Thursday, 28 September 2017

መንፈሳዊ አገልግሎት ክፍል ፪



                                                  (ቤተ ሐዋርያት መስከረም ፲፰  ፳፻፲)

እንዴት እናገለግል ዘንድ ይገባል?

1. በእምነት (በመንፈስ)ማገለገል

መንፈሳዊ አገልግሎት በምድራዊ አመክንዮ (logic) ያልተሳሰረ መሠረቱም ጉልላቱም ረቂቅ እምነት የሆነ የአምልኮ ዘርፍ ነው፡፡ በእግዚአብሔር ሳያምኑ መንፈሳዊ አገልጋይ መሆን አይችልም፡፡ ዕምነት የመጀመሪያው አንድ አገልጋይ ሊያሟላ የሚገባው ሰማያዊ የመንፈሳዊ አገልግሎት ስንቅ ነው፡፡ ሳያምኑ ማገልገል ድካም ነው፡፡ የመንፈስ ዝለትንም ያመጣል፡፡ አንድ ጥሩ እምነት ያለው አገልጋይ ከአላስፈላጊ ጭንቀት ነፃ ስለሆነና መንፈስ ቅዱስን የአገልግሎቱ መሪ ስለሚያደርግ የሚያገለግለው በመንፈስ እንጂ በሥጋ አይደለም፡፡ ይህም ማለት አገልግሎቱ የረቀቀ ነው፡፡ ምናልባትም ከአእምሮ በላይ ሆኖ በምን ችሎታ ይህን አደረገው; በየትኛው ጊዜው ሠራው ብለን የምንደነቅበት ነው፡፡ ብዙ አገልጋዮች ትልቁ ችግራቸው አገልግሎታቸው በአእምሯዊ ቀመር (calculation) ብቻ የተሰላ መሆኑ ነው፡፡ እግዚአብሔርን በፀሎት የሚጠይቁ እንኳን ጥቂት ናቸው፡፡ ስለዚህ እንደማንኛውም ሰው ግዙፍ ግዙፍን እንጂ ረቂቁን በርካታና ፀጋ አያገኙም፡፡ ቀመራዊ ስለሆኑና የእምነት መነፅር ስለሌላቸው የፀበል ይዘት እንደማንኛውም ውሃ የሃይድሮጅን እና የኦክስጅን ውሕድ እንጂ ያለበት መንፈስ እግዘአብሔር አይረዳቸውም፡፡ ምክንያቱም ምድራዊ ቤተሙከርራንእንጂ መንፈሳዊነትን አያውቁም፡፡  መናፍቃኑ ስንሳለም አይተው ድንጋይን ይስማሉ (ይቅር ይበላቸውና) እንደሚሉን መንፈሳዊነት ጎድሏቸው በመንፈስ የማያገለግሉት እነዚህ አገልጋዮችም “እግዚአብሔር በጎደለው ይሙላ”የሚለን ንግግር የማያውቁ ከመሆናቸው የተነሳ ሁሉ ነገር በእነርሱ ዝግጅትና ድካም ብቻ የሚሳካ ይመስላቸዋል፡፡ መዝሙር ላይ ተመስጦ የሚባል ነገር አያውቃቸውም፡፡ የማን ድምፅ ወጣ ; የማን ወረደ; እንዴት ልራመድ እንዴት ላጨብጭብና ሰውን ላስደስተው;  ከበሮ አመታቴ ያምር ይሁን ሰው ደስ ብሎት ይሁን; በሚሉና በመሳሰሉት ሐሳቦች ከመጠን በላይ ስለሚዋጡ በመዝሙር ተመስጠው አያውቁም ፡፡ ግን ደግሞ የቅዱስ ያሬድን  የመዝሙር ተመስጦ ታሪክ በደንብ ያውቁታል፡፡ ቅዱስ ያሬድ በአፄ ገብረመስቀል ፊት ሲዘምር ከመመሰጡ የተነሳ ምድራዊን ነገር ሁሉ 'የራሱንም ሥጋ ጭምር ረስቶ በሕሊናው ሰማየ ሰማያትን አቋርጦ ከመላእክት ጋር ያመሰግን ነበር ፡፡ እሱ ይቅርና ንጉሡም ተመስጠው በጦር እስኪወጉ ድረስ በመንፈስ ነበሩ፡፡ ቅዱስ ያሬድ ንጉሡ በተመስጦ ሲንቀሳቀሱ እግሩን ድንግት ቢወጉትም መወጋቱ እንኳን እርሱን ከተመስጦው የመመለስ ኃይል አልነበረውም፡፡በኃላ ዝማሬያቸውን ጨርሰው ዝቅ ቢሉ ምድር ላይ ደም አዩና ነገሩ በዛ ተረዱ፡፡ በእርግጥ ጀማሪ አገልጋይ ሁሉ እንዲህ መሆን አለበት አይደለም ፡፡ አየዘመርን ጉንዳን ስትበላን የምንተረማመስ ሰዎች ጦርን ያህል የቻሉትን ቅዱሳንን አንሁን ማለትም ተገቢ አይደለም ፡፡ ነገር ግን እነሱን መምሰል የተመስጦን ሕይወት የእምነትን በርታት የመንፈሳዊነት መዐዛ ለሰውነታችን ማለማመድ የግድ ነው፡፡ ጉባዔ ሲዘረጋ ተውኔት ሲሠራ ሲዘመር እና ማንኛውንም መንፈሳዊ አገልግሎት ሲገለገል ቢያንስ ጸሎት ያስፈልጋል ፡፡ ከመንፈሳዊነት የራቀ የጉባኤ ድምቀትን አምጥቶ ሰውን ለማስደሰት መጣር ይሁዳን መሆን ነው፡፡ መጀመሪያ እግዚአብሔር ማስደሰት ይቀድማል፡፡እርሱን ደግሞ ካለ እምነትና መንፈሳዊነት ማስደሰት አይቻልም ፡፡ (ዕብ. 11፡6)እግዚአብሔርን ስናስደስት የእርሱ የሆኑት ሁሉ ይደሰቱብናል ፡፡ ለዚህ ነው አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊ “መንፈሳዊነት ከተለየው አገልግሎት አገልግሎት የሌለው መንፈሳዊነት ይሻላል‘  በረለው የተናገሩት ፡፡ ቅዱስ ዩሐንስ ሐፂር በተመስጦ ከሚታወቁትና በመንፈሳዊነታቸው ከሚመሰገኑት አገልጋዮች አንዱ ነበሩ፡፡ በአንድ ወቅት በአታቸው ውስጥ የሆነው ሥራቸውን እየሠሩ እግዚአብሔርን ሲያመሰግኑ በሩ ይንኳኳል ፡፡ ሄደው ሲከፍቱ አንድ መነኩሴ “አባ ቅርጫት እንዲሰጡኝ ነው የመጣሁት‘‘ ይላቸዋል ፡፡ አባ ዩሐንስም በተመስጦ ውስጥ  ስለነበሩ ቅርጫቱን ሊሰጡት ወደ ውስጥ ገቡና ዘንግተውት ያቋረጡት ምስጋና ቀጠሉ ፡፡ በር ለይ የቆመው መነኩሴ ቢቆዩበት መልሶ አንኳኳ፡፡ አባም በሩን ከፈቱና ምን ነበር አሉት ፡፡መነኩሴውም አባ ቅርጫት ብዬዎት ነበርኮ አላቸው ፡፡ ነገር ግን አባ ዩሐንስ ሐጺር ወደ ውስጥ ሲገቡ እንደገና ወደ ተመስጦአቸው ተመለሱ፡፡ መነኩሴው ሲቆዩበት እንደገና አንኳኳ፡፡ አባ ዩሐንስ በሩን ከፈቱና “ምን ነበር;”  አሉት ፡፡ መነኩሴው ጉዳዩንመልሶ ቢያስታውሳቸው አባ ዮሐንስ እጁን አፈፍ አድርገው ወደ በዓታቸው አስገቡትና  “ና የፈለከውን መርጠህ ውሰድ ፡፡ እኔ ለእንደዚህ አይነቱ ጊዜ የለኝም አሉት ፡፡ አንድ መንፈሳዊ አገልጋይን በመንፈስ እንዲያገለግል ዘወትር የሚያንኳኩበት ጉዳዮች አሉት፡፡ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች' ቤተሰባዊ' ኅብረተሰባዊ እና ወቅታዊ ጉዳዮቸ  የስጋ ፍላጎት ወዘተ... ዘወትር በጭንቀት እንጂ በመንፈስ እንዲየገለግል ያንኳኩበታል ፡፡ በዚህን ጊዜ እንደ አባ ዩሐንስ ሐጺር ፈፅሞ የመርሳት የብቃት ደረጃ ላይ ባይደረስ እንኳን በመንፈሳዊነትና በፀሎት ማሸነፍ መቻል የጠበቅበታል ፡፡መንፈሳዊ አገልግሎት በመንፈስ መሆን አለበት ስንል መርሳት የሌለብን ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለው ሁሉ በአግባቡና በሥርዓት መሆን እንደአለበት ነው፡፡ (1ቆሮ. 14፡40) እንደ ቤተክርስቲያን ሕግና እንደ እግዚአብሔር ቃል ማገልገላችንን መመርመር ያስፈልጋል፡፡ ቅዱስ ያሬድ በዐፄ ገብረመስቀል ፊት ሲዘምር ከመመሰጡ የተነሳ ምድራዊን ነገር ሁሉ የራሱንም ሥጋ ጭምር ረስቶ በሕሊናው ሰማየ ሰማያትን አቋርጦ ከመላእክት ጋር ያመሰግን ነብረ፡፡ እሱ ይቅርና ንጉሥም ተመስጠው በጦር እሰኪወጉት ድረስ በመንፈስ ነበሩ፡፡  

2. ሰማያዊን ዋጋን አስቦ ማገልገል

እንደ መንፈሳዊ አገልጋይ ማንኛውንም ምድራዊ ሽልማት አስቦ ማገልገል ከጀመረ ምድራዊውን ዋጋ ሲያጣ አገልግሎቱ ይቆማል፡፡ እግዚአበረሔርን  ሳይሆን እገሌን ብሎ የሚመጣ እገሌ ሲጠፋ  ወይም ሲጣላው አገልግሎቱን ያበቃል ፡፡ እግዚአብሔርን ብሎ  የመጣ ግን ቢጣለና ሲሰደብ እንኳን” ስለ ክርስቶስ ብትነቅፍ የክብር መንፈስ የእግዚአብሔር መንፈስ በናንተ ላይ ያርፋልና ብፁዓን ናችው”፡፡ የሚለውን ቅዱስ መፅናኛ ያስባል ፡፡ (1ጰጥ. 4፡14) ሰማያዊ ዋጋን አሰቦ የመጣሰው ጊዜና ነገሮቸ ሲመቻቹለት ሳይሆን አመቻችቶ ያገለግላል ፡፡ኑሮው ሲሞላለት ' ሀብት ሲሰፋለት ' ዘመድ ሲበዛለት  ጊዜን ለሰጠዎ ጌታ ጊዜ አጣው ብሎ አይቀረም ፡፡ የነበረው ከሆነም  ቤቱ ሲቀዘቅዝ' ድህነት ሲያነቀው' ወዳጅ ዘመድ ሲያጣ ተማሮ አይጠፋም ፡፡ የድራዊ ሁኔታዎች መቀያየር ከአገልግሎት አይለየውም ፡፡ ይልቁንስ ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየኛል;  መከራ ወይስ ጭንቀት 'ወይስ ስደት ወይስ ራብ' ወይስ ራቁትነተወይስ ፍርሃት' ወይስ ሰይፍ ነውን' በማለት ፀንቶ ይዘምራል ፡ (ሮሜ. 8፡35)ሰማያዊ ዋጋን የሚያስብ አገልጋይ አይበረግግም ፡፡ የኑሮ ውድነት' የመንግሥት መለወጥ' የፖሊስ መቀየር እና ሌሎች ምድራዊ ነገሮች አያስደነግጡም ፡፡ ሁሌም ፅኑዕ ነው፡፡ የፅናቱ መጠን ይደንቃል ፡፡ የብርታቱም ልክ ይገርማል ፡፡ መመካቱም በእግዚአብሔር ነው፡፡  የይታይልኝ አመል የለበትም ፡፡ሰው አየው አላየው ግድ የለውም ፡፡ እግዚአብሔር እንደሚያየው ያውቃል ፡፡በብዙ ድካም የተዘጋጀበት መርሐ ግብር ተሰረዘ ሲባል  አያኮርፍም ፡፡ ገና አገልግል ሲባል አቤት የ ሁሉ ሕዝብ አለመብዛት የሚያስጨንቀው ለጥቂት ሰው የተዘጋጀሁትን አቀርባለሁ ብሎ ሳይሆን የቀረውን ሰው  ከቤተክርስቲያን መራቅ በማሰብ ነው ፡፡ ሰማያዊ  ዋጋን ማሰብ አንድን አገልጋይ ከዓለማዊ ሠራተኞች የሚለየው ታላቅ ሀብት ነው፡፡ ምደራዊ ሕሊና ያላቸው መንፈሳዊያን አግልጋዮች ግን በገንዘብ እግዚአብሐርን ያገለግሉበታል ፡፡
3. በትሕትና ማገልገል
ትኅትና ለክረስቲያኖች ከተሰጡት ሀብቶች ሁሉ ውቧ ነች፡፡ ትኅትናና እግዚአብሔርን መፍራት ባለጠግነት ክብር ሕይወትም ነው፡ (ምሳ. 22፡4)፡፡ “እግዚአብሔር ትኁታንን ይወዳል ፡፡ (ያዕ. 4፡6)፡፡ ለስም አጠራሩ ክብር ይሁንና ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  ከእርሱ እንድንማር ካዘዘን ነገሮች አንዱ ትሕትናው ነው፡፡ “ከእኔ ተማሩ እኔ የዋሕ በልቤም ትሑት ነኝ፡፡” (ማቴ. 11፡29)፡፡ጉባኤ ሲዘረጋ ፣ ሲዘመር እና ማንኛውንም መንፈሳዊ አገልግሎት ሲገለገል ቢያንስ ጸሎት ያስፈልጋል ፡፡ ካለ ትሕትና መንፈሳዊ አገልግሎትን መከወን ማለት ፍሬን የበጠሰ (የሌለው) መኪናን መንዳት ማለት ነው፡፡ መኪናው ሄዶሄዶ እንደሚጋጨው አገልጋዩም ከሆነ አካል ጋር መጋጨቱ አይቀርም ፡፡ ካለ ትሕትና በትዕቢት አገልግሎ የፀደቀ ቅዱስ በቤተክርስቲያን ታሪክ ውስጥ የለም፡፡ እንደውም ትልቁን ክብርና ልዐልና የገኙት በትሕትና የተጓዙ ቅዱሳን ናቸው ፡፡ እመቤታችን ድንግል ማርያም ምንም እንኳን በመልአከ እየተመገበች በቅድስና ብታድግም ፣ ሴቶች ጌታን የመተትወለወድ ብለው በሹፈትም ቢሆን ቢጠቁሟትም፤ ቅዱስ ገብርኤል “ትፀንሲ ፣ ትወልዲ” ቢላትም እሷ ግን ያቺ የጌታ እናት በኔ ዘመን ኑራ ምነው ባሪያ  በሆንኳት ትል ነበር፡፡ መለአኩ ለሦስተኛ ጊዜ በቤተመቅደስ እስኪነግራት እና የጌታ እናትነቷን እስከታወቀ  ድረስ ሐሳቧ ይህው ነበር ፡፡ ትሑታንን የሚየከብር እግዚአብሔርም መልዐልተ ፍጡራን ፈጣሪ አደረጋት፡፡ ሙሴንና ኤርሚያስን የመሳሰሉት ቅዱሳንንም ብናነሳ አይገባኝም፤አልችልም እሉ እንደተጋደሉ መጽሐፍ ቅዱስ ይመሰክራል ፡፡ “ወደ ፈርኦን የምሄድ የእስራኤልንም ልጆች ከግብፅ የማወጣ እኔ ማነኝ (ዘጸ.3:6)::ወዮጌታ እግዚአብሔር እነሆ ብላቴና ነኝና እናገር ዘንድ አላውቅም(ኤር.1፡6):: እኔ እያለሁ በማለት ፈንታ አላውቅም ብለው ከበሩ፡፡ጌታ በወንጌል ትሕትናን ለሐዋርያት ሲያስተምር የሚከተሉትን በሏል፡፡ ከእናንተ ታላቅ የሆነ በመካከላችሁ እንደታናሽ የሚገዛም እንዲያገለግል ይሁን፡፡ በማዕድ የተቀመጠ ወይንስ የሚያገለግል ማናቸው ታላቅ ነው; የተቀመጠው አየደለምን; እኔ ግን በመካከላችው እንደሚያገለግል ነኝ”፡፡ ሉቃ 22፡26፡፡ መንፈሳዊ አገልግሎት በመሸነፍ፣ በመሰደብና በመዋረድ ክብር፣ በመሞት ድል  የሚገኝበት የትሕትና ባሕር ነው፡፡ ከትሕትና የራቀ አገልጋይም ከባሕር ውስጥ የወጣ አሳ ነው፡፡ፍሬ የያዘ ዛፍ (ቅርንጫፍ) ዝቅ ይላል ይላሉ አበው፡፡ አባ ኤስድሮስ የተባሉ አባት “ሁል ጊዜ የምትጾም ከሆነ በትዕቢት ራስህን ወደ ላይ አታውጣ፣ ከዚህ የተነሣ ራስህን ከፍ አድረገህ የምትመለከት ከሆነ ግን ብትበላ ይሻላል ፡፡ ለአንድ ሰው ራሱን በትዕቢት ከመንፋትና ራሱን ከማክበር ሥጋ ቢበላ ይሻለዋል፡፡” ብለው የትሕትናን ጥቅም አብራርተዋል ፡፡ አንድ ሌላ አባትም ካልበደለና ጻድቅ ነኝ የሚል ሰው ይልቅ የበደለና ኃጢአተኛነቱን የሚያምን ሰው የሻለኛል ብሎ ስለ ትሕትና ገልጸዋል፡፡ አባ መቃርዮስን በአንድ ወቅት ሰይጣን ተገናኘውና “ካንተ የተነሳ የሚደርስብኝ መከራ ታለቅ ነው፡ ጉዳት ላደርስብህ ስፈልግአልችልም ፡፡ ነገር ግን አንተ የምታደርገውን ማንኛውንም ነገር እኔም አደርገዋለሁ ያውም ካንት አብልጬ አደርገዋለሁ፡፡ አንተ አብዝተህ ትጾማለህ፣እኔ ግን ምግብ የሚባል ነገር ፈጽሞ አልበላም፣ አንተ ለሊት እንቅልፍ በማጣት በትጋት ታድራለህ፣እኔ ግን ጨርሶም አልተኛም፡፡ አንተ እኔን የምትበልጠኝና እኔም እርሱን የምመሰክርልህ በአንድ ነገር ብቻ ነው” አለው፡፡ መቃርዮስም እርሱ ምንድን ነው;ሲለው ጋኔሉ “በትሕትና ነው” አለው፡፡ ቅዱሱም የህን የረቀቀና የመጨረሻ ፈተና ለማስወገድ መሬት ላይ ወደቀ፣ ሰይጣኑም ወደ አየር ተኖ ጠፋ፡፡” (ይህ ፈተና ትሑት ነኝ ብሎ እንዲመካ የቀረበ ረቂቅ ፈተና ነበርና) አንድ መንፈሳዊ አገልጋይ ለአገልግሎቱ ስኬት ትሕትና ያለውን ጠቀሜታ በመረዳት ማገልገል ይጠበቅበታል፡፡
4. በፍቅር /በመሥዋዕትነት ማገልገል
ፍቅር ግብሩ መስጠት ነው፡፡ የሚሰጡበትን ምክንያት ሳይፈልጉ እንዲሁ መስጠት፡፡አብ ዓለምን እንዲሁ ካለምክንያት ወዶ አንድያ ልጁን እንደሰጠ፡፡(ዩሐ. 3፡16)፡፡ መንፈሳዊ አገልግሎት እንዲህ አይነቱን ሕይወት ይሻል፡፡ የመስጠት ሕይወትን፡፡ አገልጋዮች የአገልግሎት ፍቅር ሲገባቸው ጊዜያቸውን ባለመሰሰት ይሰጣሉ፡፡ጉልበታቸውን፣ገንዘባቸውን፣ እውቀታቸውን በጣም የበረቱትም ሕይወታቸውን ጭምር አሳልፈው ይሰጣሉ፡፡መንፈሳዊ አገልግሎት የሚታይ፣ የሚጨበጥን ነገር ሰጥተው የማይታይ፣ የማይጨበጥ ፀጋን የሚቀበሉበት የፍቅር/ የመስጠት ሕይወት ነው፡፡ ስጡ ይሰጣችዋል (ሉቃ. 6፡38) የተባለው ለዚህ ነው፡፡ በዳግም ምፅአቱ ጌታ ጻድቃንን በቀኝ ኃጥአንን በግራ አሰልፎ የሚጠይቀው የፍቅር/የመስጠት ጥያቄን ነው፡፡ ትርቤ አብልታችሁኛል; ተጠምቼ አጠጥታችሁኛል;፣...(ማቴ. 25) የፍቅር የመስጠት ጥያቄዎች ናቸው፡፡ ፍቅር የሌለው አገልጋይ የእግዚአብሔር መሆን አይችልም፡፡ ኃጢአቱ እንኳን የማይሸፈንለት ምስኪን ነው፡፡ በፍቅር የሚያገለግል ግን የኃጢአቱ ብዛት በፍቅር ይሸፈንለታል(1ጴጥ. 4፡8፣ምሳ.10፡12) ካለ ፍቅር እግዚአብሔርን ማወቅና ወደ እርሱ መቅረብ አይቻልም፡፡ ወንጌል የፍቅር ሕግ ናት፡፡ ክርስትና የፍቅር ሃይማኖት ናት፡፡ እግዚአብሔር ፍቅር ነው፡፡ ለዚህ ነው ቅዱስ ጳውሎስ ምንም የሰመረ አገልግሎት ቢኖርም ካለፍቅር ከንቱ እንደሆነ ያስተማረው፡፡ የሰውን ሁሉ ቋንቋ ባውቅ፣ የመላእክትንም ሁሉ ቋንቋ ባውቅ፣ ነገር ግን ፍቅር ከሌለኝ አእንደሚጮህ ነሐስ ወይም እንደሚመታ ከበሮ መሆኔ ነው፡፡ ትንቢት ብናገር፣ የተሰወረውን ሁሉ፣ ጥበብን ሁሉ ባውቅ፣ ተራራ እስከ ማለፍስ የሚያደርስ ፍጹም እምነትም ቢኖረኝ ፍቅር ከሌለኝ ከንቱ ነኝ፡፡ ገንዘቤን ሁሉ ለምጽዋት ብሰጥ፣ ሥጋዬንም ለእሳት ብቃጠል ብሰጥ ነገር ግን ፍቅር ከሌለኝ ምንም አይጠቅመኝም፡፡” 1ቆሮ. 13፡1-3 ፍቅር የሌለው አገልጋይ መስጠትን አያውቅም ደግሞ ጊዜውን፣ጉልበቱን፣ ዕውቀቱን፣ ገንዘቡን በመለገስ ማገልገል አይችልም፡፡ ስለዚህ ፍቅር የሌለው መንፈሳዊ አገልጋይ መሆን አይችልም፡፡
5. በትጋት፣በጸሎትና በቅንነት ማገልገል
አንድ መንፈሳዊ አገልጋይ ተጉህ፣ ጸሎተኛና ቅንዓተ ቤተክርስቲያን ያለው መሆን ይገባዋል፡፡ ለሰው የከበረ ሀብት ትጋት ነው (ምሳ. 12፡27) እንዳለ ጠቢቡ ትጋትን የመሰለ ሀብት ከአገልጋይ ሊለየውአይገባም፡፡ ትጋትን ገንዘብ ያደረገ አገልጋይ ለደካማ ጎኖቹ ዘወትር መፍትሔ ያበጃል፡፡ አባ ቢሾይ የተባሉ አባት በትጉህ ጸሎተኛነታቸው ይታወቃሉ፡፡  በትጋኃ ሌሊት የፀኑ ከመሆናቸው የተነሳ እንቅልፍ እንዳይጥላቸው ፀጉራቸውን ከዛፍ ቅርንጫፍ ላይ አስረው ይጸልያሉ፡፡ እንቅልፋቸውን በርትቶ ዝቅ ሲሉ ፀጉራቸውን ከዛፍ ቅርንጫፍ ላይ አስረው ይጸልያሉ፡፡ እንቅልፋቸውን በርትቶ ዝቅ ሲሉ ፀጉራቸውን ስለሚነጫቸው በርትተው ይፀልዩ ነበር፡፡ አባ አርሳንዮስም ለፀሐይ ማታ ጀርባቸው ሰጥተው ለፀሎት ይቆሙና ጠዋት በምስራቅ በፊት ለፊታቸው ስትወጣ ሥጋቸውን ያሳርፋሉ፡፡ በእነዚህ አባቶች ብቃት ደረጃ ማግኘት ቢከብድም የእነርሱን ብረታት አርአያ በማድረግ ግን መትጋት ያስፈልጋል፡፡  ሌላው ወሳኝ ነጥብ አንድ አገልጋይ ቅንዓት ቤተክርስቲያን ለኖረው የሚገባ መሆኑን ማወቁ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ብዙን መከራና ግፍ ቢደርስበትም “የቀረውን ነገር ሳልቆጥር ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሐሳብ ነው፡፡” እንዳለው(2ኛ ቆሮ. 11፤28) በዚህ መናፍቃን በበዙበት ዘመን አገልጋዮች ለቤተክርስቲያን የሚቀኑ ሰይፎች መሆን ይገባቸዋል፡፡ባጠቃላይ መንፈሳዊ አገልግሎትን በመኪና ከመሰልነው እምነትን/መንፈሳዊነትን(መንፈስ ቅዱስ) በመሪ፣ትሕትናን በፍሬን፣ ሰማያዊን ዋጋን ማሰን በመስታወት ፍቅርን በቤንዚል/ነዳጅ፣ ትጋትን በጎማው መመሰል እንችላለን፡፡ መኪና ካለ መሪው አቅጣጫ እንደማይኖረውና ወደ መድረሻው እንደማሄድ ሁሉ /ካለእምነት መንፈሳዊ አገልግሎትም እንዲሁ ነው፡፡ ካለፍሬን መኪና አደጋ ላይ ይወድቃል ይጋጫል፡፡ አገልግሎትም ካለ ትሕትና እንዲሁ ነው፡፡ ካለ መስታወት የፊቱን ማየት እንደማይችል ሰማያዊ ዋጋን ማሰብም የፊቱን በተስፋ እንደናይ ይረዳናል፡፡ ካለ ቤንዚል/ነዳጅ መኪና የማይንቀሳቀስ ቆርቆሮ ነው፡፡ ካለ ፍቅርም አገልግሎት ከንቱ ድካም ነው፡፡ መኪናው በጎማው ይሄዳል፣ መንፈሳዊ አገልግሎትም በአገልጋዩ ትጋት ይገፋል፡፡ አገልጋዮችና ለማገልገል የሚፈልጉ መንገንዘብ ያለባቸው የነጨረሻው ነጥብ መንፈሳዊ አገልግሎት ከፈተና ርቆ እንደማያውቅ ነው፡፡ ከረቂቁ እስከ ግዙፉ ድረስ ሁሉንም ፈተና በአገልግሎት ላይ ሊያጋጥም ይችላል፡፡ የቤተክርስቲያን ምሥረታዋ በመስቀል ላይ እንደመሆኑከፈተና ርቆ በምድር ደልቶት የፀደቀ ቅዱስ የለም፡፡ የመንፈሳዊ አገልጋይ ሕይወትም በፈተና የታጀበ ሊሆን ይችላል፡፡
አገልጋይ እየበረታ በሄደ ቁጥር በፈተናው ይበረታል፡፡ በዚህን ጊዜ በጸሎት፣ በጾምና በስግደት መጋደል ያስፈልጋል፡፡ ከጭስ ለመሸሽ አሳት ውስጥ አይገባምና ተሸንፎ ማገልገል ማቆም እሳት ውስጥ መውደቅ ነው፡፡ ፀጥ ያለ ባሕር ምርጥ ዋናተኛ አይፈራም እንዲሉ የአገልግሎት ባሕር ፀጥ ያለ አለመሆኑን ተገንዝቦ ምርጥ ዋናተኛ ለመሆን መዘጋጀት አስፈላጊ ነው፡፡ ከመንፈሳዊ አገልግሎት በረከት አይለየን፡፡
                      አገልግሎታችንን ቅዱስ አምላካችን ይባርክልን፡፡ አሜን
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
                                      ምንጭ፡-አትሮንስ መጽሔት መስከረም 2009 ዓ.ም


No comments:

Post a Comment