Saturday, 25 February 2017

የተራራው ስብከት



 
ማቴ 5÷6 ‹‹የሚምሩ ብፁዓን ናቸው፣ ይማራሉና››
ምሕረት ሦስት ዓይነት ነው፡፡ ምሕረት ሥጋዊ፣ ምሕረት መንፈሳዊና ምሕረት ነፍሳዊ፡፡
ምሕረት ሥጋዊ፡- ቀዶ ማልበስ ቆርሶ ማጉረስ፣ ቢበድሉ ማሩኝ፣ ቢበደሉ ይቅርታ ማድረግ ነው፡፡
ምሕረት መንፈሳዊ -ክፉውን ሃይማኖት ክፉውን ምግባር በጎ ሃይማኖት በጎ ምግባር መስሎ ይዞት ሲኖር መክሮ አስተምሮ ክፉውን ሃይማኖት አስትቶ በጎውን ማስያዝ ክፉውን ምግባር አስትቶ በጎውን ማሠራት ማለት ነው፡፡
ምሕረት ነፍሳዊ፡- መጥዎተ ርእሰ /ራስን መስጠት/ ነው፡፡ /ዮሐ 1513/
ይማራሉና ማለቱም፤- ለእርሱም ሥላሴ ያዝኑላቸዋል ይራሩላቸዋል ማለቱ ነው፡፡
ማቴ 5÷8 ‹‹ልበ ንጹሖች ብፁዓን ናቸው እግዚአብሔርን ያዩታልና››
ልባቸው የነጻ አግዚአብሔርን ያዩታል ማለት፡- እግዚአብሔር በዓይነ ሥጋ ይታያል ማለት አይደለም፡፡ በዓይነ ልብ ግን ይታያል፣ ያውም በጣም ንጹሕ የሆነ እንደሆነ፡፡ የልብ ንጽሕና ማለት ከልብ የሚመነጩ መጥፎ ሐሳቦችን መተው ማለት ነው፡፡
በሥጋዊ አስያየታችን በሥጋዊ ዓይናችን ዛሬ እግዚአብሔርን ልናየው ከቶ አንችልም፡፡ ግን ነፍሳችን ጠርታ፣ ሥጋ ነፍስን መስሎ ወደ እግዚአብሔር በቀረብን ጊዜ ፊት ለፊት እግዚአብሔርን እናየዋለን /1 ቆሮ 13÷12/ እነዚህን ልቦናቸው የነጻ ወገኖች ግን አሁንም ለነጽሮተ ሥሉስ ቅዱስ የደረሱ ስለሆነ እንደ ጌታ ቃል እግዚአብሔርን ያዩታል፡፡
ማቴ 5÷9 ‹‹የሚያስታርቁ ብፁዓን ናቸው የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉና››
በመጀመሪያ ሥጋና ነፍሳቸውን ካስማሙ በኋላ ሌሎችን በመምከርና በማስተማር ሰውን ከእግዚአብሔር ጋር የሚያስታርቁ ብፁዓን ናቸው፡፡ እውነተኛ አስታራቂ ክርስቶስ ነው /ኤፌ 2÷14/፡፡ ሐዋርያት አስታራቂዎች ናቸው /2 ቆሮ 5÷17-30/፡፡ ዛሬም ካህናትና ሽማግሌዎች ሁሉ የማስታረቅ መብት አላቸው 1 ቆሮ 6÷5


ሰላምና እርቅን የሚመሠርቱ የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉ፡፡ /ዮሐ 1÷12/ በእግዚአብሔር መንፈስ የሚያምኑ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው /ሮሜ 8÷14/፡፡ እነዚህ ሁሉ ሰላማውያን ናቸው ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር የሰላም አምላክ ስለሆነ ልጆቹ ሰላማውያን ይሆናሉ፡፡ /1 ቆሮ 14÷33/
ማቴ 5÷10 ‹‹ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ ብፁዓን ናቸው፡፡ መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና››
ስለ ጽድቅ ማለት /ስለ እውነት/ የሚሰደዱ ብፁዓን ናቸው፡፡ እውነት መራራ ናትና እውነትን ተናግሮ በእውነትም ሰርቶ የሚያስቀምጠው የለም፡፡ ነብያት ስለ ጽድቅ ተሰደው ነበር፡፡ ክርስቶስም መሰደድ ብቻ ሳይሆን የተሰቀለውም ስለ ጽድቅ ነው፡፡ እነርሱም ለደቀ መዛሙርቱ እውነትን ስለምትናገሩ፣ እውነትን ስለምትሠሩ ሐሰተኞች ያሳድዷችኋል ብሎ አስቀድሞ ተናግሯል፡፡ /ዮሐ 15÷18-19/

ኃጢአተኛው ዓለም በጨለማ ውስጥ ስለሆነ ተስፋ ቆርጦ ይኖራል፡- ስለዚህ መንፈሳዊ ነገር እውነትም የሆነ ነገር ሁሉ አያስደስተውም፡፡ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ሊሰማ ፈጽሞ አይወድም፡፡ እንደዚህ ያለ ነገር የሚናገረውንና የሚሠራውንም ሁሉ ያሳድደዋል፡፡
እውነተኛ ክርስቲያን እውነት ከመመስከር ወደ ኋላ አይመለስምና መከራና ስደት ይደርሱበታል፡፡ /የሐዋ 4÷18-19/ በግፍ የሚሰደዱ ታላቅ ክብር አላቸው ሲል ነው፡፡/ሮሜ 8÷18 2ቆሮ 4÷17/
ማቴ 5÷11-12 ‹‹ሲነቅፏችሁና ሲያሳድዷችሁ ምክንያት ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲናገሩባችሁ ብፁዓን ናችሁ ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና ደስ ይበላችሁ፣ ሀሴትም አድርጉ፡፡ ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያትን እንዲሁ አሳደዋቸዋልና፡፡››
ስለ ክርስቶስ ስም የተረገሙ የተወቀሱና የተከሰሱ፣ ከሀገርም እንዲወጡና እንዲሰደዱ የተፈረደባው፣ በበለጠም የመኖር ዕድል ተነፍጓቸው የተገደሉ ብዙ ናቸው፡፡ እዚህ ሰዎች ወንጀል አልሠሩም፣ ክፉ ነገር አልተናገሩም፣ በክርስቶስ በማመናቸው ወንጌልንም በማስተማራቸው ብቻ ይህ ሁሉ መከራ የደረሰባቸው ናቸው፡፡
አስቀድሞ ነቢያት በእግዚአብሔር አምልኮ ከዚያም የመሲሕን መምጣት ተስፋ ያደርጉና ይጠባበቁ ስለነበሩ፣ ስለዚህ ሁሉ ገልጠው ትንቢት ስለተናገሩ እየተንገላቱ እየተሰደዱ የሞቱ ብዙዎች ናቸው፡፡ የኤልያስን፣ የኢሳያስን፣ የኤርሚያስንና የሌሎች ሰማዕታትን ታሪኮች ለአብነት ያህል መመልከቱ ይጠቅማል፡፡ /1 ነገ. 18 ዕብ 11÷32-40/
ሥጋን እንጂ ነፍስን ለመግደል የሚችል የለምና /ማቴ 10÷25-28/ ክርስቲያን ሁሉ ስለ እውነት /ጽድቅ/ የመጣው ቢመጣ መፍራት ማፈር የለበትም፡፡ ቢሰደድም ክብሩ ነው፣ ቢሞትም ዕረፍቱ ነው፣ ተቀባዩ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ነውና፡፡ ስለዚህም ሐዋርያው ጴጥሮስ እንዲህ ይላል ‹‹ነገር ግን ክብሩ ሲገለጥ ደግሞ ሐሴት አደረጋችሁ ደስ እንዲላችሁ በክርስቶስ መከራ በምትካፈሉበት ልክ ደስ ይበላችሁ፡፡ ስለ ክርስቶስም ስም ብትነቀፉ የክብር መንፈስ የእግዚአብሔርም መንፈስ በእናንተ ላይ ያርፋልና ብፁዓን ናችሁ፡፡›› /1ጴጥ 4÷13-14)

No comments:

Post a Comment