Sunday, 17 September 2017

ሰማዕትነት

ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ገጽ 871-872 በሰዋሰዋዊ ፤ቀጥተኛ ትርጉሙ ‹ስምዐ› ከሚለው የግእዝ ግስ የተገኘ ሲሆን መመስከር፣ምስክር መሆን፣ያዩትን የሰሙትን መንገር፣አየሁ ሰማሁ ማለት፣ሰማዒ የሚሰማ የሚቀበል ሰሚ መስካሪ ምስክር ሰማዕታት የሚመሰከር /ምስካሮች ማለት ነው፡፡ ሰማዒ ለአንድ ሲሆን ሰማዕታት ለብዙ ነው፤ ሰማዕታት የብዙ ብዙ አንዱን ቅዱስ ‹ሰማዕት› ማለት በአማርኛ ነው፡፡ የእንግልዝኛው ’’Martyt” ከግሪኩ “Martyria“  Martus” የመጣ  ሲሆን በፍቺውም ምስክር “A withess ማለት ነው፡፡

• ምስክርነት

ሰማዕትነት /Martyrdom/ በጥንት ትርጉሙ በብዙኀን በተሰበሰቡበት በአደባባይ በገሃድ ስለሚሰጠው ምስክርነት የቅርብ ዕውቀት የዐይን ምስክር እንዲሉ/ ያለውን ሰው ያመለክት ነበር፡፡ ‹‹አማን አማን እብለከ ከመ በዘናአምር ንነግር ወበዘርኢነ ሰማዕተ ንከውን ወስምዐነሰ ተአብዩነ ነሢአ›› (ዮሐ.3÷11) ‹‹የምናውቀውን እንድንናገር የአየነውን እንድንመሰክር እውነት እውነት እልሃለሁ ግን ምስክርነታችንን አትቀበሉትም›› ይላል፡፡

• ራስን መስዋዕት ማድረግ

በሌላ በኩል በኋላ ዘመን ሰማዕታት የሚለው ቃል ሃይማኖታዊ ትርጉሙ በዋነኛነት ስለ እግዚአብሔርና ስለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በአጠቃላይ ስለ ሃይማኖቱ በእውነትና በእምነት በመመስከሩ ጀርባውን ለግርፋት፣ሰውነቱን ለእሳት፣እግሩን ለሰንሰለት፣ዓይኑን ለፍሰት፣አንገቱን ለስለት አሰልፎ የሰጠ፣በደንጊያ ተወግሮ የሞቱ፣በመንኮራኩር ተፈጭቶ ለዐረፉ ቅዱስ አባት ለዐረፈች ቅድስት  እናት የሚሰጥ ሆኗል፡፡

‹አምስተኛውም ማኅተም በተፈታ ጊዜ ስለ እግዝአብሔር ቃልና ስለጠበቁት ምስክር የታረዱት የሰዎች ንፍሳት ከመሠዊያው በታች አየሁ፡፡ በታላቅ ድምጽም እየጮኹ፡-ቅዱሳኑ እውነታንና ጌታ ሆይ እስከመቼ ድረስ አትፈርድም ደማችንንስ በምድር በሚኖሩት ላይ እስከመቼ አትበቀልም? አሉ፡፡ ለእያንዳንዳቸውም ነጭ ልብስ ተሰጣቸው፡፡ እንደ እነርሱም ደግሞ ይገደሉ ዘንድ ያላቸው የባሪያዎች ባልንጀራዎቻቸውና የወንድሞቻቸው ቁጥር እኪፈጸም ድረስ ገና ጥቂት ዘመን እንዲያርፉ ተባለላቸው› ይላል፡፡ (ራዕ.6÷9-11) ሰማዕታት ስለክርስቶስ ብለው አንገታቸውን ለሰይፍ ደረታቸውን ለጦር የሰጡ፤ከእሳት የተጣሉ፤ከባሕር የተወረወሩ፤ለአውሬ የተሰጡ፤በበረሃና በዱር የተሰደዱ፤የተሰደቡ፤የተራቡ የተጠሙ የታረዙ የተቸገሩ በሙሉ ሰማዕት ይባላሉ፡፡ ኤፌ.13÷20  ሐዋርያው ቅዱስ ጰውሎስ ‹መጋደላችን ከደምና ከሥጋ ጋር አይደለምና ከአለቆችና ከሥልጣናት ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዥዎች  ጋር በሰማያዊ ሥፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳዊያን ሠራዊት ጋር ነው እንጂ› ሲል ስለ ተጋድሎ ገልጾታል በሌላም ክፍል ስለራሱ መንፈሳዊ ተጋድሎ ሲናገር እንዲህ አለ በድካም አብዝቼ፣በመገረፍ አብዝቼ በመታሰር አትርፌ፣በመሞት ብዙ ጊዜ ሆንኩ፡፡ አይሁድ አንድ ሲጎድል አርባ ግርፋት ገረፉኝ፡፡ ሦስት ጊዜ በበትር ተመታሁ፡ አንድ ጊዜ በድንጋይ ተወገርሁ፡፡ መርከቤ ሦስት ጊዜ ተሰበረ ሌሊትና ቀን በባህር ውስጥ ኖርሁ፡፡ ብዙ  ጊዜ በመንገድ ሄድሁ፡፡ በወንዝ ፍርሃት፣በወንበዴዎች ፍርሃት በወገኔ በኩል ፍርሃት፣በሕዝብ በኩል ፍርሃት፣በምድረ በዳ ፍርሃት፣በባሕር ፍርሃት፣በውሸተኞች ወንድሞች በኩል ፍርሃት ነበረብኝ፡፡ በድካምና በረት፣ብዙ ጊዜ እንቅልፍ በማጣት በረሃብና በጥም ብዙ ጊዜ በመጾም በብርድና በራቁትነት ነበርሁ››(2ቆሮ.11÷23-28) ይህን ሁሉ መከራ ከተቀበለ በኋላ ድል አድራጊነቱን ሲገልጽ ‹‹ሰናየ ገድለ ተጋደልኩ በድርየኒ ፈጸምኩ ወሃይማኖትየኒ አቀብኩ-መልካሙን ገድል ተጋድያለሁ ሩጫዬንም ጨርሻለሁ ሃይማኖቴንም ጠብቂያለሁ›› አለ፡፡ (2ኛ ጢሞ 4፥7)ቅዱስ ጳውሎስ ለደቀ መዝሙሩ ጢሞቴዎስ ‹‹የተጠራህለትን የዘለዓለም ሕይወት ትቀበል ዘንድ መልካሙን የሃይማኖት ገድል ተጋደል፡፡›› ብሎታል

ነገር ግን የሰማዕትነቱ ደረጃና ዋጋው ‹‹ኮከብ እምኮከብ ይኄይስ›› እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ አንዱ ከአንዱ ይበላለጣል፡፡እንደነ ቅዱስ ጊዮርጊስ ፤ቅዱስ መርቆርዮስ፤ሠለስቱ ደቂቅ ያሉት ሰማዕትነታችው ታላቅና ባለ100ፍሬ ያለባት ናት፡፡እንደቤተ ክርስቲያን ታሪክ ዘመነ ሰማዕታት የሚባለው ከ160-312 ሲሆን ክርስቲያኖች በጨካኝ ነገስታት እየተንገላቱና እየተሰደዱ ይልቁንም እየተሰየፉ እየተቃጠሉ መከራ ያሳለፉበት ጊዜ ነው፡፡ይህንን ያደረጉ የሮም አበይት ጨካኝ ነገስታት አስር ናቸው፡፡ኔሮን(ከ54-68 ዓ/ም)፤ዲሚቲያን (81-96)፤ትራጃን(98-117)፤ማርቆስ አውሬሊዮስ(161-180)፤ባሌርያን(253-259)፤አውሌሪያን(270-275)፤ሴፕቲመስ(193-211)፤ማክስሚያኖስ(235-238)፤ዳክዮስ(249-251)፤ዲዮቅልጥያኖስ(284-305)  ናቸው፡፡ከነዚህም በኋላ እስከ ሐሳዊ መስህ መነሳት ድረስ የሚነሱ የክርስትና ጠላቶች ያጠቃልላል፡፡ሰማዕታቱም እስከ ዓለም ፍጻሜ ነሳሉ፡፡

እንደ ቤተ ክርስቲያን በሐዲስ ኪዳን የመጀመሪያው ሰማዕት ዲያቆኑ ቅዱስ እስጢፋኖስ ነው፡፡ከርሱም በኋላ ከቅዱስ ዮሐንስ በስተቀር ሐዋርያት ሁሉ ሰማዕትነትን ተቀብለዋል፡፡ሊቀ ሰማዕታት ደግሞ ተብሎ የተሸመና ማዕረግ የተሰጠው ቅዱስ ጊዮርጊስ ነው፡፡ቤተ ክርስቲያን እነርሱን አብነት አድርገው ሰማዕት ለሚሆኑ ሁሉ የቅድስና ክብር ትሰጣለች፡፡


                     
       

የሰማዕታት ክብር

ሰማዕታትን ማክበር ክርስቶስን ማክበር ነው፤የክርስቶስ ሕማምና ሞት የገባው የሰማዕታቱ ሕማም ይገባዋል፡፡ክርስቶስም ስለርሱ ስለሞቱ ታላቅ ክብርና ቅድስና አክሊልን ይሰጣቸዋል፡፡ይህንንም ለመረዳት ሰማዕታቱን በኦሪት መስዋዕት መስለን እንመልከት፡፡

በኦሪት መስዋዕተ ዕለት(የዕለት መስዋዕት) የሚባል ነበር ጠዋት አንድ ማታ አንድ ይሰዋል፡፡የሚቀርቡትም እንስሳቶቹም አንደኛ በግ ኹለተኛ ፍየል ሦስተኛ ወጥይፈንና ጊደሮች አራተኛ ርግብና ዋኖስ ከዚያ ካለፈ እህል ይቀርባል፡፡ በግ የተባሉ ጻድቃን ሰማዕታት ናቸው፡፡ ጌታችንም ሲናገር ‹‹እንደ በግ በተኩላዎች መካከል እልካችኋለሁ›› ማቴ10፤16  በግን ተኩላ እንዲገድላት ሰማዕታት እንደተኩላ በሆኑ ክፉ ነገስታት የመታረዳቸው ምሳሌ ነው፡፡ቅዱስ ጳውሎስም የተሰዉትን እንስሳት በሰማዕታት ሲመስላቸው ‹‹ዕለት ዕለት እንደሚታረዱ በጎች ተቆጠርን›› የሚለውን የዳዊትን ቃል አንስቶ ሮሜ8፤35- ‹‹ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል መከራ ነው ኃዘን ነው ›› ይልና ‹‹ስለአንተ ዘወትር ይገድሉናል እንደሚታረዱ በጎች ተቆጠርን ነገር ግን በወደደን በእርሱ ሁሉን ድል እንነሳለን››በማለት ተናግሯል፡፡

የኦሪት መስዋዕት ጊዜያዊ ኃጠአትን ያስተሰርዩ ነበር ሌላው የነበረውም የደኅንነት መስዋዕት የሚባለው ነው፡፡ይህም የክርስቶስ ምሳሌነት አለው፡፡በአይሁድ አቶንመንት ይሉታል (የማስተሰርያ ቀን ማለት ነው) ፋሲካን ባከበሩ በ7ኛው ወር በ10ኛው ቀን ያከብሩታል የሚውለው በጾም ጊዜ ነው በዚያ ቀን ሁለት አውራ ፍየሎች ይቀርባሉ አንዱ ምድረ በዳ ይለቀቃል አንዱ ይሰዋል በመጨረሻ የደኅንነት መስዋዕት ሁለት በጎች ይቀርባሉ፡፡ፍየሉና በጎቹ የሚቀርቡት ከሕዝቡ ነው አንዱ በግ ከሊቀ ካህናቱx ይቀርባል፡፡የደኅንነት መስዋዕት የተባለው ክርስቶስ ነው በማንም የማተካ አማናዊ ድኅነትን የሚያሰጥ ነው፡፡በሕዝቡ ዘንድ የቀረቡት መስዋዕቶች የሰማዕታት ምሳሌ ናቸው አማናዊውን በግ ኢየሱስ ክርስቶስን መስለው የተገኙ እነ ቅ.ጊዮስርጊስ፤እስጢፋኖስ፤ሕጻኑ ቂርቆስ፤ቅድስት አርሴማ......... የመሳሰሉት ናቸው፡፡እነዚያን መስዋዕቶች አንዱ የደኅንነት መስዋዕት ፍጹም እንደሚያደርጋቸው የሰማዕታትም አክሊላቸው ክርስቶስ ነው ‹‹አክሊሎሙ ለሰማዕት-ለሰማእታት አክሊላቸው ነው›› እንዳለ ቅዱስ ያሬድ ሰማዕታት በክርስቶስ ይከብራሉ፡፡

ሌላው በኦሪት ዘሌዋውያን ከምዕራፍ ሰባት እስከ ዘጠኝ ስናነብ አብዛኛው የኃጢአት መስዋዕት ፍየል ነው፡፡ፍየል የኃጥአን ምሳሌ ነው ፤ማንም ኃጥዕ የነበረ ሰው ስለክርስቶስ አምኖ ሰማዕት ቢሆን ፍጹም ሰማዕት ይባላል፡፡አንዳንዶች ወንበዴ የነበረ፤ዘማዊ የነበረ፤ሱሰኛ የነበረ እንዴት ሰማዕት ሆነ እንዴትስ ይጸድቃል ብለው ይጠራጠራሉ፡፡ለምሳሌ፡- በኦሪቱ ለደኅንነት መስዋዕት ሁለት አውራ ፍየል ይቀርባል አንዱ በበረሃ ይለቀቃል አንዱ ይሰዋል፡፡ምሳሌነታቸውም የክርስቶስ ነው አንዱ ምድረ በዳ መለቀቁ ክርስቶስ ምድረ በዳ ወደተባለች ሲዖል ወርዶ ይህን ሊቃውንቱ ሲመስሉት ምድረ በዳ የተለቀቀው ፍየል ከጌታችን በግራ የተሰቀለው የፈያታዊ ዘጸጋ ፤የተሰዋው ደግሞ የፈያታዊ ዘየማን ይሉታል፡፡ፈያታዊ ዘየማን ምንም ቀድሞ ወንበዴ ቢሆን ለአማናዊው በግ ለክርስቶስ ኃጠአቱን ተናዞ አጠገቡ ያለውን ወንበዴ ገስጾ ምስክርነቱን(ሰማዕትነቱን) አሳይቷል፡፡

በተጨማሪም በኦሪቱ የታዘዘው የእንስሳውን ብልቶች ተቆራርጠው ሲሰዉ የእንስሳውን የውስጥ ብልት(አንጀቱን ጨጓራውን) በደንብ አጥባችሁ ለመስዋዕት አቅርቡ የሚል ነው፡፡ይህንንም የሚያደርግ ሊቀ ካህኑ ነው ፡፡ለጊዜው የእንስሳ ውስጣዊ የሆኑ አካላት አብልጠው መታጠብ ስለሚያስፈልጋቸው ነው፡፡ፍጻሜው ግን ሊቀ ካህን የተባለ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ለመስዋዕት የታጠቡ እንስሳቶቹ(ብልቶች) ሰማዕታት ናቸው ፡፡ቀድመው ምንም ኃጥዕ ቢሆኑ በሊቀካህኑ በኢየሱስ ክርስቶስ ሰማዕትነታቸውን አይቶ ያነጻቸዋል፡፡ከዚህም ባፈ ደግሞ ለምሳሌ ቀድሞ ኢ አማኒ የነበረ ሰው ክርስቲያኖች ሰማዕትነትን ሲቀበሉ አይቶ ቢያምንና እርሱም ሰማዕትነትን ቢቀበል እግዚአብሔር ሰማዕትነቱን እንደተጠመቀና እንደቆረበ ያደርገዋል፡፡

በዘሌ5፤14 እንደሰፈረው የኦሪቱን አውራ በጎች ለመስዋዕትነት ይቀርባሉ በተቀደሰ ነገር ላይ የበደሉ ሰዎች ምንም አማራጭ(ፍየል፤ዌፌን፤ጊደር እህል) የሌለው አውራ በግ ብቻ ያቀርባሉ፡፡የሚገዛው ደግሞ ቤተ መቅደስ ነው፡፡ተመኑንም የሚያወጣው ደግሞ ሊቀ ካህናቱ ሲሆን ገዢው ሰው የዋጋውን አንድ አምስተኛ ይጨምርበትና ለመስዋእትይቀርባል፡፡ምሳሌነቱም አውራ በግ የተባሉ እነ ቅዱስ ጊዮርጊስ ፤መርቆርዮስ ናቸው፡፡ሊቀ ካህኑ ተመኑን እንደሚያወጣ የሰማዕታትንም ክብርና ዋጋ የሚያወጣና የሚያድል አንድ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ማንም ፍጠሩ የሰማዕታትን ነገር አቅልሎ በይመስለኝ ሊሰፍረው አይችልም፡፡ይልቁንም እግዜር ባወቀ ባለ 30 ባለ60 ባለ100 ብሎ ቅድስናን ይሰጣቸዋል፡፡ በኦሪት ዕለት ዕለት እንስሳቱ እንደሚሰዉ(የዕለት መስዋዕት) ሰማዕታትም ቅዱስ ዳዊት  ‹‹ዕለት ዕለት እንደሚታረዱ በጎች ተቆጠርን›› እንዳለው ሰማዕታት እስከ ዓለም ፍጻሜ እየተነሱ ይኖራሉ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም ቅድስናቸውን በስንክሳር በገድል በተአምር አስፍራ ዕለት ዕለት ታስባቸዋለች፡፡ 

 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

 

No comments:

Post a Comment