለኮት ሥጋ ደም ይፈተታል እንዴትስ ሰው በእሳት ይቀበላል፡፡ ስለዚህም ሰውሮታል፡፡
ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታን፡- ስለ ጌታና የሰው ልጆች ትንሣኤ የምንማርበት ናቸው፡፡(ዮሐ 1125)
ስለምን ምሥጢር ተባለ
ይህንንም ምሥጢር በዓይኔ ካላየሁ በእጄ ካልዳሰስኩ አላምንም ይሉ ዘንድ አይገባም በቃል ተምሮ በልቡና ተመራምሮ አዎን ብሎ የሚማሩት የሚቀበሉት ነውና ምሥጢር ተብሏል፡፡
እነዚህን ምሥጢራት ማወቅ መማር እንደአርዮስ ወለድ ፍጡር ነው ከማለት እንደፎጢኖስ የወለድ መገኛው ከእመቤተችን ከተወለደ ወዲህ ነው እንጂ ከዚያ በፊት አልነበረው ከማለት መዓረገ መንግስት እንደሚሰጡ መናፍቃን አብ ንጉሠ ነገሥት ወልድ ቢትትደድ መንፈስ ቅዱስ ብለላቴን ጌታ ነው ከማለት መዓረገ ርቀት እንደሚሰጡ መናፍቃን ከነፍስ ነፍሳት ከነፍሳት መላእክት ይረቃሉ ከመላእእት መንፈስ ቅደስ ይረቃል ከመንፈስ ቅዱስ ወልድ ከወለድ አብ ይረቃል ከማለት በሦስቱ አካላት መካከል ልዩነት እንዳለ ሁሉ እኔ የአብ አገልገጋይ ነኝ ወልድና መንፈሰ ቅዱሰ ለእኔ ምኔ ናቸው እኔ የወለድ አገልጋይ ነኝ አብና ወልድ ምኔ ናቸው እኔ የመንፈስ ቅዱስ ባርያ ነኝ አብና ወለድ ምኔ ናቸው ከማለት ከመናናቃኑ ትምህርት ለመጠበቅ ይረደዳዳል፡፡