Saturday, 18 February 2017

ጸሎተ ፍትሐት ለምን?

ጸሎተ ፍትሐት የሚደረግባቸው ምክንያቶች

  1. እግዚአብሔር ቸርና መሐሪ ስለሆነ


ከዚህ ዓለም በሞት ለተለዩ(ላረፉ) ወገኖቻችን ጸሎት የሚደረግበት አንዱ ምክንያት እግዚአብሔር በምሕረቱ እንዲጎበኛቸው ከሰው ስህተት አይጠፋምና በደላቸውን ይቅር ብሎ በብሩህ  ገጽ እንዲቀበላቸው የእርሱ ምሕረት ደጅ ለመጽናት ነው፡፡ በመጀመርያ እነዚህ ያረፉ ወገኖቻችን የቤተ ክርስቲያን ሕያዋን አካላት እንደመሆናቸው ለእነዚህ በአንድ መንፈስ አንድ አካላት ለሆንን ወገኖቻችን መጸለይና ምሕረት መለመን የሚገባ እንጂ የማይገባ አይደለም፡፡ የማይገባ የሚሆነው ይህን መቃወም ነው፡፡

በመጽሐፍ ቅዱስ ለራሳቸው መልካም ነገርን ከለመኑ ሰዎች በበለጠ የተመሰገኑት ስለሌላው ሰው ስለወገናቸው ሲሉ እግዚአብሔርን የለመኑት ናቸው፡፡ ሙሴን በእጅጉ ያስመሰገነው እግዚአብሔር ‹‹አሁንም ቁጣዬ እንዲቃጠልባቸው እንዳጠፋቸውም ተወኝ አንተንም ለታላቅ ሕዝብ አደርግሃለሁ›› ባለው ጊዜ ‹‹ አሁን ይህን ኃጢያት ይቅር በላቸው ያለበዚያ ግን ከጸፍከው መጻሕፍህ እባክህ ደምስሰኝ›› በማለት ከራሱ ክብርና ደኅንነት ይልቅ የሕዝብ ደኅንነትና ምሕረት በማስበለጡና በማስቀደሙ ነበር፡፡ ዘጸ 32፥10-32 ታዲያ እንዲህ ‹‹ሕዝቡ ይቅር በላቸው አለዚያ ግን ከሕይወት መጽሐፍ ደምስሰኝ›› እስኪል ደርሶ ለሌሎች ምሕረትን ከለመነ እንደ እርሱ ባናደርግ እንኳ በዓቅማችን ማራቸው ብሎ መጸለይ ኃጢአትነቱንና ጥፋተኝነቱ ምኑ ላይ ነው?

ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ወገኖቹ ስለእስራኤላዊያን በክርስቶስ አለማመንና ከድኅነት ውጭ ስለመሆናቸው ያዝንና ይጨነቅ ነበር፡፡ ‹‹ብዙ ኀዘን የማያቋርጥም ጭንቀት በውስጤ አለብኝ ስል በክርስቶስ ሆኜ እውነት እናገራለሁ አልዋሽምም ሕሊናዬም በመንፈስ ቅዱስ ይመሰክርልኛል፡፡ በሥጋ ዘመዶቼ ስለሆኑ ስለ ወንድሞ ከክርስቶስ ተለይቼ እኔ ራሴ የተረገምኩ እንድሆን እጸልይ ነበርና›› ብሉ ሐዋርያው እንደገለጸው፡፡(ሮሜ. 9፥1-3) ይህን ያህል ስለሌሎች መዳን ‹‹እኔ የተረገምኩ ልሁን›› እስከማለት ደርሰው ከጸለዩና ከተጨነቁ እኛ ስለሌሎች መዳን ማሰብና መጸለይ የለብንምን?

እነዚህ ከላይ በምሳሌነት ያነሳናቸው ቅዱሳን በሕይወት ስላሉ ሰዎች መጸለያቸውን ነው፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ምንም እንኳን ሙታን በሥጋ ቢለዩንም ሁሌም ቢሆን የቤተ ክርስቲያንን ሕብረት ውስጥ ያሉና የሚኖሩ መሆናቸውን ታስተምራለች፡፡ እግዚአብሔር በዚህ ዓለም በሕይወት ከሚኖሩና ከማይኖሩ ሰዎች ጋር ግንኙነት አለው እንጂ በምድር ከዚህ በመለየታቸው ምክንያት ከቤተ ክርስቲያን ሕብረት ተለይተዋል ማለት አይደለም፡፡ የእግዚአብሔርም ቸርነት በሙታንም በሕያዋንም ላይ እንደሆነ መጽሐፍ ሲመሰክር ‹‹ቸርነትህ በሕያዋንና በሙታን ላይ አልተወምና›› ይላል(ሩት 2፥20)

የያዕቆብ የበኩር ልጅ የነበረው ሮቤል ወደ አባቱ አልጋ ወጥቶ እንደነበር መጽሐፍቅዱስ ይናገራል፡፡ እንዲህ ብሎ‹‹እስራኤል በዚህም አገር በተቀመጠ ጊዜ ሮቤል ሄደ የአባቱንም ቁባት ባላን ተገናኛት እስራኤልም ሰማ›› ዘፍ 35፥22 በሕይወቱ መጨረሻ ላይ አባቱ ያዕቆብ ልጆቹን በተመለከተ እያንዳንደቸውን ግብራቸውንና ወደፊት የሚያገኛቸውን ሲናገር ‹‹…..እንደውሃ የምትዋልል ነህ አለቅነት ለአንተ አይሁን ወደ አባትህ መኝታ ወጥተሃልና አረከስኸውም ወደ አልጋዬ ወጣህ›› ዘፍ 49፥3-4

ከዚህም የተነሳ ሮቤል ከሞተ ቢያንስ ከመቶ ዓመት በላይ ከሆነው በኋላ እስራኤልያዊያን ከግብጽ ሲወጡ የአበውን ዓጽምም አብረው ይዘው ስለነበር በኃጢያቱ ምክንያት ከሌሌ,ሎቹ አበው ተለይቶ የሮቤል አጽም ጠቁሮ ነበር፡፡ለዚህም ነው ሙሴ ከሞተ ብዙ ጊዜ ብሆነውም እንዲህ ብሎ ጸለየለት  ‹‹ወዳጄ ሮቤል በሕይወት ይኑርልኝ አይሙትብኝ..(ዘዳ. 33፥6)

  1. የቤተ ክርስቲያን ባሕርይዋንና ማንነቷን የሚገልጥ ስለሆነ


ቤተ ክርስቲያን ቀደም ሲልም እንደገለጽነው በአካለ ሥጋ ያሉ በአካለ ሥጋ የሌሉ ሰዎች መላእክት ቅዱሳን ሁሉም በሕብረትና በአንድነት እግዚአብሔርን የምናከብርባትና የምናመሰግንባት የምስጋና ግምጃ ቤት ናት፡፡ ይህንም የቤተ ክርስቲያን አንድነት የተገለጠና በተግባርም የምንሳተፍበት የጋራ ጸሎትና ሥርዓተ አምልኮ ነው፡፡ ይህም ጸሎተ ቅዳሴው መስተብቁዕ ሊጦኑ ማኅሌቱ ጸሎተ ፍትሐቱና የመሳሰለው ነው፡፡ ጸሎተ ቅዳሴው የሁሉም ርዕሰ ጸሎት ነው፡፡ በጸሎትና በአምልኮውም ቅዱሳን መላእክት የቀደሙት አበው ሊቃውንት ነቢያት ሐዋርያት ጻድቃን ሰማዕታት ሁሉም ይሳተፋሉ የጊዜና የቦታ ልዩነት አጥፍተው በሕብረት ከእኛ ጋር ይሆናሉ፡፡ ጸሎተ ቅዳሴው ጸሎተ ቁርባን የሚባለውም በዚህ ምክንያት ነው ቁርባን አማካኝነት ሁላችን አንድ እንሆናለንና፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም እንዳለው ለእግዚአብሔር ማደርያ ለመሆን በመንፈስ አብራችሁ ትሠራላችሁ ኤፌ 2፥21-22

  1. ከሞቱ በኋላ ይቅር ሊባል የሚችል ኃጢያት ስላለ


ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ ይህን በተመለተ እንዲህ ብሏል ‹‹ማንም ወንድሙን ሞት የማይገባውን ኃጢአት ሲያደርግ ይለምን ሞትም የማይገባው ኃጢአት ላደረጉት ሕይወት ይሰጥለታል፡፡ ሞት የሚገባው ኃጢአት አለ ስለዚያ እንዲጠይቅ አልልም(1ኛ 5፥16) ጌታችንም መንፈስቅዱስን የሚሳደብ ቢኖር ግን በዚህም ዓለም ወይም በሚመጣው ዓለም ቢሆን አይሰረይለትም በማለት በሚመጣው ዓለም ሊሰረይ የሚችል ኃጢያት ስለመኖሩ አስቀምጦልናል

ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ከሞቱ በኃላ ንስሐ መግባት ወይመ ለሰሩት መጸጸት ይቻላል ወይም እንደ ካቶሊካዊያኑ መካነ ንስሐ መቆያ አለ ብላ ባታምንም ግን የእግዚአብሔርን ቸርነት በሚገባ ታስተምራለች በቸርነቱ በዚህም በሚመጣወም ዓለም ኃጢያታችን እንደሚሰረይ ከመጽሐፍትም ከጌታም ትምህርት አንጻር በሚገባ የተቀመጠ ስለሆነ ይህን ታስተምራለች፡፡

  1. ከዕረፍታቸው በኋላ ሕያዋንና አዋቂዎች ስለ ሆኑ


ሞት ማለት ሕይወት(ሕያውነት) የሚጠፋበት ሳይሆን ከዚህ ቁሳዊ ሥጋዊ ዓለም አኗኗር ወደ መንፈሳዊ አኗኗር መሻገር ነው፡፡ ስለዚህም በአካለ ነፍስ ያሉ በዚህ ዓለም ስለሚደረገው ያውቃሉ፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹አባታችሁ አብርሃም ቀኔን ያይ ዘንድ ተመኘ አየም ደስም አለው›› በማለት ተናግሯል፡፡ ዮሐ 8፥56 አየም ደስም አለው የሚለው ሐረግ አብርሃም ምንም እንኳ በሥጋ ቢለይ በዚህ ዓለም የተፈጸመውን ያውቃል የጌታ ወደ ምድር መምጣት ያወቀው አብርሃም በተስፋ ሲጠብቀው የነበረው ነገር ስለተፈጸመለት ደስ አለው ይህም ምንም እንኳ በዚህ ባይኖር የጌታችንን ማዳን እንዳየ ያመለክተናል፡፡

  1. አስተምህሯቸውና እምነታችን ተስፋችንን የሚገልጥ ስለሆነ


ድስት ቤተ ክርስቲየን ያረፉ ሰዎች በሕይወት ይኖሩ ዘንድ በምታደርገው ጸሎት በእምነትና በተስፋ ሁሌም ማራቸው ይቅር በላቸው ብላ ትጸልያለች፡፡ ክርስትና ተስፋ የምናደርገውና በእምነት የምንኖረው መሆኑን እናስተውል ስለዚህም ማራቸው ስንል ክርስትናን በሚገባ እያስታማርና እየሰበክን ነው፡፡[1]
                                                                                                                           ይቆየን





[1] መድሎተ ጽድቅ ዲያቆን ያረጋል አበጋዝ መጽሐፍ የተወሰደ(ገጽ 454-462)

1 comment: