በዲያቆን ያሬድ መለሰ
ለአስታየትዎ ymelese04@gmail.comን ይጠቀሙ
ውድ ኦርቶዶክሳዊያን በክፍል ሁለት የንስሐ ሦስቱ ደረጃዎችና የንስሐ ጥቅም(አስፈላጊነትን) በተመለከተ ለማየት ሞክረናል በዚህ ክፍል ኃጢአትን መናዘዝ(ኑዛዜ)ና የኑዛዜ ምንነትና ጥቅም? በጥቂቱ እንላለን፡፡ መልካም ንባብ
የኑዛዜ ምንነትና ጥቅም?
ኑዛዜ በሚለው ቃል በግሪክኛው ሆሞሎጊያ Homologeia ሁለት ቃላትን ያቀፈ ነው። ሆሞ "ተመሳሳይ" እና ሎጊያ "ቃል" ማለት ነው። መናዘዝ ከክርስቶስ ጋር ሐሳብና ቃል ጋር መስማማት ነው ይህም ክርስቶስ የገለጠውን መግለጥ ክርስቶስ የሰበከውን መስበክ ማለት ነው።
ኑዛዜ ሁለት ዓይነት እንዳለው ተናግረናል፡- የእምነት መናዘዝ እና ኃጢአትን መናዘዝ። የመጀመሪያው የቤተክርስቲያንን እምነት በተመሳሳይ ቃላት በማወጅ የሚገለጽ ነው። ይህ ደግሞ በቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ አምልኮ ሕይወት ውስጥ በግልጽ ይታወቃል። "በእውነት በአንድ አምላክ እናምናለን"! እኛም እምነታችንን ለመግለጽ በቤተክርስቲያን የሠራችልንን ተመሳሳይ ቃል እንጠቀማለን፤ ጌታችን እንዳለ "ደግሞ እላችኋለሁ፥ በሰው ፊት የሚመሰክርልኝ ሁሉ፥ የሰው ልጅ ደግሞ በእግዚአብሔር መላእክት ፊት ይመሰክርለታል።"(ሉቃ. 12:8)
ኢየሱስ ጌታ እንደ ሆነ በአፍህ ብትመሰክር እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልብህ ብታምን ትድናለህና።በልቡ አምኖ ይጸድቃልና በአፉም መስክሮ ይድናልና። (ሮሜ 10:9-10)
ሁለተኛው ዓይነት ኑዛዜ ኃጢአትን መናዘዝ ነው። ስለራሳችን መናዘዝ…...ያለ ሰበብ፣ ያለማስረጃ ወይም ያለማሳመር ኃጢአቴን በእውነት መናዘዝና ምን እንደሆነ ልጠራው እችላለሁ! ዋሽቻለሁ፣ ሰርቄአለሁ፣ ተመኝቻለሁ፣ በሰው ላይ ክፋትን ሰርቻለሁ ወይም ለመሥራት አስቢለሁ፣…. ወዘተ.
ዲያቢሎስ ስለ ድርጊታችን፣ ሀሳባችን እና ሕይወታችን ስንናገር ሁላችንም የተለያዩ ቃላትን እንድንጠቀም ስለሚፈትነን መጠንቀቅ አለብን። ኃጢአትን በእውነት ነው ብሎ ከመጥራት ይልቅ የተለያዩ ቃላት እንድንጠቀም ይፈትነናል። ፍትወትን ሸፍኖ ፍቅር ይለዋል። ስግብግብነትን አስመስሎ ምኞት ይለዋል። ትዕቢትን ይሸፍናልና በራስ መተማመን ይለዋል ሆኖም እኛ እንደ ክርስቲያኖች እውነትን ለመስበክ ደፋር መሆን አለብን፣ እናም በዚህ ምክንያት ኃጢአትን በኃጢአት ስሙ መጥራት ይገባናል።
ኃጢአትን መናዘዝ
ኑዛዜ (ኃጢአትን መናዘዝ) አራት መሠረታዊ ነጥቦችን ያጠቃልላል፡፡ አንደኛው ኃጢያትን ለራስ ሕሊና መናዘዝ ኹለተኛው በጸሎት በደልን ለእግዚአብሔር መናዘዝ ሦስተኛ በደልን ለካህን መናዘዝ አራተኛው ለበደሉት ሰው መናዘዝ ናቸው፡፡
· ኃጢያትን ለራስ ሕሊና መናዘዝ
ኃጢያትን በመናዘዝ ውስጥ የመጀመርያው ደረጃ ኃጢያትን ለራስ ሕሊና መናዘዝ ነው፡፡ የሰው ልጅን እግዚአብሔር ሲፈጥረው ማመዛዘን የሚችልበትን አእምሮ ሰጥቶ ፈጥሮታል ስለዚህም ይህ ሕሊና ለሰው ልጅ ሲበድል ወቃሹ እውነተኛ ዳኛ ነው፡፡ ሕግ ተሰርቶልን ኦሪትንና ወንጌልን ሳናውቅ በፊት ክፉውን ከበጎ እንድንለይበት እግዚአብሔር በድንቅ አፈጣጠሩ ፈጥሮልናል፡፡ ሰዎች ታዲያ ክፉ ሲያደርጉ ይወቅሳቸው ዘንድ በጎ ሲሰሩ ያበረታቸው ዘንድ፡፡ በጎ ሕሊና ያለው ሰው ኃጢያት በሰራ ጊዜ ኃጠያቱን እንደሰራ ያምናል፡፡ ለራሱም ኃጢያቱን አምኖ ይናዘዛል በድያለኹ ይላል ይህም የንስሐ የመጀመርያው ደረጃ ነው፡፡ታላቁ መቃርስ እንዳለን ኃጢያትን ለራስ መናዘዝ እግዚአብሔር ሳይፈርድብን አስቀድመን ራሳችን ላይ መፍረድ ነው፡፡ በቅዱስ ወንጌል ተጽፎ የምናገኘው የጠፋው ልጅ ወደ ልቡ ተመልሶ እንዳለ ‹‹ እንጀራ የሚተርፋቸው የአባቴ ሙያተኞች ስንት ናቸው እኔ ግን ከዚህ በረኃብ እጠፋለሁ፡፡ ተነስቼም ወደ አባቴ እሄዳለሁና፡፡ አባቴ ሆይ በሰማይና በምድር በደልኹ ወደ ፊትም ልጅ እባል ዘንድ አይገባኝም ከሞያተኞትህ እንዳንዱ አድርገኝ እለዋለኹ›› ብሎ ኃጢያትን በቅድሚያ ለራስ እንደተናዘዘ እንዲሁ እኛም ከኹሉ በፊት ኃጢያታችንን በማመን እንናዘዝ ዘንድ ይገባል፡፡ (ሉቃ 15፥17-19)
· በጸሎት በደልን ለእግዚአብሔር መናዘዝ
ኃጢያት መስራት በመጀመርያ ደረጃ እግዚአብሔርን መበደል(ማሳዘን) ስለሆነ ለእግዚአብሔር መናዘዝ ይገባናል፡፡ ቅዱስ ዳዊት በኃጢያት በወደቀ ጊዜ እንዲህ አለ ‹‹ አንተን ብቻ በደልኩ በፊትህም ክፉን አደረኹ›› (መዝ 50፥4) ነቢዩ ዳንኤልም በጸሎቱ እንዲህ አለ ‹‹ አምላክ ሆይ ኃጢያትን ሰርተናልና በድለንማል ክፍትም አድርገናል አምጸናል ከትእዛዝህና ከፍርድህም ፈቀቅ ብለናል፡፡›› እንዳለ (ት. ዳን 9፥5) እንዲሁ እኛም የእነዚህን ታላላቅ አባቶች ጸሎት ጸሎታችን እናደርግ ዘንድ ይገባናል፡፡
· በደልን ለካህን መናዘዝ
የእግዚአብሔር እንደራሴ በሆነ አገልጋይ ፊት መናዘዝ በእግዚአብሔር ፊት መናዘዝ ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ እንደምናነበው ኢያሱ አካንን ‹‹ልጄ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ክብርን ስጥ ለእርሱም ተናዘዝ ያደረከውንም ንገረኝ አትሸሽገኝ›› (ኢያ 7፥19) እንዲሁም ወደ መጥምቁ ዮሐንስ የመጡ ኹሉ ኃጢያታቸውን እየተናዘዙ የንስሐ ጥምቀት ተጠምቀዋል፡፡ (ማቴ 3፥6) በሐዋርያት አገልግሎትም ያመኑ ብዙ ሰዎች ኃጢያታቸውን ይናዘዙ ነበር (ሐዋ 19፥18)
ካህኑ ፊት ኃጢያትን መናዘዝ አንደኛ በካህኑ ፊት የተናዘዘውን ኃጢያት ዳግም እንዳይሰራ መንፈሳዊ ብርታት ይሆነዋል፡፡ ኹለት ፍጹም የኃጢያት ሥርየት የሚገኝበትን ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ለመቀበል የሚያስችል ፍቃድ ያገኛል፡፡
ኃጢአታችን ለካህን መናገር ለምን አስፈለገ?
ብዙ ሰዎች ኃጢአታቸውን ለካህን ለመናገር ስለሚያፍሩ ኑዛዜን ይርቃሉ።እግዚአብሔር ሁሉን አዋቂ ነው ኃጢአቴን ሁሉ ያውቃል ለካህኑ መናዘዝ ኃጢአቴን ለሚያውቀው ጌታ መንገር ለምን ያስፈልጋል? የሚል አመለካከት ይይዛሉ፣ በመሠረቱ ኃጢአት የሰራ ሰው የሚያብለው የእግዚአብሔርን ሀልዎት ነው በሕይወታችን ሁሉ እግዚአብሔር እንዳለ ካመንንና ካወቅን ኃጢአት ባልሰራን ነበር። ኃጢአቴን ለሚያውቀው ጌታ መንገር ነው የሚል ሰው ይህንን አስተሳሰቡንና አመለካከቱን ኃጢአት ከመሥራቱ በፊት ቢያምንና ቢያውቅ በኃጢአት ባልወደቀ በነበር….
ኃጢአታችንን ለካህናት የምንናዘዘው ካህናት ኃጢአትን የማስተሥረይ ሥልጣን ጌታችን ስለሰጣቸው ነው
ጌታችን ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱንና ቅዱሳን ሐዋርያትን ወደ ዓለም ሄደው አገልግሎታቸውን እንዲጀምሩ ሲያዘጋጃቸው ጌታ በሚገለጥበት ጊዜ ይነግራቸዋል። ከትንሣኤው በኋላ ለእነርሱ፡- “ኢየሱስም ደግሞ፡— ሰላም ለእናንተ ይሁን! አብ እንደ ላከኝ እኔ ደግሞ እልካችኋለሁ። ይህንም ብሎ እፍ አለባቸውና መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ አላቸው። የአንዱን ኃጢአት ይቅር ብትሉ ይሰረይላቸዋል የአንዱንም ኃጢአት ብትይዙ ተይዟል።” ዮሐ 20፡21-23
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ‹‹ካህኑ እግዚአብሔር ለመላእክትና ለመላእክት አለቆች ያልሰጠውን ሥልጣን ተቀብሏል። ……እግዚአብሔር የሰማያትን ሥልጣን ሁሉ አልሰጣቸውምን? ኃጢአታቸውን ይቅር የምትላቸው ይቅር የባልላቸዋል ኃጢአታቸው የያዛችሁባቸው ተይዟል ይላል። ከዚህ የበለጠ ምን ኃይል አለ። አብ ፍርድን ሁሉ ለወልድ ሰጠው አሁን ወልድ ይህንን ሁሉ ስልጣን በሰዎች እጅ ለካህናቱ ሰጠ። ….››
· ኃጢያትን ለበደሉት ሰው መናዘዝ
ይህን ማድረግ የራስብ ልብ ለማስተካከልና ለማረጋጋት ከተበደለው ሰው ጋርም እርቅን ለመመሥረት ይረዳናል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹በመሰዊያው ፊት መባህን አስቀምጠህ ሂድ አስቀድመህ ከወንድምህ ታረቅ ከዛ በኋላ መስዋዕትን ታቀርባለህ›› እንዳለን (ማቴ 5፥24) አስቀድመን ወደ በደልነው ሰው በመሄድ በድያለሁና ይቅር በለኝ ማለት ይገባል፡፡ አባቶቻችን ሳል ይዞ ስርቆት ቂም ይዞ ጸሎት አስሰምርም እንዲሉ በቅዱስ ቃሉ መሠረት ያስቀየምነውን ይቅር ማለት ይገባናል፡፡
ይቆየን
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
it is so important preaching God protect you in his home
ReplyDeleteAmen
Delete"በእውነት በአንድ አምላክ እናምናለን"! እኛም እምነታችንን ለመግለጽ በቤተክርስቲያን የሠራችልንን ተመሳሳይ ቃል እንጠቀማለን፤ ጌታችን እንዳለ "ደግሞ እላችኋለሁ፥ በሰው ፊት የሚመሰክርልኝ ሁሉ፥ የሰው ልጅ ደግሞ በእግዚአብሔር መላእክት ፊት ይመሰክርለታል።"(ሉቃ. 12:8)
ReplyDelete