(ቤተ ሐዋርያት መስከረም ፲፰ ፳፻፲)
አገልግሎት ምን ማለት ነው?
አገልግሎት የሚለው ቃል ገልገለ ከከሚለው የግእዝ ግስ የተገኘ እንደሆነ ይጠቁማል፡፡ ገልገለ (አገለገለ)ማለት ተገኣ፣ ታዘዘ፣ ዐገዘ፣ ረዳ፣ ጠቀመ፣ ማንኛውንም ሥራ ሠርቶ ጌታውን ደስ አሰኘ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ አገልግሎት ማለተ መታዘዝ፣ መገዛት፣ መረዳት መጥቀም... ማለት ይሆናል፡፡ ማንኛውንም ሥጋዊና መንፈሳዊ ሥራ አገልግሎት ነው፡፡ ለመንግሥት የሚሰራ የመንግሥት አገልጋይ፣ ለግለሰብ የሚሠራ የግለሰብ አገልጋይ፣ ለእግዚአብሔርም የሚሠራ የእግዚአብሔር አገልጋይ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ አገልጋዮችን በተለያየ ስያሜ ጠርቷል፡፡ ምንም አይነት መብት በራሱ ላይ የሌላውንና በጌታው ሐሳብ ፍፁም አዳሪ የሆነውን ተገዢ ባሪያ በማለት ገልፆታል ፡፡ ንዋይ ኅሩይ ቅዱስ ጳውሎስ “ከሰው ሁሉ አርነት የወጣሁ ስሆን የሚበልጡትን እንዲጠቅም እንደባርያ ራሴን ከሁሉ አስገዛለሁ” በማለት የተናገረው ይህን ያጠናክራል፡፡ (1ቆሮ. 9፡19) አብሮት የሚያገለግለውን ቲኪቆስንም “በጌታም አብሮኝ ባሪያ የሆነ” በማለት ጠርቶታል፡፡ (ቁላ. 4፡7) ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም አርነት ወጥታችሁ እንደ እግዚአብሔር ቅዱሳን ባሪያዎች ሁኑ በማለት አገልግሎታችን በፍፁም መገዛት እንዲሆን ይመክረናል፡፡ (1ጴጥ. 2፡16) በራሱ ላይ ሙሉ ነፃነት ያለውን አገልጋይ መጽሐፍ ቅዱስ ሠራተኛ ይለዋል፡፡ (ሉቃ. 10፡2፣ ቆላ. 4፡11፣ 2ጴጥ. 1፤8) ይህ ከባሪያ ይልቅ በራሱ ላይ የመወሰን ሥልጣን ያለው ነው፡፡ ከፈለገ አለማገልግለ ይችላል፡፡ በባሪያና በሠራተኛ መካከል ነፃነቱ የሆነው ደግሞ ብላቴና፣ ሎሌ ተብሎ የተጠራው ነው፡፡መንፈሳዊ አገልግሎት የምንለው የእግዚአብሔር የሆነውና መንፈሳዊ ዓላማን መሠረት በማድለግ የሚገለገለውን ነው፡፡ መንፈሳዊ አገልግሎትን ከሌሎች አገልግሎቶች/ ሥራዎች የሚለዩት በርካታ ጠባያት አሉ፡፡ ትልቁና መሠረታዊው ልዩነት ዓላማው ነው፡፡ በመንፈስ ቅዱስ የሚመራ የመንፈሳውያን ሰዎችና የሰማያውያን መላእክት ረቂቅ ኅብረትና አንድነት የሚገለፅበት በማይታይ ፀጋ ወደ ክርስቶስ በእውነትና በፍቅር የሚሳድግ (ኤፌ. 4፡15) የሐዋርያዊት ቤተክርስቲያን ስንተረጉም ማንኛውም ሥራ ሠርቶ ጌታውን ደስ ማሰኘት ነው ካልን መንፈሳዊ አገልግሎትም ጌታው እንደእግዚአብሔር ነውና እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ማንኛውንም ሥራ መሥራት ነው፡፡ (ሮሜ. 12፡1)እግዚአብሔር ደስ ማሰኘት የሚቻለው ደግሞ በዕምነት ብቻ በመሆን (ዕብ. 11፡6)መንፈሳዊ አገልግሎት የመታመን ሥራ ነው፡፡ ሃይማኖት ማለት ማመንና መታመን ማለት እንደመሆኑ አምላክን አምነን የምንታመነው በመንፈሳዊ አገልግሎት መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡
መንፈሳዊ አገልጋይ ማን ማነው?
እንዲያገለግሉኝ ሕዝቤን ልቀቅ (ዘፀ. 7፡16) እግዚአብሔር አምላክ እስራኤላዊያንን ከዘመናት የግብፅ ስደት ወደ ምድረ ርስት የመመለሻው ወቅት በደረሰ ጊዜ በሙሴ በኩል ፈርኦንን እንዲያገለግሉኝ ሕዝቤን ልቀቅ (ዘፀ 7፤16) ብሎታል፡፡ የእስራኤላዊያን ከስደት መመለስ ለመንፈሳዊ አገልግሎት ነው ፡፡ በሌላ አነጋግር ከስደት የመፈታታቸው ዓላማ አገልግሎት ነው፡፡ ከስደት ተመልሶ እግዚአብሔርን የማያገለግል በስደት ቢኖር ይሻለዋል፡፡ “እንዲያገለግሉኝ” ብሏልና፡፡ በተመሳሳይ የሰው ልጅ የመፈጠሩ ዓላማ ሃይማኖት እንደመሆኑና ሃይማኖት ደግሞ የማመንና የመታመን ጉዳይ በመሆኑ' እንደዚሁም መታመን በመንፈሳዊ አገልግሎት ስለሆነ እግዚአብሔር የማያገለግል ሰወ የመፍጠሩን ዓላማ ሰቷልና ባይፈጠር ይሻለዋል ፡፡ እዚህጋ መንፈሳዊ አገልግሎት ስንል በጠበበው ትርጉም የተለመዱትን የክህነት' የሰ/ት/ቤት ወይም የመንፈሳዊ ማኅበራትን አገልግሎት ብቻ ማለታችን አይደለም፤መሠረታዊ የክርስትና ተግባራትንና የምስጋና ሕይወት አጠቃለልን እንጂ፡፡ በዚህ አረዳድ ሰው ሁሉ መንፈሳዊ አገልጋይ ነው፡፡ ለዚህ ነው ቅዱስ ጳውሎስም ስወን የእግዚአብሔር የተቀደሰ መቅደስ ብሎ የጠራው፡፡ (1ቆሮ. 3፡16) ታላቁ የቤተክርስቲያን ሊቅ ቅዱስ ዩሐንስ አፈወርቅ በሉቃ 6፡38 ላይ ጌታችን “ስጡ ይሰጣችዋል” ያለው ቃል ሲተረጉመው መንፈሳዊ አገልግሎትን የተመለከተ ቃል ስለመሆኑ መስክሯል፡፡ ጌታ ስጡ ማለቱ አገልግሉ ማለት ነው፡፡ የምድሩን ትታችሁ' ጊዜያችሁን ሰውነታችው ጉልበታችውን ገብራችሁ ዕውቀታችሁን አፍሳችሁ ገንዘባችሁን በጅታችሁ ብታገለግሉ እኔ ደግሞ በጸጋ ላይ ጸጋ በበረከት ላይ በረከት በሕይወት ላይ ቅድስናን አሰጣችኋለሁ ሲል ነው ይላል ሊቁ፡፡ የመንፈሳዊ አገልግሎት መለያዎች ምንም እንኳን አንድ ሰው ቅዳሴ' ምስጋና 'ምስክርነት እና የመሳሰሉትን ከሁላዊት ቤተክርስቲያን የተገኙ ሁሉንም የሚያሳትፍ ሁላዊት አገልግሎቶች ላይ መሳተፍ ግዴታው ቢሆንም በሰንበት ት/ ቤቶች' ቤተክርስቲያን ማኅበራትወይም በተለያዩ መንፈሳዊ ኃላፊነቶች ለማገልገል የሚያስቡ ከሆነ የመንፈሳዊ አገልግሎት የተለዩ ጠባያትን አጥርቶ ማወቅ አለበት፡፡ ይህ ካልሆነ አገልግሎቱ እንደማንኛውም ዓለማዊ ሥራ ከመሆኑም ባሻገር በረከት የተለየው ድካም ይሆናል፡፡ስለዚህ ከዚህ በታች የተዘረዘሩ ነጥቦች በመንፈሳዊ አገልግሎት ላይ ላሉ አገልጋዮችም ሆነ ለማገልገል ለሚሹ አስፈላጊ ናቸው፡፡ መንፈሳዊ አገልግሎት የምንለው የአግዚአብሔር የሆነውንና መንፈሳዊ ዓላማን መሠረት በማድረግ የሚገለገለውን ነው፡፡
ይቆየን
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ምንጭ፡-አትሮንስ መጽሔት መስከረም 2009 ዓ.ም
No comments:
Post a Comment