ማቴ
5÷13 ‹‹እናንተ የምድር ጨው ናችሁ፡፡ ጨው አልጫ ቢሆን ግን በምን ይጣፍጣል? ወደ ውጪ ተጥሎ በእግር ከመረገጥ በቀር ወደፊት ለምንም አይጠቅምም››
በዚህ ክፍል ውስጥ በጨው የተመሰሉ ክርስቲያኖችና ወንጌላውያን ናቸው፡፡ ክርስቶስ ተከታዮቹን ለምን በጨው መሰላቸው?
ጨው
ምግብን ያጣፍጣል / ኢዮብ 6÷6/ ክርስቲያኖችም በኃጢአት አልጫ የሆነውን ኅብረተሰብ ያጣፍጣሉ፡፡
አንድም፡- ጨው ቁስልን ያደርቃል፤ ክርስቲያኖችም በኃጢአት የቆሰለውን ዓለም ይፈውሳሉና /ኢሳ 1÷5/
አንድም፡- ጨው በጥንት ዘመን ገንዘብ ሆኖ ያገለግል ነበር፡፡ ክርስቲያኖችም የእግዚአብሔር ገንዘቦች ናቸውና /2ኛ ቆሮ 12÷14/
አንድም፡-ጨው በብሉይ ኪዳን ዘመን ለመሥዋዕት ይጨመር ነበር /ዘሌ 2÷13/ ክርስቲያኖችም መሥዋዕት እስከመሆን ድረስ ስለ ክርስቶስ ይመሰክራሉ /ፊሊጵ 1÷29/
አንድም፡- ጨው በጠቅላላው ፍቅርን ያመለክታል /ማር 9÷50/፡፡ ጨው አልጫ ቢሆን የሚሰጠው ጥቅም የለም፡፡ ክርስቲያኖችም በክርስቶስ ሕግ ካልተመሩ ከንቱ ይሆናሉ፡፡
አንድም፡- ጨው በሌላ መንገድ የቅጣት፣ የፍርድና የመርገም ምልክት ይሆናል፡፡ /ዘፍ 19÷26፣ መሳ 9÷45/፡፡እውነተኛ ክርሰቲያናዊ ሕይወት የሌላቸው ክርስቲያኖች የመርገምና የቅጣት ምልክቶች ናቸው/ዕብ 6÷4-6/
ማቴ
5÷14-16 ‹‹እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ፡፡ በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሰወር አይቻላትም፡፡ መብራትንም አብርተው ከእንቅብ በታች አይደለም እንጂ በመቅረዙ ላይ ያኖሩታል፡፡ መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን ያከብሩ ዘንድ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ፡፡››
እውነተኛ የዓለም ብርሃን ክርስቶስ ነው፡፡ /ዮሐ 8÷12/
እውነተኛ ተከታዮቹም የዓለም ብርሃን ተብለዋል፡፡ ብርሃንነታቸው ግን ከራሳቸው ባሕርይ ሳይሆን ከክርስቶስ ብርሃን የተቀጣጠለ ነው፡፡ /ኤፌ 5÷8)
የክርስቲያኖች ብርሃነት፡-
ክርስቶስን ሲከተሉ ነው፡፡ /ዮሐ 12÷35-36/
አንድም፡- ቃሉን ሲያስተምሩ ነው፡፡ /ፊሊጵ 2÷15/
አንድም ፡-ላላመኑት መድኃኒት ለመሆን ነው፡፡ /ኢሳ 49÷6፤ የሐዋ 13÷47/
በተራራ ላይ የተሰራች ከተማ እንዲሁም በከፍተኛ መቅረዝ ላይ የተሰቀለ መብራት ከሩቅ ይታያና ሊሰወሩት አይችሉም፡፡ ክርስቲያኖችም በመልካም ስራቸው በሁሉ ዘንድ መታየትና መታወቅ ለአምላካቸውም መመስገን ምክንያት ሊሆኑ ይገባቸዋል፡፡