የንስሐ ደረጃዎች
• ንስሐ ለመግባት ማሰብ
• ኃጠያትን መተው
• ኃጢያትን መጥላት
ንስሐ እንዴት እንገባለን?
በገቢር ለፈጸምናቸው ኃጢአቶቻችና የግድ ንስሐ ያስፈልጋል፡፡ እንደኃጢያት የሚቆጠርና የማይቆጠር ኃልዮም አለ፡፡ እሰርቃለሁ ብሎ ሄዶ ሰው ነቅቶበት ውሻ ጮኾበት አጥር ጸንቶበት ቢመለስ ሌላ ከለከለው እንጂ ያደርገው ነበርና ንስሐ ያስፈልገዋል፡፡ ከመንገድ ሳለ ግን ፈጣሪየ ያየኛል እርሱ ይፈርድብኛል ብሎ ቢመለስ እንደኃጢያት አይቆጠርበትም ነገር ግን ኃጢያት ጠልቶ አልተመለሰምና ፍጹም አይደለም፡፡
ኑዛዜ
ኑዛዜ አራት መሠረታዊ ነጥቦችን ያጠቃልላል፡፡ አንደኛው ኃጢያትን ለራስ ሕሊና መናዘዝ ኹለተኛው በጸሎት በደልን ለእግዚአብሔር መናዘዝ ሦስተኛ በደልን ለካህን መናዘዝ አራተኛው ለበደሉት ሰው መናዘዝ ናቸው፡፡
ኃጢያትን ለራስ ሕሊና መናዘዝ
ኃጢያትን በመናዘዝ ውስጥ የመጀመርያው ደረጃ ኃጢያትን ለራስ ሕሊና መናዘዝ ነው፡፡ የሰው ልጅን እግዚአብሔር ሲፈጥረው ማመዛዘን የሚችልበትን አእምሮ ሰጥቶ ፈጥሮታል ስለዚህም ይህ ሕሊና ለሰው ልጅ ሲበድል ወቃሹ እውነተኛ ዳኛ ነው፡፡ ሕግ ተሰርቶልን ኦሪትንና ወንጌልን ሳናውቅ በፊት ክፉውን ከበጎ እንድንለይበት እግዚአብሔር በድንቅ አፈጣጠሩ ፈጥሮልናል፡፡ ሰዎች ታዲያ ክፉ ሲያደርጉ ይወቅሳቸው ዘንድ በጎ ሲሰሩ ያበረታቸው ዘንድ፡፡ በጎ ሕሊና ያለው ሰው ኃጢያት በሰራ ጊዜ ኃጠያቱን እንደሰራ ያምናል፡፡ ለራሱም ኃጢያቱን አምኖ ይናዘዛል በድያለኹ ይላል ይህም የንስሐ የመጀመርያው ደረጃ ነው፡፡ታላቁ መቃርስ እንዳለን ኃጢያትን ለራስ መናዘዝ እግዚአብሔር ሳይፈርድብን አስቀድመን ራሳችን ላይ መፍረድ ነው፡፡ በቅዱስ ወንጌል ተጽፎ የምናገኘው የጠፋው ልጅ ወደ ልቡ ተመልሶ እንዳለ ‹‹ እንጀራ የሚተርፋቸው የአባቴ ሙያተኞች ስንት ናቸው እኔ ግን ከዚህ በረኃብ እጠፋለሁ፡፡ ተነስቼም ወደ አባቴ እሄዳለሁና፡፡ አባቴ ሆይ በሰማይና በምድር በደልኹ ወደ ፊትም ልጅ እባል ዘንድ አይገባኝም ከሞያተኞትህ እንዳንዱ አድርገኝ እለዋለኹ›› ብሎ ኃጢያትን በቅድሚያ ለራስ እንደተናዘዘ እንዲሁ እኛም ከኹሉ በፊት ኃጢያታችንን በማመን እንናዘዝ ዘንድ ይገባል፡፡ (ሉቃ 15፥17-19)
በጸሎት በደልን ለእግዚአብሔር መናዘዝ
ኃጢያት መስራት በመጀመርያ ደረጃ እግዚአብሔርን መበደል(ማሳዘን) ስለሆነ ለእግዚአብሔር መናዘዝ ይገባናል፡፡ ቅዱስ ዳዊት በኃጢያት በወደቀ ጊዜ እንዲህ አለ ‹‹ አንተን ብቻ በደልኩ በፊትህም ክፉን አደረኹ››(መዝ 50፥4) ነቢዩ ዳንኤልም በጸሎቱ እንዲህ አለ ‹‹ አምላክ ሆይ ኃጢያትን ሰርተናልና በድለንማል ክፍትም አድርገናል አምጸናል ከትእዛዝህና ከፍርድህም ፈቀቅ ብለናል፡፡›› እንዳለ (ት. ዳን 9፥5) እንዲሁ እኛም የእነዚህን ታላላቅ አባቶች ጸሎት ጸሎታችን እናደርግ ዘንድ ይገባናል፡፡
በደልን ለካህን መናዘዝ
የእግዚአብሔር እንደራሴ በሆነ አገልጋይ ፊት መናዘዝ በእግዚአብሔር ፊት መናዘዝ ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ እንደምናነበው ኢያሱ አካንን ‹‹ልጄ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ክብርን ስጥ ለእርሱም ተናዘዝ ያደረከውንም ንገረኝ አትሸሽገኝ›› (ኢያ 7፥19) እንዲሁም ወደ መጥምቁ ዮሐንስ የመጡ ኹሉ ኃጢያታቸውን እየተናዘዙ የንስሐ ጥምቀት ተጠምቀዋል፡፡ (ማቴ 3፥6) በሐዋርያት አገልግሎትም ያመኑ ብዙ ሰዎች ኃጢያታቸውን ይናዘዙ ነበር (ሐዋ 19፥18)
ካህኑ ፊት ኃጢያትን መናዘዝ አንደኛ በካህኑ ፊት የተናዘዘውን ኃጢያት ዳግም እንዳይሰራ መንፈሳዊ ብርታት ይሆነዋል፡፡ ኹለት ፍጹም የኃጢያት ሥርየት የሚገኝበትን ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ለመቀበል የሚያስችል ፍቃድ ያገኛል፡፡
ኃጢያትን ለበደሉት ሰው መናዘዝ
ይህን ማድረግ የራስብ ልብ ለማስተካከልና ለማረጋጋት ከተበደለው ሰው ጋርም እርቅን ለመመሥረት ይረዳናል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹በመሰዊያው ፊት መባህን አስቀምጠህ ሂድ አስቀድመህ ከወንድምህ ታረቅ ከዛ በኋላ መስዋዕትን ታቀርባለህ›› እንዳለን (ማቴ 5፥24) አስቀድመን ወደ በደልነው ሰው በመሄድ በድያለሁና ይቅር በለኝ ማለት ይገባል፡፡ አባቶቻችን ሳል ይዞ ስርቆት ቂም ይዞ ጸሎት አስሰምርም እንዲሉ በቅዱስ ቃሉ መሠረት ያስቀየምነውን ይቅር ማለት ይገባናል፡፡
የንስሐ መሰናክሎች
ሰዎች ንስሐ እንዳይገቡ የሚከተሉት ምክንያቶች መሰናክል ያሆኑባቸዋል፡፡
• ኃጢአትን አለማመን (ራስን በማጽደቅ ኃጢያተኛ እንዳልሆነ ማሰብ)
• የራስን ኃጢያት ከሰዎች ጋር በማነጻጸር የተሻሉ እንደሆኑ ማሰብ
• በማዘግየት ለንስሐ የተዘጋጀውን ልቡና መለወጥ የንስሐ እድልንም ማጥፋት
• ተስፋ መቁረጥ
እነዚህ መሰናክሎች ዘወትር ንስሐ እንዳንገባ እንድንዘናጋ ገና ነኝ ጊዜ አለኝ እንድል ያደርጉናል፡፡ በዚህም ምክንያት ብዙዎች ከንስሐ ራሳቸውን ያርቃሉ፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ግን በመልእክቱ “እውነትን በዓመፃ በሚከለክሉ ሰዎች በኃጢአተኝነታቸውና በዓመፃቸው ሁሉ ላይ የእግዚአብሔር ቍጣ ከሰማይ ይገለጣል፡፡” (ሮሜ 1፡18) እንዳለን የእግዚአብሔር ቁጣ ከመገለጡ በፊት ራስን ለንስሐ ማዘጋጀት ይገባል፡፡ እንዲሁ“ወይስ የእግዚአብሔር ቸርነት ወደ ንስሐ እንዲመራህ ሳታውቅ የቸርነቱንና የመቻሉን የትዕግሥቱንም ባለጠግነት ትንቃለህን? ነገር ግን እንደ ጥንካሬህና ንስሐ እንደማይገባ ልብህ የእግዚአብሔር ቅን ፍርድ በሚገለጥበት በቍጣ ቀን ቍጣን በራስህ ላይ ታከማቻለህ።” (ሮሜ 2፡5) የእግዚአብሔር ቸርነት ወደ ንስሐ የሚመራ እንጂ በቸልተኝነት የእግዚአብሔር ቁጣ በራሳችን ላይ እንዳይገለጥ ራስን ለንስሐ ማዘጋጀት ይገባል፡፡
ይቀጥላል በክፍል ሦስት በንስሐ የሚገኙ ለውጦች እንዲሁም ተነሳሒው በኃጢያት ዳግም እንዳይሸነፍ ሊያደርጋቸው የሚገባቸውን ጥንቃቄዎች እንመለከታለን
ይቆየን
ስብሐት ለእግዚአብሔር
No comments:
Post a Comment