ልዩን ዐሥረኛ(1513-1521) የተባለው ፖፕ በሮም ከተማ ለሚገኘው
ለታልቁ የቅዱስ ጴጥሮስ ቤተ ክርስቲያን የእድሳት ሥራ ማስፈጸምያ የሚሆን ገንዘብ ስለፈለገ በጀርመን የመንዝ ሊቀ ጳጳስ አልበርት
ቀደም ሲል ሦስት ሀገረ ስብከቶች ላይ ሲሾም ሹመቱን ላሰጠው ለሮም ፖፕ በግብርና በገጸ በረከት መልክ አውግስበርግ ከነበረው ፉገር
ከተባለው ድርጅት ገንዘብ በአራጣ ተበድሮ ነበር፡፡ ስለዚህም ለእዳው የሚከፍለው ገንዘብ ስላስፈለጋው ዮሐንስ ቴትዝል የዶሚኒካም
መነኩሴ ‹‹ኢንደልጀንስ›› የተባለውን የኃጢያት ማስተሰርያ ጽሑፍ በመሸጥ ለእዳው ክፍያ ከምእመናን እንዲከፈል
አዘዘ፡፡
ኢንድጅንስ ምንድር ነው?
ኢንድጅንስ ከፖፑ የተላከ ኃጢያት ማስተሰርያ ጽሑፍ በመግዛት ዋጋውን በሙዳይ ምጽዋት
ውስጥ ስትጥሉ የሞተ(የሞተች) ዘመዳችሁ የተኮነነች ነፍስ በቅስበት ከፐርጋቶሪ(ከመካነ ንስሐ) ነጻ ሆና ወደ መንግስተ ሰማያት ትገባለች፡፡
የራሳቸሁም ነፍስ ትማራለች ብሎ በመስበክ የዋሐን ክርስቲያኖችን ያታልል ነበር፡፡
ፐርጋቶሪ[1](መካነ ንስሐ) ምንድር ነው?
ይህ መካነ ንስሐ የሙታን መቆያ ሲሆን እንደካቶሊክ ትምህርት ይህ ቦታ
መቆያ ሆኖ የሙታኑ ዘመዶች ወዳጆች በሚገዙት የኃጢያት ማስተስርያ ሰርተፍኬት ከነበሩበት መቆያ ወደ መንግስተ ሰማያት ይገባሉ የሚል
ትምህርት ነው፡፡
ይህ የካቶሊካዊያን ትምህርት በኃላ ለተነሱ የፕሮቴስታንት ተሐድሶያዊያን
መነሻና የምዕራብ ቤተ ክርስቲያን ለሁለት መከፈል ምክንያትና ምንጭ ሆኖል፡፡ የተሐድሶያዊየኑ መሠረት ይህ ይሁን እንጂ ይህን ትምህርት
በመጥላትና በመጸየፍ ምክንያት ሌሎች ተጨማሪ የማይገቡ ትምህርቶችን በማምጣት ብዙዎችን አስቷል፡፡
ፐሪጋቶሪ (purgatory) የሚለው ቃል <> ከሚለው የላቲን ቃል የመጣ ሲሆን
ትርጉሙም ማጽዳት(ማንጻት) ማለት ነው፡፡ ይህ እንደሮም ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ጊዜያዊ ቅጣት መቀበያ ቦታ ነው፡፡ የመካነ
ደይን ጽንሰ ሐሳብ የተጀመረው እ.ኤ.አ. በ1215 በላተርን በ1274 በሊዮን 1431 በፍሎሬንስ በ1554-1563 ደግሞ
በትሬንት በተደረጉ የካቶሊክ ጉባኤያት ነው፡፡ በአጠቃላይ ከ13 መቶክፍለ ዘመን እስከ 15 መቶ ክፍለ ዘመን ድረስ ተፈጻሚ
የሆነ አስተምህሮ ነው፡፡
- የቅዱሳን ሥፍራ ይህ ቦታ በምድር ላይ በቅድስና ለሚኖሩ ሰዎች የተሰናዳ ነው ስለዚህም በቀጥታ እነዚህ ነፍሳት ወደ ብሔረ ብፁአን ይገባሉ
- በሞት ኃጢአት(moral sin) ወይም በጥንተ አብሶ ኃጢአት እንደተያዙ የሞቱ ነፍሳት ወደ ዘለዓለማዊ ቅጣት ይገባሉ
- ከተጠመቁ በኋላ የበደሉ በእውነት ንስሐ የገቡ ኃጢአታቸውን የተናዘዙ ነገር ግን ይቅርታን የሚያስገኝ የንስሐ ፍሬ ያላፈሩ ነፍሳት ወደ በመካነ ደይን ቆይተው እንደኃጢአታቸው ደረጃ በፍጥነት ወይም ዘግይተው በመንጽሔ እሳት (purgatorial fire) ይነጻሉ፡፡ ከዚያም ወደ ብፁአን ዓለም ይገባሉ፡፡ይህም የሚሆነው በምጽአት በጸሎተ ፍትሐት በስሙ በሚፈጸም መላካም ሥራ መሆኑን ያስተምራሉ
በመንጽሔ እሳት (purgatorial fire) ምንድን ነው?
እውነተኛ የፍርድ እሳት እንዳለ በሁሉም ክርስቲያኖች
ዘንድ የሚታመን ነው፡፡ ነፍስ ከእግዚአብሔር ከመለየቷ በተጨማሪ ያጠፍች ነፍስ በዘለዓለም እሳት ትቀጣለች፡፡ ከዚህ
ዓለም በኋላ ጉድለታቸው በመንጽሔ እሳት የሚያካከክሱ ነፍሳት
ስቃይ ከዚህ ይልቅ የበለጠ የማይታገሱት(የማይቻል) ነው፡፡ የመንጽሔ እሳት ቅጣት ጊዜያዊና የሚያበቃ ነው፡፡ ሁሉም ግን
ከመጨረሻው ፍርድ ቀን በፊት የሚሆኑ ናቸው፡፡
በዚህ ዓለም ያሉ አማኞች በመካነ ደይን ላሉ ነፍሳት
ስለ እነርሱ መሥዋዕትና ጸሎት ያቀርቡላቸዋል፡፡ እግዚአብሔር በደላቸውን ሁሉ ይቀር ያላቸዋል በአብርሃም እቅፍ ይቀበላቸው ዘንድ
ለዘለዓለማዊ ደስታ ያልበቁ ነገር ግን ጸሎትና ቁርባን የቀረበላቸው እነዚህ ነፍሳት ግን ወደ መካነ ደይን ገብተው ለአጭር ጊዜ
ብቻ ከእግዚአብሔር እይታ ይሰወራሉ፡፡
ካቶሊኮች ለዚህ ትምህርት የሚያቀርቡት የመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃ
‹‹ማንም
ሥራ የተቃጠለበት ቢሆን ይጎዳባታል እርሱ ራሱ ግን ይድናል ነገር ግን በእሳት እንደሚድን ይሆናል፡፡››
(አንደኛ
ቆሮ 3፥15)
በእርግጥ ቅዱስ
ጳውሎስ ይህንን ቃል የተናገረው ስለቅጣትና ስለፍርድ ሳይሆን ስለአገልግሎትና አገልጋዮች ባስተማረ(በተናገረ) ጊዜ ነው፡፡
የእርሱንና አጵሎስን አገልግሎት ከእርሻና ከግንበኛነት ጋር እያስተያየ ይናገር ነበርና፡፡ (1ኛ ቆሮ 3፥12-15) እሳቱም
ለሥራው እንጂ ለሠራተኛው አይደለም፡፡ በዚህ ክፍለ ንባብ የተገለጸው ቅጣት ለእያንዳንዱ ሰው መሆኑን አስተውል፡፡መካነ ደይን
ግን ለተወሰኑ ሰዎች ነው፡፡
እሳቱ ለመፈተኛ
እንጂ እንደመካነ ደይን ለቅጣትና ለመከራ እንደሆነ አስተውል፡፡ እሳቱ በገለባ በእንጨት ወይም በሣር የተሠራውን ያቃጥላል፡፡
በመካነ ደይን አለ የሚባለው መንጽሔ እሳት ግን አንድን ሰው ንጹሕ የሚያደርገው እና ወደ ተሻለ ቦታ የሚገባበት ነው ይባለል፡፡
ስለዚህ አብሮ ሊሔድ አይችልም፡፡
‹‹እግዚአብሔርም
ሰይጣንን ሰይጣን ሆይ እግዚአብሔር ይገሥጽህ ኢየሩሳሌምን የመረጠ እግዚአብሔር ይገሥጽህ በውኑ ይህ በእሳት የተጠበቀ ትንታግ
አይደለምን? አይደለምን›› (ትን. ዘካ. 3፥2)
በዚህ የመጽሐፍ ክፍል የተጠቀሰው ቃል ከመንጽሔ እሳት
አስተምህሮ ጋር የተገናኘ አይደለም፡፡ ኢያሱ በምድር ላይ በሕይወት ሳለ ከሕዝቡ ሁሉ ጋር ሆኖ የሠራውን ኃጢአት የሚመለከት
ነው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹ጻድቅም በጭንቅ የሚድን ከሆነ ዓመፀኛውና ኃጢአተኛው ወዴት ይታይ ዘንድ አለው? ይላል፡፡(1ኛ ጴጥሮስ
4፥18) ‹‹ዳነ›› የሚለው ቃል ባግባቡ ባለማገልገሉ የሚጸጸትና ንስሐ የሚገባ ከሆነ የሚያገኘውን እድል የሚያመለክት ነው፡፡
‹‹በሰው
ልጅ ላይ ቃል የሚናገር ሁሉ ይሠረይለታል በመንፈስ ቅዱስ ላይ ግን የሚናገር ሁሉ በዚህ ዓለም ቢሆን ወይም በሚመጣው አይሠረይለትም››(ማቴ 12፥32)
የካቶሊክ ሊቃውንት ‹‹በሚመጣው›› የሚለውን ቃል መካነ
ደይን ስለሚፈጻመው ይቅርታ እንደሆነ ያስተምራሉ፡፡ ነገር ግን ጌታችን በሚመጣውም ብሎ የገለጠው ጊዜን ሳይሆን ቦታን የሚገልጽ
ነው፡፡ ይኸውም በሚመጣው ዓለም በሚለው ይታወቃል፡፡ ጌታችን በዚህ ዘመን ስለሚፈጸመው ይቅርታ ሲናገር‹‹እውነት እላችኋለሁ
በምድር የምታስሩት ሁሉ በሰማይ የታሰረ ይሁን በምድር የምትፈቱት በሰማይ የተፈጠ ይሆናል፡፡›› (ማቴ 18፥18) ስለዚህ
በሚመጣው ዘመን የሚሆነው ይቅርታ ማለት ንስሐ ሊገባ ነገር ግን ከንስሐ አባቱ በርቀት ተለይቶ ሳለ ወይም በድንገት ከዚህ ዓለም
በ፣ሞት በመለየቱ ምክንያት ኃጢአቱን ለመናዘዝ ከምድርም ላይ በሕይወት ሳለ ፍትሐትን ለመቀበል ላልቻለ የእርሱ ትልቅ
ምሕረት(ርኅራኄ) የአንድን ሰው ንስሐ(ጸጸት) ወደ ቅጣት(መካነ ደይን) ሳይገባ ወይም መካን ሳያደርስበት እንዲቀበለው ያደርጋል
ይቅርታና መከራ አብረው አይሄዱምና፡፡
የፐሪጋቶሪ መኖር ትምህርት ስሕተት የሆነበት ምክንያት
- ከነገረ ድኅነት ትምህርት ጋር ይቃረናል
ቤዛነት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሆኖ ሳለ የካቶሊክ
ቤተ ክርስቲያን ቤዛነት የሚገኘው በመካነ ደይን ቦታ መሆኑ ከቤዛነትና ከሣ ትምህርት ጋር ይቃረናል(ሮሜ. 3፥24 1ኛ ዮሐ
2፥1 1ኛ ዮሐ 4፥10)
- ከሥርየተ ኃጢአት ትምህርት ጋር ይቃረናል
ሥርየተ ኃጢአት የሚገኘው
በእግዚአብሔር ፀጋ ሰው ንስሐ ገብቶና ተጸጽቶ ሲገኝ ነው፡፡ በትምህርተ ፐሪጋቶሪ ግን ኃጢአትን በመክፈል የሞት ኃጢአት
ይቅርታን ሊያስገኝ የሚችል በማለት ንስሐ ሳይገቡ ይጸድቃሉ ማለት ከመሠረታዊው የአባቶች ትምህርት ለመዳን ኃጢአትን መናዘዝ ጌታ
እንዳለው በብርሃን መመላለስ እንደሚገባ አለማስተዋል ነው፡፡(1ኛ ዮሐ 1፥7) ይህም ከሥርየተ ኃጢያት ትምህርት ጋር
ይቃረናል፡፡
- ከምሥጢረ ንስሐ ጋር ይቃረናል
ንስሐ ኃጢያትን ያስተሰርያል ዳግመኛም ንስሐ በገባንበት
ኃጢአት አያስጠይቅም፡፡ ይህ መሠረታዊ የምሥጢረ ንስሐ ትምህርት ነው የመጽሐፍ ቅዱስም ሐሳብ ነው፡፡(ቆላ.2፥13 ኢሳ
43፥25)
ይህ ትምህርት ምንም እንኳን መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ባይኖረውም ይህንን
በሚመለከት የካቶሊክ የነገረ መለኮት ሊቃውንቱ ጥቅስ አላጡም ፡፡ በአንደኛ ቆሮንቶስ 3፡10-15 በእሳት ስለሚገለጥ ያ ቀን ይፈርዳልና
የሚለውን በመጥቀስ ቀጥታ ባይገናኝም ስለ መካነ ንስሐ ይሰብካሉ፡፡
የኦርቶዶክሳዊያኑ ፍትሐት ተስካር ዝክር?
ጸሎተ ፍትሐት የሚደረግባቸው
ምክንያቶች
- እግዚአብሔር ቸርና መሐሪ ስለሆነ
ከዚህ ዓለም በሞት ለተለዩ(ላረፉ) ወገኖቻችን ጸሎት የሚደረግበት አንዱ
ምክንያት እግዚአብሔር በምሕረቱ እንዲጎበኛቸው ከሰው ስህተት አይጠፋምና በደላቸውን ይቅር ብሎ በብሩህ ገጽ እንዲቀበላቸው የእርሱ ምሕረት ደጅ ለመጽናት ነው፡፡ በመጀመርያ እነዚህ
ያረፉ ወገኖቻችን የቤተ ክርስቲያን ሕያዋን አካላት እንደመሆናቸው ለእነዚህ በአንድ መንፈስ አንድ አካላት ለሆንን ወገኖቻችን መጸለይና
ምሕረት መለመን የሚገባ እንጂ የማይገባ አይደለም፡፡ የማይገባ የሚሆነው ይህን መቃወም ነው፡፡
በመጽሐፍ ቅዱስ ለራሳቸው መልካም ነገርን ከለመኑ ሰዎች በበለጠ የተመሰገኑት
ስለሌላው ሰው ስለወገናቸው ሲሉ እግዚአብሔርን የለመኑት ናቸው፡፡ ሙሴን በእጅጉ ያስመሰገነው እግዚአብሔር ‹‹አሁንም ቁጣዬ እንዲቃጠልባቸው
እንዳጠፋቸውም ተወኝ አንተንም ለታላቅ ሕዝብ አደርግሃለሁ›› ባለው ጊዜ ‹‹ አሁን ይህን ኃጢያት ይቅር በላቸው ያለበዚያ ግን ከጸፍከው
መጻሕፍህ እባክህ ደምስሰኝ›› በማለት ከራሱ ክብርና ደኅንነት ይልቅ የሕዝብ ደኅንነትና ምሕረት በማስበለጡና በማስቀደሙ ነበር፡፡
ዘጸ 32፥10-32 ታዲያ እንዲህ ‹‹ሕዝቡ ይቅር በላቸው አለዚያ ግን ከሕይወት መጽሐፍ ደምስሰኝ›› እስኪል ደርሶ ለሌሎች ምሕረትን
ከለመነ እንደ እርሱ ባናደርግ እንኳ በዓቅማችን ማራቸው ብሎ መጸለይ ኃጢአትነቱንና ጥፋተኝነቱ ምኑ ላይ ነው?
ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ወገኖቹ ስለእስራኤላዊያን በክርስቶስ አለማመንና
ከድኅነት ውጭ ስለመሆናቸው ያዝንና ይጨነቅ ነበር፡፡ ‹‹ብዙ ኀዘን የማያቋርጥም ጭንቀት በውስጤ አለብኝ ስል በክርስቶስ ሆኜ እውነት
እናገራለሁ አልዋሽምም ሕሊናዬም በመንፈስ ቅዱስ ይመሰክርልኛል፡፡ በሥጋ ዘመዶቼ ስለሆኑ ስለ ወንድሞ ከክርስቶስ ተለይቼ እኔ ራሴ
የተረገምኩ እንድሆን እጸልይ ነበርና›› ብሉ ሐዋርያው እንደገለጸው፡፡(ሮሜ. 9፥1-3) ይህን ያህል ስለሌሎች መዳን ‹‹እኔ የተረገምኩ
ልሁን›› እስከማለት ደርሰው ከጸለዩና ከተጨነቁ እኛ ስለሌሎች መዳን ማሰብና መጸለይ የለብንምን?
እነዚህ ከላይ በምሳሌነት ያነሳናቸው ቅዱሳን በሕይወት ስላሉ ሰዎች
መጸለያቸውን ነው፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ምንም እንኳን ሙታን በሥጋ ቢለዩንም ሁሌም ቢሆን የቤተ ክርስቲያንን ሕብረት ውስጥ
ያሉና የሚኖሩ መሆናቸውን ታስተምራለች፡፡ እግዚአብሔር በዚህ ዓለም በሕይወት ከሚኖሩና ከማይኖሩ ሰዎች ጋር ግንኙነት አለው እንጂ
በምድር ከዚህ በመለየታቸው ምክንያት ከቤተ ክርስቲያን ሕብረት ተለይተዋል ማለት አይደለም፡፡ የእግዚአብሔርም ቸርነት በሙታንም በሕያዋንም
ላይ እንደሆነ መጽሐፍ ሲመሰክር ‹‹ቸርነትህ በሕያዋንና በሙታን ላይ አልተወምና›› ይላል(ሩት 2፥20)
የያዕቆብ የበኩር ልጅ የነበረው ሮቤል ወደ አባቱ አልጋ ወጥቶ እንደነበር
መጽሐፍቅዱስ ይናገራል፡፡ እንዲህ ብሎ‹‹እስራኤል በዚህም አገር በተቀመጠ ጊዜ ሮቤል ሄደ የአባቱንም ቁባት ባላን ተገናኛት እስራኤልም
ሰማ›› ዘፍ 35፥22 በሕይወቱ መጨረሻ ላይ አባቱ ያዕቆብ ልጆቹን በተመለከተ እያንዳንደቸውን ግብራቸውንና ወደፊት የሚያገኛቸውን
ሲናገር ‹‹…..እንደውሃ የምትዋልል ነህ አለቅነት ለአንተ አይሁን ወደ አባትህ መኝታ ወጥተሃልና አረከስኸውም ወደ አልጋዬ ወጣህ››
ዘፍ 49፥3-4
ከዚህም የተነሳ ሮቤል ከሞተ ቢያንስ ከመቶ ዓመት በላይ ከሆነው በኋላ
እስራኤልያዊያን ከግብጽ ሲወጡ የአበውን ዓጽምም አብረው ይዘው ስለነበር በኃጢያቱ ምክንያት ከሌሌ,ሎቹ አበው ተለይቶ የሮቤል አጽም
ጠቁሮ ነበር፡፡ለዚህም ነው ሙሴ ከሞተ ብዙ ጊዜ ብሆነውም እንዲህ ብሎ ጸለየለት ‹‹ወዳጄ ሮቤል በሕይወት ይኑርልኝ አይሙትብኝ..(ዘዳ. 33፥6)
- የቤተ ክርስቲያን ባሕርይዋንና ማንነቷን የሚገልጥ ስለሆነ
ቤተ ክርስቲያን ቀደም ሲልም እንደገለጽነው በአካለ ሥጋ ያሉ በአካለ
ሥጋ የሌሉ ሰዎች መላእክት ቅዱሳን ሁሉም በሕብረትና በአንድነት እግዚአብሔርን የምናከብርባትና የምናመሰግንባት የምስጋና ግምጃ ቤት
ናት፡፡ ይህንም የቤተ ክርስቲያን አንድነት የተገለጠና በተግባርም የምንሳተፍበት የጋራ ጸሎትና ሥርዓተ አምልኮ ነው፡፡ ይህም ጸሎተ
ቅዳሴው መስተብቁዕ ሊጦኑ ማኅሌቱ ጸሎተ ፍትሐቱና የመሳሰለው ነው፡፡ ጸሎተ ቅዳሴው የሁሉም ርዕሰ ጸሎት ነው፡፡ በጸሎትና በአምልኮውም
ቅዱሳን መላእክት የቀደሙት አበው ሊቃውንት ነቢያት ሐዋርያት ጻድቃን ሰማዕታት ሁሉም ይሳተፋሉ የጊዜና የቦታ ልዩነት አጥፍተው በሕብረት
ከእኛ ጋር ይሆናሉ፡፡ ጸሎተ ቅዳሴው ጸሎተ ቁርባን የሚባለውም በዚህ ምክንያት ነው ቁርባን አማካኝነት ሁላችን አንድ እንሆናለንና፡፡
ቅዱስ ጳውሎስም እንዳለው ለእግዚአብሔር ማደርያ ለመሆን በመንፈስ አብራችሁ ትሠራላችሁ ኤፌ 2፥21-22
- ከሞቱ በኋላ ይቅር ሊባል የሚችል ኃጢያት ስላለ
ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ ይህን በተመለተ እንዲህ ብሏል ‹‹ማንም ወንድሙን
ሞት የማይገባውን ኃጢአት ሲያደርግ ይለምን ሞትም የማይገባው ኃጢአት ላደረጉት ሕይወት ይሰጥለታል፡፡ ሞት የሚገባው ኃጢአት አለ
ስለዚያ እንዲጠይቅ አልልም(1ኛ 5፥16) ጌታችንም መንፈስቅዱስን የሚሳደብ ቢኖር ግን በዚህም ዓለም ወይም በሚመጣው ዓለም ቢሆን
አይሰረይለትም በማለት በሚመጣው ዓለም ሊሰረይ የሚችል ኃጢያት ስለመኖሩ አስቀምጦልናል
ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ከሞቱ በኃላ ንስሐ መግባት ወይመ ለሰሩት
መጸጸት ይቻላል ወይም እንደ ካቶሊካዊያኑ መካነ ንስሐ መቆያ አለ ብላ ባታምንም ግን የእግዚአብሔርን ቸርነት በሚገባ ታስተምራለች
በቸርነቱ በዚህም በሚመጣወም ዓለም ኃጢያታችን እንደሚሰረይ ከመጽሐፍትም ከጌታም ትምህርት አንጻር በሚገባ የተቀመጠ ስለሆነ ይህን
ታስተምራለች፡፡
- ከዕረፍታቸው በኋላ ሕያዋንና አዋቂዎች ስለ ሆኑ
ሞት ማለት ሕይወት(ሕያውነት) የሚጠፋበት ሳይሆን ከዚህ ቁሳዊ ሥጋዊ
ዓለም አኗኗር ወደ መንፈሳዊ አኗኗር መሻገር ነው፡፡ ስለዚህም በአካለ ነፍስ ያሉ በዚህ ዓለም ስለሚደረገው ያውቃሉ፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን
ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹አባታችሁ አብርሃም ቀኔን ያይ ዘንድ ተመኘ አየም ደስም አለው›› በማለት ተናግሯል፡፡ ዮሐ 8፥56 አየም ደስም
አለው የሚለው ሐረግ አብርሃም ምንም እንኳ በሥጋ ቢለይ በዚህ ዓለም የተፈጸመውን ያውቃል የጌታ ወደ ምድር መምጣት ያወቀው አብርሃም
በተስፋ ሲጠብቀው የነበረው ነገር ስለተፈጸመለት ደስ አለው ይህም ምንም እንኳ በዚህ ባይኖር የጌታችንን ማዳን እንዳየ ያመለክተናል፡፡
- አስተምህሯቸውና እምነታችን ተስፋችንን የሚገልጥ ስለሆነ
ቅድስት ቤተ ክርስቲየን ያረፉ ሰዎች በሕይወት ይኖሩ ዘንድ በምታደርገው ጸሎት በእምነትና
በተስፋ ሁሌም ማራቸው ይቅር በላቸው ብላ ትጸልያለች፡፡ ክርስትና ተስፋ የምናደርገውና በእምነት የምንኖረው መሆኑን እናስተውል ስለዚህም
ማራቸው ስንል ክርስትናን በሚገባ እያስታማርና እየሰበክን ነው፡፡[2]
ይቆየን
No comments:
Post a Comment