Thursday, 28 September 2017

መንፈሳዊ አገልግሎት ክፍል ፩



                                                       (ቤተ ሐዋርያት መስከረም ፲፰  ፳፻፲)


አገልግሎት ምን ማለት ነው?

     አገልግሎት የሚለው ቃል  ገልገለ ከከሚለው የግእዝ ግስ የተገኘ እንደሆነ ይጠቁማል፡፡ ገልገለ (አገለገለ)ማለት ተገኣ፣ ታዘዘ፣ ዐገዘ፣ ረዳ፣ ጠቀመ፣ ማንኛውንም ሥራ ሠርቶ ጌታውን ደስ አሰኘ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ አገልግሎት ማለተ መታዘዝ፣ መገዛት፣ መረዳት መጥቀም... ማለት ይሆናል፡፡ ማንኛውንም ሥጋዊና መንፈሳዊ ሥራ አገልግሎት ነው፡፡ ለመንግሥት የሚሰራ የመንግሥት አገልጋይ፣ ለግለሰብ የሚሠራ የግለሰብ አገልጋይ፣ ለእግዚአብሔርም የሚሠራ የእግዚአብሔር አገልጋይ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ አገልጋዮችን በተለያየ ስያሜ ጠርቷል፡፡ ምንም አይነት መብት በራሱ ላይ  የሌላውንና በጌታው ሐሳብ ፍፁም አዳሪ የሆነውን ተገዢ ባሪያ በማለት ገልፆታል ፡፡ ንዋይ ኅሩይ ቅዱስ ጳውሎስ “ከሰው ሁሉ አርነት የወጣሁ ስሆን የሚበልጡትን እንዲጠቅም  እንደባርያ ራሴን ከሁሉ አስገዛለሁ” በማለት የተናገረው ይህን ያጠናክራል፡፡ (1ቆሮ. 9፡19) አብሮት የሚያገለግለውን ቲኪቆስንም “በጌታም አብሮኝ ባሪያ የሆነ” በማለት ጠርቶታል፡፡ (ቁላ. 4፡7) ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም አርነት ወጥታችሁ እንደ እግዚአብሔር ቅዱሳን ባሪያዎች ሁኑ በማለት አገልግሎታችን በፍፁም መገዛት እንዲሆን ይመክረናል፡፡ (1ጴጥ. 2፡16) በራሱ ላይ ሙሉ ነፃነት ያለውን አገልጋይ መጽሐፍ ቅዱስ ሠራተኛ ይለዋል፡፡ (ሉቃ. 10፡2፣ ቆላ. 4፡11፣ 2ጴጥ. 1፤8) ይህ ከባሪያ ይልቅ በራሱ ላይ የመወሰን ሥልጣን ያለው ነው፡፡ ከፈለገ አለማገልግለ ይችላል፡፡ በባሪያና በሠራተኛ መካከል ነፃነቱ  የሆነው ደግሞ ብላቴና፣ ሎሌ ተብሎ የተጠራው ነው፡፡
     መንፈሳዊ አገልግሎት የምንለው የእግዚአብሔር የሆነውና መንፈሳዊ ዓላማን መሠረት በማድለግ የሚገለገለውን ነው፡፡ መንፈሳዊ አገልግሎትን ከሌሎች አገልግሎቶች/ ሥራዎች የሚለዩት በርካታ ጠባያት አሉ፡፡ ትልቁና መሠረታዊው ልዩነት ዓላማው ነው፡፡ በመንፈስ ቅዱስ የሚመራ የመንፈሳውያን ሰዎችና የሰማያውያን መላእክት ረቂቅ ኅብረትና አንድነት የሚገለፅበት በማይታይ ፀጋ ወደ ክርስቶስ በእውነትና በፍቅር የሚሳድግ (ኤፌ. 4፡15) የሐዋርያዊት ቤተክርስቲያን ስንተረጉም ማንኛውም ሥራ ሠርቶ ጌታውን ደስ ማሰኘት ነው ካልን መንፈሳዊ አገልግሎትም ጌታው እንደእግዚአብሔር ነውና እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ማንኛውንም ሥራ መሥራት ነው፡፡ (ሮሜ. 12፡1)እግዚአብሔር ደስ ማሰኘት የሚቻለው ደግሞ በዕምነት ብቻ በመሆን (ዕብ. 11፡6)መንፈሳዊ አገልግሎት የመታመን ሥራ ነው፡፡ ሃይማኖት ማለት ማመንና መታመን ማለት እንደመሆኑ አምላክን አምነን የምንታመነው በመንፈሳዊ አገልግሎት መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

መንፈሳዊ አገልጋይ ማን ማነው?


ፍጥረታት ሁሉ አገልጋዮች ናቸው፡፡ ቅድስት ሥላሴ አንዱንም ፍጥረት ካለዓላማ እንዲሁ በዘፈቀደ አልፈጠሩምና ይልቁንስ አበው እንዳስተማሩት ሰውና መላእክትን እንዲያመሰግኑ ሌሎቹን ፍጥረታት ደግሞ ለአንክሮ' ለተዘክሮ 'ለምስክርነት ፈጥርዋል፡፡ ስለዚህ ላያገለግል የተፈጠረ ፍጥረት የለም ፡፡ ካልእ ፍጥረታት የሰው ልጅ አገልግሎቱን በዘነጋ ጊዜ ስለ አምላክ እየመሰከሩ ሰውን ወደተፈጠረበት ዓላማ (አገልግሎት) ለመመለስ በመጣር አገልግለዋል ፡፡ የበለዓም አህያ (ዘፍ 22) እና የቢታኒያ ድንጋዮች (ሉቃ 19)ለዚህ ምስክሮች ናቸው፡፡ስለ ቅዱሳን መላእክት መንፈሳዊ አገልጋይነት በመጽሐፍ ቅዱስ በተለያዩ ቦታ ተጽፏል ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ በዕብራውያን መልእክቱ ምዕራፍ 1 ቁጥር 14 ላይ ‘ሁሉ መዳንን ይወርሱ ዘንድ ስላላቸው ለማገዝ የሚላኩም የሚያገለግሉም መናፍስት አይደሉምን” በማለት ከርቀታቸው (ረቂቅነታቸው) የተነሳመናፍስት ብሎ የሚያገለግሉ ያላቸው መላእክትን ነው፡፡ ልበ አምላክ ዳዊትም “መላእክቱን መንፈስ የሚያደርግ አገልጋዮቹንም የእሳት ነበልባል”በማለት (መዝ 103፡4) ይህንኑ አጠናክሯል፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስና ነባቢ መለኮት ዮሐንስም የምስጋና አገልግሎታቸውን በእራይ ተመልክተው ጽፈውታል ፡፡(ኢሳ 6፡1-6 ራዕ 4፡5-8)፡፡


እንዲያገለግሉኝ ሕዝቤን ልቀቅ (ዘፀ. 7፡16) እግዚአብሔር አምላክ እስራኤላዊያንን ከዘመናት የግብፅ ስደት ወደ ምድረ ርስት የመመለሻው ወቅት በደረሰ ጊዜ በሙሴ በኩል ፈርኦንን እንዲያገለግሉኝ ሕዝቤን ልቀቅ (ዘፀ 7፤16) ብሎታል፡፡ የእስራኤላዊያን ከስደት መመለስ ለመንፈሳዊ አገልግሎት ነው ፡፡ በሌላ አነጋግር ከስደት የመፈታታቸው ዓላማ አገልግሎት ነው፡፡ ከስደት ተመልሶ እግዚአብሔርን የማያገለግል በስደት ቢኖር ይሻለዋል፡፡ “እንዲያገለግሉኝ” ብሏልና፡፡ በተመሳሳይ የሰው ልጅ የመፈጠሩ ዓላማ ሃይማኖት እንደመሆኑና ሃይማኖት ደግሞ የማመንና የመታመን ጉዳይ በመሆኑ' እንደዚሁም መታመን በመንፈሳዊ አገልግሎት ስለሆነ እግዚአብሔር የማያገለግል ሰወ የመፍጠሩን ዓላማ ሰቷልና ባይፈጠር ይሻለዋል ፡፡ እዚህጋ መንፈሳዊ አገልግሎት ስንል በጠበበው ትርጉም የተለመዱትን የክህነት' የሰ/ት/ቤት ወይም የመንፈሳዊ ማኅበራትን አገልግሎት ብቻ ማለታችን አይደለም፤መሠረታዊ የክርስትና ተግባራትንና የምስጋና ሕይወት አጠቃለልን እንጂ፡፡ በዚህ አረዳድ ሰው ሁሉ መንፈሳዊ አገልጋይ ነው፡፡ ለዚህ ነው ቅዱስ ጳውሎስም ስወን የእግዚአብሔር የተቀደሰ መቅደስ ብሎ የጠራው፡፡ (1ቆሮ. 3፡16)  ታላቁ የቤተክርስቲያን ሊቅ ቅዱስ ዩሐንስ አፈወርቅ በሉቃ 6፡38 ላይ ጌታችን “ስጡ ይሰጣችዋል” ያለው ቃል ሲተረጉመው መንፈሳዊ አገልግሎትን የተመለከተ ቃል ስለመሆኑ መስክሯል፡፡ ጌታ ስጡ ማለቱ አገልግሉ ማለት ነው፡፡ የምድሩን ትታችሁ' ጊዜያችሁን ሰውነታችው ጉልበታችውን ገብራችሁ ዕውቀታችሁን አፍሳችሁ ገንዘባችሁን በጅታችሁ ብታገለግሉ እኔ ደግሞ በጸጋ ላይ ጸጋ በበረከት ላይ በረከት በሕይወት ላይ ቅድስናን አሰጣችኋለሁ ሲል ነው ይላል ሊቁ፡፡ የመንፈሳዊ አገልግሎት መለያዎች ምንም እንኳን አንድ ሰው ቅዳሴ' ምስጋና 'ምስክርነት እና የመሳሰሉትን ከሁላዊት ቤተክርስቲያን የተገኙ ሁሉንም የሚያሳትፍ ሁላዊት አገልግሎቶች ላይ መሳተፍ ግዴታው ቢሆንም በሰንበት ት/ ቤቶች' ቤተክርስቲያን ማኅበራትወይም በተለያዩ መንፈሳዊ ኃላፊነቶች ለማገልገል የሚያስቡ ከሆነ የመንፈሳዊ አገልግሎት የተለዩ ጠባያትን አጥርቶ ማወቅ አለበት፡፡ ይህ ካልሆነ አገልግሎቱ እንደማንኛውም ዓለማዊ ሥራ ከመሆኑም ባሻገር በረከት የተለየው ድካም ይሆናል፡፡ስለዚህ ከዚህ በታች የተዘረዘሩ ነጥቦች በመንፈሳዊ አገልግሎት ላይ ላሉ አገልጋዮችም ሆነ ለማገልገል ለሚሹ አስፈላጊ ናቸው፡፡ መንፈሳዊ አገልግሎት የምንለው የአግዚአብሔር የሆነውንና መንፈሳዊ ዓላማን መሠረት በማድረግ የሚገለገለውን ነው፡፡
ይቆየን
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
                                                                          ምንጭ፡-አትሮንስ መጽሔት መስከረም 2009 ዓ.ም

መንፈሳዊ አገልግሎት ክፍል ፪



                                                  (ቤተ ሐዋርያት መስከረም ፲፰  ፳፻፲)

እንዴት እናገለግል ዘንድ ይገባል?

1. በእምነት (በመንፈስ)ማገለገል

መንፈሳዊ አገልግሎት በምድራዊ አመክንዮ (logic) ያልተሳሰረ መሠረቱም ጉልላቱም ረቂቅ እምነት የሆነ የአምልኮ ዘርፍ ነው፡፡ በእግዚአብሔር ሳያምኑ መንፈሳዊ አገልጋይ መሆን አይችልም፡፡ ዕምነት የመጀመሪያው አንድ አገልጋይ ሊያሟላ የሚገባው ሰማያዊ የመንፈሳዊ አገልግሎት ስንቅ ነው፡፡ ሳያምኑ ማገልገል ድካም ነው፡፡ የመንፈስ ዝለትንም ያመጣል፡፡ አንድ ጥሩ እምነት ያለው አገልጋይ ከአላስፈላጊ ጭንቀት ነፃ ስለሆነና መንፈስ ቅዱስን የአገልግሎቱ መሪ ስለሚያደርግ የሚያገለግለው በመንፈስ እንጂ በሥጋ አይደለም፡፡ ይህም ማለት አገልግሎቱ የረቀቀ ነው፡፡ ምናልባትም ከአእምሮ በላይ ሆኖ በምን ችሎታ ይህን አደረገው; በየትኛው ጊዜው ሠራው ብለን የምንደነቅበት ነው፡፡ ብዙ አገልጋዮች ትልቁ ችግራቸው አገልግሎታቸው በአእምሯዊ ቀመር (calculation) ብቻ የተሰላ መሆኑ ነው፡፡ እግዚአብሔርን በፀሎት የሚጠይቁ እንኳን ጥቂት ናቸው፡፡ ስለዚህ እንደማንኛውም ሰው ግዙፍ ግዙፍን እንጂ ረቂቁን በርካታና ፀጋ አያገኙም፡፡ ቀመራዊ ስለሆኑና የእምነት መነፅር ስለሌላቸው የፀበል ይዘት እንደማንኛውም ውሃ የሃይድሮጅን እና የኦክስጅን ውሕድ እንጂ ያለበት መንፈስ እግዘአብሔር አይረዳቸውም፡፡ ምክንያቱም ምድራዊ ቤተሙከርራንእንጂ መንፈሳዊነትን አያውቁም፡፡  መናፍቃኑ ስንሳለም አይተው ድንጋይን ይስማሉ (ይቅር ይበላቸውና) እንደሚሉን መንፈሳዊነት ጎድሏቸው በመንፈስ የማያገለግሉት እነዚህ አገልጋዮችም “እግዚአብሔር በጎደለው ይሙላ”የሚለን ንግግር የማያውቁ ከመሆናቸው የተነሳ ሁሉ ነገር በእነርሱ ዝግጅትና ድካም ብቻ የሚሳካ ይመስላቸዋል፡፡ መዝሙር ላይ ተመስጦ የሚባል ነገር አያውቃቸውም፡፡ የማን ድምፅ ወጣ ; የማን ወረደ; እንዴት ልራመድ እንዴት ላጨብጭብና ሰውን ላስደስተው;  ከበሮ አመታቴ ያምር ይሁን ሰው ደስ ብሎት ይሁን; በሚሉና በመሳሰሉት ሐሳቦች ከመጠን በላይ ስለሚዋጡ በመዝሙር ተመስጠው አያውቁም ፡፡ ግን ደግሞ የቅዱስ ያሬድን  የመዝሙር ተመስጦ ታሪክ በደንብ ያውቁታል፡፡ ቅዱስ ያሬድ በአፄ ገብረመስቀል ፊት ሲዘምር ከመመሰጡ የተነሳ ምድራዊን ነገር ሁሉ 'የራሱንም ሥጋ ጭምር ረስቶ በሕሊናው ሰማየ ሰማያትን አቋርጦ ከመላእክት ጋር ያመሰግን ነበር ፡፡ እሱ ይቅርና ንጉሡም ተመስጠው በጦር እስኪወጉ ድረስ በመንፈስ ነበሩ፡፡ ቅዱስ ያሬድ ንጉሡ በተመስጦ ሲንቀሳቀሱ እግሩን ድንግት ቢወጉትም መወጋቱ እንኳን እርሱን ከተመስጦው የመመለስ ኃይል አልነበረውም፡፡በኃላ ዝማሬያቸውን ጨርሰው ዝቅ ቢሉ ምድር ላይ ደም አዩና ነገሩ በዛ ተረዱ፡፡ በእርግጥ ጀማሪ አገልጋይ ሁሉ እንዲህ መሆን አለበት አይደለም ፡፡ አየዘመርን ጉንዳን ስትበላን የምንተረማመስ ሰዎች ጦርን ያህል የቻሉትን ቅዱሳንን አንሁን ማለትም ተገቢ አይደለም ፡፡ ነገር ግን እነሱን መምሰል የተመስጦን ሕይወት የእምነትን በርታት የመንፈሳዊነት መዐዛ ለሰውነታችን ማለማመድ የግድ ነው፡፡ ጉባዔ ሲዘረጋ ተውኔት ሲሠራ ሲዘመር እና ማንኛውንም መንፈሳዊ አገልግሎት ሲገለገል ቢያንስ ጸሎት ያስፈልጋል ፡፡ ከመንፈሳዊነት የራቀ የጉባኤ ድምቀትን አምጥቶ ሰውን ለማስደሰት መጣር ይሁዳን መሆን ነው፡፡ መጀመሪያ እግዚአብሔር ማስደሰት ይቀድማል፡፡እርሱን ደግሞ ካለ እምነትና መንፈሳዊነት ማስደሰት አይቻልም ፡፡ (ዕብ. 11፡6)እግዚአብሔርን ስናስደስት የእርሱ የሆኑት ሁሉ ይደሰቱብናል ፡፡ ለዚህ ነው አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊ “መንፈሳዊነት ከተለየው አገልግሎት አገልግሎት የሌለው መንፈሳዊነት ይሻላል‘  በረለው የተናገሩት ፡፡ ቅዱስ ዩሐንስ ሐፂር በተመስጦ ከሚታወቁትና በመንፈሳዊነታቸው ከሚመሰገኑት አገልጋዮች አንዱ ነበሩ፡፡ በአንድ ወቅት በአታቸው ውስጥ የሆነው ሥራቸውን እየሠሩ እግዚአብሔርን ሲያመሰግኑ በሩ ይንኳኳል ፡፡ ሄደው ሲከፍቱ አንድ መነኩሴ “አባ ቅርጫት እንዲሰጡኝ ነው የመጣሁት‘‘ ይላቸዋል ፡፡ አባ ዩሐንስም በተመስጦ ውስጥ  ስለነበሩ ቅርጫቱን ሊሰጡት ወደ ውስጥ ገቡና ዘንግተውት ያቋረጡት ምስጋና ቀጠሉ ፡፡ በር ለይ የቆመው መነኩሴ ቢቆዩበት መልሶ አንኳኳ፡፡ አባም በሩን ከፈቱና ምን ነበር አሉት ፡፡መነኩሴውም አባ ቅርጫት ብዬዎት ነበርኮ አላቸው ፡፡ ነገር ግን አባ ዩሐንስ ሐጺር ወደ ውስጥ ሲገቡ እንደገና ወደ ተመስጦአቸው ተመለሱ፡፡ መነኩሴው ሲቆዩበት እንደገና አንኳኳ፡፡ አባ ዩሐንስ በሩን ከፈቱና “ምን ነበር;”  አሉት ፡፡ መነኩሴው ጉዳዩንመልሶ ቢያስታውሳቸው አባ ዮሐንስ እጁን አፈፍ አድርገው ወደ በዓታቸው አስገቡትና  “ና የፈለከውን መርጠህ ውሰድ ፡፡ እኔ ለእንደዚህ አይነቱ ጊዜ የለኝም አሉት ፡፡ አንድ መንፈሳዊ አገልጋይን በመንፈስ እንዲያገለግል ዘወትር የሚያንኳኩበት ጉዳዮች አሉት፡፡ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች' ቤተሰባዊ' ኅብረተሰባዊ እና ወቅታዊ ጉዳዮቸ  የስጋ ፍላጎት ወዘተ... ዘወትር በጭንቀት እንጂ በመንፈስ እንዲየገለግል ያንኳኩበታል ፡፡ በዚህን ጊዜ እንደ አባ ዩሐንስ ሐጺር ፈፅሞ የመርሳት የብቃት ደረጃ ላይ ባይደረስ እንኳን በመንፈሳዊነትና በፀሎት ማሸነፍ መቻል የጠበቅበታል ፡፡መንፈሳዊ አገልግሎት በመንፈስ መሆን አለበት ስንል መርሳት የሌለብን ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለው ሁሉ በአግባቡና በሥርዓት መሆን እንደአለበት ነው፡፡ (1ቆሮ. 14፡40) እንደ ቤተክርስቲያን ሕግና እንደ እግዚአብሔር ቃል ማገልገላችንን መመርመር ያስፈልጋል፡፡ ቅዱስ ያሬድ በዐፄ ገብረመስቀል ፊት ሲዘምር ከመመሰጡ የተነሳ ምድራዊን ነገር ሁሉ የራሱንም ሥጋ ጭምር ረስቶ በሕሊናው ሰማየ ሰማያትን አቋርጦ ከመላእክት ጋር ያመሰግን ነብረ፡፡ እሱ ይቅርና ንጉሥም ተመስጠው በጦር እሰኪወጉት ድረስ በመንፈስ ነበሩ፡፡  

2. ሰማያዊን ዋጋን አስቦ ማገልገል

እንደ መንፈሳዊ አገልጋይ ማንኛውንም ምድራዊ ሽልማት አስቦ ማገልገል ከጀመረ ምድራዊውን ዋጋ ሲያጣ አገልግሎቱ ይቆማል፡፡ እግዚአበረሔርን  ሳይሆን እገሌን ብሎ የሚመጣ እገሌ ሲጠፋ  ወይም ሲጣላው አገልግሎቱን ያበቃል ፡፡ እግዚአብሔርን ብሎ  የመጣ ግን ቢጣለና ሲሰደብ እንኳን” ስለ ክርስቶስ ብትነቅፍ የክብር መንፈስ የእግዚአብሔር መንፈስ በናንተ ላይ ያርፋልና ብፁዓን ናችው”፡፡ የሚለውን ቅዱስ መፅናኛ ያስባል ፡፡ (1ጰጥ. 4፡14) ሰማያዊ ዋጋን አሰቦ የመጣሰው ጊዜና ነገሮቸ ሲመቻቹለት ሳይሆን አመቻችቶ ያገለግላል ፡፡ኑሮው ሲሞላለት ' ሀብት ሲሰፋለት ' ዘመድ ሲበዛለት  ጊዜን ለሰጠዎ ጌታ ጊዜ አጣው ብሎ አይቀረም ፡፡ የነበረው ከሆነም  ቤቱ ሲቀዘቅዝ' ድህነት ሲያነቀው' ወዳጅ ዘመድ ሲያጣ ተማሮ አይጠፋም ፡፡ የድራዊ ሁኔታዎች መቀያየር ከአገልግሎት አይለየውም ፡፡ ይልቁንስ ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየኛል;  መከራ ወይስ ጭንቀት 'ወይስ ስደት ወይስ ራብ' ወይስ ራቁትነተወይስ ፍርሃት' ወይስ ሰይፍ ነውን' በማለት ፀንቶ ይዘምራል ፡ (ሮሜ. 8፡35)ሰማያዊ ዋጋን የሚያስብ አገልጋይ አይበረግግም ፡፡ የኑሮ ውድነት' የመንግሥት መለወጥ' የፖሊስ መቀየር እና ሌሎች ምድራዊ ነገሮች አያስደነግጡም ፡፡ ሁሌም ፅኑዕ ነው፡፡ የፅናቱ መጠን ይደንቃል ፡፡ የብርታቱም ልክ ይገርማል ፡፡ መመካቱም በእግዚአብሔር ነው፡፡  የይታይልኝ አመል የለበትም ፡፡ሰው አየው አላየው ግድ የለውም ፡፡ እግዚአብሔር እንደሚያየው ያውቃል ፡፡በብዙ ድካም የተዘጋጀበት መርሐ ግብር ተሰረዘ ሲባል  አያኮርፍም ፡፡ ገና አገልግል ሲባል አቤት የ ሁሉ ሕዝብ አለመብዛት የሚያስጨንቀው ለጥቂት ሰው የተዘጋጀሁትን አቀርባለሁ ብሎ ሳይሆን የቀረውን ሰው  ከቤተክርስቲያን መራቅ በማሰብ ነው ፡፡ ሰማያዊ  ዋጋን ማሰብ አንድን አገልጋይ ከዓለማዊ ሠራተኞች የሚለየው ታላቅ ሀብት ነው፡፡ ምደራዊ ሕሊና ያላቸው መንፈሳዊያን አግልጋዮች ግን በገንዘብ እግዚአብሐርን ያገለግሉበታል ፡፡
3. በትሕትና ማገልገል
ትኅትና ለክረስቲያኖች ከተሰጡት ሀብቶች ሁሉ ውቧ ነች፡፡ ትኅትናና እግዚአብሔርን መፍራት ባለጠግነት ክብር ሕይወትም ነው፡ (ምሳ. 22፡4)፡፡ “እግዚአብሔር ትኁታንን ይወዳል ፡፡ (ያዕ. 4፡6)፡፡ ለስም አጠራሩ ክብር ይሁንና ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  ከእርሱ እንድንማር ካዘዘን ነገሮች አንዱ ትሕትናው ነው፡፡ “ከእኔ ተማሩ እኔ የዋሕ በልቤም ትሑት ነኝ፡፡” (ማቴ. 11፡29)፡፡ጉባኤ ሲዘረጋ ፣ ሲዘመር እና ማንኛውንም መንፈሳዊ አገልግሎት ሲገለገል ቢያንስ ጸሎት ያስፈልጋል ፡፡ ካለ ትሕትና መንፈሳዊ አገልግሎትን መከወን ማለት ፍሬን የበጠሰ (የሌለው) መኪናን መንዳት ማለት ነው፡፡ መኪናው ሄዶሄዶ እንደሚጋጨው አገልጋዩም ከሆነ አካል ጋር መጋጨቱ አይቀርም ፡፡ ካለ ትሕትና በትዕቢት አገልግሎ የፀደቀ ቅዱስ በቤተክርስቲያን ታሪክ ውስጥ የለም፡፡ እንደውም ትልቁን ክብርና ልዐልና የገኙት በትሕትና የተጓዙ ቅዱሳን ናቸው ፡፡ እመቤታችን ድንግል ማርያም ምንም እንኳን በመልአከ እየተመገበች በቅድስና ብታድግም ፣ ሴቶች ጌታን የመተትወለወድ ብለው በሹፈትም ቢሆን ቢጠቁሟትም፤ ቅዱስ ገብርኤል “ትፀንሲ ፣ ትወልዲ” ቢላትም እሷ ግን ያቺ የጌታ እናት በኔ ዘመን ኑራ ምነው ባሪያ  በሆንኳት ትል ነበር፡፡ መለአኩ ለሦስተኛ ጊዜ በቤተመቅደስ እስኪነግራት እና የጌታ እናትነቷን እስከታወቀ  ድረስ ሐሳቧ ይህው ነበር ፡፡ ትሑታንን የሚየከብር እግዚአብሔርም መልዐልተ ፍጡራን ፈጣሪ አደረጋት፡፡ ሙሴንና ኤርሚያስን የመሳሰሉት ቅዱሳንንም ብናነሳ አይገባኝም፤አልችልም እሉ እንደተጋደሉ መጽሐፍ ቅዱስ ይመሰክራል ፡፡ “ወደ ፈርኦን የምሄድ የእስራኤልንም ልጆች ከግብፅ የማወጣ እኔ ማነኝ (ዘጸ.3:6)::ወዮጌታ እግዚአብሔር እነሆ ብላቴና ነኝና እናገር ዘንድ አላውቅም(ኤር.1፡6):: እኔ እያለሁ በማለት ፈንታ አላውቅም ብለው ከበሩ፡፡ጌታ በወንጌል ትሕትናን ለሐዋርያት ሲያስተምር የሚከተሉትን በሏል፡፡ ከእናንተ ታላቅ የሆነ በመካከላችሁ እንደታናሽ የሚገዛም እንዲያገለግል ይሁን፡፡ በማዕድ የተቀመጠ ወይንስ የሚያገለግል ማናቸው ታላቅ ነው; የተቀመጠው አየደለምን; እኔ ግን በመካከላችው እንደሚያገለግል ነኝ”፡፡ ሉቃ 22፡26፡፡ መንፈሳዊ አገልግሎት በመሸነፍ፣ በመሰደብና በመዋረድ ክብር፣ በመሞት ድል  የሚገኝበት የትሕትና ባሕር ነው፡፡ ከትሕትና የራቀ አገልጋይም ከባሕር ውስጥ የወጣ አሳ ነው፡፡ፍሬ የያዘ ዛፍ (ቅርንጫፍ) ዝቅ ይላል ይላሉ አበው፡፡ አባ ኤስድሮስ የተባሉ አባት “ሁል ጊዜ የምትጾም ከሆነ በትዕቢት ራስህን ወደ ላይ አታውጣ፣ ከዚህ የተነሣ ራስህን ከፍ አድረገህ የምትመለከት ከሆነ ግን ብትበላ ይሻላል ፡፡ ለአንድ ሰው ራሱን በትዕቢት ከመንፋትና ራሱን ከማክበር ሥጋ ቢበላ ይሻለዋል፡፡” ብለው የትሕትናን ጥቅም አብራርተዋል ፡፡ አንድ ሌላ አባትም ካልበደለና ጻድቅ ነኝ የሚል ሰው ይልቅ የበደለና ኃጢአተኛነቱን የሚያምን ሰው የሻለኛል ብሎ ስለ ትሕትና ገልጸዋል፡፡ አባ መቃርዮስን በአንድ ወቅት ሰይጣን ተገናኘውና “ካንተ የተነሳ የሚደርስብኝ መከራ ታለቅ ነው፡ ጉዳት ላደርስብህ ስፈልግአልችልም ፡፡ ነገር ግን አንተ የምታደርገውን ማንኛውንም ነገር እኔም አደርገዋለሁ ያውም ካንት አብልጬ አደርገዋለሁ፡፡ አንተ አብዝተህ ትጾማለህ፣እኔ ግን ምግብ የሚባል ነገር ፈጽሞ አልበላም፣ አንተ ለሊት እንቅልፍ በማጣት በትጋት ታድራለህ፣እኔ ግን ጨርሶም አልተኛም፡፡ አንተ እኔን የምትበልጠኝና እኔም እርሱን የምመሰክርልህ በአንድ ነገር ብቻ ነው” አለው፡፡ መቃርዮስም እርሱ ምንድን ነው;ሲለው ጋኔሉ “በትሕትና ነው” አለው፡፡ ቅዱሱም የህን የረቀቀና የመጨረሻ ፈተና ለማስወገድ መሬት ላይ ወደቀ፣ ሰይጣኑም ወደ አየር ተኖ ጠፋ፡፡” (ይህ ፈተና ትሑት ነኝ ብሎ እንዲመካ የቀረበ ረቂቅ ፈተና ነበርና) አንድ መንፈሳዊ አገልጋይ ለአገልግሎቱ ስኬት ትሕትና ያለውን ጠቀሜታ በመረዳት ማገልገል ይጠበቅበታል፡፡
4. በፍቅር /በመሥዋዕትነት ማገልገል
ፍቅር ግብሩ መስጠት ነው፡፡ የሚሰጡበትን ምክንያት ሳይፈልጉ እንዲሁ መስጠት፡፡አብ ዓለምን እንዲሁ ካለምክንያት ወዶ አንድያ ልጁን እንደሰጠ፡፡(ዩሐ. 3፡16)፡፡ መንፈሳዊ አገልግሎት እንዲህ አይነቱን ሕይወት ይሻል፡፡ የመስጠት ሕይወትን፡፡ አገልጋዮች የአገልግሎት ፍቅር ሲገባቸው ጊዜያቸውን ባለመሰሰት ይሰጣሉ፡፡ጉልበታቸውን፣ገንዘባቸውን፣ እውቀታቸውን በጣም የበረቱትም ሕይወታቸውን ጭምር አሳልፈው ይሰጣሉ፡፡መንፈሳዊ አገልግሎት የሚታይ፣ የሚጨበጥን ነገር ሰጥተው የማይታይ፣ የማይጨበጥ ፀጋን የሚቀበሉበት የፍቅር/ የመስጠት ሕይወት ነው፡፡ ስጡ ይሰጣችዋል (ሉቃ. 6፡38) የተባለው ለዚህ ነው፡፡ በዳግም ምፅአቱ ጌታ ጻድቃንን በቀኝ ኃጥአንን በግራ አሰልፎ የሚጠይቀው የፍቅር/የመስጠት ጥያቄን ነው፡፡ ትርቤ አብልታችሁኛል; ተጠምቼ አጠጥታችሁኛል;፣...(ማቴ. 25) የፍቅር የመስጠት ጥያቄዎች ናቸው፡፡ ፍቅር የሌለው አገልጋይ የእግዚአብሔር መሆን አይችልም፡፡ ኃጢአቱ እንኳን የማይሸፈንለት ምስኪን ነው፡፡ በፍቅር የሚያገለግል ግን የኃጢአቱ ብዛት በፍቅር ይሸፈንለታል(1ጴጥ. 4፡8፣ምሳ.10፡12) ካለ ፍቅር እግዚአብሔርን ማወቅና ወደ እርሱ መቅረብ አይቻልም፡፡ ወንጌል የፍቅር ሕግ ናት፡፡ ክርስትና የፍቅር ሃይማኖት ናት፡፡ እግዚአብሔር ፍቅር ነው፡፡ ለዚህ ነው ቅዱስ ጳውሎስ ምንም የሰመረ አገልግሎት ቢኖርም ካለፍቅር ከንቱ እንደሆነ ያስተማረው፡፡ የሰውን ሁሉ ቋንቋ ባውቅ፣ የመላእክትንም ሁሉ ቋንቋ ባውቅ፣ ነገር ግን ፍቅር ከሌለኝ አእንደሚጮህ ነሐስ ወይም እንደሚመታ ከበሮ መሆኔ ነው፡፡ ትንቢት ብናገር፣ የተሰወረውን ሁሉ፣ ጥበብን ሁሉ ባውቅ፣ ተራራ እስከ ማለፍስ የሚያደርስ ፍጹም እምነትም ቢኖረኝ ፍቅር ከሌለኝ ከንቱ ነኝ፡፡ ገንዘቤን ሁሉ ለምጽዋት ብሰጥ፣ ሥጋዬንም ለእሳት ብቃጠል ብሰጥ ነገር ግን ፍቅር ከሌለኝ ምንም አይጠቅመኝም፡፡” 1ቆሮ. 13፡1-3 ፍቅር የሌለው አገልጋይ መስጠትን አያውቅም ደግሞ ጊዜውን፣ጉልበቱን፣ ዕውቀቱን፣ ገንዘቡን በመለገስ ማገልገል አይችልም፡፡ ስለዚህ ፍቅር የሌለው መንፈሳዊ አገልጋይ መሆን አይችልም፡፡
5. በትጋት፣በጸሎትና በቅንነት ማገልገል
አንድ መንፈሳዊ አገልጋይ ተጉህ፣ ጸሎተኛና ቅንዓተ ቤተክርስቲያን ያለው መሆን ይገባዋል፡፡ ለሰው የከበረ ሀብት ትጋት ነው (ምሳ. 12፡27) እንዳለ ጠቢቡ ትጋትን የመሰለ ሀብት ከአገልጋይ ሊለየውአይገባም፡፡ ትጋትን ገንዘብ ያደረገ አገልጋይ ለደካማ ጎኖቹ ዘወትር መፍትሔ ያበጃል፡፡ አባ ቢሾይ የተባሉ አባት በትጉህ ጸሎተኛነታቸው ይታወቃሉ፡፡  በትጋኃ ሌሊት የፀኑ ከመሆናቸው የተነሳ እንቅልፍ እንዳይጥላቸው ፀጉራቸውን ከዛፍ ቅርንጫፍ ላይ አስረው ይጸልያሉ፡፡ እንቅልፋቸውን በርትቶ ዝቅ ሲሉ ፀጉራቸውን ከዛፍ ቅርንጫፍ ላይ አስረው ይጸልያሉ፡፡ እንቅልፋቸውን በርትቶ ዝቅ ሲሉ ፀጉራቸውን ስለሚነጫቸው በርትተው ይፀልዩ ነበር፡፡ አባ አርሳንዮስም ለፀሐይ ማታ ጀርባቸው ሰጥተው ለፀሎት ይቆሙና ጠዋት በምስራቅ በፊት ለፊታቸው ስትወጣ ሥጋቸውን ያሳርፋሉ፡፡ በእነዚህ አባቶች ብቃት ደረጃ ማግኘት ቢከብድም የእነርሱን ብረታት አርአያ በማድረግ ግን መትጋት ያስፈልጋል፡፡  ሌላው ወሳኝ ነጥብ አንድ አገልጋይ ቅንዓት ቤተክርስቲያን ለኖረው የሚገባ መሆኑን ማወቁ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ብዙን መከራና ግፍ ቢደርስበትም “የቀረውን ነገር ሳልቆጥር ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሐሳብ ነው፡፡” እንዳለው(2ኛ ቆሮ. 11፤28) በዚህ መናፍቃን በበዙበት ዘመን አገልጋዮች ለቤተክርስቲያን የሚቀኑ ሰይፎች መሆን ይገባቸዋል፡፡ባጠቃላይ መንፈሳዊ አገልግሎትን በመኪና ከመሰልነው እምነትን/መንፈሳዊነትን(መንፈስ ቅዱስ) በመሪ፣ትሕትናን በፍሬን፣ ሰማያዊን ዋጋን ማሰን በመስታወት ፍቅርን በቤንዚል/ነዳጅ፣ ትጋትን በጎማው መመሰል እንችላለን፡፡ መኪና ካለ መሪው አቅጣጫ እንደማይኖረውና ወደ መድረሻው እንደማሄድ ሁሉ /ካለእምነት መንፈሳዊ አገልግሎትም እንዲሁ ነው፡፡ ካለፍሬን መኪና አደጋ ላይ ይወድቃል ይጋጫል፡፡ አገልግሎትም ካለ ትሕትና እንዲሁ ነው፡፡ ካለ መስታወት የፊቱን ማየት እንደማይችል ሰማያዊ ዋጋን ማሰብም የፊቱን በተስፋ እንደናይ ይረዳናል፡፡ ካለ ቤንዚል/ነዳጅ መኪና የማይንቀሳቀስ ቆርቆሮ ነው፡፡ ካለ ፍቅርም አገልግሎት ከንቱ ድካም ነው፡፡ መኪናው በጎማው ይሄዳል፣ መንፈሳዊ አገልግሎትም በአገልጋዩ ትጋት ይገፋል፡፡ አገልጋዮችና ለማገልገል የሚፈልጉ መንገንዘብ ያለባቸው የነጨረሻው ነጥብ መንፈሳዊ አገልግሎት ከፈተና ርቆ እንደማያውቅ ነው፡፡ ከረቂቁ እስከ ግዙፉ ድረስ ሁሉንም ፈተና በአገልግሎት ላይ ሊያጋጥም ይችላል፡፡ የቤተክርስቲያን ምሥረታዋ በመስቀል ላይ እንደመሆኑከፈተና ርቆ በምድር ደልቶት የፀደቀ ቅዱስ የለም፡፡ የመንፈሳዊ አገልጋይ ሕይወትም በፈተና የታጀበ ሊሆን ይችላል፡፡
አገልጋይ እየበረታ በሄደ ቁጥር በፈተናው ይበረታል፡፡ በዚህን ጊዜ በጸሎት፣ በጾምና በስግደት መጋደል ያስፈልጋል፡፡ ከጭስ ለመሸሽ አሳት ውስጥ አይገባምና ተሸንፎ ማገልገል ማቆም እሳት ውስጥ መውደቅ ነው፡፡ ፀጥ ያለ ባሕር ምርጥ ዋናተኛ አይፈራም እንዲሉ የአገልግሎት ባሕር ፀጥ ያለ አለመሆኑን ተገንዝቦ ምርጥ ዋናተኛ ለመሆን መዘጋጀት አስፈላጊ ነው፡፡ ከመንፈሳዊ አገልግሎት በረከት አይለየን፡፡
                      አገልግሎታችንን ቅዱስ አምላካችን ይባርክልን፡፡ አሜን
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
                                      ምንጭ፡-አትሮንስ መጽሔት መስከረም 2009 ዓ.ም


Tuesday, 26 September 2017

“ንሴብሕ ክርስቶስሃ ለዘበመስቀሉ አርኀወ ገነተ”


 (በዲ/ን ፍሬው ለማ ቤተ ሐዋርያት መስከረም 16/2008 ዓ.ም)

"በመስቀሉ ገነትን የከፈለ ክርስቶስን እናወድሰዋለን ቅዱስ ያሬድ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በአደባባይ ከሚከበሩ በዓላት መካከል አንዱ የሆነው የቅዱስ መስቀል በዓል በሚከበርበት ዓማዊ በዓል ላይ ደርሰናል፡፡የዚህ ወቅት ማለትም የመስከረም ሶስተኛ ሳምንት(ከመስከረም 15-25) መዝሙር ዝ ውእቱ መስቀል ይባላል፡፡ በዚህ መዝሙር ውስጥ ነው በመግቢያ ላይ የጠቀስነው ቃል ያለው፡፡ የቅዳሴ ምንባባቱም ምልጣኑም ወረቡም ቁመቱም ይህን የጌታ ሥራ የሚያዘክሩ ናቸው፡፡
ይህ ወቀት በኢትዮጵያ ምእመናን ዘንድ ታሪካዊ፣ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ ገፅታ አለው፡፡ በዚህ ጽሐፍ ውስጥ ሀይማኖታዊ ገፅታውን እናያለን፡፡ መስቀል የሚለው ቃል በኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል በተዘጋጀው የአማርኛ መዝገበ ቃላት
ላይ ለሦሥት ነገሮች መጠሪያነት ሊያገለግል እንደሚችል ተጽፏል፡፡
1. መስቀል ቀጥ ባለ እንጨት አናት አካባቢ ሌላ አጠር ያለ እንጨት በማጋደም ሁለቱን በማያያዝ የሚዘጋጅ በጥንት እስራኤላዊያንና ሮማውያን ጊዜ ወንጀለኞችን ለመግደል ያገለገለ መስቀያ፣
2. ከብረት፣ እንጨት፣ የሚዘጋጅ ክርስቶስ የተሰቀለበት ምሳሌ እና የክርስትና እምነት ተከታዮች ምልክት፣
3. የክርስቶስ መስቀል ከተቀበረበት ቦታ መገኘትን ምክንያት በማድረግ መስከረም 17 ቀን የሚከበር በዓል፡፡
ከዚህም በላይ በክርስትና ውስጥ ስለ ክርስቶስ ሲባል የምንቀበለውን ፀዋትወ መከራም መስቀል እንለዋለን ዘኢጾረ መስቀለ ሞትየ ኢይክል ይፀመደኒ ማቴ 10፡38 እንዲል ይህም መከራ ውስጣዊም ውጫዊም ነው፡፡ ውስጣዊው ከፍትወት/ምኞት የተነሳ የሚመጣብን ሐልዮ ነው፤ ውጫዊው ከሰይጣን(ከአለም) የሚቀርብልን መከራ ነው፡፡ ከእነዚህም በአኮቴት የምንቀበላቸው እና በመስቀሉ ድል የምንነሳቸው አሉ፡፡
መስቀል ከሥላሴ፣ከእመቤታችን ምስጋና ቀጥሎ ምስጋና የሚቀርብለት ታቦት የተቀረፀለት መልክዕ(ውዳሴ) የተደረሰለት የመማጸኛ ጸሎት (መስተብቁዕ ዘመስቀል) የተጻፈለት በነገረ ድህነት ውስጥ ካሉ ታላላቅ ተስፋዎች፣ምልክቶች አንዱ ነው፡፡ በኢትዪጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በነገረ ድህነት ውስጥ ሁለት ታላላቅ ምስክሮችን(ተስፋዎችን) እንዘክራለን፡፡እነዚህም እመቤታች እና ቅዱስ መስቀል ናቸው፡፡ ሁለቱም በተለያዩ ህብረ አምሳል በብሉይ ኪዳን መጻሕፍት የተገለጡ ናቸው፡፡እመቤታችን ድንግል ማርያም የድህነታችን መሰረት እና መጀመሪያ የሆነች ጌታ ከእርሷ ሥጋን ይነሳ ዘንድ የተገባች ሆና የተገኘች ነችና አንድም የሰውነታችን ባሕርይ የከበረባት የታደሰበት ነች፤ ቅዱስ መስቀሉም ለጠላት ማሳፈሪያ ምልክት ሆኖ የተሰጠን በእመቤታችን ማህፀን የተጀመረው ድህነት የተፈፀመበት በመለኮት ደም የተቀደሰ በክርስቶስ ያገኘነው የትንሣኤ ሰላማችን አርማ ነው፡፡ ለዚህም ነው አባቶች በመስተብቁዕ ዘመስቀል ጸሎታችን በእንተ ዝንቱ አዘዙ መምህራነ ቅዱስ ወንጌል አምሳለ ፈጣሪ ልዑል ንሰግድ ለመስቀል ወለማርያም ድንግል ስለዚህም የቅዱስ ወንጌል መምህራን ለልዑል በሚቀርብ ስግደት አምሳል(በጸጋ) እንድሰግድላቸው አዘውናል::
ከማርያም ድንግልም ከሥጋዋ ሥጋን ነስቷልና ከእርሷም መድኃኒትን አግኝተናልና ለመስቀልም የቃል ደም በላዩ ተንጠባጥቧልና ያሉት በመልክዐ ሥላሴም ላይ ሰላም ለኵልያቲክሙ በሚለው ሥር ተፈጸመ ተስፋ አበው በማርያም ድንግል ወበቀራንዮ ተተክለ መድኃኒት መስቀል የአበው ተስፋ በድንግል ማርያም ተፈጸመ በቀራንዮም መድኃኒት የሆነ መስቀል ተተከለ ተብሎ ተጽፏል ፡፡ ይህም ከላይ የጠቀስነውን ሐሳብ የሚያጠናክርልን ነው፡፡ የሁለቱም(እመቤታችን እና ቅዱስ መስቀል) በአምልኳችን ውስጥ ተደጋግሞ መነሳት ምክንያት ከላይ በጠቀስነው ነገረ ድህነት ውስጥ ካላቸው ሥፍራ የተነሣ ነው፡፡ ክርስቲያን ዘወትር በአዕምሮው ከሚያሰላስለው የክርስቶስ የማዳን ስራ በተጨማሪ በአንገቱ የሚያጠልቀው መስቀል፣በየአብያተ ክርስቲያናቱ ጉልላት ላይ የሚደረጉ መስቀሎች፣ በካህናት እጅ የምንሳለመው መስቀል አለ እነዚህ ሁሉ በተግባርም ይህን ነገረ ድህነትየምንመሰክርባቸው ናቸው፡፡


መስቀል አምላካችን ለሰው ልጅ ፍቅሩን የገለጸበት ታላቁ የፍቅር ት/ቤት ነው፡፡ በምድር ታሪክ ውስጥ ተደርጎ የማያውቅ ወደፊትም የማይደረግ ታላቁ የፍቅር ሥራ በመስቀል ተደርጓል፡፡ እግዚአብሔር ፍጥረታቱ ሲበድሉ ዝም ብሎ የሚያይ አምባገነን ወይም ምንም ማድረግ የማይቻለው ደካማ አይደለምና ወርዶ ተወልዶ ይልቁንም ሞቶ አዳነን እርሱ ግን ፍጥረቶቹን አልተወንም ቸልም አላለንም እርሱን እንደበደልነው መጠን ፈጽመን እንጠፋ ዘንድ በኃጢአታችን አልተቀየመንም፣ወደደን እንጂ፣ጎበኘንም፣ማረን፣ይቅርም አለን፣ከሚገዛንም እጅ አዳነን እንዲል ቅዳሴ ዘዮሐንስ አፈ ወርቅ፡፡
ከሌሎች የእምነት ድርጅቶችም ተለይተን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን (1ቆሮ1፡23) የክርስቶስን ሞት መቀበል የክርስትና የእምነት መሠረት ነው፡፡ ይህም እንዴት የሰውን ሥጋ ይነሳል እንዴትስ ይሞታል ብለው አምላክን ያከበሩ ለሚመስላቸው ሞኝነት ነው፡፡ የሐዲስ ኪዳን ታላቁ ምስጢር ይህ የአምላክ ለፍጥረቶቹ ሲል መሞት ነው፡፡ በሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት ክርስቶስ በሰውም፣ በእርሱም በመላእክትም አንደበት ይሞት ዘንድ እንዳለው ተደጋግሞ ተገልጧል፡፡ ይልቁንም ከትንሳኤው በኋላ እንኳን የሞተው፣የተሰቀለው ተብሎ ተቀጽሎለታል(ማቴ28፡5፣ሮሜ8፡34፣ራዕ1፡18፣ራዕ2፡8) የመምጣቱም ትልቅ ዓላማ ይሞት ዘንድ ነው ይህም በመስቀል ላይ የተፈጸመ ነው፡፡
አባታችን ዮሐንስ አፈ ወርቅ የመዝሙረኛውን ቅዱስ ዳዊት ቃል ሰነፍ በልቡ አምላክ የለም ይላል መዝ13፡1 በተረጎመበት ድርሳኑ እንዲህ ብሏል ክርስቶስን ተሰቅሎ ማየት ያልቻለ በዚህ ስንፍናው ይገለጣል ብሏል ፡፡ ስንፍና የተባለውም ክርሰቶስን እንደተሰቀለ አለማመን ነው (ገላ3፡1)፡፡ በዚህም ቸልተኝነቱ እግዚአብሔርን አያየውም፡፡ የእግዚአብሔርን ኃይል፣ ድል፣ ጠላትን ማሳፈር ማየት፤ማወቅ ለሚፈልጉ ሁሉ መስቀል ታላቁ ምላሽ ነው፡፡የክርስቶስ ሕማም የአምልኳችን መሰረት እና ሁሉ ነገራችን ነው በየቅዳሴው ይህንን ሕማሙን እንሳተፋለን በጥምቀት ከእርሱ ጋር እንሞታለን እንነሳለን የዓመቱ የአምልኮ ጊዜያት በሕማማት ማዕከልነት የተሰደሩ ናቸው ሳምንታችንም የአይሁድን ፍርድ እና ስቅለትን የሚያዘክሩ የአዕፅዋማት ቀኖች ያሉት ነው በቃልም፣በሐሳብም፣በተግባርም መከራውን እናስባለን፡፡
እግዚአብሔር ኃጢአትን፣ ሞትን ፣ በአጠቃላይ ክፉ ነገርን በምድር ላይ እንዲሆን አልፈቀደም አይፈቅድምም፡፡ ለዚህም ትልቁ ማሳያችን ጠላታችንን በመስቀል ጠርቆ ያሳየን ሰላም ነው፡፡ ያለ መስቀል እግዚአብሔርን እና በእኛ ላይ ያለውን አለማ መረዳት አይቻልም፡፡ ክርስቶስ እንደሞተ እና እንደተነሳ እኛም የዚህ ተሳታፊዎች መሆን እንዳለብን የማያስብ ሁሉ ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ እንዳስተማረን ለክርስቶስ ሊሆን አይገባውም(1ዮሐ4፡23) ፡፡ የሰው ልጅ በእግዚአብሔር አርአያ እና አምሳል የተፈጠረ ታላቅ ፍጡር ነው፡፡ ይህም ብቻ አይደለም አምላክ ሰው ሆኖ ያዳነውም ታላቅ ፍጡር ነው፡፡ ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ እርሱ በአምላክነት ያደረገውን(የሆነውን) ሁሉ እኛ በጸጋ እንሆን ዘንድ አድሎናል (ልጅነት፣ንጉሥነት፣ቅዱስነት) ይህ ግን ብቻ አይደለም በስሙ መከራ እንቀበል ዘንድ ጭምር ነው እንጂ ስለ እርሱ መከራ ደግሞ ልትቀበሉ እንጂ በእርሱ ልታምኑ ብቻ አይደለም ፊል1፡29 እንዳለ ሐዋርያው ይህንን ተልዕኳንችን እንፈፅም ዘንድ መስቀል ምልክታችን ነው ክርስቲያን ሁሉ ክርስቶስ መከራ ተቀብሎ ካደለን ማዕድ(ሥጋ ወደሙ) እየተቀበለ መከራው አይንካኝ ይል ዘንድ አይገባም ይልቁንም እንደ ቅዱስ ጳውሎስ ቀኑን ሙሉ ስለአንተ እንገደላለን እንል ዘንድ ይገባናል (ሮሜ8፡36)፡፡ መስቀል እግዚአብሔርን እና ፍጥረትን ሁሉ በመውደዳችን የምንጋፈጠው መከራ ነው፡፡
ከዚህም መከራ እንሸሽ ዘንድ አይገባም በሥጋ መልካም ሆነው ሊታዩ የሚወዱ ሁሉ እንድትገረዙ ግድ አሉአችሁ፥ ነገር ግን ስለ ክርስቶስ መስቀል እንዳይሰደዱ ብቻ ነ ገላ 6፡12 ብሎ እንደወቀሳቸው ሰዎች ከዓለም ጋር ተመሳስለን ሳይሆን ከክርስቶስ ጋር ተባብረን በአኮቴት መስቀላችንን እንቀበል ዘንድ ይቻላል፡፡ ቅዱሳንን ሁሉ አንድ የሚያደርጋቸውም መከራውን በአኮቴት መቀበላቸው ነው እነርሱ እንደ ጌታቸው ከመከራው በኋላ ያለውን ደስታ ናፍቀው ሀይማኖታቸውን ጠብቀዋል፡፡ እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና። ዕብ12፡2 እንዲል ይህ መስቀል ከቤተክርስቲያን አይለይም ለዚህም ስለ ስሜ ስንት መከራ ሊቀበል እንዲያስፈልገው እኔ አመለክተዋለሁና አለው ሐዋ9፡16 ተብሎ የተጠራው ቅዱስ ጳውሎስ ሲመሰክር ስለ አካሉም ማለት ስለ ቤተ ክርስቲያን በሥጋዬ በክርስቶስ መከራ የጐደለውን እፈጽማለሁ። ቆላ1፡24 ይህም ቃል የተነገረው በክርስቶስ ድህነት ህፀፅ ኖሮ ሳይሆን በክርስቶስ ላይ መከራ ያጸና አለም በዚያ አያቆምም የተረፈውን መከራ በቤተክርስቲያኒቷ ያደርሳል ለማለት ነው ለዚህም ሐዋርያው ራሱን ፊት አውራሪ አድርጓል፡፡ እኛም ይህን አሰረ ፍኖት እንከተል ዘንድ ይገባል፡፡
መስቀላችንን በአኮቴት ተቀብለን እንሸከም ዘንድ እንደ ምሳሌ ከተጠቀሱልን ታሪኮች መካከል የፈያታዊ ዘየማን ታሪክ አንደኛው ነው እርሱ በወንጌል እንደተጠቀሰ ስለ አደረግነውም የሚገባንን እንቀበላለንና በእኛስ እውነተኛ ፍርድ ነው፤ ይህ ግን ምንም ክፋት አላደረገም ብሎ ገሠጸው።ሉቃ23፡41 ተብሎ እንደተነገለት እርሱ ምንም እንኳን በኃጢአቱ ምክንያት የመጣበት ቢሆንም በግራው ከተሰቀለው ይልቅ ያለተስፋ መቁረጥ በእምነት መስቀሉን ተቀብሏል በዚህም ጌታን ስለ መሻቱ መድኃኒታችን እውነት እልሃለሁ፥ ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ አለው ሉቃ23፡43 ፡፡ ለ5500 ዘመን ተዘግቶ የነበረውን ገነትም በደመ ማኅተሙ ሲከፍት እርሱን ቀዳሚ አደረገው ይህም አባቶቻችን እንዳስተማሩን በአኮቴት መስቀላችንን ተቀብለን በተከፈተልን ገነት በክብር እንመላለስ ዘንድ የተጻፈልን ነው፡፡
ሌላው ቅዱስ ያሬድ በመስቀል መዝሙር የተናገረው ብከ ንወግዖሙ ለኵሎሙ ፀርነ ወበስምከ ነኀስሮሙ ለእለ ቆሙ ላእሌነ ይቤ ዳዊት በመንፈሰ ትንቢት በእንተ ዝንቱ ዕፀ መስቀል የሚለው ነው በዚህም በመዝ44፡5 ላይ የተጠቀሰውን በአንተ ጠላቶቻችንን እንወጋቸዋለን፥ በስምህም በላያችን የቆሙትን እናዋርዳቸዋለን። ለመስቀል ሰጥቶ ተርጉሟል ጌታችን መከራ እንቀበል ዘንድ መከራ በሚያመጡብን እንፈተን ዘንድ ዝም ብሎ አልተወንም በእርሱ ጠላቶቻችንን ድል እናደርግበት(እንወጋበት) ዘንድ ምልክቱን መስቀሉን ትቶልናል እርሱም ከዲያቢሎስ ፍላፆች ሁሉ የምንድንበት ነው በስምከ ተወከልነ ወበኃይልከ ተማኅፀነ መዓልተ ምስሌነ ወሌሊተ ማዕከሌነ ዝንቱ ትእምርተ መስቀል ቤዛነ በዘቦቱ ንመውዖ ለኵሉ ኃይለ እኩይ እንዲል(መጽሐፈ ዚቅ ዘመስቀል)፡፡ ጌታ በወንገል እንደተናገረው እነዚህ ነገሮች(መከራዎቸን)መቀበል ለቅዱስ ጴጥሮስ እንደ ነገረው በሰው ዘንድ የማይቻል በእግዚአብሔር ዘንድ ግን የሚቻል ነው ማቴ19፡26 ይህም እርሱ በእኛ ካላደረ ወይም ለእርሱ ማደሪያ ራሳችንን ካላመቻቸን ከምስጢራትም ተሳትፈን የእርሱ አካል ካልሆንን በሥጋዊ ጥበብ በእውቀት ብዛት በሥጋችንም በነፍሳችንም (በኀልዮ፣በነቢብ፣በገቢር) የሚመጣብንን ፆር (ፈተና) እንሸከም ዘንድ የማንችለው ነው፡፡ መጋደላችን ከሥጋ እና ከመንፈስ ጋር አይደለምና፡፡
ከንጉሥ ቆስጠንጢኖስ እና ከንግሥት እሌኒ በረከትን ያሳትፈን በኃጢአት ውስጥ የተቀበረውንም መስቀላችንን በተቃጠለ ልብ በክርስቶስ ፍቅር መዓዛ አውጥተን እንሸከም ዘንድ አምላከ ቅዱሳን ይርዳን አሜን፡፡

Thursday, 21 September 2017

ንስሐ ክፍል ኹለት


የንስሐ ደረጃዎች
ንስሐ ለመግባት ማሰብ
ኃጠያትን መተው
ኃጢያትን መጥላት
ንስሐ እንዴት እንገባለን?
በገቢር ለፈጸምናቸው ኃጢአቶቻችና የግድ ንስሐ ያስፈልጋል፡፡ እንደኃጢያት የሚቆጠርና የማይቆጠር ኃልዮም አለ፡፡ እሰርቃለሁ ብሎ ሄዶ ሰው ነቅቶበት ውሻ ጮኾበት አጥር ጸንቶበት ቢመለስ ሌላ ከለከለው እንጂ ያደርገው ነበርና ንስሐ ያስፈልገዋል፡፡ ከመንገድ ሳለ ግን ፈጣሪየ ያየኛል እርሱ ይፈርድብኛል ብሎ ቢመለስ እንደኃጢያት አይቆጠርበትም ነገር ግን ኃጢያት ጠልቶ አልተመለሰምና ፍጹም አይደለም፡፡

ኑዛዜ
ኑዛዜ አራት መሠረታዊ ነጥቦችን ያጠቃልላል፡፡  አንደኛው ኃጢያትን ለራስ ሕሊና መናዘዝ ኹለተኛው በጸሎት በደልን ለእግዚአብሔር መናዘዝ ሦስተኛ በደልን ለካህን መናዘዝ አራተኛው ለበደሉት ሰው መናዘዝ ናቸው፡፡
ኃጢያትን ለራስ ሕሊና መናዘዝ
ኃጢያትን በመናዘዝ ውስጥ የመጀመርያው ደረጃ ኃጢያትን ለራስ ሕሊና መናዘዝ ነው፡፡ የሰው ልጅን እግዚአብሔር ሲፈጥረው ማመዛዘን የሚችልበትን አእምሮ ሰጥቶ ፈጥሮታል ስለዚህም ይህ ሕሊና ለሰው ልጅ ሲበድል ወቃሹ እውነተኛ ዳኛ ነው፡፡ ሕግ ተሰርቶልን ኦሪትንና ወንጌልን ሳናውቅ በፊት ክፉውን ከበጎ እንድንለይበት እግዚአብሔር በድንቅ አፈጣጠሩ ፈጥሮልናል፡፡ ሰዎች ታዲያ ክፉ ሲያደርጉ ይወቅሳቸው ዘንድ በጎ ሲሰሩ ያበረታቸው ዘንድ፡፡ በጎ ሕሊና ያለው ሰው ኃጢያት በሰራ ጊዜ ኃጠያቱን እንደሰራ ያምናል፡፡ ለራሱም ኃጢያቱን አምኖ ይናዘዛል በድያለኹ ይላል ይህም የንስሐ የመጀመርያው ደረጃ ነው፡፡ታላቁ መቃርስ እንዳለን ኃጢያትን ለራስ መናዘዝ እግዚአብሔር ሳይፈርድብን አስቀድመን ራሳችን ላይ መፍረድ ነው፡፡ በቅዱስ ወንጌል ተጽፎ የምናገኘው የጠፋው ልጅ ወደ ልቡ ተመልሶ እንዳለ ‹‹ እንጀራ የሚተርፋቸው የአባቴ ሙያተኞች ስንት ናቸው እኔ ግን ከዚህ በረኃብ እጠፋለሁ፡፡ ተነስቼም ወደ አባቴ እሄዳለሁና፡፡ አባቴ ሆይ በሰማይና በምድር በደልኹ ወደ ፊትም ልጅ እባል ዘንድ አይገባኝም ከሞያተኞትህ እንዳንዱ አድርገኝ እለዋለኹ›› ብሎ ኃጢያትን በቅድሚያ ለራስ እንደተናዘዘ እንዲሁ እኛም ከኹሉ በፊት ኃጢያታችንን በማመን እንናዘዝ ዘንድ ይገባል፡፡ (ሉቃ 15፥17-19)
        በጸሎት በደልን ለእግዚአብሔር መናዘዝ
ኃጢያት መስራት በመጀመርያ ደረጃ እግዚአብሔርን መበደል(ማሳዘን) ስለሆነ ለእግዚአብሔር መናዘዝ ይገባናል፡፡ ቅዱስ ዳዊት በኃጢያት በወደቀ ጊዜ እንዲህ አለ ‹‹ አንተን ብቻ በደልኩ በፊትህም ክፉን አደረኹ››(መዝ 50፥4) ነቢዩ ዳንኤልም በጸሎቱ እንዲህ አለ ‹‹ አምላክ ሆይ ኃጢያትን ሰርተናልና በድለንማል ክፍትም አድርገናል አምጸናል ከትእዛዝህና ከፍርድህም ፈቀቅ ብለናል፡፡›› እንዳለ (ት. ዳን 9፥5) እንዲሁ እኛም የእነዚህን ታላላቅ አባቶች ጸሎት ጸሎታችን እናደርግ ዘንድ ይገባናል፡፡
          በደልን ለካህን መናዘዝ
የእግዚአብሔር እንደራሴ በሆነ አገልጋይ ፊት መናዘዝ በእግዚአብሔር ፊት መናዘዝ ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ እንደምናነበው ኢያሱ አካንን ‹‹ልጄ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ክብርን ስጥ ለእርሱም ተናዘዝ ያደረከውንም ንገረኝ አትሸሽገኝ›› (ኢያ 7፥19) እንዲሁም ወደ መጥምቁ ዮሐንስ የመጡ ኹሉ ኃጢያታቸውን እየተናዘዙ የንስሐ ጥምቀት ተጠምቀዋል፡፡ (ማቴ 3፥6) በሐዋርያት አገልግሎትም ያመኑ ብዙ ሰዎች ኃጢያታቸውን ይናዘዙ ነበር (ሐዋ 19፥18)
ካህኑ ፊት ኃጢያትን መናዘዝ አንደኛ በካህኑ ፊት የተናዘዘውን ኃጢያት ዳግም እንዳይሰራ መንፈሳዊ ብርታት ይሆነዋል፡፡ ኹለት ፍጹም የኃጢያት ሥርየት የሚገኝበትን ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ለመቀበል የሚያስችል ፍቃድ ያገኛል፡፡
ኃጢያትን ለበደሉት ሰው መናዘዝ
ይህን ማድረግ የራስብ ልብ ለማስተካከልና ለማረጋጋት ከተበደለው ሰው ጋርም እርቅን ለመመሥረት ይረዳናል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹በመሰዊያው ፊት መባህን አስቀምጠህ ሂድ አስቀድመህ ከወንድምህ ታረቅ ከዛ በኋላ መስዋዕትን ታቀርባለህ›› እንዳለን (ማቴ 5፥24) አስቀድመን ወደ በደልነው ሰው በመሄድ በድያለሁና ይቅር በለኝ ማለት ይገባል፡፡ አባቶቻችን ሳል ይዞ ስርቆት ቂም ይዞ ጸሎት አስሰምርም እንዲሉ በቅዱስ ቃሉ መሠረት ያስቀየምነውን ይቅር ማለት ይገባናል፡፡
የንስሐ መሰናክሎች
ሰዎች ንስሐ እንዳይገቡ የሚከተሉት ምክንያቶች መሰናክል ያሆኑባቸዋል፡፡
ኃጢአትን አለማመን (ራስን በማጽደቅ ኃጢያተኛ እንዳልሆነ ማሰብ)
የራስን ኃጢያት ከሰዎች ጋር በማነጻጸር የተሻሉ እንደሆኑ ማሰብ
በማዘግየት ለንስሐ የተዘጋጀውን ልቡና መለወጥ የንስሐ እድልንም ማጥፋት
ተስፋ መቁረጥ
እነዚህ መሰናክሎች ዘወትር ንስሐ እንዳንገባ እንድንዘናጋ ገና ነኝ ጊዜ አለኝ እንድል ያደርጉናል፡፡ በዚህም ምክንያት ብዙዎች ከንስሐ ራሳቸውን ያርቃሉ፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ግን በመልእክቱ “እውነትን በዓመፃ በሚከለክሉ ሰዎች በኃጢአተኝነታቸውና በዓመፃቸው ሁሉ ላይ የእግዚአብሔር ቍጣ ከሰማይ ይገለጣል፡፡” (ሮሜ 1፡18) እንዳለን የእግዚአብሔር ቁጣ ከመገለጡ በፊት ራስን ለንስሐ ማዘጋጀት ይገባል፡፡ እንዲሁ“ወይስ የእግዚአብሔር ቸርነት ወደ ንስሐ እንዲመራህ ሳታውቅ የቸርነቱንና የመቻሉን የትዕግሥቱንም ባለጠግነት ትንቃለህን? ነገር ግን እንደ ጥንካሬህና ንስሐ እንደማይገባ ልብህ የእግዚአብሔር ቅን ፍርድ በሚገለጥበት በቍጣ ቀን ቍጣን በራስህ ላይ ታከማቻለህ።” (ሮሜ 2፡5) የእግዚአብሔር ቸርነት ወደ ንስሐ የሚመራ እንጂ በቸልተኝነት የእግዚአብሔር ቁጣ በራሳችን ላይ እንዳይገለጥ ራስን ለንስሐ ማዘጋጀት ይገባል፡፡

ይቀጥላል በክፍል ሦስት በንስሐ የሚገኙ ለውጦች እንዲሁም ተነሳሒው በኃጢያት ዳግም እንዳይሸነፍ ሊያደርጋቸው የሚገባቸውን ጥንቃቄዎች እንመለከታለን
ይቆየን
ስብሐት ለእግዚአብሔር

Sunday, 17 September 2017

ሰማዕትነት

ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ገጽ 871-872 በሰዋሰዋዊ ፤ቀጥተኛ ትርጉሙ ‹ስምዐ› ከሚለው የግእዝ ግስ የተገኘ ሲሆን መመስከር፣ምስክር መሆን፣ያዩትን የሰሙትን መንገር፣አየሁ ሰማሁ ማለት፣ሰማዒ የሚሰማ የሚቀበል ሰሚ መስካሪ ምስክር ሰማዕታት የሚመሰከር /ምስካሮች ማለት ነው፡፡ ሰማዒ ለአንድ ሲሆን ሰማዕታት ለብዙ ነው፤ ሰማዕታት የብዙ ብዙ አንዱን ቅዱስ ‹ሰማዕት› ማለት በአማርኛ ነው፡፡ የእንግልዝኛው ’’Martyt” ከግሪኩ “Martyria“  Martus” የመጣ  ሲሆን በፍቺውም ምስክር “A withess ማለት ነው፡፡

• ምስክርነት

ሰማዕትነት /Martyrdom/ በጥንት ትርጉሙ በብዙኀን በተሰበሰቡበት በአደባባይ በገሃድ ስለሚሰጠው ምስክርነት የቅርብ ዕውቀት የዐይን ምስክር እንዲሉ/ ያለውን ሰው ያመለክት ነበር፡፡ ‹‹አማን አማን እብለከ ከመ በዘናአምር ንነግር ወበዘርኢነ ሰማዕተ ንከውን ወስምዐነሰ ተአብዩነ ነሢአ›› (ዮሐ.3÷11) ‹‹የምናውቀውን እንድንናገር የአየነውን እንድንመሰክር እውነት እውነት እልሃለሁ ግን ምስክርነታችንን አትቀበሉትም›› ይላል፡፡

• ራስን መስዋዕት ማድረግ

በሌላ በኩል በኋላ ዘመን ሰማዕታት የሚለው ቃል ሃይማኖታዊ ትርጉሙ በዋነኛነት ስለ እግዚአብሔርና ስለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በአጠቃላይ ስለ ሃይማኖቱ በእውነትና በእምነት በመመስከሩ ጀርባውን ለግርፋት፣ሰውነቱን ለእሳት፣እግሩን ለሰንሰለት፣ዓይኑን ለፍሰት፣አንገቱን ለስለት አሰልፎ የሰጠ፣በደንጊያ ተወግሮ የሞቱ፣በመንኮራኩር ተፈጭቶ ለዐረፉ ቅዱስ አባት ለዐረፈች ቅድስት  እናት የሚሰጥ ሆኗል፡፡

‹አምስተኛውም ማኅተም በተፈታ ጊዜ ስለ እግዝአብሔር ቃልና ስለጠበቁት ምስክር የታረዱት የሰዎች ንፍሳት ከመሠዊያው በታች አየሁ፡፡ በታላቅ ድምጽም እየጮኹ፡-ቅዱሳኑ እውነታንና ጌታ ሆይ እስከመቼ ድረስ አትፈርድም ደማችንንስ በምድር በሚኖሩት ላይ እስከመቼ አትበቀልም? አሉ፡፡ ለእያንዳንዳቸውም ነጭ ልብስ ተሰጣቸው፡፡ እንደ እነርሱም ደግሞ ይገደሉ ዘንድ ያላቸው የባሪያዎች ባልንጀራዎቻቸውና የወንድሞቻቸው ቁጥር እኪፈጸም ድረስ ገና ጥቂት ዘመን እንዲያርፉ ተባለላቸው› ይላል፡፡ (ራዕ.6÷9-11) ሰማዕታት ስለክርስቶስ ብለው አንገታቸውን ለሰይፍ ደረታቸውን ለጦር የሰጡ፤ከእሳት የተጣሉ፤ከባሕር የተወረወሩ፤ለአውሬ የተሰጡ፤በበረሃና በዱር የተሰደዱ፤የተሰደቡ፤የተራቡ የተጠሙ የታረዙ የተቸገሩ በሙሉ ሰማዕት ይባላሉ፡፡ ኤፌ.13÷20  ሐዋርያው ቅዱስ ጰውሎስ ‹መጋደላችን ከደምና ከሥጋ ጋር አይደለምና ከአለቆችና ከሥልጣናት ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዥዎች  ጋር በሰማያዊ ሥፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳዊያን ሠራዊት ጋር ነው እንጂ› ሲል ስለ ተጋድሎ ገልጾታል በሌላም ክፍል ስለራሱ መንፈሳዊ ተጋድሎ ሲናገር እንዲህ አለ በድካም አብዝቼ፣በመገረፍ አብዝቼ በመታሰር አትርፌ፣በመሞት ብዙ ጊዜ ሆንኩ፡፡ አይሁድ አንድ ሲጎድል አርባ ግርፋት ገረፉኝ፡፡ ሦስት ጊዜ በበትር ተመታሁ፡ አንድ ጊዜ በድንጋይ ተወገርሁ፡፡ መርከቤ ሦስት ጊዜ ተሰበረ ሌሊትና ቀን በባህር ውስጥ ኖርሁ፡፡ ብዙ  ጊዜ በመንገድ ሄድሁ፡፡ በወንዝ ፍርሃት፣በወንበዴዎች ፍርሃት በወገኔ በኩል ፍርሃት፣በሕዝብ በኩል ፍርሃት፣በምድረ በዳ ፍርሃት፣በባሕር ፍርሃት፣በውሸተኞች ወንድሞች በኩል ፍርሃት ነበረብኝ፡፡ በድካምና በረት፣ብዙ ጊዜ እንቅልፍ በማጣት በረሃብና በጥም ብዙ ጊዜ በመጾም በብርድና በራቁትነት ነበርሁ››(2ቆሮ.11÷23-28) ይህን ሁሉ መከራ ከተቀበለ በኋላ ድል አድራጊነቱን ሲገልጽ ‹‹ሰናየ ገድለ ተጋደልኩ በድርየኒ ፈጸምኩ ወሃይማኖትየኒ አቀብኩ-መልካሙን ገድል ተጋድያለሁ ሩጫዬንም ጨርሻለሁ ሃይማኖቴንም ጠብቂያለሁ›› አለ፡፡ (2ኛ ጢሞ 4፥7)ቅዱስ ጳውሎስ ለደቀ መዝሙሩ ጢሞቴዎስ ‹‹የተጠራህለትን የዘለዓለም ሕይወት ትቀበል ዘንድ መልካሙን የሃይማኖት ገድል ተጋደል፡፡›› ብሎታል

ነገር ግን የሰማዕትነቱ ደረጃና ዋጋው ‹‹ኮከብ እምኮከብ ይኄይስ›› እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ አንዱ ከአንዱ ይበላለጣል፡፡እንደነ ቅዱስ ጊዮርጊስ ፤ቅዱስ መርቆርዮስ፤ሠለስቱ ደቂቅ ያሉት ሰማዕትነታችው ታላቅና ባለ100ፍሬ ያለባት ናት፡፡እንደቤተ ክርስቲያን ታሪክ ዘመነ ሰማዕታት የሚባለው ከ160-312 ሲሆን ክርስቲያኖች በጨካኝ ነገስታት እየተንገላቱና እየተሰደዱ ይልቁንም እየተሰየፉ እየተቃጠሉ መከራ ያሳለፉበት ጊዜ ነው፡፡ይህንን ያደረጉ የሮም አበይት ጨካኝ ነገስታት አስር ናቸው፡፡ኔሮን(ከ54-68 ዓ/ም)፤ዲሚቲያን (81-96)፤ትራጃን(98-117)፤ማርቆስ አውሬሊዮስ(161-180)፤ባሌርያን(253-259)፤አውሌሪያን(270-275)፤ሴፕቲመስ(193-211)፤ማክስሚያኖስ(235-238)፤ዳክዮስ(249-251)፤ዲዮቅልጥያኖስ(284-305)  ናቸው፡፡ከነዚህም በኋላ እስከ ሐሳዊ መስህ መነሳት ድረስ የሚነሱ የክርስትና ጠላቶች ያጠቃልላል፡፡ሰማዕታቱም እስከ ዓለም ፍጻሜ ነሳሉ፡፡

እንደ ቤተ ክርስቲያን በሐዲስ ኪዳን የመጀመሪያው ሰማዕት ዲያቆኑ ቅዱስ እስጢፋኖስ ነው፡፡ከርሱም በኋላ ከቅዱስ ዮሐንስ በስተቀር ሐዋርያት ሁሉ ሰማዕትነትን ተቀብለዋል፡፡ሊቀ ሰማዕታት ደግሞ ተብሎ የተሸመና ማዕረግ የተሰጠው ቅዱስ ጊዮርጊስ ነው፡፡ቤተ ክርስቲያን እነርሱን አብነት አድርገው ሰማዕት ለሚሆኑ ሁሉ የቅድስና ክብር ትሰጣለች፡፡


                     
       

የሰማዕታት ክብር

ሰማዕታትን ማክበር ክርስቶስን ማክበር ነው፤የክርስቶስ ሕማምና ሞት የገባው የሰማዕታቱ ሕማም ይገባዋል፡፡ክርስቶስም ስለርሱ ስለሞቱ ታላቅ ክብርና ቅድስና አክሊልን ይሰጣቸዋል፡፡ይህንንም ለመረዳት ሰማዕታቱን በኦሪት መስዋዕት መስለን እንመልከት፡፡

በኦሪት መስዋዕተ ዕለት(የዕለት መስዋዕት) የሚባል ነበር ጠዋት አንድ ማታ አንድ ይሰዋል፡፡የሚቀርቡትም እንስሳቶቹም አንደኛ በግ ኹለተኛ ፍየል ሦስተኛ ወጥይፈንና ጊደሮች አራተኛ ርግብና ዋኖስ ከዚያ ካለፈ እህል ይቀርባል፡፡ በግ የተባሉ ጻድቃን ሰማዕታት ናቸው፡፡ ጌታችንም ሲናገር ‹‹እንደ በግ በተኩላዎች መካከል እልካችኋለሁ›› ማቴ10፤16  በግን ተኩላ እንዲገድላት ሰማዕታት እንደተኩላ በሆኑ ክፉ ነገስታት የመታረዳቸው ምሳሌ ነው፡፡ቅዱስ ጳውሎስም የተሰዉትን እንስሳት በሰማዕታት ሲመስላቸው ‹‹ዕለት ዕለት እንደሚታረዱ በጎች ተቆጠርን›› የሚለውን የዳዊትን ቃል አንስቶ ሮሜ8፤35- ‹‹ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል መከራ ነው ኃዘን ነው ›› ይልና ‹‹ስለአንተ ዘወትር ይገድሉናል እንደሚታረዱ በጎች ተቆጠርን ነገር ግን በወደደን በእርሱ ሁሉን ድል እንነሳለን››በማለት ተናግሯል፡፡

የኦሪት መስዋዕት ጊዜያዊ ኃጠአትን ያስተሰርዩ ነበር ሌላው የነበረውም የደኅንነት መስዋዕት የሚባለው ነው፡፡ይህም የክርስቶስ ምሳሌነት አለው፡፡በአይሁድ አቶንመንት ይሉታል (የማስተሰርያ ቀን ማለት ነው) ፋሲካን ባከበሩ በ7ኛው ወር በ10ኛው ቀን ያከብሩታል የሚውለው በጾም ጊዜ ነው በዚያ ቀን ሁለት አውራ ፍየሎች ይቀርባሉ አንዱ ምድረ በዳ ይለቀቃል አንዱ ይሰዋል በመጨረሻ የደኅንነት መስዋዕት ሁለት በጎች ይቀርባሉ፡፡ፍየሉና በጎቹ የሚቀርቡት ከሕዝቡ ነው አንዱ በግ ከሊቀ ካህናቱx ይቀርባል፡፡የደኅንነት መስዋዕት የተባለው ክርስቶስ ነው በማንም የማተካ አማናዊ ድኅነትን የሚያሰጥ ነው፡፡በሕዝቡ ዘንድ የቀረቡት መስዋዕቶች የሰማዕታት ምሳሌ ናቸው አማናዊውን በግ ኢየሱስ ክርስቶስን መስለው የተገኙ እነ ቅ.ጊዮስርጊስ፤እስጢፋኖስ፤ሕጻኑ ቂርቆስ፤ቅድስት አርሴማ......... የመሳሰሉት ናቸው፡፡እነዚያን መስዋዕቶች አንዱ የደኅንነት መስዋዕት ፍጹም እንደሚያደርጋቸው የሰማዕታትም አክሊላቸው ክርስቶስ ነው ‹‹አክሊሎሙ ለሰማዕት-ለሰማእታት አክሊላቸው ነው›› እንዳለ ቅዱስ ያሬድ ሰማዕታት በክርስቶስ ይከብራሉ፡፡

ሌላው በኦሪት ዘሌዋውያን ከምዕራፍ ሰባት እስከ ዘጠኝ ስናነብ አብዛኛው የኃጢአት መስዋዕት ፍየል ነው፡፡ፍየል የኃጥአን ምሳሌ ነው ፤ማንም ኃጥዕ የነበረ ሰው ስለክርስቶስ አምኖ ሰማዕት ቢሆን ፍጹም ሰማዕት ይባላል፡፡አንዳንዶች ወንበዴ የነበረ፤ዘማዊ የነበረ፤ሱሰኛ የነበረ እንዴት ሰማዕት ሆነ እንዴትስ ይጸድቃል ብለው ይጠራጠራሉ፡፡ለምሳሌ፡- በኦሪቱ ለደኅንነት መስዋዕት ሁለት አውራ ፍየል ይቀርባል አንዱ በበረሃ ይለቀቃል አንዱ ይሰዋል፡፡ምሳሌነታቸውም የክርስቶስ ነው አንዱ ምድረ በዳ መለቀቁ ክርስቶስ ምድረ በዳ ወደተባለች ሲዖል ወርዶ ይህን ሊቃውንቱ ሲመስሉት ምድረ በዳ የተለቀቀው ፍየል ከጌታችን በግራ የተሰቀለው የፈያታዊ ዘጸጋ ፤የተሰዋው ደግሞ የፈያታዊ ዘየማን ይሉታል፡፡ፈያታዊ ዘየማን ምንም ቀድሞ ወንበዴ ቢሆን ለአማናዊው በግ ለክርስቶስ ኃጠአቱን ተናዞ አጠገቡ ያለውን ወንበዴ ገስጾ ምስክርነቱን(ሰማዕትነቱን) አሳይቷል፡፡

በተጨማሪም በኦሪቱ የታዘዘው የእንስሳውን ብልቶች ተቆራርጠው ሲሰዉ የእንስሳውን የውስጥ ብልት(አንጀቱን ጨጓራውን) በደንብ አጥባችሁ ለመስዋዕት አቅርቡ የሚል ነው፡፡ይህንንም የሚያደርግ ሊቀ ካህኑ ነው ፡፡ለጊዜው የእንስሳ ውስጣዊ የሆኑ አካላት አብልጠው መታጠብ ስለሚያስፈልጋቸው ነው፡፡ፍጻሜው ግን ሊቀ ካህን የተባለ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ለመስዋዕት የታጠቡ እንስሳቶቹ(ብልቶች) ሰማዕታት ናቸው ፡፡ቀድመው ምንም ኃጥዕ ቢሆኑ በሊቀካህኑ በኢየሱስ ክርስቶስ ሰማዕትነታቸውን አይቶ ያነጻቸዋል፡፡ከዚህም ባፈ ደግሞ ለምሳሌ ቀድሞ ኢ አማኒ የነበረ ሰው ክርስቲያኖች ሰማዕትነትን ሲቀበሉ አይቶ ቢያምንና እርሱም ሰማዕትነትን ቢቀበል እግዚአብሔር ሰማዕትነቱን እንደተጠመቀና እንደቆረበ ያደርገዋል፡፡

በዘሌ5፤14 እንደሰፈረው የኦሪቱን አውራ በጎች ለመስዋዕትነት ይቀርባሉ በተቀደሰ ነገር ላይ የበደሉ ሰዎች ምንም አማራጭ(ፍየል፤ዌፌን፤ጊደር እህል) የሌለው አውራ በግ ብቻ ያቀርባሉ፡፡የሚገዛው ደግሞ ቤተ መቅደስ ነው፡፡ተመኑንም የሚያወጣው ደግሞ ሊቀ ካህናቱ ሲሆን ገዢው ሰው የዋጋውን አንድ አምስተኛ ይጨምርበትና ለመስዋእትይቀርባል፡፡ምሳሌነቱም አውራ በግ የተባሉ እነ ቅዱስ ጊዮርጊስ ፤መርቆርዮስ ናቸው፡፡ሊቀ ካህኑ ተመኑን እንደሚያወጣ የሰማዕታትንም ክብርና ዋጋ የሚያወጣና የሚያድል አንድ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ማንም ፍጠሩ የሰማዕታትን ነገር አቅልሎ በይመስለኝ ሊሰፍረው አይችልም፡፡ይልቁንም እግዜር ባወቀ ባለ 30 ባለ60 ባለ100 ብሎ ቅድስናን ይሰጣቸዋል፡፡ በኦሪት ዕለት ዕለት እንስሳቱ እንደሚሰዉ(የዕለት መስዋዕት) ሰማዕታትም ቅዱስ ዳዊት  ‹‹ዕለት ዕለት እንደሚታረዱ በጎች ተቆጠርን›› እንዳለው ሰማዕታት እስከ ዓለም ፍጻሜ እየተነሱ ይኖራሉ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም ቅድስናቸውን በስንክሳር በገድል በተአምር አስፍራ ዕለት ዕለት ታስባቸዋለች፡፡ 

 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር