Friday, 15 December 2017

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ



በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

እንደምን አላችሁ በዛሬው ቅዱሳን አበው ዓምዳችን ስለቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ታሪክ ይዘን ቀርበናል። 

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በ347ዓ/ም የሶርያ ዋና ከተማ በነበረችው ከአሕዛብ ወደ ክርስትና የሚገቡ ክርስቲያኖች መነኃርያ ማዕከል በነበረችውና ክርስቲያኖች መጀመሪያ ‹‹ክርስቲያን›› ተብለው በተጠሩባት በአንጾኪያ ከተማ ተወለደ፡፡አንጾኪያ የምስራቁ ሮም ግዛት ሁለተኛ ከተማ (ቁስጥንጥንያ ቀጥላ) ነበረች፡፡አራተኛው መቶ ዓመት የተለያዩ መናፍቃን (መነናውያን፤ግኖስቲኮች፤አርዮሳውያን አቡሊናርዮሳውን ወዘተ) እንዲሁም አይሁዶችና መምለክያነ ጣዖታት የሆኑት ሁሉ በአንጾያ ከተማ ሁሉም የየራሳቸውን እምነት ለማስፋፋት ይሯሯጡ የነበረበት ዘመን ነው፡፡ ኦርቶዶክሳውያኑ ደግሞ በጳጳስ መላጥዮስና በጳጳስ ጳውሊኖስ መካከል በነበረው ልዩነትና ክፍፍል ምክንያት ለሁለት ተከፍለው ነበር፡፡ስለዚህ የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የወጣትነት ዘመን ቤተ ክርስቲያን በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ በነበረችበት ጊዜ ላይ ነበር፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ አባቱ አስፋኒዶስ  የታወቀ የጦር መኮንን የነበረ ቢሆንም ነገር ግን ቅ/ዮሐንስ አፈወርቅ ገና ሕጻን እያለ ነበር የሞተው ፡፡እናቱ አትናስያ ትባላለች ፤በሃይማኖትና በምግባር እጅግ በጣም የተደነቀችና የተመሰገነች ክርስቲያናዊት ሴት ነበረች፡፡ገና በሃያ ዓመቷ ባለቤቷ በሞት ቢለያትም ማንኛውንም ሁለተኛ ጋብቻ ጥያቄ ሁሉ ባለመቀበል አባታቸው ጥሏቸው የሞቱትን ሁለቱን ልጆቿን ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅንና ታላቅ እኅቱን በማስተማር ላይ አተኮረች፡፡
አንቱዛ ልጇ ዮሐንስ አፈወርቅ ፍልስፍናንና ሕግን እንዲሁም የንግግርን ጥበብ በዘመኑ ከነበሩት ታላላቅ መምህራን እንዲማር አደረገች፡፡እንዲሁም በልጇ አዕምሮ ውስጥ ከልጅነቱ ጀምሮ የእምነትን ዘር ጥሩ አድርጋ ዘራችበት፡፡ይህ የእምነት ዘርም ለራሱና ለቤተ ክርስቲያን እጅግ ጠቃሚ የሆነ ብዙ ፍሬ አፍርቷል፡፡በእናቱ ተግሳጽና በመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ በዘመኑ ተንሰራፍቶ ከነበረው አሕዛባዊ ነገረ ዘርቅና ከንቱ አስተሳሰብ ተጠበቀ፡፡ሆኖም ግን እስኪያድግ ድረስ አልተጠመቀም ነበር፡፡ቤተ ክርስቲያን ልጆቿ ከአህዛብነት ወደ ክርስትና በሽግግር ላይ በነበረበት በዚያን ዘመን የንዑሰ ክርስቲያን ተጠማቂዎች ብዛት ብዙ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት (እነ ቅዱስ ቄርሎስ ጳጳስ ዘኢየሩሳሌም ፤ራሱ ቅ/ዮሐንስ አፈወርቅ እና ሌሎቹም) ለንዑሰ ክርስቲያኖች ከመጠመቃቸውና ወደ ቅዱስ ቁርባን ከመቅረባቸው በፊት የሚማሯቸው ወጥና መሠረታዊ ትምህርቶችን አዘጋጅተዋል፡፡አንዳንድ ክርስቲያን ቤተ ሰብች ሳይቀሩ የልጆቻቸውን ጥምቀት ካላቸው ከፍተኛ ከበሬታ የተነሳና ቶሎ መጠመቅ የጥምቀትን ጸጋ መልሶ የማጣት ሥጋት አለው ከሚል በዘመኑ ከነበረ የፍርሃት አስተሳሰብ የተነሳ ነበር፡፡ይህም ዛሬ ብዙች ንስሃ መግባትንና መቁረብን ሊሞቱ እስኪጣጣሩ ድረስ እንደሚያዘገዩት ዓይነት ያ አስተሳሰብ ነው፡፡ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በኋላ ላይ ይህ ልማድ ትክክል አለመሆኑን በመግለጥ አጥብቆ ይኮንናል፡፡


ቅ/ዮሐንስ አፈወርቅ በዘመኑ የነበረውን የንግግር ጥበብ ትምህርት ከሊባንዮስ ከተባለው መምህር ተምሯል፡፡ፍልስፍናንም በዘመኑ አሉ ከተባሉ መምህራን ተምሯል፡፡በአጠቃላይ ዕውቀቱና ማስተዋሉ አብረውት ከሚማሩት ሁሉ በላይ የነበረ ትጉህ ተማሪ ነበር፡፡እንዲያውም መምህሩ ሊባንዮስ ሊሞት ሲል ‹‹ማን ቢተካህ ትወዳለህ ;›› ብለው ቢጠይቂት ‹‹ክርስቲያኖች ከእኛ ሰርቀው ባይወስዱት ኖሮ የሚተካኝ ዮሐንስ ነበር›› ማለቱ ይነገራል፡፡ቅ/ዮህንስም ትምህርቱን እንደጨረሰ ለትንሽ ጊዜ ጠበቃ ሆነ፡፡ይህም ሥራ ለመንግሥት ሹመትና ሥልጣን ዋና በር ከፋች ነበር፡፡ቤቶች ውስጥ የንግግር ክህሎትንና ልዩ ተሰጥዖን ማሳየት ለታላላቅ ሹመቶች ከሚኒስትርነት እስከ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ድረስ ሊደርስ የሚችል ዋና ጥርጊያ ጎዳና ነበር፡፡በፍርድ  ቤት የሚያደርጋቸው ንግግሮቹ በሰማያኑና በመምህሩ በሊባንዮስ ሳይቀር ከፍተኛ አድናቆትን አስገኝቶ ነበር፡፡ሆኖም ግን እርሱ በነዚህ ነገሮች ሆሉ ደስተኛ አልነበረም የልቡ ምኞትና ሐሳብ ቤተ ክርስቲያን ነበር፡፡ለክርስትናው ትልቅ ፍቅር ነበረው፡፡ ከዚያም ወደ ቤተ ክርስቲያን ገብቶ መማር ጀመረ፤ቅዱሳት መጻሕፍትን ተማረ ፤በተለይም ከጳጳሱ መላጥዮስ ጋር ተዋወቀ በጊዜውም ካደጉ በኋላ ከሚጠመቁበት የ3ት ዓመት ትምህርት ተምሮ በ23 ዓመቱ በ370ዓ/ም በጳጳሱ መላጥዮስ እጅ ተጠመቀ፡፡
   ቅ/ዮሐንስም ከጊዜ ወደ ጊዜ ሃይማኖቱና ምግባሩ ተወዳጅነትን አገኘ በተለይም ለጳጳሱ መላጥዮስ ይህንንም አይቶ የአናገጉንስጢስነት(የአንባቢነት ማዕረግ) ሾመው፡፡እርሱ ግን ፍላጎቱ የነበረው በገዳም ገብቶ በምንኩስና ሕይወት መኖር ነበር፡፡ትንሽ ትንሽ እያለም የጾምና የጸሎት ሕይወትን አጠንክሮ ያዘ፡፡ለስጋው ምቾትና ድሎትን ነፈገውም የገዳማዊ ሕይወትን መኖር ጀመረ፡፡በቤተ ክርስቲያንም የሚያገለግሉ ካህናትና ሕዝብ እርሱንና ጓደኛው የነበረውን ባስልዮስን ጵጵስና ሊሾሟቸው ፈለጉ፡፡እርሱ ግን እኔ ለዚህ ከባድ የቤ/ክ ኃላፊነት የሚያበቃውና የሚጠቅመው ወንድሜ ባስልዮስ ነው፡፡በማለት ባስልዮስ እንዲሾ ለማድረግ እርሱ ተደበቀ፡፡ባስልዮስ ይህንን ሹመት የተቀበለው ጓደኛው ቅ/ዮሐንስም አብሮ የሚሾም መስሎት ነበር፤ባስልዮስም ጳጳስ ተደርጎ ተሾመ ፡፡

              የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የጵጵስና ሹመት

ቅ/ዮሐንስ ምንም ከባስልዮስ ጋር ለጊዜው ባይሾም በኋላ ግን ለመቀበል ችሏል፡፡በ347 ዓ/ም የቁስጥንጥንያ ፓትርያርክ የነበረው ኔክታርርዮስ ዐረፈ፡፡በዚያን ጊዜ ክፍት በሆነው በሮም ምስራቃዊ ግዛት ወዋና ከተማ በቁስጥንጥንያ መንበር ላይ ለመሾም በገሃድም ሆነ በስውር አጠቃላይ የሆነ ሽኩቻ ነበር፡፡ሆኖም ከትንሽ ወራት በኋላ በመንበሩ ላይ ለመተካት ሲናፍቁ ሆኖም ከትንሽ ወራት በኋላ በመንበሩ ላይ ለመተካት ሲናፍቁ የነበሩትን ጳጳሳት የሚያስደነግጥ ነገረ ተሰማ የአንጾኪያ ምዕመናን አባታችንን አንሰድም ብለው ረብሻ እንዳያስነሱና ሁከት እንዳይፈጠር ከእርሱ በከራሱም ሆነ ሌላ የሚመጣውን ተቃውሞ ዋጋ ቢስ ለማድረግ በዘዴ ከከተማው እንዲወጣ ከተደረገ በኋላ ከቤተ መንግስት በተላከ አጃቢ በአስቸኳይ ወደ ቁስጥንጥንያ ተወሰደ፡፡የአንጾኪያው ገዢ የነበረው ሰው የንጉሡ ትእዛዝ እንደደረሰው ቅ/ዮሐንስ አፈወርቅን ከከተማ ውጪ ወደሚገኝ አንድ ቤተ ክርስቲያን አብሮት እንዲሄድ ጠየቀው፡፡በእርሱ ሠረገላ ላይ እንደ ተቀመጠለትም ወዲያውኑ በፍጥነት ወደ ቁስጥንጥንያ ሊወስዱት ተዘጋጅተው የሚጠብቁ መኳንንትንና ወታደሮች ወደ ነበሩበት ወደ ቁስጥንጥንያ ወደሚወስደው ጎዳና ይዞት ሄደ፡፡በቤተ ክርስቲያን ታሪክና በቅዱሳን መዝገብ የጎላና ደማቅ ስምና ክብር ሊያሰጡት ወዳሉት የፈተናዎችና የተጋድሎዎች መድረክ በዚህ ዓይነት ድንገተኛ ሁኔታ ተወሰደ፡፡ወዴትና ለምን እንደሚወስዱት ያወቀው ቁስጥንጥንያ ከደረሰ በኋላ ነበር፡፡እንዲያ ባለ ሁኔታ ያለ ፈቃድና ያለ ውዴታው ፈቃደኝነቱን እንኳን ሳይጠየቅ በድንገት የቁስጥንጥንያ ሊቀ ጳጳሳ እንዲሆን ተደረገ፡፡የካቲት 26 ቀን 398ዓ/ም ብዙ ጳጳሳት ባሉበት በታላቅ ሥነ ሥርዓት በቁስጥንጥንያ መንበር ላይ 23ኛው የእስክንድርያ ፓትርያሊክ በነበረው በቴዎፍሎስ እጅ ፓትርያርክ ተደርጎ ተሸመ፡፡ፓትርያርክ ቴዎፍሎስም ያለውዴታው በንጉሡ በአርቃዴዎስ ትእዛዝ ቅ/ዮሐንስ አፈወርቅ ወርቅ ለመሾም ተገደደ፡፡ቴዎፍሎስም በቁስጥንጥንያ መንበር ላይ ለመሾም የራሱ ዕጩ አዘጋጅቶ የነበረ ቢሆንም ይህን ማድረግ እንደማይችል  በመረዳቱ የንጉሡን ትእዛዝ ፈጸመ፡፡ ዮሐንስ አፈወርቅም ገና እንደተሸመ ያደረገው ነገር ለብዙ ጊዜ ዘልቆ የነበረውን የአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን ችግር መፍታት ነበር፡፡        
              ዮሐንስ ‹‹አፈወርቅ›› ስለመባሉ
ዮሐንስ ‹‹አፈወርቅ›› ብላ ስም ያወጣችለት ቤተ መቅደስ የነበረች ስዕለማርያም ናት ፡፡በቁስጥንጥንያ እያለ በዚያ የሁለት ባህርይ ምንፍቅና ትምህርትን በልቡ የቋጠረ ንስጥሮስ ነበር፡፡ንስጥሮስ ምንፍቅናውን ሊቀ ጳጳስ ሆኖ እስኪሾምበት ጊዜ ድረስ አልገለጣትም፡፡ከጊዜያትም በአንዱ በዓል ዕለት ምዕመናኑ ቅርባን ሲቀበሉ አንዲት በወር ግዳጅ(የወር አበባ) ላይ ያለች ሴት ሳትነጻ ልትቀበል ቀረበች፡፡ሕዝቡም የመንፈስ ቅዱስ ጥላ ከእርሷ ሲርቅ አዩ፡፡የጸሐይ ጮራም በራሷ ላይ አላረፈም፡፡ሕዝቡም ፓትርያርክ ወደሆነው ንስጥሮስ ፊት አቆሟት ፡፡አንቺ ሴት ንገሪኝ የመንፈስ ቅዱስ ጥላ ካንቺ እስኪጠፋ ድረስ ኃጢአትሽ ምንድር ነው፡፡ንስጥሮስም ተቆጥቶ የሥጋዋ ዕርቃን እንደተገለጠ ቁልቁል ይሰቅሉት ዘንድ አዘዘ፡፡ እግዚአብሔር በዚህ ስጋ ከማርያም ከተወለደ መንፈስ ቅዱስ ይህችን ሴትእንደምን ናቃት፡፡እግዚአብሔር ከሴት ከተወለደ በማርያም ምክንያት ሴቶች ሁሉ ርኩሰታቸው በተቀደሰ ነበር አለ፡፡ሕዝቡም ሁሉ ወደርሷ ቀርበው እግዚአብሔር በዚህ ሥጋ ከሴት እንደተወለደ የሚያምን የተለየ ይሁን እግዚአብሔር በመወለጃ ማኅጸን እደተወሰነ የጡት ወተት በመመገብ በሴቶች የመወለድ ሥርዓት ነው ሁሉ ሕጻናትን እንደመሰላቸው የሚያምን የተረገመ ነው እያሉ በአፍረተ ሥጋዋ ላይ ምራቅ እንዲተፉ አዘዘ፡፡ ያንጊዜ ሊቁ ዮሐንስ አፈወርቅ ጠርዜቤጤር(ቀሲስ) በዚያ ነበር፡፡እንዲህ አለ‹‹እኔ እግዚአብሔር በድንግልና ወተት እንዳደገ በሕጻናትም ሥርዓት ሕጻናትን እንደመሰላቸው ከብቻዋ ከኃጢአትም በቀር የሰውን ሕግ ሁሉ እንደፈጸመ አምናለሁ››  ብሎ ኃፍረተ ስጋዋን በአፉ ሳመ፡፡በቤተ መቅደስም የነበረ የእመቤታችን ስዕል ‹‹አፈወርቅ›› ብላ ጠራችው፡፡ከዚያን ጊዜም በኋላ ‹‹ዮሐንስ አፈወርቅ››  እየተባለ የተጠራው፡፡
         ታላቁ ሊቅ ኢትዮጵያዊው ዮሐንስ አፈወርቅ የተሰኘ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ስለርሱ ሲያደንቁ ‹‹እኔም ስለርሱ እላለሁ በእውት አፈወርቅ ፤አፈ ዕንቁ፤አፈ ጳዝዮን በድርሰቱ ቤተ ክርስቲያንን የሚያጌጣት አፈ ባህርይ በእውነት አፈ መዓር በቃ ጣፋጭነት ምዕመናንን የሚያለመልማቸው አፈ ሦከር በእውነት በትምህርቱ መዓዛ የምስጢር በጎችን ደስ የሚያሰኛቸው አፈ ሽቱ አፈ ርኄ ነው፡፡በእውነት በውግዘቱ ሥልጣን ከሃዲዮችን የሚቆርጥ አፈ ሰይፍ ፤አፈ መጥባህት ነው፡፡በእውነት የማይነዋወጥ ዓምድ የማይፈርስ መሠረት በእውነት ከሞገዶች መነሳት የሚዋኝ ዋናተኛ ነው በእውነት የማይፈርስ ግንብ በጠላት ፊት የሚጸና አዳራሽ ነው›› መጽሐፈ ምስጢር ገጽ 37
 ተአምኖ ቅዱሳን በተባለው መጽሐፉት
 ‹‹ሰላም ለዮሐንስ አፉሁ ዘወርቅ ለጳጳሳት ሊቅ 
እለይነባ ከናፍሪሁ ምድራሳተ ጽድቅ -
ከናፍሮቹ የእውነት ድርሳናትን የሚናገሩ 
የጳጳሳት አለቃቸው አፉ የወርቅ የተባለ(ለሆነ) ለዮሐንስ ሰላምታ ይገባል››

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የእረፍቱን መታሰቢያ ግንቦት 12 ቀን ትዘክረዋለች፡፡
 
 

ከጻፋቸው መጻሕፍት ጥቂቶቹ


67-የትርጓሜ ድርሳናት (በኦሪት ዘፍጥረት)      59-የትርጓሜ ድርሳናት (በመዝሙረ ዳዊት)
የኢሳይያስ ትንቢት ምዕራፍ አንድ ሐተታ                 የመጽሐፈ ኢዮብ የተወሰኑ ክፍሎች
የመጽሐፈ ምሳሌ የተወሰኑ ክፍሎች    የትንቢተ ኤርምያስና ዳንኤል የትርጓሜ ድርሳናት እና  ሌሎችም
90 -የትርጓሜ ድርሳናት (በማቴዎስ ወንጌል)        88 -የትርጓሜ ድርሳናት (በግብረ ሐዋርያት)
32 -የትርጓሜ ድርሳናት ወደ ሮሜ ሰዎች         44 -የትርጓሜ ድርሳናት በ1ኛቆሮንቶስ
30 -የትርጓሜ ድርሳናት በ2ኛ ቆሮንቶስ             24 -የትርጓሜ ድርሳናት ወደ ኤፌሶን ሰዎች
15 የትርጓሜ ድርሳናት ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች     12 -የትርጓሜ ድርሳናት ወደ ቆላሲስ ሰዎች
11 -የስብከት ድርሳናት በ1ኛ ተሰሎንቄ           5  -የትርጓሜ ድርሳናት በ2ኛ ተሰሎንቄ
18 -የትርጓሜ ድርሳናት በ1ኛ ጢሞቴዎስ        10  -የትርጓሜ ድርሳናት በ2ኛ ጢሞቴዎስ
6 -ስድስት የትርጓሜ ድርሳናት ለቲቶ            3   -የትርጓሜ ድርሳናት ለፊልሞን
34 -የትርጓሜ ድርሳናት ለዕብራውያን ሰዎች እና ከ600 በላይ እጅግ ብዙ መጻሕፍቶችን ጽፏል፡፡

                                        ከቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በረከትና ረድኤት ያሳትፈን !

ወስብሐት ለእግዚአብሔር



Wednesday, 15 November 2017

የትርጉሜ አስፈላጊነትና ምንነት

በዲያቆን ያሬድ መለሰ

ጥንት በቀደመው ዘመን አባቶቻችን በቃል የተማሩትን በቃል ሲያስተምሩ እኩሌታዎቹ በቃል የተማሩትን ብዕር ቀርጸው ብራና ዳምጠው ቀለም በጥብጠው በጽሑፍ ሲያሰፍሩ በብዙ ድካም ነበር አያሌ ነገሮችን ያቆዩልን፡፡ ከእነርሱም ሲወርድ ሲወራረድ ከእኛ የደረሰው አንዱ የአንድምታ ትርጓሜ ትምህርት ነው፡፡ አንድምታ ቅዱሳት መጻሕፍትን ለማብራራት፣ የተቋጠረን ለመፍታት የሚያገለግል የትምህርት ዓይነት ነው፡፡ እንዲሁም ምዕመናን እምነታቸውን በስፋትና በጥልቀት እንዲገነዘቡት ያደርጋል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ትርጓሜ የሰውን ልብ እንዲያበራና አስተዋይ እንደሚያደርግ ተጠቅሷል (መዝ 118፡130) ስለዚህም የትርጓሜ ትምህርት ለአንድ ክርስቲያን እንደሚያስፈልገው ምንም ጥርጥር የሌለው ነገር ነው፡፡ ከዚህ የተነሳ ትርጓሜን ማወቅና መማር የግድ አስፈላጊ ነው፡፡ ምክንያቱም ክርስቲያኖች በቀላልና ግልጽ በሆነ መንገድ ወንጌልን እንዲረዱ ስለሚደረግ እና የአባቶችን ትምህርት በሚገባ እንዲያውቁ አንድምታን መነሻ በማድረግ እንመለከታለን፡፡ የምሥጢር መጻሕፍትን ክቡር ማዕድ የመፈተትና የማደል ሙያ የተቀዳጁ (የታደሉ) ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ‹‹አንባቢ የሆነ አስቀድሞ የመጽሐፍን አርዕስቱን' መቅደመ ነገሩን' ምክንያተ ጽሕፈቱን ሳይዝ ወይም ሳያውቅ ምልዐተ ንባቡን የሚመለከት አይኑር›› ብለዋል፡፡ ሊቃውንቱ እንዲህ የሚያደርግ ቢኖር እርካብ ሳይረግጥ ወደ ኮርቻ'ድንክ (ደረጃ) ሳይረግጥ ወደ ዙፋን የሚወጣ የዋህ ሰውን ይመስላል እንዳሉት እንዳይሆንብን የወንጌል አንድምታ ትምህርት ከመጻፋችንና ከመናገራችን በፊት ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን አስቀድሞ መማር ይገባል፡፡

የትርጓሜ አስፈላጊነት 

ሰው እንደመላእክት አዋቂ ብሩህ አእምሮ ያለው ሆኖ ተፈጥሮ ሳለ በኃጢአት ምክንያት ብሩህ አእምሮው ጨለመ'ፀጋ እግዚአብሔር ተለየው'ተሰጥቶት የነበረውን ክብር በማጣቱም የፈጣሪውን ቃል ትቶ የፍጡር ቃል በመስማቱ አዋቂ ሆኖ ሳለ አላዋቂ ሆነ፣ የእግዚአብሔርን መልእክት በቀጥታ ከማስተዋል ተገታ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው ‹‹መጻሕፍትንና የእግዚአብሔርን ኃይል አታውቁምና ትስታላችሁ›› ማቴ 22፣29 እንዲህ ሲል የሰው ልቡና ነገረ እግዚአብሔር እንደተሰወረበት የሚያስረዳ ነው፡፡ ስለዚህ የእግዚአብሔርን መልዕክታት የያዙ ቅዱሳት መጻሕፍት እንደመሆናቸው ሰው የእግዚአብሔርን ምስጢር እንዲያውቅና እንዲረዳ ትርጓሜ አስፈላጊ ነው፡፡ ነገረ እግዚአብሔር ተሰውሮበታልና፡፡ 
የእግዚአብሔር ቃል እንደ ድንች እና እንደ ካሮት ተቆፍሮ ወጥቶ የሚበላ እንጂ በዓይን ታይቶ በእጅ የሚቀነጠስ አይደለም፡፡ ሥጋዊ ምግብ እንኳን በእሳት በስሎ ሲበሉት ለሰውነት ተስማሚ እንደሚሆን ሁሉ መጽሐፍ ቅዱስን በትርጓሜ ተብራርቶ ሲማሩት ሲመገቡት ለህይወት ተስማሚ ይሆናል ብሎም ለሰማዕትነት ያበቃል፡፡ ስለዚህ የሰው ልጅ መንፈሳዊ ሕይወቱ እንዲያምር የመጻሕፍት ትርጓሜ ትምህርት አስፈላጊ ነው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም ከዚህ በታች ያሉትን ነገሮች ለመረዳት ለመገንዘብ አስተዋጽኦ ስለሚያደርግ ነው፡፡ 
ሰዎች አንዱ ከሌላው በብዙ መንገድ ይለያሉ፡፡ ለምሳሌ፡-
በሀገር፡- የአንዱ ሀገር ትምህርት'ባህል ወግና ልማድ ቋንቋ ወዘተ ከሌላው ሀገር ይለያል፡፡ 
በትምህርት፡- አንዱ ምሁር ሌላው ኢምሁር ሊሆን ይችላል፡፡ እንዲሁም በማስተዋል በሞራል በማገናዘብ አንዱ ሰው ከሌላው ሰው በትምህርቱ ብቃት በእውቀት የመቀበል የመረዳት ችሎታው ይለያያል፡፡ ስለዚህ እነዚህን የመሳሰሉት እውነታዎች ከግንዛ ያስገባ ግሩም የሆነ ገለጻና ማብራሪያ ለመስጠት ትርጓሜ አስፈላጊ ነው፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ የተነገረበትና የተጻፈበት ዘመን እጅግ ሩቅ ነው፡፡ ቦታው ባህሉ ሥርዓቱ ኑሮው ልማዱ ቋንቋው ዛሬ ካንበት ዘመን የተለየ ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ በመጀመሪያ የተነገረላቸው ህብረተሰቦች በአስተሳሰብና በዕውቀት ከእግዚአብሔርም ጋር ከነበራቸው ቅርብነት አኳያ ከዛሬው ህብረተሰብ የተለዩ ነበሩ፡፡ ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስን ለዛሬው ኅብረተሰብ መተርጎም አስፈላጊ ነው፡፡
ሌላው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተለያዩ የንግግር ዓይነቶች እንደ ሕልም፣ እንቆቅልሽ፣ ምሳሌያዊና ቅኔያዊ፣ ራዕይና ትንቢት ጥበብም ስላሉት ሌላም በእንስሳት ጠባይ በርካታ መልእክቶች አሉ፡፡ እነዚህን ለመረዳት ትርጓሜ አስፈላጊ ነው፡፡ የቀድው ንባብ በኋለኛው ተተርጉሞ ይገኛል፡፡ ብሉይ ኪዳን በሐዲስ ኪዳን፣መጽሐፈ ሳሙኤልና መጽሐፈ ነገሥት በመጽሐፈ ዜና መዋዕል ተብራርተዋል፡፡ እንዲሁም ቀደም ያሉ የሐዲስ ኪዳን ምንባባት በኋለኞቹ ተተርጉመዋል፡፡ ዘፍ 40፣1-23፣ መሳ 14፣12፣ ዳኤል 5፣12፣ ሉቃ 13፣32፣ ዮሐ 10፣11፣ ኤር 31፣29-30 ሕዝ 18፣1፣ ማቴ 10፣10 በ1ኛጢሞ 5፡18 ዮሐ 2፣21፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ ከመጀመሪያ እርስ በርሱ የተያያዘ እንደመሆኑ በአንድ ቦታ ትንቢት የተነገረለት በሌላ ቦታ ተፈጽሞ በአንድ ቦታ ያልተተረጎመው በሌላኛው ተተርጉሞ ይገኛል፡፡ ሌላው መጽሐፍት እርስ በእሳቸው የሚጋጩ መስለው የሚታዩት ትርጉማቸውን ካለማወቅ የተነሣ ነው፡፡ ትርጓሜ ግን ይህን ሁሉ ያስታርቀዋል፡፡ ስለዚህ ከላይ እንደተገለጸው የመጻሕፍትን ከላይ አርእስታቸውን ከታች ህዳጋቸውን ተመልክቶ አንዱን በአንዱ መርምሮ አመዛዝኖ እነ ዮሐንስ አፈወርቅ እነ ቅዱስ ቄርሎስ በአጠቃላይ በሃይማኖተ አበው ያሉ ሊቃውንት ከተረጎሙት ትርጓሜ ከሰጡት አስተያየት ሳይወጡ መተርጎም ይገባል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ እንደተናገረው በቃል ከመምህራን በመማር የተቀበለውንም እንዳለ በትውፊትም በትርጓሜ መጻሕፍትም ማግኘት ይችላል(ፊሊ 4፣9)፡፡ አባቶቻችን ገጽ በገጽ ከሐዋርያት የተማሩትን ያዩትንና የሰሙትን በትውፊትም በትርጓሜ መጻሕፍትም ማግኘት ይቻላል በጽሑፍም በቀጥታ ለእኛ አድርሰዋል፡፡ በተለይም በቤተ ክርስቲያን የተለመደው የትምሀርት አሰጣጥ የቃል ትምሀርት ይህንን የቅዱስ ጳውሎስን ቃል መሠረት ያደረገ ነው፡፡ እንግዲህ ከአባቶቻችን የአስተምህሮ ሥርዓት እንዳንወጣ ልንጠነቀቅ ይገባናል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን የመተርጎም ሥልጣንን በተመለከተም ማንም ሰው የመጽሐፍ ቅዱስን ቃል በራሱ ሐሳብ እንደራሱ ፈቃድ ሊተረጉም እንደማይገባው ተጽፎአል፡፡ 2ኛ ጀጴጥሮ 1፣20 ከዚህ የምንረዳው አንድምታ ትርጉም ማንም እንደፈለገው ርዕስ መዞ የሚጽፈው ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ ያልተቃኘ' ሐዋርያትን፣ የሐዋርያነ አበውን ከእነርሱም ቀጥለው የተነሡ የኦርቶዶክሳውያን አበው ሊቃውንትን ትውፊት ያልተከተሉ መጽሐፍ ቅዱስን በነጻነት ለመተርጎም ቢሞክሩም እንኳን በሥጋዊ ጥበብ በፍልስፍና ብቻ ስለሚመሩ ከስህተት ላይ ይወድቃል፡፡ 2ኛ ጴጥ 3፣18

የትርጓሜ ዓይነት

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የራሷ የሆነ የትርጓሜ ስልት አላት፡፡ የራቀውን አቅርባ የቀረበውን አጉልታ የምታቀርብባቸው ልዩ ልዩ የትርጓሜ ዓይነቶች ሲኖሯት ከእነዚህ ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው፡፡ ነጠላ ትርጓሜ'ምሳሌ'ምስጢራዊ ትርጉም እና አንድምታ ትርጓሜ ናቸው፡፡

ነጠላ ትርጓሜ

ነጠላ ትርጓሜ የሚባለው ዘይቤውን ብቻ በቀጥታ የሚተረጉም ምንም ዓይነት ሐተታ የማያደርግ የትርጓሜ ስልት ሲሆን ከአንድ ቋንቋ ወደ ሌላ ቋንቋ የሚተረጉም ነጠላ ትርጓሜ ይባላል፡፡ በዚህ ዓይነት ትርጉም ጥንታውያን የሆኑት መጻሕፍት ከውጪ ቋንቋ ወደ ግእዝ ከግእዝም ወደ አማርኛ ተተርጉመዋል፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍት በዓለም ላይ አንድ ሆነው የተገኙት እንዲሁ በቀጥተኛው ዘይቤ ብቻ በመተርጎማቸው ነው፡፡ ለምሳሌ በግእዝ ልሳን ‹‹በልዋ ለዛቲ ቁንጽል›› ይላል ወደ አማርኛ ሲተረጎም ‹‹ለዚያች ቀበሮ እንዲህ በሏት›› ይላል፡፡ ነጠላ ትርጓሜ ማለት ይህ ነው፡፡

ምሳሌያዊ

ምሳሌ ማለት አንድን ነገር ግልጽ ለማድረግ የሚረዳ ስለሆነ በምሳሌ ሲነገር ነገርን በቀላሉ መረዳት ይችላል፡፡ ‹‹ነገር በምሳሌ. . . . .›› እንዲሉ፡፡ ይህንን የአስተምህሮ መንገድ ጌታ ከምስጢራዊ ትርጓሜ ጋር በማጣመር በወንጌልም ላይ ብዙ ቦታ ካስተማረባቸው መንገዶች አንደኛው ነው፡፡ ልበ አምላክ ዳዊት ‹‹አፌን በምሳሌ እከፍታለሁ›› መዝ 77፣2 ማር 4፣34 እንዳለው እንግዲህ ምሳሌ ሁልጊዜ ከሚመስለው ነገር ያንሳል፡፡ ስለዚህም ምሳሌ ‹‹ዘይሐጽጽ›› ይባላል ‹‹የሚያንስ›› ‹‹ጎዶሎ›› ለማለት ፡፡ ምሳሌ በዕብራይስጥ ‹‹ማሻል›› ይባላል፡፡

ምሥጢራዊ

ምስጢር ማለት የተሰወረ ግን በውስጥ ያለ ላይ በላይ የማይታይ እንደ ማለት ነው፡፡ ሌላው የምስጢር ትርጓሜ የሚባለው ደግሞ ምንባቡን ሳይሻ አገባቡን ሳይጠበቅ ምስጢሩን ብቻ በመጠበቅ የሚተረጉም ነው፡፡ በዕብራይስጥ ‹‹ሳተር›› በዐረብኛ ‹‹ሰተር›› በሱርስት ደግሞ ‹‹ስታር›› በእንግሊዝኛም ‹‹ Mystery ›› ይሉታል፡፡ በምሳሌ የተነገረውን ኃይለ ቃል በውስጡ ምስጢር ይዟል ስለዚሁ ሲያስረዱን ትርጓሜ ይሆናል፡፡ ምስጢር የሚባለው ነገር እኛ ልንረዳው የምንችለው ነገር ግን ነጠላ ትርጓሜውን ይዟል ስለዚሁ ሲያስረዱን ትርጓሜ ይሆናል፡፡ ምስጢር የሚለው ነገር እኛ ልንረዳው የምንችለው ነገር ግን ነጠላ ትርጓሜውን ነው፡፡ በሥጋዊ ጥበብ መርምረን ልንደርስበት የማንችለውን ነገር ነው፡፡ ለምሳሌ፡- በምሥጢራዊ ትርጉም ‹‹አንተ ኮክህ›› የሚለው ፍቺ ‹‹አንተ መሠረት ነህ›› ማለት ነው፡፡ በኮክህ(ዓለት መሠረት) የተመሰለው ቅዱስ ጴጥሮስ ነው፡፡ ‹‹በልዋ ለዛቲ ቁንጽል›› ‹‹ለዚያች ቀበሮ እንዲህ በሏት›› ሲል በቀበሮ የተመሰለው ሄሮድስ ነው፡፡ ማቴ 16፣18 ሉቃስ 13፣22 

የአንድምታ ትርጓሜ

የአንድምታ ትርጓሜ የሚባለው አንድ ጊዜ ከተተረጎመ በኋላ መሠረታዊ የሐሳብ አንድነቱን ሳይለቅ እንደገና አንድም እያለ እስከ አሥርና አስራ አምስት ጊዜ የሚያወርዱበት አወራረድ የሚሰጡት ሐተታ ነው፡፡ አንድምታ ትርጉም በግእዝ ቋንቋ አንድም በማለት ፈንታ ‹‹ቦ›› ይላል፡፡ የዚህም ፍቺ ሌላ ይህንን የመሰለ ትርጉም አለው እንደማለት ነው፡፡ በአማርኛ ግን ሁለተኛ ሦስተኛ አይልም እንጂ አንድ እያለ እስከ አስራ አምስትና ከዚያ በላይ ጊዜ ይወርዳል፡፡ ሆኖም ግን ሁለተኛ ሦስተኛ እንደማለት ሦስተኛ አይልም እንጂ አንድም እያለ እስከ አሥራ አምስትና ከዚያ በላይ ጊዜ ይወርዳል፡፡ ሆኖም ግን ሁለተኛ ሦስተኛ እንደማለት የሚያስቆጥር ነው፡፡

የአንድምታ ትርጓሜ (ትምህርት) መቼ ተጀመረ?

የአንድምታ ትምህርት በግልጽ ሊታወቅ የቻለው በአንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ ነው፡፡ ከዚያ በፊት ሊቃውንተ አይሁድ አምስቱን የሙሴ መጻሕፍትንና መጻሕፍተ ነብያትን በአንድምታ ለውጠዋል፡፡ ይህ እንዲህ ሲሆን የጌታችን ተከታዮች ቅዱሳን ሐዋርያት ትክክለኛውን የአንድምታ ትርጓሜ ትምህርት በር ከፍተዋል፡፡
ጌታ ለደቀ መዛሙርቱ (ሐዋርያት) ወንጌልን ባስተማራቸው ጊዜ መጽሐፍ ስላልነበራቸው ትርጓሜውንም የነገራቸው በጥቂት ሥፍራ ላይ ብቻ ስለነበር ለጊዜው ትምህርቱን ፈጽመው አልተረዱትም ነበር፡፡ ከዕርገቱ በኋላ ግን መንፈስ ቅዱስን በጽርሐ ጽዮን ተቀብለው በአእምሮ ጎለመሱ፣ ምሥጢር ተረጎሙ፣ ብዙ ቋንቋም ተገለጸላቸው፡፡ ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ እንደገለጸላቸው ወንጌልን ጽፈው ለሕዝብ ለአሕዛብም እየተረጎሙ ማስተማር ጀመሩ፡፡
ሐዋርያት 3 ዓመት ከ3 ወር ያጠኑትን ትምህርት ለዓለም ለማስተላለፍ የረዳቸው ት/ቤቶችን ማቋቋማቸው ነበር፡፡ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ የሚታወቀው የመጀመሪው የክርስቲያኖች ት/ቤት በ60 ዓ.ም በቅ/ማርቆስ ወንጌላዊ የተመሠረተው የእስክንድሪያ የትርጓሜ ት/ቤት ነው፡፡ ሌላው መንፈሳዊ ት/ቤት ደግሞ በሦተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተመሰረተው የሦሪያ ትምህርት ቤት ነበር፡፡ በተለይ ከ2ኛው እስከ 3ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ ከነዚህ ት/ቤቶች በሚወጡ መምህራን አማካኝነት የትርጓሜ ትምህርት ሊያድግና ሊስፋፋ ችሏል፡፡ ከዚህም ሌላ ሠለስቱ ምእት /318ቱ ሊቃውንት/ በ325 ዓ.ም አርዮስን ለማውገዝ በኒቂያ ጉባኤ በተሰበሱ ጊዜ የመጽሐፍተ ብሉያትና መጽሐፍተ ሐዲሳትን እየተረጎሙ ጽፈዋል፡፡
ከ150ው ሊቃውንት በኋላም 200ው ሊቃውንት ንስጥሮን ለማውገዝ በ431 ዓ.ም በኤፌሶን ጉባኤ ባደረጉ ጊዜ እንደዚሁ የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍትን ተርጉመዋል፡፡ዮሐንስ ዘቡርልስና አባ ሚካኤል ዘሀገረ አትሪብ በሦስቱ ጉባኤያት የተሰበሰቡ አባቶች የጻፏቸውን ለሰው ልብ እንዲረዳ አድርገው ባጭሩ ጽፈውታል፡፡ ይህም መጽሐፈ ሃይማኖተ አበው በመባል ይታወቃል፡፡ ከዚህም በቀር በ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበሩ እንደ ቅ/አትናቴዎስ፣ ቅ/ዮሐንስ አፈወርቅ ወዘተ ያሉ ቅዱሳን አባቶች ቅዱሳት መጻሕፍትን እየተረጎሙ ጽፈዋል፡፡

የአንድምታ ትርጓሜ ትምህርት በኢትዮጵያ

የመጻሕፍት አንድምታ ትርጓሜ ስልት በሀገራችን መቼ እንደተጀመረ የትና በማን እንደተጀመረ ግልጽ ሆኖ ስለማይታወቅ ያለው አስተያየት ግምታዊ ነው፡፡ይህም፡-መጻሕፍተ ኦሪት ከዕብራይስጥ ወደ ግእዝ ተተርጉመው ወደ ሀገራችን ሲገቡ የመጻሕፍቱ ጥንታዊ የአንድምታ ትርጉም አብሮ እንደገባ ይታመናል፡፡ ከዚህም ሌላ ከሕገ ኦሪት ጋር ሊቃውንተ ኦሪት በንግሥተ ሳባ ጊዜ ከቀዳማዊ ምኒልክ ጋር አብረው ወደ ኢትዮጵያ ስለመጡ እነርሱ ሲተረጉሙት ሲያስተምሩት ኑረዋል በማለት አስተያየት ይሰጣል፡፡ በእርግጥም ኦሪት በጥንት ዘመን ተተርጉሞ በሀገራችን ቋንቋ ይሰራበት ነበር የሚለው ታሪክ እውነተኛ እስከሆነ ድረስ ሊቃውንተ ኦሪትም ወደ ሀገራችን መግባታቸውን አምነን ከተቀበለን መጻሕፍትም ሲተረጎሙ መኖራቸው ከቶ ሊያጠራጥረን አይችልም፡፡

በኋላም በዘመነ ክርስትና መጻሕፍተ ሐዲሳት ከጽርእ ወደ ግእዝ በቀጥታ በተተረጎሙ ጊዜ የአንድምታ ትርጓሜ ስልት የሆኑ መጻሕፍት ሁሉ ሳይተረጎሙ አልቀሩም የሚል አስተያየት ይሰጣል፡፡
ከዚያም አያይዞ ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚውሉ ብዙ መጻሕፍተ ሊቃውንት ሲተረጎሙ የትርጓሜ ስልት የሆኑ መጻሕፍት ሁሉ ሳይተረጎሙ አልቀሩም የሚል አስተያየት ይሰጣል፡፡ ነሐሴ 20 ቀን የሚነበበው ስንክሳር የአንድምታ ትርጓሜ ወደ ኢትዮጵያ የገባው በአባ ሰላማ በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንደሆነና አባ ሰላማ እንደጀመረው ይተረካል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ቅዱስ ያሬድ ጥበባት ሁሉ ከእግዚአብሔር ስለተገለጹለት የመጻሕፍትን ትርጓሜ ሁሉ ያወቀው ወይም የጀመረው እሱ ራሱ ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ነው ሲል ገድሉ ይናገራል፡፡
ይህ አይነት አስተያየት የወል በመሆኑ እንደ እውነት ይቆጠራል እንጂ የትርጓሜውንም መጻሕፍት ቃል በቃል አጥንቶ ወይም ከሰው አግኝቶ ወይም ራሱ ተጣጥሮ እገሌ ደረሰው ጀመረው ስለማይባልና ታሪኩም ከታሪክ ጋር ተያይዞ ስላልመጣ ልብ አኩርቶ አፍን ሞልቶ እንዲናገሩ አያደርግም፡፡
የአንድምታ ትርጓሜ አካል ገዝቶ መልክ አግኝቶ ለመታወቅ የቻለው በጎንደር ዘመነ መንግሥት ነው፡፡ ሊስፋፋ የቻለውም በየጊዜው የተነሡ የኢትዮጵያ ሊቃውንት የተለያዩ መጻሕፍትን በአንድምታ እየተረጎሙ በማቅረባቸው ነው፡፡ 
ይቆየን 
ስብሐት ለእግዚአብሔር

Monday, 13 November 2017

†††ከእምነትና ከእውቀት የቱ ይቀድማል†††?


                                   በዲ/ን ያሬድ መለሰ

††የእምነትና የእውቀት ግንኙነት ††

ከእምነትና ከእውቀት የቱ ይቀድማል የሚለው ጥያቄ በፍልስፍናው ዓለም አከራካሪ ነጥቦች መካከል አንዱ ነው፡፡ ይህ የእምነትንና የሰውን ባሕርያት በሚገባ ካለመረዳት የመነጨ ነው፡፡ እንደ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ እምነትና እውቀት ተጻራሪ ሳይሆኑ የሚደጋገፉ ናቸው፡፡

†††የእምነት ባሕርያት †††

የእምነት ባሕርያት መካከል አንዱ ምክንያትን የሚቃወም መሆኑ ነው፡፡ በእምነት የሚደረገው አንዳንዴ ምክንያት አልባ ነው በትርጉም በማብራሪያ ሊገለጹ የማይችል ከአእምሮችን በላይ የሆነ ነውና ለማብራርያ ብዙም አንጨነቅም፡፡ ሃይማኖት የሚቀበሉት ነው የምንለውም ለዚህ ነው፡፡ሁለተኛው የምናምነው ነገር ምክንያታዊ ነው(እምነት አመክናዊ ነው) ለምሳሌ ሰው በጣዖት ቢያምን የምንቃወመው አመክናዊ ትንታኔ በመስጠት ነው፡፡ ሦስተኛው እውቀት በእምነት የተገነባ ነው፡፡ ሰው በማያምነው ነገር ላይ እውቀት ሊሰበስብ አይችልም፡፡ ለምሳሌ አንድ የታሪክ ጽሑፍ የሚያነብ ሰው ቅድሚያ በጸሐፊው ወይም በጽሑፉ ላይ እምነት ያሳድራል፡፡ ታሪኩን የሚቀበለው እንደምንጭ የሚጠቅሰው አስቀድሞ እምነት ስላሳደርንበት ነው፡፡ ሰው ሳያምን አይቀበልም ሳይቀበል አይመረምርም አያጠናም፡፡ስለዚህም ያለ እምነት እውቀት አይገኝም የማያምን ቢኖር ግን ፍጹም እምነት ስለሌለው ለማወቅ ተነሳሽነት የለውም፡፡የሚያምንና የማያምን ሰው ነገሮችን የሚረዱት እንደ እምነታቸው መጠን ነው፡፡

ፍኖተ አእምሮ በእግረ ልቡና አምላክ መድረስ

በርግጥ ሰው በተፈጥሮ እውቀቱ በፍኖተ አእምሮ በእግረ ልቡና አምላኩ ወደ ማወቅ ሊደርስ ይችላል፡፡ በዚህ መንገድ ከተጓዙት መካከል አባታችን አብርሃም በምሳሌነት የሚጠቀስ ነው፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ ሰዎች አምላካቸውን ወደ ማወቅ የደረሱት ሁለት ነገር አስተባብረው በመገኘታቸው ነው፡፡ማመንና መታመንን፡፡ ያለ እምነት በእውቀት በአመክንዮ ወይም በሳይንስ የሚደረግ ምርምር ውጤቱ አምላክን ወደ መካድ የሚመራ ነው፡፡ አባታችን አብርሃም ሰማይና ምድርን የፈጠረው ማን እንደሆነ ባያውቅም አንድ ሁሉን የፈጠረ ሁሉን ማድረግ የሚችል አምላክ እንዳለ አስቀድሞ አመነ፡፡ በኋላም አምላከ ፀሐይ ተናበበኒ ብሎ በእምነት ወደ አምላክ ጸለየ፡፡እምነቱን በመታመን ገለጸ፡፡ ስለዚህ አብርሃም በፍኖተ አእምሮ ቢጓዝም እንዲጓዝ ያደረገው እምነቱ ከእግዚአብሔር መገለጥ ጋር ተዳምሮ ለእውነተኛ እምነት በቅቷል፡፡ማመን ከእውቀትና ከምክንያት በላይ መልካም ፈቃድና ፍላጎት ይጠይቃል፡፡ ቀሌምንጦስ ዘእስክንድርያ ‹‹የማምነው ለማወቅ እንድችል ነው--I believe in order that I may know›› ይላል፡፡ ሮማዊው ኦገስቲን በበኩሉ ‹‹በነገረ ሃይማኖት ረገድ ዕውቀት በምክንያት አትወሰንም፤በልብ መሻት እንጂ…እምነትን የተመለከተ አመክንዮ በነጠላ ግለሰብ አይደመደምም (በማዕከላዊት) ቤተ ክርስቲያን እንጂ-- [to believe] is an act of intellect determined not by the reason, but by the will….the final authority for the determination of the reason in faith lies not with the individual, but with the Church itself.›› ይላል፡፡

አስቀድሞ ማመን እንደሚገባ

ቅዱሳን አባቶቻችን ሐዋርያትም ይህንን በተመለከተ በመልክታቸው በጎልህ አስፍረውታል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ከማወቅ በፊት አስቀድመን ማመን እንዲገባ ሲነግረን ‹‹ ሁላችን የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማወቅ ወደሚገኝ አንድነት…›› ኤፌ 4÷13 ቅዱስ ዮሐንስም ይህንን በተመለከተ ሲገልጥ ለተቀበሉት በስሙም ለሚያምኑት የእግዚአብሔር ልጆች ይባሉ ዘንድ ስልጣንን ሰጣቸው›› ይህም አስቀድሞ በእምነት መቀበል እንዲገባ የሚያስገነዝብ ነው (ዮሐ 1÷13) በወንጌልም ሰፍሮ እንደምናነበው ቅዱስ ጴጥሮስም ‹‹ እኛስ አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጁ እንሆንህ አምነናል አውቀናልም›› ብሏል (ዮሐ 6÷69) ከላይ ለዘረዘርነው ነጥብ አስረጅ ነው፡፡





ይቆየን
ስብሐት ለእግዚአብሔር

Thursday, 12 October 2017

የንስሐ ሕይወት ክፍል አራት(የመጨረሻ ክፍል)


ንስሐ የገባ ሰው ዳግም በኃጢያት እንዳይወድቅ ሊያደርጋቸው የሚገቡ ጥንቃቄዎች

ምንም እንኳን ንስሐ የሚደገም ምሥጢር ቢሆንም ወደፊትም ለምንሰራቸው ኃጢያቶች ንስሐ የሚገባ ቢሆንም ተነሳሒው በሕይወቱ አምላኩን ያከበረ ስለሆነ ኃጢያጥ በሕይወቱ ላይ ያደረሰውን ተረድቶ ከኃጢያት መጠንቀቅ መራቅ ብሎም ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለው መሸሽ ይገባዋል፡፡(1ኛ ቆሮ 6፥18 2ኛ ጢሞ 2፥22) ስለዚህም ተነሳሒው የሚከተሉትን ጥንቃቄዎች ያደርግ ዘንድ ይገባዋል፡፡

ለኃጢያት ሌላ ስም አለመስጠት

ኃጢያት እንደኃጢያት አለመቁጠር የዘመናችን ትልቁ በሽታ ነው፡፡ ኃጢያትን በሌላ ካባ ማሳመርና ማስጌጥ ለሰው ልጆች ውድቀት ዋንኛ መነሻ ነው፡፡ አንዳንዶችም የሰሩትን ኃጢያት ለመሸፈንና ሕሊናቸው እንዳይወቅሳቸው ስለንስሐ   መስማት አይፈልጉም፡፡ ጥንተ ጠላታችን ዲያቢሎስ አባታችን አዳምን ና እናታችን ሔዋንን ሲያስት ዕጸ በለሱን ‹‹ዓይን ከፋች እውቀት ገላጭ›› ብሎ ሲያሜ ሰጥቶ ለኃጢያት ቦታ እንዲኖራቸው አድርጎል፡፡(ዘፍ 3፥5) በዓለማችን የምናየውም ይህንን ነው፡፡ ተነሳሒው ግን ቀድሞ ንስሐ የገባ ኃጢያትን ጠልቶ ነውና ኃጢያት ለመሥራት መናፈቅ የለበትም፡፡

ክፉ ነገሮችን አለማወቅ

ጠቢቡ ሰሎሞን ‹‹የጥበብ መብዛት ትካዜ ያበዛልና ዕውቀትንም የሚጨምር ኃዘንን ይጨምራል፡፡›› (መክ 1፥18) እንዳለ ስለኃጢያት ማወቅ ወደ ሞት ያመራናል፡፡ ሔዋን አምላክ የመሆንን ክፉ ዕውቀት ባወቀች ጊዜ ዕጹን ትበላ ዘንድ ምኞት በውስጧ ተቀሰቀሰ፡፡ በሕገ ተፈጥሮ ንጹሕ የሆነው ሕጻን ኃጢያት መሥራት የሚጀምረው በአካባቢው ያሉ ሰዎችን በማየት ነው፡፡ ኃጢያትን ማወቅ ለመሥራት ይጋብዛልና ከዚህ መጠበቅ ይኖርብናል፡፡ አክአብ የናቡቴን እርሻ ቦታ መቀማት ብሎም መግደል የተማረው ከክፉ መካሪው ሚስቱ ኤልዛቤል ነው፡፡(1ኛ ነገ 20፥9) አምኖን እኅቱ ትዕማርን ከክብር ያሳነሳት በአሚናዳብ ክፉ ምክር ነው(2ኛ ሳሙ 13፥5) ሮብዓም ክፉ ነገር የተማረው ከገዛ አብሮ አደጎቹ ነው፡፡(1ኛ ነገ 12፥10) ስለዚህም ተነሳሒው ዳግመኛ ወደ ኃጢያት እንዳያመራ ክፉ ነገሮችን መሸሽ ማረቅ ከእውቀታቸውም ራሱን መከልከል ይገባዋል፡፡

ንስሐን ለመሞከር አለመጋበዝ

በቀልድ በዋዛ ፈዛዛ የሚጀመረው ቀላል ኃጢያት ‹‹ንዑስ ቀበሮ›› ሆኖ እንድንጠፋ ምክንያት ሊሆነን ይችላል፡፡ መጽሐፍ እንዳለን ‹‹የወይናችንን ቦታ የሚያጠፉትን ጥቃቅን ቀበሮዎች አጥምዳችሁ ያዙልን፡፡›› (መኃ 2፥15) ተነሳሒው ቀላሉ ኃጢያት ወደ ሞት እንዲወስደው ስለሚያምን ይህንን ከማድረግ ራሱን መጠበቅ አለበት የኃጢያት ቀላል የለውምና፡፡ ይሁዳ ጌታን ለመሸጥ ያባቃው አስቀድሞ ለድሆች ከሚሰጠው ገንዘብ ይሰርቅ ስለነበረ ነው፡(ዮሐ 12፥6) ይህንንም የሚያስተውል ሰው ጥቃቅኑን ቀድሞ ማቆም ይገባዋል፡፡

ከክፉ ባንጀራ መራቅ

ተነሳሒው ሌሎች በእርሱ እንዲሳቡ አስተማሪ እንጂ ሌሎችን እርሱን እንዲስቡት መሆን የለበትም፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋል›› እንዳለ(1ኛ ቆሮ 15፥33) ጌታም ‹‹ወደ ሳምራዊያን ከተማ አትግቡ›› (ማቴ 10፥5) እንዳለ ከሳምራዊያን ክፉ ግብር ተሳታፊ እንዳንሆን ጥንቃቄ ማድረግ ይገባናል፡፡ ቅዱስ ዳዊት እንዳለ ‹‹ከንጹሕ ጋር ንጹሕ ሆነህ ትገኛለህ ከጠማማ ጋር ጠማማ ሆነህ ትገኛለህ››(መዝ 17፥26) ስለዚህም በክፉዎች መንገድ አለመሄድ በኃጢያቶች መንገድ አለመቆም ይገባል የክፉዎችና የኃጢያተኞች መንገድ ትጠፋለችና፡(መዝ 1፥1-)
ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ መልእክቱ  “ለቀደመውም ዓለም ሳይራራ ከሌሎች ሰባት ጋር ጽድቅን የሚሰብከውን ኖኅን አድኖ በኃጢአተኞች ዓለም ላይ የጥፋትን ውኃ ካወረደ፥ “ኃጢአትንም ያደርጉ ዘንድ ላሉት ምሳሌ አድርጎ ከተማዎችን ሰዶምንና ገሞራን አመድ እስኪሆኑ ድረስ አቃጥሎና ገልብጦ ከፈረደባቸው ጻድቅ ሎጥም በመካከላቸው ሲኖር እያየና እየሰማ ዕለት ዕለት በዓመፀኛ ሥራቸው ጻድቅ ነፍሱን አስጨንቆ ነበርና በዓመፀኞች ሴሰኛ ኑሮ የተገፋውን ያን ጻድቅ ካዳነ ከክፉ አድራጊዎቻችን ግብር ሳንቀላቀል ነፍሳችን በእነሱ ሥራ እንዳይቆሽሽ ምንጨነቅ ከሆነ ከዓመፀኞች ሴሰኛ ኑሮ የተገፋውን ሰዎች ያድን ዘንድ ዛሬም የታመነ ነው፡፡

ሰይጣንን መቃወም

ቅዱስ ያዕቆብ ‹‹ዲያቢሎስን ተቃወሙት ከእናንተ ይሸሻል›› (ያዕ 4፥7) እንዳለ የዲያቢሎስ የሆነውን ሥራን መቃወም ይገባል፡፡ ሰይጣን ጌታን በሦስቱ ኃጢያቶች እንደፈተነ ጌታም ዲያቢሎስን ድል አድርጎ ‹‹ሑር እምኔየ›› ከእኔ ሂድ እንዳለ  እንዲሁ ዲያቢሎስንና የዓለምን ኃጢያት ከእኔ ራቅ ሂድ እንለው ዘንድ ይገባናል፡፡

ማጠቃለያ

ቅዱስ ጳውሎስ  “እውነትን በዓመፃ በሚከለክሉ ሰዎች በኃጢአተኝነታቸውና በዓመፃቸው ሁሉ ላይ የእግዚአብሔር ቍጣ ከሰማይ ይገለጣል፡፡” (ሮሜ 1፡18) እንዳለ የእግዚአብሔር ቁጣ ከመገለጡ በፊት ኹላችን ኃጢያት ከመሥራት መታቀብ ወደ ንስሐም መቅረብ ይገባናል፡፡ ለዚህም የእግዚአብሔር ቸርነት የእመቤታችን ምልጃ የቅዱሳኑ ጸሎት ይርዳን፡፡
ስብሐት ለእግዚአብሔር

የንስሐ ሕይወት ክፍል ሦስት


በንስሐ የሚገኙ ለውጦች

በሕይወት  ውስጥ መንፈሳዊ ለውጥ ከሌለ የክርስትና ሕይወት ጣዕም ያጣል፡፡ ይህንን መንፈሳዊ ለውጥ ለማምጣት ታዲያ ንስሐ አስፈላጊ ነው፡፡ ንስሐ ማለት መናዘዝን ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን መቀበል ብቻ ማለት አይደለም፡፡ ኃጢያትን በፍጹም በመተው በተቀደሰ የሕይወት  ጎዳና መመላለስ እንጂ፡፡ ንስሐ አንድ ወቅት ከክርስቶስ እግር በታች ራስን መጣል ብቻ ሳይሆን በመንፈሳዊ ሕይወት መኖርና የእግዚአብሔርን ትእዛዛት በመፈጸም ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ‹‹በእርሱ የሚኖር ኹሉ ኃጢያትን አያደርግም፡፡ ኃጢያትን የሚያደርግ ኹሉ አላየውም አላወቀውም››(1 ኛ ዮሐ 3፥6) እንዳለን ለአንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ኹሌም ብሆን በእርሱ የምንኖር ኹላችን ኃጢያትን ማድረግ የለብንም፡፡



በንስሐ የተመለሰ ሰው ጠባያት

ትኁት ሰብእና  አለው (ሉቃ 14፥10)

ትዕቢት መታጀርን አያውቅም፡፡ በጉባኤ እንኳን ዝቅ ያለ ሥፍራ ላይ መቀመጥን ይመርጣል፡፡ 

ትእግስተኛ ነው

ስለሰዎች ኃጢያት ሲሰማ ወይም ስህተትን ሲያይ ሲሰድቡት ወይም ከክብሩ ዝቅ ቢያደርጉት እርሱም ያንን በደል ከዚህ በፊት ስለሰራ ይታገሳል፡፡ የእርሱ ሐሳብ ብቻ ተቀባይነት እንዲኖረው አይሞክርም ከእኔ ከኃጥኡ አእምሮ ምን መልካም ነገር ይገኛል ይላልና ራሱንም በትኅትና ዝቅ ያደርጋል፡፡

ምሕረትን ያውቃል   (ማቴ 6፥15 1ኛ ሳሙ 26፥11)

ሰዎች ክፉ ነገር ቢያደርጉት ክፋትን አይመልስም  ቢሰድቡት አይራገምም እርሱ ይቅር ካላለ ኃጢያቱ እንደሚያዝበት ያውቃል፡፡ የዘወትር ጸሎቱንም በተግባር በይቅር ባይነቱ ይተገብረዋል፡፡ 

አርምሞን ገንዘብ ያደርጋል

ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ ‹‹እኔ ሌሎች ሲናገሩ ባደምጥ ከንግግራቸውም መማር ይሻለኛል›› እንዳለ (ያዕ 1፥19) ንስሐ የገባ ከእግዚአብሔር ጋር እርቅ የፈጸመ ንግግሩ የማይሰማ በአርምሞ የተሞላ ነው፡፡

የመንፈስ ደኃ ይሆናል

በመንፈስ ድሆች(ነዳያነ መንፈስ) የሆኑ ማለት የዋሐን ትሑት የሆኑ ማለት ነው፡፡ እንዲህ ያሉ ሰዎች ራሳቸውን ችሎታ እንዳላቸው አድርገው አይቆጥሩትም፡፡ በራሳቸው ዘር፣ ጠባይ፣ ተፈጥሮ፣ ሀብት፣ አቅምና ችሎታ ተስፋ አያደርጉም፡፡
ነዳያን በመንፈስ ያልተማሩ ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን ማንነታቸውን አውቀው በፈቃዳቸው ሁሉን የተዉ ማለት ነው፡፡ ነዲያን በመንፈስ በእግዚአብሔር ፊት የተሰበረና የተዋረደ ልብ ይኖራቸዋል፡፡ ይህን የሚያደርጉት ከእነሱ እጅግ የሚበልጥ ሁሉን የሚያውቅ አምላክ መኖሩን በማሰብ ነው፡፡
አንድ ሰው ራሱን ዝቅ ካላደረገ የትኅትናም ሥራ ካልሰራ አምላካዊ ጸጋን አያገኝም እርሱም አይፈልገውም፤ ሁሉ ያለው ይመሰለዋልና፡፡ ክርስቲያን የሆኑ ሁሉ ግን ይህን የትሩፋት ሥራ መንገድ መከተል ራስን ከመውደድ መራቅ እያለውም እንደሌለው ሆኖ መታየት ተገቢው ነው፡፡
መኮንነ ተሰሎንቄ ዮሐንስ አፈ ወርቅን እንደጠየቀው ብፁዓን ከበቁ በኋላ ነዳያነ አእምሮ መሆናቸው እንደምንድነው? አለው ዮሐንስም ‹‹አንተ በሃገርህ እንደምን ትኖራለህ›› አለው ‹‹ከሁሉ በላይ ነኝ›› አለው እልፍ ብለህ ‹‹በቂሳርያሳ›› ‹‹የምበልጣቸውም የሚተካከሉኝም አሉ›› አለው ዝቅ እያለ ሄደ፡፡ ‹‹አንጾክያስ አለው›› ‹‹የሚያውቀኝ የለም›› አለው ቅዱሳንም በአእምሮ ነዳይ የሆኑት ከበላላቸው ያለውን ፈጣሬ መጋቤ ዓለማትን እያዮ ራሳቸውን ዝቅ ያደርጋሉ እንጂ አይታበዩም፡፡ በምግባር በሃይማኖት በንስሐ ድሆች ነን ብለው የሚያዝኑ የሚተክዙ ንዑዳን ክቡራን ናቸው፡፡
የምንመካበት ምንነታችን የእኛ አይደለም፡፡ የምንመካበትን ዕውቀት ሐብት  ጉልበት ሥልጣን የሰጠን አምላካችን ነው፡፡ ነዳያነ መንፈስ ይህንን መመልከት የሚችሉ ናቸው፡፡ የእነርሱን ዕውቀት ከአምላክ ፍጹም እውቀት ጋር እያነጻጸሩ ኢምንትና ትንሽ መሆኑንን ይገነዘባሉ፡፡ ሐብታቸውን ጉልበታቸውንም ከሁሉ ኃያል ሁሉ በእጁ ከሆነው አምላክ ጋር እያነጻጸሩ ራሳቸውን በጌታ ፊት ያዋርዳሉ፡፡ መንግስቱን የሚርሱ እንደነዚህ ያሉት ናቸው፡፡ መመካታቸውን በአምላክ ላይ ያደረጉ በራሳቸው የማይመኩ የመንግስቱ ወራሾች ናቸው፡፡
የመንፈስ ደኃ መሆን ኹሉ እያለው እንደሌለው መሆን ማለት ነው፡፡ ጥበበኛ ሆኖ ሳለ ባለፀጋ ሆኖ ሳለ ደኃ መሆን ራስን በትኅትና መስበር ነው፡፡ ሰው በሌለው ነገር የሚኮራ ፍጡር ነው አላዋቂው አዋቂ ተብሎ ይመሰገን ዘንድ ይወዳል ንስሐ የገባ ሰው ግን እንኳን በሌለው ባለው ይወደስ ዘንድ አይሻም፡፡ ‹‹በሰማይና ምድር የተዋረዱትን የሚያይ ከአለቆች ጋር ከሕዝቡም አለቆች ጋር ያኖረው ዘንድ ችግረኛውን ከመሬት የሚያነሳ ምስኪኑን ከትቢያ ከፍ ከፍ የሚያደርግ››(መዝ 112፥8) ትዕቢተኞችን በልባቸው ሐሳብ የሚበትን ትኁታኑን ከፍ የሚያደርግ ጌታን በማሰብ ኹሌም በትኅትና የሚኖር ነው፡፡(ሉቃ 1፥52)
በአጠቃላይ ተነሳሒው በሕይወቱ ፈጽም ለውጥ ያሳያል አስተሳሰቡ አስታያየቱ አነጋገሩ ኹሉ ይቀየራል፡፡ ሰዎች ከአንደበቱ ይልቅ በሕይወቱ ይሰበካሉ ሳይናገር ምግባሩ ሰዎችን ይለውጣል፡፡ በእርሱም ምክንያት ብዙዎች ወደ ንስሐ ይቀርባሉ፡፡
ስብሐት ለእግዚአብሔር

እስመ ውእቱ ኮከብ ብሩህ ዘቤተክርስቲያን


         በዲ/ን ፍሬው ለማ
«ገብረ መንፈስ ቅዱስ ሞተከ ታብዕል ኢትዮጵያ ለጴጥሮስ በዓለ መርሆ ወለጳውሎስ
ሐዋርያ ከመ ተዝካሮም ታብዕል ሮምያ»
ትርጉም
«ገብረ መንፈስቅዱስ ሆይ ኢትየጵያ ሞትህን ከፍ አድርጋ ታስባለች የሮም ሀገር የሐዋርያትን ጴጥሮስ ና ጳውሎስ በዓል ከፍ አድርጋ እንደምታከብር»

                መልክዐ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ

ከወይን ፍሬ ይልቅ የጣፈጠ ከሮማን አበባም ይልቅ ቡሩክ የሆነ የአንድ ተጋዳይ ምስጋናን
እንነግራችኋለን ይኸውም በሰነፎቹ ዘንድ የተናቀ በአዋቂዎች ግን ተቀባይነት ያለው በቅዱሳን ዘንድ የተወደደ ለርኩሳኑ የሚያስፈራቸው ነው ይህም ኮከብ ለቤተክርስቲያን ጳዝዮን የሚባል ዕንቁ ጸሎቱ እንደ ዕጣን የሚሸት የታመነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ነው።

ደብራችን ደብረ ብርሃናት (የብርሃናተ ዓለም ቅዱስ ጴጥሮስ ወጳውሉስ ቤተ ክርስቲያንን ለማለት ነው) ከምትዘክራቸው ከጌታ ምስክሮች አንዱ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ናቸው ልክ በመልክአቸው እንደተገለጸው ኢትዮጵያ ዝክራቸውን ዘወትር ወር በገባ በ፭ ከፍ አድርጋ ታከብራለች፡፡ምዕመናንም አቡዬ(አባቴ) ብለው በፍቅር ቃል ይጠሯቸዋል ከገድላቸውና ከመጽሐፍ ባገኘው ከፍ አድርገን የማግነናችን ሥራ መሠረት ከዚህ በኃላ እንዳስሳለን

† ትውልዳቸውና እድገታቸው


አባታችን አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ በገድላቸው ተጽፎ እንደምናነበው የተወለዱት በግብጽ ሀገር ልዩ ስሙ ንሂሳ በሚባል ቦታ ነው። አባታቸው ስምዖን እናታቸው አቅሌስያ ይባላሉ። አቅሌስያ ልጅ አጥታ 30 ዘመን እያለቀስቸ ኖራለች። የንጹሀንን ጸሎት የሚቀበል ጌታም ደም ግባቱ ያማረ ልጅ ሰጣት። ይህም በመልክአቸው ላይ «ስምዖን ወ አቅሌስያ ዘ ነበሩ በንሂሳ በኃጢአ ውሉድ በከዩ መጠነ አመታት ሠላሳ» ተብሎ ተገልጿል አባታችን መጋቢት 29 ተጸንሰው በታህሣሥ 29 ተወልዱ። በተወለዱበት ቀንም መልአኩ ገብርኤል በሰው አምሳል ተመስሎ የዚህ ህጻን ስም ገብረ መንፈስ ቅዱስ ይሁን ብሎ ተናገረ። በዚያን ቀንም ህጻኑ ከእናቱ ጭን ወርዶ ለ ቅድስት ሥላሴ ሶስት ጊዜ ሰገደ።ከሦስት ዓመት በኋላ መልአኩ በክንፉ ተሸክሞ ኖብ ወደሚባል ገዳም ወስዶ ህጻኑን አባ ዘመደብርሀን ለሚባሉ አባትሰጠው። ያም አባት ሕጻኑን በፍቅር በስርዓት ቅዱሳት መጻሕፍትን እያስተማረ አሳደገው፣ አባ ዘመደ ብርሃንም ሕጻን ገብረመንፈስ በትምህርቱ በትህትናው እግዚአብሔርን በመፍራቱ ታዛዥ መሆኑን በተመለከተ ጊዜ አቡነ አብርሃም ወደ ተባሉ ጳጳስ ወስዶ መዓረገ ዲቁናንም አሰጠው ።

ከዚያ በኋላ ፍጹም መናኝ በጸሎት ትጉህ ሆነው ሲያገኛቸው መንኩሰው የቅስና መዓረግ እንዲቀበሉ ሆኑ አቡነ ገብረ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ እንደ ሐዋርያት በመንፈስቅዱስ ተሞልተው ቅዱስ ወንጌልን እያስተማሩ በጾም በጸሎትና በስግደት እግዚአብሔርን እየለመኑ ብዙ ሕሙማንን ያድኑ ነበር።የጻድቁ አቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ ዝናቸው ቅድስናቸው በኢየሱስ ክርስቶስ ስም የሚያደርጉትን ተዓምራት በብዙ አገር ስለተሰማ ውዳሴ ከንቱ እንዳይሆንባቸው ወደ ጫካ ገቡ ከነምሮችና ከአንበሶች ጋር ተስማምተው መኖር ጀመሩ። 300 ዓመትም በታላቅ ተጋድሎ በግብጽ፣የመን ፣ በሱዳን ና በሌሎችም ሃገሮችም እያስተማሩ ከኖሩ በኋላ የእግዚአብሔር መልአክ ከቦታ ቦታ የሚጓጓዙበት የብርሀን ሰረገላ ሰጣቸው ወደ ኢትዮጵያም እንዲመጡ አዘዘዛቸው። ይህም በዘመነ ላሊበላ በ11ዐዐ ዓ.ም. በጥቅምት ወር በ ፭ተኛው ቀን ነው። አባታችንም 60 አንበሶች በፊቱ 60 ነምሮች በኃላው ሆነው ወደ ኢትዩጵያ መጣ ። በመጀመሪያ ታቦተ ጽዮን ወደ አለችበት ወደ አክሱም ሄደው ለሶስት ሳምንታት እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ሰነበቱ ከዚያም ንጉሥ ላሊበላ ከአለት ፈልፍሎ ወደ አሰራቸው አብያተ ክርስቲያናት ወደ ሮሐ ሄዱ ንጉሥ ላሊበላ ከእግዚአብሔር የተሰጣቸውን ሞገስና ግርማ እያደነቀ በክብር ተቀብሎ አስተናገዳቸው ከዚያም ንጉሱን ና ቦታውን ባርከው እግዚአብሔር ወደ ፈቀደላቸው ዝቋላ ለመሄድ ተነሱ በዚያም በከበረ በጌታችን ስም ተጋድሎን ፈጽመዋል

† እረፍቱ ለአቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ


ስለ ዕረፍታቸው በገድላቸው እንዲህ ተጽፏል ቀኑ መጋቢት 5 ዕለቱ ቅዳሜ ለእሑድ አጥቢያ ሰዓቱ ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት ሆኗል፤ አሁንም ህማሙን እየታገለ እያላበው በድካም ለፍጥረቱ ሁሉ ይለምናል፤ “አቤቱ ህዝብህን አድን ርስትህን ኢትዮጰያንም ባርክ” ይላል። ሕመም የጀመረው መጋቢት 3 ዓርብ ቀን ነው፤ መታመሙን የሰሙ እንደርሱ ቅዱሳን የሆኑት ዘርአ ቡሩክ፤ ፍሬ ቅዱስ፤ያዕቆብ፤ብንያምና ዮሴፍ እንዲሁምበወቅቱ የኢትዮጰያ ንጉስ የነበረው እንድርያስ ሊጠይቁት ተሰብስበዋል ወደ አጠገቡ መድረስ ግንአልተቻላቸውም አባታችን ገብረመንፈስ ቅዱስ የሚጋርደው እንጨት ዛፍ በሌለበት በርሃ እንደ አንበሳ ተኝቶ አዩት በላዩ ያረፈው የእግዚአብሔር ጸጋ ከፊቱ የሚወጣው ብርሃን ቀይ መልኩ ረዥም የራስ ጠጉሩ እንደ ነጭ ሐር የሚሆን ጽሕሙ አስደነቃቸው። ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት ሲሆን ከሰማይ ታላቅ ነጎድጓድ ድምጽ ተሰማ ጌታችን መላአክትን አስከትሎ ወደ አባታችን ወረደ፤ ከሰማይ ወደ ምድር ህብሩ አምሳያው ልዩ ልዩ የሆነ እንደ ፀሐይናእንደ ጨረቃ የሚያበራ እንደ ወንጭፍ ድንጋይ ይወረ ወር ነበር ከዚያ የነበሩ ሁሉ ፈሩ ወደ ኃላም ሸሹ ምድር ራደች ተራሮች ኮረብቶች ተናወጡ ብርቱ ጩኸት ንውጽውጽታ ሆነ። “ወዳጄ ገብረመንፈስ ቅዱስ ሰላም ላንተ ይሁን” እነሆ የማይታበል ቃል ኪዳን እገባልኃለው ስምህን የጠራ መታሰቢያህን ያደረገውን፤ እጣን ቋጥሮ ግብር ሰፍሮ መባ ይዞ ቤትህ የመጣውን እምርልኃለው አንተ ከገባህበት ገነት መንግስተ ሰማያት አገባዋለሁ አላቸው፤ አባታችንም “አቤቱ ጌታ ሆይ የኢትዮጰያን ህዝብ ማርልኝ” አሉት፤ እነሆ ምሬልኃለው አስራት በኩራት አድርጌም ሰጥቼሃለው። ከዚህ በኃላ ሰባቱ ሊቃነ መላዕክት የአባታችንን ነፍስ ሊቀበሉ ወረዱ በታላቅ ምስጋናም ወደ ሰማይ አሳረጉት ስጋውንም ይዘውት ሄዱ የት እንደተቀበረ ግን እስካሁን አይታወቅም አንዳንዶች በኢየሩሳሌም ነው ይላሉ፤ ሌላው በምድረ ከብድ ነው ይላል ግን እስካሁን ልክ እንደ ሊቀ ነብያት ሙሴ ስጋ የት እንደተቀበረ አይታወቅም። ገድሉ ትሩፋቱ ከሰማይ ከዋክብት ከምድር አሸዋ ይበዛል ኢትዮጰያን አብዝቶ ይወዳታል፤ ምድራዊ ምግብ አልተመገበም የእናቱን ጡት እንኳን አልጠባም፤ ልብስ፤ መጠለያ አልፈለገም፤ የክረምት ቁር የበጋ ሐሩር እየተፈራረቀበት በተጋድሎ 562 ዓመት ኖረ፤ በመጋቢት 5 ቀን ሩጫውን ጨረሰ።

† አቡነ ገብረ መንፈስቅዱስና የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን

የኢትዮጲያ ቤተክርስቲያን ታሪክ የጥቂቶች ታሪክ አይደለም የብዙ ቅዱሳን ታሪክ ነው        ብዙዎች የደም ዋጋ ከፍለውበታል ከነዚህ ዕንቁዎች አንዱ አባታችን አቡነ ገብረመንፈስቅዱስ ናቸው። አባታችን ለቤተክርስቲያንችን ካበረከቱት አስተዋፅዎች በጥቂቱ እንኳን ብንዘረዝር

ምንኩስናን በማስፋፋት
ኢትዮጵያ በ34 ዓ.ም ክርስትናን በ4ተኛው መ/ክ/ዘ ደግሞ ክህነትን በአባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን ተቀብላለች፡፡ የምንኩስና ሥርዓት ደግሞ በተሰዓቱ ቅዱሳን ወደ ኢትዮጲያ መጥቶአል፡፡ በኢትዮጵያ የምንኵስናና የገዳማት ታሪክ ውስጥ ከ3ኛው – 12ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ያለው ጊዜ በአብዛኛው ከውጭ በመጡ አበው ሥርዓተ ምንኵስና የተስፋፋበት ሲሆን ከ12ኛው-15ኛው ያለው ደግሞ ከመላ ኢትዮጵያ በተነሡ አበው ቅዱሳን ሥርዓተ ምንኵስናና የገዳማት ትክል ከሰሜን ወደ ምዕራብ፣ ምሥራቅና ደቡብ የተስፋፋበት ወቅት ነው ከውጭ ከመጡት ቅዱሳንም አበታችን ተጠቃች ናቸው ፡፡

አባታችን አቡነ ገብረ መንፈስቅዱስ እግዚአብሔር በሰጣቸው የ562 ዓመት ዕድሜ አያሌ ገዳማትን የገደሙ ሲሆን በተለይም የዝቋላና የምድረ ከብድ ገዳማት እስከዛሬ የፀኑ ናቸው፡፡ ብዙ ደቀመዛሙርትንም አፍርተዋል፡፡

ወንጌልን በማስፋፋት
ክቡር አባታችን አቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ በኢትዮጲያ ምድር በየመንና በምድረ ሱዳን ሳይቀር እየተዘዋወሩ ቅዱስ ወንጌልን አስተምረዋል ጠንቋይ ቃልቻ በልዩ ልዩ አምልኮት የነበሩትን ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር መልሰዋል የታመሙትን በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም አድነዋል ለዚህም ማሳያ የሚሆኑን በአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ስም በተለያዩ የሃገራችን ክፍላት የታነጹት አብያተ ክርስቲያን ናቸው ዝክራቸውንም ሁሉም ኢትዮጵያውያን ያከብራሉ ለዚህም ነው አባቶች በጥቅምት ፭ ማኅሌት «ዝንቱሰ ሐዋርያ ገብረ ሕይወት ዘተፈነወ ውስተ ምድርነ ከመ ይክስት ብርሃነ ይፈውስ ዱያነ» ብለው የሚያመሰግኑት

ጸሎታቸውና በረከታቸው ከ እኛ ጋር ይሁን አሜን

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Sunday, 8 October 2017

አገልግሎታችንን ከየት እንጀምር?


                    

ጌታችን አምላካችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከዕርገቱ በፊት ሐዋርያትን መንፈስ ቅዱስን እስኪቀበሉ ድረስ ከኢየሩሳሌም እንዳይወጡ እና የተስፋውን ቃል እንዲጠብ አዟቸው ነበር (ሐዋ.1፡4) ግና መንፈስ ቅዱስን ከተቀበላችሁ በኋላ በኢየሩሳሌም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድርም ዳር ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ አለ (ሐዋ.1፡8) እነዚህ ቃላት ከዕርገት በፊት ጌታችን ለመጨረሻ ጊዜ ለሐዋርያት ያዘዛቸው ናቸው፡፡ እስኪ አእዚህ ጋር እንምና ጌታችን የተናገራቸውን እያንዳንዱን ቃላት እናስተውል፤ እነዚህ ለየትኛውም አገልጋይ መርሕ ሊሆኑት ይገባል፡፡ የጌታችን ቃላት  ሳይታሰቡ የተነገሩ እንዳልሆኑ መቼም አንዘነጋውም፡፡ መንፈስ ቅዱስን እስኪቀበሉ  በኢየሩሳሌም ከዛ በይሁዳ እንዲሁም በሰማርያ በመጨረሻም በዓለም ሁሉ እንዲሰብኩ ተናገረ፡፡

በኢየሩሳሌም

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት ኢየሩሳሌምን ለቅቀው እንዳይወጡና ምስክሩንም በዚያ እንዲጠብቁ ሲያዝዛቸው እናነባለን፡፡ ኢየሩሳሌም ሲል ምን ማለቱ ነው የመጀመርያ ምስክር የምንሆንላት እርሷ ማን ናት ኢየሩሳሌም  የታላቁ ንጉስ ከተማ ናት፤ እንዲሁም የመመስገኛ መቅደሱ የሚገኘባት፡፡ አዎ! ኢየሩሳሌም የጌታችን ማደሪያ የሆነች፤ ቅ/ጳውሎስ  በቤተ መቅደስ እያለ የሚጠራት (1ቆሮ.3፡16) ሊቁ አውግስጢኖስም አንተን እስክታገኝ ድረስ እንዳታርፍ አደረግካት ያላት ልባችን  ናት፡፡ ኢየሩሳሌም ፤ የጌታ የግሉ መኖርያ፡፡ በኢየሩሳሌም ምስክር ትሆኑኛላችሁ ማለት በግል ሕይወታችን እና በራሳችን ምስክር መሆን ማለት ነው፡፡
ብዙዎች ይህንን ቅደም ተከተል እናዛባዋለን፤ ወደ ሰማርያና ወደ ዓለም ዳርቻ እንጓዛለን፡፡በዚህም ብዙ ስህተቶች ይከተሉናል፡፡ የኛ ጌታ ያዘዘን ግን መጀመርያ በኢየሩሳሌም ምስክሮቹ እንድንሆን ነው፡፡ ከኢየሩሳሌም ጥሩ ዜና እንደተገኘ ሁሉ ከእኛም የግል ሕይወት ለሌሎች የሚተርፍ በረከት ይወጣል፡፡
ኢየሩሳሌም የይሁዳ ማዕከል ፣ የቤተ መቅደስ መገኛ መስዋዕቱ የሚቀርብባት ነበረች፡፡ ይህች ብ አይሁዶች ከተለያዩ ሀገራት የምትስብ አእና እረፍትም የምትሰጥ ነበረች፡፡ ልክ እንደዚሁ ኢየሩሳሌም ልባችን፤ መንፈሳዊ ሕይወታችን በብዙ ሰዎች ትታያለች፡፡ በዚህም በአንተ ሰማያዊው አምላክን ያመሰግናሉ፡፡ ስለዚ አንተ የእግዚአብሔር አገልጋይ ሆይ ከውስጠኛው ልብህ (ከኢየሩሳሌም) ምስጋናን መሥዋዕት አድርገህ አቅርብ፡፡
ግን ለምንድን ነው ከኢየሩሳሌም የምንጀምረው ይህች ለጌታችን ምስክር የምንሆንባት ቅርብ ከተማ ናት፡፡ በዚህ በጎ ትሩፋትን ከሰራን ቀደ ውጪ ለመውጣት የበቃን ነን ማለት ነው፤ ምክንያቱም የእግዚአብሔር ኃይል የምንቀበለው ከዚህ ነውና፡፡ ጌታችን ሐዋርያትን የመንፈስ ቅዱስን ኃይል እስኪቀበሉ ድረስ ከኢየሩሳሌም እንዳይወጡ አዟቸዋል፡፡እግዚአብሔር ሁልጊዜ አገልግሎታችን በመንፈስ ቅዱስ ኃይል እንዲከወን ይፈልጋል፤ በዚህም እርሱ ይመሰገናልና፡፡ በራሳችን ጥበብና አቅም ለማገልገል ስንሞክር ስንት ጊዜ በደልን ይሆን ይህ ኃይል ለሐዋርያት የተሰጣቸው በሰገነቱ ላይ (ከምድር ቤት በላይ) ሆነው የአብን የተስፋ ቃል እየጠበቁ በአንድ ልብ ሆነው ሲጸልዩ   ፡ መስኮትና በራቸውንም ዘግተው ስለነበር ነው፡፡(ሐዋ.1፡13) አዎ! በከፍታው ላይ ካልወጣን በስተቀር የመንፈስ ቅዱስን ኃይል መቀበል አይቻለንም፡፡ ይህም ከምድራዊ አስተሳሰብ ከፍ ማለት ፣የነፍስን በርና መስኮት (የስሜት ሕዋሳት) በመዝጋት የአምላካችን ሥራና እና እርዳታ መሻትን ያሳየናል፡፡ በዚህ መንፈሳዊ ሰገነት ላይ ለሐዋርያት ደስታንና ሰላምን ሊሰጣቸው የተገለጠ አምላክ ለእኛም እንዲሁ ይገለጣል፡፡ በዚህ መንፈሳዊ ኃይል ቅ/ጴጥሮስ በአንዲት ደካማ ሴት ፊት የካደውን ኢየሱስ ክርስቶስን ፡ በብዙ ሺ ሰዎች ፊት መሰከረ፤ እኛም በዚህ መንፈሳዊ ኃይል ብቻ አምላካችንን ማገልገል እና በየትኛውም ስፍራ መመስከር ይቻለናል፡፡

በይሁዳ

አይሁዶች የእግዚአብሔር ሕዝቦች የተባሉ፣ ትንቢት የተነገረላቸው፣ እርሱም በሥጋ የተገለጠላቸው እነርሱ ግን ያልተቀበሉት ናቸው፡፡ በይሁዳ ምስክር መሆን ማለት፡ በቤት በቤተሰብ መሐል እንዲሁም በአካባቢያችን ስለ እርሱ መመስከርን ያሳየናል በአብዛኛው ማናችንም ይህን አገልግሎት እንረሳዋለን ፤ ኢያሱ ግን እኔና ቤቴ ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን ይላል፡፡ (ኢያሱ 24፡15)
ቅ/ጳውሎስ ደግሞ ነገር ግን ለእርሱ ስለ ሆኑት ይልቁንም ስለቤተሰቦቹ የማያስብ ማንም ቢሆን ሃይማኖትን የካደ ከማያምን ሰው ይልቅ የሚከፋ ነው፡፡  (1ጢሞ.5፡8) አዎ! ሐዋርያው እውነተኛ አገልጋይ የሚመዘነው  በቤቱ ባለው ማንነት ነው  እያለ ያስረግጥልናል፡፡ስለቤተሰቡ የማያስብ እንዴት ስለእግዚአብሔር እጨነቃለሁ ይላል በእውነት ይህስ የመታየት ፍላጎት አይመስላችሁም

በሰማርያ

ሰማርያ የአይሁድ እና የአህዛብ ድብልቅ የሆነች ከተማ ናት፡፡ በዚህ የሚደረግ አገልግሎት በሃይማኖት ባሉና በማያምኑ መካከል የሚኖርን ምስክርነት ያሳየና ፡፡ በእውነተኛ ማንነቱ እንዲሁም በቤተሰቡ መካከል የክስቶስን ፍቅር የገለጠ አገልጋይ ብዙ ዝግጅት እና ተጋድሎ ወደሚጠይቀው የመንፈሳዊ ትግል ሜዳ ይገባል፡፡ በሰማርያ ማገልገል ፍቅርን ፣ ምሕረትን እንዲሁም ስለሌሎች መጨነቅን ይፈልጋል፡፡ መንፈሳዊውን ኃይል ሳይቀበሉ በፊት ወደዚህች ከተማ የገቡ ፍቁረ እግዚእ ዮሐንስና ወንድሙ ያዕቆብ ከተማዋ የጌታን ቃል ስላልተቀበለች እሳት ከሰማይ ወርዶ ሰዎቹን እንዲበላቸው ለምነው ነበር ፤ እርሱም ይህን ስጋዊ መንፈስ በመቃወም እንዲህ አላቸው ምን ዓይነት መነፈስ እንደሆነላችሁ አታቁም የሰው ልጅ የሰውን ነፍስ ሊያድን እንጂ ሊያጠፋ አልመጣም አላቸው፡፡ (ሉዋ9፡51-56)
አገልጋይ በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ለማገልገል የተለየ መንፈሳዊ አቅም ያስፈልገዋል፡፡ ይህ ከባድ የአገልግሎት ሜዳ ቢሆንም አንድ በእምነት የሆነ ለብዙዎች እንደሚተርፉ በዮሐንስ ወንጌል ያለችው ሳምራዊቷ ሴት ጠንካራ ማስረጃችን ናት፡፡ (ዮሐ.4፡6)

እስከ ዓለም ዳርም ድረስ

የጌታችን ወንጌል በየቦታው ሲነገር ማየትን የመሰለ ምን ደስታ አለ፡፡መልካሙ የምሰራች የሚያወሩ እግሮቻቸው እንዴት ያማሩ ናቸው፡፡ (ሮሜ.10፡15) ምንም በማያውቃቸው ሰዎች መሐል፤ ወገኖቼ አሉልኝ በማይባልበት ስፍራ፣ በቋንቋ እና መልክ ፣ በባህልና በሥርዓት በማይተሳሰርባቸው አካባቢዎች የጌታን ቃል የፍቅርን ኃይል ተሸክሞ መጓዝ ምንኛ ያስደስታል፤ እንዴት ያለ መባረክ ነው!
አምላኩን መስሎ ስለእርሱ በፍቅር የሞተለትን እያሰበ ለሰይጣን እንኳን ንስሐ የለመኑትን እነ ቅድስት ክርስቶስ ሠምራን በዓይነ ኅሊናው እየሳለ የፍቅርን ደሞዝ ለመቀበል የሚጓዝ እውነተኛ አገልጋይ ይህ ነው፡፡
በእርግጥ እነዚህ ሁሉ የተለየ ስብዕና ይፈልጋሉ ፤ እምነት እና እርጋታን ያስቀድማሉ፡፡ በሃይማኖትን መኖርን የክርስቶስን ትእዛዝ መከተልን አጥብቀው ይሻሉ፡፡


ምንጭ፡- Paradise of the spiritual service
 (By Bishop Youhanis )

Thursday, 28 September 2017

መንፈሳዊ አገልግሎት ክፍል ፩



                                                       (ቤተ ሐዋርያት መስከረም ፲፰  ፳፻፲)


አገልግሎት ምን ማለት ነው?

     አገልግሎት የሚለው ቃል  ገልገለ ከከሚለው የግእዝ ግስ የተገኘ እንደሆነ ይጠቁማል፡፡ ገልገለ (አገለገለ)ማለት ተገኣ፣ ታዘዘ፣ ዐገዘ፣ ረዳ፣ ጠቀመ፣ ማንኛውንም ሥራ ሠርቶ ጌታውን ደስ አሰኘ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ አገልግሎት ማለተ መታዘዝ፣ መገዛት፣ መረዳት መጥቀም... ማለት ይሆናል፡፡ ማንኛውንም ሥጋዊና መንፈሳዊ ሥራ አገልግሎት ነው፡፡ ለመንግሥት የሚሰራ የመንግሥት አገልጋይ፣ ለግለሰብ የሚሠራ የግለሰብ አገልጋይ፣ ለእግዚአብሔርም የሚሠራ የእግዚአብሔር አገልጋይ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ አገልጋዮችን በተለያየ ስያሜ ጠርቷል፡፡ ምንም አይነት መብት በራሱ ላይ  የሌላውንና በጌታው ሐሳብ ፍፁም አዳሪ የሆነውን ተገዢ ባሪያ በማለት ገልፆታል ፡፡ ንዋይ ኅሩይ ቅዱስ ጳውሎስ “ከሰው ሁሉ አርነት የወጣሁ ስሆን የሚበልጡትን እንዲጠቅም  እንደባርያ ራሴን ከሁሉ አስገዛለሁ” በማለት የተናገረው ይህን ያጠናክራል፡፡ (1ቆሮ. 9፡19) አብሮት የሚያገለግለውን ቲኪቆስንም “በጌታም አብሮኝ ባሪያ የሆነ” በማለት ጠርቶታል፡፡ (ቁላ. 4፡7) ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም አርነት ወጥታችሁ እንደ እግዚአብሔር ቅዱሳን ባሪያዎች ሁኑ በማለት አገልግሎታችን በፍፁም መገዛት እንዲሆን ይመክረናል፡፡ (1ጴጥ. 2፡16) በራሱ ላይ ሙሉ ነፃነት ያለውን አገልጋይ መጽሐፍ ቅዱስ ሠራተኛ ይለዋል፡፡ (ሉቃ. 10፡2፣ ቆላ. 4፡11፣ 2ጴጥ. 1፤8) ይህ ከባሪያ ይልቅ በራሱ ላይ የመወሰን ሥልጣን ያለው ነው፡፡ ከፈለገ አለማገልግለ ይችላል፡፡ በባሪያና በሠራተኛ መካከል ነፃነቱ  የሆነው ደግሞ ብላቴና፣ ሎሌ ተብሎ የተጠራው ነው፡፡
     መንፈሳዊ አገልግሎት የምንለው የእግዚአብሔር የሆነውና መንፈሳዊ ዓላማን መሠረት በማድለግ የሚገለገለውን ነው፡፡ መንፈሳዊ አገልግሎትን ከሌሎች አገልግሎቶች/ ሥራዎች የሚለዩት በርካታ ጠባያት አሉ፡፡ ትልቁና መሠረታዊው ልዩነት ዓላማው ነው፡፡ በመንፈስ ቅዱስ የሚመራ የመንፈሳውያን ሰዎችና የሰማያውያን መላእክት ረቂቅ ኅብረትና አንድነት የሚገለፅበት በማይታይ ፀጋ ወደ ክርስቶስ በእውነትና በፍቅር የሚሳድግ (ኤፌ. 4፡15) የሐዋርያዊት ቤተክርስቲያን ስንተረጉም ማንኛውም ሥራ ሠርቶ ጌታውን ደስ ማሰኘት ነው ካልን መንፈሳዊ አገልግሎትም ጌታው እንደእግዚአብሔር ነውና እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ማንኛውንም ሥራ መሥራት ነው፡፡ (ሮሜ. 12፡1)እግዚአብሔር ደስ ማሰኘት የሚቻለው ደግሞ በዕምነት ብቻ በመሆን (ዕብ. 11፡6)መንፈሳዊ አገልግሎት የመታመን ሥራ ነው፡፡ ሃይማኖት ማለት ማመንና መታመን ማለት እንደመሆኑ አምላክን አምነን የምንታመነው በመንፈሳዊ አገልግሎት መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

መንፈሳዊ አገልጋይ ማን ማነው?


ፍጥረታት ሁሉ አገልጋዮች ናቸው፡፡ ቅድስት ሥላሴ አንዱንም ፍጥረት ካለዓላማ እንዲሁ በዘፈቀደ አልፈጠሩምና ይልቁንስ አበው እንዳስተማሩት ሰውና መላእክትን እንዲያመሰግኑ ሌሎቹን ፍጥረታት ደግሞ ለአንክሮ' ለተዘክሮ 'ለምስክርነት ፈጥርዋል፡፡ ስለዚህ ላያገለግል የተፈጠረ ፍጥረት የለም ፡፡ ካልእ ፍጥረታት የሰው ልጅ አገልግሎቱን በዘነጋ ጊዜ ስለ አምላክ እየመሰከሩ ሰውን ወደተፈጠረበት ዓላማ (አገልግሎት) ለመመለስ በመጣር አገልግለዋል ፡፡ የበለዓም አህያ (ዘፍ 22) እና የቢታኒያ ድንጋዮች (ሉቃ 19)ለዚህ ምስክሮች ናቸው፡፡ስለ ቅዱሳን መላእክት መንፈሳዊ አገልጋይነት በመጽሐፍ ቅዱስ በተለያዩ ቦታ ተጽፏል ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ በዕብራውያን መልእክቱ ምዕራፍ 1 ቁጥር 14 ላይ ‘ሁሉ መዳንን ይወርሱ ዘንድ ስላላቸው ለማገዝ የሚላኩም የሚያገለግሉም መናፍስት አይደሉምን” በማለት ከርቀታቸው (ረቂቅነታቸው) የተነሳመናፍስት ብሎ የሚያገለግሉ ያላቸው መላእክትን ነው፡፡ ልበ አምላክ ዳዊትም “መላእክቱን መንፈስ የሚያደርግ አገልጋዮቹንም የእሳት ነበልባል”በማለት (መዝ 103፡4) ይህንኑ አጠናክሯል፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስና ነባቢ መለኮት ዮሐንስም የምስጋና አገልግሎታቸውን በእራይ ተመልክተው ጽፈውታል ፡፡(ኢሳ 6፡1-6 ራዕ 4፡5-8)፡፡


እንዲያገለግሉኝ ሕዝቤን ልቀቅ (ዘፀ. 7፡16) እግዚአብሔር አምላክ እስራኤላዊያንን ከዘመናት የግብፅ ስደት ወደ ምድረ ርስት የመመለሻው ወቅት በደረሰ ጊዜ በሙሴ በኩል ፈርኦንን እንዲያገለግሉኝ ሕዝቤን ልቀቅ (ዘፀ 7፤16) ብሎታል፡፡ የእስራኤላዊያን ከስደት መመለስ ለመንፈሳዊ አገልግሎት ነው ፡፡ በሌላ አነጋግር ከስደት የመፈታታቸው ዓላማ አገልግሎት ነው፡፡ ከስደት ተመልሶ እግዚአብሔርን የማያገለግል በስደት ቢኖር ይሻለዋል፡፡ “እንዲያገለግሉኝ” ብሏልና፡፡ በተመሳሳይ የሰው ልጅ የመፈጠሩ ዓላማ ሃይማኖት እንደመሆኑና ሃይማኖት ደግሞ የማመንና የመታመን ጉዳይ በመሆኑ' እንደዚሁም መታመን በመንፈሳዊ አገልግሎት ስለሆነ እግዚአብሔር የማያገለግል ሰወ የመፍጠሩን ዓላማ ሰቷልና ባይፈጠር ይሻለዋል ፡፡ እዚህጋ መንፈሳዊ አገልግሎት ስንል በጠበበው ትርጉም የተለመዱትን የክህነት' የሰ/ት/ቤት ወይም የመንፈሳዊ ማኅበራትን አገልግሎት ብቻ ማለታችን አይደለም፤መሠረታዊ የክርስትና ተግባራትንና የምስጋና ሕይወት አጠቃለልን እንጂ፡፡ በዚህ አረዳድ ሰው ሁሉ መንፈሳዊ አገልጋይ ነው፡፡ ለዚህ ነው ቅዱስ ጳውሎስም ስወን የእግዚአብሔር የተቀደሰ መቅደስ ብሎ የጠራው፡፡ (1ቆሮ. 3፡16)  ታላቁ የቤተክርስቲያን ሊቅ ቅዱስ ዩሐንስ አፈወርቅ በሉቃ 6፡38 ላይ ጌታችን “ስጡ ይሰጣችዋል” ያለው ቃል ሲተረጉመው መንፈሳዊ አገልግሎትን የተመለከተ ቃል ስለመሆኑ መስክሯል፡፡ ጌታ ስጡ ማለቱ አገልግሉ ማለት ነው፡፡ የምድሩን ትታችሁ' ጊዜያችሁን ሰውነታችው ጉልበታችውን ገብራችሁ ዕውቀታችሁን አፍሳችሁ ገንዘባችሁን በጅታችሁ ብታገለግሉ እኔ ደግሞ በጸጋ ላይ ጸጋ በበረከት ላይ በረከት በሕይወት ላይ ቅድስናን አሰጣችኋለሁ ሲል ነው ይላል ሊቁ፡፡ የመንፈሳዊ አገልግሎት መለያዎች ምንም እንኳን አንድ ሰው ቅዳሴ' ምስጋና 'ምስክርነት እና የመሳሰሉትን ከሁላዊት ቤተክርስቲያን የተገኙ ሁሉንም የሚያሳትፍ ሁላዊት አገልግሎቶች ላይ መሳተፍ ግዴታው ቢሆንም በሰንበት ት/ ቤቶች' ቤተክርስቲያን ማኅበራትወይም በተለያዩ መንፈሳዊ ኃላፊነቶች ለማገልገል የሚያስቡ ከሆነ የመንፈሳዊ አገልግሎት የተለዩ ጠባያትን አጥርቶ ማወቅ አለበት፡፡ ይህ ካልሆነ አገልግሎቱ እንደማንኛውም ዓለማዊ ሥራ ከመሆኑም ባሻገር በረከት የተለየው ድካም ይሆናል፡፡ስለዚህ ከዚህ በታች የተዘረዘሩ ነጥቦች በመንፈሳዊ አገልግሎት ላይ ላሉ አገልጋዮችም ሆነ ለማገልገል ለሚሹ አስፈላጊ ናቸው፡፡ መንፈሳዊ አገልግሎት የምንለው የአግዚአብሔር የሆነውንና መንፈሳዊ ዓላማን መሠረት በማድረግ የሚገለገለውን ነው፡፡
ይቆየን
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
                                                                          ምንጭ፡-አትሮንስ መጽሔት መስከረም 2009 ዓ.ም

መንፈሳዊ አገልግሎት ክፍል ፪



                                                  (ቤተ ሐዋርያት መስከረም ፲፰  ፳፻፲)

እንዴት እናገለግል ዘንድ ይገባል?

1. በእምነት (በመንፈስ)ማገለገል

መንፈሳዊ አገልግሎት በምድራዊ አመክንዮ (logic) ያልተሳሰረ መሠረቱም ጉልላቱም ረቂቅ እምነት የሆነ የአምልኮ ዘርፍ ነው፡፡ በእግዚአብሔር ሳያምኑ መንፈሳዊ አገልጋይ መሆን አይችልም፡፡ ዕምነት የመጀመሪያው አንድ አገልጋይ ሊያሟላ የሚገባው ሰማያዊ የመንፈሳዊ አገልግሎት ስንቅ ነው፡፡ ሳያምኑ ማገልገል ድካም ነው፡፡ የመንፈስ ዝለትንም ያመጣል፡፡ አንድ ጥሩ እምነት ያለው አገልጋይ ከአላስፈላጊ ጭንቀት ነፃ ስለሆነና መንፈስ ቅዱስን የአገልግሎቱ መሪ ስለሚያደርግ የሚያገለግለው በመንፈስ እንጂ በሥጋ አይደለም፡፡ ይህም ማለት አገልግሎቱ የረቀቀ ነው፡፡ ምናልባትም ከአእምሮ በላይ ሆኖ በምን ችሎታ ይህን አደረገው; በየትኛው ጊዜው ሠራው ብለን የምንደነቅበት ነው፡፡ ብዙ አገልጋዮች ትልቁ ችግራቸው አገልግሎታቸው በአእምሯዊ ቀመር (calculation) ብቻ የተሰላ መሆኑ ነው፡፡ እግዚአብሔርን በፀሎት የሚጠይቁ እንኳን ጥቂት ናቸው፡፡ ስለዚህ እንደማንኛውም ሰው ግዙፍ ግዙፍን እንጂ ረቂቁን በርካታና ፀጋ አያገኙም፡፡ ቀመራዊ ስለሆኑና የእምነት መነፅር ስለሌላቸው የፀበል ይዘት እንደማንኛውም ውሃ የሃይድሮጅን እና የኦክስጅን ውሕድ እንጂ ያለበት መንፈስ እግዘአብሔር አይረዳቸውም፡፡ ምክንያቱም ምድራዊ ቤተሙከርራንእንጂ መንፈሳዊነትን አያውቁም፡፡  መናፍቃኑ ስንሳለም አይተው ድንጋይን ይስማሉ (ይቅር ይበላቸውና) እንደሚሉን መንፈሳዊነት ጎድሏቸው በመንፈስ የማያገለግሉት እነዚህ አገልጋዮችም “እግዚአብሔር በጎደለው ይሙላ”የሚለን ንግግር የማያውቁ ከመሆናቸው የተነሳ ሁሉ ነገር በእነርሱ ዝግጅትና ድካም ብቻ የሚሳካ ይመስላቸዋል፡፡ መዝሙር ላይ ተመስጦ የሚባል ነገር አያውቃቸውም፡፡ የማን ድምፅ ወጣ ; የማን ወረደ; እንዴት ልራመድ እንዴት ላጨብጭብና ሰውን ላስደስተው;  ከበሮ አመታቴ ያምር ይሁን ሰው ደስ ብሎት ይሁን; በሚሉና በመሳሰሉት ሐሳቦች ከመጠን በላይ ስለሚዋጡ በመዝሙር ተመስጠው አያውቁም ፡፡ ግን ደግሞ የቅዱስ ያሬድን  የመዝሙር ተመስጦ ታሪክ በደንብ ያውቁታል፡፡ ቅዱስ ያሬድ በአፄ ገብረመስቀል ፊት ሲዘምር ከመመሰጡ የተነሳ ምድራዊን ነገር ሁሉ 'የራሱንም ሥጋ ጭምር ረስቶ በሕሊናው ሰማየ ሰማያትን አቋርጦ ከመላእክት ጋር ያመሰግን ነበር ፡፡ እሱ ይቅርና ንጉሡም ተመስጠው በጦር እስኪወጉ ድረስ በመንፈስ ነበሩ፡፡ ቅዱስ ያሬድ ንጉሡ በተመስጦ ሲንቀሳቀሱ እግሩን ድንግት ቢወጉትም መወጋቱ እንኳን እርሱን ከተመስጦው የመመለስ ኃይል አልነበረውም፡፡በኃላ ዝማሬያቸውን ጨርሰው ዝቅ ቢሉ ምድር ላይ ደም አዩና ነገሩ በዛ ተረዱ፡፡ በእርግጥ ጀማሪ አገልጋይ ሁሉ እንዲህ መሆን አለበት አይደለም ፡፡ አየዘመርን ጉንዳን ስትበላን የምንተረማመስ ሰዎች ጦርን ያህል የቻሉትን ቅዱሳንን አንሁን ማለትም ተገቢ አይደለም ፡፡ ነገር ግን እነሱን መምሰል የተመስጦን ሕይወት የእምነትን በርታት የመንፈሳዊነት መዐዛ ለሰውነታችን ማለማመድ የግድ ነው፡፡ ጉባዔ ሲዘረጋ ተውኔት ሲሠራ ሲዘመር እና ማንኛውንም መንፈሳዊ አገልግሎት ሲገለገል ቢያንስ ጸሎት ያስፈልጋል ፡፡ ከመንፈሳዊነት የራቀ የጉባኤ ድምቀትን አምጥቶ ሰውን ለማስደሰት መጣር ይሁዳን መሆን ነው፡፡ መጀመሪያ እግዚአብሔር ማስደሰት ይቀድማል፡፡እርሱን ደግሞ ካለ እምነትና መንፈሳዊነት ማስደሰት አይቻልም ፡፡ (ዕብ. 11፡6)እግዚአብሔርን ስናስደስት የእርሱ የሆኑት ሁሉ ይደሰቱብናል ፡፡ ለዚህ ነው አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊ “መንፈሳዊነት ከተለየው አገልግሎት አገልግሎት የሌለው መንፈሳዊነት ይሻላል‘  በረለው የተናገሩት ፡፡ ቅዱስ ዩሐንስ ሐፂር በተመስጦ ከሚታወቁትና በመንፈሳዊነታቸው ከሚመሰገኑት አገልጋዮች አንዱ ነበሩ፡፡ በአንድ ወቅት በአታቸው ውስጥ የሆነው ሥራቸውን እየሠሩ እግዚአብሔርን ሲያመሰግኑ በሩ ይንኳኳል ፡፡ ሄደው ሲከፍቱ አንድ መነኩሴ “አባ ቅርጫት እንዲሰጡኝ ነው የመጣሁት‘‘ ይላቸዋል ፡፡ አባ ዩሐንስም በተመስጦ ውስጥ  ስለነበሩ ቅርጫቱን ሊሰጡት ወደ ውስጥ ገቡና ዘንግተውት ያቋረጡት ምስጋና ቀጠሉ ፡፡ በር ለይ የቆመው መነኩሴ ቢቆዩበት መልሶ አንኳኳ፡፡ አባም በሩን ከፈቱና ምን ነበር አሉት ፡፡መነኩሴውም አባ ቅርጫት ብዬዎት ነበርኮ አላቸው ፡፡ ነገር ግን አባ ዩሐንስ ሐጺር ወደ ውስጥ ሲገቡ እንደገና ወደ ተመስጦአቸው ተመለሱ፡፡ መነኩሴው ሲቆዩበት እንደገና አንኳኳ፡፡ አባ ዩሐንስ በሩን ከፈቱና “ምን ነበር;”  አሉት ፡፡ መነኩሴው ጉዳዩንመልሶ ቢያስታውሳቸው አባ ዮሐንስ እጁን አፈፍ አድርገው ወደ በዓታቸው አስገቡትና  “ና የፈለከውን መርጠህ ውሰድ ፡፡ እኔ ለእንደዚህ አይነቱ ጊዜ የለኝም አሉት ፡፡ አንድ መንፈሳዊ አገልጋይን በመንፈስ እንዲያገለግል ዘወትር የሚያንኳኩበት ጉዳዮች አሉት፡፡ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች' ቤተሰባዊ' ኅብረተሰባዊ እና ወቅታዊ ጉዳዮቸ  የስጋ ፍላጎት ወዘተ... ዘወትር በጭንቀት እንጂ በመንፈስ እንዲየገለግል ያንኳኩበታል ፡፡ በዚህን ጊዜ እንደ አባ ዩሐንስ ሐጺር ፈፅሞ የመርሳት የብቃት ደረጃ ላይ ባይደረስ እንኳን በመንፈሳዊነትና በፀሎት ማሸነፍ መቻል የጠበቅበታል ፡፡መንፈሳዊ አገልግሎት በመንፈስ መሆን አለበት ስንል መርሳት የሌለብን ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለው ሁሉ በአግባቡና በሥርዓት መሆን እንደአለበት ነው፡፡ (1ቆሮ. 14፡40) እንደ ቤተክርስቲያን ሕግና እንደ እግዚአብሔር ቃል ማገልገላችንን መመርመር ያስፈልጋል፡፡ ቅዱስ ያሬድ በዐፄ ገብረመስቀል ፊት ሲዘምር ከመመሰጡ የተነሳ ምድራዊን ነገር ሁሉ የራሱንም ሥጋ ጭምር ረስቶ በሕሊናው ሰማየ ሰማያትን አቋርጦ ከመላእክት ጋር ያመሰግን ነብረ፡፡ እሱ ይቅርና ንጉሥም ተመስጠው በጦር እሰኪወጉት ድረስ በመንፈስ ነበሩ፡፡  

2. ሰማያዊን ዋጋን አስቦ ማገልገል

እንደ መንፈሳዊ አገልጋይ ማንኛውንም ምድራዊ ሽልማት አስቦ ማገልገል ከጀመረ ምድራዊውን ዋጋ ሲያጣ አገልግሎቱ ይቆማል፡፡ እግዚአበረሔርን  ሳይሆን እገሌን ብሎ የሚመጣ እገሌ ሲጠፋ  ወይም ሲጣላው አገልግሎቱን ያበቃል ፡፡ እግዚአብሔርን ብሎ  የመጣ ግን ቢጣለና ሲሰደብ እንኳን” ስለ ክርስቶስ ብትነቅፍ የክብር መንፈስ የእግዚአብሔር መንፈስ በናንተ ላይ ያርፋልና ብፁዓን ናችው”፡፡ የሚለውን ቅዱስ መፅናኛ ያስባል ፡፡ (1ጰጥ. 4፡14) ሰማያዊ ዋጋን አሰቦ የመጣሰው ጊዜና ነገሮቸ ሲመቻቹለት ሳይሆን አመቻችቶ ያገለግላል ፡፡ኑሮው ሲሞላለት ' ሀብት ሲሰፋለት ' ዘመድ ሲበዛለት  ጊዜን ለሰጠዎ ጌታ ጊዜ አጣው ብሎ አይቀረም ፡፡ የነበረው ከሆነም  ቤቱ ሲቀዘቅዝ' ድህነት ሲያነቀው' ወዳጅ ዘመድ ሲያጣ ተማሮ አይጠፋም ፡፡ የድራዊ ሁኔታዎች መቀያየር ከአገልግሎት አይለየውም ፡፡ ይልቁንስ ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየኛል;  መከራ ወይስ ጭንቀት 'ወይስ ስደት ወይስ ራብ' ወይስ ራቁትነተወይስ ፍርሃት' ወይስ ሰይፍ ነውን' በማለት ፀንቶ ይዘምራል ፡ (ሮሜ. 8፡35)ሰማያዊ ዋጋን የሚያስብ አገልጋይ አይበረግግም ፡፡ የኑሮ ውድነት' የመንግሥት መለወጥ' የፖሊስ መቀየር እና ሌሎች ምድራዊ ነገሮች አያስደነግጡም ፡፡ ሁሌም ፅኑዕ ነው፡፡ የፅናቱ መጠን ይደንቃል ፡፡ የብርታቱም ልክ ይገርማል ፡፡ መመካቱም በእግዚአብሔር ነው፡፡  የይታይልኝ አመል የለበትም ፡፡ሰው አየው አላየው ግድ የለውም ፡፡ እግዚአብሔር እንደሚያየው ያውቃል ፡፡በብዙ ድካም የተዘጋጀበት መርሐ ግብር ተሰረዘ ሲባል  አያኮርፍም ፡፡ ገና አገልግል ሲባል አቤት የ ሁሉ ሕዝብ አለመብዛት የሚያስጨንቀው ለጥቂት ሰው የተዘጋጀሁትን አቀርባለሁ ብሎ ሳይሆን የቀረውን ሰው  ከቤተክርስቲያን መራቅ በማሰብ ነው ፡፡ ሰማያዊ  ዋጋን ማሰብ አንድን አገልጋይ ከዓለማዊ ሠራተኞች የሚለየው ታላቅ ሀብት ነው፡፡ ምደራዊ ሕሊና ያላቸው መንፈሳዊያን አግልጋዮች ግን በገንዘብ እግዚአብሐርን ያገለግሉበታል ፡፡
3. በትሕትና ማገልገል
ትኅትና ለክረስቲያኖች ከተሰጡት ሀብቶች ሁሉ ውቧ ነች፡፡ ትኅትናና እግዚአብሔርን መፍራት ባለጠግነት ክብር ሕይወትም ነው፡ (ምሳ. 22፡4)፡፡ “እግዚአብሔር ትኁታንን ይወዳል ፡፡ (ያዕ. 4፡6)፡፡ ለስም አጠራሩ ክብር ይሁንና ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  ከእርሱ እንድንማር ካዘዘን ነገሮች አንዱ ትሕትናው ነው፡፡ “ከእኔ ተማሩ እኔ የዋሕ በልቤም ትሑት ነኝ፡፡” (ማቴ. 11፡29)፡፡ጉባኤ ሲዘረጋ ፣ ሲዘመር እና ማንኛውንም መንፈሳዊ አገልግሎት ሲገለገል ቢያንስ ጸሎት ያስፈልጋል ፡፡ ካለ ትሕትና መንፈሳዊ አገልግሎትን መከወን ማለት ፍሬን የበጠሰ (የሌለው) መኪናን መንዳት ማለት ነው፡፡ መኪናው ሄዶሄዶ እንደሚጋጨው አገልጋዩም ከሆነ አካል ጋር መጋጨቱ አይቀርም ፡፡ ካለ ትሕትና በትዕቢት አገልግሎ የፀደቀ ቅዱስ በቤተክርስቲያን ታሪክ ውስጥ የለም፡፡ እንደውም ትልቁን ክብርና ልዐልና የገኙት በትሕትና የተጓዙ ቅዱሳን ናቸው ፡፡ እመቤታችን ድንግል ማርያም ምንም እንኳን በመልአከ እየተመገበች በቅድስና ብታድግም ፣ ሴቶች ጌታን የመተትወለወድ ብለው በሹፈትም ቢሆን ቢጠቁሟትም፤ ቅዱስ ገብርኤል “ትፀንሲ ፣ ትወልዲ” ቢላትም እሷ ግን ያቺ የጌታ እናት በኔ ዘመን ኑራ ምነው ባሪያ  በሆንኳት ትል ነበር፡፡ መለአኩ ለሦስተኛ ጊዜ በቤተመቅደስ እስኪነግራት እና የጌታ እናትነቷን እስከታወቀ  ድረስ ሐሳቧ ይህው ነበር ፡፡ ትሑታንን የሚየከብር እግዚአብሔርም መልዐልተ ፍጡራን ፈጣሪ አደረጋት፡፡ ሙሴንና ኤርሚያስን የመሳሰሉት ቅዱሳንንም ብናነሳ አይገባኝም፤አልችልም እሉ እንደተጋደሉ መጽሐፍ ቅዱስ ይመሰክራል ፡፡ “ወደ ፈርኦን የምሄድ የእስራኤልንም ልጆች ከግብፅ የማወጣ እኔ ማነኝ (ዘጸ.3:6)::ወዮጌታ እግዚአብሔር እነሆ ብላቴና ነኝና እናገር ዘንድ አላውቅም(ኤር.1፡6):: እኔ እያለሁ በማለት ፈንታ አላውቅም ብለው ከበሩ፡፡ጌታ በወንጌል ትሕትናን ለሐዋርያት ሲያስተምር የሚከተሉትን በሏል፡፡ ከእናንተ ታላቅ የሆነ በመካከላችሁ እንደታናሽ የሚገዛም እንዲያገለግል ይሁን፡፡ በማዕድ የተቀመጠ ወይንስ የሚያገለግል ማናቸው ታላቅ ነው; የተቀመጠው አየደለምን; እኔ ግን በመካከላችው እንደሚያገለግል ነኝ”፡፡ ሉቃ 22፡26፡፡ መንፈሳዊ አገልግሎት በመሸነፍ፣ በመሰደብና በመዋረድ ክብር፣ በመሞት ድል  የሚገኝበት የትሕትና ባሕር ነው፡፡ ከትሕትና የራቀ አገልጋይም ከባሕር ውስጥ የወጣ አሳ ነው፡፡ፍሬ የያዘ ዛፍ (ቅርንጫፍ) ዝቅ ይላል ይላሉ አበው፡፡ አባ ኤስድሮስ የተባሉ አባት “ሁል ጊዜ የምትጾም ከሆነ በትዕቢት ራስህን ወደ ላይ አታውጣ፣ ከዚህ የተነሣ ራስህን ከፍ አድረገህ የምትመለከት ከሆነ ግን ብትበላ ይሻላል ፡፡ ለአንድ ሰው ራሱን በትዕቢት ከመንፋትና ራሱን ከማክበር ሥጋ ቢበላ ይሻለዋል፡፡” ብለው የትሕትናን ጥቅም አብራርተዋል ፡፡ አንድ ሌላ አባትም ካልበደለና ጻድቅ ነኝ የሚል ሰው ይልቅ የበደለና ኃጢአተኛነቱን የሚያምን ሰው የሻለኛል ብሎ ስለ ትሕትና ገልጸዋል፡፡ አባ መቃርዮስን በአንድ ወቅት ሰይጣን ተገናኘውና “ካንተ የተነሳ የሚደርስብኝ መከራ ታለቅ ነው፡ ጉዳት ላደርስብህ ስፈልግአልችልም ፡፡ ነገር ግን አንተ የምታደርገውን ማንኛውንም ነገር እኔም አደርገዋለሁ ያውም ካንት አብልጬ አደርገዋለሁ፡፡ አንተ አብዝተህ ትጾማለህ፣እኔ ግን ምግብ የሚባል ነገር ፈጽሞ አልበላም፣ አንተ ለሊት እንቅልፍ በማጣት በትጋት ታድራለህ፣እኔ ግን ጨርሶም አልተኛም፡፡ አንተ እኔን የምትበልጠኝና እኔም እርሱን የምመሰክርልህ በአንድ ነገር ብቻ ነው” አለው፡፡ መቃርዮስም እርሱ ምንድን ነው;ሲለው ጋኔሉ “በትሕትና ነው” አለው፡፡ ቅዱሱም የህን የረቀቀና የመጨረሻ ፈተና ለማስወገድ መሬት ላይ ወደቀ፣ ሰይጣኑም ወደ አየር ተኖ ጠፋ፡፡” (ይህ ፈተና ትሑት ነኝ ብሎ እንዲመካ የቀረበ ረቂቅ ፈተና ነበርና) አንድ መንፈሳዊ አገልጋይ ለአገልግሎቱ ስኬት ትሕትና ያለውን ጠቀሜታ በመረዳት ማገልገል ይጠበቅበታል፡፡
4. በፍቅር /በመሥዋዕትነት ማገልገል
ፍቅር ግብሩ መስጠት ነው፡፡ የሚሰጡበትን ምክንያት ሳይፈልጉ እንዲሁ መስጠት፡፡አብ ዓለምን እንዲሁ ካለምክንያት ወዶ አንድያ ልጁን እንደሰጠ፡፡(ዩሐ. 3፡16)፡፡ መንፈሳዊ አገልግሎት እንዲህ አይነቱን ሕይወት ይሻል፡፡ የመስጠት ሕይወትን፡፡ አገልጋዮች የአገልግሎት ፍቅር ሲገባቸው ጊዜያቸውን ባለመሰሰት ይሰጣሉ፡፡ጉልበታቸውን፣ገንዘባቸውን፣ እውቀታቸውን በጣም የበረቱትም ሕይወታቸውን ጭምር አሳልፈው ይሰጣሉ፡፡መንፈሳዊ አገልግሎት የሚታይ፣ የሚጨበጥን ነገር ሰጥተው የማይታይ፣ የማይጨበጥ ፀጋን የሚቀበሉበት የፍቅር/ የመስጠት ሕይወት ነው፡፡ ስጡ ይሰጣችዋል (ሉቃ. 6፡38) የተባለው ለዚህ ነው፡፡ በዳግም ምፅአቱ ጌታ ጻድቃንን በቀኝ ኃጥአንን በግራ አሰልፎ የሚጠይቀው የፍቅር/የመስጠት ጥያቄን ነው፡፡ ትርቤ አብልታችሁኛል; ተጠምቼ አጠጥታችሁኛል;፣...(ማቴ. 25) የፍቅር የመስጠት ጥያቄዎች ናቸው፡፡ ፍቅር የሌለው አገልጋይ የእግዚአብሔር መሆን አይችልም፡፡ ኃጢአቱ እንኳን የማይሸፈንለት ምስኪን ነው፡፡ በፍቅር የሚያገለግል ግን የኃጢአቱ ብዛት በፍቅር ይሸፈንለታል(1ጴጥ. 4፡8፣ምሳ.10፡12) ካለ ፍቅር እግዚአብሔርን ማወቅና ወደ እርሱ መቅረብ አይቻልም፡፡ ወንጌል የፍቅር ሕግ ናት፡፡ ክርስትና የፍቅር ሃይማኖት ናት፡፡ እግዚአብሔር ፍቅር ነው፡፡ ለዚህ ነው ቅዱስ ጳውሎስ ምንም የሰመረ አገልግሎት ቢኖርም ካለፍቅር ከንቱ እንደሆነ ያስተማረው፡፡ የሰውን ሁሉ ቋንቋ ባውቅ፣ የመላእክትንም ሁሉ ቋንቋ ባውቅ፣ ነገር ግን ፍቅር ከሌለኝ አእንደሚጮህ ነሐስ ወይም እንደሚመታ ከበሮ መሆኔ ነው፡፡ ትንቢት ብናገር፣ የተሰወረውን ሁሉ፣ ጥበብን ሁሉ ባውቅ፣ ተራራ እስከ ማለፍስ የሚያደርስ ፍጹም እምነትም ቢኖረኝ ፍቅር ከሌለኝ ከንቱ ነኝ፡፡ ገንዘቤን ሁሉ ለምጽዋት ብሰጥ፣ ሥጋዬንም ለእሳት ብቃጠል ብሰጥ ነገር ግን ፍቅር ከሌለኝ ምንም አይጠቅመኝም፡፡” 1ቆሮ. 13፡1-3 ፍቅር የሌለው አገልጋይ መስጠትን አያውቅም ደግሞ ጊዜውን፣ጉልበቱን፣ ዕውቀቱን፣ ገንዘቡን በመለገስ ማገልገል አይችልም፡፡ ስለዚህ ፍቅር የሌለው መንፈሳዊ አገልጋይ መሆን አይችልም፡፡
5. በትጋት፣በጸሎትና በቅንነት ማገልገል
አንድ መንፈሳዊ አገልጋይ ተጉህ፣ ጸሎተኛና ቅንዓተ ቤተክርስቲያን ያለው መሆን ይገባዋል፡፡ ለሰው የከበረ ሀብት ትጋት ነው (ምሳ. 12፡27) እንዳለ ጠቢቡ ትጋትን የመሰለ ሀብት ከአገልጋይ ሊለየውአይገባም፡፡ ትጋትን ገንዘብ ያደረገ አገልጋይ ለደካማ ጎኖቹ ዘወትር መፍትሔ ያበጃል፡፡ አባ ቢሾይ የተባሉ አባት በትጉህ ጸሎተኛነታቸው ይታወቃሉ፡፡  በትጋኃ ሌሊት የፀኑ ከመሆናቸው የተነሳ እንቅልፍ እንዳይጥላቸው ፀጉራቸውን ከዛፍ ቅርንጫፍ ላይ አስረው ይጸልያሉ፡፡ እንቅልፋቸውን በርትቶ ዝቅ ሲሉ ፀጉራቸውን ከዛፍ ቅርንጫፍ ላይ አስረው ይጸልያሉ፡፡ እንቅልፋቸውን በርትቶ ዝቅ ሲሉ ፀጉራቸውን ስለሚነጫቸው በርትተው ይፀልዩ ነበር፡፡ አባ አርሳንዮስም ለፀሐይ ማታ ጀርባቸው ሰጥተው ለፀሎት ይቆሙና ጠዋት በምስራቅ በፊት ለፊታቸው ስትወጣ ሥጋቸውን ያሳርፋሉ፡፡ በእነዚህ አባቶች ብቃት ደረጃ ማግኘት ቢከብድም የእነርሱን ብረታት አርአያ በማድረግ ግን መትጋት ያስፈልጋል፡፡  ሌላው ወሳኝ ነጥብ አንድ አገልጋይ ቅንዓት ቤተክርስቲያን ለኖረው የሚገባ መሆኑን ማወቁ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ብዙን መከራና ግፍ ቢደርስበትም “የቀረውን ነገር ሳልቆጥር ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሐሳብ ነው፡፡” እንዳለው(2ኛ ቆሮ. 11፤28) በዚህ መናፍቃን በበዙበት ዘመን አገልጋዮች ለቤተክርስቲያን የሚቀኑ ሰይፎች መሆን ይገባቸዋል፡፡ባጠቃላይ መንፈሳዊ አገልግሎትን በመኪና ከመሰልነው እምነትን/መንፈሳዊነትን(መንፈስ ቅዱስ) በመሪ፣ትሕትናን በፍሬን፣ ሰማያዊን ዋጋን ማሰን በመስታወት ፍቅርን በቤንዚል/ነዳጅ፣ ትጋትን በጎማው መመሰል እንችላለን፡፡ መኪና ካለ መሪው አቅጣጫ እንደማይኖረውና ወደ መድረሻው እንደማሄድ ሁሉ /ካለእምነት መንፈሳዊ አገልግሎትም እንዲሁ ነው፡፡ ካለፍሬን መኪና አደጋ ላይ ይወድቃል ይጋጫል፡፡ አገልግሎትም ካለ ትሕትና እንዲሁ ነው፡፡ ካለ መስታወት የፊቱን ማየት እንደማይችል ሰማያዊ ዋጋን ማሰብም የፊቱን በተስፋ እንደናይ ይረዳናል፡፡ ካለ ቤንዚል/ነዳጅ መኪና የማይንቀሳቀስ ቆርቆሮ ነው፡፡ ካለ ፍቅርም አገልግሎት ከንቱ ድካም ነው፡፡ መኪናው በጎማው ይሄዳል፣ መንፈሳዊ አገልግሎትም በአገልጋዩ ትጋት ይገፋል፡፡ አገልጋዮችና ለማገልገል የሚፈልጉ መንገንዘብ ያለባቸው የነጨረሻው ነጥብ መንፈሳዊ አገልግሎት ከፈተና ርቆ እንደማያውቅ ነው፡፡ ከረቂቁ እስከ ግዙፉ ድረስ ሁሉንም ፈተና በአገልግሎት ላይ ሊያጋጥም ይችላል፡፡ የቤተክርስቲያን ምሥረታዋ በመስቀል ላይ እንደመሆኑከፈተና ርቆ በምድር ደልቶት የፀደቀ ቅዱስ የለም፡፡ የመንፈሳዊ አገልጋይ ሕይወትም በፈተና የታጀበ ሊሆን ይችላል፡፡
አገልጋይ እየበረታ በሄደ ቁጥር በፈተናው ይበረታል፡፡ በዚህን ጊዜ በጸሎት፣ በጾምና በስግደት መጋደል ያስፈልጋል፡፡ ከጭስ ለመሸሽ አሳት ውስጥ አይገባምና ተሸንፎ ማገልገል ማቆም እሳት ውስጥ መውደቅ ነው፡፡ ፀጥ ያለ ባሕር ምርጥ ዋናተኛ አይፈራም እንዲሉ የአገልግሎት ባሕር ፀጥ ያለ አለመሆኑን ተገንዝቦ ምርጥ ዋናተኛ ለመሆን መዘጋጀት አስፈላጊ ነው፡፡ ከመንፈሳዊ አገልግሎት በረከት አይለየን፡፡
                      አገልግሎታችንን ቅዱስ አምላካችን ይባርክልን፡፡ አሜን
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
                                      ምንጭ፡-አትሮንስ መጽሔት መስከረም 2009 ዓ.ም


Tuesday, 26 September 2017

“ንሴብሕ ክርስቶስሃ ለዘበመስቀሉ አርኀወ ገነተ”


 (በዲ/ን ፍሬው ለማ ቤተ ሐዋርያት መስከረም 16/2008 ዓ.ም)

"በመስቀሉ ገነትን የከፈለ ክርስቶስን እናወድሰዋለን ቅዱስ ያሬድ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በአደባባይ ከሚከበሩ በዓላት መካከል አንዱ የሆነው የቅዱስ መስቀል በዓል በሚከበርበት ዓማዊ በዓል ላይ ደርሰናል፡፡የዚህ ወቅት ማለትም የመስከረም ሶስተኛ ሳምንት(ከመስከረም 15-25) መዝሙር ዝ ውእቱ መስቀል ይባላል፡፡ በዚህ መዝሙር ውስጥ ነው በመግቢያ ላይ የጠቀስነው ቃል ያለው፡፡ የቅዳሴ ምንባባቱም ምልጣኑም ወረቡም ቁመቱም ይህን የጌታ ሥራ የሚያዘክሩ ናቸው፡፡
ይህ ወቀት በኢትዮጵያ ምእመናን ዘንድ ታሪካዊ፣ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ ገፅታ አለው፡፡ በዚህ ጽሐፍ ውስጥ ሀይማኖታዊ ገፅታውን እናያለን፡፡ መስቀል የሚለው ቃል በኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል በተዘጋጀው የአማርኛ መዝገበ ቃላት
ላይ ለሦሥት ነገሮች መጠሪያነት ሊያገለግል እንደሚችል ተጽፏል፡፡
1. መስቀል ቀጥ ባለ እንጨት አናት አካባቢ ሌላ አጠር ያለ እንጨት በማጋደም ሁለቱን በማያያዝ የሚዘጋጅ በጥንት እስራኤላዊያንና ሮማውያን ጊዜ ወንጀለኞችን ለመግደል ያገለገለ መስቀያ፣
2. ከብረት፣ እንጨት፣ የሚዘጋጅ ክርስቶስ የተሰቀለበት ምሳሌ እና የክርስትና እምነት ተከታዮች ምልክት፣
3. የክርስቶስ መስቀል ከተቀበረበት ቦታ መገኘትን ምክንያት በማድረግ መስከረም 17 ቀን የሚከበር በዓል፡፡
ከዚህም በላይ በክርስትና ውስጥ ስለ ክርስቶስ ሲባል የምንቀበለውን ፀዋትወ መከራም መስቀል እንለዋለን ዘኢጾረ መስቀለ ሞትየ ኢይክል ይፀመደኒ ማቴ 10፡38 እንዲል ይህም መከራ ውስጣዊም ውጫዊም ነው፡፡ ውስጣዊው ከፍትወት/ምኞት የተነሳ የሚመጣብን ሐልዮ ነው፤ ውጫዊው ከሰይጣን(ከአለም) የሚቀርብልን መከራ ነው፡፡ ከእነዚህም በአኮቴት የምንቀበላቸው እና በመስቀሉ ድል የምንነሳቸው አሉ፡፡
መስቀል ከሥላሴ፣ከእመቤታችን ምስጋና ቀጥሎ ምስጋና የሚቀርብለት ታቦት የተቀረፀለት መልክዕ(ውዳሴ) የተደረሰለት የመማጸኛ ጸሎት (መስተብቁዕ ዘመስቀል) የተጻፈለት በነገረ ድህነት ውስጥ ካሉ ታላላቅ ተስፋዎች፣ምልክቶች አንዱ ነው፡፡ በኢትዪጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በነገረ ድህነት ውስጥ ሁለት ታላላቅ ምስክሮችን(ተስፋዎችን) እንዘክራለን፡፡እነዚህም እመቤታች እና ቅዱስ መስቀል ናቸው፡፡ ሁለቱም በተለያዩ ህብረ አምሳል በብሉይ ኪዳን መጻሕፍት የተገለጡ ናቸው፡፡እመቤታችን ድንግል ማርያም የድህነታችን መሰረት እና መጀመሪያ የሆነች ጌታ ከእርሷ ሥጋን ይነሳ ዘንድ የተገባች ሆና የተገኘች ነችና አንድም የሰውነታችን ባሕርይ የከበረባት የታደሰበት ነች፤ ቅዱስ መስቀሉም ለጠላት ማሳፈሪያ ምልክት ሆኖ የተሰጠን በእመቤታችን ማህፀን የተጀመረው ድህነት የተፈፀመበት በመለኮት ደም የተቀደሰ በክርስቶስ ያገኘነው የትንሣኤ ሰላማችን አርማ ነው፡፡ ለዚህም ነው አባቶች በመስተብቁዕ ዘመስቀል ጸሎታችን በእንተ ዝንቱ አዘዙ መምህራነ ቅዱስ ወንጌል አምሳለ ፈጣሪ ልዑል ንሰግድ ለመስቀል ወለማርያም ድንግል ስለዚህም የቅዱስ ወንጌል መምህራን ለልዑል በሚቀርብ ስግደት አምሳል(በጸጋ) እንድሰግድላቸው አዘውናል::
ከማርያም ድንግልም ከሥጋዋ ሥጋን ነስቷልና ከእርሷም መድኃኒትን አግኝተናልና ለመስቀልም የቃል ደም በላዩ ተንጠባጥቧልና ያሉት በመልክዐ ሥላሴም ላይ ሰላም ለኵልያቲክሙ በሚለው ሥር ተፈጸመ ተስፋ አበው በማርያም ድንግል ወበቀራንዮ ተተክለ መድኃኒት መስቀል የአበው ተስፋ በድንግል ማርያም ተፈጸመ በቀራንዮም መድኃኒት የሆነ መስቀል ተተከለ ተብሎ ተጽፏል ፡፡ ይህም ከላይ የጠቀስነውን ሐሳብ የሚያጠናክርልን ነው፡፡ የሁለቱም(እመቤታችን እና ቅዱስ መስቀል) በአምልኳችን ውስጥ ተደጋግሞ መነሳት ምክንያት ከላይ በጠቀስነው ነገረ ድህነት ውስጥ ካላቸው ሥፍራ የተነሣ ነው፡፡ ክርስቲያን ዘወትር በአዕምሮው ከሚያሰላስለው የክርስቶስ የማዳን ስራ በተጨማሪ በአንገቱ የሚያጠልቀው መስቀል፣በየአብያተ ክርስቲያናቱ ጉልላት ላይ የሚደረጉ መስቀሎች፣ በካህናት እጅ የምንሳለመው መስቀል አለ እነዚህ ሁሉ በተግባርም ይህን ነገረ ድህነትየምንመሰክርባቸው ናቸው፡፡


መስቀል አምላካችን ለሰው ልጅ ፍቅሩን የገለጸበት ታላቁ የፍቅር ት/ቤት ነው፡፡ በምድር ታሪክ ውስጥ ተደርጎ የማያውቅ ወደፊትም የማይደረግ ታላቁ የፍቅር ሥራ በመስቀል ተደርጓል፡፡ እግዚአብሔር ፍጥረታቱ ሲበድሉ ዝም ብሎ የሚያይ አምባገነን ወይም ምንም ማድረግ የማይቻለው ደካማ አይደለምና ወርዶ ተወልዶ ይልቁንም ሞቶ አዳነን እርሱ ግን ፍጥረቶቹን አልተወንም ቸልም አላለንም እርሱን እንደበደልነው መጠን ፈጽመን እንጠፋ ዘንድ በኃጢአታችን አልተቀየመንም፣ወደደን እንጂ፣ጎበኘንም፣ማረን፣ይቅርም አለን፣ከሚገዛንም እጅ አዳነን እንዲል ቅዳሴ ዘዮሐንስ አፈ ወርቅ፡፡
ከሌሎች የእምነት ድርጅቶችም ተለይተን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን (1ቆሮ1፡23) የክርስቶስን ሞት መቀበል የክርስትና የእምነት መሠረት ነው፡፡ ይህም እንዴት የሰውን ሥጋ ይነሳል እንዴትስ ይሞታል ብለው አምላክን ያከበሩ ለሚመስላቸው ሞኝነት ነው፡፡ የሐዲስ ኪዳን ታላቁ ምስጢር ይህ የአምላክ ለፍጥረቶቹ ሲል መሞት ነው፡፡ በሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት ክርስቶስ በሰውም፣ በእርሱም በመላእክትም አንደበት ይሞት ዘንድ እንዳለው ተደጋግሞ ተገልጧል፡፡ ይልቁንም ከትንሳኤው በኋላ እንኳን የሞተው፣የተሰቀለው ተብሎ ተቀጽሎለታል(ማቴ28፡5፣ሮሜ8፡34፣ራዕ1፡18፣ራዕ2፡8) የመምጣቱም ትልቅ ዓላማ ይሞት ዘንድ ነው ይህም በመስቀል ላይ የተፈጸመ ነው፡፡
አባታችን ዮሐንስ አፈ ወርቅ የመዝሙረኛውን ቅዱስ ዳዊት ቃል ሰነፍ በልቡ አምላክ የለም ይላል መዝ13፡1 በተረጎመበት ድርሳኑ እንዲህ ብሏል ክርስቶስን ተሰቅሎ ማየት ያልቻለ በዚህ ስንፍናው ይገለጣል ብሏል ፡፡ ስንፍና የተባለውም ክርሰቶስን እንደተሰቀለ አለማመን ነው (ገላ3፡1)፡፡ በዚህም ቸልተኝነቱ እግዚአብሔርን አያየውም፡፡ የእግዚአብሔርን ኃይል፣ ድል፣ ጠላትን ማሳፈር ማየት፤ማወቅ ለሚፈልጉ ሁሉ መስቀል ታላቁ ምላሽ ነው፡፡የክርስቶስ ሕማም የአምልኳችን መሰረት እና ሁሉ ነገራችን ነው በየቅዳሴው ይህንን ሕማሙን እንሳተፋለን በጥምቀት ከእርሱ ጋር እንሞታለን እንነሳለን የዓመቱ የአምልኮ ጊዜያት በሕማማት ማዕከልነት የተሰደሩ ናቸው ሳምንታችንም የአይሁድን ፍርድ እና ስቅለትን የሚያዘክሩ የአዕፅዋማት ቀኖች ያሉት ነው በቃልም፣በሐሳብም፣በተግባርም መከራውን እናስባለን፡፡
እግዚአብሔር ኃጢአትን፣ ሞትን ፣ በአጠቃላይ ክፉ ነገርን በምድር ላይ እንዲሆን አልፈቀደም አይፈቅድምም፡፡ ለዚህም ትልቁ ማሳያችን ጠላታችንን በመስቀል ጠርቆ ያሳየን ሰላም ነው፡፡ ያለ መስቀል እግዚአብሔርን እና በእኛ ላይ ያለውን አለማ መረዳት አይቻልም፡፡ ክርስቶስ እንደሞተ እና እንደተነሳ እኛም የዚህ ተሳታፊዎች መሆን እንዳለብን የማያስብ ሁሉ ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ እንዳስተማረን ለክርስቶስ ሊሆን አይገባውም(1ዮሐ4፡23) ፡፡ የሰው ልጅ በእግዚአብሔር አርአያ እና አምሳል የተፈጠረ ታላቅ ፍጡር ነው፡፡ ይህም ብቻ አይደለም አምላክ ሰው ሆኖ ያዳነውም ታላቅ ፍጡር ነው፡፡ ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ እርሱ በአምላክነት ያደረገውን(የሆነውን) ሁሉ እኛ በጸጋ እንሆን ዘንድ አድሎናል (ልጅነት፣ንጉሥነት፣ቅዱስነት) ይህ ግን ብቻ አይደለም በስሙ መከራ እንቀበል ዘንድ ጭምር ነው እንጂ ስለ እርሱ መከራ ደግሞ ልትቀበሉ እንጂ በእርሱ ልታምኑ ብቻ አይደለም ፊል1፡29 እንዳለ ሐዋርያው ይህንን ተልዕኳንችን እንፈፅም ዘንድ መስቀል ምልክታችን ነው ክርስቲያን ሁሉ ክርስቶስ መከራ ተቀብሎ ካደለን ማዕድ(ሥጋ ወደሙ) እየተቀበለ መከራው አይንካኝ ይል ዘንድ አይገባም ይልቁንም እንደ ቅዱስ ጳውሎስ ቀኑን ሙሉ ስለአንተ እንገደላለን እንል ዘንድ ይገባናል (ሮሜ8፡36)፡፡ መስቀል እግዚአብሔርን እና ፍጥረትን ሁሉ በመውደዳችን የምንጋፈጠው መከራ ነው፡፡
ከዚህም መከራ እንሸሽ ዘንድ አይገባም በሥጋ መልካም ሆነው ሊታዩ የሚወዱ ሁሉ እንድትገረዙ ግድ አሉአችሁ፥ ነገር ግን ስለ ክርስቶስ መስቀል እንዳይሰደዱ ብቻ ነ ገላ 6፡12 ብሎ እንደወቀሳቸው ሰዎች ከዓለም ጋር ተመሳስለን ሳይሆን ከክርስቶስ ጋር ተባብረን በአኮቴት መስቀላችንን እንቀበል ዘንድ ይቻላል፡፡ ቅዱሳንን ሁሉ አንድ የሚያደርጋቸውም መከራውን በአኮቴት መቀበላቸው ነው እነርሱ እንደ ጌታቸው ከመከራው በኋላ ያለውን ደስታ ናፍቀው ሀይማኖታቸውን ጠብቀዋል፡፡ እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና። ዕብ12፡2 እንዲል ይህ መስቀል ከቤተክርስቲያን አይለይም ለዚህም ስለ ስሜ ስንት መከራ ሊቀበል እንዲያስፈልገው እኔ አመለክተዋለሁና አለው ሐዋ9፡16 ተብሎ የተጠራው ቅዱስ ጳውሎስ ሲመሰክር ስለ አካሉም ማለት ስለ ቤተ ክርስቲያን በሥጋዬ በክርስቶስ መከራ የጐደለውን እፈጽማለሁ። ቆላ1፡24 ይህም ቃል የተነገረው በክርስቶስ ድህነት ህፀፅ ኖሮ ሳይሆን በክርስቶስ ላይ መከራ ያጸና አለም በዚያ አያቆምም የተረፈውን መከራ በቤተክርስቲያኒቷ ያደርሳል ለማለት ነው ለዚህም ሐዋርያው ራሱን ፊት አውራሪ አድርጓል፡፡ እኛም ይህን አሰረ ፍኖት እንከተል ዘንድ ይገባል፡፡
መስቀላችንን በአኮቴት ተቀብለን እንሸከም ዘንድ እንደ ምሳሌ ከተጠቀሱልን ታሪኮች መካከል የፈያታዊ ዘየማን ታሪክ አንደኛው ነው እርሱ በወንጌል እንደተጠቀሰ ስለ አደረግነውም የሚገባንን እንቀበላለንና በእኛስ እውነተኛ ፍርድ ነው፤ ይህ ግን ምንም ክፋት አላደረገም ብሎ ገሠጸው።ሉቃ23፡41 ተብሎ እንደተነገለት እርሱ ምንም እንኳን በኃጢአቱ ምክንያት የመጣበት ቢሆንም በግራው ከተሰቀለው ይልቅ ያለተስፋ መቁረጥ በእምነት መስቀሉን ተቀብሏል በዚህም ጌታን ስለ መሻቱ መድኃኒታችን እውነት እልሃለሁ፥ ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ አለው ሉቃ23፡43 ፡፡ ለ5500 ዘመን ተዘግቶ የነበረውን ገነትም በደመ ማኅተሙ ሲከፍት እርሱን ቀዳሚ አደረገው ይህም አባቶቻችን እንዳስተማሩን በአኮቴት መስቀላችንን ተቀብለን በተከፈተልን ገነት በክብር እንመላለስ ዘንድ የተጻፈልን ነው፡፡
ሌላው ቅዱስ ያሬድ በመስቀል መዝሙር የተናገረው ብከ ንወግዖሙ ለኵሎሙ ፀርነ ወበስምከ ነኀስሮሙ ለእለ ቆሙ ላእሌነ ይቤ ዳዊት በመንፈሰ ትንቢት በእንተ ዝንቱ ዕፀ መስቀል የሚለው ነው በዚህም በመዝ44፡5 ላይ የተጠቀሰውን በአንተ ጠላቶቻችንን እንወጋቸዋለን፥ በስምህም በላያችን የቆሙትን እናዋርዳቸዋለን። ለመስቀል ሰጥቶ ተርጉሟል ጌታችን መከራ እንቀበል ዘንድ መከራ በሚያመጡብን እንፈተን ዘንድ ዝም ብሎ አልተወንም በእርሱ ጠላቶቻችንን ድል እናደርግበት(እንወጋበት) ዘንድ ምልክቱን መስቀሉን ትቶልናል እርሱም ከዲያቢሎስ ፍላፆች ሁሉ የምንድንበት ነው በስምከ ተወከልነ ወበኃይልከ ተማኅፀነ መዓልተ ምስሌነ ወሌሊተ ማዕከሌነ ዝንቱ ትእምርተ መስቀል ቤዛነ በዘቦቱ ንመውዖ ለኵሉ ኃይለ እኩይ እንዲል(መጽሐፈ ዚቅ ዘመስቀል)፡፡ ጌታ በወንገል እንደተናገረው እነዚህ ነገሮች(መከራዎቸን)መቀበል ለቅዱስ ጴጥሮስ እንደ ነገረው በሰው ዘንድ የማይቻል በእግዚአብሔር ዘንድ ግን የሚቻል ነው ማቴ19፡26 ይህም እርሱ በእኛ ካላደረ ወይም ለእርሱ ማደሪያ ራሳችንን ካላመቻቸን ከምስጢራትም ተሳትፈን የእርሱ አካል ካልሆንን በሥጋዊ ጥበብ በእውቀት ብዛት በሥጋችንም በነፍሳችንም (በኀልዮ፣በነቢብ፣በገቢር) የሚመጣብንን ፆር (ፈተና) እንሸከም ዘንድ የማንችለው ነው፡፡ መጋደላችን ከሥጋ እና ከመንፈስ ጋር አይደለምና፡፡
ከንጉሥ ቆስጠንጢኖስ እና ከንግሥት እሌኒ በረከትን ያሳትፈን በኃጢአት ውስጥ የተቀበረውንም መስቀላችንን በተቃጠለ ልብ በክርስቶስ ፍቅር መዓዛ አውጥተን እንሸከም ዘንድ አምላከ ቅዱሳን ይርዳን አሜን፡፡