(በዲ/ን ፍሬው ለማ ቤተ ሐዋርያት መስከረም 16/2008 ዓ.ም)
"በመስቀሉ ገነትን የከፈለ ክርስቶስን እናወድሰዋለን ቅዱስ ያሬድ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በአደባባይ ከሚከበሩ በዓላት መካከል አንዱ የሆነው የቅዱስ መስቀል በዓል በሚከበርበት ዓማዊ በዓል ላይ ደርሰናል፡፡የዚህ ወቅት ማለትም የመስከረም ሶስተኛ ሳምንት(ከመስከረም 15-25) መዝሙር ዝ ውእቱ መስቀል ይባላል፡፡ በዚህ መዝሙር ውስጥ ነው በመግቢያ ላይ የጠቀስነው ቃል ያለው፡፡ የቅዳሴ ምንባባቱም ምልጣኑም ወረቡም ቁመቱም ይህን የጌታ ሥራ የሚያዘክሩ ናቸው፡፡
ይህ ወቀት በኢትዮጵያ ምእመናን ዘንድ ታሪካዊ፣ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ ገፅታ አለው፡፡ በዚህ ጽሐፍ ውስጥ ሀይማኖታዊ ገፅታውን እናያለን፡፡ መስቀል የሚለው ቃል በኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል በተዘጋጀው የአማርኛ መዝገበ ቃላት
ላይ ለሦሥት ነገሮች መጠሪያነት ሊያገለግል እንደሚችል ተጽፏል፡፡
1. መስቀል ቀጥ ባለ እንጨት አናት አካባቢ ሌላ አጠር ያለ እንጨት በማጋደም ሁለቱን በማያያዝ የሚዘጋጅ በጥንት እስራኤላዊያንና ሮማውያን ጊዜ ወንጀለኞችን ለመግደል ያገለገለ መስቀያ፣
2. ከብረት፣ እንጨት፣ የሚዘጋጅ ክርስቶስ የተሰቀለበት ምሳሌ እና የክርስትና እምነት ተከታዮች ምልክት፣
3. የክርስቶስ መስቀል ከተቀበረበት ቦታ መገኘትን ምክንያት በማድረግ መስከረም 17 ቀን የሚከበር በዓል፡፡
ከዚህም በላይ በክርስትና ውስጥ ስለ ክርስቶስ ሲባል የምንቀበለውን ፀዋትወ መከራም መስቀል እንለዋለን ዘኢጾረ መስቀለ ሞትየ ኢይክል ይፀመደኒ ማቴ 10፡38 እንዲል ይህም መከራ ውስጣዊም ውጫዊም ነው፡፡ ውስጣዊው ከፍትወት/ምኞት የተነሳ የሚመጣብን ሐልዮ ነው፤ ውጫዊው ከሰይጣን(ከአለም) የሚቀርብልን መከራ ነው፡፡ ከእነዚህም በአኮቴት የምንቀበላቸው እና በመስቀሉ ድል የምንነሳቸው አሉ፡፡
መስቀል ከሥላሴ፣ከእመቤታችን ምስጋና ቀጥሎ ምስጋና የሚቀርብለት ታቦት የተቀረፀለት መልክዕ(ውዳሴ) የተደረሰለት የመማጸኛ ጸሎት (መስተብቁዕ ዘመስቀል) የተጻፈለት በነገረ ድህነት ውስጥ ካሉ ታላላቅ ተስፋዎች፣ምልክቶች አንዱ ነው፡፡ በኢትዪጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በነገረ ድህነት ውስጥ ሁለት ታላላቅ ምስክሮችን(ተስፋዎችን) እንዘክራለን፡፡እነዚህም እመቤታች እና ቅዱስ መስቀል ናቸው፡፡ ሁለቱም በተለያዩ ህብረ አምሳል በብሉይ ኪዳን መጻሕፍት የተገለጡ ናቸው፡፡እመቤታችን ድንግል ማርያም የድህነታችን መሰረት እና መጀመሪያ የሆነች ጌታ ከእርሷ ሥጋን ይነሳ ዘንድ የተገባች ሆና የተገኘች ነችና አንድም የሰውነታችን ባሕርይ የከበረባት የታደሰበት ነች፤ ቅዱስ መስቀሉም ለጠላት ማሳፈሪያ ምልክት ሆኖ የተሰጠን በእመቤታችን ማህፀን የተጀመረው ድህነት የተፈፀመበት በመለኮት ደም የተቀደሰ በክርስቶስ ያገኘነው የትንሣኤ ሰላማችን አርማ ነው፡፡ ለዚህም ነው አባቶች በመስተብቁዕ ዘመስቀል ጸሎታችን በእንተ ዝንቱ አዘዙ መምህራነ ቅዱስ ወንጌል አምሳለ ፈጣሪ ልዑል ንሰግድ ለመስቀል ወለማርያም ድንግል ስለዚህም የቅዱስ ወንጌል መምህራን ለልዑል በሚቀርብ ስግደት አምሳል(በጸጋ) እንድሰግድላቸው አዘውናል::
ከማርያም ድንግልም ከሥጋዋ ሥጋን ነስቷልና ከእርሷም መድኃኒትን አግኝተናልና ለመስቀልም የቃል ደም በላዩ ተንጠባጥቧልና ያሉት በመልክዐ ሥላሴም ላይ ሰላም ለኵልያቲክሙ በሚለው ሥር ተፈጸመ ተስፋ አበው በማርያም ድንግል ወበቀራንዮ ተተክለ መድኃኒት መስቀል የአበው ተስፋ በድንግል ማርያም ተፈጸመ በቀራንዮም መድኃኒት የሆነ መስቀል ተተከለ ተብሎ ተጽፏል ፡፡ ይህም ከላይ የጠቀስነውን ሐሳብ የሚያጠናክርልን ነው፡፡ የሁለቱም(እመቤታችን እና ቅዱስ መስቀል) በአምልኳችን ውስጥ ተደጋግሞ መነሳት ምክንያት ከላይ በጠቀስነው ነገረ ድህነት ውስጥ ካላቸው ሥፍራ የተነሣ ነው፡፡ ክርስቲያን ዘወትር በአዕምሮው ከሚያሰላስለው የክርስቶስ የማዳን ስራ በተጨማሪ በአንገቱ የሚያጠልቀው መስቀል፣በየአብያተ ክርስቲያናቱ ጉልላት ላይ የሚደረጉ መስቀሎች፣ በካህናት እጅ የምንሳለመው መስቀል አለ እነዚህ ሁሉ በተግባርም ይህን ነገረ ድህነትየምንመሰክርባቸው ናቸው፡፡
መስቀል አምላካችን ለሰው ልጅ ፍቅሩን የገለጸበት ታላቁ የፍቅር ት/ቤት ነው፡፡ በምድር ታሪክ ውስጥ ተደርጎ የማያውቅ ወደፊትም የማይደረግ ታላቁ የፍቅር ሥራ በመስቀል ተደርጓል፡፡ እግዚአብሔር ፍጥረታቱ ሲበድሉ ዝም ብሎ የሚያይ አምባገነን ወይም ምንም ማድረግ የማይቻለው ደካማ አይደለምና ወርዶ ተወልዶ ይልቁንም ሞቶ አዳነን እርሱ ግን ፍጥረቶቹን አልተወንም ቸልም አላለንም እርሱን እንደበደልነው መጠን ፈጽመን እንጠፋ ዘንድ በኃጢአታችን አልተቀየመንም፣ወደደን እንጂ፣ጎበኘንም፣ማረን፣ይቅርም አለን፣ከሚገዛንም እጅ አዳነን እንዲል ቅዳሴ ዘዮሐንስ አፈ ወርቅ፡፡
ከሌሎች የእምነት ድርጅቶችም ተለይተን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን (1ቆሮ1፡23) የክርስቶስን ሞት መቀበል የክርስትና የእምነት መሠረት ነው፡፡ ይህም እንዴት የሰውን ሥጋ ይነሳል እንዴትስ ይሞታል ብለው አምላክን ያከበሩ ለሚመስላቸው ሞኝነት ነው፡፡ የሐዲስ ኪዳን ታላቁ ምስጢር ይህ የአምላክ ለፍጥረቶቹ ሲል መሞት ነው፡፡ በሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት ክርስቶስ በሰውም፣ በእርሱም በመላእክትም አንደበት ይሞት ዘንድ እንዳለው ተደጋግሞ ተገልጧል፡፡ ይልቁንም ከትንሳኤው በኋላ እንኳን የሞተው፣የተሰቀለው ተብሎ ተቀጽሎለታል(ማቴ28፡5፣ሮሜ8፡34፣ራዕ1፡18፣ራዕ2፡8) የመምጣቱም ትልቅ ዓላማ ይሞት ዘንድ ነው ይህም በመስቀል ላይ የተፈጸመ ነው፡፡
አባታችን ዮሐንስ አፈ ወርቅ የመዝሙረኛውን ቅዱስ ዳዊት ቃል ሰነፍ በልቡ አምላክ የለም ይላል መዝ13፡1 በተረጎመበት ድርሳኑ እንዲህ ብሏል ክርስቶስን ተሰቅሎ ማየት ያልቻለ በዚህ ስንፍናው ይገለጣል ብሏል ፡፡ ስንፍና የተባለውም ክርሰቶስን እንደተሰቀለ አለማመን ነው (ገላ3፡1)፡፡ በዚህም ቸልተኝነቱ እግዚአብሔርን አያየውም፡፡ የእግዚአብሔርን ኃይል፣ ድል፣ ጠላትን ማሳፈር ማየት፤ማወቅ ለሚፈልጉ ሁሉ መስቀል ታላቁ ምላሽ ነው፡፡የክርስቶስ ሕማም የአምልኳችን መሰረት እና ሁሉ ነገራችን ነው በየቅዳሴው ይህንን ሕማሙን እንሳተፋለን በጥምቀት ከእርሱ ጋር እንሞታለን እንነሳለን የዓመቱ የአምልኮ ጊዜያት በሕማማት ማዕከልነት የተሰደሩ ናቸው ሳምንታችንም የአይሁድን ፍርድ እና ስቅለትን የሚያዘክሩ የአዕፅዋማት ቀኖች ያሉት ነው በቃልም፣በሐሳብም፣በተግባርም መከራውን እናስባለን፡፡
እግዚአብሔር ኃጢአትን፣ ሞትን ፣ በአጠቃላይ ክፉ ነገርን በምድር ላይ እንዲሆን አልፈቀደም አይፈቅድምም፡፡ ለዚህም ትልቁ ማሳያችን ጠላታችንን በመስቀል ጠርቆ ያሳየን ሰላም ነው፡፡ ያለ መስቀል እግዚአብሔርን እና በእኛ ላይ ያለውን አለማ መረዳት አይቻልም፡፡ ክርስቶስ እንደሞተ እና እንደተነሳ እኛም የዚህ ተሳታፊዎች መሆን እንዳለብን የማያስብ ሁሉ ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ እንዳስተማረን ለክርስቶስ ሊሆን አይገባውም(1ዮሐ4፡23) ፡፡ የሰው ልጅ በእግዚአብሔር አርአያ እና አምሳል የተፈጠረ ታላቅ ፍጡር ነው፡፡ ይህም ብቻ አይደለም አምላክ ሰው ሆኖ ያዳነውም ታላቅ ፍጡር ነው፡፡ ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ እርሱ በአምላክነት ያደረገውን(የሆነውን) ሁሉ እኛ በጸጋ እንሆን ዘንድ አድሎናል (ልጅነት፣ንጉሥነት፣ቅዱስነት) ይህ ግን ብቻ አይደለም በስሙ መከራ እንቀበል ዘንድ ጭምር ነው እንጂ ስለ እርሱ መከራ ደግሞ ልትቀበሉ እንጂ በእርሱ ልታምኑ ብቻ አይደለም ፊል1፡29 እንዳለ ሐዋርያው ይህንን ተልዕኳንችን እንፈፅም ዘንድ መስቀል ምልክታችን ነው ክርስቲያን ሁሉ ክርስቶስ መከራ ተቀብሎ ካደለን ማዕድ(ሥጋ ወደሙ) እየተቀበለ መከራው አይንካኝ ይል ዘንድ አይገባም ይልቁንም እንደ ቅዱስ ጳውሎስ ቀኑን ሙሉ ስለአንተ እንገደላለን እንል ዘንድ ይገባናል (ሮሜ8፡36)፡፡ መስቀል እግዚአብሔርን እና ፍጥረትን ሁሉ በመውደዳችን የምንጋፈጠው መከራ ነው፡፡
ከዚህም መከራ እንሸሽ ዘንድ አይገባም በሥጋ መልካም ሆነው ሊታዩ የሚወዱ ሁሉ እንድትገረዙ ግድ አሉአችሁ፥ ነገር ግን ስለ ክርስቶስ መስቀል እንዳይሰደዱ ብቻ ነ ገላ 6፡12 ብሎ እንደወቀሳቸው ሰዎች ከዓለም ጋር ተመሳስለን ሳይሆን ከክርስቶስ ጋር ተባብረን በአኮቴት መስቀላችንን እንቀበል ዘንድ ይቻላል፡፡ ቅዱሳንን ሁሉ አንድ የሚያደርጋቸውም መከራውን በአኮቴት መቀበላቸው ነው እነርሱ እንደ ጌታቸው ከመከራው በኋላ ያለውን ደስታ ናፍቀው ሀይማኖታቸውን ጠብቀዋል፡፡ እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና። ዕብ12፡2 እንዲል ይህ መስቀል ከቤተክርስቲያን አይለይም ለዚህም ስለ ስሜ ስንት መከራ ሊቀበል እንዲያስፈልገው እኔ አመለክተዋለሁና አለው ሐዋ9፡16 ተብሎ የተጠራው ቅዱስ ጳውሎስ ሲመሰክር ስለ አካሉም ማለት ስለ ቤተ ክርስቲያን በሥጋዬ በክርስቶስ መከራ የጐደለውን እፈጽማለሁ። ቆላ1፡24 ይህም ቃል የተነገረው በክርስቶስ ድህነት ህፀፅ ኖሮ ሳይሆን በክርስቶስ ላይ መከራ ያጸና አለም በዚያ አያቆምም የተረፈውን መከራ በቤተክርስቲያኒቷ ያደርሳል ለማለት ነው ለዚህም ሐዋርያው ራሱን ፊት አውራሪ አድርጓል፡፡ እኛም ይህን አሰረ ፍኖት እንከተል ዘንድ ይገባል፡፡
መስቀላችንን በአኮቴት ተቀብለን እንሸከም ዘንድ እንደ ምሳሌ ከተጠቀሱልን ታሪኮች መካከል የፈያታዊ ዘየማን ታሪክ አንደኛው ነው እርሱ በወንጌል እንደተጠቀሰ ስለ አደረግነውም የሚገባንን እንቀበላለንና በእኛስ እውነተኛ ፍርድ ነው፤ ይህ ግን ምንም ክፋት አላደረገም ብሎ ገሠጸው።ሉቃ23፡41 ተብሎ እንደተነገለት እርሱ ምንም እንኳን በኃጢአቱ ምክንያት የመጣበት ቢሆንም በግራው ከተሰቀለው ይልቅ ያለተስፋ መቁረጥ በእምነት መስቀሉን ተቀብሏል በዚህም ጌታን ስለ መሻቱ መድኃኒታችን እውነት እልሃለሁ፥ ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ አለው ሉቃ23፡43 ፡፡ ለ5500 ዘመን ተዘግቶ የነበረውን ገነትም በደመ ማኅተሙ ሲከፍት እርሱን ቀዳሚ አደረገው ይህም አባቶቻችን እንዳስተማሩን በአኮቴት መስቀላችንን ተቀብለን በተከፈተልን ገነት በክብር እንመላለስ ዘንድ የተጻፈልን ነው፡፡
ሌላው ቅዱስ ያሬድ በመስቀል መዝሙር የተናገረው ብከ ንወግዖሙ ለኵሎሙ ፀርነ ወበስምከ ነኀስሮሙ ለእለ ቆሙ ላእሌነ ይቤ ዳዊት በመንፈሰ ትንቢት በእንተ ዝንቱ ዕፀ መስቀል የሚለው ነው በዚህም በመዝ44፡5 ላይ የተጠቀሰውን በአንተ ጠላቶቻችንን እንወጋቸዋለን፥ በስምህም በላያችን የቆሙትን እናዋርዳቸዋለን። ለመስቀል ሰጥቶ ተርጉሟል ጌታችን መከራ እንቀበል ዘንድ መከራ በሚያመጡብን እንፈተን ዘንድ ዝም ብሎ አልተወንም በእርሱ ጠላቶቻችንን ድል እናደርግበት(እንወጋበት) ዘንድ ምልክቱን መስቀሉን ትቶልናል እርሱም ከዲያቢሎስ ፍላፆች ሁሉ የምንድንበት ነው በስምከ ተወከልነ ወበኃይልከ ተማኅፀነ መዓልተ ምስሌነ ወሌሊተ ማዕከሌነ ዝንቱ ትእምርተ መስቀል ቤዛነ በዘቦቱ ንመውዖ ለኵሉ ኃይለ እኩይ እንዲል(መጽሐፈ ዚቅ ዘመስቀል)፡፡ ጌታ በወንገል እንደተናገረው እነዚህ ነገሮች(መከራዎቸን)መቀበል ለቅዱስ ጴጥሮስ እንደ ነገረው በሰው ዘንድ የማይቻል በእግዚአብሔር ዘንድ ግን የሚቻል ነው ማቴ19፡26 ይህም እርሱ በእኛ ካላደረ ወይም ለእርሱ ማደሪያ ራሳችንን ካላመቻቸን ከምስጢራትም ተሳትፈን የእርሱ አካል ካልሆንን በሥጋዊ ጥበብ በእውቀት ብዛት በሥጋችንም በነፍሳችንም (በኀልዮ፣በነቢብ፣በገቢር) የሚመጣብንን ፆር (ፈተና) እንሸከም ዘንድ የማንችለው ነው፡፡ መጋደላችን ከሥጋ እና ከመንፈስ ጋር አይደለምና፡፡
ከንጉሥ ቆስጠንጢኖስ እና ከንግሥት እሌኒ በረከትን ያሳትፈን በኃጢአት ውስጥ የተቀበረውንም መስቀላችንን በተቃጠለ ልብ በክርስቶስ ፍቅር መዓዛ አውጥተን እንሸከም ዘንድ አምላከ ቅዱሳን ይርዳን አሜን፡፡
No comments:
Post a Comment