Saturday, 18 February 2017

‹‹የሚያዝኑ ብፁዓን ናቸው መጽናናትን ያገኛሉና››(ማቴ 5፡4)



ክፍል ሁለት
ዛሬ የሚያዝኑ ብፁዓን ማለት ንዑዳን ክቡራን ናቸው አለ፡፡ ኀዘን /ልቅሶ/ የሚገባና የማይገባ በመባል ለሁለት ይከፈላል፡፡

    የማይገባ ኀዘን፡-

እናት፣ አባት፣ እኅት፣ ወንድም፣ ዘመድ የለኝ፣ ርስት ጉልት ሄደብኝ ብሎ ማዘን የማይገባ ነው፡፡ እንደ አባት እንደ እናት ሥላሴ፣ እንደ ወንድም እንደ እኅት መላእክት አሉና፡፡ እንደ ርስት እንደ ጉልት የማታልፍ መንግሥተ ሰማያት አለችና፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ስለዚህ ሲናገር እንዲህ ይላል ‹‹እንደ እግዚአብሔር ፍቃድ የሆነ ኀዘን ጸጸት የለበትም ወደ መዳን የሚያደርሰውን ንስሐ ያደርጋልና የዓለም ኀዘን ግን ሞትን ያመጣል››(2ቆሮ 7÷10-11)
ሰዎች የሚያዝኑት በምድራዊ ነገር ነው፡፡ እግዚአብሔርንም ለምን በእንዲህ ዓይነት ፈተና መከራ ውስጥ ጣልከኝ ይላሉ ይህ የማይገባ ኀዘን ነው፡፡ ለምን አባት እናቴን እኅት ወንድሜን አጣው ለምን ንብረቴን አጣው ብለው ራሳቸውን በማይረባ ነገር ያስጨንቃሉ ይህ የማይገባ ኀዘን ነው ጌታ ለእኛ የሚሆነውንና የሚያስፈልገውን ያደርጋል እንጂ ፍጹም የማንወጣው መከራ ውስጥ አይጥለንም፡፡ ከዚህ በፊት ያለፍንበትን መከራ እስኪ እናስተውለው፡፡ ከስንት ችግር ምንም ሳይኖረን ከውድቀት ያነሳንን ጌታ እንመልከው ከእኛ በታች በብዙ መከራ ያለፉትን እንመልከታቸው ባጣነው ነገር ሳይሆን ባለን ነገር እናመስግነው፡፡ ጌታን ዘወትር እንድናመሰግነው ብዙ ምክንያቶች አሉን በዚህ ነገር ማዘን መተከዝ እንደማይገባ ጌታችን በዚህ የወንጌል ክፍለ ትምህርት ይነግረናል፡፡

     የሚገባ ኀዘን

የራስን ኃጢአት አስቦ ማልቀስ /እንደ አዳም፣ እንደ ዳዊት(2 ሳሙ 11÷12) እንደ ቅዱስ ጴጥሮስ (ሉቃ 22÷54-62)
የባልንጀራን ኃጢአት አስቦ ማልቀስ እንደ ሳሙኤል 1 ሳሙ 15÷35
ግፍዓ ሰማዕታትን አስቦ ማልቀስ እንደእስጢፋኖስ
ሞተ ወልደ እግዚአብሔርን አስቦ ማዘን  እንደ ዮሐንስ ወንጌላዊ የጌታችንን የዕለተ ዓርብ መከራውን እያሰበ ሰባ ዘመን ቁጹረ ገጽ ሆኖ ኖሯልና፡፡
እንዲህ ያሉ ሰዎች ይጽናናሉ/ ይደሰታሉ/፡፡ ይህም እውነተኛ ደስታ የሚገኘው በመንግሥተ ሰማያት ነውና፡፡ ይጽናናሉ /ይደሰታሉ/ ማለቱ - መንግሥተ ሰማያትን ይወርሳሉ ሲል ነው፡፡
የቅዱሳን ኀዘናቸው ምድራዊ አይደለም፡፡ የእነርሱን ኀዘን ልንጋራ እንደሚገባ አስተማረን፡፡ ስለራስ ኀጢአት ማዘን የሚገባ ነው፡፡ የሚጸጸት ሕሊና ያለው ሰው መንግስቱን ለመውረስ መንገድ የጀመረ ነው፡፡ በጎ ሕሊና በሠራው ክፉ ሥራ የሚጸጸትና ንስሐ የሚገባ ነው፡፡ለዚህም ነው ቅዱስ ጳውሎስ ለመንፈስ ልጁ ለጢሞቲዎስ ሲመክረው እምነትና በጎ ሕሊና ይኑርህ ያለው፡፡
 ስለባልንጀረው የሚያዝንና የሚተክዝ ከዚህ የበለጠ ነው ከራሱ አልፎ ስለሌሎች ማሰብ መቻል ምንኛ ሚደንቅ ነው፡፡ ቅዱሳን ስለሌሎች ያዝናሉ ይተክዛሉ ዮሐንስ ሐጺር የተባለው ቅዱስ አባት አንዲት በቀድሞ ሥራዋ እንግዶችን ስትቀበል የነበረች ክርስቲያን በኃላ ዘማ ሆና የማይገባ ድርጊት ስትፈጽም ከቆየች በኃላ ይህን ክፉ ግብር ከምትፈጽምበት ቦታ ድረስ ሄዶ በሠራችው ሥራ እንድትጸጸት አበቃት በዚህ ብቻ አላበቃም ወደ በዓት ጉዞ ሲጀምሩ በመንገድ ትሞትበታለች ይህም ቅዱስ አባት እንዴት ለንስሐ ሳላበቃት  ትሞታለች ብሎ አምላኩን ጠየቀ አምላክም ጸጸቷን እንደንስሐ መንገዱን እንደቀኖና ቆጠረራት ለመንግስቱም አበቃት፡፡ እነዚህ ቅዱሳን ለሰው ይገዳቸዋል ለእነርሱም ያዝናሉ፡፡ ሊቀ ነቢያት ሙሴን ተመልከቱ እስራኤል ሕዝቤን ከምታጠፋ እኔን ከሕይወት መጽሐፍ ደምስሰኝ ብሎ አምላኩን የጠየቀው ከራሱ በላይ ስለሕዝቡ ስለሚያስብ ነው፡፡ እነ ሳሙኤል ለሳኦል እንዳዘኑት ኀዘን ያለ ኀዘን ማዘን ይገባል ሲል ነው፡፡ ስለሌሎች እናስባለን እናዝናለንን? ከእኛ ጋር ስያገልግሉ የነበሩ ዛሬ በማይገባ ሕይወት ውስጥ ሲመላለሱ ስናይ እናዝናለንን ይህንን ካደረግን የሚገባ ኀዘን ነውና አምላክ በመንግስቱ ብፁዓን ያለናል፡፡
ይቆየን


1 comment: